text
stringlengths
4
267
ዳዊትም እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በምድረ በዳ የዚህን ሰው ንብረት የጠበቅኩለት ለካስ እንዲያው በከንቱ ነበር። ደግሞም ከንብረቱ መካከል አንድም ነገር አልጠፋበትም፤ እሱ ግን ደግ በሠራሁለት ክፉ መለሰልኝ።
የእሱ ከሆኑት ወንዶች መካከል እስከ ነገ ጠዋት ድረስ አንድ ሰው እንኳ ባስቀር አምላክ በዳዊት ጠላቶች ላይ ይህን ያድርግ፤ ከዚህ የከፋም ነገር ያምጣ።”
አቢጋኤልም ዳዊትን ባየችው ጊዜ፣ ከተቀመጠችበት አህያ ላይ በፍጥነት በመውረድ በዳዊት ፊት በግንባሯ ተደፍታ ሰገደች።
ከዚያም እግሩ ላይ ወድቃ እንዲህ አለችው፦ “ጌታዬ ሆይ፣ ጥፋቱ በእኔ ላይ ይሁን፤ እባክህ አገልጋይህ እንድታናግርህ ፍቀድላት፤ የአገልጋይህንም ቃል ስማ።
እባክህ ጌታዬ፣ ናባል የተባለውን ይህን የማይረባ ሰው ከቁብ አትቁጠረው፤ እሱ ልክ እንደ ስሙ ነውና። ስሙ ናባል ነው፤ ደግሞም ማስተዋል የጎደለው ሰው ነው። እኔ አገልጋይህ ግን ጌታዬ የላካቸውን ወጣቶች አላየሁም።
እናም አሁን ጌታዬ፣ ሕያው በሆነው በይሖዋና በሕያውነትህ እምላለሁ፣ በደም ዕዳ ተጠያቂ ከመሆንና በራስህ እጅ ከመበቀል የጠበቀህ ይሖዋ ነው። አሁንም ጠላቶችህና ጌታዬን ሊጎዱ የሚፈልጉ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ።
ስለዚህ አገልጋይህ ለጌታዬ ያመጣችው ይህ ስጦታ ጌታዬን ለሚከተሉት ወጣቶች ይሰጥ።
ጌታዬ እየተዋጋ ያለው የይሖዋን ጦርነት ስለሆነ ይሖዋ የጌታዬን ቤት ለዘለቄታው ያጸናለታል፤ ስለሆነም እባክህ የአገልጋይህን መተላለፍ ይቅር በል፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህ።
ማንም ሰው አንተን ለማሳደድ ቢነሳና ሕይወትህን ለማጥፋት ቢፈልግ የጌታዬ ሕይወት በአምላክህ በይሖዋ ዘንድ በደንብ በታሰረ የሕይወት ከረጢት ውስጥ ትቀመጣለች፤ የጠላቶችህን ሕይወት ግን ከወንጭፍ እንደሚወረወር ድንጋይ ይወነጭፈዋል።
ይሖዋ ቃል የገባለትን መልካም ነገር ሁሉ ለጌታዬ በሚፈጽምለትና በእስራኤል ላይ መሪ አድርጎ በሚሾመው ጊዜ
ጌታዬ ያለምክንያት ደም በማፍሰሱና እጁን ለበቀል በማንሳቱ ልቡን የሚቆጨው ወይም የሚጸጽተው ነገር አይኖርም። ይሖዋ ለጌታዬ መልካም ነገር በሚያደርግለት ጊዜ አገልጋይህን አስባት።”
በዚህ ጊዜ ዳዊት አቢጋኤልን እንዲህ አላት፦ “ዛሬ እኔን እንድታገኚኝ የላከሽ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ይወደስ!
