text
stringlengths
4
267
ሳኦልም ይህን ሲሰማ የአምላክ መንፈስ ኃይል ሰጠው፤ ቁጣውም ነደደ።
እሱም ጥንድ በሬዎችን ወስዶ ቆራረጣቸው፤ እነዚህንም በመልእክተኞቹ እጅ አስይዞ “ሳኦልንና ሳሙኤልን የማይከተል ማንኛውም ሰው ከብቱ እንዲህ ይቆራረጣል!” በማለት እንዲናገሩ ወደ መላው የእስራኤል ግዛት ላካቸው። በሕዝቡም ላይ የይሖዋ ፍርሃት ስለወደቀ ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆኖ ወጣ።
ከዚያም ሳኦል ሰዎቹን ቤዜቅ ላይ ቆጠራቸው፤ እነሱም 300,000 እስራኤላውያንና 30,000 የይሁዳ ሰዎች ነበሩ።
የመጡትንም መልእክተኞች እንዲህ አሏቸው፦ “በጊልያድ ባለችው በኢያቢስ የሚኖሩትን ሰዎች ‘በነገው ዕለት ፀሐይዋ በምትከርበት ጊዜ መዳን ታገኛላችሁ’ በሏቸው።” ከዚያም መልእክተኞቹ መጥተው ለኢያቢስ ሰዎች ነገሯቸው፤ እነሱም በደስታ ፈነደቁ።
ስለሆነም የኢያቢስ ሰዎች “ነገ እጃችንን ለእናንተ እንሰጣለን፤ እናንተም መልካም መስሎ የታያችሁን ሁሉ ልታደርጉብን ትችላላችሁ” አሏቸው።
በማግስቱ ሳኦል ሕዝቡን በሦስት ቡድን ከፈለው፤ እነሱም በማለዳው ክፍለ ሌሊት ወደ አሞናውያን ሰፈር ገብተው ፀሐይዋ እስክትከር ድረስ መቷቸው። የተረፉትም ቢሆኑ ሁለቱ እንኳ አንድ ላይ መሆን እስከማይችሉ ድረስ ተበታተኑ።
ከዚያም ሕዝቡ ሳሙኤልን “‘አሁን ሳኦል በእኛ ላይ ንጉሥ ሊሆን ነው?’ ሲሉ የነበሩት እነማን ናቸው? እነዚህን ሰዎች ስጡንና እንግደላቸው” አለው።
ሳኦል ግን “ይህ ዕለት ይሖዋ እስራኤልን ያዳነበት ስለሆነ በዚህ ቀን ማንም ሰው መገደል የለበትም” አለ።
በኋላም ሳሙኤል ሕዝቡን “ኑ፣ ወደ ጊልጋል እንውጣና ንግሥናውን እንደገና እናጽና” አለ።
በመሆኑም ሕዝቡ ሁሉ ወደ ጊልጋል ሄደ፤ በጊልጋልም ሳኦልን በይሖዋ ፊት አነገሡት። በዚያም በይሖዋ ፊት የኅብረት መሥዋዕቶችን አቀረቡ፤ ሳኦልና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ እጅግ ተደሰቱ።
ከጊዜ በኋላ የዚፍ ሰዎች በጊብዓ ወደሚገኘው ወደ ሳኦል መጥተው “ዳዊት በየሺሞን ፊት ለፊት በሚገኘው በሃኪላ ኮረብታ ተደብቆ የለም?” አሉት።
ስለሆነም ሳኦል ከእስራኤል የተመረጡ 3,000 ሰዎችን በማስከተል ዳዊትን በዚፍ ምድረ በዳ ለመፈለግ ወደዚያ ወረደ።
ሳኦልም ከየሺሞን ፊት ለፊት በሚገኘው በሃኪላ ኮረብታ ላይ መንገድ ዳር ሰፈረ። በዚህ ጊዜ ዳዊት በምድረ በዳ ይኖር ነበር፤ ዳዊትም ሳኦል እሱን ለመፈለግ ወደ ምድረ በዳ እንደመጣ ሰማ።
በመሆኑም ሳኦል በእርግጥ መጥቶ እንደሆነ ለማወቅ ሰላዮችን ላከ።
