text stringlengths 4 267 |
|---|
በመጨረሻም ዮሴፍ ወንድሞቹን “እኔ ዮሴፍ ነኝ። አባቴ እስካሁን በሕይወት አለ?” አላቸው። ወንድሞቹ ግን በሁኔታው በጣም ስለደነገጡ ምንም ሊመልሱለት አልቻሉም። |
ስለሆነም ዮሴፍ ወንድሞቹን “እባካችሁ ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው። እነሱም ወደ እሱ ቀረቡ። ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “እኔ ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። |
አሁን ግን እኔን ወደዚህ በመሸጣችሁ አትዘኑ፤ እርስ በርሳችሁም አትወቃቀሱ፤ ምክንያቱም አምላክ ከእናንተ አስቀድሞ የላከኝ ሕይወት ለማዳን ሲል ነው። |
ረሃቡ በምድር ላይ ከጀመረ ይህ ሁለተኛ ዓመቱ ነው፤ ምንም የማይታረስባቸውና አዝመራ የማይሰበሰብባቸው አምስት ዓመታት ገና ይቀራሉ። |
አምላክ ግን በምድር ላይ ዘራችሁን ሊያስቀርና በታላቅ ማዳን ሕይወታችሁን ሊታደግ ከእናንተ አስቀድሞ ላከኝ። |
ስለዚህ ለፈርዖን ዋና አማካሪ፣ በቤቱም ሁሉ ላይ ጌታ እንዲሁም በመላው የግብፅ ምድር ላይ ገዢ ሊያደርገኝ ወደዚህ የላከኝ እውነተኛው አምላክ እንጂ እናንተ አይደላችሁም። |
“ቶሎ ብላችሁ ወደ አባቴ ሂዱና እንዲህ በሉት፦ ‘ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ በመላው ግብፅ ላይ ጌታ አድርጎኛል። ሳትዘገይ ወደ እኔ ና። |
ወንዶች ልጆችህን፣ የልጅ ልጆችህን፣ መንጎችህን፣ ከብቶችህንና ያለህን ነገር በሙሉ ይዘህ በመምጣት በአቅራቢያዬ በጎሸን ምድር ትኖራለህ። |
ረሃቡ ገና ለአምስት ዓመታት ስለሚቀጥል እኔ የሚያስፈልግህን ምግብ እሰጥሃለሁ። አለዚያ አንተም ሆንክ ቤትህ እንዲሁም የአንተ የሆነው ሁሉ ችግር ላይ ትወድቃላችሁ።”’ |
እንግዲህ አሁን እያናገርኳችሁ ያለሁት እኔው ራሴ መሆኔን እናንተም ሆናችሁ ወንድሜ ቢንያም በገዛ ዓይናችሁ አይታችኋል። |
በመሆኑም በግብፅ ስላለኝ ክብር ሁሉ እንዲሁም ስላያችሁት ስለ ማንኛውም ነገር ለአባቴ ንገሩት። አሁንም በፍጥነት ሄዳችሁ አባቴን ወደዚህ ይዛችሁት ኑ።” |
ከዚያም በወንድሙ በቢንያም አንገት ላይ ተጠምጥሞ አለቀሰ፤ ቢንያምም አንገቱን አቅፎት አለቀሰ። |
የቀሩትን ወንድሞቹንም አንድ በአንድ እየሳመ አለቀሰ፤ ከዚህ በኋላም ወንድሞቹ ከእሱ ጋር ማውራት ጀመሩ። |
“የዮሴፍ ወንድሞች መጥተዋል!” የሚለው ወሬ በፈርዖን ቤት ተሰማ። ፈርዖንና አገልጋዮቹም ደስ አላቸው። |
ስለዚህ ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “ወንድሞችህን እንዲህ በላቸው፦ ‘እንዲህ አድርጉ፦ የጋማ ከብቶቻችሁን ጫኑና ወደ ከነአን ምድር ሂዱ። |
የግብፅን ምድር መልካም ነገሮች እንድሰጣችሁ አባታችሁንና ቤተሰባችሁን ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ ከዚያም ለም ከሆነው የምድሪቱ ክፍል ትበላላችሁ።’ |
