text stringlengths 4 267 |
|---|
ሙሉ ሽልማት እንድታገኙ እንጂ የደከምንባቸውን ነገሮች እንዳታጡ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። |
ከክርስቶስ ትምህርት አልፎ የሚሄድና በትምህርቱ ጸንቶ የማይኖር ሁሉ አምላክ የለውም። በዚህ ትምህርት ጸንቶ የሚኖር ሰው ግን አብና ወልድ አሉት። |
ማንም ሰው ወደ እናንተ ቢመጣና ይህን ትምህርት ይዞ ባይመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ወይም ሰላም አትበሉት። |
ሰላም የሚለው ሰው የክፉ ሥራው ተባባሪ ይሆናልና። |
የምነግራችሁ ብዙ ነገር ቢኖረኝም በወረቀትና በቀለም ልጽፈው አልፈልግም፤ ከዚህ ይልቅ ደስታችሁ የተሟላ እንዲሆን ወደ እናንተ መጥቼ ፊት ለፊት እንደማነጋግራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። |
የተመረጠችው የእህትሽ ልጆች ሰላምታ ያቀርቡልሻል። |
ከሽማግሌው፣ ከልብ ለምወደው ለተወዳጁ ጋይዮስ። |
የተወደድክ ወንድም፣ አሁን በመልካም ሁኔታ ላይ እንዳለህ ሁሉ፣ በሁሉም ነገር እንዲሳካልህና ጥሩ ጤንነት እንዲኖርህ እጸልያለሁ። |
ወንድሞች መጥተው እውነትን አጥብቀህ እንደያዝክ ሲመሠክሩ በመስማቴ እጅግ ደስ ብሎኛልና፤ ደግሞም በእውነት ውስጥ እየተመላለስክ መሆኑ በጣም አስደስቶኛል። |
ልጆቼ በእውነት ውስጥ እየተመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የበለጠ ደስታ የለኝም። |
የተወደድክ ወንድም፣ በግል ባታውቃቸውም እንኳ ለወንድሞች በምታደርገው ነገር ታማኝ መሆንህን እያሳየህ ነው። |
እነሱም በጉባኤው ፊት ስለ አንተ ፍቅር መሥክረዋል። እባክህ፣ አምላክ ደስ በሚሰኝበት ሁኔታ ሸኛቸው። |
ከአሕዛብ ምንም ሳይቀበሉ የወጡት ለስሙ ሲሉ ነውና። |
ስለዚህ በእውነት ውስጥ አብረን የምንሠራ እንሆን ዘንድ እንዲህ ላሉ ሰዎች የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ የማሳየት ግዴታ አለብን። |
ለጉባኤው የጻፍኩት ነገር ነበር፤ ሆኖም በመካከላቸው የመሪነት ቦታ መያዝ የሚፈልገው ዲዮጥራጢስ ከእኛ በአክብሮት የሚቀበለው ምንም ነገር የለም። |
በመሆኑም እኔ ከመጣሁ ስለ እኛ መጥፎ ወሬ በማናፈስ የሚሠራውን ሥራ ይፋ አወጣለሁ። ይህም አልበቃ ብሎት ወንድሞችን በአክብሮት አይቀበልም፤ እነሱን መቀበል የሚፈልጉትንም ለመከልከልና ከጉባኤ ለማባረር ይጥራል። |
ወዳጄ ሆይ፣ መጥፎ የሆነውን አትከተል፤ ይልቁንም ጥሩ የሆነውን ተከተል። መልካም የሚያደርግ የአምላክ ወገን ነው። መጥፎ የሚያደርግ አምላክን አላየውም። |
ሁሉም ወንድሞች ስለ ድሜጥሮስ በሚገባ መሥክረዋል፤ እውነት ራሱም ይህን አረጋግጧል። እንዲያውም እኛም ጭምር ስለ እሱ እየመሠከርን ነው፤ የምንሰጠው ምሥክርነት ደግሞ እውነት እንደሆነ ታውቃለህ። |