ማስተዋልሽም የተባረከ ይሁን! በዚህ ዕለት በራሴ ላይ የደም ዕዳ እንዳላመጣና በገዛ እጄ እንዳልበቀል ስለጠበቅሽኝ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ።
በአንቺ ላይ ጉዳት ከማድረስ በጠበቀኝ ሕያው በሆነው በእስራኤል አምላክ በይሖዋ እምላለሁ፣ እኔን ለማግኘት ፈጥነሽ ባትመጪ ኖሮ እስከ ነገ ጠዋት ድረስ የናባል የሆነ አንድም ወንድ ባልተረፈ ነበር።”
ከዚያም ዳዊት ያመጣችለትን ነገር ከእጇ ተቀብሎ “ወደ ቤትሽ በሰላም ሂጂ። ይኸው ቃልሽን ሰምቻለሁ፤ የጠየቅሽኝንም እፈጽምልሻለሁ” አላት።
በኋላም አቢጋኤል በቤቱ እንደ ንጉሥ ግብዣ ያለ ታላቅ ግብዣ አዘጋጅቶ ወደነበረው ወደ ናባል ተመለሰች፤ ናባልም ልቡ በሐሴት ተሞልቶ በጣም ሰክሮ ነበር። እሷም እስኪነጋ ድረስ ምንም ነገር አልነገረችውም።
ጠዋት ላይ ናባል ስካሩ ሲበርድለት ሚስቱ የሆነውን ሁሉ ነገረችው። ልቡም እንደ ሞተ ሰው ልብ ሆነ፤ ሰውነቱም እንደ ድንጋይ በድን ሆነ።
ከአሥር ቀን ገደማ በኋላም ይሖዋ ናባልን ስለቀሰፈው ሞተ።
ዳዊት፣ ናባል መሞቱን ሲሰማ እንዲህ አለ፦ “ከናባል የደረሰብኝን ነቀፋ የተሟገተልኝና አገልጋዩን መጥፎ ድርጊት ከመፈጸም የጠበቀው ይሖዋ ይወደስ፤ ይሖዋ የናባልን ክፋት በራሱ ላይ መለሰው!” ከዚያም ዳዊት አቢጋኤል ሚስት እንድትሆነው ጥያቄ ለማቅረብ መልእክት ላከ።
በመሆኑም የዳዊት አገልጋዮች በቀርሜሎስ ወዳለችው ወደ አቢጋኤል መጥተው “ዳዊት ሊያገባሽ ስለፈለገ ወደ አንቺ ልኮናል” አሏት።
እሷም ወዲያውኑ ተነሳች፤ በግንባሯም ተደፍታ በመስገድ “ባሪያህ እንደ አገልጋይ በመሆን የጌታዬን አገልጋዮች እግር ለማጠብ ዝግጁ ነች” አለች።
ከዚያም አቢጋኤል ፈጥና ተነሳች፤ አምስት ሴት አገልጋዮቿንም በማስከተል በአህያ ላይ ተቀምጣ ጉዞ ጀመረች፤ ከዳዊት መልእክተኞችም ጋር አብራ ሄደች፤ የዳዊትም ሚስት ሆነች።
በተጨማሪም ዳዊት ከኢይዝራኤል አኪኖዓምን አግብቶ ነበር፤ ሁለቱም ሴቶች ሚስቶቹ ሆኑ።
ሳኦል ግን የዳዊት ሚስት የነበረችውን ልጁን ሜልኮልን የጋሊም ሰው ለሆነው ለላይሽ ልጅ ለፓልጢ ድሯት ነበር።
ሳኦል በነገሠ ጊዜ ዕድሜው . . . ነበር፤ እሱም በእስራኤል ላይ ሁለት ዓመት ገዛ።
ሳኦል ከእስራኤላውያን መካከል 3,000 ሰዎችን መረጠ፤ ከእነዚህም መካከል 2,000ዎቹ በሚክማሽና በቤቴል ተራራማ አካባቢ ከሳኦል ጋር ሆኑ፤ ሌሎቹ 1,000 ሰዎች ደግሞ በቢንያም ግዛት በጊብዓ ከዮናታን ጋር ሆኑ። የቀሩትን ሰዎች እያንዳንዳቸውን ወደየድንኳናቸው አሰናበታቸው።
ዮናታንም በጌባ የነበረውን የፍልስጤማውያንን የጦር ሰፈር መታ፤ ፍልስጤማውያንም ይህን ሰሙ። ሳኦልም “ዕብራውያን ይስሙ!” በማለት በምድሩ ሁሉ ቀንደ መለከት አስነፋ።
