text
stringlengths
4
267
ይህ በእንዲህ እንዳለ ብላቴናው ሳሙኤል በይሖዋም ሆነ በሰዎች ፊት በአካል እያደገና ይበልጥ ሞገስ እያገኘ ሄደ።
አንድ የአምላክ ሰው ወደ ኤሊ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የአባትህ ቤት በግብፅ በፈርዖን ቤት በባርነት ያገለግል በነበረበት ጊዜ ራሴን በይፋ ገልጬለት አልነበረም?
ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ፣ መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ መሠዊያዬ እንዲወጣ፣ ዕጣን እንዲያጥንና በፊቴ ኤፉድ እንዲለብስ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል ተመርጦ ነበር፤ እኔም እስራኤላውያን በእሳት የሚያቀርቧቸውን መባዎች በሙሉ ለአባትህ ቤት ሰጠሁ።
ታዲያ እናንተ በማደሪያዬ እንዲቀርብ ያዘዝኩትን መሥዋዕቴንና መባዬን የናቃችሁት ለምንድን ነው? ሕዝቤ እስራኤል ከሚያመጣው ከእያንዳንዱ መባ ላይ ምርጡን ወስዳችሁ ራሳችሁን በማደለብ ከእኔ ይልቅ ልጆችህን ያከበርከው ለምንድን ነው?
“‘ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የይሖዋ ቃል እንዲህ ይላል፦ “የአንተ ቤትና የአባትህ ቤት ምንጊዜም በፊቴ እንደሚሄዱ ተናግሬ ነበር።” አሁን ግን ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ይህ ፈጽሞ የማላስበው ነገር ነው፤ ምክንያቱም የሚያከብሩኝን አከብራለሁ፤ የሚንቁኝ ግን ይናቃሉ።”
በቤትህ እስከ ሽምግልና ድረስ በሕይወት የሚቆይ ሰው እንዳይኖር የአንተንም ሆነ የአባትህን ቤት ብርታት የምቆርጥበት ቀን ይመጣል።
ለእስራኤል በተደረገው ብዙ መልካም ነገር መካከል በማደሪያዬ ውስጥ ተቀናቃኝ ታያለህ፤ በቤትህም ዳግመኛ አረጋዊ የሚባል አይገኝም።
በመሠዊያዬ ፊት እንዲያገለግል የምተወው የአንተ የሆነ ሰው ዓይኖችህ እንዲፈዙና ለሐዘን እንድትዳረግ ያደርጋል፤ ከቤትህ ሰዎች መካከል ግን አብዛኞቹ በሰዎች ሰይፍ ይሞታሉ።
በሁለቱ ልጆችህ በሆፍኒ እና በፊንሃስ ላይ የሚደርሰው ነገር ምልክት ይሆንሃል፦ ሁለቱም በአንድ ቀን ይሞታሉ።
ከዚያም ለራሴ ታማኝ የሆነ ካህን አስነሳለሁ። እሱም ከልቤ ፍላጎት ጋር የሚስማማ ተግባር ይፈጽማል፤ እኔም ዘላቂ የሆነ ቤት እሠራለታለሁ፤ እሱም እኔ በቀባሁት ፊት ሁልጊዜ ይሄዳል።
ከቤትህ የሚተርፍ ሰው ቢኖር የሚከፈለው ገንዘብና ቁራሽ ዳቦ ለማግኘት ሲል መጥቶ ይሰግድለታል፤ ከዚያም “እባክህ፣ ቁራሽ ዳቦ እንዳገኝ በማንኛውም የክህነት ሥራ ላይ መድበኝ” ይላል።’”
ሳሙኤልም የዘይት ዕቃውን አንስቶ ዘይቱን በሳኦል ራስ ላይ አፈሰሰው። ከዚያም ሳመውና እንዲህ አለው፦ “በርስቱ ላይ መሪ እንድትሆን ይሖዋ ቀብቶህ የለም?
