text
stringlengths
4
267
ስለዚህ ፈውስ ማግኘት እንድትችሉ አንዳችሁ ለሌላው ኃጢአታችሁን በግልጽ ተናዘዙ፤ እንዲሁም አንዳችሁ ለሌላው ጸልዩ። ጻድቅ ሰው የሚያቀርበው ምልጃ ታላቅ ኃይል አለው።
ኤልያስ እንደ እኛው ዓይነት ስሜት ያለው ሰው ነበር፤ ያም ሆኖ ዝናብ እንዳይዘንብ አጥብቆ በጸለየ ጊዜ በምድሩ ላይ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ዝናብ አልዘነበም።
ከዚያም እንደገና ጸለየ፤ ሰማዩም ዝናብ ሰጠ፤ ምድሩም ፍሬ አፈራ።
ወንድሞቼ፣ ከእናንተ መካከል አንድ ሰው ከእውነት መንገድ ስቶ ቢወጣና ሌላ ሰው ቢመልሰው፣
ኃጢአተኛን ከስህተት ጎዳናው የሚመልስ ማንኛውም ሰው ኃጢአተኛውን ከሞት እንደሚያድንና ብዙ ኃጢአትን እንደሚሸፍን እወቁ።
በእናንተ መካከል ያለው ጦርነትና ጠብ ከየት የመጣ ነው? በውስጣችሁ ከሚዋጉት ሥጋዊ ፍላጎቶቻችሁ የመነጨ አይደለም?
ትመኛላችሁ ሆኖም አታገኙም። ትገድላላችሁ እንዲሁም ትጎመጃላችሁ፤ ይሁንና ማግኘት አትችሉም። ትጣላላችሁ እንዲሁም ትዋጋላችሁ። ስለማትጠይቁም አታገኙም።
በምትጠይቁበት ጊዜም አታገኙም፤ ምክንያቱም የምትጠይቁት ለተሳሳተ ዓላማ ይኸውም ሥጋዊ ፍላጎታችሁን ለማርካት ነው።
አመንዝሮች ሆይ፣ ከዓለም ጋር መወዳጀት ከአምላክ ጋር ጠላትነት መፍጠር እንደሆነ አታውቁም? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ራሱን የአምላክ ጠላት ያደርጋል።
ወይስ ቅዱስ መጽሐፉ “በውስጣችን ያደረው መንፈስ በቅናት ሁልጊዜ ይመኛል” ያለው ያለምክንያት ይመስላችኋል?
ይሁን እንጂ አምላክ የሚሰጠው ጸጋ እንዲህ ካለው መንፈስ የላቀ ነው። በመሆኑም ቅዱስ መጽሐፉ “አምላክ ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል።
ስለዚህ ራሳችሁን ለአምላክ አስገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል።
ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች እጆቻችሁን አንጹ፤ እናንተ ወላዋዮች ልባችሁን አጥሩ።
ተጨነቁ፣ እዘኑ፣ አልቅሱ። ሳቃችሁ ወደ ሐዘን፣ ደስታችሁም ወደ ተስፋ መቁረጥ ይለወጥ።
በይሖዋ ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል።
ወንድሞች፣ አንዳችሁ ሌላውን መንቀፋችሁን ተዉ። ወንድሙን የሚነቅፍ ወይም በወንድሙ ላይ የሚፈርድ ሁሉ ሕግን ይነቅፋል እንዲሁም በሕግ ላይ ይፈርዳል። በሕግ ላይ የምትፈርድ ከሆነ ደግሞ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን ፈጻሚ አይደለህም።
ሕግ የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ብቻ ነው፤ እሱ ማዳንም ሆነ ማጥፋት ይችላል። ታዲያ በባልንጀራህ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?