እስራኤላውያን በሙሉ “ሳኦል የፍልስጤማውያንን የጦር ሰፈር መታ፤ እስራኤላውያንም በፍልስጤማውያን ዘንድ እንደ ግም ተቆጠሩ” ሲባል ሰሙ። በመሆኑም ሕዝቡ ሳኦልን ለመከተል በጊልጋል ተሰበሰበ።
ፍልስጤማውያንም 30,000 የጦር ሠረገሎች፣ 6,000 ፈረሰኞችና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ እጅግ ብዙ የሆነ ሠራዊት ይዘው ከእስራኤላውያን ጋር ለመዋጋት ተሰባሰቡ፤ እነሱም ወጥተው ከቤትአዌን በስተ ምሥራቅ በሚክማሽ ሰፈሩ።
የእስራኤል ሰዎችም አደጋ እንደተጋረጠባቸው ስላዩ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገብተው ነበር፤ በመሆኑም ሕዝቡ በየዋሻው፣ በየጉድጓዱ፣ በየዓለቱ፣ በየጎሬውና በየውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓዱ ውስጥ ተደበቀ።
እንዲያውም አንዳንድ ዕብራውያን ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ጊልያድ ምድር ሄዱ። ሳኦል ግን እዚያው ጊልጋል ነበር፤ የተከተሉት ሰዎችም ሁሉ በፍርሃት ይንቀጠቀጡ ነበር።
እሱም ሳሙኤል የቀጠረው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ለሰባት ቀን ጠበቀ፤ ሳሙኤል ግን ወደ ጊልጋል አልመጣም፤ ሕዝቡም ሳኦልን ትቶ መበታተን ጀመረ።
በመጨረሻም ሳኦል “የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕቶቹን አምጡልኝ” አለ። ከዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ።
ሆኖም ሳኦል የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርቦ እንደጨረሰ ሳሙኤል መጣ። በመሆኑም ሳኦል ሊቀበለውና ሊባርከው ወጣ።
ከዚያም ሳሙኤል “ያደረግከው ነገር ምንድን ነው?” አለው። ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ሕዝቡ ትቶኝ መበታተን እንደጀመረና አንተም በተቀጠረው ጊዜ እንዳልመጣህ እንዲሁም ፍልስጤማውያኑ በሚክማሽ እየተሰባሰቡ መሆናቸውን አየሁ።
በመሆኑም ‘እንግዲህ ፍልስጤማውያን ወደ ጊልጋል ወርደው ሊወጉኝ ነው፤ እኔ ደግሞ ይሖዋ ሞገስ እንዲያሳየኝ አለመንኩም’ ብዬ አሰብኩ። ስለሆነም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ማቅረብ ግድ ሆነብኝ።”
በዚህ ጊዜ ሳሙኤል ሳኦልን እንዲህ አለው፦ “የፈጸምከው የሞኝነት ድርጊት ነው። አምላክህ ይሖዋ የሰጠህን ትእዛዝ አልጠበቅክም። ጠብቀህ ቢሆን ኖሮ ይሖዋ መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም ባጸናልህ ነበር።