በኋላም ዳዊት ሳኦል ወደሰፈረበት ቦታ ሄደ፤ ሳኦልና የሠራዊቱ አዛዥ የሆነው የኔር ልጅ አበኔር የተኙበትንም ቦታ አየ፤ ሳኦል በሰፈሩ መሃል ተኝቶ ነበር፤ ሠራዊቱም ዙሪያውን ሰፍሮ ነበር።
ከዚያም ዳዊት ሂታዊውን አሂሜሌክንና የኢዮዓብ ወንድም የሆነውን የጽሩያን ልጅ አቢሳን “ሳኦል ወደሰፈረበት ቦታ አብሮኝ የሚወርድ ማን ነው?” አላቸው። አቢሳም “እኔ አብሬህ እወርዳለሁ” አለ።
ስለዚህ ዳዊትና አቢሳ በሌሊት ሠራዊቱ ወዳለበት ሄዱ፤ ሳኦልም ጦሩን ራስጌው አጠገብ መሬት ላይ ሰክቶ በሰፈሩ መሃል ተኝቶ አገኙት፤ አበኔርና ሠራዊቱም በዙሪያው ተኝተው ነበር።
አቢሳም ዳዊትን “አምላክ ዛሬ ጠላትህን እጅህ ላይ ጥሎታል። እባክህ አሁን አንድ ጊዜ ብቻ በጦር ወግቼ ከመሬት ጋር ላጣብቀው፤ መድገም አያስፈልገኝም” አለው።
ሆኖም ዳዊት አቢሳን “ጉዳት እንዳታደርስበት፤ ለመሆኑ ይሖዋ በቀባው ላይ እጁን አንስቶ ከበደል ነፃ የሚሆን ማን ነው?” አለው።
ከዚያም ዳዊት እንዲህ አለው፦ “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ ይሖዋ ራሱ ይቀስፈዋል፤ ወይም ደግሞ እንደ ማንኛውም ሰው አንድ ቀን ይሞታል፤ አሊያም ወደ ጦርነት ወርዶ እዚያ ይገደላል።
በእኔ በኩል ይሖዋ በቀባው ላይ እጄን ማንሳት በይሖዋ ዓይን ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው! በል አሁን ራስጌው አጠገብ ያለውን ጦርና የውኃ መያዣውን አንሳና እንሂድ።”
በመሆኑም ዳዊት ጦሩንና የውኃ መያዣውን ከሳኦል ራስጌ ወሰደ፤ ከዚያም ሄዱ። ሁሉም ተኝተው ስለነበር ያያቸውም ሆነ ልብ ያላቸው ወይም ከእንቅልፉ የነቃ አንድም ሰው አልነበረም፤ ምክንያቱም ይሖዋ ከባድ እንቅልፍ ጥሎባቸው ነበር።
ከዚያም ዳዊት ወደ ማዶ ተሻግሮ በተራራው ጫፍ ላይ ራቅ ብሎ ቆመ፤ በመካከላቸውም ያለው ርቀት ሰፊ ነበር።
ዳዊትም ወደ ሠራዊቱና ወደ ኔር ልጅ ወደ አበኔር ተጣርቶ “አበኔር፣ የማትመልስልኝ ለምንድን ነው?” አለ። አበኔርም “ንጉሡን የምትጣራው አንተ ማን ነህ?” ሲል መለሰለት።
ዳዊትም አበኔርን እንዲህ አለው፦ “አንተ ወንድ አይደለህም? ደግሞስ በእስራኤል ውስጥ እንደ አንተ ያለ ማን አለ? ታዲያ ጌታህን ንጉሡን በንቃት ያልጠበቅከው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ከወታደሮቹ አንዱ ንጉሡን ጌታህን ለመግደል መጥቶ ነበር።
ይህ ያደረግከው ነገር ጥሩ አይደለም። ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ ይሖዋ የቀባውን ጌታችሁን በንቃት ስላልጠበቃችሁ ሞት ይገባችኋል። እስቲ ዙሪያህን ተመልከት! በንጉሡ ራስጌ አጠገብ የነበረው የንጉሡ ጦርና የውኃ መያዣ የት አለ?”
