text
stringlengths
4
267
እሱም “ከእነሱ ጋር የምትከራከሩት ስለ ምን ጉዳይ ነው?” ሲል ጠየቃቸው።
ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “መምህር፣ ልጄ ዱዳ የሚያደርግ መንፈስ ስላደረበት ወደ አንተ አመጣሁት።
በያዘው ስፍራ ሁሉ መሬት ላይ ይጥለዋል፤ ከዚያም አፉ አረፋ ይደፍቃል፤ ጥርሱን ያፋጫል እንዲሁም ይዝለፈለፋል። ደቀ መዛሙርትህ እንዲያስወጡት ጠየቅኳቸው፤ እነሱ ግን ሊያስወጡት አልቻሉም።”
እሱም መልሶ “እምነት የለሽ ትውልድ ሆይ፣ ከእናንተ ጋር እስከ መቼ መቆየት ሊኖርብኝ ነው? እስከ መቼስ እናንተን መታገሥ ሊኖርብኝ ነው? ልጁን ወደ እኔ አምጡት” አላቸው።
ልጁንም ወደ እሱ አመጡት፤ ልጁን የያዘው መንፈስም ኢየሱስን ባየው ጊዜ ወዲያውኑ ልጁን አንዘፈዘፈው። ልጁም መሬት ላይ ከወደቀ በኋላ አፉ አረፋ እየደፈቀ ይንከባለል ጀመር።
ከዚያም ኢየሱስ አባትየውን “እንዲህ ማድረግ ከጀመረው ምን ያህል ጊዜ ሆነው?” ሲል ጠየቀው። አባትየውም እንዲህ አለው፦ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤
ሊገድለው ፈልጎ ብዙ ጊዜ እሳት ውስጥና ውኃ ውስጥ ይጥለዋል። ማድረግ የምትችለው ነገር ካለ እዘንልንና እርዳን።”
ኢየሱስም “‘የምትችለው ነገር ካለ’ አልክ? እምነት ላለው ሰው፣ ሁሉ ነገር ይቻላል” አለው።
ወዲያውም የልጁ አባት “እምነት አለኝ! እምነቴ እንዲጠነክር ደግሞ አንተ እርዳኝ!” በማለት ጮክ ብሎ ተናገረ።
ኢየሱስ ሕዝቡ ወደ እነሱ ግር ብሎ እየሮጠ በመምጣት ላይ መሆኑን ሲያይ ርኩሱን መንፈስ “አንተ ዱዳና ደንቆሮ የምታደርግ መንፈስ ከእሱ ውጣ፤ ዳግመኛም ወደ እሱ እንዳትገባ አዝሃለሁ!” ሲል ገሠጸው።
ርኩሱ መንፈስ በኃይል ከጮኸና ብዙ ካንዘፈዘፈው በኋላ ወጣ፤ ልጁም የሞተ ያህል ሆነ፤ በዚህ ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች “ሞቷል!” ይሉ ጀመር።
ይሁን እንጂ ኢየሱስ እጁን ይዞ አስነሳው፤ ልጁም ተነስቶ ቆመ።
ከዚያም ወደ ቤት ከገባ በኋላ ብቻውን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።
እሱም “እንዲህ ዓይነቱ በጸሎት ካልሆነ በቀር ሊወጣ አይችልም” አላቸው።
ከዚያ ተነስተው በገሊላ በኩል አለፉ፤ ሆኖም ይህን ማንም እንዲያውቅ አልፈለገም።
ምክንያቱም ደቀ መዛሙርቱን እያስተማራቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ “የሰውን ልጅ ለሰዎች አሳልፈው ይሰጡታል፤ እነሱም ይገድሉታል፤ ይሁንና ቢገደልም ከሦስት ቀን በኋላ ይነሳል” በማለት እየነገራቸው ነበር።
ይሁን እንጂ የተናገረው ነገር አልገባቸውም፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ።
ከዚህ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም መጡ። ወደ ቤት ከገባም በኋላ “በመንገድ ላይ ስትከራከሩ የነበረው ስለ ምን ጉዳይ ነው?” ሲል ጠየቃቸው።
በመንገድ ላይ እርስ በርስ የተከራከሩት “ከሁላችን የሚበልጠው ማን ነው?” በሚል ስለነበረ ዝም አሉ።
ስለዚህ ከተቀመጠ በኋላ አሥራ ሁለቱን ጠርቶ “መጀመሪያ መሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉም መጨረሻና የሁሉም አገልጋይ መሆን አለበት” አላቸው።
ከዚያም አንድ ትንሽ ልጅ አምጥቶ በመካከላቸው አቆመ፤ አቅፎትም እንዲህ አላቸው፦