ብዙ የምነግርህ ነገር ነበረኝ፤ ሆኖም ከዚህ በላይ በብዕርና በቀለም ልጽፍልህ አልፈልግም። |
ከዚህ ይልቅ በቅርቡ እንደማይህ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በዚያን ጊዜ ፊት ለፊት እንነጋገራለን። ሰላም ለአንተ ይሁን። ወዳጆች ሰላምታ ያቀርቡልሃል። በግለሰብ ደረጃ ሰላምታዬን ለወዳጆች አቅርብልኝ። |
የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና የያዕቆብ ወንድም ከሆነው ከይሁዳ፣ ለተጠሩትና አባታችን በሆነው አምላክ ለተወደዱት እንዲሁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ይሆኑ ዘንድ ጥበቃ ለተደረገላቸው፦ |
ምሕረት፣ ሰላምና ፍቅር ይብዛላችሁ። |
የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ሁላችንም ስለምናገኘው መዳን ልጽፍላችሁ እጅግ ጓጉቼ የነበረ ቢሆንም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለቅዱሳን ስለተሰጠው እምነት ብርቱ ተጋድሎ እንድታደርጉ ለማሳሰብ ልጽፍላችሁ ተገደድኩ። |
ይህን ያደረግኩት ፍርድ እንደሚጠብቃቸው በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አስቀድሞ የተነገረላቸው አንዳንድ ሰዎች ሾልከው ስለገቡ ነው፤ እነዚህ ሰዎች ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው፣ በአምላካችን ጸጋ እያሳበቡ ዓይን ያወጣ ምግባር የሚፈጽሙ እንዲሁም የዋጀንንና እሱ ብቻ ጌታችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱ ናቸው። |
ምንም እንኳ ይህን ሁሉ አስቀድማችሁ በሚገባ ታውቁ የነበረ ቢሆንም ይሖዋ ሕዝቡን ከግብፅ ምድር እንዳዳነ፣ በኋላም እምነት ያላሳዩትን እንዳጠፋ ላስታውሳችሁ እወዳለሁ። |
በተጨማሪም መጀመሪያ የነበራቸውን ቦታ ያልጠበቁትንና ተገቢ የሆነውን የመኖሪያ ስፍራቸውን የተዉትን መላእክት በታላቁ ቀን ለሚፈጸምባቸው ፍርድ በዘላለም እስራት በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ አቆይቷቸዋል። |
በተመሳሳይም ሰዶምና ገሞራ እንዲሁም በዙሪያቸው የነበሩ ከተሞች ራሳቸውን ልቅ ለሆነ የፆታ ብልግና አሳልፈው የሰጡ ከመሆኑም ሌላ ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ የሥጋ ፍላጎታቸውን ያሳድዱ ነበር፤ በመሆኑም በዘላለም እሳት ፍርድ ተቀጥተው ለእኛ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ሆነዋል። |
ያም ሆኖ ግን እነዚህ ሕልም አላሚዎች ሥጋን ያረክሳሉ፤ ሥልጣንን ይንቃሉ፤ የተከበሩትንም ይሳደባሉ። |
ይሁንና የመላእክት አለቃ ሚካኤል የሙሴን ሥጋ በተመለከተ ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ የስድብ ቃል በመናገር ሊፈርድበት አልደፈረም፤ ከዚህ ይልቅ “ይሖዋ ይገሥጽህ” አለው። |