ሳኦልም የዳዊት ድምፅ መሆኑን ስለለየ “ልጄ ዳዊት ሆይ፣ ይህ የአንተ ድምፅ ነው?” አለው። ዳዊትም መልሶ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ አዎ የእኔ ድምፅ ነው” አለ።
አክሎም እንዲህ አለ፦ “ጌታዬ አገልጋዩን የሚያሳድደው ለምንድን ነው? ምን አድርጌ ነው? የተገኘብኝስ በደል ምንድን ነው?
ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ እባክህ የአገልጋይህን ቃል ስማ፦ በእኔ ላይ እንድትነሳ ያደረገህ ይሖዋ ከሆነ የማቀርበውን የእህል መባ ይቀበል። ሆኖም እንዲህ እንድታደርግ ያነሳሱህ ሰዎች ከሆኑ በይሖዋ ፊት የተረገሙ ይሁኑ፤ ምክንያቱም ‘ሂድ፣ ሌሎች አማልክትን አገልግል!’ ብለው በይሖዋ ርስት ውስጥ ድርሻ እንዳይኖረኝ ዛሬ አባረውኛል።
አሁንም ደሜ ከይሖዋ ፊት ርቆ መሬት ላይ እንዲፈስ አታድርግ፤ ምክንያቱም የእስራኤል ንጉሥ በተራራ ላይ ቆቅ የሚያሳድድ ይመስል አንዲት ቁንጫ ለመፈለግ ወጥቷል።”
ሳኦልም መልሶ እንዲህ አለው፦ “በእርግጥ ኃጢአት ሠርቻለሁ። ልጄ ዳዊት ሆይ፣ ከእንግዲህ ምንም ጉዳት ስለማላደርስብህ ተመለስ፤ ምክንያቱም በዛሬው ዕለት ሕይወቴን ውድ አድርገህ ተመልክተሃታል። በእርግጥም የሞኝነት ድርጊት ፈጽሜአለሁ፤ ትልቅ ስህተት ሠርቻለሁ።”
ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “የንጉሡ ጦር ይኸውና። ከወጣቶቹ መካከል አንዱ ይምጣና ይውሰደው።
ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ጽድቁና እንደ ታማኝነቱ የሚከፍለው ይሖዋ ነው፤ ይኸው ዛሬ ይሖዋ እጄ ላይ ጥሎህ ነበር፤ እኔ ግን ይሖዋ በቀባው ላይ እጄን ለማንሳት ፈቃደኛ አልሆንኩም።
እነሆ፣ ዛሬ የአንተ ሕይወት በፊቴ ውድ እንደሆነች ሁሉ የእኔም ሕይወት በይሖዋ ፊት ውድ ትሁን፤ ከመከራም ሁሉ ያድነኝ።”
ሳኦልም ዳዊትን “ልጄ ዳዊት ሆይ፣ የተባረክ ሁን። አንተ ታላላቅ ሥራዎችን ታከናውናለህ፤ ድል አድራጊም ትሆናለህ” አለው። ከዚያም ዳዊት መንገዱን ቀጠለ፤ ሳኦልም ወደ ስፍራው ተመለሰ።
በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ በምትገኘው በራማታይምጾፊም የሚኖር ሕልቃና የተባለ አንድ ሰው ነበር፤ ይህ ሰው ኤፍሬማዊ ሲሆን የጹፍ ልጅ፣ የቶሁ ልጅ፣ የኤሊሁ ልጅ፣ የየሮሃም ልጅ ነበር።
እሱም ሁለት ሚስቶች ነበሩት፤ የአንደኛዋ ስም ሐና ሲሆን የሌላኛዋ ደግሞ ፍናና ነበር። ፍናና ልጆች ነበሯት፤ ሐና ግን ምንም ልጅ አልነበራትም።
ያም ሰው አምልኮ ለማቅረብና ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ መሥዋዕት ለመሠዋት በየዓመቱ ከከተማው ወደ ሴሎ ይወጣ ነበር። በዚያም ሁለቱ የኤሊ ልጆች ሆፍኒ እና ፊንሃስ ለይሖዋ ካህናት ሆነው ያገለግሉ ነበር።
አንድ ቀን ሕልቃና መሥዋዕት ሲያቀርብ ለሚስቱ ለፍናና እንዲሁም ለወንዶች ልጆቿና ለሴቶች ልጆቿ በሙሉ ድርሻቸውን ሰጣቸው፤
