text
stringlengths
4
267
ሌላውን ወንድማችሁንና ቢንያምን እንዲለቅላችሁ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የሰውየውን ልብ ያራራላችሁ። እንግዲህ ልጆቼን አጥቼ ለሐዘን ከተዳረግኩም ምን አደርጋለሁ፤ የመጣውን እቀበላለሁ!”
ስለዚህ ሰዎቹ ይህን ስጦታና እጥፍ ገንዘብ እንዲሁም ቢንያምን ይዘው ተነሱ። ወደ ግብፅም ወረዱ፤ እንደገናም ዮሴፍ ፊት ቀረቡ።
ዮሴፍ ቢንያምን ከእነሱ ጋር ሲያየው የቤቱ ኃላፊ የሆነውን ሰው ወዲያውኑ እንዲህ አለው፦ “ሰዎቹን ወደ ቤት ውሰዳቸው፤ አብረውኝ ምሳ ስለሚበሉ እንስሳ አርደህ ምግብ አዘጋጅ።”
ሰውየውም ወዲያውኑ ልክ ዮሴፍ እንዳለው አደረገ፤ ሰዎቹንም ወደ ዮሴፍ ቤት ወሰዳቸው።
ሰዎቹ ግን ወደ ዮሴፍ ቤት ሲወሰዱ ፈሩ፤ እንዲህም ይሉ ጀመር፦ “ወደዚህ ያመጡን ባለፈው ጊዜ በከረጢቶቻችን ውስጥ በተመለሰው ገንዘብ የተነሳ ነው። በቃ አሁን ያሠቃዩናል፤ ባሪያ ያደርጉናል፤ አህዮቻችንንም ይቀሙናል!”
በመሆኑም የዮሴፍ ቤት ኃላፊ ወደሆነው ሰው ቀርበው በቤቱ በራፍ ላይ አነጋገሩት።
እነሱም እንዲህ አሉት፦ “ይቅርታ ጌታዬ! እኛ ባለፈው ጊዜ ወደዚህ የመጣነው እህል ለመግዛት ነበር።
ሆኖም የምናርፍበት ቦታ ደርሰን ከረጢቶቻችንን ስንከፍት የእያንዳንዳችንን ገንዘብ ምንም ሳይጎድል በየከረጢታችን አፍ ላይ አገኘነው። ስለዚህ ራሳችን ገንዘቡን መመለስ እንፈልጋለን።
እህል ለመግዛት ተጨማሪ ገንዘብ ይዘናል። ገንዘባችንን በከረጢታችን ውስጥ መልሶ ያስቀመጠው ማን እንደሆነ አናውቅም።”
እሱም “አይዟችሁ፣ አትፍሩ። ይህን ገንዘብ በከረጢቶቻችሁ ውስጥ ያስቀመጠላችሁ የእናንተ አምላክና የአባታችሁ አምላክ ነው። እኔ እንደሆነ ገንዘባችሁ ደርሶኛል” አላቸው። ከዚያም ስምዖንን አውጥቶ ወደ እነሱ አመጣው።
ከዚያም ሰውየው ሰዎቹን ወደ ዮሴፍ ቤት አስገባቸው፤ እግራቸውን እንዲታጠቡም ውኃ አቀረበላቸው፤ እንዲሁም ለአህዮቻቸው ገፈራ ሰጣቸው።
እነሱም እዚያው ምሳ እንደሚበሉ ስለሰሙ ዮሴፍ ቀትር ላይ ሲመጣ የሚሰጡትን ስጦታ ማዘገጃጀት ጀመሩ።
ዮሴፍ ወደ ቤት ሲገባ፣ ያዘጋጁትን ስጦታ ይዘው ወደ እሱ በመግባት አበረከቱለት፤ መሬት ላይም ተደፍተው ሰገዱለት።
ከዚያም ስለ ደህንነታቸው ጠየቃቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ “ባለፈው ጊዜ የነገራችሁኝ አረጋዊ አባታችሁ ደህና ነው? አሁንም በሕይወት አለ?”
