text
stringlengths
4
267
ስለዚህ እየደረሰባችሁ ያለውን ስደትና መከራ ሁሉ ችላችሁ በመኖር ባሳያችሁት ጽናትና እምነት የተነሳ በአምላክ ጉባኤዎች መካከል እኛ ራሳችን ስለ እናንተ በኩራት እንናገራለን።
ይህ ሁሉ አምላክ ትክክለኛ ፍርድ እንደፈረደ የሚያሳይ ማስረጃ ከመሆኑም በተጨማሪ መከራ እየተቀበላችሁለት ላለው የአምላክ መንግሥት ብቁ ሆናችሁ እንድትቆጠሩ የሚያደርግ ነው።
ከዚህ አንጻር አምላክ መከራን ለሚያመጡባችሁ በአጸፋው መከራን መክፈሉ የጽድቅ እርምጃ ነው።
መከራን የምትቀበሉት እናንተ ግን ጌታ ኢየሱስ ከኃያላን መላእክቱ ጋር ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ ከእኛ ጋር እረፍት ይሰጣችኋል፤
የሚገለጠውም በሚንበለበል እሳት ነው፤ በዚያን ጊዜ አምላክን በማያውቁትና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ለሚገልጸው ምሥራች በማይታዘዙት ላይ የበቀል እርምጃ ይወስዳል።
እነዚህ ሰዎች ዘላለማዊ ጥፋት ተፈርዶባቸው ከጌታ ፊት ይወገዳሉ፤ ክብራማ ኃይሉንም አያዩም፤
በዚያን ጊዜ ከቅዱሳኑ ጋር ሊከበር ይመጣል፤ በእሱ የሚያምኑም ሁሉ በአድናቆት ያዩታል፤ እናንተም የሰጠናችሁን ምሥክርነት በእምነት ስለተቀበላችሁ ከእነሱ መካከል ትቆጠራላችሁ።
በዚህ ምክንያት አምላካችን ለጥሪው ብቁዎች አድርጎ እንዲቆጥራችሁ እንዲሁም የወደደውን መልካም ነገር ሁሉና በእምነት ተገፋፍታችሁ የምታከናውኑትን ሥራ በኃይሉ አማካኝነት ሙሉ በሙሉ እንዲፈጽም ስለ እናንተ ሁልጊዜ እንጸልያለን።
ይህም በአምላካችንና በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ መሠረት የጌታችን የኢየሱስ ስም በእናንተ እንዲከበርና እናንተም ከእሱ ጋር ባላችሁ አንድነት እንድትከበሩ ነው።
በመጨረሻም ወንድሞች፣ በእናንተ ዘንድ እንደሆነው ሁሉ የይሖዋ ቃል በፍጥነት መስፋፋቱን እንዲቀጥልና እንዲከበር ስለ እኛ መጸለያችሁን አታቋርጡ፤
ደግሞም ከመጥፎና ከክፉ ሰዎች እንድንድን ጸልዩልን፤ እምነት ሁሉም ሰው የሚኖረው ነገር አይደለምና።
ጌታ ግን ታማኝ ነው፤ እሱ ያጠነክራችኋል፤ እንዲሁም ከክፉው ይጠብቃችኋል።
ከዚህም በላይ እኛ የጌታ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን፣ ያዘዝናችሁን እያደረጋችሁ እንዳለና ወደፊትም ማድረጋችሁን እንደምትቀጥሉ በእናንተ እንተማመናለን።
አምላክን እንድትወዱና ክርስቶስን በጽናት እንድትከተሉ ጌታ ልባችሁን በትክክለኛው አቅጣጫ መምራቱን ይቀጥል።
ወንድሞች፣ በሥርዓት ከማይሄድና ከእኛ የተቀበላችሁትን ወግ ከማይከተል ማንኛውም ወንድም እንድትርቁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን።