ዛሬ ከእኔ ተለይተህ ስትሄድ በቢንያም ግዛት ውስጥ በምትገኘው በጸልጻህ ባለው የራሔል መቃብር አጠገብ ሁለት ሰዎች ታገኛለህ፤ እነሱም እንዲህ ይሉሃል፦ ‘ስትፈልጋቸው የነበሩት አህዮች ተገኝተዋል፤ አባትህ ግን ስለ አህዮቹ ማሰቡን ትቶ ስለ እናንተ እየተጨነቀ ነው። ደግሞም “የልጄን ነገር ምን ባደርግ ይሻላል?” እያለ ነው።’
አንተም ከዚያ ተነስተህ ታቦር የሚገኘው ትልቅ ዛፍ አጠገብ እስክትደርስ ድረስ ጉዞህን ቀጥል፤ እዚያም ሦስት ሰዎች በቤቴል ወደሚገኘው ወደ እውነተኛው አምላክ ሲወጡ ታገኛለህ፤ እነሱም አንደኛው ሦስት የፍየል ግልገል፣ ሌላኛው ሦስት ዳቦ፣ ሌላኛው ደግሞ በእንስራ የወይን ጠጅ ይዘዋል።
እነዚህ ሰዎች ስለ ደህንነትህ ከጠየቁህ በኋላ ሁለት ዳቦ ይሰጡሃል፤ አንተም ዳቦዎቹን ተቀበላቸው።
ከዚህ በኋላ የፍልስጤማውያን የጦር ሰፈር ወዳለበት ወደ እውነተኛው አምላክ ኮረብታ ትመጣለህ። ወደ ከተማዋም በምትደርስበት ጊዜ ትንቢት እየተናገረ ከኮረብታው የሚወርድ አንድ የነቢያት ቡድን ታገኛለህ፤ ከፊት ከፊቱም ባለ አውታር መሣሪያ፣ አታሞ፣ ዋሽንትና በገና የሚጫወቱ ሰዎች ይሄዳሉ።
የይሖዋ መንፈስ ኃይል ይሰጥሃል፤ አንተም ከእነሱ ጋር ትንቢት ትናገራለህ፤ ተለውጠህም እንደ ሌላ ሰው ትሆናለህ።
እነዚህ ምልክቶች ሲፈጸሙ ስታይ ማድረግ የምትችለውን ሁሉ አድርግ፤ ምክንያቱም እውነተኛው አምላክ ከአንተ ጋር ነው።
ከዚያም ከእኔ ቀድመህ ወደ ጊልጋል ውረድ፤ እኔም የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችንና የኅብረት መሥዋዕቶችን ለማቅረብ አንተ ወዳለህበት እወርዳለሁ። እኔ ወደ አንተ እስክመጣ ድረስ ሰባት ቀን መጠበቅ አለብህ። ከዚያም ምን ማድረግ እንዳለብህ አሳውቅሃለሁ።”
ሳኦልም ከሳሙኤል ተለይቶ ለመሄድ ፊቱን ሲያዞር አምላክ የሳኦል ልብ ወደ ሌላ ሰው ልብ እንዲለወጥ አደረገ፤ እነዚህም ሁሉ ምልክቶች በዚያው ቀን ተፈጸሙ።
በመሆኑም ከዚያ ተነስተው ወደ ኮረብታው ሄዱ፤ አንድ የነቢያት ቡድንም አገኘው። ወዲያውም የአምላክ መንፈስ ኃይል ሰጠው፤ እሱም አብሯቸው ትንቢት መናገር ጀመረ።
ቀደም ሲል ያውቁት የነበሩት ሁሉ ከነቢያቱ ጋር ሆኖ ትንቢት ሲናገር ሲያዩት እርስ በርሳቸው “የቂስ ልጅ ምን ሆኗል? ሳኦልም ከነቢያት አንዱ ሆነ እንዴ?” ተባባሉ።
ከዚያም የአካባቢው ነዋሪ የሆነ አንድ ሰው “ለመሆኑ የእነሱስ አባት ማን ነው?” አለ። “ሳኦልም ከነቢያት አንዱ ሆነ እንዴ?” የሚል ምሳሌያዊ አባባል የኖረው በዚህ የተነሳ ነው።
እሱም ትንቢት ተናግሮ ሲጨርስ ወደ ኮረብታው መጣ።
በኋላም የሳኦል አባት ወንድም ሳኦልንና አገልጋዩን “የት ነበራችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ሳኦልም “አህዮቹን ፍለጋ ሄደን ነበር፤ ሆኖም በዚያ ልናገኛቸው ስላልቻልን ወደ ሳሙኤል ሄድን” አለው።
የሳኦልም አጎት “እስቲ ንገረኝ፣ ሳሙኤል ምን አላችሁ?” አለው።
