text
stringlengths
4
267
አካል በሙሉ ዓይን ቢሆን ኖሮ እንዴት መስማት ይቻል ነበር? አካል በሙሉ ጆሮ ቢሆን ኖሮስ እንዴት ማሽተት ይቻል ነበር?
ሆኖም አምላክ እያንዳንዱን የአካል ክፍል እሱ በፈለገው ቦታ መድቦታል።
የአካል ክፍሎች ሁሉ አንድ ዓይነት ቢሆኑ ኖሮ ሙሉ አካል ከየት ይገኝ ነበር?
አሁን ግን የአካል ክፍሎች ብዙ ቢሆኑም አካል ግን አንድ ነው።
ዓይን እጅን “አንተ አታስፈልገኝም” ሊለው አይችልም፤ ወይም ደግሞ ራስ እግርን “አንተ አታስፈልገኝም” ሊለው አይችልም።
እንዲያውም ደካማ የሚመስሉት የአካል ክፍሎች በጣም አስፈላጊ ናቸው፤
እምብዛም ክብር የላቸውም ብለን የምናስባቸውን የአካል ክፍሎች የበለጠ ክብር እንሰጣቸዋለን፤ በመሆኑም የምናፍርባቸውን የአካል ክፍሎች ይበልጥ በክብር እንይዛቸዋለን፤
በአንጻሩ ደግሞ የሚያምሩት የአካል ክፍሎቻችን ምንም አያስፈልጋቸውም። ይሁንና አምላክ ክብር የሚጎድለውን የአካል ክፍል ታላቅ ክብር በማልበስ አካልን ገንብቷል፤
ይህን ያደረገው በአካል መካከል ክፍፍል እንዳይኖር፣ ከዚህ ይልቅ የአካል ክፍሎች በእኩል ደረጃ አንዳቸው ለሌላው አሳቢነት እንዲያሳዩ ነው።
አንድ የአካል ክፍል ቢሠቃይ ሌሎቹ የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረውት ይሠቃያሉ፤ ወይም አንድ የአካል ክፍል ክብር ቢያገኝ ሌሎቹ የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረውት ይደሰታሉ።
እንግዲህ እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም በግለሰብ ደረጃ የአካሉ ክፍል ናችሁ።
አምላክ የተለያዩ የአካል ክፍሎችን ይኸውም አንደኛ ሐዋርያትን፣ ሁለተኛ ነቢያትን፣ ሦስተኛ አስተማሪዎችን፣ ከዚያም ተአምር የሚፈጽሙትን፣ ከዚያም የመፈወስ ስጦታ ያላቸውን፣ ጠቃሚ አገልግሎት የሚያከናውኑትን፣ የመምራት ችሎታ ያላቸውንና በተለያዩ ልሳኖች የሚናገሩትን በጉባኤ ውስጥ መድቧል።
ሁሉ ሐዋርያት ናቸው? ሁሉስ ነቢያት ናቸው? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸው? ሁሉስ ተአምር ይሠራሉ?
ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸው? ሁሉስ በልሳን ይናገራሉ? ሁሉስ ተርጓሚዎች ናቸው?
ይሁንና ብልጫ ያላቸውን ስጦታዎች ለማግኘት ጥረት ማድረጋችሁን ቀጥሉ። ደግሞም ከሁሉ የላቀውን መንገድ አሳያችኋለሁ።
ከእናንተ መካከል አንዱ ከሌላው ጋር የሚከራከርበት ጉዳይ ቢኖረው፣ ጉዳዩን በቅዱሳን ፊት በማቅረብ ፋንታ በዓመፀኛ ሰዎች ፊት ለማቅረብ ፍርድ ቤት ለመሄድ እንዴት ይደፍራል?
ወይስ ቅዱሳን በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁም? ታዲያ እናንተ በዓለም ላይ የምትፈርዱ ከሆነ በጣም ተራ የሆኑ ጉዳዮችን ለመዳኘት አትበቁም?
