text
stringlengths
4
267
ተመልሶ ሲመጣ ተኝተው አገኛቸውና ጴጥሮስን እንዲህ አለው፦ “ስምዖን፣ ተኝተሃል? አንድ ሰዓት እንኳ ነቅተህ መጠበቅ አልቻልክም?
ወደ ፈተና እንዳትገቡ ነቅታችሁ ጠብቁ፤ ሳታሰልሱም ጸልዩ። እርግጥ፣ መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።”
እንደገናም ሄዶ ስለዚያው ነገር ጸለየ።
ዳግመኛም ተመልሶ ሲመጣ እንቅልፍ ተጫጭኗቸው ስለነበር ተኝተው አገኛቸው፤ በመሆኑም የሚሉት ነገር ጠፋቸው።
ለሦስተኛ ጊዜም ተመልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ይህ የእንቅልፍና የእረፍት ሰዓት ነው? በቃ! ሰዓቱ ደርሷል! እነሆ፣ የሰው ልጅ ለኃጢአተኞች አልፎ ሊሰጥ ነው።
ተነሱ፣ እንሂድ። እነሆ፣ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል።”
ወዲያውም ገና እየተናገረ ሳለ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ መጣ፤ ከካህናት አለቆች፣ ከጸሐፍትና ከሽማግሌዎች የተላኩ ሰይፍና ቆመጥ የያዙ ብዙ ሰዎችም አብረውት ነበሩ።
አሳልፎ የሚሰጠውም “እኔ የምስመው ሰው እሱ ነው፤ ያዙትና እንዳያመልጥ ተጠንቅቃችሁ ውሰዱት” በማለት አስቀድሞ ምልክት ሰጥቷቸው ነበር።
ይሁዳም በቀጥታ መጥቶ ወደ እሱ በመቅረብ “ረቢ!” ብሎ ሳመው።
ሰዎቹም ያዙት፤ ደግሞም አሰሩት።
ይሁን እንጂ አጠገቡ ቆመው ከነበሩት አንዱ ሰይፉን በመምዘዝ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቆረጠው።
ኢየሱስ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ወንበዴ የምትይዙ ይመስል ሰይፍና ቆመጥ ይዛችሁ የመጣችሁት እኔን ለመያዝ ነው?
በየዕለቱ በቤተ መቅደስ እያስተማርኩ ከእናንተ ጋር ነበርኩ፤ ሆኖም ያን ጊዜ አልያዛችሁኝም። ይሁንና ይህ የሆነው ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲፈጸሙ ነው።”
በዚህ ጊዜ ሁሉም ጥለውት ሸሹ።
ሆኖም እርቃኑን ለመሸፈን በፍታ ብቻ የለበሰ አንድ ወጣት በቅርብ ርቀት ይከተለው ጀመር፤ ሊይዙትም ሞከሩ፤
እሱ ግን በፍታውን ትቶ ራቁቱን አመለጠ።
ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤ የካህናት አለቆች፣ ሽማግሌዎችና ጸሐፍትም በሙሉ ተሰበሰቡ።
ይሁንና ጴጥሮስ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ በርቀት ተከተለው፤ ከዚያም ከቤቱ አገልጋዮች ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ጀመር።
በዚህ ጊዜ የካህናት አለቆችና መላው የሳንሄድሪን ሸንጎ ኢየሱስን ለመግደል በእሱ ላይ የምሥክሮች ቃል እየፈለጉ ነበር፤ ነገር ግን ምንም አላገኙም።
እርግጥ ብዙዎች በእሱ ላይ የሐሰት ምሥክርነት ይሰጡ ነበር፤ ሆኖም ቃላቸው ሊስማማ አልቻለም።
አንዳንዶችም ተነስተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት ይመሠክሩበት ነበር፦
“‘ይህን በእጅ የተሠራ ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ውስጥ በእጅ ያልተሠራ ሌላ እገነባለሁ’ ሲል ሰምተነዋል።”
በዚህ ጉዳይም ቢሆን የምሥክርነት ቃላቸው ሊስማማ አልቻለም።
ከዚያም ሊቀ ካህናቱ በመካከላቸው ቆሞ ኢየሱስን “ምንም መልስ አትሰጥም? እነዚህ ሰዎች በአንተ ላይ ስለሰጡት ምሥክርነት ምን ትላለህ?” ሲል ጠየቀው።
እሱ ግን ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም። ሊቀ ካህናቱም እንደገና “አንተ ብሩክ የሆነው አምላክ ልጅ ክርስቶስ ነህ?” እያለ ይጠይቀው ጀመር።
ኢየሱስም “አዎ ነኝ፤ እናንተም የሰው ልጅ በኃያሉ ቀኝ ተቀምጦ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” አለ።
በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ እንዲህ አለ፦ “ከዚህ በላይ ምን ምሥክሮች ያስፈልጉናል?