እነሱም “አገልጋይህ አባታችን ደህና ነው። አሁንም በሕይወት አለ” አሉት። ከዚያም መሬት ላይ ተደፍተው ሰገዱ።
ዮሴፍም ቀና ብሎ ሲመለከት የእናቱን ልጅ ወንድሙን ቢንያምን አየ፤ እሱም “ባለፈው ጊዜ ስለ እሱ የነገራችሁኝ ትንሹ ወንድማችሁ ይሄ ነው?” አላቸው። ቢንያምንም “የእኔ ልጅ፣ አምላክ ሞገሱን ያሳይህ” አለው።
ዮሴፍ ወንድሙን ሲያይ ስሜቱን መቆጣጠር ስላቃተው በፍጥነት ወጣ፤ የሚያለቅስበትንም ቦታ ፈለገ። ብቻውን ወደ አንድ ክፍል ገብቶም አለቀሰ።
ከዚያም ፊቱን ተጣጥቦ ወጣ፤ እንደ ምንም ስሜቱን ተቆጣጥሮም “ምግብ ይቅረብ” አለ።
እነሱም ለዮሴፍ ለብቻው አቀረቡለት፤ ለእነሱም ለብቻቸው አቀረቡላቸው። እንዲሁም በቤቱ ለሚበሉት ግብፃውያን ለብቻቸው አቀረቡላቸው። ይህን ያደረጉት ግብፃውያን ከዕብራውያን ጋር አብረው ምግብ ስለማይበሉ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ለግብፃውያን አስጸያፊ ነገር ነው።
ወንድማማቾቹም የበኩሩ እንደ ብኩርና መብቱ፣ ታናሹም እንደ ታናሽነቱ በፊቱ ተቀመጡ፤ እርስ በርሳቸውም በመገረም ይተያዩ ነበር።
እሱም ፊቱ ከቀረበው ምግብ እየተነሳ ለእነሱ እንዲሰጣቸው ያደርግ ነበር፤ የቢንያም ድርሻ ግን ከሌሎቹ አምስት እጥፍ እንዲበልጥ ያደርግ ነበር። እነሱም እስኪጠግቡ ድረስ አብረውት በሉ፣ ጠጡም።
ያዕቆብ በግብፅ እህል መኖሩን ባወቀ ጊዜ ወንዶች ልጆቹን “ለምን ዝም ብላችሁ እርስ በርስ ትተያያላችሁ?” አላቸው።
ከዚያም “በግብፅ እህል እንዳለ ሰምቻለሁ። በሕይወት እንድንኖር ወደዚያ ወርዳችሁ እህል ግዙልን፤ አለዚያ ማለቃችን ነው” አላቸው።
ስለሆነም አሥሩ የዮሴፍ ወንድሞች እህል ለመግዛት ወደ ግብፅ ወረዱ።
ሆኖም ያዕቆብ የዮሴፍን ወንድም ቢንያምን “ምናልባት አደጋ ሊደርስበትና ሊሞትብኝ ይችላል” ብሎ ስላሰበ ከሌሎቹ ወንድሞቹ ጋር አላከውም።
ረሃቡ እስከ ከነአን ምድር ድረስ ተስፋፍቶ ስለነበር የእስራኤል ወንዶች ልጆች እህል ለመግዛት ወደ ግብፅ ከሚመጡት ሰዎች ጋር አብረው መጡ።
በዚያን ጊዜ በምድሩ ላይ አስተዳዳሪ የነበረውና ለምድር ሕዝቦች ሁሉ እህል የሚሸጠው ዮሴፍ ነበር። በመሆኑም የዮሴፍ ወንድሞች መጥተው መሬት ላይ በመደፋት ሰገዱለት።
ዮሴፍም ወንድሞቹን ሲያያቸው ወዲያውኑ አወቃቸው፤ እሱ ግን ማንነቱን ከእነሱ ደበቀ። በመሆኑም “የመጣችሁት ከየት ነው?” በማለት በቁጣ ተናገራቸው፤ እነሱም “እህል ለመግዛት ከከነአን ምድር ነው የመጣነው” አሉት።
ዮሴፍ ወንድሞቹን ያወቃቸው ቢሆንም እነሱ ግን አላወቁትም።
ዮሴፍም ስለ እነሱ ያያቸው ሕልሞች ወዲያው ትዝ አሉት፤ እሱም “እናንተ ሰላዮች ናችሁ! የመጣችሁት ምድሪቱ በየት በኩል ለጥቃት እንደተጋለጠች ለማየት ነው!” አላቸው።
እነሱም እንዲህ አሉት፦ “ኧረ እንደዚያ አይደለም ጌታዬ፤ እኛ አገልጋዮችህ የመጣነው እህል ለመግዛት ነው።
ሁላችንም የአንድ ሰው ልጆች ነን። እኛ ንጹሐን ሰዎች ነን። አገልጋዮችህ ሰላዮች አይደለንም።”