የእኛን አርዓያ እንዴት መከተል እንዳለባችሁ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ ምክንያቱም በመካከላችሁ ሳለን ሥርዓት በጎደለው መንገድ አልተመላለስንም፤
እንዲሁም የማንንም ምግብ በነፃ አልበላንም። እንዲያውም ብዙ ወጪ በማስወጣት በማናችሁም ላይ ሸክም ላለመሆን ሌት ተቀን በመሥራት እንደክምና እንለፋ ነበር።
ይህን ያደረግነው የእኛን አርዓያ እንድትከተሉ ራሳችንን ለእናንተ ምሳሌ አድርገን ለማቅረብ ብለን እንጂ ሥልጣን ሳይኖረን ቀርቶ አይደለም።
እንዲያውም ከእናንተ ጋር በነበርንበት ጊዜ “መሥራት የማይፈልግ ሁሉ አይብላ” የሚል ትእዛዝ ሰጥተናችሁ ነበር።
አንዳንዶች ሥራ ፈት በመሆን በማይመለከታቸው ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ ሥርዓት በጎደለው መንገድ በመካከላችሁ እንደሚመላለሱ እንሰማለንና።
እንዲህ ያሉ ሰዎች አርፈው ሥራቸውን በመሥራት በድካማቸው ያገኙትን እንዲበሉ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛቸዋለን፤ እንዲሁም አጥብቀን እንመክራቸዋለን።
እናንተ ግን ወንድሞች፣ መልካም የሆነውን ከማድረግ አትታክቱ።
ሆኖም በዚህ ደብዳቤ አማካኝነት ላስተላለፍነው ቃል የማይታዘዝ ሰው ቢኖር ይህን ሰው ምልክት አድርጉበት፤ ያፍርም ዘንድ ከእሱ ጋር አትግጠሙ።
ይሁን እንጂ እንደ ጠላት አትመልከቱት፤ ከዚህ ይልቅ እንደ ወንድም አጥብቃችሁ መምከራችሁን ቀጥሉ።
የሰላም ጌታ ራሱ በሁሉም መንገድ ዘወትር ሰላም ይስጣችሁ። ጌታ ከሁላችሁም ጋር ይሁን።
እኔ ጳውሎስ በገዛ እጄ የጻፍኩላችሁ ሰላምታ ይድረሳችሁ፤ ይህ የእጅ ጽሑፍ የደብዳቤዎቼ ሁሉ መለያ ነው፤ አጻጻፌ እንዲህ ነው።
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁም ጋር ይሁን።
ይሁን እንጂ ወንድሞች፣ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገኘትና ከእሱ ጋር ለመሆን አንድ ላይ መሰብሰባችንን በተመለከተ ይህን እንለምናችኋለን፤
በመንፈስ በተነገረ ቃል ወይም በቃል መልእክት ወይም ደግሞ ከእኛ የተላከ በሚመስል ደብዳቤ አማካኝነት የይሖዋ ቀን ደርሷል ብላችሁ በማሰብ የማመዛዘን ችሎታችሁ በቀላሉ አይናወጥ፤ ደግሞም አትደናገጡ።
ማንም ሰው በምንም መንገድ አያሳስታችሁ፤ ምክንያቱም በመጀመሪያ ክህደቱ ሳይመጣና የጥፋት ልጅ የሆነው የዓመፅ ሰው ሳይገለጥ ያ ቀን አይመጣም።
እሱ አምላክ ነኝ እያለ በማወጅ በአምላክ ቤተ መቅደስ ይቀመጥ ዘንድ አምላክ ተብሎ ከሚጠራ ወይም ከሚመለክ ነገር ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ተቃዋሚ ነው።
ያኔ ከእናንተ ጋር በነበርኩበት ጊዜ እነዚህን ነገሮች እነግራችሁ እንደነበር አታስታውሱም?