በመላእክት ላይ እንኳ እንደምንፈርድ አታውቁም? ታዲያ በአሁኑ ሕይወት በሚያጋጥሙ ጉዳዮች ላይ ለምን አትፈርዱም?
ደግሞስ በአሁኑ ሕይወት የሚያጋጥሙ ዳኝነት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ካሉ ጉባኤው የሚንቃቸው ሰዎች እንዲዳኙት ታደርጋላችሁ?
ይህን የምለው ኀፍረት እንዲሰማችሁ ብዬ ነው። ወንድሞቹን መዳኘት የሚችል አንድ እንኳ ጥበበኛ ሰው በመካከላችሁ የለም?
አንድ ወንድም ሌላውን ወንድም ፍርድ ቤት ይወስዳል፤ ያውም የማያምኑ ሰዎች ፊት!
እንግዲህ እርስ በርስ ተካስሳችሁ ፍርድ ቤት መሄዳችሁ ለእናንተ ትልቅ ሽንፈት ነው። ከዚህ ይልቅ እናንተ ራሳችሁ ብትበደሉ አይሻልም? ደግሞስ እናንተ ራሳችሁ ብትታለሉ አይሻልም?
እናንተ ግን ትበድላላችሁ እንዲሁም ታታልላላችሁ፤ ያውም የገዛ ወንድሞቻችሁን!
ወይስ ዓመፀኞች የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁም? አትታለሉ፤ ሴሰኞችም ሆኑ ጣዖት አምላኪዎች ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ግብረ ሰዶማውያን
ወይም ሌቦች ወይም ስግብግቦች ወይም ሰካራሞች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ቀማኞች የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።
አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ። ሆኖም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ታጥባችሁ ነጽታችኋል፣ ተቀድሳችኋል እንዲሁም ጻድቃን ተብላችኋል።
ሁሉም ነገር ተፈቅዶልኛል፤ ሆኖም ሁሉም ነገር ይጠቅማል ማለት አይደለም። ሁሉም ነገር ተፈቅዶልኛል፤ ሆኖም ለምንም ነገር ተገዢ መሆን አልሻም።
ምግብ ለሆድ፣ ሆድም ለምግብ ነው፤ አምላክ ግን ሁለቱንም ያጠፋቸዋል። አካል ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታ ደግሞ ለአካል ነው።
ይሁን እንጂ አምላክ በኃይሉ አማካኝነት ጌታን እንዳስነሳው እኛንም ከሞት ያስነሳናል።
ሰውነታችሁ የክርስቶስ አካል ክፍል እንደሆነ አታውቁም? ታዲያ የክርስቶስ አካል ክፍል የሆነውን ወስጄ ከዝሙት አዳሪ ጋር ላጣምረው? በፍጹም!
ከዝሙት አዳሪ ጋር የሚጣመር ሁሉ ከእሷ ጋር አንድ አካል እንደሚሆን አታውቁም? አምላክ “ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ብሏልና።
ሆኖም ከጌታ ጋር የተቆራኘ ሁሉ በመንፈስ ከእሱ ጋር አንድ ነው።
ከዝሙት ሽሹ! አንድ ሰው የሚፈጽመው ሌላ ኃጢአት ሁሉ ከአካሉ ውጭ ነው፤ ዝሙት የሚፈጽም ሁሉ ግን በራሱ አካል ላይ ኃጢአት እየሠራ ነው።
የእናንተ አካል ከአምላክ ለተቀበላችሁት፣ በውስጣችሁ ላለው መንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሆነ አታውቁም? በተጨማሪም እናንተ የራሳችሁ አይደላችሁም፤
በዋጋ ተገዝታችኋልና። ስለዚህ በሰውነታችሁ አምላክን አክብሩ።
ለጣዖቶች የቀረበን ምግብ በተመለከተ፣ ሁላችንም እውቀት እንዳለን እናውቃለን። እውቀት ያስታብያል፤ ፍቅር ግን ያንጻል።
