text
stringlengths 4
267
|
|---|
እሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሄዳችሁ የሰማችሁትንና ያያችሁትን ነገር ለዮሐንስ ንገሩት፦ ዓይነ ስውሮች እያዩ ነው፤ አንካሶች እየተራመዱ ነው፤ የሥጋ ደዌ የያዛቸው እየነጹ ነው፤ መስማት የተሳናቸው እየሰሙ ነው፤ ሙታን እየተነሱ ነው፤ ድሆችም ምሥራቹ እየተነገራቸው ነው።
|
በእኔ ምክንያት የማይሰናከል ደስተኛ ነው።”
|
የዮሐንስ መልእክተኞች ከሄዱ በኋላ ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ይናገር ጀመር፦ “ወደ ምድረ በዳ የሄዳችሁት ምን ለማየት ነበር? ነፋስ የሚያወዛውዘውን ሸምበቆ?
|
ታዲያ ምን ለማየት ነበር የሄዳችሁት? ምርጥ ልብስ የለበሰ ሰው ለማየት? የተንቆጠቆጠ ልብስ የሚለብሱና በቅንጦት የሚኖሩማ የሚገኙት በቤተ መንግሥት ነው።
|
ታዲያ ምን ለማየት ሄዳችሁ? ነቢይ? አዎ፣ እላችኋለሁ፣ ከነቢይም የሚበልጥ ነው።
|
‘እነሆ፣ ከፊትህ እየሄደ መንገድህን እንዲያዘጋጅ መልእክተኛዬን ከአንተ አስቀድሜ እልካለሁ’ ተብሎ የተጻፈው ስለ እሱ ነው።
|
እላችኋለሁ፣ ከሴት ከተወለዱት መካከል ከዮሐንስ የሚበልጥ የለም፤ ሆኖም በአምላክ መንግሥት ዝቅተኛ የሆነው እንኳ ይበልጠዋል።”
|
(ሕዝቡ ሁሉ እንዲሁም ቀራጮች ይህን በሰሙ ጊዜ በዮሐንስ ጥምቀት ተጠምቀው ስለነበር አምላክ ጻድቅ መሆኑን አምነው ተቀበሉ።
|
ሆኖም ፈሪሳውያንና የሕጉ አዋቂዎች በዮሐንስ ባለመጠመቃቸው የአምላክን ምክር አቃለሉ።)
|
ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ የዚህን ትውልድ ሰዎች ከማን ጋር ላነጻጽራቸው? ማንንስ ይመስላሉ?
|
በገበያ ስፍራ ተቀምጠው እርስ በርሳቸው እየተጠራሩ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ እናንተ ግን አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ እናንተ ግን አላለቀሳችሁም’ ከሚባባሉ ልጆች ጋር ይመሳሰላሉ።
|
በተመሳሳይም መጥምቁ ዮሐንስ እህል ሳይበላና ወይን ጠጅ ሳይጠጣ መጣ፤ እናንተ ግን ‘ጋኔን አለበት’ አላችሁ።
|
የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤ እናንተ ግን ‘እዩ፣ ይህን ሆዳምና ለወይን ጠጅ ያደረ፣ የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኃጢአተኞች ወዳጅ!’ አላችሁ።
|
የሆነ ሆኖ፣ ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በልጆቿ ሁሉ ተረጋግጧል።”
|
ከዚህ በኋላ ከፈሪሳውያን አንዱ አብሮት እንዲበላ ኢየሱስን ደጋግሞ ለመነው። ስለሆነም ኢየሱስ ወደ ፈሪሳዊው ቤት ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ።
|
እነሆም፣ በከተማው ውስጥ በኃጢአተኝነቷ የምትታወቅ አንዲት ሴት ኢየሱስ በፈሪሳዊው ቤት እየበላ መሆኑን በሰማች ጊዜ ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት የያዘ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ መጣች።
|
እሷም ከበስተ ኋላ እግሩ አጠገብ ሆና እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመር፤ ከዚያም በፀጉሯ አበሰችው። በተጨማሪም እግሩን እየሳመች ዘይቱን ቀባችው።
|
የጋበዘው ፈሪሳዊም ይህን ሲያይ “ይህ ሰው በእርግጥ ነቢይ ቢሆን ኖሮ የምትነካው ማን መሆኗንና ምን ዓይነት ሴት እንደሆነች ይኸውም ኃጢአተኛ መሆኗን ባወቀ ነበር” ብሎ በልቡ አሰበ።
|
ኢየሱስ ግን መልሶ “ስምዖን፣ አንድ የምነግርህ ነገር አለኝ” አለው። እሱም “መምህር፣ እሺ ንገረኝ” አለው።
|
“ከአንድ አበዳሪ ገንዘብ የተበደሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ አንዱ 500 ሌላው ደግሞ 50 ዲናር ተበድረው ነበር።
|
ሁለቱም የተበደሩትን መክፈል ባቃታቸው ጊዜ አበዳሪው ዕዳቸውን ሙሉ በሙሉ ተወላቸው። እንግዲህ ከሁለቱ ሰዎች አበዳሪውን አብልጦ የሚወደው የትኛው ነው?”