እንግዲህ እናንተ “ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህች ከተማ እንሄዳለን፤ እዚያም ዓመት እንቆያለን፤ እንነግዳለን እንዲሁም እናተርፋለን” የምትሉ ስሙ፤
ሕይወታችሁ ነገ ምን እንደሚሆን እንኳ አታውቁም። ለጥቂት ጊዜ ታይቶ እንደሚጠፋ እንፋሎት ናችሁና።
ከዚህ ይልቅ “ይሖዋ ከፈቀደ በሕይወት እንኖራለን፤ ደግሞም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን” ማለት ይገባችኋል።
አሁን ግን እናንተ ከልክ በላይ ጉራ በመንዛት ትኩራራላችሁ። እንዲህ ያለው ጉራ ሁሉ ክፉ ነው።
ስለዚህ አንድ ሰው ትክክል የሆነውን ነገር እንዴት ማድረግ እንዳለበት እያወቀ ሳያደርገው ቢቀር ኃጢአት ይሆንበታል።
የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጴጥሮስ፤ በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በእስያና በቢቲኒያ ተበትነው ለሚገኙ፣ ጊዜያዊ ነዋሪዎች ለሆኑ የአምላክ ምርጦች፣
ይኸውም አባት የሆነው አምላክ አስቀድሞ ባወቀው መሠረት ለተመረጡት ደግሞም ታዛዥ እንዲሆኑና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም እንዲረጩ በመንፈስ ለተቀደሱት፦ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይወደስ፤ እሱ በታላቅ ምሕረቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካኝነት ለሕያው ተስፋ እንደ አዲስ ወልዶናልና፤
እንዲሁም ለማይበሰብስ፣ ለማይረክስና ለማይጠፋ ርስት ወልዶናል። ይህም በሰማይ ለእናንተ ተጠብቆላችኋል፤
እናንተንም አምላክ በዘመኑ መጨረሻ ለሚገለጠው መዳን በእምነት አማካኝነት በኃይሉ እየጠበቃችሁ ነው።
አሁን ለአጭር ጊዜ በልዩ ልዩ ፈተናዎች መጨነቃችሁ የግድ ቢሆንም በእነዚህ ሁሉ ነገሮች የተነሳ እጅግ እየተደሰታችሁ ነው፤
እነዚህ ፈተናዎች የሚደርሱባችሁ፣ በእሳት የተፈተነ ቢሆንም እንኳ ሊጠፋ ከሚችለው ወርቅ እጅግ የላቀ ዋጋ ያለውና ተፈትኖ የተረጋገጠው እምነታችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን፣ ግርማንና ክብርን ያስገኝ ዘንድ ነው።
እሱን አይታችሁት ባታውቁም ትወዱታላችሁ። አሁን ባታዩትም እንኳ በእሱ ላይ እምነት እያሳያችሁና በቃላት ሊገለጽ በማይችል ታላቅ ደስታ እጅግ ሐሴት እያደረጋችሁ ነው፤
ምክንያቱም የእምነታችሁ ግብ ላይ እንደምትደርሱ ይኸውም ራሳችሁን እንደምታድኑ ታውቃላችሁ።
ለእናንተ ስለሚሰጠው ጸጋ የተነበዩት ነቢያት ይህን መዳን በተመለከተ ትጋት የተሞላበት ምርምርና ጥልቅ ጥናት አካሂደዋል።
በውስጣቸው ያለው መንፈስ በክርስቶስ ላይ ስለሚደርሱት መከራዎችና ከዚያ በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ ሲመሠክር ከክርስቶስ ጋር በተያያዘ ስለ የትኛው ጊዜ ወይም ወቅት እያመለከተ እንዳለ ይመረምሩ ነበር።
እነሱ ራሳቸውን እያገለገሉ እንዳልሆነ ተገልጦላቸው ነበር። ከዚህ ይልቅ ከሰማይ በተላከ መንፈስ ቅዱስ ምሥራቹን ባበሰሩላችሁ ሰዎች አማካኝነት ከተነገሯችሁ ነገሮች ጋር በተያያዘ እናንተን እያገለገሉ ነበር። መላእክትም እነዚህን ነገሮች ለማየት ይጓጓሉ።
በመሆኑም አእምሯችሁን ዝግጁ በማድረግ ለሥራ ታጠቁ፤ የማስተዋል ስሜታችሁን በሚገባ ጠብቁ፤ ተስፋችሁን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ በምታገኙት ጸጋ ላይ አድርጉ።
ታዛዥ ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን ቀድሞ እውቀት ባልነበራችሁ ጊዜ ትከተሉት በነበረው ምኞት መሠረት መቀረጻችሁን አቁሙ፤
ከዚህ ይልቅ የጠራችሁ ቅዱስ አምላክ፣ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እናንተም በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤
“እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ተብሎ ተጽፏልና።