አሁን ግን መንግሥትህ አይዘልቅም። ይሖዋ እንደ ልቡ የሚሆንለት ሰው ያገኛል፤ ይሖዋም በሕዝቡ ላይ መሪ አድርጎ ይሾመዋል፤ ምክንያቱም አንተ የይሖዋን ትእዛዝ አልጠበቅክም።”
ከዚያም ሳሙኤል ተነስቶ ከጊልጋል በቢንያም ግዛት ወደምትገኘው ወደ ጊብዓ ወጣ፤ ሳኦልም ሕዝቡን ቆጠረ፤ አብረውት ያሉት ሰዎች ብዛታቸው 600 ገደማ ነበር።
ሳኦልና ልጁ ዮናታን እንዲሁም አብረዋቸው የቀሩት ሰዎች በቢንያም ግዛት በምትገኘው በጌባ ሰፍረው የነበረ ሲሆን ፍልስጤማውያን ደግሞ በሚክማሽ ሰፍረው ነበር።
በሦስት ምድብ የተከፈለው የወራሪዎች ቡድን ከፍልስጤማውያን ሰፈር ይወጣል። አንደኛው ቡድን ወደ ሹአል ምድር ወደ ኦፍራ ወደሚወስደው መንገድ ያቀናል፤
ሌላኛው ቡድን ወደ ቤትሆሮን ወደሚወስደው መንገድ ይሄዳል፤ ሦስተኛው ቡድን ደግሞ የጸቦይምን ሸለቆ ቁልቁል ወደሚያሳየው ወሰን ይኸውም ወደ ምድረ በዳው ወደሚወስደው መንገድ ያቀናል።
በመላው የእስራኤል ምድር አንድም ብረት ቀጥቃጭ አልነበረም፤ ምክንያቱም ፍልስጤማውያን “ዕብራውያን ሰይፍ ወይም ጦር እንዳይሠሩ” ብለው ነበር።
ስለዚህ እስራኤላውያን በሙሉ ማረሻቸውን ወይም ዶማቸውን አሊያም መጥረቢያቸውን ወይም ማጭዳቸውን ለማሳል ወደ ፍልስጤማውያን ይወርዱ ነበር።
ማረሻ፣ ዶማ፣ መንሽና መጥረቢያ ለማሳል እንዲሁም የበሬ መውጊያ ለማሳሰር ዋጋው አንድ ፊም ነበር።
ውጊያው በተደረገበት ቀን ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ባሉት ሰዎች እጅ አንድም ሰይፍ ወይም ጦር አልተገኘም፤ መሣሪያ የነበራቸው ሳኦልና ልጁ ዮናታን ብቻ ነበሩ።
በዚህ ጊዜ አንደኛው የፍልስጤማውያን ጦር በሚክማሽ ወደሚገኝ ጠባብ ሸለቆ ወጥቶ ነበር።
በኋላም ዳዊት ካህኑ አሂሜሌክ ወደሚገኝበት ወደ ኖብ መጣ። አሂሜሌክም ዳዊትን ሲያገኘው ተንቀጠቀጠ፤ እሱም “ምነው ብቻህን? ሰው አብሮህ የለም?” አለው።
ዳዊትም ለካህኑ ለአሂሜሌክ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ንጉሡ አንድ ጉዳይ እንዳስፈጽም አዞኝ ነበር፤ ሆኖም ‘ስለሰጠሁህ ተልእኮና ስላዘዝኩህ ነገር ማንም ሰው ምንም ነገር እንዳያውቅ’ ብሎኛል። ከሰዎቼም ጋር የሆነ ቦታ ላይ ለመገናኘት ተቀጣጥረናል።
ስለዚህ አሁን እጅህ ላይ አምስት ዳቦ ካለ ወይም የተገኘውን ማንኛውንም ነገር ስጠኝ።”
ካህኑ ግን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ማንኛውም ሰው የሚበላው ዓይነት ዳቦ የለኝም፤ ሰሞኑን ሰዎቹ ራሳቸውን ከሴት ጠብቀው ከሆነ ግን የተቀደሰው ኅብስት አለ።”
ስለዚህ ዳዊት ካህኑን እንዲህ አለው፦ “ከዚህ በፊት ለውጊያ እንደወጣሁባቸው ጊዜያት ሁሉ አሁንም ፈጽሞ ሴቶች ወደ እኛ አልቀረቡም። ተራ በሆነ ተልእኮም እንኳ የሰዎቹ አካል ቅዱስ ከነበረ ታዲያ ዛሬማ እንዴት ይበልጥ ቅዱስ አይሆን!”