እሱ ግን “በፍጹም አይደለም! የመጣችሁት ምድሪቱ በየት በኩል ለጥቃት እንደተጋለጠች ለማየት ነው!” አላቸው።
በዚህ ጊዜ እንዲህ አሉት፦ “እኛ አገልጋዮችህ 12 ወንድማማቾች ነን። በከነአን ምድር የሚኖር የአንድ ሰው ልጆች ነን፤ ትንሹ ወንድማችን አሁን ከአባታችን ጋር ነው፤ አንደኛው ግን የለም።”
ይሁን እንጂ ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፦ “‘እናንተ ሰላዮች ናችሁ!’ አልኳችሁ እኮ፤
እንግዲህ ሰላዮች መሆን አለመሆናችሁ በዚህ ይረጋገጣል፤ በፈርዖን ሕይወት እምላለሁ፣ ትንሹ ወንድማችሁ ወደዚህ ካልመጣ በስተቀር ከዚህች ንቅንቅ አትሉም።
እናንተ እዚሁ ታስራችሁ እያላችሁ ከመካከላችሁ አንዱን ላኩትና ወንድማችሁን ይዞት ይምጣ። በዚህ መንገድ የተናገራችሁት ነገር እውነት መሆን አለመሆኑ ይረጋገጣል። አለዚያ ግን በፈርዖን ሕይወት እምላለሁ፣ እናንተ ሰላዮች ናችሁ።”
ከዚያም ለሦስት ቀን አንድ ላይ እስር ቤት አቆያቸው።
በሦስተኛውም ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፦ “እንግዲህ እኔ አምላክን ስለምፈራ እንዲህ በማድረግ ሕይወታችሁን አትርፉ።
እንዳላችሁት ንጹሐን ሰዎች ከሆናችሁ ከመካከላችሁ አንዱ ወንድማችሁ እዚሁ እስር ቤት ውስጥ ይቆይ፤ የቀራችሁት ግን ለተራቡት ቤተሰቦቻችሁ እህል ይዛችሁ መሄድ ትችላላችሁ።
የተናገራችሁት ቃል እውነት መሆኑ እንዲረጋገጥና ከሞት እንድትተርፉ ትንሹን ወንድማችሁን ወደ እኔ ይዛችሁት ኑ።” እነሱም እንደተባሉት አደረጉ።
ከዚያም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ “ይህ ሁሉ እየደረሰብን ያለው በወንድማችን ላይ በፈጸምነው ግፍ የተነሳ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም ተጨንቆ እንድንራራለት ሲማጸነን እኛ ግን አልሰማነውም። ይህ ሁሉ መከራ እየደረሰብን ያለው በዚህ ምክንያት ነው።”
በዚህ ጊዜ ሮቤል እንዲህ አላቸው፦ “‘በዚህ ልጅ ላይ ክፉ ነገር አታድርጉ’ ብያችሁ አልነበረም? እናንተ ግን አልሰማችሁኝም። ይኸው አሁን ደሙ ከእጃችን እየተፈለገ ነው።”
ይሁንና ዮሴፍ ያነጋገራቸው በአስተርጓሚ ስለነበር ምን እየተባባሉ እንዳለ እንደሚሰማ አላወቁም ነበር።
በመሆኑም ከፊታቸው ዞር ብሎ አለቀሰ። ከዚያም ወደ እነሱ ተመልሶ በመምጣት በድጋሚ ካነጋገራቸው በኋላ ስምዖንን ከእነሱ ለይቶ በመውሰድ ዓይናቸው እያየ አሰረው።
በኋላም ዮሴፍ በየከረጢቶቻቸው እህል እንዲሞሉላቸው አዘዘ፤ በተጨማሪም የእያንዳንዳቸውን ገንዘብ በየከረጢቶቻቸው መልሰው እንዲያስቀምጡና ለጉዟቸው የሚሆን ስንቅ እንዲሰጧቸው ትእዛዝ አስተላለፈ። ልክ እንዳለውም ተደረገላቸው።
እነሱም እህላቸውን በአህዮቻቸው ላይ ጭነው ጉዞ ጀመሩ።
ከእነሱ መካከል አንዱ ባረፉበት ቦታ ለአህያው መኖ ለመስጠት ከረጢቱን ሲፈታ ገንዘቡን ከረጢቱ አፍ ላይ አገኘው።