እነዚህ ሰዎች ግን ስለማያውቁት ነገር ሁሉ ትችት ይሰነዝራሉ። ደግሞም አእምሮ እንደሌላቸው እንስሳት፣ በደመ ነፍስ የሚረዷቸውን ነገሮች ሁሉ ሲያደርጉ የራሳቸውን ሥነ ምግባር ያበላሻሉ። |
በቃየን መንገድ ስለሄዱ፣ ለጥቅም ሲሉ የበለዓምን የተሳሳተ መንገድ በጭፍን ስለተከተሉና በቆሬ የዓመፅ ንግግር ስለጠፉ ወዮላቸው! |
እነዚህ ሰዎች ፍቅራችሁን ለመግለጽ በምታዘጋጁት ግብዣ ላይ ተገኝተው አብረዋችሁ ሲመገቡ ልክ በባሕር ውስጥ እንደተደበቀ ዓለት ከመሆናቸውም ሌላ ያላንዳች ኀፍረት ለሆዳቸው ብቻ የሚያስቡ እረኞች ናቸው፤ በነፋስ ወዲያና ወዲህ የሚነዱ ዝናብ የሌላቸው ደመናዎች እንዲሁም በመከር ጊዜ ፍሬ የማይገኝባቸው፣ ሁለት ጊዜ የሞቱና ከሥራቸው የተነቀሉ ዛፎች ናቸው፤ |
አረፋ እንደሚደፍቅ ኃይለኛ የባሕር ማዕበል አሳፋሪ ድርጊታቸውን ይገልጣሉ፤ ለዘላለም ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የሚጣሉ ተንከራታች ከዋክብት ናቸው። |
ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ ትውልድ የሆነው ሄኖክ ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ሲል ተንብዮአል፦ “እነሆ! ይሖዋ ከአእላፋት ቅዱሳን መላእክቱ ጋር መጥቷል፤ |
የመጣውም በሁሉ ላይ ለመፍረድ፣ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለአምላክ አክብሮት በጎደለው መንገድ የፈጸሙትን ክፉ ድርጊትና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ኃጢአተኞች በእሱ ላይ የተናገሩትን ክፉ ቃል ለማጋለጥ ነው።” |
እነዚህ ሰዎች የሚያጉረመርሙና ኑሯቸውን የሚያማርሩ እንዲሁም የራሳቸውን ምኞት የሚከተሉ ናቸው፤ ጉራ መንዛት ይወዳሉ፤ ለጥቅማቸው ሲሉም ሌሎችን ይክባሉ። |
የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እናንተ ግን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት አስቀድመው የነገሯችሁን ቃል አስታውሱ፤ |
እነሱ “በመጨረሻው ዘመን መጥፎ ምኞታቸውን የሚከተሉ ዘባቾች ይነሳሉ” ይሏችሁ ነበር። |
እነዚህ ሰዎች ክፍፍል የሚፈጥሩ፣ የእንስሳ ባሕርይ ያላቸውና መንፈሳዊ ያልሆኑ ናቸው። |
የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እናንተ ግን እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ላይ ራሳችሁን ገንቡ፤ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ጸልዩ፤ |
ይህን የምታደርጉት የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝላችሁን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት እየተጠባበቃችሁ ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ እንድትኖሩ ነው። |