ሳኦልም መልሶ አጎቱን “አህዮቹ መገኘታቸውን በትክክል ነገረን” አለው። ይሁን እንጂ ሳሙኤል ስለ ንግሥና የነገረውን ነገር አልነገረውም።
ከዚያም ሳሙኤል ሕዝቡን በምጽጳ በይሖዋ ፊት እንዲሰበሰብ ከጠራ በኋላ
እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እስራኤልን ከግብፅ ያወጣሁት እንዲሁም ከግብፅ እጅና ይጨቁኗችሁ ከነበሩት መንግሥታት ሁሉ እጅ የታደግኳችሁ እኔ ነኝ።
ዛሬ ግን እናንተ ከመከራችሁና ከጭንቀታችሁ ሁሉ ያዳናችሁን አምላካችሁን አንቀበልም በማለት “አይሆንም፣ ንጉሥ እንዲነግሥልን እንፈልጋለን” አላችሁ። ስለዚህ አሁን በየነገዳችሁና በየሺህ ምድባችሁ ሆናችሁ በይሖዋ ፊት ቁሙ።’”
ስለዚህ ሳሙኤል የእስራኤል ነገዶች በሙሉ እንዲቀርቡ አደረገ፤ ከእነሱም መካከል የቢንያም ነገድ ተመረጠ።
ከዚያም የቢንያም ነገድ በየቤተሰቡ ሆኖ እንዲቀርብ አደረገ፤ የማጥራውያን ቤተሰብም ተመረጠ። በመጨረሻም የቂስ ልጅ ሳኦል ተመረጠ። ሆኖም ፈልገው ሊያገኙት አልቻሉም።
ስለዚህ “ለመሆኑ ሰውየው እዚህ መጥቷል?” በማለት ይሖዋን ጠየቁ። ይሖዋም “ያውላችሁ፣ ጓዙ መካከል ተደብቋል” አላቸው።
በመሆኑም ሮጠው ከዚያ አመጡት። እሱም በሕዝቡ መካከል በቆመ ጊዜ ከትከሻው በላይ ዘለግ ብሎ በቁመት ከሌሎቹ ሰዎች ሁሉ በልጦ ይታይ ነበር።
ሳሙኤልም ሕዝቡን ሁሉ “ይሖዋ የመረጠውን ሰው አያችሁት? ከሕዝቡ ሁሉ መካከል እንደ እሱ ያለ የለም” አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!” በማለት መጮኽ ጀመረ።
ሳሙኤልም ለነገሥታት ምን ሊደረግላቸው እንደሚገባ ለሕዝቡ ተናገረ፤ እንዲሁም በመጽሐፍ ጽፎ በይሖዋ ፊት አስቀመጠው። ከዚያም ሳሙኤል ሕዝቡን ሁሉ ወደየቤቱ አሰናበተ።
ሳኦልም ይሖዋ ልባቸውን ባነሳሳው ተዋጊዎች ታጅቦ በጊብዓ ወዳለው ቤቱ ሄደ።
አንዳንድ የማይረቡ ሰዎች ግን “ይህ ሰው እንዴት ሊያድነን ይችላል?” አሉ። በመሆኑም ናቁት፤ ምንም ዓይነት ስጦታም አላመጡለትም። እሱ ግን ዝም አለ።
ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “ሳኦል በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዲሆን አልፈለግኩም፤ ታዲያ አንተ ለእሱ የምታዝነው እስከ መቼ ነው? በል ቀንድህን ዘይት ሙላና ሂድ። የቤተልሔም ሰው ወደሆነው ወደ እሴይ እልክሃለሁ፤ ምክንያቱም ከወንዶች ልጆቹ መካከል ንጉሥ የሚሆንልኝ ሰው መርጫለሁ።”
ሳሙኤል ግን “እንዴት መሄድ እችላለሁ? ሳኦል ይህን ከሰማ ይገድለኛል” አለ። ይሖዋም እንዲህ አለው፦ “አንዲት ጊደር ይዘህ ሂድ፤ ከዚያም ‘የመጣሁት ለይሖዋ መሥዋዕት ለማቅረብ ነው’ በል።
እሴይንም ወደ መሥዋዕቱ ጥራው፤ እኔም ምን ማድረግ እንዳለብህ አሳውቅሃለሁ። አንተም እኔ የምመርጥልህን ሰው ትቀባልኛለህ።”