እሱም በዚህ ጊዜ ወንድሞቹን “ኧረ ገንዘቤ ተመልሶልኛል፤ ይኸው እዚህ ከረጢቴ ውስጥ አገኘሁት!” አላቸው። እነሱም ልባቸው በፍርሃት ራደ፤ እየተንቀጠቀጡም እርስ በርሳቸው “አምላክ ያደረገብን ይህ ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ።
በከነአን ምድር ወዳለው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ በደረሱም ጊዜ ያጋጠማቸውን ሁሉ እንዲህ በማለት ነገሩት፦
“የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው በቁጣ ተናገረን፤ አገሪቱን ለመሰለል እንደሄድን አድርጎም ቆጠረን።
እኛ ግን እንዲህ አልነው፦ ‘እኛ ንጹሐን ሰዎች ነን። ሰላዮች አይደለንም።
እኛ የአንድ አባት ልጆች የሆን 12 ወንድማማቾች ነን። አንዱ የለም፤ ትንሹ ወንድማችን ደግሞ አሁን ከአባታችን ጋር በከነአን ምድር ይገኛል’፤
ሆኖም የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው እንዲህ አለን፦ ‘እንግዲህ ንጹሐን ሰዎች መሆን አለመሆናችሁን በዚህ አውቃለሁ፤ አንዱ ወንድማችሁ እዚህ እኔ ጋ እንዲቆይ አድርጉ። የቀራችሁት ግን ለተራቡት ቤተሰቦቻችሁ የሆነ ነገር ይዛችሁ ሂዱ።
ንጹሐን ሰዎች እንጂ ሰላዮች አለመሆናችሁንም እንዳውቅ ትንሹን ወንድማችሁን ወደ እኔ ይዛችሁት ኑ። ወንድማችሁንም መልሼ እሰጣችኋለሁ፤ እናንተም በምድሪቱ መነገድ ትችላላችሁ።’”
እያንዳንዳቸውም ከረጢታቸውን ሲያራግፉ ገንዘባቸውን እንደተቋጠረ በከረጢታቸው ውስጥ አገኙት። እነሱም ሆኑ አባታቸው የተቋጠረውን ገንዘብ ሲያዩ ደነገጡ።
አባታቸው ያዕቆብም “ለሐዘን የዳረጋችሁት እኔን ነው! ዮሴፍ የለም፤ ስምዖንም የለም፤ አሁን ደግሞ ቢንያምን ልትወስዱት ነው! ኧረ ምን ጉድ ነው የመጣብኝ!” አላቸው።
ሮቤል ግን አባቱን “ልጁን መልሼ ባላመጣልህ ሁለቱን ወንዶች ልጆቼን ግደላቸው። ለእኔ በኃላፊነት ስጠኝ፤ እኔ ራሴ መልሼ አስረክብሃለሁ” አለው።
እሱ ግን እንዲህ አለ፦ “ልጄ ከእናንተ ጋር ወደዚያ አይወርድም። ምክንያቱም ወንድሙ ሞቷል፤ አሁን የቀረው እሱ ብቻ ነው። ከእናንተ ጋር አብሮ ሲሄድ መንገድ ላይ አደጋ ቢደርስበትና ቢሞት ሽበቴን በሐዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ።”
ሁለት ድፍን ዓመታት ካለፉ በኋላ ፈርዖን በሕልሙ አባይ ወንዝ ዳር ቆሞ አየ።
ከዚያም ቁመናቸው ያማረ ሰባት የሰቡ ላሞች ከአባይ ወንዝ ሲወጡ አየ፤ እነሱም አባይ ወንዝ ዳር ያለውን ሣር ይበሉ ነበር።
ከእነሱም ቀጥሎ አስቀያሚ መልክ ያላቸውና ከሲታ የሆኑ ሌሎች ሰባት ላሞች ከአባይ ወንዝ ወጡ፤ እነሱም አባይ ወንዝ ዳር ከነበሩት የሰቡ ላሞች አጠገብ ቆሙ።
ከዚያም አስቀያሚ መልክ ያላቸው ከሲታ የሆኑት ላሞች ያማረ ቁመና ያላቸውን የሰቡትን ሰባት ላሞች በሏቸው። በዚህ ጊዜ ፈርዖን ከእንቅልፉ ባነነ።
ከዚያም ፈርዖን በድጋሚ እንቅልፍ ወሰደው፤ ለሁለተኛ ጊዜም ሕልም አለመ። በሕልሙም በአንድ አገዳ ላይ የተንዠረገጉና ያማሩ ሰባት የእህል ዛላዎች ሲወጡ አየ።