ደግሞም ምንም ሳያዳላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት የምትለምኑ ከሆነ ጊዜያዊ ነዋሪዎች ሆናችሁ በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ አምላክን በመፍራት ኑሩ።
እናንተ ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከንቱ አኗኗር ነፃ የወጣችሁት ሊበላሹ በሚችሉ ነገሮች ይኸውም በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁና።
ከዚህ ይልቅ ነፃ የወጣችሁት ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ ደም ባለ ውድ ደም ይኸውም በክርስቶስ ደም ነው።
እርግጥ እሱ አስቀድሞ የታወቀው፣ ዓለም ከመመሥረቱ በፊት ነው፤ ሆኖም ለእናንተ ሲባል በዘመናት መጨረሻ ላይ እንዲገለጥ ተደረገ።
እናንተም እምነታችሁና ተስፋችሁ በአምላክ ላይ ይሆን ዘንድ እሱን ከሞት ባስነሳውና ክብር ባጎናጸፈው አምላክ ያመናችሁት በእሱ አማካኝነት ነው።
እንግዲህ ለእውነት በመታዘዝ ራሳችሁን ስላነጻችሁ ግብዝነት የሌለበት የወንድማማች መዋደድ አላችሁ፤ በመሆኑም እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ።
ሕያው በሆነውና ጸንቶ በሚኖረው አምላክ ቃል አማካኝነት እንደ አዲስ የተወለዳችሁት በሚበሰብስ ሳይሆን በማይበሰብስ ዘር ነው።
“ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ነውና፤ ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነው፤ ሣሩ ይጠወልጋል፤ አበባውም ይረግፋል፤
የይሖዋ ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” ለእናንተም የተሰበከላችሁ ምሥራች ይህ “ቃል” ነው።
በተመሳሳይም እናንተ ሚስቶች፣ ለቃሉ የማይታዘዙ ባሎች ካሉ ያለቃል በሚስቶቻቸው ምግባር እንዲማረኩ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤
ሊማረኩ የሚችሉትም ንጹሕ ምግባራችሁንና የምታሳዩትን ጥልቅ አክብሮት ሲመለከቱ ነው።
ውበታችሁ በውጫዊ ነገሮች በማጌጥ ይኸውም ሹሩባ በመሠራት፣ የወርቅ ጌጣጌጦች በማድረግ ወይም ያማረ ልብስ በመልበስ አይሁን፤
ከዚህ ይልቅ ውበታችሁ የማይጠፋውን ጌጥ ይኸውም በአምላክ ፊት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውን የሰከነና ገር መንፈስ የተላበሰ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁን።
ተስፋቸውን በአምላክ ላይ የጣሉ በቀድሞ ጊዜ የነበሩ ቅዱሳን ሴቶች ራሳቸውን ለባሎቻቸው በማስገዛት በዚህ ዓይነት ሁኔታ ራሳቸውን ያስውቡ ነበርና፤
ሣራም አብርሃምን ጌታዬ እያለች በመጥራት ትታዘዘው ነበር። እናንተም መልካም ማድረጋችሁን ከቀጠላችሁና በፍርሃት ካልተሸነፋችሁ ልጆቿ ናችሁ።
በተመሳሳይም እናንተ ባሎች ከእነሱ ጋር በእውቀት አብራችሁ ኑሩ። እነሱም ከእናንተ ጋር የሕይወትን ጸጋ አብረው ስለሚወርሱ ጸሎታችሁ እንዳይታገድ ከእናንተ ይበልጥ እንደ ተሰባሪ ዕቃ የሆኑትን ሴቶችን አክብሯቸው።
በመጨረሻም ሁላችሁም የአስተሳሰብ አንድነት ይኑራችሁ፤ የሌላውን ስሜት የምትረዱ ሁኑ፤ የወንድማማች መዋደድ ይኑራችሁ፤ ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ ትሑታን ሁኑ።
ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ አትመልሱ። ከዚህ ይልቅ ባርኩ፤ የተጠራችሁት ይህን ጎዳና በመከተል በረከትን እንድትወርሱ ነውና።
ስለዚህ “ሕይወትን የሚወድና መልካም ቀኖችን ማየት የሚፈልግ ሰው በምላሱ ክፉ ነገር ከመናገር፣ በከንፈሩም ከማታለል ይቆጠብ።
ክፉ ከሆነ ነገር ይራቅ፤ መልካም የሆነውንም ያድርግ፤ ሰላምን ይፈልግ፤ ይከተለውም።
የይሖዋ ዓይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉና፤ ጆሮዎቹም ምልጃቸውን ይሰማሉ፤ የይሖዋ ፊት ግን ክፉ ነገሮችን በሚያደርጉ ላይ ነው።”
መልካም ነገር ለማድረግ ቀናተኞች ብትሆኑ ጉዳት የሚያደርስባችሁ ማን ነው?