ሆኖም ሐናን ይወዳት ስለነበር ልዩ የሆነ ድርሻ ሰጣት፤ ይሁንና ይሖዋ ለሐና ልጅ አልሰጣትም ነበር።
በተጨማሪም ይሖዋ ልጅ ስላልሰጣት ጣውንቷ እሷን ለማበሳጨት ዘወትር ትሳለቅባት ነበር።
እሷም በየዓመቱ እንዲህ ታደርግባት ነበር፤ ሐና ወደ ይሖዋ ቤት በወጣች ቁጥር፣ እስክታለቅስና መብላት እስኪያቅታት ድረስ ጣውንቷ ትሳለቅባት ነበር።
ባሏ ሕልቃና ግን “ሐና፣ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትበይም? ልብሽስ ለምን ያዝናል? ከአሥር ወንዶች ልጆች እኔ አልበልጥብሽም?” አላት።
ከዚያም ሐና በሴሎ ከበሉና ከጠጡ በኋላ ተነሳች። በዚህ ጊዜ ካህኑ ኤሊ በይሖዋ ቤተ መቅደስ መቃን አጠገብ ወንበር ላይ ተቀምጦ ነበር።
እሷም በጣም ተማርራ ነበር፤ ስቅስቅ ብላም እያለቀሰች ወደ ይሖዋ ትጸልይ ጀመር።
እንዲህም ስትል ተሳለች፦ “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አገልጋይህ እየደረሰባት ያለውን መከራ ተመልክተህ ብታስበኝና አገልጋይህን ሳትረሳት ወንድ ልጅ ብትሰጣት በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለይሖዋ እሰጠዋለሁ፤ ራሱንም ምላጭ አይነካውም።”
ሐና በይሖዋ ፊት ለረጅም ሰዓት ስትጸልይ ኤሊ አፏን ይመለከት ነበር።
ሐና የምትናገረው በልቧ ነበር፤ በመሆኑም ከንፈሯ ሲንቀጠቀጥ ቢታይም ድምፅዋ አይሰማም ነበር። በመሆኑም ኤሊ የሰከረች መሰለው።
ስለዚህ “ስካሩ የማይለቅሽ እስከ መቼ ነው? የወይን ጠጅሽን መጠጣት ተይ” አላት።
ሐናም መልሳ እንዲህ አለች፦ “አልሰከርኩም ጌታዬ! እኔ ብዙ ጭንቀት ያለብኝ ሴት ነኝ፤ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣሁም፤ ይልቅስ ነፍሴን በይሖዋ ፊት እያፈሰስኩ ነው።
እኔ እስካሁን ድረስ እየተናገርኩ ያለሁት በውስጤ ካለው ብሶትና ጭንቀት የተነሳ ስለሆነ አገልጋይህን እንደማትረባ ሴት አትቁጠራት።”
ከዚያም ኤሊ “በሰላም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ የለመንሽውን ነገር ይስጥሽ” አላት።
እሷም “አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ ታግኝ” አለችው። ከዚያም ተነስታ ሄደች፤ ምግብም በላች፤ ዳግመኛም በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም።
እነሱም በማለዳ ተነስተው በይሖዋ ፊት ሰገዱ፤ ከዚያም በራማ ወደሚገኘው ቤታቸው ተመለሱ። ሕልቃናም ከሚስቱ ከሐና ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጸመ፤ ይሖዋም አሰባት።
ከዚያም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሐና ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ እሷም “ከይሖዋ የለመንኩት ነው” በማለት ስሙን ሳሙኤል አለችው።