አንተንም እንዲህ ብለህ እንድትነግራቸው አዝዤሃለሁ፦ ‘እንዲህ አድርጉ፦ ልጆቻችሁንና ሚስቶቻችሁን የምታጓጉዙባቸውን ሠረገሎች ከግብፅ ምድር ውሰዱ፤ አባታችሁንም በአንዱ ሠረገላ ላይ ጭናችሁ ወደዚህ ኑ። |
ስለ ንብረታችሁ ምንም አትጨነቁ፤ ምክንያቱም በግብፅ ምድር ያለ ምርጥ ነገር ሁሉ የእናንተው ነው።’” |
የእስራኤልም ወንዶች ልጆች እንደተባሉት አደረጉ፤ ዮሴፍ በፈርዖን ትእዛዝ መሠረት ሠረገሎችን ሰጣቸው፤ ለጉዟቸው የሚሆን ስንቅም አስያዛቸው። |
ለእያንዳንዳቸው ቅያሪ ልብስ ሰጣቸው፤ ለቢንያም ግን 300 የብር ሰቅልና አምስት ቅያሪ ልብስ ሰጠው። |
ለአባቱም የግብፅን ምድር መልካም ነገሮች የጫኑ አሥር አህዮችን እንዲሁም ለጉዞ ስንቅ እንዲሆነው እህል፣ ዳቦና ሌሎች ምግቦችን የጫኑ አሥር እንስት አህዮችን ላከ። |
በዚህ መንገድ ወንድሞቹን ሸኛቸው፤ እነሱም ጉዞ ሲጀምሩ “ደግሞ በመንገድ ላይ እርስ በርስ እንዳትጣሉ” አላቸው። |
እነሱም ከግብፅ ወጥተው ሄዱ፤ በከነአን ምድር ወዳለው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብም መጡ። |
ከዚያም “ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ ደግሞም በመላው የግብፅ ምድር ላይ ገዢ ሆኗል!” ሲሉ ነገሩት። እሱ ግን ክው ብሎ ቀረ፤ ሊያምናቸውም አልቻለም። |
ዮሴፍ የነገራቸውን ነገር በሙሉ ሲነግሩትና ዮሴፍ እሱን ለመውሰድ የላካቸውን ሠረገሎች ሲያይ የአባታቸው የያዕቆብ መንፈስ ታደሰ። |
እስራኤልም “በቃ አምኛችኋለሁ! ልጄ ዮሴፍ በሕይወት አለ! እንግዲህ ከመሞቴ በፊት ሄጄ ዓይኑን ማየት አለብኝ!” አላቸው። |
ሁለቱ መላእክት ምሽት ላይ ሰዶም ደረሱ፤ ሎጥም በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር። እሱም ባያቸው ጊዜ ተነስቶ ወደ እነሱ ሄደ፤ በግንባሩም መሬት ላይ ተደፋ። |
እንዲህም አለ፦ “ጌቶቼ፣ እባካችሁ ወደ አገልጋያችሁ ቤት ጎራ በሉና እደሩ፤ እግራችሁንም ታጠቡ። ከዚያም በማለዳ ተነስታችሁ ጉዟችሁን ትቀጥላላችሁ።” እነሱም መልሰው “አይሆንም፣ አደባባዩ ላይ እናድራለን” አሉ። |
እሱ ግን አጥብቆ ስለለመናቸው አብረውት ወደ ቤቱ ሄዱ። ከዚያም ግብዣ አደረገላቸው። ቂጣም ጋገረላቸው፤ እነሱም በሉ። |
ከመተኛታቸውም በፊት የከተማዋ ሰዎች ማለትም በሰዶም ያሉ ወንዶች ሁሉ ከልጅ እስከ አዋቂ ድረስ ግልብጥ ብለው በመውጣት ቤቱን ከበቡት። |
ሎጥንም ደጋግመው በመጥራት “በዚህ ምሽት ወደ አንተ የመጡት ሰዎች የት አሉ? ከእነሱ ጋር የፆታ ግንኙነት እንድንፈጽም ወደ ውጭ አውጣልን” ይሉት ጀመር። |
ከዚያም ሎጥ ወደ እነሱ ወደ ውጭ ወጣ፤ በሩንም ከኋላው ዘጋው። |
እንዲህም አላቸው፦ “እባካችሁ ወንድሞቼ፣ እንዲህ ያለ ክፉ ድርጊት አትፈጽሙ። |