ከእነሱም በኋላ የቀጨጩና በምሥራቅ ነፋስ የተመቱ ሰባት የእህል ዛላዎች በቀሉ።
የቀጨጩት የእህል ዛላዎች የተንዠረገጉትንና የፋፉትን ሰባት የእህል ዛላዎች ዋጧቸው። በዚህ ጊዜ ፈርዖን ከእንቅልፉ ባነነ፤ ሕልም እንደሆነም ተገነዘበ።
በነጋም ጊዜ መንፈሱ ተረበሸ። በመሆኑም በግብፅ የሚገኙ አስማተኛ ካህናትን በሙሉ እንዲሁም ጥበበኞቿን በሙሉ አስጠራ። ፈርዖንም ያያቸውን ሕልሞች ነገራቸው፤ ሆኖም ለፈርዖን ሕልሞቹን ሊፈታለት የቻለ አንድም ሰው አልነበረም።
በዚህ ጊዜ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ፈርዖንን እንዲህ አለው፦ “ኃጢአቴን ዛሬ ልናዘዝ።
ፈርዖን በአገልጋዮቹ ተቆጥቶ ነበር። በመሆኑም እኔንና የዳቦ ጋጋሪዎቹን አለቃ በዘቦቹ አለቃ ቤት በሚገኘው ወህኒ ቤት ውስጥ አስሮን ነበር።
ከዚያም ሁለታችንም በአንድ ሌሊት ሕልም አለምን። እኔም ሆንኩ እሱ ያለምነው ሕልም የተለያየ ፍቺ ነበረው።
ከእኛም ጋር የዘቦቹ አለቃ አገልጋይ የሆነ አንድ ወጣት ዕብራዊ ነበር። ያየናቸውንም ሕልሞች በነገርነው ጊዜ የእያንዳንዳችንን ሕልም ፈታልን።
ነገሩ ሁሉ ልክ እሱ እንደፈታልን ሆነ። እኔ ወደ ሹመቴ ተመለስኩ፤ ሌላኛው ሰው ግን ተሰቀለ።”
ስለሆነም ፈርዖን ዮሴፍን እንዲያመጡት ሰዎች ላከ፤ እነሱም ከእስር ቤቱ በፍጥነት ይዘውት መጡ። እሱም ተላጭቶና ልብሱን ለውጦ ወደ ፈርዖን ገባ።
ከዚያም ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “ሕልም አይቼ ነበር፤ የሚፈታልኝ ሰው ግን አልተገኘም። አንተ ሕልም ሰምተህ መፍታት እንደምትችል ሰማሁ።”
በዚህ ጊዜ ዮሴፍ ለፈርዖን “ኧረ እኔ እዚህ ግባ የምባል ሰው አይደለሁም! ለፈርዖን መልካም የሆነውን ነገር የሚያሳውቀው አምላክ ነው” ሲል መለሰለት።
ፈርዖንም ለዮሴፍ እንዲህ ሲል ነገረው፦ “በሕልሜ አባይ ወንዝ ዳር ቆሜ ነበር።
ከዚያም ቁመናቸው ያማረ የሰቡ ሰባት ላሞች ከአባይ ወንዝ ሲወጡ አየሁ፤ እነሱም አባይ ወንዝ ዳር ያለውን ሣር ይበሉ ጀመር።
ከእነሱ ቀጥሎም የተጎሳቆሉ እንዲሁም አስቀያሚ ቁመና ያላቸውና ከሲታ የሆኑ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ፤ በመላው የግብፅ ምድር እንደ እነሱ ያሉ አስቀያሚ ላሞች ፈጽሞ አይቼ አላውቅም።
ከዚያም ከሲታ የሆኑት አስቀያሚ ላሞች የመጀመሪያዎቹን ሰባት የሰቡ ላሞች በሏቸው።
ከበሏቸው በኋላም ግን ቁመናቸው ልክ እንደቀድሞው አስቀያሚ ስለነበር ማንም ሰው እንደበሏቸው እንኳ ሊያውቅ አይችልም ነበር። በዚህ ጊዜ ከእንቅልፌ ባነንኩ።
“ከዚያ በኋላ የፋፉና ያማሩ ሰባት የእህል ዛላዎች በአንድ አገዳ ላይ ሲወጡ በሕልሜ አየሁ።
ከእነሱም በኋላ የቀጨጩና በምሥራቅ ነፋስ የተመቱ ሰባት የጠወለጉ የእህል ዛላዎች በቀሉ።
ከዚያም የቀጨጩት የእህል ዛላዎች ያማሩትን ሰባት የእህል ዛላዎች ዋጧቸው። እኔም ሕልሜን አስማተኛ ለሆኑት ካህናት ነገርኳቸው፤ ሆኖም ሊያብራራልኝ የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም።”