በተጨማሪም ጥርጣሬ ላደረባቸው ምሕረት አሳዩ፤ |
ከእሳት ነጥቃችሁ በማውጣት አድኗቸው። ለሌሎች ምሕረት ማሳየታችሁንም ቀጥሉ፤ ሆኖም ይህን ስታደርጉ ለራሳችሁ መጠንቀቅና በሥጋ ሥራ ያደፈውን ልብሳቸውን መጥላት ይኖርባችኋል። |
እንዳትሰናከሉ ሊጠብቃችሁና ነቀፋ የሌለባችሁ አድርጎ በታላቅ ደስታ፣ በክብሩ ፊት ሊያቆማችሁ ለሚችለው፣ |
አዳኛችን ለሆነው ብቸኛው አምላክ ከዘመናት ሁሉ በፊት፣ አሁንና እስከ ዘላለም በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ክብር፣ ግርማ፣ ኃይልና ሥልጣን ይሁን። አሜን። |
ሰባቱን ሳህኖች ይዘው ከነበሩት ሰባት መላእክት አንዱ መጥቶ እንዲህ አለኝ፦ “ና፣ በብዙ ውኃዎች ላይ በምትቀመጠው በታላቂቱ አመንዝራ ላይ የተበየነውን ፍርድ አሳይሃለሁ፤ |
የምድር ነገሥታት ከእሷ ጋር አመነዘሩ፤ የምድር ነዋሪዎች ደግሞ በዝሙቷ ወይን ጠጅ ሰከሩ።” |
እሱም በመንፈስ ኃይል ወደ ምድረ በዳ ወሰደኝ። በዚያም አንዲት ሴት አምላክን የሚሰድቡ ስሞች በሞሉበት እንዲሁም ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች ባሉት ደማቅ ቀይ አውሬ ላይ ተቀምጣ አየሁ። |
ሴቲቱ ሐምራዊና ደማቅ ቀይ ልብስ ለብሳ እንዲሁም በወርቅ፣ በከበሩ ድንጋዮችና በዕንቁዎች አጊጣ ነበር፤ በእጇም አስጸያፊ ነገሮችና የዝሙቷ ርኩሰት የሞላበት የወርቅ ጽዋ ይዛ ነበር። |
በግንባሯ ላይ “ታላቂቱ ባቢሎን፣ የአመንዝሮችና የምድር አስጸያፊ ነገሮች እናት” የሚል ሚስጥራዊ ስም ተጽፎ ነበር። |
እኔም ሴቲቱ በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምሥክሮች ደም ሰክራ አየኋት። ባየኋትም ጊዜ እጅግ ተደነቅኩ። |
መልአኩም እንዲህ አለኝ፦ “የተደነቅከው ለምንድን ነው? የሴቲቱን እንዲሁም እሷ የተቀመጠችበትን ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች ያሉት አውሬ ሚስጥር እነግርሃለሁ፦ |
ያየኸው አውሬ ከዚህ በፊት ነበር፤ አሁን ግን የለም፤ ይሁንና በቅርቡ ከጥልቁ ይወጣል፤ ወደ ጥፋትም ይሄዳል። ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል ላይ ያልተጻፈው የምድር ነዋሪዎች አውሬው ከዚህ በፊት እንደነበረ፣ አሁን ግን እንደሌለና ወደፊት እንደሚኖር ሲያዩ በአድናቆት ይዋጣሉ። |
“ይህ ነገር ጥበብ ያለው አእምሮ ይጠይቃል፦ ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የተቀመጠችባቸውን ሰባት ተራሮች ያመለክታሉ። |
ደግሞም ሰባት ነገሥታት ናቸው፦ አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱ አለ፤ ሌላው ደግሞ ገና አልመጣም፤ በሚመጣበት ጊዜ ግን ለአጭር ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል። |