“እንዲህ ካሉት ልጆች አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔንም ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል ሁሉ እኔን ብቻ ሳይሆን የላከኝንም ይቀበላል።”
ዮሐንስ እንዲህ አለው፦ “መምህር፣ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያስወጣ አየን፤ ሆኖም እኛን ስለማይከተል ልንከለክለው ሞከርን።”
ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ “በስሜ ተአምር ሠርቶ ወዲያውኑ ስለ እኔ ክፉ ነገር ሊናገር የሚችል ስለሌለ አትከልክሉት።
እኛን የማይቃወም ሁሉ ከእኛ ጋር ነውና።
ደግሞም የክርስቶስ በመሆናችሁ ምክንያት አንድ ጽዋ የሚጠጣ ውኃ የሚሰጣችሁ ሁሉ፣ እውነት እላችኋለሁ፣ በምንም መንገድ ብድራቱን አያጣም።
ሆኖም ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል።
“እጅህ ቢያሰናክልህ ቁረጠው። ሁለት እጅ ኖሮህ እሳቱ ሊጠፋ ወደማይችልበት ወደ ገሃነም ከምትሄድ ጉንድሽ ሆነህ ሕይወት ብታገኝ ይሻልሃል።
እግርህም ቢያሰናክልህ ቁረጠው። ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ገሃነም ከምትጣል አንካሳ ሆነህ ሕይወት ብታገኝ ይሻልሃል።
ዓይንህም ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው። ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ ገሃነም ከምትጣል አንድ ዓይን ኖሮህ ወደ አምላክ መንግሥት ብትገባ ይሻልሃል፤
በገሃነም ትሉ አይሞትም፤ እሳቱም አይጠፋም።
“ሰው ጨው እንደሚነሰንስ ሁሉ እንዲህ ዓይነት ሰዎችም እሳት ሊወርድባቸው ይገባል።
ጨው መልካም ነው፤ ነገር ግን ጨው የጨውነት ጣዕሙን ቢያጣ ጨውነቱን በምን መመለስ ትችላላችሁ? በሕይወታችሁ ውስጥ ጨው ይኑራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም ሰላም ይኑራችሁ።”
ይሁን እንጂ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ተመልሶ መጣ፤ ደግሞም ቤት ውስጥ እንዳለ ተወራ።
በመሆኑም ቤቱ ሞልቶ ደጅ ላይ እንኳ ቦታ እስኪታጣ ድረስ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ እሱም የአምላክን ቃል ይነግራቸው ጀመር።
ሰዎችም አንድ ሽባ በአራት ሰዎች አሸክመው ወደ እሱ አመጡ።
ሆኖም ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ሽባውን ወደ ኢየሱስ ማቅረብ ስላልቻሉ ከኢየሱስ በላይ ያለውን ጣሪያ ከነደሉ በኋላ ሽባው የተኛበትን ቃሬዛ ወደ ታች አወረዱት።
ኢየሱስም እምነታቸውን በማየት ሽባውን “ልጄ ሆይ፣ ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል” አለው።
በዚያ ተቀምጠው የነበሩ አንዳንድ ጸሐፍት ግን እንዲህ ሲሉ በልባቸው አሰቡ፦
“ይህ ሰው እንዲህ ብሎ የሚናገረው ለምንድን ነው? አምላክን እየተዳፈረ እኮ ነው። ከአንዱ ከአምላክ በቀር ኃጢአትን ማን ይቅር ሊል ይችላል?”
ሆኖም ኢየሱስ በልባቸው ይህን እያሰቡ እንዳሉ ወዲያው በመንፈሱ ተረድቶ “በልባችሁ እንዲህ እያላችሁ የምታስቡት ለምንድን ነው?
ሽባውን ‘ኃጢአትህ ይቅር ተብሏል’ ከማለትና ‘ተነሳና ቃሬዛህን ተሸክመህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀላል?