ሳሙኤልም ይሖዋ የነገረውን አደረገ። ቤተልሔም እንደደረሰም የከተማዋ ሽማግሌዎች ባገኙት ጊዜ እየተንቀጠቀጡ “የመጣኸው በሰላም ነው?” አሉት።
እሱም “አዎ በሰላም ነው። የመጣሁት ለይሖዋ መሥዋዕት ለማቅረብ ነው። ራሳችሁን ቀድሱ፤ ወደ መሥዋዕቱም አብራችሁኝ ሂዱ” አላቸው። ከዚያም እሴይንና ልጆቹን ቀደሳቸው፤ ወደ መሥዋዕቱ እንዲመጡም ጠራቸው።
እነሱም እዚያ በደረሱ ጊዜ ሳሙኤል ኤልያብን ሲያየው “መቼም ይሖዋ የሚቀባው ሰው ይህ መሆን አለበት” አለ።
ሆኖም ይሖዋ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “እኔ ስላልተቀበልኩት መልኩንና የቁመቱን ርዝማኔ አትይ። አምላክ የሚያየው ሰው በሚያይበት መንገድ አይደለም፤ ምክንያቱም ሰው የሚያየው ውጫዊ ገጽታን ነው፤ ይሖዋ ግን የሚያየው ልብን ነው።”
ከዚያም እሴይ አቢናዳብን ጠርቶ በሳሙኤል ፊት እንዲያልፍ አደረገ፤ እሱ ግን “ይሄኛውንም ይሖዋ አልመረጠውም” አለ።
ቀጥሎም እሴይ ሻማህ እንዲቀርብ አደረገ፤ እሱ ግን “ይሄኛውንም ይሖዋ አልመረጠውም” አለ።
በመሆኑም እሴይ ሰባቱም ወንዶች ልጆቹ በሳሙኤል ፊት እንዲያልፉ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን እሴይን “ይሖዋ ከእነዚህ መካከል ማናቸውንም አልመረጠም” አለው።
በመጨረሻም ሳሙኤል እሴይን “ወንዶች ልጆችህ እነዚሁ ብቻ ናቸው?” አለው። እሱም “ታናሽየው ገና ይቀራል፤ በጎች እየጠበቀ ነው” አለ። ከዚያም ሳሙኤል እሴይን “በል ልከህ አስመጣው፤ ምክንያቱም እሱ ሳይመጣ ምግብ ለመብላት መቀመጥ አንችልም” አለው።
በመሆኑም ልኮ አስመጣው። እሱም የቀይ ዳማ፣ ዓይኑ የሚያምርና መልከ መልካም ነበር። ከዚያም ይሖዋ “ተነስ፣ ቀባው፤ የመረጥኩት እሱን ነው!” አለው።
ስለዚህ ሳሙኤል የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ ፊት ቀባው። ከዚያም ቀን አንስቶ የይሖዋ መንፈስ ለዳዊት ኃይል ሰጠው። በኋላም ሳሙኤል ተነስቶ ወደ ራማ ሄደ።
በዚህ ጊዜ የይሖዋ መንፈስ ከሳኦል ራቀ፤ ከይሖዋ የመጣ መጥፎ መንፈስም ይረብሸው ጀመር።
የሳኦል አገልጋዮችም እንዲህ አሉት፦ “እንግዲህ ከአምላክ የመጣ መጥፎ መንፈስ እየረበሸህ ነው።
ጌታችን በፊቱ የቆሙትን አገልጋዮቹን በገና የሚደረድር ጥሩ ችሎታ ያለው ሰው እንዲፈልጉ ይዘዝ። ከአምላክ የመጣው መጥፎ መንፈስ በአንተ ላይ ሲወርድ ይህ ሰው በገና ይጫወትልሃል፤ አንተም ደህና ትሆናለህ።”
ስለዚህ ሳኦል አገልጋዮቹን “እንግዲያው እባካችሁ ጥሩ አድርጎ በገና የሚደረድር ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ” አላቸው።
ከአገልጋዮቹም አንዱ እንዲህ አለ፦ “የቤተልሔሙ ሰው የእሴይ ልጅ በገና የመደርደር ጥሩ ችሎታ እንዳለው አይቻለሁ፤ እሱም ደፋርና ኃያል ተዋጊ ነው። ደግሞም አንደበተ ርቱዕና መልከ መልካም ሲሆን ይሖዋም ከእሱ ጋር ነው።”
ከዚያም ሳኦል ወደ እሴይ መልእክተኞችን ልኮ “በጎች የሚጠብቀውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ” አለው።
በመሆኑም እሴይ ዳቦና በወይን ጠጅ የተሞላ አቁማዳ በአህያ አስጭኖ እንዲሁም የፍየል ግልገል አስይዞ ልጁን ዳዊትን ወደ ሳኦል ላከው።
በዚህ መንገድ ዳዊት ወደ ሳኦል መጣ፤ እሱንም ያገለግለው ጀመር። ሳኦልም እጅግ እየወደደው ሄደ፤ ጋሻ ጃግሬውም ሆነ።
ሳኦልም “ዳዊት በፊቴ ሞገስ ስላገኘ እባክህ እዚሁ እኔ ጋ ሆኖ እንዲያገለግለኝ ፍቀድልኝ” በማለት ወደ እሴይ መልእክት ላከ።
ከአምላክ የሚመጣ መጥፎ መንፈስ በሳኦል ላይ በሚወርድበት ጊዜ ሁሉ ዳዊት በገናውን አንስቶ ይደረድር ነበር፤ ሳኦልም ቀለል ይለውና ደህና ይሆን ነበር፤ መጥፎው መንፈስም ከእሱ ይርቅ ነበር።
ፍልስጤማውያኑ የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ከማረኩ በኋላ ከኤቤንዔዘር ወደ አሽዶድ አመጡት።
እነሱም የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ወስደው ወደ ዳጎን ቤት አስገቡት፤ ከዳጎን አጠገብም አስቀመጡት።
በማግስቱም አሽዶዳውያን በማለዳ ሲነሱ ዳጎን በይሖዋ ታቦት ፊት መሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ አገኙት። በመሆኑም ዳጎንን አንስተው ወደ ቦታው መለሱት።
በሚቀጥለውም ቀን ማለዳ ሲነሱ ዳጎን በይሖዋ ታቦት ፊት በግንባሩ ተደፍቶ አገኙት። የዳጎን ራስና መዳፎቹም ተቆርጠው ደፉ ላይ ወድቀው ነበር። ባለበት የቀረው የዓሣው ክፍል ብቻ ነበር።
እስከ ዛሬም ድረስ የዳጎን ካህናትና ወደ ዳጎን ቤት የሚገቡ ሁሉ በአሽዶድ የሚገኘውን የዳጎንን ደፍ የማይረግጡት ለዚህ ነው።
የይሖዋም እጅ በአሽዶዳውያን ላይ ከበደባቸው፤ እሱም አሽዶድንና ግዛቶቿን በኪንታሮት በመምታት አጠፋቸው።
የአሽዶድ ሰዎች የተከሰተውን ነገር ሲያዩ “የእስራኤል አምላክ ታቦት በመካከላችን እንዲቆይ አታድርጉ፤ ምክንያቱም እጁ በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ጨክኖብናል” አሉ።
በመሆኑም ሰዎችን ልከው የፍልስጤምን ገዢዎች በሙሉ በመሰብሰብ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ምን ብናደርገው ይሻላል?” ብለው ጠየቋቸው። እነሱም “የእስራኤል አምላክ ታቦት ወደ ጌት ይወሰድ” ሲሉ መለሱላቸው። ስለሆነም የእስራኤልን አምላክ ታቦት ወደዚያ ወሰዱት።
ታቦቱንም ወደዚያ ከወሰዱት በኋላ የይሖዋ እጅ በከተማዋ ላይ ሆነ፤ ታላቅ ሽብርም ለቀቀባቸው። እሱም የከተማዋን ሰዎች ከትንሽ እስከ ትልቅ መታቸው፤ ኪንታሮትም ወጣባቸው።
በመሆኑም የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ወደ ኤቅሮን ላኩት፤ ሆኖም የእውነተኛው አምላክ ታቦት ኤቅሮን ሲደርስ ኤቅሮናውያን “እኛንም ሆነ ሕዝባችንን ለማስፈጀት የእስራኤልን አምላክ ታቦት ይኸው ወደ እኛ ደግሞ አመጡብን!” በማለት ይጮኹ ጀመር።