ሆኖም ለጽድቅ ስትሉ መከራ ብትቀበሉ ደስተኞች ናችሁ። ይሁን እንጂ እነሱ የሚፈሩትን እናንተ አትፍሩ፤ ደግሞም አትሸበሩ።
ነገር ግን ክርስቶስን እንደ ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ፣ ምክንያት እንድታቀርቡ ለሚጠይቃችሁ ሰው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁ ሁኑ፤ ይህን ስታደርጉ ግን በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት ይሁን።
ስለ እናንተ መጥፎ ነገር የሚናገሩ ሰዎች፣ የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችሁ መጠን በምታሳዩት መልካም ምግባር የተነሳ ስለ እናንተ በሚናገሩት በማንኛውም መጥፎ ነገር እንዲያፍሩ ጥሩ ሕሊና ይኑራችሁ።
ክፉ ነገር ሠርታችሁ መከራ ከምትቀበሉ ይልቅ የአምላክ ፈቃድ ከሆነ፣ መልካም ነገር ሠርታችሁ መከራ ብትቀበሉ ይሻላልና።
ጻድቅ የሆነው ክርስቶስ እንኳ ለዓመፀኞች ሲል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመሞት ከኃጢአት ነፃ አውጥቷቸዋልና። ይህን ያደረገው እናንተን ወደ አምላክ ለመምራት ነው። ሥጋ ሆኖ ተገደለ፤ ሆኖም መንፈስ ሆኖ ሕያው ሆነ።
በዚህ ሁኔታ እያለም ሄዶ በእስር ላሉት መናፍስት ሰበከላቸው፤
እነዚህ መናፍስት ቀደም ሲል ማለትም በኖኅ ዘመን ጥቂት ሰዎች ይኸውም ስምንት ነፍሳት በውኃው መካከል አልፈው የዳኑበት መርከብ እየተሠራ በነበረበት ጊዜ፣ አምላክ በትዕግሥት እየጠበቀ ሳለ ሳይታዘዙ የቀሩ ናቸው።
አሁንም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነው ጥምቀት በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካኝነት እናንተን እያዳናችሁ ነው። ጥምቀት የሰውነትን እድፍ የሚያስወግድ ሳይሆን ጥሩ ሕሊና ለማግኘት ለአምላክ የሚቀርብ ልመና ነው።
ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሄደ ሲሆን አሁን በአምላክ ቀኝ ይገኛል፤ እንዲሁም መላእክት፣ ሥልጣናትና ኃይላት እንዲገዙለት ተደርጓል።
እንግዲህ ክፋትን ሁሉ፣ ማታለልን፣ ግብዝነትን፣ ቅናትንና ሐሜትን ሁሉ አስወግዱ።
ገና እንደተወለዱ ሕፃናት በአምላክ ቃል ውስጥ ለሚገኘው ያልተበረዘ ወተት ጉጉት አዳብሩ፤ ይህም በእሱ አማካኝነት ወደ መዳን ማደግ እንድትችሉ ነው፤
ጌታ ደግ መሆኑን ቀምሳችኋልና።
በሰዎች ወደተናቀው በአምላክ ግን ወደተመረጠውና በፊቱ ክቡር ወደሆነው ወደ እሱ ይኸውም ሕያው ወደሆነው ድንጋይ በመምጣት
እናንተ ራሳችሁ ቅዱሳን ካህናት ለመሆን እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ለመሆን እየተገነባችሁ ነው፤ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መንፈሳዊ መሥዋዕት ማቅረብ ትችሉ ዘንድ ነው።
ምክንያቱም ቅዱስ መጽሐፉ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ በጽዮን የተመረጠ ድንጋይ ይኸውም ክቡር የሆነ የማዕዘን የመሠረት ድንጋይ አኖራለሁ፤ ደግሞም በእሱ የሚያምን ሁሉ ፈጽሞ አያፍርም።”
በመሆኑም እናንተ አማኞች ስለሆናችሁ እሱ ለእናንተ ክቡር ነው፤ የማያምኑትን በተመለከተ ግን እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፦ “ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ እሱ የማዕዘን ራስ ድንጋይ ሆነ”፤
እንዲሁም “የሚያደናቅፍ ድንጋይና የሚያሰናክል ዓለት ሆነ።” እነሱ የሚሰናከሉት ለቃሉ ስለማይታዘዙ ነው። እነዚህ ሰዎች የሚጠብቃቸው ነገር ይኸው ነው።
እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእሱን “ድንቅ ባሕርያት በየቦታው እንድታውጁ የተመረጠ ዘር፣ ንጉሣዊ ካህናት፣ ቅዱስ ብሔር፣ ልዩ ንብረት እንዲሆን የተለየ ሕዝብ” ናችሁ።
እናንተ በአንድ ወቅት የአምላክ ሕዝብ አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የአምላክ ሕዝብ ናችሁ፤ ቀደም ሲል ምሕረት አልተደረገላችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረት አግኝታችኋል።
የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ የባዕድ አገር ሰዎችና ጊዜያዊ ነዋሪዎች እንደመሆናችሁ መጠን እናንተን ከሚዋጉት ሥጋዊ ፍላጎቶች ምንጊዜም እንድትርቁ አሳስባችኋለሁ።
ክፉ አድራጊዎች እንደሆናችሁ አድርገው ሲከሷችሁ መልካም ሥራችሁን በዓይናቸው ማየት እንዲችሉ ብሎም አምላክ ለመመርመር በሚመጣበት ቀን እሱን እንዲያከብሩ በዓለም ባሉ ሰዎች መካከል መልካም ምግባር ይኑራችሁ።
ለጌታ ብላችሁ ለሰብዓዊ ሥልጣን ሁሉ ተገዙ፦ የበላይ ስለሆነ ለንጉሥ ተገዙ፤
ደግሞም ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣት፣ መልካም የሚያደርጉትን ግን ለማመስገን በእሱ የተላኩ ስለሆኑ ለገዢዎች ተገዙ።
የአምላክ ፈቃድ፣ መልካም ነገር በማድረግ ከንቱ ንግግር የሚናገሩትን ምክንያታዊ ያልሆኑ ሰዎች አፍ ዝም እንድታሰኙ ነውና።
እንደ ነፃ ሰዎች ኑሩ፤ ነፃነታችሁን እንደ አምላክ ባሪያዎች ሆናችሁ ተጠቀሙበት እንጂ ለክፋት መሸፈኛ አታድርጉት።
ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ፤ ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ፤ አምላክን ፍሩ፤ ንጉሥን አክብሩ።
አገልጋዮች ጥሩና ምክንያታዊ ለሆኑት ብቻ ሳይሆን በቀላሉ ለማይደሰቱ ጌቶቻቸውም እንኳ ተገቢ ፍርሃት በማሳየት ይገዙ።
አንድ ሰው በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረው ሲል መከራን ችሎ ቢያሳልፍና ግፍ ቢደርስበት ይህ ደስ የሚያሰኝ ነውና።
ኃጢአት በመሥራታችሁ የሚደርስባችሁን ዱላ ብትቋቋሙ ምን ጥቅም አለው? መልካም ነገር በማድረጋችሁ መከራ ሲደርስባችሁ ችላችሁ ብታሳልፉ ግን ይህ አምላክ ደስ የሚሰኝበት ነገር ነው።
ደግሞም የተጠራችሁት በዚህ ጎዳና እንድትሄዱ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስም እንኳ የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራ ተቀብሏል።
እሱ ምንም ኃጢአት አልሠራም፤ በአንደበቱም የማታለያ ቃል አልተገኘም።
ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም። መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን በአደራ ሰጠ።
ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እሱ ራሱ በገዛ አካሉ ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ። ደግሞም “በእሱ ቁስል እናንተ ተፈወሳችሁ።”
እናንተ እንደባዘኑ በጎች ነበራችሁና፤ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።
ስለዚህ እኔም እንደ እነሱ ሽማግሌ እንዲሁም የክርስቶስ መከራ ምሥክርና ወደፊት የሚገለጠው ክብር ተካፋይ እንደመሆኔ መጠን በመካከላችሁ ያሉትን ሽማግሌዎች እንዲህ በማለት አጥብቄ እለምናለሁ፦
የበላይ ተመልካቾች ሆናችሁ በማገልገል በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክን መንጋ እንደ እረኛ ጠብቁ፤ ሥራችሁን በግዴታ ሳይሆን በአምላክ ፊት በፈቃደኝነት ተወጡ፤ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በመመኘት ሳይሆን ለማገልገል በመጓጓት፣
የአምላክ ንብረት በሆኑት ላይ ሥልጣናችሁን በማሳየት ሳይሆን ለመንጋው ምሳሌ በመሆን ጠብቁ።
የእረኞች አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማይጠፋ የክብር አክሊል ትቀበላላችሁ።
በተመሳሳይም እናንተ ወጣቶች፣ ለሽማግሌዎች ተገዙ። ይሁንና እርስ በርስ ባላችሁ ግንኙነት ሁላችሁም ትሕትናን ልበሱ፤ ምክንያቱም አምላክ ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።
ስለዚህ በተገቢው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው የአምላክ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