text
stringlengths
4
267
ይሁዳ ተጎሳቁላና ለአስከፊ ባርነት ተዳርጋ በግዞት ተወስዳለች። በብሔራት መካከል ትቀመጣለች፤ ምንም ማረፊያ ስፍራ አታገኝም። በተጨነቀች ጊዜ አሳዳጆቿ ሁሉ ያዟት።
በዓል ለማክበር የሚመጣ ስለሌለ ወደ ጽዮን የሚወስዱት መንገዶች አዝነዋል። በሮቿ ሁሉ ወና ሆነዋል፤ ካህናቷም ሲቃ ይዟቸዋል። ደናግሏ አዝነዋል፤ እሷም አስከፊ ሥቃይ ደርሶባታል።
ባላጋራዎቿ አሁን ጌቶቿ ሆነዋል፤ ጠላቶቿ ጭንቀት የለባቸውም። ከበደሏ ብዛት የተነሳ ይሖዋ ሐዘን አምጥቶባታልና። ልጆቿ በጠላት ፊት ተማርከው ተወስደዋል።
የጽዮን ሴት ልጅ፣ ግርማ ሞገሷ ሁሉ ተገፏል። መኳንንቷ መሰማሪያ ቦታ እንዳጡ አጋዘኖች ሆነዋል፤በሚያሳድዳቸውም ፊት አቅም አጥተው ይጓዛሉ።
ኢየሩሳሌም በምትጎሳቆልበትና መኖሪያ በምታጣበት ጊዜ፣በጥንት ዘመን የነበሯትን ውድ ነገሮች ሁሉ ታስታውሳለች። ሕዝቧ በጠላት እጅ በወደቀበትና የሚረዳት ባልነበረበት ጊዜጠላቶቿ አዩአት፤ በደረሰባትም ውድቀት ሳቁ። ח[ኼት]
ኢየሩሳሌም ከባድ ኃጢአት ፈጽማለች። አስጸያፊ ነገር የሆነችው ለዚህ ነው። ያከብሯት የነበሩ ሁሉ አሁን ናቋት፤ እርቃኗን አይተዋልና። እሷ ራሷም ትቃትታለች፤ በኀፍረትም ፊቷን ታዞራለች።
ርኩሰቷ ቀሚሷ ላይ አለ። ወደፊት የሚገጥማትን ቆም ብላ አላሰበችም። ውድቀቷ አስደንጋጭ ነበር፤ የሚያጽናናትም የለም። ይሖዋ ሆይ፣ ጉስቁልናዬን ተመልከት፤ ጠላት ራሱን ከፍ ከፍ አድርጓልና።
ጠላት በውድ ሀብቶቿ ሁሉ ላይ እጁን አሳርፏል። ወደ አንተ ጉባኤ እንዳይገቡ ያዘዝካቸው ብሔራትወደ መቅደሷ ሲገቡ አይታለችና።
ነዋሪዎቿ ሁሉ ሲቃ ይዟቸዋል፤ የሚበላ ነገር ይፈልጋሉ። ምግብ ለማግኘትና በሕይወት ለመቆየት ብቻ ሲሉ ያሏቸውን ውድ ነገሮች ሰጥተዋል። ይሖዋ ሆይ፣ እይ ደግሞም ተመልከት፤ እንደማትረባ ሴት ሆኛለሁና።
በዚህ መንገድ የምታልፉ ሁሉ፣ ይህ ለእናንተ ከምንም የማይቆጠር ነገር ነው? እዩ፤ ደግሞም ተመልከቱ! ይሖዋ በሚነድ ቁጣው ቀን እንድሠቃይ ያደረገበትን፣በእኔ ላይ የደረሰውን ሥቃይ የመሰለ ሥቃይ አለ?