አንድ ሰው ስለ አንድ ነገር አውቃለሁ ብሎ የሚያስብ ከሆነ ስለዚያ ነገር ማወቅ የሚገባውን ያህል ገና አያውቅም።
ሆኖም አንድ ሰው አምላክን የሚወድ ከሆነ በእሱ ዘንድ የታወቀ ነው።
ለጣዖቶች የቀረበ ምግብ መብላትን በተመለከተ፣ በዓለም ላይ ጣዖት ከንቱ እንደሆነና ከአንዱ በቀር አምላክ እንደሌለ እናውቃለን።
ብዙ “አማልክት” እና ብዙ “ጌቶች” እንደመኖራቸው መጠን በሰማይም ሆነ በምድር አማልክት ተብለው የሚጠሩ ቢኖሩም እንኳ
እኛ ግን ሁሉም ነገር ከእሱ የሆነ እኛም ለእሱ የሆን አንድ አምላክ አብ አለን፤ እንዲሁም ሁሉም ነገር በእሱ በኩል የሆነና እኛም በእሱ በኩል የሆን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለ።
ይሁንና ይህ እውቀት ያላቸው ሁሉም ሰዎች አይደሉም። አንዳንዶች ግን ቀደም ሲል ጣዖት ያመልኩ ስለነበር የሚበሉት ምግብ ለጣዖት የተሠዋ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ፤ ሕሊናቸው ደካማ ስለሆነም ይረክሳል።
ይሁን እንጂ ምግብ ከአምላክ ጋር አያቀራርበንም፤ ባንበላ የሚጎድልብን ነገር የለም፤ ብንበላም የምናተርፈው ነገር የለም።
ነገር ግን የመምረጥ መብታችሁ፣ ደካማ የሆኑትን በሆነ መንገድ እንዳያሰናክላቸው ተጠንቀቁ።
አንተ እውቀት ያለህ በጣዖት ቤተ መቅደስ ውስጥ ስትበላ አንድ ሰው ቢያይህ ደካማ የሆነው ይህ ሰው ሕሊናው ለጣዖት የቀረበውን ምግብ እንዲበላ አያደፋፍረውም?
እንግዲህ ክርስቶስ የሞተለት ይህ ደካማ የሆነው ወንድምህ በአንተ እውቀት ሳቢያ ጠፋ ማለት ነው።
በዚህ መንገድ ወንድሞቻችሁን ስትበድሉና ደካማ የሆነውን ሕሊናቸውን ስታቆስሉ በክርስቶስ ላይ ኃጢአት እየሠራችሁ ነው።
ስለዚህ ምግብ ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ ወንድሜን ላለማሰናከል ስል ከእንግዲህ ፈጽሞ ሥጋ አልበላም።
በመጠኑ ምክንያታዊነት ቢጎድለኝ እንድትታገሡኝ እፈልጋለሁ። ደግሞም እየታገሣችሁኝ ነው!
በአምላክ ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፤ እኔ ራሴ እንደ አንዲት ንጽሕት ድንግል ለክርስቶስ አቀርባችሁ ዘንድ ለአንድ ባል አጭቻችኋለሁ።
ሆኖም እባቡ ሔዋንን በተንኮሉ እንዳታለላት ሁሉ እናንተም አስተሳሰባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ልታሳዩ የሚገባውን ቅንነትና ንጽሕና በሆነ መንገድ እንዳታጡ እፈራለሁ።
አንድ ሰው መጥቶ እኛ የሰበክንላችሁን ሳይሆን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክላችሁ ወይም ከተቀበላችሁት መንፈስ የተለየ ዓይነት መንፈስ ቢያመጣ ወይም ከተቀበላችሁት ምሥራች የተለየ ሌላ ምሥራች ቢናገር እንዲህ ያለውን ሰው በቸልታ ታልፉታላችሁ ማለት ነው።
እኔ ከእናንተ የተራቀቁ ሐዋርያት በምንም ነገር የማንስ አይመስለኝም።
የተዋጣልኝ ተናጋሪ ባልሆን እንኳ እውቀት አይጎድለኝም፤ ይህን በሁሉም መንገድ እንዲሁም በሁሉም ነገር አሳይተናችኋል።
ወይስ እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን ዝቅ አድርጌ የአምላክን ምሥራች ለእናንተ ያለዋጋ በደስታ መስበኬ እንደ ኃጢአት ተቆጥሮብኝ ይሆን?