አምላክን ሲሳደብ ሰምታችኋል። ታዲያ ውሳኔያችሁ ምንድን ነው?” ሁሉም ሞት ይገባዋል ብለው ፈረዱበት።
አንዳንዶች ይተፉበት ጀመር፤ ፊቱንም ሸፍነው በቡጢ እየመቱት “ነቢይ ከሆንክ እስቲ ማን እንደመታህ ንገረን!” ይሉት ነበር። የሸንጎው አገልጋዮችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት።
ጴጥሮስ ግቢው ውስጥ በታች በኩል ሳለ ከሊቀ ካህናቱ ሴት አገልጋዮች አንዷ መጣች።
እሳት ሲሞቅ አይታ ትኩር ብላ ተመለከተችውና “አንተም ከዚህ ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበርክ” አለችው።
እሱ ግን “ሰውየውን አላውቀውም፤ ምን እንደምታወሪም አላውቅም” ሲል ካደ፤ ከዚያም ወደ መግቢያው ሄደ።
አገልጋይዋም እዚያ አየችውና በአጠገቡ ለቆሙት “ይህ ከእነሱ አንዱ ነው” ብላ እንደገና ትናገር ጀመር።
አሁንም ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ በዚያ ቆመው የነበሩት ጴጥሮስን እንደገና “የገሊላ ሰው ስለሆንክ፣ በእርግጥ አንተም ከእነሱ አንዱ ነህ” ይሉት ጀመር።
እሱ ግን “ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም!” ሲል ይምልና ራሱን ይረግም ጀመር።
ወዲያውኑ ዶሮ ለሁለተኛ ጊዜ ጮኸ፤ ጴጥሮስም “ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ሲል ኢየሱስ የተናገረው ቃል ትዝ አለው። ከዚያም እጅግ አዝኖ ያለቅስ ጀመር።
ወዲያውኑ በማለዳ የካህናት አለቆች፣ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ማለትም መላው የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት ተሰብስበው ተማከሩ፤ ኢየሱስንም አስረው በመውሰድ ለጲላጦስ አስረከቡት።
ጲላጦስም “አንተ የአይሁዳውያን ንጉሥ ነህ?” ሲል ጠየቀው። እሱም መልሶ “አንተው ራስህ ተናገርከው” አለው።
የካህናት አለቆቹ ግን በእሱ ላይ በርካታ ክስ መደርደራቸውን ቀጠሉ።
በዚህ ጊዜ ጲላጦስ “ምንም መልስ አትሰጥም? በስንት ነገር እየከሰሱህ እንዳሉ ተመልከት” ሲል እንደገና ጠየቀው።
ሆኖም ኢየሱስ ምንም ተጨማሪ መልስ አልሰጠም፤ በመሆኑም ጲላጦስ ተገረመ።
ጲላጦስ ሁልጊዜ በዚህ በዓል ወቅት፣ ሕዝቡ ይፈታልን ብለው የጠየቁትን አንድ እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው።
በወቅቱ፣ በመንግሥት ላይ ዓመፅ በማነሳሳት ሰው ገድለው ከታሰሩ ዓመፀኞች መካከል በርባን የሚባል ሰው ይገኝ ነበር።
ሕዝቡም መጥተው ጲላጦስ እንደ ልማዱ ያደርግላቸው ዘንድ ይጠይቁት ጀመር።
እሱም መልሶ “የአይሁዳውያንን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።
ጲላጦስ ይህን ያለው የካህናት አለቆች አሳልፈው የሰጡት በቅናት ተነሳስተው እንደሆነ ያውቅ ስለነበር ነው።
ይሁንና የካህናት አለቆቹ በኢየሱስ ምትክ በርባንን ይፈታላቸው ዘንድ እንዲጠይቁ ሕዝቡን አነሳሱ።
ጲላጦስም እንደገና መልሶ “እንግዲያው የአይሁዳውያን ንጉሥ የምትሉትን ምን ባደርገው ይሻላል?” አላቸው።
እነሱም “ይሰቀል!” ብለው እንደገና ጮኹ።
ሆኖም ጲላጦስ “ለምን? ምን ያጠፋው ነገር አለ?” አላቸው። እነሱ ግን “ይሰቀል!” እያሉ የባሰ ጮኹ።
በዚህ ጊዜ ጲላጦስ ሕዝቡን ለማስደሰት ስለፈለገ በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስንም ካስገረፈው በኋላ በእንጨት ላይ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።