ይሁንና የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ . . .” ካለ በኋላ ሽባውን እንዲህ አለው፦
“ተነስ፣ ቃሬዛህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ።”
በዚህ ጊዜ ሽባው ብድግ ብሎ ወዲያው ቃሬዛውን በማንሳት በሁሉ ፊት እየተራመደ ወጣ። ይህን ሲያዩ ሁሉም እጅግ ተደነቁ፤ ደግሞም “እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይተን አናውቅም” በማለት አምላክን አከበሩ።
ኢየሱስ እንደገና ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሄደ፤ ሕዝቡም ወደ እሱ ጎረፈ፤ እሱም ያስተምራቸው ጀመር።
በመንገድ እያለፈ ሳለም የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን በቀረጥ መሰብሰቢያው ቦታ ተቀምጦ አየውና “ተከታዬ ሁን” አለው። በዚህ ጊዜ ተነስቶ ተከተለው።
በኋላም በሌዊ ቤት ተቀምጦ እየበላ ነበር፤ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኃጢአተኞችም ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እየበሉ ነበር። ከእነሱም መካከል ብዙዎቹ እሱን መከተል ጀምረው ነበር።
ሆኖም ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ ጸሐፍት ከኃጢአተኞችና ከቀረጥ ሰብሳቢዎች ጋር ሲበላ ባዩ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “እንዴት ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኃጢአተኞች ጋር ይበላል?” አሏቸው።
ኢየሱስ ይህን ሲሰማ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም። እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ልጠራ ነው” አላቸው።
የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን የመጾም ልማድ ነበራቸው። ስለዚህም ወደ እሱ መጥተው “የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ዘወትር ሲጾሙ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጾሙት ለምንድን ነው?” አሉት።
ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ሙሽራው ከእነሱ ጋር እያለ ጓደኞቹ የሚጾሙበት ምን ምክንያት አለ? ሙሽራው አብሯቸው እስካለ ድረስ ሊጾሙ አይችሉም።
ሆኖም ሙሽራው ከእነሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ።
በአሮጌ ልብስ ላይ ውኃ ያልነካው አዲስ ጨርቅ የሚጥፍ ሰው የለም። እንዲህ ቢያደርግ ግን አዲሱ ጨርቅ ሲሸበሸብ አሮጌውን ስለሚስበው ቀዳዳው የባሰ ይሰፋል።
እንዲሁም ባረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያስቀምጥ ሰው የለም። እንዲህ ቢያደርግ ግን የወይን ጠጁ አቁማዳውን ያፈነዳዋል፤ ወይኑ ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ይሁንና አዲስ የወይን ጠጅ የሚቀመጠው በአዲስ አቁማዳ ነው።”
በሰንበት ቀን በእህል እርሻ መካከል እያለፈ ሳለ አብረውት ይሄዱ የነበሩት ደቀ መዛሙርቱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር።
በመሆኑም ፈሪሳውያን “ተመልከት! በሰንበት ቀን በሕግ የተከለከለ ነገር የሚያደርጉት ለምንድን ነው?” አሉት።
እሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ዳዊት የሚበላው ባጣ ጊዜ እንዲሁም እሱና አብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ያደረገውን ነገር ፈጽሞ አላነበባችሁም?
ሊቀ ካህናት ስለሆነው ስለ አብያታር በሚናገረው ታሪክ ላይ ዳዊት ወደ አምላክ ቤት ገብቶ ከካህናት በቀር ማንም እንዲበላ ያልተፈቀደውን በአምላክ ፊት የቀረበ ኅብስት እንደበላና ከእሱ ጋር ለነበሩትም እንደሰጣቸው አላነበባችሁም?”
ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ሰንበት ለሰው ተሰጠ እንጂ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም።
በመሆኑም የሰው ልጅ የሰንበትም እንኳ ጌታ ነው።”
ከዚያም ተነስቶ ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳሉት የይሁዳ ድንበሮች መጣ፤ ብዙ ሰዎችም እንደገና ወደ እሱ ተሰበሰቡ። አሁንም እንደ ልማዱ ያስተምራቸው ጀመር።
ፈሪሳውያንም ቀርበው እሱን ለመፈተን በማሰብ አንድ ሰው ሚስቱን እንዲፈታ ሕግ ይፈቅድለት እንደሆነ ጠየቁት።
እሱም መልሶ “ሙሴ ምን ብሎ ነው ያዘዛችሁ?” አላቸው።
እነሱም “ሙሴ የፍቺ የምሥክር ወረቀት ጽፎ እንዲፈታት ፈቅዷል” አሉት።
ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ሙሴ ይህን ትእዛዝ የጻፈላችሁ ልባችሁ ደንዳና መሆኑን አይቶ ነው።
ይሁን እንጂ በፍጥረት መጀመሪያ ‘አምላክ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።
ከዚህ የተነሳ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤
ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’፤ በመሆኑም ከዚህ በኋላ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም።
ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።”
እንደገና ወደ ቤት በገቡ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ጉዳይ ይጠይቁት ጀመር።
እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ በማመንዘር ሚስቱን ይበድላል፤
አንዲት ሴትም ብትሆን ባሏን ፈታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች።”
ሰዎችም ኢየሱስ እጁን እንዲጭንባቸው ትናንሽ ልጆችን ወደ እሱ ያመጡ ጀመር፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው።
ኢየሱስ ይህን ሲያይ ተቆጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “ልጆቹ ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ የአምላክ መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ነውና።
እውነት እላችኋለሁ፣ የአምላክን መንግሥት እንደ አንድ ትንሽ ልጅ ሆኖ የማይቀበል ሁሉ ፈጽሞ ወደዚህ መንግሥት አይገባም።”
ልጆቹንም አቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ባረካቸው።
ከዚያ ወጥቶ በመሄድ ላይ ሳለ አንድ ሰው እየሮጠ መጣ፤ በፊቱም በጉልበቱ ተንበርክኮ “ጥሩ መምህር ሆይ፣ የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” ሲል ጠየቀው።
ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “ለምን ጥሩ ብለህ ትጠራኛለህ? ከአንዱ ከአምላክ በቀር ጥሩ የለም።
‘አትግደል፣ አታመንዝር፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመሥክር፣ አታታል፣ አባትህንና እናትህን አክብር’ የሚሉትን ትእዛዛት ታውቃለህ።”
ሰውየውም “መምህር፣ እነዚህን ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ስጠብቅ ኖሬአለሁ” አለው።
ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ ከዚያም “አንድ ነገር ይጎድልሃል፤ ሂድና ያለህን ነገር ሁሉ ሸጠህ ገንዘቡን ለድሆች ስጥ፤ በሰማይም ውድ ሀብት ታገኛለህ፤ ደግሞም መጥተህ ተከታዬ ሁን” አለው።
ሰውየው ግን ይህን ሲሰማ አዘነ፤ ብዙ ንብረት ስለነበረውም እያዘነ ሄደ።
ኢየሱስ ዙሪያውን ከተመለከተ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “ገንዘብ ላላቸው ሰዎች ወደ አምላክ መንግሥት መግባት ምንኛ አስቸጋሪ ነው!” አላቸው።
ደቀ መዛሙርቱ ግን በንግግሩ ተገረሙ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ልጆቼ ሆይ፣ ወደ አምላክ መንግሥት መግባት እንዴት አስቸጋሪ ነው!
ሀብታም ሰው ወደ አምላክ መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀልላል።”
ደቀ መዛሙርቱ ይበልጥ በመገረም “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” አሉት።
ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ትኩር ብሎ በመመልከት “ይህ በሰዎች ዘንድ አይቻልም፤ በአምላክ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ በአምላክ ዘንድ ሁሉ ነገር ይቻላል” አለ።
ጴጥሮስም “እነሆ፣ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል” አለው።
ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ስለ እኔና ስለ ምሥራቹ ሲል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም እናትን ወይም አባትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ፣
አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እህቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችንና እርሻን 100 እጥፍ፣ በሚመጣው ሥርዓት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያገኛል።
ሆኖም ፊተኞች የሆኑ ብዙዎች ኋለኞች፣ ኋለኞች የሆኑ ደግሞ ፊተኞች ይሆናሉ።”
ወደ ኢየሩሳሌም በሚወስደው መንገድ እያቀኑ ሳሉ ኢየሱስ ከፊት ከፊታቸው ይሄድ ነበር፤ እነሱም ተደነቁ፤ ይከተሉት የነበሩት ሰዎች ግን ፍርሃት አደረባቸው። እሱም እንደገና አሥራ ሁለቱን ገለል አድርጎ በመውሰድ የሚደርስበትን ነገር ይነግራቸው ጀመር፦
“እነሆ፣ ወደ ኢየሩሳሌም እየወጣን ነው፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት አልፎ ይሰጣል። እነሱም ሞት ይፈርዱበታል፤ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፤
ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፤ ይገርፉታል፤ ከዚያም ይገድሉታል፤ ሆኖም ከሦስት ቀን በኋላ ይነሳል።”
ሁለቱ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ወደ እሱ ቀርበው “መምህር፣ የምንለምንህን ማንኛውንም ነገር እንድታደርግልን እንፈልጋለን” አሉት።
እሱም “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።
እነሱም “በክብር ቦታህ ላይ ስትቀመጥ አንዳችን በቀኝህ፣ አንዳችን ደግሞ በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን” ሲሉ መለሱለት።
ኢየሱስ ግን “የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ ወይም እኔ የምጠመቀውን ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁ?” አላቸው።
እነሱም “እንችላለን” አሉት። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ።