text
stringlengths
4
267
በሌሎች ላይ በፈጸመችው በዚያው መንገድ ብድራቷን መልሱላት፤ አዎ፣ ለሠራቻቸው ነገሮች እጥፍ ክፈሏት፤ በቀላቀለችበት ጽዋ እጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት።
ለራሷ ክብር የሰጠችውንና ያላንዳች ኀፍረት ውድ ነገሮች በማከማቸት የተቀማጠለችውን ያህል፣ በዚያው ልክ ሥቃይና ሐዘን ስጧት። ሁልጊዜ በልቧ ‘ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ፤ መበለትም አይደለሁም፤ ሐዘንም ፈጽሞ አይደርስብኝም’ ትላለችና።
መቅሰፍቶቿ ይኸውም ሞትና ሐዘን እንዲሁም ረሃብ በአንድ ቀን የሚመጡባት ለዚህ ነው፤ ሙሉ በሙሉም በእሳት ትቃጠላለች፤ ምክንያቱም የፈረደባት ይሖዋ አምላክ ብርቱ ነው።
“ከእሷ ጋር ያመነዘሩና ያላንዳች ኀፍረት ከእሷ ጋር በቅንጦት የኖሩ የምድር ነገሥታትም እሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጭስ በሚያዩበት ጊዜ ስለ እሷ ያለቅሳሉ እንዲሁም በሐዘን ደረታቸውን ይደቃሉ።
ደግሞም ሥቃይዋን በመፍራት በሩቅ ቆመው ‘አንቺ ታላቂቱ ከተማ፣ አንቺ ብርቱ የሆንሽው ከተማ ባቢሎን፣ እንዴት ያሳዝናል! እንዴት ያሳዝናል! ፍርድሽ በአንድ ሰዓት ተፈጽሟልና’ ይላሉ።
“የምድር ነጋዴዎችም ከዚህ በኋላ ብዛት ያለውን ሸቀጣቸውን የሚገዛቸው ስለማይኖር ስለ እሷ ያለቅሳሉ እንዲሁም ያዝናሉ፤
ብዛት ያለው ሸቀጣቸውም ወርቅን፣ ብርን፣ የከበሩ ድንጋዮችን፣ ዕንቁን፣ ጥሩ በፍታን፣ ሐምራዊ ጨርቅን፣ ሐርንና ደማቅ ቀይ ጨርቅን ያካተተ ነው፤ በተጨማሪም ጥሩ መዓዛ ካለው እንጨት የተሠራ ነገር ሁሉ፣ ከዝሆን ጥርስ፣ ውድ ከሆነ እንጨት፣ ከመዳብ፣ ከብረትና ከእብነ በረድ የተሠራ ማንኛውም ዓይነት ዕቃ ሁሉ ይገኝበታል፤
ደግሞም ቀረፋ፣ የሕንድ ቅመም፣ ዕጣን፣ ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት፣ ነጭ ዕጣን፣ ወይን፣ የወይራ ዘይት፣ የላመ ዱቄት፣ ስንዴ፣ ከብቶች፣ በጎች፣ ፈረሶች፣ ሠረገላዎች፣ ባሪያዎችና ሰዎች ይገኙበታል።
አዎ፣ የተመኘሽው ጥሩ ፍሬ ከአንቺ ርቋል፤ ምርጥና ማራኪ የሆኑ ነገሮችም ሁሉ ከአንቺ ጠፍተዋል፤ ዳግመኛም አይገኙም።
“እነዚህን ነገሮች በመሸጥ በእሷ የበለጸጉ ነጋዴዎች ሥቃይዋን በመፍራት በሩቅ ቆመው እያለቀሱና እያዘኑ
እንዲህ ይላሉ፦ ‘ጥሩ በፍታ፣ ሐምራዊና ደማቅ ቀይ ልብስ የለበሰችው እንዲሁም በወርቅ ጌጣጌጥ፣ በከበሩ ድንጋዮችና በዕንቁዎች የተንቆጠቆጠችው ታላቂቱ ከተማ፣ እንዴት ያሳዝናል! እንዴት ያሳዝናል!
ምክንያቱም ያ ሁሉ ታላቅ ሀብት በአንድ ሰዓት ውስጥ እንዳልነበረ ሆኗል።’ “የመርከብ አዛዦች ሁሉ፣ በባሕር ላይ የሚጓዙ ሁሉ፣ መርከበኞችና መተዳደሪያቸው በባሕር ላይ የተመሠረተ ሁሉ በሩቅ ቆመው
እሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጭስ እያዩ ‘እንደ ታላቂቱ ከተማ ያለ ከተማ የት ይገኛል?’ በማለት ጮኹ።
በራሳቸው ላይ አቧራ በትነው እያለቀሱና እያዘኑ እንዲህ ሲሉ ጮኹ፦ ‘በባሕር ላይ መርከቦች ያሏቸውን ሁሉ በሀብቷ ያበለጸገችው ታላቂቱ ከተማ በአንድ ሰዓት ውስጥ መጥፋቷ እንዴት ያሳዝናል! እንዴት ያሳዝናል!’