በገዛ ራሱ ጊዜ ይገለጥ ዘንድ አሁን የሚያግደው ነገር ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ።
እርግጥ ሚስጥራዊ የሆነው ይህ ዓመፅ አሁንም እየሠራ ነው፤ ሆኖም ሚስጥር ሆኖ የሚቆየው አሁን አግዶት ያለው ነገር ከመንገድ እስኪወገድ ድረስ ብቻ ነው።
ከዚያ በኋላ ጌታ ኢየሱስ በአፉ መንፈስ የሚያስወግደውና የእሱ መገኘት ይፋ በሚሆንበት ጊዜ እንዳልነበረ የሚያደርገው ዓመፀኛ ይገለጣል።
ሆኖም የዓመፀኛው መገኘት የሰይጣን ሥራ ሲሆን ይህም የሚፈጸመው በተአምራት፣ በሐሰተኛ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ሁሉ
እንዲሁም ለማታለል ማንኛውንም ዓይነት የክፋት ዘዴ በመጠቀም ነው። ወደ ጥፋት እያመሩ ያሉት ሰዎች ይድኑ ዘንድ የእውነት ፍቅር በውስጣቸው ስለሌለ ይህ ሁሉ እንደ ቅጣት ይደርስባቸዋል።
በዚህም ምክንያት አምላክ ሐሰት የሆነውን ያምኑ ዘንድ አታላይ በሆነ ተጽዕኖ ተሸንፈው እንዲስቱ ይፈቅዳል፤
ይህን የሚያደርገው እውነትን ከማመን ይልቅ በዓመፅ ስለሚደሰቱ ሁሉም እንዲፈረድባቸው ነው።
ይሁን እንጂ በይሖዋ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ አምላክ እናንተን በመንፈሱ በመቀደስ እንዲሁም በእውነት ላይ ባላችሁ እምነት መዳን እንድታገኙ ከመጀመሪያው አንስቶ ስለመረጣችሁ አምላክን ስለ እናንተ ሁልጊዜ ለማመስገን እንገፋፋለን።
የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር እንድታገኙ፣ እኛ በምናውጀው ምሥራች አማካኝነት ለዚህ ዓላማ ጠርቷችኋል።
ስለዚህ ወንድሞች ጸንታችሁ ቁሙ፤ እንዲሁም ከእኛ በተላከ የቃል መልእክትም ሆነ ደብዳቤ የተማራችኋቸውን ወጎች አጥብቃችሁ ያዙ።
በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እንዲሁም የወደደን፣ በጸጋም አማካኝነት ዘላለማዊ መጽናኛና መልካም ተስፋ የሰጠን አባታችን የሆነው አምላክ
ልባችሁን ያጽናኑ፤ እንዲሁም ምንጊዜም መልካም የሆነውን ነገር እንድታደርጉና እንድትናገሩ ያጽኗችሁ።
አዳኛችን በሆነው አምላክና ተስፋችን በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ ትእዛዝ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፣
በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነው ለጢሞቴዎስ፦ አባት ከሆነው አምላክና ከጌታችን ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋ፣ ምሕረትና ሰላም ለአንተ ይሁን።
ወደ መቄዶንያ ልሄድ በተነሳሁበት ጊዜ በኤፌሶን እንድትቆይ እንዳበረታታሁህ ሁሉ አሁንም አንዳንዶች የሐሰት ትምህርት እንዳያስፋፉ ታዛቸው ዘንድ በዚያው እንድትቆይ አበረታታሃለሁ፤
በተጨማሪም ለፈጠራ ወሬዎችና ለትውልድ ሐረግ ቆጠራ ትኩረት እንዳይሰጡ እዘዛቸው። እንዲህ ያሉ ነገሮች ለግምታዊ ሐሳቦች በር ከመክፈት ውጭ የሚያስገኙት ፋይዳ የለም፤ አምላክ እምነትን ለማጠናከር ከሚሰጠው ነገር ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም።
የዚህ ትእዛዝ ዓላማ ከንጹሕ ልብ፣ ከጥሩ ሕሊናና ግብዝነት ከሌለበት እምነት የሚመነጭ ፍቅር እንዲኖረን ነው።
አንዳንዶች እነዚህን ነገሮች በመተው ፍሬ ቢስ ወደሆነ ወሬ ፊታቸውን አዙረዋል።
የሕግ አስተማሪዎች መሆን ይፈልጋሉ፤ ሆኖም የሚናገሯቸውን ነገሮችም ሆነ አጥብቀው የሚሟገቱላቸውን ነገሮች አያስተውሉም።