ከዚህ በፊት የነበረው፣ አሁን ግን የሌለው አውሬም ስምንተኛ ንጉሥ ነው፤ የሚወጣው ግን ከሰባቱ ነው፤ እሱም ወደ ጥፋት ይሄዳል። |
“ያየሃቸው አሥሩ ቀንዶች ገና መንግሥትን ያልተቀበሉ አሥር ነገሥታትን ያመለክታሉ፤ ይሁንና ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት እንዲነግሡ ሥልጣን ይቀበላሉ። |
እነዚህ አንድ ዓይነት ሐሳብ አላቸው፤ በመሆኑም ኃይላቸውንና ሥልጣናቸውን ለአውሬው ይሰጣሉ። |
እነዚህ ከበጉ ጋር ይዋጋሉ፤ ሆኖም በጉ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለሆነ ድል ይነሳቸዋል። ከእሱ ጋር ያሉት የተጠሩት፣ የተመረጡትና የታመኑትም ድል ያደርጋሉ።” |
እሱም እንዲህ አለኝ፦ “አመንዝራዋ ተቀምጣባቸው ያየሃቸው ውኃዎች ወገኖችን፣ ብዙ ሕዝብን፣ ብሔራትንና ቋንቋዎችን ያመለክታሉ። |
ያየሃቸው አሥሩ ቀንዶችና አውሬውም አመንዝራዋን ይጠሏታል፤ ከዚያም ይበዘብዟታል፤ ራቁቷንም ያስቀሯታል፤ እንዲሁም ሥጋዋን ይበላሉ፤ ሙሉ በሙሉም በእሳት ያቃጥሏታል። |
አምላክ ቃሉ ፍጻሜውን እስኪያገኝ ድረስ ሐሳቡን ዳር እንዲያደርሱ አዎ፣ መንግሥታቸውን ለአውሬው በመስጠት አንድ የሆነውን የራሳቸውን ሐሳብ እንዲፈጽሙ ይህን በልባቸው አኑሯልና። |
ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ መንግሥት ያላትን ታላቂቱን ከተማ ታመለክታለች።” |
ከዚህ በኋላ በሰማይ እንደ ብዙ ሠራዊት ድምፅ ያለ ታላቅ ድምፅ ሰማሁ። እንዲህም አሉ፦ “ያህን አወድሱ! ማዳን፣ ክብርና ኃይል የአምላካችን ነው፤ |
ምክንያቱም ፍርዶቹ እውነትና ጽድቅ ናቸው። ምድርን በዝሙቷ ባረከሰችው በታላቂቱ አመንዝራ ላይ የፍርድ እርምጃ ወስዷልና፤ እንዲሁም ስለ ባሪያዎቹ ደም ተበቅሏታል።” |
ወዲያውኑም ለሁለተኛ ጊዜ “ያህን አወድሱ! ከእሷ የሚወጣው ጭስም ለዘላለም ወደ ላይ ይወጣል” አሉ። |
ደግሞም 24ቱ ሽማግሌዎችና አራቱ ሕያዋን ፍጥረታት ተደፍተው በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው አምላክ ሰገዱ፤ እንዲሁም “አሜን! ያህን አወድሱ!” አሉ። |
በተጨማሪም ከዙፋኑ የወጣ አንድ ድምፅ “እሱን የምትፈሩ ባሪያዎቹ ሁሉ፣ ታናናሾችና ታላላቆች፣ አምላካችንን አወድሱ” አለ። |
እንደ ብዙ ሠራዊት ድምፅ፣ እንደ ብዙ ውኃዎች ድምፅና እንደ ኃይለኛ ነጎድጓድ ድምፅ ያለ ነገር ሰማሁ። እንዲህም አሉ፦ “ያህን አወድሱ፤ ምክንያቱም ሁሉን ቻይ የሆነው አምላካችን ይሖዋ ነግሦአል! |
የበጉ ሠርግ ስለደረሰና ሙሽራዋ ራሷን ስላዘጋጀች እንደሰት፤ ሐሴትም እናድርግ፤ ለእሱም ክብር እንስጠው። |
አዎ፣ የሚያንጸባርቅና ንጹሕ የሆነ ጥሩ በፍታ እንድትለብስ ተሰጥቷታል፤ ይህ ጥሩ በፍታ የቅዱሳንን የጽድቅ ተግባር ያመለክታልና።” |