ከጊዜ በኋላም ሕልቃና ለይሖዋ ዓመታዊውን መሥዋዕት ለመሠዋትና የስእለት መባውን ለማቅረብ ቤተሰቡን ሁሉ ይዞ ወጣ።
ሐና ግን አልወጣችም፤ ምክንያቱም ለባሏ “ሕፃኑ ጡት እንደጣለ አመጣዋለሁ፤ እሱም ይሖዋ ፊት ይቀርባል፤ ዕድሜውንም ሙሉ በዚያ ይኖራል” በማለት ነግራው ነበር።
ባሏ ሕልቃናም “መልካም መስሎ የታየሽን አድርጊ። ልጁን ጡት እስክታስጥዪው ድረስ ቤት ሁኚ። ይሖዋም ያልሽውን ይፈጽም” ብሏት ነበር። በመሆኑም ሐና ቤት ተቀመጠች፤ ልጇንም ጡት እስክታስጥለው ድረስ ተንከባከበችው።
እሷም ልክ ልጁን ጡት እንዳስጣለችው ከልጁ ጋር የሦስት ዓመት ወይፈን፣ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄትና አንድ እንስራ የወይን ጠጅ ይዛ ወጣች፤ ልጁንም በሴሎ ወደሚገኘው ወደ ይሖዋ ቤት ይዛው መጣች።
እነሱም ወይፈኑን ካረዱ በኋላ ልጁን ወደ ኤሊ አመጡት።
እሷም እንዲህ አለች፦ “ጌታዬ ሆይ፣ በሕያውነትህ እምላለሁ፤ ጌታዬ ሆይ፣ እኔ ወደ ይሖዋ ለመጸለይ ከአንተ ጋር እዚህ ቦታ ቆሜ የነበርኩት ሴት ነኝ።
ይህን ልጅ እንዲሰጠኝ ጸልዬ ነበር፤ ይሖዋም የለመንኩትን ሰጠኝ።
እኔ ደግሞ በበኩሌ ልጁን ለይሖዋ እሰጠዋለሁ። በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ለይሖዋ የተሰጠ ይሆናል።” እሱም በዚያ ለይሖዋ ሰገደ።
በመሆኑም የቂርያትየአሪም ሰዎች መጥተው የይሖዋን ታቦት በኮረብታው ላይ ወደሚገኘው ወደ አቢናዳብ ቤት ወሰዱት፤ የይሖዋን ታቦት እንዲጠብቅም ልጁን አልዓዛርን ቀደሱት።
ታቦቱም ወደ ቂርያትየአሪም ከመጣ ረጅም ጊዜ ይኸውም በአጠቃላይ 20 ዓመት አለፈው፤ የእስራኤልም ቤት ሁሉ ይሖዋን መፈለግ ጀመረ።
ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ “በሙሉ ልባችሁ ወደ ይሖዋ የምትመለሱ ከሆነ ባዕዳን አማልክትንና የአስታሮትን ምስሎች ከመካከላችሁ አስወግዱ፤ ልባችሁንም ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ስጡ፤ እሱን ብቻ አገልግሉ፤ እሱም ከፍልስጤማውያን እጅ ይታደጋችኋል” አላቸው።
በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን የባአልንና የአስታሮትን ምስሎች አስወግደው ይሖዋን ብቻ አገለገሉ።
ከዚያም ሳሙኤል “እስራኤልን ሁሉ በምጽጳ ሰብስቡ፤ እኔም ስለ እናንተ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ” አለ።
እነሱም በምጽጳ ተሰበሰቡ፤ ከዚያም ውኃ ቀድተው በይሖዋ ፊት አፈሰሱ፤ ያን ዕለትም ሲጾሙ ዋሉ። በዚያም “በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሠርተናል” አሉ። ሳሙኤልም በምጽጳ በእስራኤላውያን ላይ ፈራጅ ሆኖ ማገልገል ጀመረ።
ፍልስጤማውያንም እስራኤላውያን በምጽጳ አንድ ላይ መሰብሰባቸውን በሰሙ ጊዜ የፍልስጤም ገዢዎች እስራኤልን ለመውጋት ወጡ። እስራኤላውያንም ይህን ሲሰሙ ፍልስጤማውያንን ፈሩ።