አንድ ሰው በአግባቡ ሥራ ላይ እስካዋለው ድረስ ሕጉ መልካም ነው፤
ደግሞም ሕግ የሚወጣው ለጻድቅ ሰው ሳይሆን ሕግ ለሚተላለፉና ለዓመፀኞች፣ ፈሪሃ አምላክ ለሌላቸውና ለኃጢአተኞች፣ ታማኞች ላልሆኑና ቅዱስ የሆነውን ለሚንቁ፣ አባትንና እናትን ለሚገድሉ እንዲሁም ለነፍሰ ገዳዮች መሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል፤
በተጨማሪም ለሴሰኞች፣ ግብረ ሰዶም ለሚፈጽሙ ወንዶች፣ ለአፋኞች፣ ለውሸታሞችና በሐሰት ለሚምሉ እንዲሁም ትክክለኛውን ትምህርት ለሚጻረሩ ነገሮች ሁሉ ነው፤
ይህ ትምህርት ደስተኛው አምላክ ከገለጸው ክብራማ ምሥራች ጋር የሚስማማ ሲሆን እሱም ምሥራቹን በአደራ ሰጥቶኛል።
ለአገልግሎቱ በመሾም ታማኝ አድርጎ ስለቆጠረኝ ኃይል የሰጠኝን ጌታችን ክርስቶስ ኢየሱስን አመሰግናለሁ፤
ምንም እንኳ ቀደም ሲል አምላክን የምሳደብ፣ አሳዳጅና እብሪተኛ የነበርኩ ብሆንም ይህን አድርጎልኛል። ደግሞም ባለማወቅና ባለማመን ስላደረግኩት፣ ምሕረት ተደርጎልኛል።
የጌታችን ጸጋም ከእምነት እንዲሁም የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታይ በመሆኔ ምክንያት ካገኘሁት ፍቅር ጋር እጅግ ተትረፍርፎልኛል።
‘ክርስቶስ ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ’ የሚለው ቃል እምነት የሚጣልበትና ሙሉ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚገባው ነው። ከኃጢአተኞች ደግሞ እኔ ዋነኛ ነኝ።
ይሁንና ለእኔ ምሕረት የተደረገው ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ዋነኛ ኃጢአተኛ የሆንኩትን እኔን ምሳሌ አድርጎ በመጠቀም የዘላለም ሕይወት ለማግኘት እምነታቸውን በእሱ ላይ ለሚጥሉ ሰዎች ትዕግሥቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ነው።
እንግዲህ ለማይጠፋውና ለማይታየው፣ እሱ ብቻ አምላክ ለሆነው ለዘላለሙ ንጉሥ ክብርና ግርማ ለዘላለም ይሁን። አሜን።
ልጄ ጢሞቴዎስ፣ ከዚህ ቀደም ስለ አንተ በተነገሩት ትንቢቶች መሠረት ይህን ትእዛዝ በአደራ እሰጥሃለሁ፤ ይኸውም ከእነዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ መልካሙን ውጊያ መዋጋትህን እንድትቀጥል ነው፤
ይህን የምታደርገው እምነትንና ጥሩ ሕሊናን አጥብቀህ በመያዝ ነው፤ አንዳንዶች ሕሊናቸውን ወደ ጎን ገሸሽ በማድረጋቸው ባሕር ላይ አደጋ ደርሶበት እንደተሰባበረ መርከብ እምነታቸው ጠፍቷል።
ከእነሱም መካከል ሄሜኔዎስና እስክንድር ይገኙበታል፤ እነሱ ከተግሣጽ ተምረው በአምላክ ላይ የስድብ ቃል ከመናገር እንዲቆጠቡ ለሰይጣን አሳልፌ ሰጥቻቸዋለሁ።
ይህ ቃል እምነት የሚጣልበት ነው፦ የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚጣጣር ሰው መልካም ሥራን ይመኛል።
ስለዚህ የበላይ ተመልካች የማይነቀፍ፣ የአንዲት ሚስት ባል፣ በልማዶቹ ልከኛ የሆነ፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው፣ ሥርዓታማ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ የማስተማር ብቃት ያለው፣
የማይሰክር፣ ኃይለኛ ያልሆነ፣ ይልቁንም ምክንያታዊ የሆነ፣ የማይጣላ፣ ገንዘብ ወዳድ ያልሆነ፣
ታዛዥና ቁም ነገረኛ የሆኑ ልጆች ያሉትና የራሱን ቤተሰብ በተገቢው ሁኔታ የሚያስተዳድር ሊሆን ይገባዋል፤
(ደግሞስ አንድ ሰው የራሱን ቤተሰብ እንዴት እንደሚያስተዳድር ካላወቀ የአምላክን ጉባኤ እንዴት ሊንከባከብ ይችላል?)