“ሰማይ ሆይ፣ በእሷ ላይ በደረሰው ነገር ደስ ይበልህ፤ ደግሞም እናንተ ቅዱሳን፣ ሐዋርያትና ነቢያት ደስ ይበላችሁ፤ ምክንያቱም አምላክ ለእናንተ ሲል ፈርዶባታል!”
አንድ ብርቱ መልአክም ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ የሚመስል ድንጋይ አንስቶ ወደ ባሕር በመወርወር እንዲህ አለ፦ “ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ በፍጥነት ቁልቁል ትወረወራለች፤ ዳግመኛም አትገኝም።
በተጨማሪም ራሳቸውን በበገና የሚያጅቡ ዘማሪዎች፣ የሙዚቀኞች፣ የዋሽንት ነፊዎችና የመለከት ነፊዎች ድምፅ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ ፈጽሞ አይሰማም። ደግሞም የማንኛውም ዓይነት የእጅ ጥበብ ባለሙያ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይገኝም፤ እንዲሁም የወፍጮ ድምፅ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም።
የመብራት ብርሃን ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይበራም፤ የሙሽራና የሙሽሪት ድምፅም ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ ይህም የሚሆነው ነጋዴዎችሽ የምድር ታላላቅ ሰዎች ስለነበሩና በመናፍስታዊ ድርጊቶችሽ ብሔራት ሁሉ ስለተሳሳቱ ነው።
በእሷም ውስጥ የነቢያት፣ የቅዱሳንና በምድር ላይ የታረዱ ሰዎች ሁሉ ደም ተገኝቷል።”
እኔም በጉ ከሰባቱ ማኅተሞች አንዱን ሲከፍት አየሁ፤ ከአራቱ ሕያዋን ፍጥረታትም አንዱ እንደ ነጎድጓድ ባለ ድምፅ “ና!” ሲል ሰማሁ።
እኔም አየሁ፣ እነሆ ነጭ ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፤ አክሊልም ተሰጠው፤ እሱም ድል እያደረገ ወጣ፤ ድሉንም ለማጠናቀቅ ወደ ፊት ገሰገሰ።
ሁለተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ ሁለተኛው ሕያው ፍጡር “ና!” ሲል ሰማሁ።
ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ሌላ ፈረስ ወጣ፤ በእሱም ላይ ለተቀመጠው ሰዎች እርስ በርሳቸው ይተራረዱ ዘንድ ሰላምን ከምድር እንዲወስድ ተፈቀደለት፤ እንዲሁም ትልቅ ሰይፍ ተሰጠው።
ሦስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ ሦስተኛው ሕያው ፍጡር “ና!” ሲል ሰማሁ። እኔም አየሁ፣ እነሆ ጥቁር ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ይዞ ነበር።
ከአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት መካከል እንደ ድምፅ ያለ ነገር “አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር፣ ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፤ ደግሞም የወይራ ዘይቱንና ወይኑን አትጉዳ” ሲል ሰማሁ።
አራተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ አራተኛው ሕያው ፍጡር “ና!” ሲል ሰማሁ።
እኔም አየሁ፣ እነሆ ግራጫ ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበር። መቃብርም በቅርብ ይከተለው ነበር። ሞትና መቃብርም በረጅም ሰይፍ፣ በምግብ እጥረት፣ በገዳይ መቅሰፍትና በምድር አራዊት እንዲገድሉ በምድር አንድ አራተኛ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።
አምስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ በአምላክ ቃል የተነሳና በሰጡት ምሥክርነት የተነሳ የታረዱትን ሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያው በታች አየሁ።
እነሱም “ቅዱስና እውነተኛ የሆንከው ሉዓላዊ ጌታ ሆይ፣ በምድር በሚኖሩት ላይ የማትፈርደውና ደማችንን የማትበቀለው እስከ መቼ ነው?” ብለው በታላቅ ድምፅ ጮኹ።
ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤ እንዲሁም ወደፊት እንደ እነሱ የሚገደሉት ባልንጀሮቻቸው የሆኑ ባሪያዎችና የወንድሞቻቸው ቁጥር እስኪሞላ ድረስ ለጥቂት ጊዜ እንዲጠብቁ ተነገራቸው።
ስድስተኛውንም ማኅተም ሲከፍት አየሁ፤ ታላቅ የምድር ነውጥም ተከሰተ፤ ፀሐይም ከፀጉር እንደተሠራ ማቅ ጠቆረች፤ ጨረቃም ሙሉ በሙሉ ደም መሰለች፤
ኃይለኛ ነፋስ የበለስን ዛፍ ሲያወዛውዝ ያልበሰሉት ፍሬዎች ከዛፉ ላይ እንደሚረግፉ፣ የሰማይ ከዋክብትም ወደ ምድር ወደቁ።
ሰማይም እየተጠቀለለ እንዳለ የመጽሐፍ ጥቅልል ከቦታው ተነሳ፤ እንዲሁም ተራሮች ሁሉና ደሴቶች ሁሉ ከቦታቸው ተወገዱ።
ከዚያም የምድር ነገሥታት፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የጦር አዛዦች፣ ሀብታሞች፣ ብርቱዎች፣ ባሪያዎች ሁሉና ነፃ ሰዎች ሁሉ በዋሻዎች ውስጥና ተራራ ላይ ባሉ ዓለቶች መካከል ተደበቁ።
ተራሮቹንና ዓለቶቹንም እንዲህ እያሉ ተማጸኑ፦ “በላያችን ውደቁና በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ፊትና ከበጉ ቁጣ ሰውሩን፤
ምክንያቱም ቁጣቸውን የሚገልጹበት ታላቁ ቀን መጥቷል፤ ማንስ ሊቆም ይችላል?”
ሰባተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ በሰማይ ለግማሽ ሰዓት ያህል ጸጥታ ሰፈነ።
እኔም በአምላክ ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፤ ሰባት መለከትም ተሰጣቸው።
የወርቅ ጥና የያዘ ሌላ መልአክ መጥቶ በመሠዊያው አጠገብ ቆመ፤ እሱም የቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት እየተሰማ በነበረበት ወቅት በዙፋኑ ፊት ባለው በወርቁ መሠዊያ ላይ እንዲያቀርበው ከፍተኛ መጠን ያለው ዕጣን ተሰጠው።
በመልአኩ እጅ ያለው የዕጣኑ ጭስ እንዲሁም የቅዱሳኑ ጸሎት በአምላክ ፊት ወደ ላይ ወጣ።
ሆኖም መልአኩ ወዲያውኑ ጥናውን ይዞ ከመሠዊያው ላይ እሳት በመውሰድ ጥናውን ሞላውና እሳቱን ወደ ምድር ወረወረው። ከዚያም ነጎድጓድ፣ ድምፅ፣ የመብረቅ ብልጭታና የምድር ነውጥ ተከሰተ።
ሰባቱን መለከቶች የያዙት ሰባቱ መላእክትም ሊነፉ ተዘጋጁ።
የመጀመሪያው መለከቱን ነፋ። ከደም ጋር የተቀላቀለ በረዶና እሳት ታየ፤ ወደ ምድርም ተወረወረ፤ የምድር አንድ ሦስተኛ ተቃጠለ፤ የዛፎችም አንድ ሦስተኛ ተቃጠለ፤ የለመለሙ ተክሎችም ሁሉ ተቃጠሉ።
ሁለተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ። በእሳት የተቀጣጠለ ትልቅ ተራራ የሚመስል ነገርም ወደ ባሕር ተወረወረ። የባሕሩም አንድ ሦስተኛ ደም ሆነ፤
በባሕር ውስጥ ካሉ ሕያዋን ፍጥረታትም አንድ ሦስተኛው ሞተ፤ ከመርከቦችም አንድ ሦስተኛው ወደመ።
ሦስተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ። እንደ መብራት ቦግ ያለ አንድ ትልቅ ኮከብም ከሰማይ ወደቀ፤ በወንዞች አንድ ሦስተኛና በውኃ ምንጮች ላይ ወደቀ።
ኮከቡ ጭቁኝ ይባላል። የውኃውም አንድ ሦስተኛ እንደ ጭቁኝ መራራ ሆነ፤ ውኃውም መራራ ከመሆኑ የተነሳ ብዙ ሰዎች በውኃው ጠንቅ ሞቱ።
አራተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ። የፀሐይ አንድ ሦስተኛ፣ የጨረቃ አንድ ሦስተኛና የከዋክብት አንድ ሦስተኛ ተመታ፤ ይህም የሆነው የእነዚህ አካላት አንድ ሦስተኛው እንዲጨልም እንዲሁም የቀኑ አንድ ሦስተኛና የሌሊቱ አንድ ሦስተኛ ብርሃን እንዳያገኝ ነው።
እኔም አየሁ፤ አንድ ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ “መለከቶቻቸውን ሊነፉ የተዘጋጁት ሦስቱ መላእክት በሚያሰሟቸው በቀሩት ኃይለኛ የመለከት ድምፆች የተነሳ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው! ወዮላቸው! ወዮላቸው!”