ከከፍታ ቦታ ወደ አጥንቶቼ እሳት ላከ፤ በእያንዳንዳቸውም ላይ አየለባቸው። ለእግሬ መረብ ዘረጋ፤ ወደ ኋላ እንድመለስ አስገደደኝ። የተጣለች ሴት አድርጎኛል። ቀኑን ሙሉ ታምሜአለሁ።
በደሎቼ እንደ ቀንበር ታስረዋል፤ በእጁም ተገምደዋል። አንገቴ ላይ ተደርገዋል፤ ጉልበቴም ተዳክሟል። ይሖዋ መቋቋም ለማልችላቸው ሰዎች አሳልፎ ሰጥቶኛል።
ይሖዋ በውስጤ ያሉትን ኃያላን በሙሉ አስወገደ። ወጣቶቼን ለማድቀቅ በእኔ ላይ ጉባኤ ጠርቷል። ይሖዋ ድንግሊቱን የይሁዳን ልጅ በወይን መጭመቂያ ውስጥ ረግጧል።
በእነዚህ ነገሮች የተነሳ አለቅሳለሁ፤ ዓይኖቼ እንባ ያፈሳሉ። ሊያጽናናኝ ወይም መንፈሴን ሊያድስ የሚችል ሰው ከእኔ ርቋልና። ወንዶች ልጆቼ ተጥለዋል፤ ጠላት አይሏልና።
ጽዮን እጆቿን ዘረጋች፤ የሚያጽናናትም የለም። በያዕቆብ ዙሪያ ያሉት ሁሉ ጠላቶቹ እንዲሆኑ ይሖዋ ትእዛዝ አስተላልፏል። ኢየሩሳሌም ለእነሱ አስጸያፊ ነገር ሆናለች።
ይሖዋ ጻድቅ ነው፤ ትእዛዙን ተላልፌአለሁና። እናንተ ሰዎች ሁሉ፣ አዳምጡ፤ ሥቃዬንም ተመልከቱ። ደናግሌና ወጣት ወንዶቼ በግዞት ተወስደዋል።
ወዳጆቼን ጠራኋቸው፤ እነሱ ግን ከዱኝ። ካህናቴና ሽማግሌዎቼ በሕይወት ለመቆየት ብለውየሚበላ ነገር ሲፈልጉ በከተማዋ ውስጥ አለቁ።
ይሖዋ ሆይ፣ ተመልከት፤ በከባድ ጭንቀት ተውጫለሁና። አንጀቴም ተላወሰ። ልቤ በውስጤ እጅግ ተረብሿል፤ የለየለት ዓመፀኛ ሆኛለሁና። በውጭ ሰይፍ ይፈጃል፤ በቤት ውስጥ ደግሞ ሞት አለ።
ሰዎች ሲቃዬን ሰምተዋል፤ የሚያጽናናኝም የለም። ጠላቶቼ ሁሉ ስለደረሰብኝ ጥፋት ሰምተዋል። ይህን ጥፋት ስላመጣህ ደስ ተሰኝተዋል። አንተ ግን የተናገርከውን ቀን በእነሱ ላይ ታመጣለህ፤ በዚያን ጊዜ እነሱ እንደ እኔ ይሆናሉ።
ክፋታቸው ሁሉ በፊትህ ይቅረብ፤ በሠራኋቸው በደሎች ሁሉ የተነሳእኔን እንደቀጣኸኝ፣ እነሱንም ቅጣቸው። ለቅሶዬ በዝቷልና፤ ልቤም ታሟል።
እኔ ከቁጣው በትር የተነሳ መከራ ያየሁ ሰው ነኝ።
ወደ ውጭ አስወጥቶኛል፤ በብርሃን ሳይሆን በጨለማ ውስጥ እንድሄድ አድርጎኛል።
ቀኑን ሙሉ በተደጋጋሚ እጁን በእኔ ላይ ሰነዘረ።
ሥጋዬና ቆዳዬ እንዲያልቅ አደረገ፤አጥንቶቼን ሰባበረ።
ቅጥር ሠራብኝ፤ በመራራ መርዝና በመከራ ዙሪያዬን ከበበኝ።
ከሞቱ ብዙ ጊዜ እንደሆናቸው ሰዎች፣ በጨለማ ስፍራዎች እንድቀመጥ አስገደደኝ።
ማምለጥ እንዳልችል በቅጥር ዘጋብኝ፤ከመዳብ በተሠራ ከባድ የእግር ብረት አሰረኝ።
