text
stringlengths
4
267
የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።
የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ፤ ንቁ ሆናችሁ ኑሩ! ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል።
ሆኖም በዓለም ዙሪያ በመላው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያሉት ወንድሞቻችሁ ተመሳሳይ መከራ እየደረሰባቸው እንዳለ ተገንዝባችሁ በእምነት ጸንታችሁ በመቆም ተቃወሙት።
ከክርስቶስ ጋር ባላችሁ አንድነት ወደ ዘላለማዊ ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እሱ ራሱ ሥልጠናችሁ እንዲጠናቀቅ ያደርጋል። ጽኑ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል፤ ደግሞም ያጠነክራችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል።
ኃይል ለዘላለም የእሱ ይሁን። አሜን።
እኔ ታማኝ ወንድም አድርጌ በምቆጥረው በስልዋኖስ አማካኝነት ይህን በአጭሩ ጽፌላችኋለሁ፤ የጻፍኩላችሁም እናንተን ለማበረታታትና ይህ የአምላክ እውነተኛ ጸጋ እንደሆነ አጥብቄ ለመመሥከር ነው። ይህን ጸጋ አጥብቃችሁ ያዙ።
እንደ እናንተ የተመረጠችው በባቢሎን የምትገኘው ሰላምታ ታቀርብላችኋለች፤ ልጄ ማርቆስም ሰላምታ ያቀርብላችኋል።
በፍቅር እርስ በርስ በመሳሳም ሰላምታ ተለዋወጡ። ከክርስቶስ ጋር አንድነት ያላችሁ ሁሉ፣ ሰላም ለእናንተ ይሁን።
ክርስቶስ በሥጋ መከራ ስለተቀበለ እናንተም ይህንኑ አስተሳሰብ ለማንጸባረቅ ዝግጁ ሁኑ፤ ምክንያቱም በሥጋ መከራ የተቀበለ ሰው ኃጢአት መሥራት አቁሟል፤
ይኸውም ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋ በሚኖርበት ቀሪ ሕይወቱ ለሰው ፍላጎት ሳይሆን ለአምላክ ፈቃድ መኖር ይችል ዘንድ ነው።
ዓይን ባወጣ ምግባር፣ ልቅ በሆነ የሥጋ ፍላጎት፣ ከልክ በላይ በመጠጣት፣ መረን በለቀቀ ድግስ፣ በመጠጥ ግብዣዎችና በአስጸያፊ የጣዖት አምልኮ በመካፈል የአሕዛብን ፈቃድ የፈጸማችሁበት ያለፈው ጊዜ ይበቃል።
ይህን በመሰለው ያዘቀጠ ወራዳ ሕይወት ከእነሱ ጋር መሮጣችሁን ስለማትቀጥሉ ግራ ይጋባሉ፤ በመሆኑም ይሰድቧችኋል።
ይሁንና እነዚህ ሰዎች በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው መልስ ይሰጣሉ።
እንዲያውም ምሥራቹ ለሙታንም የተሰበከው በዚህ ምክንያት ነው፤ በመሆኑም ከሰው አመለካከት አንጻር በሥጋ የሚፈረድባቸው ቢሆንም ከአምላክ አመለካከት አንጻር ከመንፈስ ጋር በሚስማማ ሁኔታ መኖር ይችላሉ።
ሆኖም የሁሉም ነገር መጨረሻ ቀርቧል። ስለዚህ ጤናማ አስተሳሰብ ይኑራችሁ፤ እንዲሁም በጸሎት ረገድ ንቁዎች ሁኑ።
ከሁሉም በላይ አንዳችሁ ለሌላው የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ፤ ምክንያቱም ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል።
ሳታጉረመርሙ አንዳችሁ ለሌላው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳዩ።
በልዩ ልዩ መንገዶች የተገለጸው የአምላክ ጸጋ መልካም መጋቢዎች እንደመሆናችሁ መጠን፣ እያንዳንዳችሁ በተቀበላችሁት ስጦታ መሠረት የተሰጣችሁን ስጦታ አንዳችሁ ሌላውን ለማገልገል ተጠቀሙበት።
የሚናገር ማንም ቢኖር ከአምላክ የተቀበለውን ቃል እየተናገረ እንዳለ ሆኖ ይናገር፤ የሚያገለግል ማንም ቢኖር አምላክ በሚሰጠው ኃይል ተማምኖ ያገልግል፤ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት አምላክ በሁሉም ነገር እንዲከበር ነው። ክብርና ኃይል ለዘላለም የእሱ ነው። አሜን።
የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እንደ እሳት ባሉ ከባድ ፈተናዎች ስትፈተኑ እንግዳ የሆነ ነገር እየደረሰባችሁ እንዳለ አድርጋችሁ በማሰብ አትደነቁ።