በመሆኑም ካህኑ የተቀደሰውን ኅብስት ሰጠው፤ ምክንያቱም ትኩስ ኅብስት በሚተካበት ቀን ከይሖዋ ፊት ከተነሳው ገጸ ኅብስት በስተቀር ሌላ ዳቦ አልነበረም።
ከሳኦል አገልጋዮች አንዱ በይሖዋ ፊት እንዲቆይ በመገደዱ ያን ቀን እዚያ ነበር። ዶይቅ የተባለው ይህ ኤዶማዊ የሳኦል እረኞች አለቃ ነበር።
ከዚያም ዳዊት አሂሜሌክን “ንጉሡ የሰጠኝ ተልእኮ አስቸኳይ ስለነበር ሰይፌንም ሆነ የጦር መሣሪያዎቼን አልያዝኩም፤ እዚህ አንተ ጋ ጦር ወይም ሰይፍ ይኖራል?” አለው።
ካህኑም “በኤላህ ሸለቆ አንተ የገደልከው የፍልስጤማዊው የጎልያድ ሰይፍ አለ፤ ያውልህ ከኤፉዱ ኋላ በጨርቅ ተጠቅልሎ ተቀምጧል። ከእሱ ሌላ እዚህ ምንም ስለሌለ ከፈለግክ እሱን ውሰደው” አለው። ዳዊትም “ከእሱ የተሻለማ የትም አይገኝም። እሱኑ ስጠኝ” አለው።
በዚያም ቀን ዳዊት ተነስቶ ከሳኦል ሸሸ፤ ከጊዜ በኋላም ወደ ጌት ንጉሥ ወደ አንኩስ መጣ።
የአንኩስ አገልጋዮችም እንዲህ አሉት፦ “ይህ የምድሪቱ ንጉሥ፣ ዳዊት አይደለም?‘ሳኦል ሺዎችን ገደለ፤ዳዊት ደግሞ አሥር ሺዎችን ገደለ’ በማለት እየዘፈኑ የጨፈሩለትስ ለዚህ ሰው አይደለም?”
ዳዊትም ይህን ቃል በቁም ነገር ተመለከተው፤ የጌትን ንጉሥ አንኩስንም እጅግ ፈራው።
በመሆኑም በፊታቸው አእምሮውን እንደሳተ ሰው ሆነ፤ በመካከላቸውም እንደአበደ ሰው አደረገው። የከተማዋን በሮች ይቦጫጭር እንዲሁም ለሃጩን በጢሙ ላይ ያዝረበርብ ጀመር።
አንኩስም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፦ “እስቲ ተመልከቱ፣ ሰውየው እኮ እብድ ነው! ታዲያ ወደ እኔ ያመጣችሁት ለምንድን ነው?
ይህን ሰው ፊቴ እንዲህ እንዲያብድ ያመጣችሁት እኔ እብድ አጥቼ ነው? ይህስ ሰው ቤቴ መግባት ይገባዋል?”
ይህ በእንዲህ እንዳለ ብላቴናው ሳሙኤል በኤሊ ፊት ይሖዋን ያገለግል ነበር፤ ይሁን እንጂ በዚያ ዘመን ከይሖዋ የሚመጣ ቃል ብርቅ ነበር፤ ራእይ ማየትም ቢሆን ብዙ የተለመደ አልነበረም።
አንድ ቀን ኤሊ የተለመደው ቦታው ላይ ተኝቶ ነበር፤ ዓይኖቹ ስለደከሙ ማየት ተስኖታል።
የአምላክም መብራት ገና አልጠፋም፤ ሳሙኤልም የአምላክ ታቦት ባለበት የይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ ተኝቶ ነበር።
ከዚያም ይሖዋ ሳሙኤልን ጠራው። እሱም “አቤት” አለ።
ወደ ኤሊም እየሮጠ ሄዶ “አቤት፣ ጠራኸኝ?” አለው። እሱ ግን “አይ፣ አልጠራሁህም። ተመልሰህ ተኛ” አለው። በመሆኑም ሄዶ ተኛ።
ይሖዋም እንደገና “ሳሙኤል!” ሲል ጠራው። በዚህ ጊዜ ሳሙኤል ተነስቶ ወደ ኤሊ በመሄድ “አቤት፣ ጠራኸኝ?” አለው። እሱ ግን “ኧረ አልጠራሁህም ልጄ። ተመልሰህ ተኛ” አለው።
(ሳሙኤል ይሖዋን ገና አላወቀውም ነበር፤ የይሖዋም ቃል ቢሆን ገና አልተገለጠለትም ነበር።)
በመሆኑም ይሖዋ ለሦስተኛ ጊዜ እንደገና “ሳሙኤል!” ሲል ጠራው። እሱም ተነስቶ ወደ ኤሊ በመሄድ “አቤት፣ ጠራኸኝ?” አለው። ኤሊም ብላቴናውን እየጠራው ያለው ይሖዋ መሆኑን አስተዋለ።