እሱም “ይህን ጻፍ፦ ወደ በጉ ሠርግ የራት ግብዣ የተጠሩ ደስተኞች ናቸው” አለኝ። ደግሞም “እነዚህ እውነተኛ የአምላክ ቃሎች ናቸው” አለኝ። |
እኔም በዚህ ጊዜ ልሰግድለት በእግሩ ፊት ተደፋሁ። እሱ ግን “ተጠንቀቅ! ፈጽሞ እንዳታደርገው! እኔ ከአንተም ሆነ ስለ ኢየሱስ የመመሥከር ሥራ ካላቸው ወንድሞችህ ጋር አብሬ የማገለግል ባሪያ ነኝ። ለአምላክ ስገድ! ትንቢት የሚነገረው ስለ ኢየሱስ ለመመሥከር ነውና” አለኝ። |
እኔም ሰማይ ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆም፣ ነጭ ፈረስ ነበር። በእሱም ላይ የተቀመጠው “ታማኝና እውነተኛ” ተብሎ ይጠራል፤ እሱም በጽድቅ ይፈርዳል እንዲሁም ይዋጋል። |
ዓይኖቹ የእሳት ነበልባል ናቸው፤ በራሱም ላይ ብዙ ዘውዶች አሉ። ከራሱ በቀር ማንም የማያውቀው ስም ተጽፎበታል፤ |
ደም የነካው መደረቢያም ለብሷል፤ ደግሞም “የአምላክ ቃል” በሚል ስም ይጠራል። |
በተጨማሪም በሰማይ ያሉት ሠራዊቶች በነጭ ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር፤ እነሱም ነጭና ንጹሕ የሆነ ጥሩ በፍታ ለብሰው ነበር። |
እሱም ብሔራትን ይመታበት ዘንድ ከአፉ ረጅም ስለታም ሰይፍ ይወጣል፤ እንደ እረኛም በብረት በትር ይገዛቸዋል። በተጨማሪም ሁሉን ቻይ የሆነውን የአምላክን የመዓቱን የቁጣ ወይን ጠጅ መጭመቂያ ይረግጣል። |
በመደረቢያው አዎ፣ በጭኑ ላይ “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ” የሚል ስም ተጽፏል። |
በተጨማሪም አንድ መልአክ በፀሐይ መካከል ቆሞ አየሁ፤ እሱም በታላቅ ድምፅ ጮኾ በሰማይ መካከል ለሚበርሩት ወፎች ሁሉ እንዲህ አለ፦ “ወደዚህ ኑ፤ ወደ ታላቁ የአምላክ ራት ተሰብሰቡ፤ |
የነገሥታትን ሥጋ፣ የጦር አዛዦችን ሥጋ፣ የብርቱ ሰዎችን ሥጋ፣ የፈረሶችንና የፈረሰኞችን ሥጋ እንዲሁም የሁሉንም ሥጋ ይኸውም የነፃ ሰዎችንና የባሪያዎችን፣ የታናናሾችንና የታላላቆችን ሥጋ ብሉ።” |
ከዚህ በኋላ አውሬው፣ የምድር ነገሥታትና ሠራዊታቸው በፈረሱ ላይ ከተቀመጠውና ከሠራዊቱ ጋር ለመዋጋት ተሰብስበው አየሁ። |
አውሬውም ተያዘ፤ በፊቱ ተአምራዊ ምልክቶች የፈጸመው ሐሰተኛው ነቢይም ከእሱ ጋር ተያዘ፤ ይህ ነቢይ በእነዚህ ምልክቶች አማካኝነት፣ የአውሬውን ምስል የተቀበሉትንና ለምስሉ የሰገዱትን አስቷል። ሁለቱም በሕይወት እንዳሉ በድኝ ወደሚነደው የእሳት ሐይቅ ተወረወሩ። |
የቀሩት ግን በፈረሱ ላይ ከተቀመጠው አፍ በወጣው ረጅም ሰይፍ ተገደሉ። ወፎችም ሁሉ ሥጋቸውን በልተው ጠገቡ። |
እኔም ዘንግ የሚመስል ሸምበቆ ተሰጠኝ፤ እንዲህም አለኝ፦ “ተነስና የአምላክን ቤተ መቅደስ ቅዱስ ስፍራ፣ መሠዊያውንና በዚያ የሚያመልኩትን ለካ። |
ሆኖም ከቤተ መቅደሱ ቅዱስ ስፍራ ውጭ ያለውን ግቢ ሙሉ በሙሉ ተወው፤ አትለካው፤ ምክንያቱም ለአሕዛብ ተሰጥቷል፤ እነሱም የተቀደሰችውን ከተማ ለ42 ወራት ይረግጧታል። |