ከዚህ ይልቅ ክርስቶስ በክብሩ በሚገለጥበት ወቅት እናንተም እንድትደሰቱና እጅግ ሐሴት እንድታደርጉ እሱ የተቀበለው መከራ ተካፋዮች በመሆናችሁ ምንጊዜም ደስ ይበላችሁ።
ለክርስቶስ ስም ስትሉ ብትነቀፉ ደስተኞች ናችሁ፤ ምክንያቱም የክብር መንፈስ ይኸውም የአምላክ መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋል።
ይሁን እንጂ ከእናንተ መካከል ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ ወይም በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ የሚገባ ሆኖ መከራ አይቀበል።
ይሁንና ማንም ሰው ክርስቲያን በመሆኑ መከራ ቢደርስበት ምንም ኀፍረት አይሰማው፤ ይልቁንም ይህን ስም ተሸክሞ አምላክን ያክብር።
ፍርድ ከአምላክ ቤት የሚጀምርበት አስቀድሞ የተወሰነው ጊዜ ይህ ነውና። እንግዲህ ፍርድ በእኛ የሚጀምር ከሆነ ለአምላክ ምሥራች ታዛዥ ያልሆኑ ሰዎች መጨረሻ ምን ይሆን?
“እንግዲህ ጻድቅ በጭንቅ የሚድን ከሆነ ኃጢአተኛውና ፈሪሃ አምላክ የሌለው ሰውማ ምን ይውጠው ይሆን?”
ስለዚህ የአምላክን ፈቃድ በማድረጋቸው መከራ የሚደርስባቸው ሰዎች መልካም እያደረጉ ራሳቸውን ታማኝ ለሆነው ፈጣሪ አደራ ይስጡ።
የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ ከሆነው ከስምዖን ጴጥሮስ፣ በአምላካችን ጽድቅ እንዲሁም በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ አማካኝነት እኛ ያገኘነውን ዓይነት ክቡር እምነት ለተቀበሉ፦
ስለ አምላክና ስለ ጌታችን ኢየሱስ በምትቀስሙት ትክክለኛ እውቀት አማካኝነት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።
መለኮታዊ ኃይሉ፣ በገዛ ክብሩና በጎነቱ ስለጠራን አምላክ ባገኘነው ትክክለኛ እውቀት ለአምላክ ያደርን ሆነን ለመኖር የሚረዱንን ነገሮች ሁሉ ሰጥቶናል።
በእነዚህ ነገሮች አማካኝነት ክቡርና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋ ሰጥቶናል፤ ይህን ያደረገውም የመጥፎ ምኞት ውጤት ከሆነው ከዓለም ብልሹ ምግባር አምልጣችሁ፣ በዚህ ተስፋ አማካኝነት ከመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች እንድትሆኑ ነው።
በመሆኑም ልባዊ ጥረት በማድረግ በእምነታችሁ ላይ በጎነትን ጨምሩ፤ በበጎነት ላይ እውቀትን፣
በእውቀት ላይ ራስን መግዛትን፣ ራስን በመግዛት ላይ ጽናትን፣ በጽናት ላይ ለአምላክ ማደርን፣
ለአምላክ በማደር ላይ ወንድማዊ መዋደድን፣ በወንድማዊ መዋደድ ላይ ፍቅርን ጨምሩ።
እነዚህ ነገሮች በውስጣችሁ ቢኖሩና ቢትረፈረፉ፣ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁን ትክክለኛ እውቀት ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ይጠብቋችኋል።
እነዚህ ነገሮች የሚጎድሉት ማንኛውም ሰው ብርሃን ላለማየት ዓይኑን የጨፈነ ዕውር ሰው ነው፤ ደግሞም ከቀድሞ ኃጢአቱ መንጻቱን ረስቷል።
በመሆኑም ወንድሞች፣ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን አስተማማኝ ለማድረግ ከበፊቱ ይበልጥ ትጉ፤ እነዚህን ነገሮች የምታደርጉ ከሆነ ፈጽሞ አትወድቁምና።
እንዲያውም በእጅጉ ትባረካላችሁ፤ ጌታችንና አዳኛችን ወደሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥትም ትገባላችሁ።
ስለዚህ ምንም እንኳ እነዚህን ነገሮች የምታውቁና በተማራችሁት እውነት ጸንታችሁ የቆማችሁ ብትሆኑም፣ ስለ እነዚህ ነገሮች ሁልጊዜ እናንተን ከማሳሰብ ወደኋላ አልልም።
በዚህ ድንኳን እስካለሁ ድረስ እናንተን በማሳሰብ ማነቃቃት ተገቢ ይመስለኛል፤
ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽ እንዳሳወቀኝ ይህ ድንኳን የሚወገድበት ጊዜ እንደቀረበ አውቃለሁ።
እኔ ከሄድኩ በኋላ እነዚህን ነገሮች ማስታወስ እንድትችሉ ሁልጊዜ አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ አደርጋለሁ።
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መገኘት ያሳወቅናችሁ በብልሃት የተፈጠረ ተረት ተከትለን ሳይሆን ግርማውን በገዛ ዓይናችን አይተን ነው።
ከግርማዊው ክብር “እኔ ራሴ በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ቃል ለእሱ በተነገረ ጊዜ ከአባታችንና ከአምላካችን ክብርና ሞገስ ተቀብሏል።
ከእሱ ጋር በቅዱሱ ተራራ በነበርንበት ጊዜ ይህ ቃል ከሰማይ ሲመጣ ሰምተናል።
በመሆኑም ትንቢታዊው ቃል ይበልጥ ተረጋግጦልናል፤ ጎህ እስኪቀድና የንጋት ኮከብ እስኪወጣ ድረስ በጨለማ ቦታ፣ በልባችሁ ውስጥ ለሚበራ መብራት የምትጠነቀቁትን ያህል ለትንቢታዊው ቃል ትኩረት መስጠታችሁ መልካም ነው።
በመጀመሪያ ደረጃ፣ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያለው ትንቢት ሁሉ በሰው ሐሳብ ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ።
መቼም ቢሆን ትንቢት በሰው ፈቃድ አልመጣምና፤ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍተው ተናገሩ።
የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ይህ አሁን የምጽፍላችሁ ሁለተኛ ደብዳቤ ነው። በመጀመሪያው ደብዳቤዬ እንዳደረግሁት አሁንም ልጽፍላችሁ የተነሳሁት ማሳሰቢያ በመስጠት በትክክል ማሰብ እንድትችሉ ለማነቃቃት ሲሆን
ይህም ቀደም ሲል ቅዱሳን ነቢያት የተናገሩትን ቃል እንዲሁም ጌታችንና አዳኛችን በሐዋርያት አማካኝነት የሰጠውን ትእዛዝ እንድታስታውሱ ለመርዳት ነው።
ከሁሉ አስቀድሞ ይህን እወቁ፦ በመጨረሻዎቹ ቀናት የራሳቸውን ምኞት እየተከተሉ የሚያፌዙ ፌዘኞች ይመጣሉ።
እነዚህ ፌዘኞች “‘እገኛለሁ’ ያለው ታዲያ የት አለ? አባቶች በሞት ካንቀላፉበት ጊዜ ጀምሮ ሁሉም ነገር ከፍጥረት መጀመሪያ አንስቶ እንዳለ ይቀጥላል” ይላሉ።
በጥንት ዘመን ሰማያት እንደነበሩ እንዲሁም ደረቁ ምድር በአምላክ ቃል ከውኃ በላይ ጸንቶ እንደቆመና በውኃ መካከል እንደነበረ የሚያረጋግጠውን ሐቅ ሆን ብለው ችላ ይላሉ።
በዚያ ጊዜ የነበረው ዓለም በእነዚህ ነገሮች ጠፍቷል። ይህም የሆነው መላዋ ምድር በውኃ በተጥለቀለቀች ጊዜ ነው።
ሆኖም በዚያው ቃል አሁን ያሉት ሰማያትም ሆኑ ምድር ለእሳትና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለሚጠፉበት የፍርድ ቀን ተጠብቀው ይቆያሉ።
የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እናንተ ግን በይሖዋ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፣ ሺህ ዓመት ደግሞ እንደ አንድ ቀን መሆኑን ልትዘነጉ አይገባም።
አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት ይሖዋ የገባውን ቃል ለመፈጸም አይዘገይም፤ ከዚህ ይልቅ እናንተን የታገሠው፣ ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ ነው።
ይሁንና የይሖዋ ቀን እንደ ሌባ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በነጎድጓድ ድምፅ ያልፋሉ፤ ንጥረ ነገሮቹም በኃይለኛ ሙቀት ይቀልጣሉ፤ ምድርና በላይዋ የተሠሩ ነገሮችም ይጋለጣሉ።
እነዚህ ሁሉ ነገሮች በዚህ ሁኔታ የሚቀልጡ ከሆነ ቅዱስ ሥነ ምግባር በመከተልና ለአምላክ ያደራችሁ መሆናችሁን የሚያሳዩ ተግባሮች በመፈጸም ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ ልታስቡበት ይገባል!