በመሆኑም ኤሊ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “ሂድና ተኛ፤ እንደገና ከጠራህ ‘ይሖዋ ሆይ፣ አገልጋይህ እየሰማ ስለሆነ ተናገር’ በል።” ሳሙኤልም ወደ ስፍራው ተመልሶ ተኛ።
ይሖዋም መጥቶ በዚያ ቆመ፤ እንደ ሌላው ጊዜም “ሳሙኤል፣ ሳሙኤል!” ሲል ጠራው። ሳሙኤልም “አገልጋይህ እየሰማ ስለሆነ ተናገር” አለ።
ይሖዋ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “ለሰሚው ሁሉ ጆሮ የሚሰቀጥጥ ነገር በእስራኤል ውስጥ አደርጋለሁ።
በዚያ ቀን ስለ ኤሊ ቤት የተናገርኩትን ነገር ሁሉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በእሱ ላይ እፈጽማለሁ።
እሱ በሚያውቀው ጥፋት የተነሳ በቤቱ ላይ ለዘለቄታው እንደምፈርድ ንገረው፤ ምክንያቱም ልጆቹ አምላክን ረግመዋል፤ እሱ ግን አልገሠጻቸውም።
በዚህም የተነሳ የኤሊ ቤት የፈጸመው ጥፋት መሥዋዕት ወይም መባ በማቅረብ ፈጽሞ እንደማይሰረይ ለኤሊ ቤት ምያለሁ።”
ሳሙኤልም እስከ ንጋት ድረስ ተኛ፤ ከዚያም የይሖዋን ቤት በሮች ከፈተ። ሳሙኤል ራእዩን ለኤሊ መንገር ፈርቶ ነበር።
ኤሊ ግን ሳሙኤልን ጠርቶ “ልጄ፣ ሳሙኤል!” አለው። እሱም “አቤት” አለው።
ኤሊም እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ “ለመሆኑ የነገረህ መልእክት ምንድን ነው? እባክህ አትደብቀኝ። እሱ ከነገረህ ነገር ውስጥ አንዲት ቃል እንኳ ብትደብቀኝ አምላክ እንዲህ ያድርግብህ፤ ከዚያም የከፋ ነገር ያምጣብህ።”
በመሆኑም ሳሙኤል እሱ የነገረውን በሙሉ ምንም ሳይደብቅ ነገረው። ኤሊም “ይህ ከይሖዋ ነው። እሱ መልካም መስሎ የታየውን ያድርግ” አለ።
ሳሙኤል እያደገ ሄደ፤ ይሖዋም ከእሱ ጋር ነበር፤ የሚናገረውም ቃል ሁሉ እንዲፈጸም ያደርግ ነበር።
ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያሉ እስራኤላውያን በሙሉ ሳሙኤል ተቀባይነት ያገኘ የይሖዋ ነቢይ እንደሆነ ተገነዘቡ።
ይሖዋም በሴሎ ይገለጥ ነበር፤ ምክንያቱም ይሖዋ በሴሎ በይሖዋ ቃል አማካኝነት ራሱን ለሳሙኤል ገልጦለት ነበር።
በሦስተኛው ቀን ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ጺቅላግ ሲመጡ አማሌቃውያን በስተ ደቡብ ያለውን አካባቢና ጺቅላግን ወረው ነበር፤ እነሱም በጺቅላግ ላይ ጥቃት ሰነዘሩ፤ በእሳትም አቃጠሏት።
ሴቶችንና በዚያ የነበሩትንም ሁሉ ትንሽ ትልቅ ሳይሉ ማርከው ወሰዱ። አንድም ሰው አልገደሉም፤ ከዚህ ይልቅ ሁሉንም ይዘው ሄዱ።
ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ጺቅላግ ሲመጡ ከተማዋ በእሳት ተቃጥላ አገኟት፤ ሚስቶቻቸውም ሆኑ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው በምርኮ ተወስደው ነበር።