እኔም ሁለቱ ምሥክሮቼ ማቅ ለብሰው ለ1,260 ቀናት ትንቢት እንዲናገሩ አደርጋለሁ።” |
እነዚህ በሁለቱ የወይራ ዛፎችና በሁለቱ መቅረዞች ተመስለዋል፤ እነሱም በምድር ጌታ ፊት ቆመዋል። |
ማንም እነሱን ሊጎዳ ቢፈልግ እሳት ከአፋቸው ወጥቶ ጠላቶቻቸውን ይበላል። ማንም ሊጎዳቸው ቢፈልግ በዚህ ዓይነት ሁኔታ መገደል አለበት። |
እነዚህ ሰዎች ትንቢት በሚናገሩባቸው ቀናት ምንም ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን የመዝጋት ሥልጣን አላቸው፤ እንዲሁም ውኃዎችን ወደ ደም የመለወጥና የፈለጉትን ጊዜ ያህል፣ በማንኛውም ዓይነት መቅሰፍት ምድርን የመምታት ሥልጣን አላቸው። |
የምሥክርነት ሥራቸውን ባጠናቀቁ ጊዜ፣ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ውጊያ ይከፍትባቸዋል፤ ድል ይነሳቸዋል፤ እንዲሁም ይገድላቸዋል። |
አስከሬናቸውም በመንፈሳዊ ሁኔታ ሰዶምና ግብፅ ተብላ በምትጠራውና የእነሱም ጌታ በእንጨት ላይ በተሰቀለባት በታላቂቱ ከተማ አውራ ጎዳና ላይ ይጋደማል። |
ከተለያዩ ሕዝቦች፣ ነገዶች፣ ቋንቋዎችና ብሔራት የተውጣጡ ሰዎችም ለሦስት ቀን ተኩል አስከሬናቸውን ያያሉ፤ አስከሬናቸውም እንዲቀበር አይፈቅዱም። |
እነዚህ ሁለት ነቢያት በምድር ላይ የሚኖሩትን አሠቃይተው ስለነበር በምድር ላይ የሚኖሩት በእነሱ ሞት ይደሰታሉ፤ ሐሴትም ያደርጋሉ እንዲሁም እርስ በርሳቸው ስጦታ ይሰጣጣሉ። |
ከሦስት ቀን ተኩል በኋላ ከአምላክ የመጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው፤ በእግሮቻቸውም ቆሙ፤ ያዩአቸውም ሰዎች በታላቅ ፍርሃት ተዋጡ። |
ከሰማይም አንድ ታላቅ ድምፅ “ወደዚህ ውጡ” ሲላቸው ሰሙ። እነሱም በደመና ውስጥ ሆነው ወደ ሰማይ ወጡ፤ ጠላቶቻቸውም አዩአቸው። |
በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር ነውጥ ተከሰተ፤ የከተማዋ አንድ አሥረኛም ወደቀ፤ በምድር ነውጡም 7,000 ሰዎች ሞቱ፤ የቀሩትም ፍርሃት አደረባቸው፤ ለሰማይ አምላክም ክብር ሰጡ። |
ሁለተኛው ወዮታ አልፏል። እነሆ፣ ሦስተኛው ወዮታ በፍጥነት ይመጣል። |
ሰባተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ። በሰማይም ታላላቅ ድምፆች እንዲህ ሲሉ ተሰሙ፦ “የዓለም መንግሥት የጌታችንና የእሱ መሲሕ መንግሥት ሆነ፤ እሱም ለዘላለም ይነግሣል።” |
በአምላክ ፊት በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው የነበሩት 24ቱ ሽማግሌዎችም በግንባራቸው ተደፍተው ለአምላክ ሰገዱ፤ |
Subsets and Splits
No community queries yet
The top public SQL queries from the community will appear here once available.