እናንተን ለማገልገል ከሌሎች ጉባኤዎች ቁሳዊ እርዳታ በመቀበሌ እነሱን አራቁቻለሁ።
ከእናንተ ጋር ሳለሁ ተቸግሬ በነበረበት ጊዜ ከመቄዶንያ የመጡት ወንድሞች የጎደለኝን ነገር በሙሉ በሚገባ ስላሟሉልኝ ለማንም ሸክም አልሆንኩም። አዎ፣ እስካሁን ድረስ በእናንተ ላይ በምንም መንገድ ሸክም አልሆንኩም፤ ወደፊትም ሸክም አልሆንም።
የክርስቶስ እውነት በውስጤ እስካለ ድረስ በአካይያ ክልሎች ሁሉ በዚህ ነገር እንዳልኩራራ ምንም ነገር ሊያግደኝ አይችልም።
ይህን ያደረግኩት ለምንድን ነው? ስለማልወዳችሁ ነው? እንደምወዳችሁ አምላክ ያውቃል።
ይሁንና ከእኛ ጋር እኩል ለመሆን የሚፈልጉትና እኛም ሐዋርያት ነን ብለው የሚኩራሩት ሰዎች ለዚህ የሚሆን መሠረት እንዳያገኙ አሁን እያደረግኩት ያለሁትን ወደፊትም አደርጋለሁ።
እንዲህ ያሉት ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን የሚለውጡ ሐሰተኛ ሐዋርያትና አታላይ ሠራተኞች ናቸውና።
ይህም ምንም አያስደንቅም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋውጣልና።
ስለዚህ አገልጋዮቹም የጽድቅ አገልጋዮች ለመምሰል ራሳቸውን ቢለዋውጡ ምንም አያስገርምም። ሆኖም ፍጻሜያቸው እንደ ሥራቸው ይሆናል።
አሁንም ዳግመኛ እናገራለሁ፦ ማንም ሰው ምክንያታዊ እንዳልሆንኩ አድርጎ አያስብ። እንደዚያ አድርጋችሁ የምትመለከቱኝ ከሆነ ግን እኔም እንደ እነሱ በመጠኑ መኩራራት እንድችል ምክንያታዊነት እንደሚጎድለው ሰው አድርጋችሁ ተቀበሉኝ።
እንደዚህ የምናገረው የጌታን ምሳሌ በመከተል ሳይሆን ምክንያታዊ ያልሆነ ሰው እንደሚያደርገው በኩራትና በትምክህት ነው።
ብዙዎች በሥጋዊ ነገር ስለሚኩራሩ እኔም እኩራራለሁ።
እናንተ በጣም “ምክንያታዊ” ስለሆናችሁ ምክንያታዊ ያልሆኑ ሰዎችን በደስታ ትታገሣላችሁ።
እንዲያውም ማንም እንደ ባሪያ ቢያደርጋችሁ፣ ማንም ንብረታችሁን ሙልጭ አድርጎ ቢወስድባችሁ፣ ማንም ያላችሁን ቢቀማችሁ፣ ማንም ራሱን ከፍ ከፍ ቢያደርግባችሁ ወይም ማንም በጥፊ ቢመታችሁ ትታገሣላችሁ።
ይህን መናገር ለእኛ አሳፋሪ ነው፤ ምክንያቱም አንዳንዶች በሥልጣናችን በአግባቡ መጠቀም የማንችል ደካሞች እንደሆን አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ። ሆኖም ምክንያታዊነት እንደሚጎድለው ሰው ልናገርና ማንም ሰው በሆነ ነገር የልብ ልብ የሚሰማው ከሆነ እኔም የልብ ልብ ሊሰማኝ ይችላል።
ዕብራውያን ናቸው? እኔም ነኝ። እስራኤላውያን ናቸው? እኔም ነኝ። የአብርሃም ዘር ናቸው? እኔም ነኝ።
የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸው? እንደ እብድ ሰው ልናገርና እኔ ከሁሉ በላቀ ደረጃ የክርስቶስ አገልጋይ ነኝ፦ ከሁሉም ይበልጥ ሠርቻለሁ፣ ብዙ ጊዜ ታስሬአለሁ፣ ብዙ ጊዜ ተደብድቤአለሁ እንዲሁም ብዙ ጊዜ ሞት አፋፍ ደርሻለሁ።
አይሁዳውያን ለ40 ጅራፍ አንድ የቀረው ግርፋት አምስት ጊዜ ገርፈውኛል፤
ሦስት ጊዜ በዱላ ተደብድቤአለሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወግሬአለሁ፤ ሦስት ጊዜ የመርከብ መሰበር አደጋ አጋጥሞኛል፤ አንድ ሌሊትና አንድ ቀን በባሕር ላይ አሳልፌአለሁ፤
ብዙ ጊዜ ተጉዣለሁ፤ ደግሞም በወንዝ ሙላት ለሚመጣ አደጋ፣ ዘራፊዎች ለሚያደርሱት አደጋ፣ የገዛ ወገኖቼ ለሚያደርሱት አደጋ፣ ከአሕዛብ ለሚሰነዘር አደጋ፣ በከተማ፣ በምድረ በዳና በባሕር ላይ ለሚያጋጥም አደጋ እንዲሁም በሐሰተኛ ወንድሞች መካከል ለሚያጋጥም አደጋ ተጋልጬ ነበር፤
ብዙ ጥሬአለሁ፤ ብዙ ደክሜአለሁ፤ ብዙ ጊዜ እንቅልፍ ሳልተኛ አድሬአለሁ፤ ተርቤአለሁ፤ ተጠምቻለሁ፤ ብዙ ጊዜ ምግብ በማጣት ተቸግሬአለሁ፤ በብርድ ተቆራምጃለሁ፤ በልብስ እጦትም ተቸግሬአለሁ።
ከእነዚህ ውጫዊ ችግሮች በተጨማሪ ዕለት ዕለት የሚያስጨንቀኝ የጉባኤዎች ሁሉ ሐሳብ ነው።
ድካም የሚሰማው አለ? እኔስ ብሆን ድካም አይሰማኝም? የተሰናከለ አለ? ይህ እኔን በጣም አያናድደኝም?
መኩራራት ካስፈለገ ድክመቴን በሚያሳዩ ነገሮች እኩራራለሁ።
ለዘላለም የሚመሰገነው የጌታ ኢየሱስ አምላክና አባት እየዋሸሁ እንዳልሆነ ያውቃል።
በደማስቆ የንጉሥ አሬጣስ የበታች የሆነው ገዢ ሊይዘኝ ፈልጎ የደማስቆ ሰዎችን ከተማ ያስጠብቅ ነበር፤
ሆኖም በከተማዋ ግንብ ላይ በሚገኘው መስኮት በኩል በቅርጫት አውርደውኝ ከእጁ አመለጥኩ።
በአምላክ ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፣ በቆሮንቶስ ለሚገኘው የአምላክ ጉባኤ እንዲሁም በመላው አካይያ ለሚኖሩ ቅዱሳን ሁሉ፦
አባታችን ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
የምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይወደስ፤
እኛ ከአምላክ በምናገኘው መጽናኛ በማንኛውም ዓይነት መከራ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ማጽናናት እንድንችል እሱ በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል።
ስለ ክርስቶስ ብለን የምንቀበለው መከራ ብዙ እንደሆነ ሁሉ በክርስቶስ በኩል የምናገኘው መጽናኛም የዚያኑ ያህል ብዙ ነው።