እባካችሁ፣ ከወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽመው የማያውቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ። እባካችሁ፣ እነሱን ላውጣላችሁና መልካም መስሎ የታያችሁን አድርጉባቸው። እነዚህ ሰዎች ግን በጣሪያዬ ጥላ ሥር ስለተጠለሉ በእነሱ ላይ ምንም ነገር አታድርጉ።” |
በዚህ ጊዜ ሰዎቹ “ዞር በል!” አሉት። ከዚያም “ይህ ወገን የሌለው መጤ፣ ደግሞ በእኛ ላይ ዳኛ ልሁን ይላል እንዴ! በእነሱ ላይ ልናደርግ ካሰብነው የከፋ ነገር እንዳናደርግብህ” አሉት። ሎጥንም በኃይል ገፉት፤ በሩንም ሊሰብሩት ተቃረቡ። |
ስለሆነም ውስጥ የነበሩት ሰዎች እጃቸውን ወደ ውጭ ዘርግተው ሎጥን እነሱ ወዳሉበት ወደ ቤት አስገቡት፤ በሩንም ዘጉት። |
ሆኖም በቤቱ ደጃፍ ላይ የነበሩትን ሰዎች ከትንሹ አንስቶ እስከ ትልቁ ድረስ አሳወሯቸው፤ በዚህም የተነሳ ሰዎቹ በሩን ለማግኘት ሲዳክሩ ደከሙ። |
ከዚያም ሰዎቹ ሎጥን እንዲህ አሉት፦ “እዚህ የሚኖሩ ሌሎች ዘመዶች አሉህ? አማቾችህን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህን እንዲሁም በከተማዋ ውስጥ የሚኖር ዘመድ አዝማድህን በሙሉ ከዚህ ስፍራ ይዘህ ውጣ! |
ይህን ስፍራ ልናጠፋው ነው፤ ምክንያቱም ሕዝቦቿን በተመለከተ የሚሰማው ጩኸት በይሖዋ ፊት እየጨመረ ስለመጣ ይሖዋ ከተማዋን እንድናጠፋት ልኮናል።” |
በመሆኑም ሎጥ ወጥቶ የሴት ልጆቹ እጮኛ የሆኑትን አማቾቹን “ተነሱ! ይሖዋ ከተማዋን ሊያጠፋት ስለሆነ ከዚህ ስፍራ ውጡ!” አላቸው። አማቾቹ ግን የሚያሾፍ መሰላቸው። |
ጎህ ሲቀድ መላእክቱ ሎጥን “ተነስ! በከተማዋ በደል የተነሳ እንዳትጠፋ ከአንተ ጋር ያሉትን ሚስትህንና ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ይዘህ ውጣ!” በማለት አቻኮሉት። |
ሎጥ በዘገየ ጊዜ ይሖዋ ስለራራለት ሰዎቹ የእሱን እጅ፣ የሚስቱን እጅና የሁለቱን ሴቶች ልጆቹን እጅ ይዘው ከከተማዋ አስወጡት። |
ልክ ከተማዋ ዳርቻ ላይ እንዳደረሷቸውም ከእነሱ አንዱ እንዲህ አለ፦ “ሕይወትህን ለማትረፍ ሽሽ! ወደ ኋላህ እንዳትመለከት፤ አውራጃውንም ለቀህ እስክትወጣ ድረስ የትኛውም ቦታ ላይ እንዳትቆም! እንዳትጠፋ ወደ ተራራማው አካባቢ ሽሽ!” |
ከዚያም ሎጥ እንዲህ አላቸው፦ “እባክህ ይሖዋ፣ ወደዚያስ አልሂድ! |
መቼም አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ አግኝቷል፤ ሕይወቴን በማትረፍ ታላቅ ደግነት አሳይተኸኛል፤ ሆኖም አደጋ እንዳይደርስብኝና እንዳልሞት ስለምፈራ ወደ ተራራማው አካባቢ ሸሽቼ ማምለጥ አልችልም። |
እባክህ ይህች ከተማ ቅርብ ነች፤ ወደዚያ መሸሽ እችላለሁ፤ ትንሽ ስፍራ እኮ ናት። እባክህ፣ ወደዚያ መሸሽ እችላለሁ? ትንሽ ስፍራ እኮ ናት። እንደዚያ ከሆነ እተርፋለሁ።” |