ስለሆነም እስራኤላውያን ሳሙኤልን “አምላካችን ይሖዋ እንዲረዳንና ከፍልስጤማውያን እጅ እንዲያድነን ወደ እሱ መጮኽህን አታቁም” አሉት።
ከዚያም ሳሙኤል አንድ የሚጠባ ግልገል ወስዶ ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባ አድርጎ አቀረበው፤ ሳሙኤልም ይሖዋ እስራኤላውያንን እንዲረዳቸው ተማጸነ፤ ይሖዋም መለሰለት።
ሳሙኤል የሚቃጠለውን መባ እያቀረበ ሳለ ፍልስጤማውያን እስራኤላውያንን ለመውጋት ቀረቡ። ይሖዋም በዚያን ዕለት በፍልስጤማውያን ላይ ኃይለኛ የነጎድጓድ ድምፅ ለቀቀባቸው፤ ግራ እንዲጋቡም አደረጋቸው፤ እነሱም በእስራኤላውያን ፊት ድል ተመቱ።
በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሰዎች ከምጽጳ ወጥተው ፍልስጤማውያንን ማሳደዳቸውን ተያያዙት፤ ከቤትካር በስተ ደቡብ እስከሚገኘው አካባቢም ድረስ መቷቸው።
ከዚያም ሳሙኤል አንድ ድንጋይ ወስዶ በምጽጳ እና በየሻና መካከል አስቀመጠው፤ ስሙንም ኤቤንዔዘር አለው፤ ይህን ያለው “ይሖዋ እስካሁን ድረስ ረድቶናል” ሲል ነው።
በዚህ ሁኔታ ፍልስጤማውያን ድል ተመቱ፤ ዳግመኛም ወደ እስራኤላውያን ክልል መጥተው አያውቁም፤ በሳሙኤል ዘመን ሁሉ የይሖዋ እጅ በፍልስጤማውያን ላይ ነበር።
በተጨማሪም ፍልስጤማውያን ከእስራኤላውያን ላይ የወሰዷቸው ከኤቅሮን እስከ ጌት ያሉት ከተሞች ለእስራኤላውያን ተመለሱላቸው፤ እንዲሁም እስራኤላውያን በእነዚህ ከተሞች ሥር ያሉትን ክልሎች ከፍልስጤማውያን እጅ አስለቀቁ። በእስራኤላውያንና በአሞራውያን መካከልም ሰላም ወረደ።
ሳሙኤልም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለእስራኤላውያን ፈራጅ ሆኖ አገለገለ።
በየዓመቱም በቤቴል፣ በጊልጋል እና በምጽጳ በመዘዋወር በእነዚህ አካባቢዎች ሁሉ ለሚገኙ እስራኤላውያን ፈራጅ ሆኖ አገለገለ።
ሆኖም ቤቱ የሚገኘው በራማ ስለነበር ወደዚያ ይመለስ ነበር፤ በዚያም ለእስራኤላውያን ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። በዚያም ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ።
ከጊዜ በኋላም ሳሙኤል ሞተ፤ እስራኤላውያንም በሙሉ ሊያለቅሱለትና በራማ በሚገኘው ቤቱ ሊቀብሩት ተሰበሰቡ። ከዚያም ዳዊት ተነስቶ ወደ ፋራን ምድረ በዳ ወረደ።
በማኦን የሚኖር እጅግ ባለጸጋ የሆነ አንድ ሰው ነበር። ይህ ሰው የሚሠራው በቀርሜሎስ ሲሆን 3,000 በጎችና 1,000 ፍየሎች ነበሩት፤ በዚያን ወቅት በቀርሜሎስ በጎቹን እየሸለተ ነበር።
የሰውየው ስም ናባል፣ የሚስቱ ስም ደግሞ አቢጋኤል ነበር። እሷም በጣም አስተዋይና ውብ ሴት ነበረች፤ ከካሌብ ወገን የሆነው ባሏ ግን ኃይለኛና ምግባረ ብልሹ ሰው ነበር።
ዳዊት በምድረ በዳ ሳለ ናባል በጎቹን እየሸለተ መሆኑን ሰማ።