|
ስምዖንም መልሶ “ብዙ ዕዳ የተተወለት ይመስለኛል” አለው። እሱም “በትክክል ፈርደሃል” አለው።
|
ከዚያም ወደ ሴቲቱ ዞር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፦ “ይህችን ሴት ታያታለህ? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፤ ይሁንና አንተ ለእግሬ ውኃ አልሰጠኸኝም። ይህች ሴት ግን እግሬን በእንባዋ እያራሰች በፀጉሯ አበሰች።
|
አንተ አልሳምከኝም፤ ይህች ሴት ግን ከገባሁበት ሰዓት አንስቶ እግሬን መሳሟን አላቋረጠችም።
|
አንተ ራሴን ዘይት አልቀባህም፤ ይህች ሴት ግን እግሬን ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ቀባች።
|
ስለዚህ እልሃለሁ፣ ኃጢአቷ ብዙ ቢሆንም ይቅር ተብሎላታል፤ ምክንያቱም ታላቅ ፍቅር አሳይታለች። በትንሹ ይቅር የተባለ ግን የሚያሳየውም ፍቅር አነስተኛ ነው።”
|
ከዚያም ሴትየዋን “ኃጢአትሽ ይቅር ተብሎልሻል” አላት።
|
በማዕድ አብረውት የተቀመጡት በልባቸው “ኃጢአትን እንኳ ይቅር የሚል ይህ ሰው ማን ነው?” ይሉ ጀመር።
|
ኢየሱስ ግን ሴትየዋን “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ” አላት።
|
በወቅቱ፣ በዚያ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስለደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች ለኢየሱስ አወሩለት።
|
እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ስለደረሰባቸው ከሌሎቹ የገሊላ ሰዎች ይበልጥ ኃጢአተኞች እንደሆኑ አድርጋችሁ ታስባላችሁ?
|
በፍጹም፤ ነገር ግን ንስሐ ካልገባችሁ ሁላችሁም እንደ እነሱ ትጠፋላችሁ።
|
ወይም ደግሞ የሰሊሆም ግንብ ተንዶባቸው የሞቱት 18 ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ በደለኞች የነበሩ ይመስላችኋል?