ደግሞም እርዳታ ለማግኘት አምርሬ ስጮኽ ጸሎቴን አይሰማም።
መንገዶቼን በተጠረቡ ድንጋዮች ዘጋ፤ጎዳናዎቼን አጣመመ።
እንደ ድብ፣ እንዳደፈጠ አንበሳም አድብቶ ይጠብቀኛል።
ከመንገድ ገፍትሮ አስወጣኝ፤ ገነጣጠለኝም፤ወና አስቀረኝ።
ደጋኑን ወጠረ፤ የፍላጻውም ዒላማ አደረገኝ።
ኮሮጆው ውስጥ በያዛቸው ፍላጻዎች ኩላሊቴን ወጋ።
የሕዝብ ሁሉ ማላገጫ ሆንኩ፤ ቀኑን ሙሉ በእኔ ላይ እየዘፈኑ ይሳለቁብኛል።
መራራ ነገሮችን እስኪበቃኝ ድረስ አበላኝ፤ ጭቁኝም አጠገበኝ።
ጥርሶቼን በጠጠር ይሰብራል፤አመድ ላይ ይጥለኛል።
ሰላም ነፈግከኝ፤ ጥሩ ነገር ምን እንደሆነ እንኳ ረሳሁ።
ስለዚህ “ግርማ ሞገሴ ተገፏል፤ ከይሖዋ የጠበቅኩት ነገርም ጠፍቷል” እላለሁ።
መጎሳቆሌንና ዱር አዳሪ መሆኔን እንዲሁም ጭቁኝና መራራ መርዝ መብላቴን አስታውስ።
አንተ በእርግጥ ታስታውሳለህ፤ እኔን ለመርዳትም ታጎነብሳለህ።
ይህ ከልቤ አይጠፋም፤ ከዚህም የተነሳ በትዕግሥት እጠባበቃለሁ።
ከይሖዋ ታማኝ ፍቅር የተነሳ ሙሉ በሙሉ አልጠፋንም፤ምሕረቱ ፈጽሞ አያልቅምና።
በየማለዳው አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ እጅግ ብዙ ነው።
እኔ “ይሖዋ ድርሻዬ ነው” አልኩ፤ “እሱን በትዕግሥት የምጠባበቀው ለዚህ ነው።”
ይሖዋ በእሱ ተስፋ ለሚያደርግ፣ እሱንም ዘወትር ለሚሻ ሰው ጥሩ ነው።
የይሖዋን ማዳን ዝም ብሎ መጠባበቅ ጥሩ ነው።
ሰው በልጅነቱ ቀንበር ቢሸከም ጥሩ ነው።
አምላክ ቀንበሩን በእሱ ላይ ሲጥልበት ዝም ብሎ ለብቻው ይቀመጥ።
ፊቱን አቧራ ውስጥ ይቅበር፤ ገና ተስፋ ሊኖር ይችላል።
ጉንጩን፣ ለሚመታው ሰው ይስጥ፤ ስድብንም ይጥገብ።
ይሖዋ ለዘላለም አይጥለንምና።
ለሐዘን የዳረገን ቢሆንም እንኳ እንደ ታማኝ ፍቅሩ ብዛት ምሕረት ያሳያል።
የልቡ ፍላጎት የሰው ልጆች እንዲጎሳቆሉ ወይም እንዲያዝኑ ማድረግ አይደለምና።
የምድር እስረኞች ሁሉ በእግር ሲረገጡ፣
በልዑል አምላክ ፊት ሰው ፍትሕ ሲነፈግ፣
ሰው ከፍርድ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሲጭበረበር፣ይሖዋ እንዲህ ያለውን ነገር በቸልታ አያልፍም።
ይሖዋ ካላዘዘ በቀር አንድን ነገር ተናግሮ መፈጸም የሚችል ማን ነው?
ከልዑሉ አምላክ አፍክፉ ነገርና መልካም ነገር በአንድነት አይወጣም።
ሕያው የሆነ ሰው ኃጢአቱ ባስከተለበት መዘዝ ለምን ያጉረመርማል?