እሱም እንዲህ አለው፦ “እሺ ይሁን፣ ያልካትን ከተማ ባለማጥፋት አሁንም አሳቢነት አሳይሃለሁ። |
ፍጠን! አንተ እዚያ እስክትደርስ ድረስ ምንም ነገር ማድረግ ስለማልችል ወደዚያ ሽሽ!” ከተማዋን ዞአር ብሎ የሰየማት ለዚህ ነው። |
ሎጥ ዞአር ሲደርስ ፀሐይ በምድሩ ላይ ወጥታ ነበር። |
ከዚያም ይሖዋ በሰዶምና በገሞራ ላይ እሳትና ድኝ አዘነበ፤ ይህም የመጣው ከሰማይ ከይሖዋ ዘንድ ነው። |
እሱም እነዚህን ከተሞች ገለባበጠ፤ አዎ፣ የከተሞቹን ነዋሪዎችና የምድሪቱን ተክል ሁሉ ጨምሮ መላውን አውራጃ ገለባበጠ። |
ሆኖም ከሎጥ በስተ ኋላ የነበረችው የሎጥ ሚስት ወደ ኋላ ዞራ መመልከት ጀመረች፤ እሷም የጨው ዓምድ ሆነች። |
አብርሃምም በማለዳ ተነሳ፤ ቀደም ሲል በይሖዋ ፊት ቆሞ ወደነበረበትም ስፍራ ሄደ። |
ወደ ሰዶምና ወደ ገሞራ እንዲሁም በአውራጃው ውስጥ ወዳሉት ከተሞች በሙሉ ቁልቁል ሲያይም የሚያስገርም ነገር ተመለከተ። ከእቶን እንደሚወጣ ያለ የሚትጎለጎል ጭስ ከምድሩ እየተትጎለጎለ ይወጣ ነበር! |
አምላክ የአውራጃውን ከተሞች ባጠፋበት ጊዜ ሎጥ ይኖርባቸው ከነበሩትና አምላክ ካጠፋቸው ከተሞች ውስጥ ሎጥን በማውጣት አብርሃምን አሰበው። |
በኋላም ሎጥ በዞአር መኖር ስለፈራ ከዞአር ወጥቶ ከሁለቱ ሴቶች ልጆቹ ጋር በተራራማው አካባቢ መኖር ጀመረ። ስለዚህ ከሁለቱ ሴቶች ልጆቹ ጋር በዋሻ ውስጥ መኖር ጀመረ። |
የመጀመሪያዋ ልጅ ታናሿን እንዲህ አለቻት፦ “አባታችን አርጅቷል፤ በመላው ምድር ላይ ባለው ልማድ መሠረት ከእኛ ጋር ግንኙነት የሚፈጽም ወንድ በዚህ አካባቢ የለም። |
ነይ፣ አባታችንን የወይን ጠጅ እናጠጣውና ከእሱ ጋር እንተኛ፤ እንዲህ በማድረግ ከአባታችን ዘር እናስቀር።” |
በመሆኑም በዚያ ምሽት አባታቸውን ደጋግመው የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ከዚያም የመጀመሪያዋ ልጅ ገብታ ከአባቷ ጋር ተኛች። እሱ ግን ስትተኛም ሆነ ስትነሣ አላወቀም። |
በማግስቱም የመጀመሪያዋ ልጅ ታናሿን እንዲህ አለቻት፦ “ይኸው እኔ ትናንት ሌሊት ከአባቴ ጋር ተኝቻለሁ። ዛሬ ማታም የወይን ጠጅ እናጠጣው። ከዚያም አንቺ ገብተሽ ከእሱ ጋር ትተኚያለሽ። እንዲህ በማድረግ ከአባታችን ዘር እናስቀር።” |
በመሆኑም በዚያ ምሽትም አባታቸውን ደጋግመው የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ከዚያም ታናሽየዋ ልጅ ሄዳ ከአባቷ ጋር ተኛች። እሱ ግን ስትተኛም ሆነ ስትነሳ አላወቀም። |
ስለሆነም ሁለቱም የሎጥ ሴቶች ልጆች ከአባታቸው ፀነሱ። |
ታላቅየዋም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሞዓብ አለችው፤ እሱም ዛሬ ያሉት ሞዓባውያን አባት ነው። |
ታናሽየዋም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ቤንአሚ አለችው፤ እሱም ዛሬ ያሉት አሞናውያን አባት ነው። |