ስለዚህ ዳዊት አሥር ወጣቶችን ወደ እሱ ላከ፤ ዳዊትም ወጣቶቹን እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ቀርሜሎስ ወጥታችሁ ናባልን ስታገኙት በስሜ ስለ ደህንነቱ ጠይቁት።
ከዚያም ናባልን እንዲህ በሉት፦ ‘ረጅም ዕድሜና ጤና እመኝልሃለሁ፤ ለመላ ቤተሰብህና የአንተ ለሆነው ሁሉ ሰላም ይሁን።
በጎችህን እየሸለትክ እንዳለህ ሰምቻለሁ። እረኞችህም ከእኛ ጋር በነበሩበት ጊዜ ምንም ዓይነት ጉዳት አላደረስንባቸውም፤ በቀርሜሎስ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ ምንም ነገር አልጠፋባቸውም።
ወጣቶችህን ጠይቅ፤ ይነግሩሃል። እንግዲህ የመጣነው በደስታ ቀን ስለሆነ ወጣቶቼ በፊትህ ሞገስ ያግኙ። እባክህ ለአገልጋዮችህና ለልጅህ ለዳዊት የቻልከውን ያህል ስጥ።’”
በመሆኑም ዳዊት የላካቸው ወጣቶች ሄደው ይህን ሁሉ በዳዊት ስም ለናባል ነገሩት። ተናግረው እንዳበቁም
ናባል የዳዊትን አገልጋዮች እንዲህ አላቸው፦ “ለመሆኑ ዳዊት ማን ነው? ደግሞስ የእሴይ ልጅ ማን ነው? በአሁኑ ጊዜ እንደሆነ ከጌቶቻቸው የሚኮበልሉ አገልጋዮች ብዙ ናቸው።
ታዲያ ዳቦዬን፣ ውኃዬንና ለሚሸልቱልኝ ሰዎች ያረድኩትን ሥጋ ከየት እንደመጡ እንኳ ለማላውቃቸው ሰዎች መስጠት ይኖርብኛል?”
ዳዊት የላካቸው ወጣቶችም ወደመጡበት ተመልሰው በመሄድ የተባሉትን ሁሉ ነገሩት።
ዳዊትም ወዲያውኑ አብረውት ላሉት ሰዎች “በሉ ሁላችሁም ሰይፋችሁን ታጠቁ!” አላቸው። በመሆኑም ሁሉም ሰይፋቸውን ታጠቁ፤ ዳዊትም ሰይፉን ታጠቀ፤ ወደ 400 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ከዳዊት ጋር ሲወጡ 200ዎቹ ግን ጓዙን ለመጠበቅ እዚያው ቀሩ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአገልጋዮቹ አንዱ ለናባል ሚስት ለአቢጋኤል እንዲህ አላት፦ “እነሆ፣ ዳዊት ለጌታችን መልካም ምኞቱን ለመግለጽ መልእክተኞችን ከምድረ በዳ ልኮ ነበር፤ እሱ ግን የስድብ ናዳ አወረደባቸው።
ሰዎቹ ለእኛ እጅግ ጥሩ ነበሩ። ምንም ዓይነት ጉዳት አድርሰውብን አያውቁም፤ በመስክ ከእነሱ ጋር አብረን በነበርንባቸው ጊዜያት ሁሉ አንድም ነገር ጠፍቶብን አያውቅም።
መንጋውን እየጠበቅን ከእነሱ ጋር በቆየንባቸው ጊዜያት ሁሉ ሌሊትም ሆነ ቀን በዙሪያችን እንደ መከላከያ ቅጥር ሆነውልን ነበር።
እንግዲህ አሁን በጌታችንና በቤቱ ሁሉ ላይ ጥፋት መምጣቱ ስለማይቀር ምን ማድረግ እንዳለብሽ ወስኚ፤ እሱ እንደሆነ የማይረባ ሰው ስለሆነ ማንም ሊያናግረው አይችልም።”
ስለሆነም አቢጋኤል ወዲያውኑ 200 ዳቦ፣ ሁለት እንስራ የወይን ጠጅ፣ ታርደው የተሰናዱ አምስት በጎች፣ አምስት የሲህ መስፈሪያ ቆሎ፣ 100 የዘቢብ ቂጣ እንዲሁም 200 የበለስ ጥፍጥፍ ወስዳ ሁሉንም በአህዮች ላይ ጫነች።
ከዚያም አገልጋዮቿን “ቀድማችሁኝ ሂዱ፤ እኔም እከተላችኋለሁ” አለቻቸው። ለባሏ ለናባል ግን ምንም አልነገረችውም።
አቢጋኤልም አህያ ላይ እንደተቀመጠች በተራራው ተከልላ እየወረደች ሳለ ዳዊትና ሰዎቹም ወደ እሷ እየወረዱ ነበር፤ እሷም አገኘቻቸው።