|
በፍጹም፤ ነገር ግን ንስሐ ካልገባችሁ ሁላችሁም ልክ እንደ እነሱ ትጠፋላችሁ።”
|
ከዚያም እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ተናገረ፦ “አንድ ሰው በወይን እርሻው ውስጥ የተተከለች አንዲት የበለስ ዛፍ ነበረችው፤ እሱም ከዛፏ ፍሬ ሊለቅም መጣ፤ ሆኖም ምንም አላገኘባትም።
|
በዚህ ጊዜ የወይን አትክልት ሠራተኛውን ‘ከዚህች የበለስ ዛፍ ፍሬ ለማግኘት ሦስት ዓመት ሙሉ ተመላለስኩ፤ ሆኖም ምንም አላገኘሁባትም። ስለዚህ ቁረጣት! ለምን በከንቱ ቦታ ትይዛለች?’ አለው።
|
እሱም መልሶ እንዲህ አለው፦ ‘ጌታዬ፣ ዙሪያዋን ቆፍሬ ፍግ ላድርግባትና እስቲ ለአንድ ዓመት ደግሞ እንያት።
|
ወደፊት ፍሬ ካፈራች ጥሩ፤ ካልሆነ ግን ትቆርጣታለህ።’”
|
ኢየሱስ በሰንበት ቀን አንድ ምኩራብ ውስጥ እያስተማረ ነበር።
|
በዚያም ባደረባት ክፉ መንፈስ የተነሳ ለ18 ዓመት በበሽታ ስትማቅቅ የኖረች አንዲት ሴት ነበረች፤ በጣም ከመጉበጧም የተነሳ ፈጽሞ ቀና ማለት አትችልም ነበር።
|
ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና “አንቺ ሴት፣ ከበሽታሽ ተገላግለሻል” አላት።
|
እጁንም ጫነባት፤ ወዲያውም ቀጥ አለች፤ አምላክንም ማመስገን ጀመረች።
|
የምኩራቡ አለቃ ግን ኢየሱስ በሰንበት ቀን በመፈወሱ ተቆጥቶ ሕዝቡን “ሥራ የሚሠራባቸው ስድስት ቀኖች አሉ፤ ስለዚህ በእነዚያ ቀኖች እየመጣችሁ ተፈወሱ እንጂ በሰንበት ቀን አይደለም” አላቸው።
|
ይሁን እንጂ ጌታ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እናንተ ግብዞች፣ እያንዳንዳችሁ በሰንበት ቀን በሬያችሁን ወይም አህያችሁን ከጋጣው ፈታችሁ ውኃ ለማጠጣት ትወስዱ የለም?
|
ታዲያ የአብርሃም ልጅ የሆነችውና 18 ዓመት ሙሉ በሰይጣን ታስራ የኖረችው ይህች ሴት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራቷ መፈታት አይገባትም?”
|
ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ ተቃዋሚዎቹ ሁሉ በኀፍረት ተሸማቀቁ፤ ሕዝቡ በሙሉ ግን እሱ ባደረጋቸው አስደናቂ ነገሮች ሁሉ ይደሰቱ ጀመር።
|
ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የአምላክ መንግሥት ከምን ጋር ይመሳሰላል? ከምንስ ጋር ላነጻጽረው?
|
አንድ ሰው ወስዶ በአትክልት ቦታው ከዘራት የሰናፍጭ ዘር ጋር ይመሳሰላል፤ ይህች ዘር አድጋ ዛፍ ሆነች፤ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎቿ ላይ ሰፈሩ።”
|
ደግሞም እንዲህ አለ፦ “የአምላክን መንግሥት ከምን ጋር ላነጻጽረው?
|
አንዲት ሴት ወስዳ ሊጡ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ ከሦስት ትላልቅ መስፈሪያ ዱቄት ጋር ከደባለቀችው እርሾ ጋር ይመሳሰላል።”
|
ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዘ ሳለ በየከተማውና በየመንደሩ እያስተማረ ያልፍ ነበር።
|
በዚህ ጊዜ አንድ ሰው “ጌታ ሆይ፣ የሚድኑት ጥቂቶች ናቸው?” ሲል ጠየቀው። እሱም እንዲህ አላቸው፦
|
“በጠባቡ በር ለመግባት ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጉ፤ እላችኋለሁ፦ ብዙዎች ለመግባት ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን አይችሉም።
|
የቤቱ ባለቤት ተነስቶ አንዴ በሩን ከዘጋው በኋላ ውጭ ቆማችሁ ‘ጌታ ሆይ፣ ክፈትልን’ እያላችሁ በሩን ብታንኳኩ ‘ከየት እንደመጣችሁ አላውቅም’ ብሎ ይመልስላችኋል።
|
በዚህ ጊዜ ‘አብረንህ እኮ በልተናል፤ ደግሞም ጠጥተናል፤ በአውራ ጎዳናዎቻችንም አስተምረሃል’ ማለት ትጀምራላችሁ።
|
እሱ ግን ‘ከየት እንደመጣችሁ አላውቅም። እናንተ ክፉ አድራጊዎች ሁሉ፣ ከእኔ ራቁ!’ ይላችኋል።
|
አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብንና ነቢያትን ሁሉ በአምላክ መንግሥት ውስጥ ስታዩና እናንተ ግን በውጭ ተጥላችሁ ስትቀሩ በዚያ ታለቅሳላችሁ፤ ጥርሳችሁንም ታፋጫላችሁ።
|
በተጨማሪም ሰዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ እንዲሁም ከሰሜንና ከደቡብ መጥተው በአምላክ መንግሥት በማዕድ ይቀመጣሉ።
|
ደግሞም ከኋለኞች መካከል ፊተኞች የሚሆኑ፣ ከፊተኞች መካከልም ኋለኞች የሚሆኑ አሉ።”
|
በዚያን ጊዜ አንዳንድ ፈሪሳውያን መጥተው “ሄሮድስ ሊገድልህ ስለሚፈልግ ከዚህ ውጣና ሂድ” አሉት።
|
እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ሄዳችሁ ያንን ቀበሮ ‘ዛሬና ነገ አጋንንትን አስወጣለሁ እንዲሁም ሰዎችን እፈውሳለሁ፤ በሦስተኛውም ቀን ሥራዬን አጠናቅቃለሁ’ በሉት።
|
ይሁንና ነቢይ ከኢየሩሳሌም ውጭ ሊገደል ስለማይችል ዛሬና ነገ እንዲሁም ከነገ ወዲያ ጉዞዬን መቀጠል አለብኝ።
|
ኢየሩሳሌም፣ ኢየሩሳሌም፣ ነቢያትን የምትገድል፤ ወደ እሷ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግር፤ ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ እኔም ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግኩ! እናንተ ግን አልፈለጋችሁም።
|
እነሆ፣ ቤታችሁ ለእናንተ የተተወ ይሆናል። እላችኋለሁ፣ ‘በይሖዋ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!’ እስክትሉ ድረስ ፈጽሞ አታዩኝም።”
|
ኢየሱስ ቀና ብሎ ሲመለከት ሀብታሞች በመዋጮ ሣጥኖቹ ውስጥ መባቸውን ሲከቱ አየ።
|
ከዚያም አንዲት ድሃ መበለት በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች ስትከት አይቶ
|
እንዲህ አለ፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ የበለጠ የሰጠችው ይህች ድሃ መበለት ነች።
|
ሁሉም መባ የሰጡት ከትርፋቸው ነውና፤ እሷ ግን በድሃ አቅሟ ያላትን መተዳደሪያ ሁሉ ሰጥታለች።”
|
በኋላም አንዳንዶች ቤተ መቅደሱ ውብ በሆኑ ድንጋዮችና ለአምላክ በተሰጡ ስጦታዎች እንዴት እንዳጌጠ በተናገሩ ጊዜ
|
“ይህ የምታዩት ነገር ሁሉ የሚፈርስበት ጊዜ ይመጣል፤ እንዲህ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደተነባበረ አይኖርም” አለ።
|
እነሱም “መምህር፣ እነዚህ ነገሮች በእርግጥ የሚፈጸሙት መቼ ነው? እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙበትን ጊዜ የሚጠቁመው ምልክትስ ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።
|
እሱም እንዲህ አለ፦ “እንዳያሳስቷችሁ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች ‘እኔ እሱ ነኝ’ እንዲሁም ‘ጊዜው ቀርቧል’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና። እነሱን አትከተሉ።
|
በተጨማሪም ስለ ጦርነትና ብጥብጥ ስትሰሙ አትሸበሩ። በመጀመሪያ እነዚህ ነገሮች መፈጸም አለባቸውና፤ ፍጻሜው ግን ወዲያው አይመጣም።”
|
ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳል።
|
ታላላቅ የምድር ነውጦች ይከሰታሉ፤ በተለያየ ስፍራም የምግብ እጥረትና ቸነፈር ይሆናል፤ ደግሞም የሚያስፈሩ ነገሮች እንዲሁም ከሰማይ ታላላቅ ምልክቶች ይታያሉ።
|
“እነዚህ ሁሉ ነገሮች ከመፈጸማቸው በፊት ግን ሰዎች ይይዟችኋል፤ ስደት ያደርሱባችኋል እንዲሁም ለምኩራብና ለወህኒ ቤት አሳልፈው ይሰጧችኋል። በስሜም ምክንያት በነገሥታትና በገዢዎች ፊት ያቀርቧችኋል።
|
ይህም ለመመሥከር የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍትላችኋል።
|
የምትሰጡትን መልስ አስቀድማችሁ መዘጋጀት እንደማያስፈልጋችሁ ልብ በሉ፤
|