ያዕቆብም ቀና ብሎ ሲመለከት ኤሳው ሲመጣ አየ፤ ከእሱም ጋር 400 ሰዎች ነበሩ። በመሆኑም ልጆቹን ለሊያ፣ ለራሔልና ለሁለቱ ሴት አገልጋዮች አከፋፈላቸው። |
እሱም ሴት አገልጋዮቹንና ልጆቻቸውን ከፊት፣ ሊያንና ልጆቿን ከእነሱ ቀጥሎ፣ ራሔልንና ዮሴፍን ደግሞ ከእነሱ በኋላ እንዲሆኑ አደረገ። |
ከዚያም እሱ ቀድሟቸው ሄደ፤ ወደ ወንድሙ ሲቀርብም ሰባት ጊዜ ወደ መሬት ዝቅ ብሎ ሰገደ። |
ሆኖም ኤሳው ወደ እሱ እየሮጠ በመሄድ አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ሳመው፤ ሁለቱም ተላቀሱ። |
ኤሳውም ቀና ብሎ ሴቶቹንና ልጆቹን ሲያይ እንዲህ አለ፦ “እነዚህ አብረውህ ያሉት እነማን ናቸው?” እሱም “አምላክ በቸርነቱ ለአገልጋይህ የሰጣቸው ልጆች ናቸው” አለው። |
በዚህ ጊዜ ሴት አገልጋዮቹ ከልጆቻቸው ጋር ወደ ፊት ቀርበው ሰገዱ፤ |
ሊያና ልጆቿም ወደ ፊት ቀርበው ሰገዱ። ከዚያም ዮሴፍና ራሔል ወደ ፊት ቀርበው ሰገዱ። |
ኤሳውም “ቀደም ሲል ያገኘኋቸውን ሰዎችና እንስሳት የላክሃቸው ለምንድን ነው?” አለው። እሱም “በጌታዬ ፊት ሞገስ ባገኝ ብዬ ነው” አለው። |
ከዚያም ኤሳው “ወንድሜ ሆይ፣ እኔ ከበቂ በላይ አለኝ። የአንተ የሆነው ለራስህ ይሁን” አለው። |
ያዕቆብ ግን እንዲህ አለው፦ “የለም፣ እንዲህማ አይሆንም። በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ ስጦታዬን ከእጄ መውሰድ አለብህ፤ ምክንያቱም ስጦታውን የላክሁት ፊትህን እንዳይ ብዬ ነው። እንዲህ በደስታ ተቀብለኸኝ የአንተን ፊት ማየቴ ራሱ ለእኔ የአምላክን ፊት የማየት ያህል ነው። |
አምላክ ሞገስ ስላሳየኝና የሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ ስላለኝ የመልካም ምኞት መግለጫ እንዲሆን ያመጣሁልህን ይህን ስጦታ እባክህ ተቀበለኝ።” ያዕቆብም አጥብቆ ለመነው፤ ስለዚህ ስጦታውን ወሰደ። |
በኋላም ኤሳው “በል እንነሳና ጉዟችንን እንቀጥል፤ እኔም ከፊት ከፊትህ እሄዳለሁ” አለው። |
እሱ ግን እንዲህ አለው፦ “ልጆቹ አቅም እንደሌላቸው እንዲሁም የሚያጠቡ በጎችና ከብቶች እንዳሉኝ ጌታዬ ያውቃል። እንስሳቱ ለአንድ ቀን እንኳ በጥድፊያ ቢነዱ መንጋው በሙሉ ያልቃል። |
ስለዚህ ጌታዬ ከአገልጋዩ ቀድሞ ይሂድ፤ እኔ ግን ከጌታዬ ጋር እዚያው ሴይር እስከምንገናኝ ድረስ በምነዳቸው ከብቶች ፍጥነትና እንደ ልጆቹ እርምጃ ቀስ እያልኩ ላዝግም።” |
ኤሳውም “እባክህ ከእኔ ጋር ካሉት ሰዎች መካከል ጥቂቶቹን ልተውልህ” አለው። እሱም “ለምን ብለህ? በጌታዬ ፊት ሞገስ ማግኘቴ ብቻ ይበቃኛል” አለው። |
በመሆኑም በዚያ ቀን ኤሳው ወደ ሴይር ለመመለስ ጉዞ ጀመረ። |
ያዕቆብም ወደ ሱኮት ሄደ፤ በዚያም ለራሱ ቤት፣ ለመንጎቹም ዳስ ሠራ። የቦታውንም ስም ሱኮት ያለው ለዚህ ነበር። |