ወታደሮቹ ወደ ግቢው ይኸውም ወደ አገረ ገዢው መኖሪያ ቤት ወሰዱት፤ ሠራዊቱንም ሁሉ አንድ ላይ ሰበሰቡ።
ሐምራዊ ልብስም አለበሱት፤ የእሾህ አክሊል ጎንጉነውም በራሱ ላይ ደፉበት፤
ደግሞም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “የአይሁዳውያን ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን!” ይሉት ጀመር።
ከዚህም ሌላ ራሱን በመቃ ይመቱትና ይተፉበት ነበር፤ ተንበርክከውም እጅ ነሱት።
ሲያፌዙበት ከቆዩ በኋላም ሐምራዊውን ልብስ ገፈው የራሱን መደረቢያዎች አለበሱት። ከዚያም በእንጨት ላይ ሊቸነክሩት ይዘውት ሄዱ።
ስምዖን የተባለ አንድ የቀሬና ሰው ከገጠር መጥቶ በዚያ ሲያልፍ አግኝተው ኢየሱስ የሚሰቀልበትን የመከራ እንጨት እንዲሸከም አስገደዱት፤ ይህ ሰው የእስክንድርና የሩፎስ አባት ነበር።
በኋላም ኢየሱስን ጎልጎታ ወደተባለ ቦታ አመጡት፤ ትርጉሙም “የራስ ቅል ቦታ” ማለት ነው።
እዚያም ከርቤ የተቀላቀለበት የወይን ጠጅ ሰጡት፤ እሱ ግን አልተቀበለም።
ከዚያም እንጨት ላይ ቸነከሩት፤ ማን ምን እንደሚወስድ ለመወሰንም ዕጣ ተጣጥለው መደረቢያዎቹን ተከፋፈሉ።
እንጨት ላይ ሲቸነክሩትም ጊዜው ሦስት ሰዓት ነበር።
የተከሰሰበትን ጉዳይ የሚገልጽ “የአይሁዳውያን ንጉሥ” የሚል ጽሑፍ ተጽፎ ነበር።
ከእሱም ጋር ሁለት ዘራፊዎችን፣ አንዱን በቀኙ ሌላውን ደግሞ በግራው በእንጨት ላይ ሰቀሉ።
በዚያ የሚያልፉም ይሰድቡትና ራሳቸውን እየነቀነቁ እንዲህ ይሉት ነበር፦ “ቤተ መቅደሱን አፍርሼ በሦስት ቀን እሠራዋለሁ ባይ!
እስቲ ከተሰቀልክበት እንጨት ላይ ወርደህ ራስህን አድን።”
የካህናት አለቆችም እንደዚሁ ከጸሐፍት ጋር ሆነው እርስ በርሳቸው እንዲህ እያሉ ያፌዙበት ነበር፦ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አልቻለም!
አይተን እናምን ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ እስቲ አሁን ከተሰቀለበት እንጨት ይውረድ።” ከእሱ ጋር በእንጨት ላይ የተሰቀሉትም እንኳ ሳይቀሩ ይነቅፉት ነበር።
ስድስት ሰዓት በሆነ ጊዜም አገሩ በሙሉ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በጨለማ ተሸፈነ።
በዘጠነኛውም ሰዓት ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ “ኤሊ፣ ኤሊ፣ ላማ ሳባቅታኒ?” ብሎ ጮኸ፤ ትርጉሙም “አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው።
በአቅራቢያው ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ሲሰሙ “አያችሁ! ኤልያስን እየተጣራ ነው” ይሉ ጀመር።
ከዚያም አንድ ሰው ሮጦ በመሄድ የኮመጠጠ የወይን ጠጅ ውስጥ ሰፍነግ ከነከረ በኋላ በመቃ ላይ አድርጎ እንዲጠጣ ሰጠውና “ተዉት! እስቲ ኤልያስ መጥቶ ያወርደው እንደሆነ እንይ” አለ።
ሆኖም ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ሞተ።
የቤተ መቅደሱ መጋረጃም ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ።
ከፊት ለፊቱ ቆሞ የነበረው መኮንንም በዚህ ሁኔታ መሞቱን ሲያይ “ይህ ሰው በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነበር” አለ።