ከዚያም ሰዎችን ልከው የፍልስጤምን ገዢዎች በሙሉ በመሰብሰብ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ከዚህ አርቁልን፤ እኛም ሆንን ሕዝባችን እንዳናልቅ ወደ ቦታው እንዲመለስ አድርጉ” አሏቸው። ምክንያቱም መላ ከተማዋ በሞት ፍርሃት ተውጣ ነበር፤ የእውነተኛውም አምላክ እጅ በዚያ በጣም ከብዶ ነበር፤
ያልሞቱት ሰዎችም በኪንታሮት ተመቱ። ከተማዋ እርዳታ ለማግኘት የምታሰማው ጩኸትም ወደ ሰማይ ወጣ።
አንድ ቀን የሳኦል ልጅ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን “ና፣ በዚያ በኩል ወዳለው የፍልስጤማውያን የጦር ሰፈር እንሻገር” አለው። ይህን ግን ለአባቱ አልነገረውም።
ሳኦልም በጊብዓ ዳርቻ በሚግሮን በሚገኘው የሮማን ዛፍ ሥር ሰፍሮ ነበር፤ ከእሱም ጋር 600 ሰዎች ነበሩ።
(በሴሎ የይሖዋ ካህን የሆነው የኤሊ ልጅ፣ የፊንሃስ ልጅ፣ የኢካቦድ ወንድም የአኪጡብ ልጅ አኪያህ ኤፉድ ለብሶ ነበር።) ሕዝቡም ዮናታን መሄዱን አላወቀም።
ዮናታን ወደ ፍልስጤማውያን የጦር ሰፈር ለመሻገር ባሰበባቸው መተላለፊያዎች መካከል በአንደኛው በኩል እንደ ጥርስ የሾለ ዓለት፣ በሌላኛውም በኩል እንደ ጥርስ የሾለ ዓለት ነበር፤ የአንደኛው ስም ቦጼጽ ሲሆን የሌላኛው ስም ደግሞ ሴኔ ነበር።
አንደኛው ዓለት በሚክማሽ ትይዩ በስተ ሰሜን እንደ ዓምድ ቆሞ ነበር፤ ሌላኛው ደግሞ በጊብዓ ትይዩ በስተ ደቡብ ቆሞ ነበር።
በመሆኑም ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን “ና፣ ወደ እነዚህ ያልተገረዙ ሰዎች የጦር ሰፈር እንሻገር። ይሖዋ በብዙም ሆነ በጥቂት ሰዎች ተጠቅሞ ከማዳን የሚያግደው ነገር ስለሌለ ምናልባት ይሖዋ ስለ እኛ ሲል እርምጃ ይወስድ ይሆናል” አለው።
በዚህ ጊዜ ጋሻ ጃግሬው “ልብህ ያነሳሳህን ማንኛውንም ነገር አድርግ። ወደፈለግክበት ሂድ፤ እኔም ልብህ ወዳነሳሳህ ወደየትኛውም ቦታ ተከትዬህ እሄዳለሁ” አለው።
ከዚያም ዮናታን እንዲህ አለው፦ “እንግዲያውስ ወደ እነዚያ ሰዎች እንሻገርና እንታያቸው።
እነሱም ‘ወደ እናንተ እስክንመጣ ድረስ ባላችሁበት ጠብቁን’ ካሉን ባለንበት ሆነን እንጠብቃቸዋለን፤ ወደ እነሱም አንወጣም።
ይሁንና ‘ውጡና ግጠሙን!’ ካሉን ወደዚያ እንወጣለን፤ ምክንያቱም ይሖዋ እነሱን በእጃችን አሳልፎ ይሰጠናል። እንግዲህ ይህ ምልክት ይሆነናል።”
ከዚያም ሁለቱ ወጥተው ለፍልስጤማውያን የጦር ሰፈር ታዩ። ፍልስጤማውያኑም “አያችሁ፣ ዕብራውያኑ ከተደበቁባቸው ጉድጓዶች እየወጡ ነው” አሉ።
በመሆኑም በጦር ሰፈሩ የነበሩት ሰዎች ዮናታንንና ጋሻ ጃግሬውን “ኑ፣ ወደ እኛ ውጡ፤ እናሳያችኋለን!” አሏቸው። ዮናታንም ወዲያውኑ ጋሻ ጃግሬውን “ይሖዋ እስራኤላውያን እጅ ላይ ስለሚጥላቸው ተከተለኝ” አለው።