ከዚያም ዮሴፍ ፈርዖንን እንዲህ አለው፦ “ሁለቱም የፈርዖን ሕልሞች አንድ ዓይነትና ተመሳሳይ ናቸው። እውነተኛው አምላክ ወደፊት የሚያደርገውን ነገር ለፈርዖን አሳውቆታል።
ሰባቱ ያማሩ ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው። በተመሳሳይም ሰባቱ ያማሩ የእህል ዛላዎች ሰባት ዓመታት ናቸው። ሕልሞቹ አንድ ዓይነትና ተመሳሳይ ናቸው።
ከእነሱ በኋላ የመጡት ሰባቱ ከሲታና አስቀያሚ ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ በምሥራቅ ነፋስ የተመቱት ሰባቱ ፍሬ አልባ የእህል ዛላዎች ረሃብ የሚከሰትባቸው ሰባት ዓመታት ይሆናሉ።
ቀደም ብዬ ለፈርዖን እንደተናገርኩት እውነተኛው አምላክ ወደፊት የሚያደርገውን ነገር ለፈርዖን አሳይቶታል።
“በመላው የግብፅ ምድር እህል እጅግ የሚትረፈረፍባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ።
ከዚያ በኋላ ግን ረሃብ የሚከሰትባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ። በግብፅ ምድር እህል የተትረፈረፈበት ዘመን ፈጽሞ ይረሳል፤ ረሃቡም ምድሪቱን በእጅጉ ይጎዳል።
ከዚያ በኋላ በሚከሰተው ረሃብ የተነሳ በምድሪቱ እህል የተትረፈረፈበት ጊዜ ፈጽሞ አይታወስም፤ ምክንያቱም ረሃቡ በጣም አስከፊ ይሆናል።
ሕልሙ ለፈርዖን ሁለት ጊዜ መታየቱ ነገሩ በእውነተኛው አምላክ ዘንድ የተቆረጠ መሆኑን ያሳያል፤ እውነተኛውም አምላክ ይህን በቅርቡ ይፈጽመዋል።
“ስለሆነም አሁን ፈርዖን ልባምና ጠቢብ የሆነ ሰው ይፈልግና በግብፅ ምድር ላይ ይሹም።
ፈርዖን በምድሪቱ ላይ የበላይ ተመልካቾችን በመሾም እርምጃ ይውሰድ፤ እህል በሚትረፈረፍባቸው ሰባት ዓመታትም በግብፅ ምድር ከሚገኘው ምርት አንድ አምስተኛውን ያከማች።
እነሱም በመጪዎቹ መልካም ዓመታት የሚገኘውን እህል በሙሉ ይሰብስቡ፤ ለምግብነት የሚሆነውንም እህል በፈርዖን ሥልጣን ሥር በየከተማው ያከማቹ፤ የተከማቸውንም እህል ይጠብቁት።
በግብፅ ምድር ረሃብ በሚከሰትባቸው ሰባት ዓመታት ምድሪቱ በረሃቡ እንዳትጠፋ የተከማቸው እህል ለአገሪቱ ነዋሪዎች ይሰጣል።”
ፈርዖንና አገልጋዮቹ በሙሉ ይህን ሐሳብ መልካም ሆኖ አገኙት።
በመሆኑም ፈርዖን አገልጋዮቹን “ታዲያ የአምላክ መንፈስ ያለበት እንዲህ ያለ ሌላ ሰው ሊገኝ ይችላል?” አላቸው።
ከዚያም ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “አምላክ ይህን ሁሉ እንድታውቅ ስላደረገህ እንደ አንተ ያለ ልባምና ጠቢብ ሰው የለም።
አንተው ራስህ በቤቴ ላይ ትሾማለህ፤ ሕዝቤም ሁሉ ያላንዳች ማንገራገር ይታዘዝልሃል። እኔ ከአንተ የምበልጠው ንጉሥ በመሆኔ ብቻ ይሆናል።”
በመቀጠልም ፈርዖን ዮሴፍን “ይኸው በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ሾሜሃለሁ” አለው።