መንገዳችንን እንመርምር፤ ደግሞም እንፈትን፤ ከዚያም ወደ ይሖዋ እንመለስ።
በሰማያት ወዳለው አምላክ እጃችንን ዘርግተን ከልብ የመነጨ ልመና እናቅርብ፦
“እኛ በድለናል፤ ደግሞም ዓምፀናል፤ አንተም ይቅር አላልክም።
ጨርሶ እንዳንቀርብ በቁጣ አገድከን፤አሳደድከን፤ ያለርኅራኄም ገደልከን።
ጸሎታችን እንዳያልፍ ወደ አንተ መቅረብ የሚቻልበትን መንገድ በደመና ዘጋህ።
በሕዝቦች መካከል ጥራጊና ቆሻሻ አደረግከን።”
ጠላቶቻችን ሁሉ በእኛ ላይ አፋቸውን ከፈቱ።
ፍርሃትና ወጥመድ፣ ባድማነትና ጥፋት ዕጣ ፋንታችን ሆነ።
ከሕዝቤ ሴት ልጅ ጥፋት የተነሳ ዓይኔ የእንባ ጎርፍ አፈሰሰ።
ዓይኖቼ ያለማቋረጥና ያለእረፍት ያነባሉ፤
ይሖዋ ከሰማይ ወደ ታች እስኪያይና እስኪመለከት ድረስ ያነባሉ።
በከተማዬ ሴቶች ልጆች ሁሉ ላይ የደረሰውን በማየቴ አዘንኩ።
ጠላቶቼ ያለምክንያት እንደ ወፍ አደኑኝ።
ሕይወቴን በጉድጓድ ውስጥ ጸጥ ሊያደርጓት ሞከሩ፤ በላዬም ላይ የድንጋይ ናዳ ያወርዱብኛል።
በራሴ ላይ ውኃ ጎረፈ፤ እኔም “አለቀልኝ!” አልኩ።
ይሖዋ ሆይ፣ ከጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ስምህን ጠራሁ።
ድምፄን ስማ፤ እርዳታና እፎይታ ለማግኘት የማሰማውን ጩኸት ላለመስማት ጆሮህን አትድፈን።
   በጠራሁህ ቀን ወደ እኔ ቀረብክ። “አትፍራ” አልከኝ።
ይሖዋ ሆይ፣ ተሟገትክልኝ፤ ሕይወቴን ዋጀህ።
ይሖዋ ሆይ፣ በእኔ ላይ የደረሰውን በደል አይተሃል፤ እባክህ ፍትሕ እንዳገኝ አድርግ።
በቀላቸውን ሁሉ፣ በእኔም ላይ ያሴሩትን ሁሉ ተመልክተሃል።
ይሖዋ ሆይ፣ ዘለፋቸውን፣ በእኔም ላይ ያሴሩትን ሁሉ ሰምተሃል፤
ከባላንጣዎቼ አፍ የሚወጣውን ቃልና ቀኑን ሙሉ በእኔ ላይ የሚያንሾካሹኩትን ነገር ሰምተሃል።
እያቸው፤ ተቀምጠውም ሆነ ቆመው በዘፈናቸው ይሳለቁብኛል!