ዮናታንም በእጁና በእግሩ እየቧጠጠ ወጣ፤ ጋሻ ጃግሬውም ይከተለው ነበር፤ ዮናታንም በፍልስጤማውያን ላይ ጥቃት ሰነዘረ፤ ጋሻ ጃግሬውም ከኋላው እየተከተለ ገደላቸው።
ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው መጀመሪያ ላይ በሰነዘሩት ጥቃት አንድ ጥማድ በሚያውል የእርሻ መሬት ላይ ግማሽ ትልም በሚያህል ቦታ 20 ሰው ገደሉ።
ከዚያም በእርሻው ውስጥ በሰፈረው ሠራዊትና በጦር ሰፈሩ ውስጥ በነበረው ሕዝብ ሁሉ መካከል ሽብር ተነዛ፤ ሌላው ቀርቶ ወራሪ ቡድኖቹ እንኳ ተሸበሩ። ምድሪቱም መንቀጥቀጥ ጀመረች፤ ከአምላክ የመጣ ሽብርም ወረደባቸው።
በቢንያም ግዛት በምትገኘው በጊብዓ የነበሩት የሳኦል ጠባቂዎችም በየአቅጣጫው ሁከት መሰራጨቱን አዩ።
ሳኦልም አብረውት የነበሩትን ሰዎች “እስቲ ሕዝቡን ቁጠሩና ትቶን የሄደው ማን እንደሆነ እወቁ” አላቸው። እነሱም ሲቆጥሩ ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው እዚያ እንዳልነበሩ ተረዱ።
ሳኦልም አኪያህን “የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ወደዚህ አምጣ!” አለው። (በዚያ ጊዜ የእውነተኛው አምላክ ታቦት በእስራኤላውያን ዘንድ ነበር።)
ሳኦል ካህኑን እያነጋገረ ሳለ በፍልስጤማውያን ሰፈር የነበረው ትርምስ ይበልጥ እየጨመረ ሄደ። ከዚያም ሳኦል ካህኑን “እያደረግክ ያለኸውን ነገር ተው” አለው።
በመሆኑም ሳኦልና አብረውት የነበሩት ሰዎች በሙሉ ተሰባስበው ውጊያው ወደሚደረግበት ቦታ ሄዱ፤ እዚያ ሲደርሱም ፍልስጤማውያኑ እርስ በርሳቸው በሰይፍ ሲጨፋጨፉ አገኟቸው፤ ከፍተኛ ትርምስ ተፈጥሮ ነበር።
ቀደም ሲል ከፍልስጤማውያን ጋር ወግነው የነበሩትና አብረዋቸው ወደ ሰፈሩ የመጡት ዕብራውያንም በሳኦልና በዮናታን ሥር ከነበሩት እስራኤላውያን ጋር ተቀላቀሉ።
በተጨማሪም በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ ተደብቀው የነበሩት የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ፍልስጤማውያን እየሸሹ መሆኑን ሰሙ፤ እነሱም ከሌሎቹ ጋር በመተባበር ፍልስጤማውያንን ማሳደዱን ተያያዙት።
በዚህ መንገድ ይሖዋ በዚያ ቀን እስራኤልን አዳነ፤ ውጊያውም እስከ ቤትአዌን ድረስ ዘለቀ።
ሆኖም ሳኦል “ጠላቶቼን ከመበቀሌ በፊት እስከ ማታ ድረስ እህል የሚቀምስ ሰው የተረገመ ይሁን!” በማለት ሕዝቡን አስምሎ ስለነበር በዚያ ዕለት የእስራኤል ሰዎች ተጨንቀው ዋሉ። በመሆኑም ከሕዝቡ መካከል አንድም ሰው እህል አልቀመሰም።
ሕዝቡም ሁሉ ወደ ጫካው ገባ፤ መሬቱም ላይ ማር ነበር።
ሕዝቡም ወደ ጫካው ሲገባ ማሩ ሲንጠባጠብ አየ፤ ሆኖም ሁሉም መሐላውን ስለፈሩ እጁን ወደ አፉ ያነሳ አንድም ሰው አልነበረም።
ዮናታን ግን አባቱ ሕዝቡን ሲያስምል አልሰማም ነበር፤ በመሆኑም በእጁ የነበረውን በትር ዘርግቶ ጫፉን የማር እንጀራው ውስጥ አጠቀሰ። ከዚያም እጁን ወደ አፉ ሲመልስ ዓይኑ በራ።