በትዕቢት ተነፍቶ ዲያብሎስ የተፈረደበት ዓይነት ፍርድ እንዳይፈረድበት አዲስ ክርስቲያን አይሁን።
ከዚህም በተጨማሪ እንዳይነቀፍና በዲያብሎስ ወጥመድ ውስጥ እንዳይወድቅ በውጭ ባሉት ሰዎች ዘንድ በመልካም የተመሠከረለት ሊሆን ይገባል።
የጉባኤ አገልጋዮችም በተመሳሳይ ቁም ነገረኞች፣ በሁለት ምላስ የማይናገሩ፣ ብዙ የወይን ጠጅ የማይጠጡ፣ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የማይስገበገቡ፣
የእምነትን ቅዱስ ሚስጥር በንጹሕ ሕሊና አጥብቀው የሚይዙ መሆን ይገባቸዋል።
በተጨማሪም ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በቅድሚያ ይፈተኑ፤ ከዚያም ከክስ ነፃ ሆነው ከተገኙ አገልጋይ ሆነው ያገልግሉ።
ሴቶችም እንደዚሁ ቁም ነገረኞች፣ የሰው ስም የማያጠፉ፣ በልማዶቻቸው ልከኞችና በሁሉም ነገር ታማኞች ሊሆኑ ይገባል።
የጉባኤ አገልጋዮች የአንዲት ሚስት ባል እንዲሁም ልጆቻቸውንና የራሳቸውን ቤተሰብ በተገቢው ሁኔታ የሚያስተዳድሩ ሊሆኑ ይገባል።
በተገቢው ሁኔታ የሚያገለግሉ ወንዶች ለራሳቸው መልካም ስም የሚያተርፉ ከመሆናቸውም በላይ በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ስላላቸው እምነት አፋቸውን ሞልተው ለመናገር የሚያስችል ነፃነት ያገኛሉና።
በቅርቡ ወደ አንተ እንደምመጣ ተስፋ ባደርግም እነዚህን ነገሮች ጽፌልሃለሁ፤
ይህን ያደረግኩት ምናልባት ብዘገይ በአምላክ ቤተሰብ ይኸውም የእውነት ዓምድና ድጋፍ በሆነው የሕያው አምላክ ጉባኤ ውስጥ ምን ዓይነት ምግባር ማሳየት እንዳለብህ ታውቅ ዘንድ ነው።
በእርግጥም ይህ ለአምላክ የማደር ቅዱስ ሚስጥር ያለጥርጥር ታላቅ ነው፦ ‘በሥጋ እንዲገለጥ ተደረገ፤ በመንፈስ ጻድቅ ተባለ፤ ለመላእክት ታየ፤ በአሕዛብ መካከል ተሰበከ፤ በዓለም ያሉ አመኑበት፤ በክብር አረገ።’
እንግዲህ ከሁሉ አስቀድሞ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች በተመለከተ ምልጃ፣ ጸሎት፣ ልመናና ምስጋና እንዲቀርብ አሳስባለሁ፤
በተጨማሪም ነገሥታትንና በሥልጣን ላይ ያሉትን ሁሉ በተመለከተ እንዲሁ እንዲደረግ አሳስባለሁ፤ ይህም ሙሉ በሙሉ ለአምላክ በማደርና ሁሉንም ነገር በትጋት በማከናወን በጸጥታና በተረጋጋ ሁኔታ መኖራችንን እንቀጥል ዘንድ ነው።
ይህም አዳኛችን በሆነው አምላክ ፊት መልካምና ተቀባይነት ያለው ነው፤
የእሱ ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።