ይሖዋ ሆይ፣ እንደ ሥራቸው መልሰህ ትከፍላቸዋለህ።
እርግማንህን በእነሱ ላይ በማውረድ ደንዳና ልብ እንዲኖራቸው ታደርጋለህ።
ይሖዋ ሆይ፣ በቁጣ ታሳድዳቸዋለህ፤ ከሰማያትህም በታች ታጠፋቸዋለህ።
ይሖዋ የጽዮንን ሴት ልጅ በቁጣው ደመና እንዴት ሸፈናት! የእስራኤልን ውበት ከሰማይ ወደ ምድር ጥሏል። በቁጣው ቀን የእግሩን ማሳረፊያ አላስታወሰም።
ይሖዋ የያዕቆብን መኖሪያዎች በሙሉ ያላንዳች ርኅራኄ ውጧል። የይሁዳን ሴት ልጅ የተመሸጉ ቦታዎች በቁጣው አፈራርሷል። መንግሥቱንና መኳንንቷን ወደ መሬት ጥሏል፤ ደግሞም አርክሷል።
የእስራኤልን ብርታት ሁሉ በታላቅ ቁጣ ቆረጠ። ጠላት በቀረበ ጊዜ እሱ ቀኝ እጁን መለሰ፤በዙሪያው ያለውን ሁሉ እንደሚበላ እሳትም ቁጣው በያዕቆብ ላይ ነደደ።
እንደ ጠላት ደጋኑን ወጠረ፤ ቀኝ እጁም እንደ ባላጋራ ተዘጋጀች፤ለዓይን የሚማርኩትን ሁሉ ገደለ። በጽዮን ሴት ልጅ ድንኳንም ላይ ቁጣውን እንደ እሳት አፈሰሰ።
ይሖዋ እንደ ጠላት ሆነ፤እስራኤልን ዋጠ። ማማዎቿን ሁሉ ዋጠ፤የተመሸጉ ስፍራዎቿን ሁሉ አወደመ። በይሁዳ ሴት ልጅ ዘንድ ለቅሶንና ዋይታን አበዛ።
የራሱን ዳስ በአትክልት ቦታ እንዳለች ጎጆ አፈረሰ። በዓሉ እንዲያከትም አደረገ። ይሖዋ በጽዮን፣ በዓልና ሰንበት እንዲረሳ አድርጓል፤በኃይለኛ ቁጣውም ንጉሡንና ካህኑን አቃሏል።
ይሖዋ መሠዊያውን ናቀ፤መቅደሱን ተወ። የማይደፈሩ ማማዎቿን ግንቦች ለጠላት አሳልፎ ሰጠ። በበዓል ቀን እንደሚደረገው ሁሉ በይሖዋ ቤት በታላቅ ድምፅ ጮኹ።
ይሖዋ የጽዮንን ሴት ልጅ ቅጥር ለማፍረስ ቆርጧል። የመለኪያ ገመዱን ዘርግቷል። ከማጥፋትም እጁን አልመለሰም። የመከላከያ ግንቡና ቅጥሩ እንዲያዝኑ አደረገ። በአንድነትም ደከሙ።
በሮቿ ወደ መሬት ሰጠሙ። መቀርቀሪያዎቿን አስወገደ፤ ደግሞም ሰባበረ። ንጉሥዋና መኳንንቷ በብሔራት መካከል ናቸው። ሕግ የለም፤ ነቢያቷም እንኳ ከይሖዋ የተገለጠላቸው ራእይ የለም።
የጽዮን ሴት ልጅ ሽማግሌዎች ዝም ብለው መሬት ላይ ይቀመጣሉ። በራሳቸው ላይ አቧራ ይነሰንሳሉ፤ ማቅም ይለብሳሉ። የኢየሩሳሌም ደናግል ራሳቸውን ወደ መሬት ደፍተዋል።
ከማልቀሴ ብዛት ዓይኖቼ ፈዘዙ። አንጀቴ ተላወሰ። በሕዝቤ ሴት ልጅ ላይ ከደረሰው ውድቀትእንዲሁም በከተማዋ አደባባዮች ተዝለፍልፈው ከወደቁት ልጆችና ሕፃናት የተነሳ ጉበቴ መሬት ላይ ፈሰሰ።
ልክ እንደቆሰለ ሰው በከተማዋ አደባባዮች ተዝለፍልፈው ሲወድቁና በእናቶቻቸው ጉያ ሆነው ለመሞት ሲያጣጥሩ፣እናቶቻቸውን “እህልና የወይን ጠጅ የት አለ?” ብለው ይጠይቃሉ።
የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ሆይ፣ ምሥክር የሚሆን ምን ነገር ላቀርብልሽ እችላለሁ?ከምንስ ጋር ላመሳስልሽ እችላለሁ? ድንግሊቱ የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፣ አጽናናሽ ዘንድ ከማን ጋር ላወዳድርሽ እችላለሁ? የደረሰብሽ ጥፋት እንደ ባሕር ሰፊ ነውና። ማን ሊፈውስሽ ይችላል?
ነቢያትሽ ያዩልሽ ራእይ ሐሰትና ከንቱ ነው፤ተማርከሽ እንዳትወሰጂ ለማድረግ በደልሽን አላጋለጡም፤ይልቁንም ራእይ ተገለጠልን እያሉ ሐሰትና አሳሳች ቃል ይነግሩሻል።