ስለዚህ እኛ መከራ ቢደርስብን ለእናንተ መጽናኛና መዳን ያስገኛል፤ መጽናኛ ብናገኝ ደግሞ በእኛ ላይ የደረሰው መከራ በእናንተም ላይ ሲደርስ እንድትጸኑ የሚረዳ መጽናኛ ይሆንላችኋል።
እናንተን በተመለከተ ያለን ተስፋ የማይናወጥ ነው፤ ይህም የሆነው መከራውን ከእኛ ጋር እንደምትካፈሉ ሁሉ መጽናኛውንም እንደምትካፈሉ ስለምናውቅ ነው።
ወንድሞች፣ በእስያ አውራጃ ስለደረሰብን መከራ እንድታውቁ እንፈልጋለን። ከአቅማችን በላይ የሆነ ከባድ ጫና ደርሶብን ስለነበር በሕይወት የመትረፍ ተስፋችን እንኳ ተሟጦ ነበር።
እንዲያውም የሞት ፍርድ ተፈርዶብናል የሚል ስሜት አድሮብን ነበር። ይህ የሆነው ግን በራሳችን ሳይሆን ሙታንን በሚያስነሳው አምላክ እንድንታመን ነው።
እሱ እንዲህ ካለ ለሞት ሊዳርግ የሚችል አደገኛ ሁኔታ አድኖናል፤ ደግሞም ያድነናል፤ ወደፊትም እንደሚያድነን በእሱ ተስፋ እናደርጋለን።
እናንተም ስለ እኛ ምልጃ በማቅረብ ልትረዱን ትችላላችሁ። ይህን ማድረጋችሁ ብዙዎች በሚያቀርቡት ጸሎት የተነሳ ለሚደረግልን ቸርነት ብዙዎች ስለ እኛ የምስጋና ጸሎት እንዲያቀርቡ ያነሳሳቸዋል።
የምንኮራበት ነገር ይህ ነው፦ በዓለም ውስጥ በተለይም በእናንተ መካከል በቅድስናና አምላካዊ ቅንነት በማሳየት እንደኖርን ሕሊናችን ይመሠክራል፤ ይህን ያደረግነው በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን በአምላክ ጸጋ ነው።
ልታነብቡትና ልትረዱት ከምትችሉት በቀር ስለ ሌላ ነገር አንጽፍላችሁም፤ ይህን ነገር በተሟላ ሁኔታ መረዳታችሁን እንደምትቀጥሉ ተስፋ አደርጋለሁ፤
አንዳንዶቻችሁ በእኛ መኩራት እንደምትችሉ እንደተገነዘባችሁ ሁሉ እኛም በጌታችን በኢየሱስ ቀን በእናንተ እንኮራለን።
በመሆኑም በዚህ በመተማመን ዳግመኛ እንድትደሰቱ በመጀመሪያ ወደ እናንተ ለመምጣት አቅጄ ነበር፤
ወደ መቄዶንያ ስሄድ እግረ መንገዴን እናንተን ለማየት፣ ከዚያም ከመቄዶንያ ተመልሼ ከእናንተ ጋር ለመገናኘትና ወደ ይሁዳ እንድትሸኙኝ ለማድረግ አስቤ ነበር።
እንዲህ ዓይነት ዕቅድ አውጥቼ የነበረው እንዲሁ ሳላስብበት ይመስላችኋል? ወይስ ማንኛውንም ነገር ሳቅድ በሥጋዊ አስተሳሰብ ተነድቼ በማቀድ አንዴ “አዎ፣ አዎ” ከዚያ ደግሞ “አይሆንም፣ አይሆንም” የምል ይመስላችኋል?
አምላክ እምነት የሚጣልበት እንደመሆኑ መጠን እኛ ለእናንተ የምንናገረውም ነገር እውነት ነው። መጀመሪያ ላይ “አዎ” ብለን ከዚያ ደግሞ “አይሆንም” አንልም።
ምክንያቱም እኛ ማለትም እኔ፣ ስልዋኖስና ጢሞቴዎስ የሰበክንላችሁ የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ “አዎ” ሆኖ እያለ “አይደለም” ሊሆን አይችልም፤ ከዚህ ይልቅ ከእሱ ጋር በተያያዘ “አዎ” የተባለው “አዎ” ሆኗል።