ሰማያት በእሳት ተቃጥለው የሚጠፉበትንና ንጥረ ነገሮቹም በኃይለኛ ሙቀት የሚቀልጡበትን የይሖዋን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና በአእምሯችሁ አቅርባችሁ እየተመለከታችሁ ልትኖሩ ይገባል!
በሌላ በኩል ግን አምላክ በገባው ቃል መሠረት አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን፤ በእነዚህም ውስጥ ጽድቅ ይሰፍናል።
ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እነዚህን ነገሮች እየተጠባበቃችሁ ስለሆነ በመጨረሻ በእሱ ፊት ቆሻሻና እድፍ ሳይኖርባችሁ በሰላም እንድትገኙ የተቻላችሁን ጥረት አድርጉ።
በተጨማሪም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ በተሰጠው ጥበብ እንደጻፈላችሁ የጌታችንን ትዕግሥት እንደ መዳን ቁጠሩት፤
እንዲያውም በሁሉም ደብዳቤዎቹ ላይ ስለ እነዚህ ነገሮች ጽፏል። ይሁንና በደብዳቤዎቹ ውስጥ ለመረዳት የሚከብዱ አንዳንድ ነገሮች አሉ፤ እውቀት የጎደላቸውና የሚወላውሉ ሰዎች ሌሎቹን ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ ሁሉ እነዚህንም ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።
ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ይህን አስቀድማችሁ ስላወቃችሁ ሕግ የሚተላለፉ ሰዎች በሚፈጽሙት ስህተት ከእነሱ ጋር ተታልላችሁ እንዳትወሰዱና ጽኑ አቋማችሁ እንዳይናጋ ተጠንቀቁ።
ከዚህ ይልቅ በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እድገት አድርጉ። አሁንም ሆነ ለዘላለም ለእሱ ክብር ይሁን። አሜን።
ይሁን እንጂ በሕዝቡ መካከል ሐሰተኛ ነቢያት እንደነበሩ ሁሉ በእናንተም መካከል ሐሰተኛ አስተማሪዎች ይነሳሉ። እነዚህ ሰዎች ጥፋት የሚያስከትል ኑፋቄ በስውር ያስገባሉ፤ የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ሳይቀር ክደው በራሳቸው ላይ ፈጣን ጥፋት ያመጣሉ።
በተጨማሪም ብዙዎች እነሱ የሚፈጽሙትን ዓይን ያወጣ ምግባር ይከተላሉ፤ በዚህም ምክንያት የእውነት መንገድ ይሰደባል።
እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች አስመሳይ ቃላት በመናገር እናንተን በስግብግብነት ይበዘብዟችኋል። ሆኖም ከብዙ ዘመን በፊት የተበየነባቸው ፍርድ አይዘገይም፤ ጥፋት እንደሚደርስባቸውም ጥርጥር የለውም።
ደግሞም አምላክ ኃጢአት የሠሩትን መላእክት ከመቅጣት ወደኋላ አላለም፤ ይልቁንም በድቅድቅ ጨለማ አስሮ በማስቀመጥ ፍርዳቸውን እንዲጠባበቁ ወደ እንጦሮጦስ ጣላቸው።
እንዲሁም የጽድቅ ሰባኪ የነበረውን ኖኅን ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር አድኖ ፈሪሃ አምላክ ባልነበራቸው ሰዎች በተሞላው ዓለም ላይ የጥፋት ውኃ ባመጣ ጊዜ የጥንቱን ዓለም ከመቅጣት ወደኋላ አላለም።