በመሆኑም ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ለማልቀስ አቅም እስኪያጡ ድረስ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ።
ሁለቱ የዳዊት ሚስቶችም ማለትም ኢይዝራኤላዊቷ አኪኖዓም እና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቢጋኤል በምርኮ ተወስደው ነበር።
ዳዊት ሰዎቹ ሊወግሩት እየተማከሩ ስለነበር እጅግ ተጨነቀ፤ ምክንያቱም ሰዎቹ ሁሉ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው በመወሰዳቸው ተመርረው ነበር። ይሁንና ዳዊት በአምላኩ በይሖዋ ራሱን አበረታ።
ከዚያም ዳዊት የአሂሜሌክን ልጅ ካህኑን አብያታርን “እባክህ፣ ኤፉዱን አምጣልኝ” አለው። አብያታርም ኤፉዱን ለዳዊት አመጣለት።
ዳዊትም “ይህን ወራሪ ቡድን ላሳደው? እደርስበት ይሆን?” ሲል ይሖዋን ጠየቀ። እሱም “በእርግጥ ስለምትደርስባቸውና የወሰዱትን ሁሉ ከእጃቸው ስለምታስጥል ሂድ አሳዳቸው” አለው።
ዳዊትም ወዲያውኑ አብረውት ከነበሩት 600 ሰዎች ጋር ወጣ፤ እነሱም እስከ በሶር ሸለቆ ድረስ ሄዱ፤ በዚያም የተወሰኑ ሰዎች ወደ ኋላ ቀሩ።
ዳዊትም ከ400 ሰዎች ጋር ሆኖ ማሳደዱን ቀጠለ፤ በጣም ከመድከማቸው የተነሳ የበሶርን ሸለቆ መሻገር ያልቻሉት 200 ሰዎች ግን እዚያው ቀሩ።
ከዚያም ሜዳ ላይ አንድ ግብፃዊ አግኝተው ወደ ዳዊት አመጡት። የሚበላው ምግብና የሚጠጣው ውኃ ሰጡት።
በተጨማሪም ቁራሽ የበለስ ጥፍጥፍና ሁለት የዘቢብ ቂጣ ሰጡት። እሱም ከበላ በኋላ ብርታት አገኘ፤ ምክንያቱም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ሙሉ እህልም ሆነ ውኃ አልቀመሰም ነበር።
ዳዊትም “ለመሆኑ አንተ የማን ነህ? የመጣኸውስ ከየት ነው?” አለው፤ እሱም መልሶ እንዲህ አለው፦ “እኔ ለአንድ አማሌቃዊ ባሪያ የሆንኩ ግብፃዊ ነኝ፤ ሆኖም ከሦስት ቀን በፊት ታምሜ ስለነበር ጌታዬ ጥሎኝ ሄደ።
የከሪታውያንን ምድር ደቡባዊ ክፍል፣ የይሁዳን ግዛትና የካሌብን ደቡባዊ ክፍል ወረርን፤ ጺቅላግንም በእሳት አጋየናት።”
በዚህ ጊዜ ዳዊት “ይህ ወራሪ ቡድን ወዳለበት መርተህ ትወስደኛለህ?” አለው። እሱም “ብቻ እንደማትገድለኝና ለጌታዬ አሳልፈህ እንደማትሰጠኝ በአምላክ ማልልኝ እንጂ ወራሪው ቡድን ወዳለበት መርቼ አደርስሃለሁ” አለው።
በመሆኑም ሰዎቹ ከፍልስጤማውያን ምድርና ከይሁዳ ምድር በወሰዱት ታላቅ ምርኮ የተነሳ በየቦታው ተበታትነው ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ይደሰቱ ወደነበረበት ቦታ መርቶ ወሰደው።
ከዚያም ዳዊት ጎህ ሳይቀድ ጀምሮ እስከ ማግስቱ ምሽት ድረስ መታቸው፤ ፈጽሞም አጠፋቸው፤ በግመል ተቀምጠው ከሸሹት 400 ሰዎች በስተቀር አንድም ሰው አላመለጠም።