ተቃዋሚዎቻችሁ ሁሉ በአንድነት ሆነው ሊቋቋሙት ወይም ሊከራከሩት የማይችሉት አንደበትና ጥበብ እሰጣችኋለሁና።
|
ከዚህም በተጨማሪ ወላጆቻችሁ፣ ወንድሞቻችሁ፣ ዘመዶቻችሁና ጓደኞቻችሁ እንኳ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ አንዳንዶቻችሁንም ይገድላሉ፤
|
በስሜ የተነሳም ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል።
|
ይሁን እንጂ ከራሳችሁ ፀጉር አንዷ እንኳ አትጠፋም።
|
ከጸናችሁ ሕይወታችሁን ታተርፋላችሁ።
|
“ይሁንና ኢየሩሳሌም በጦር ሠራዊት ተከባ ስታዩ መጥፊያዋ እንደቀረበ እወቁ።
|
በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በከተማዋ ውስጥ ያሉም ከዚያ ይውጡ፤ በገጠር ያሉም ወደ እሷ አይግቡ፤
|
ምክንያቱም የተጻፈው ነገር ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይህ የፍትሕ እርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ ነው።
|
በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው! ምክንያቱም በምድሪቱ ላይ ታላቅ መከራ፣ በዚህ ሕዝብም ላይ ቁጣ ይመጣል።
|
በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፤ ተማርከውም ወደየአገሩ ይወሰዳሉ፤ የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት እስኪፈጸሙ ድረስም ኢየሩሳሌም በአሕዛብ ትረገጣለች።
|
“እንዲሁም በፀሐይ፣ በጨረቃና በከዋክብት ላይ ምልክቶች ይታያሉ፤ በምድርም ላይ ሕዝቦች ከባሕሩ ድምፅና ነውጥ የተነሳ የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ይጨነቃሉ።
|
የሰማያት ኃይላት ስለሚናወጡ ሰዎች ከፍርሃትና በዓለም ላይ የሚመጡትን ነገሮች ከመጠበቅ የተነሳ ይዝለፈለፋሉ።
|
ከዚያም የሰው ልጅ በኃይልና በታላቅ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።
|
ሆኖም እነዚህ ነገሮች መከሰት ሲጀምሩ መዳናችሁ እየቀረበ ስለሆነ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ቀና አድርጉ።”
|
ከዚያም እንዲህ ሲል አንድ ምሳሌ ነገራቸው፦ “የበለስ ዛፍንና ሌሎች ዛፎችን ሁሉ ተመልከቱ።
|
ዛፎቹ ሲያቆጠቁጡ ራሳችሁ አይታችሁ በጋ እንደቀረበ ታውቃላችሁ።
|
በተመሳሳይ እናንተም እነዚህ ነገሮች ሲፈጸሙ ስታዩ የአምላክ መንግሥት እንደቀረበ እርግጠኞች ሁኑ።
|
እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እስኪፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ ፈጽሞ አያልፍም።
|
ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም።
|
“ይሁንና ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት እንዲሁም ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ ሸክም እንዳይበዛበት ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ ያ ቀን ድንገት ሳታስቡት
|
እንደ ወጥመድ ይመጣባችኋል። ይህ በመላው ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ይደርስባቸዋልና።
|
እንግዲያው መፈጸማቸው ከማይቀረው ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች ማምለጥና በሰው ልጅ ፊት መቆም እንድትችሉ ሁልጊዜ ምልጃ እያቀረባችሁ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።”
|
Subsets and Splits
No community queries yet
The top public SQL queries from the community will appear here once available.