ደግሞም ፈሪሃ አምላክ ለሌላቸው ሰዎች ለወደፊቱ ምሳሌ እንዲሆኑ የሰዶምና የገሞራ ከተሞችን አመድ በማድረግ ፈርዶባቸዋል።
ሆኖም ለሕግ የማይገዙ ሰዎች በሚፈጽሙት ዓይን ያወጣ ምግባር እጅግ እየተሳቀቀ ይኖር የነበረውን ጻድቁን ሎጥን አድኖታል።
ይህ ጻድቅ ሰው ዕለት ተዕለት በመካከላቸው ሲኖር በሚያየውና በሚሰማው መረን የለቀቀ ድርጊታቸው ጻድቅ ነፍሱን ያስጨንቅ ነበር።
በመሆኑም ይሖዋ፣ ለአምላክ ያደሩ ሰዎችን ከፈተና እንዴት እንደሚያድንና ዓመፀኞችን ደግሞ በፍርድ ቀን ለሚደርስባቸው ጥፋት እንዴት ጠብቆ እንደሚያቆይ ያውቃል።
በተለይ ደግሞ ሰዎችን ለማርከስ ሲሉ ከእነሱ ጋር የፆታ ብልግና ለመፈጸም የሚመኙትንና ሥልጣን ያላቸውን የሚንቁትን ለፍርድ ጠብቆ ያቆያቸዋል። ደፋሮችና በራሳቸው የሚመሩ ከመሆናቸውም በላይ የተከበሩትን ሲሳደቡ አይፈሩም።
ይሁንና መላእክት፣ ከእነሱ የላቀ ብርታትና ኃይል ያላቸው ቢሆንም ለይሖዋ ካላቸው አክብሮት የተነሳ ሐሰተኛ አስተማሪዎቹን በመስደብ አልነቀፏቸውም።
እነዚህ ሰዎች ግን ተይዘው ለመገደል እንደተወለዱ፣ በደመ ነፍስ እንደሚንቀሳቀሱ አእምሮ የሌላቸው እንስሳት ናቸው፤ በማያውቁት ነገር እየገቡ ይሳደባሉ። በሚከተሉት የጥፋት ጎዳና የተነሳ ለጥፋት ይዳረጋሉ።
በሠሩት ክፉ ድርጊት የተነሳ በራሳቸው ላይ ክፉ ነገር በማምጣት ብድራታቸውን ይቀበላሉ። በጠራራ ፀሐይ የሥጋ ፍላጎታቸውን ማርካትን እንደ ደስታ ይቆጥሩታል። እነዚህ ሰዎች እንደ ቆሻሻና እድፍ ናቸው፤ ከእናንተ ጋር በግብዣ ላይ ሲገኙ አታላይ በሆኑ ትምህርቶቻቸው ሌሎችን በማሳት እጅግ ይደሰታሉ።
አመንዝራ ዓይን ያላቸው በመሆኑ ኃጢአት ከመሥራት መታቀብ አይችሉም፤ ጸንተው ያልቆሙትንም ያማልላሉ። መስገብገብ የለመደ ልብ አላቸው። የተረገሙ ልጆች ናቸው።
ቀናውን መንገድ ትተው በተሳሳተ ጎዳና ሄደዋል። ለጥቅም ሲል ክፉ ድርጊት መፈጸም የመረጠውን የቢዖርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከትለዋል።
በለዓም ግን ትክክለኛውን መመሪያ በመጣሱ ተወቅሷል። መናገር የማትችል አህያ እንደ ሰው ተናግራ የነቢዩን የእብደት አካሄድ ለመግታት ሞከረች።
እነዚህ ሰዎች የደረቁ ምንጮችና በአውሎ ነፋስ የሚነዱ ደመናዎች ናቸው፤ ድቅድቅ ጨለማም ይጠብቃቸዋል።
በከንቱ ጉራ ይነዛሉ። በተሳሳተ ጎዳና ከሚመላለሱ ሰዎች መካከል በቅርቡ ያመለጡትን በሥጋ ምኞቶችና ዓይን ባወጣ ምግባር ያማልላሉ።
እነሱ ራሳቸው የመጥፎ ሥነ ምግባር ባሪያዎች ሆነው ሳሉ ነፃ ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጧቸዋል፤ ማንም ሰው በሌላ ሰው ከተሸነፈ የዚያ ሰው ባሪያ ይሆናልና።