አንድ አምላክ አለና፤ በአምላክና በሰው መካከል ደግሞ አንድ መካከለኛ አለ፤ እሱም ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤
ራሱን ለሁሉ ተመጣጣኝ ቤዛ አድርጎ ሰጠ፤ በተወሰነለት ጊዜም የምሥክርነት ቃል የሚነገርለት ነገር ይህ ነው።
ሰባኪና ሐዋርያ ይኸውም እምነትንና እውነትን በተመለከተ የአሕዛብ አስተማሪ ሆኜ የተሾምኩት ለዚህ ምሥክርነት ሲባል ነው፤ ይህን ስል እውነቱን እየተናገርኩ ነው እንጂ እየዋሸሁ አይደለም።
ስለዚህ በሁሉም ቦታ ወንዶች ቁጣንና ክርክርን አስወግደው ታማኝ እጆችን ወደ ላይ በማንሳት አዘውትረው እንዲጸልዩ እፈልጋለሁ።
በተመሳሳይም ሴቶች ፀጉር በመሸረብና በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም ደግሞ በጣም ውድ በሆነ ልብስ ሳይሆን በልከኝነትና በማስተዋል፣ ተገቢ በሆነ ልብስ ራሳቸውን ያስውቡ፤
ለአምላክ ያደርን ነን የሚሉ ሴቶች ሊያደርጉት እንደሚገባ በመልካም ሥራ ይዋቡ።
ሴት ሙሉ በሙሉ በመገዛት በጸጥታ ትማር።
ሴት ዝም እንድትል እንጂ እንድታስተምር ወይም በወንድ ላይ ሥልጣን እንዲኖራት አልፈቅድም።
በመጀመሪያ የተፈጠረው አዳም ነውና፤ ከዚያም ሔዋን ተፈጠረች።
በተጨማሪም አዳም አልተታለለም፤ ከዚህ ይልቅ ፈጽሞ የተታለለችውና ሕግ የተላለፈችው ሴቷ ናት።
ይሁን እንጂ ሴት ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ በእምነት፣ በፍቅርና በቅድስና ብትጸና ልጅ በመውለድ ደህንነቷ ተጠብቆ ትኖራለች።
ሽማግሌ የሆነውን በኃይለ ቃል አትናገረው። ከዚህ ይልቅ እንደ አባት ቆጥረህ በደግነት ምከረው፤ ወጣት ወንዶችን እንደ ወንድሞች፣
አሮጊቶችን እንደ እናቶች፣ ወጣት ሴቶችን ደግሞ እንደ እህቶች አድርገህ በፍጹም ንጽሕና ያዛቸው።
በእርግጥ መበለት ለሆኑ መበለቶች አሳቢነት አሳያቸው።
ሆኖም አንዲት መበለት ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ካሏት እነዚህ ልጆች በመጀመሪያ በራሳቸው ቤተሰብ ውስጥ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ማንጸባረቅን እንዲሁም ለወላጆቻቸውና ለአያቶቻቸው የሚገባቸውን ብድራት መክፈልን ይማሩ፤ ይህ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ነውና።
በእርግጥ መበለት የሆነችና ምንም የሌላት ሴት ተስፋዋን በአምላክ ላይ ትጥላለች እንዲሁም ሌት ተቀን ያለማሰለስ ምልጃና ጸሎት ታቀርባለች።