ያዕቆብ ከጳዳንአራም ተነስቶ በመጓዝ በከነአን ምድር ወደምትገኘው ወደ ሴኬም ከተማ በሰላም ደረሰ፤ በከተማዋም አቅራቢያ ሰፈረ። |
ከዚያም ድንኳኑን የተከለበትን ቦታ ከሴኬም አባት ከኤሞር ወንዶች ልጆች እጅ በ100 ጥሬ ገንዘብ ገዛ። |
በዚያም መሠዊያ አቆመ፤ መሠዊያውንም አምላክ፣ የእስራኤል አምላክ ብሎ ጠራው። |
በዚህ ጊዜ፣ ምድር ሁሉ አንድ ቋንቋና ተመሳሳይ ቃላት ትጠቀም ነበር። |
ወደ ምሥራቅ ሲጓዙም በሰናኦር ምድር ወደሚገኝ አንድ ሸለቋማ ሜዳ ደረሱ፤ በዚያም መኖር ጀመሩ። |
እርስ በርሳቸውም “ኑ! ጡብ እንሥራ፤ በእሳትም እንተኩሰው” ይባባሉ ጀመር። በመሆኑም በድንጋይ ፋንታ ጡብ፣ ለማያያዣም ቅጥራን ተጠቀሙ። |
ከዚያም “ኑ! በመላው ምድር ላይ እንዳንበተን ከተማና ጫፉ ሰማይ የሚደርስ ግንብ ለራሳችን እንገንባ፤ ስማችንንም እናስጠራ” ተባባሉ። |
ከዚያም ይሖዋ ሰዎች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ። |
ይሖዋም እንዲህ አለ፦ “እነዚህ ሰዎች አንድ ቋንቋ የሚናገሩ አንድ ሕዝብ ናቸው፤ ይኸው አሁን ደግሞ ይህን መሥራት ጀምረዋል። በዚህ ከቀጠሉ ያሰቡትን ሁሉ ከማከናወን የሚያግዳቸው ምንም ነገር አይኖርም። |
ና! እንውረድና በቋንቋ እርስ በርስ እንዳይግባቡ ቋንቋቸውን እናዘበራርቅ።” |
በመሆኑም ይሖዋ ከዚያ ቦታ ተነስተው በመላው ምድር ላይ እንዲበተኑ አደረገ፤ እነሱም ቀስ በቀስ ከተማዋን መገንባታቸውን አቆሙ። |
የከተማዋ ስም ባቤል የተባለውም በዚህ የተነሳ ነው፤ ምክንያቱም ይሖዋ በዚያ የምድርን ሁሉ ቋንቋ አዘበራርቋል፤ እንዲሁም ይሖዋ ሰዎቹ ከዚያ ቦታ ተነስተው በመላው ምድር ላይ እንዲበተኑ አድርጓል። |
የሴም ታሪክ ይህ ነው። ሴም የጥፋት ውኃ ከተከሰተ ከሁለት ዓመት በኋላ አርፋክስድን ሲወልድ የ100 ዓመት ሰው ነበር። |
ሴም አርፋክስድን ከወለደ በኋላ 500 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። |
አርፋክስድ 35 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሴሎምን ወለደ። |
አርፋክስድ ሴሎምን ከወለደ በኋላ 403 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። |
ሴሎም 30 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ኤቤርን ወለደ። |
ሴሎም ኤቤርን ከወለደ በኋላ 403 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። |
ኤቤር 34 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ፋሌቅን ወለደ። |
Subsets and Splits
No community queries yet
The top public SQL queries from the community will appear here once available.