ስለ ጌታችንና አዳኛችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ባገኙት ትክክለኛ እውቀት አማካኝነት ከዓለም ርኩሰት ካመለጡ በኋላ ተመልሰው በዚሁ ነገር ከተጠመዱና ከተሸነፉ ከመጀመሪያው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታቸው የከፋ እንደሚሆንባቸው ምንም ጥርጥር የለውም።
የጽድቅን መንገድ በትክክል ካወቁ በኋላ ከተሰጣቸው ቅዱስ ትእዛዝ ወደኋላ ከሚሉ ቀድሞውኑ ባያውቁት ይሻላቸው ነበር።
“ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፤ የታጠበች አሳማም ተመልሳ ጭቃ ላይ ትንከባለላለች” የሚለው እውነተኛ ምሳሌ በእነሱ ላይ ተፈጽሟል።
ከመጀመሪያ የነበረውን፣ የሰማነውን፣ በዓይናችን ያየነውን፣ በትኩረት የተመለከትነውንና በእጃችን የዳሰስነውን የሕይወትን ቃል በተመለከተ እንጽፍላችኋለን፤
(አዎ፣ ይህ ሕይወት ተገልጧል፤ እኛም አይተናል፤ ደግሞም እየመሠከርን ነው፤ እንዲሁም በአብ ዘንድ የነበረውንና ለእኛ የተገለጠውን የዘላለም ሕይወት ለእናንተ እየነገርናችሁ ነው፤)
እናንተም ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተም እየነገርናችሁ ነው። ደግሞም ይህ ኅብረታችን ከአብና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው።
እነዚህን ነገሮች የምንጽፍላችሁ ደስታችን የተሟላ እንዲሆን ነው።
ከእሱ የሰማነውና ለእናንተ የምናሳውቀው መልእክት ይህ ነው፦ አምላክ ብርሃን ነው፤ በእሱም ዘንድ ጨለማ ፈጽሞ የለም።
“ከእሱ ጋር ኅብረት አለን” ብለን እየተናገርን በጨለማ የምንመላለስ ከሆነ እየዋሸን ነው፤ እውነትንም ሥራ ላይ እያዋልን አይደለም።
ይሁን እንጂ እሱ ራሱ በብርሃን እንዳለ ሁሉ እኛም በብርሃን የምንመላለስ ከሆነ እርስ በርሳችን ኅብረት ይኖረናል፤ እንዲሁም የልጁ የኢየሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።
“ኃጢአት የለብንም” ብለን የምንናገር ከሆነ ራሳችንን እያታለልን ነው፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም።
ኃጢአታችንን የምንናዘዝ ከሆነ እሱ ታማኝና ጻድቅ ስለሆነ ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል፤ እንዲሁም ከክፋት ሁሉ ያነጻናል።
“ኃጢአት አልሠራንም” ብለን የምንናገር ከሆነ እሱን ውሸታም እያደረግነው ነው፤ ቃሉም በውስጣችን የለም።
የአምላክ ልጆች ተብለን እንድንጠራ አብ ምን ያህል ታላቅ ፍቅር እንዳሳየን ተመልከቱ! ደግሞም ልጆቹ ነን። ዓለም እኛን የማያውቀን ለዚህ ነው፤ ምክንያቱም ዓለም እሱን አላወቀውም።
የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እኛ አሁን የአምላክ ልጆች ነን፤ ሆኖም ወደፊት ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። እሱ በሚገለጥበት ጊዜ እንደ እሱ እንደምንሆን እናውቃለን፤ ምክንያቱም እሱን በእርግጥ እናየዋለን።