በተጨማሪም ከሩቅ ሆነው የሚያዩ ሴቶች የነበሩ ሲሆን ከእነሱም መካከል መግደላዊቷ ማርያም እንዲሁም የትንሹ ያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያምና ሰሎሜ ነበሩ፤
እነዚህም በገሊላ ሳለ ይከተሉትና ያገለግሉት የነበሩ ናቸው፤ ከእሱ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሌሎች በርካታ ሴቶችም ነበሩ።
ቀኑ በመገባደዱና የዝግጅት ቀን ማለትም የሰንበት ዋዜማ በመሆኑ
የተከበረ የሸንጎ አባል የሆነውና የአምላክን መንግሥት ይጠባበቅ የነበረው የአርማትያሱ ዮሴፍ መጣ። ደፍሮም ወደ ጲላጦስ ገባና የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው ጠየቀ።
ጲላጦስ ግን ኢየሱስ ሞቶ እንደሆነ ለማወቅ የመቶ አለቃውን ጠርቶ በእርግጥ ሞቶ እንደሆነ ጠየቀው።
መሞቱን ከመቶ አለቃው ካረጋገጠ በኋላም አስከሬኑን እንዲወስድ ለዮሴፍ ፈቀደለት።
እሱም በፍታ ገዝቶ አስከሬኑን ካወረደ በኋላ በበፍታው ገነዘው፤ ከዚያም ከዓለት ተፈልፍሎ በተሠራ መቃብር ውስጥ አኖረው፤ ድንጋይ አንከባሎም የመቃብሩን ደጃፍ ዘጋው።
በዚህ ጊዜ መግደላዊቷ ማርያምና የዮሳ እናት ማርያም አስከሬኑ የተቀመጠበትን ቦታ ይመለከቱ ነበር።
ዳግመኛም በባሕሩ አጠገብ ሆኖ ያስተምር ጀመር፤ እጅግ ብዙ ሕዝብም ወደ እሱ መጥቶ ተሰበሰበ። በመሆኑም ጀልባ ላይ ወጥቶ ከተቀመጠ በኋላ ከባሕሩ ዳርቻ ፈቀቅ አለ፤ ሕዝቡ ሁሉ ግን በባሕሩ ዳርቻ ነበር።
ከዚያም ብዙ ነገር በምሳሌ ያስተምራቸው ጀመር፤ እንዲህም አላቸው፦
“ስሙ። እነሆ፣ ዘሪው ሊዘራ ወጣ።
በሚዘራበት ጊዜ አንዳንዶቹ ዘሮች መንገድ ዳር ወደቁ፤ ወፎችም መጥተው ለቀሟቸው።
ሌሎቹ ደግሞ ብዙ አፈር በሌለው ድንጋያማ መሬት ላይ ወደቁ፤ አፈሩም ጥልቀት ስላልነበረው ወዲያውኑ በቀሉ።
ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ተቃጠሉ፤ ሥር ስላልነበራቸውም ደረቁ።
ሌሎቹ ዘሮች ደግሞ በእሾህ መካከል ወደቁ፤ እሾሁም አድጎ አነቃቸው፤ ፍሬም አልሰጡም።
ሌሎቹ ግን ጥሩ አፈር ላይ ወድቀው ከበቀሉና ካደጉ በኋላ ፍሬ ማፍራት ጀመሩ፤ ደግሞም 30፣ 60 እና 100 እጥፍ አፈሩ።”
ከዚያም “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ።
ብቻውን በሆነ ጊዜ አሥራ ሁለቱና በዙሪያው የነበሩት ሌሎች ሰዎች ስለ ምሳሌዎቹ ይጠይቁት ጀመር።
እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ለእናንተ የአምላክን መንግሥት ቅዱስ ሚስጥር የመረዳት ችሎታ ተሰጥቷችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን የሚሰሙት ነገር ሁሉ እንዲሁ ምሳሌ ብቻ ሆኖ ይቀርባቸዋል፤
በመሆኑም ማየቱን ያያሉ ግን ልብ አይሉም፤ መስማቱን ይሰማሉ ግን ትርጉሙን አይረዱም፤ ደግሞም ሙሉ በሙሉ ስለማይመለሱ ይቅርታ አያገኙም።”
በተጨማሪም እንዲህ አላቸው፦ “ይህን ምሳሌ ካልተረዳችሁ ታዲያ ሌሎቹን ምሳሌዎች ሁሉ እንዴት ትረዳላችሁ?
“ዘሪው ቃሉን ይዘራል።
ቃሉ ሲዘራ መንገድ ዳር እንደወደቁት ዘሮች የሆኑት እነዚህ ናቸው፤ ቃሉን እንደሰሙ ግን ሰይጣን መጥቶ በውስጣቸው የተዘራውን ቃል ይወስደዋል።
በተመሳሳይም በድንጋያማ መሬት እንደተዘሩት ዘሮች የሆኑት እነዚህ ናቸው፤ ቃሉን እንደሰሙ በደስታ ይቀበሉታል።
ሆኖም ቃሉ በውስጣቸው ሥር ስለማይሰድ የሚቆዩት ለጥቂት ጊዜ ነው፤ ከዚያም በቃሉ የተነሳ መከራ ወይም ስደት ሲደርስባቸው ወዲያውኑ ይሰናከላሉ።
በእሾህ መካከል እንደተዘሩት ዘሮች የሆኑ ሌሎች ደግሞ አሉ። እነዚህ ቃሉን የሰሙ ናቸው፤