text stringlengths 4 267 |
|---|
ከመልከጼዴቅ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ለዘላለም ሊቀ ካህናት የሆነው ኢየሱስ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ስለ እኛ ወደዚያ ገብቷል። |
እንግዲህ የምንናገረው ነገር ዋና ነጥብ ይህ ነው፦ በሰማያት በግርማዊው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ |
እሱም የቅዱሱ ስፍራና የእውነተኛው ድንኳን አገልጋይ ነው፤ ይህም ድንኳን በሰው ሳይሆን በይሖዋ የተተከለ ነው። |
እያንዳንዱ ሊቀ ካህናት የሚሾመው ስጦታና መሥዋዕት ለማቅረብ ነውና፤ በመሆኑም ይሄኛው ሊቀ ካህናትም የሚያቀርበው ነገር ያስፈልገዋል። |
እሱ ምድር ላይ ቢሆን ኖሮ ካህን ባልሆነ ነበር፤ ምክንያቱም ሕጉ በሚያዘው መሠረት ስጦታ የሚያቀርቡ ሰዎች አሉ። |
እነዚህ ሰዎች ለሰማያዊ ነገሮች ዓይነተኛ አምሳያና ጥላ የሆነ ቅዱስ አገልግሎት ያቀርባሉ፤ ይህም የሆነው ሙሴ ድንኳኑን ለመሥራት በተዘጋጀ ጊዜ “በተራራው ላይ ተገልጦልህ ባየኸው ንድፍ መሠረት ሁሉንም ነገር በጥንቃቄ ሥራ” ተብሎ ከተሰጠው መለኮታዊ ትእዛዝ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ነው። |
ይሁንና ኢየሱስ እጅግ የላቀ አገልግሎት ተቀብሏል፤ ልክ እንደዚሁም ለተሻለ ቃል ኪዳን መካከለኛ ሆኗል፤ ይህም ቃል ኪዳን በተሻሉ ተስፋዎች ላይ በሕግ የጸና ነው። |
የመጀመሪያው ቃል ኪዳን ምንም ጉድለት ባይኖረው ኖሮ ሁለተኛ ቃል ኪዳን ባላስፈለገ ነበር። |
አምላክ በሕዝቡ ላይ ጉድለት ስላገኘ እንዲህ ብሎ ተናግሯልና፦ “‘እነሆ፣ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ጊዜ ይመጣል’ ይላል ይሖዋ። |
‘ይህም ቃል ኪዳን አባቶቻቸውን እጃቸውን ይዤ ከግብፅ ምድር እየመራሁ ባወጣኋቸው ቀን ከእነሱ ጋር እንደገባሁት ዓይነት ቃል ኪዳን አይሆንም፤ ምክንያቱም እነሱ በቃል ኪዳኔ አልጸኑም፤ በመሆኑም ችላ አልኳቸው’ ይላል ይሖዋ። |
“‘ከዚያ ጊዜ በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና’ ይላል ይሖዋ። ‘ሕግጋቴን በአእምሯቸው ውስጥ አኖራለሁ፤ በልባቸውም ላይ እጽፋቸዋለሁ። እኔም አምላካቸው እሆናለሁ፤ እነሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። |
“‘እነሱም እያንዳንዳቸው የአገራቸውን ሰው፣ እያንዳንዳቸውም ወንድማቸውን “ይሖዋን እወቅ!” ብለው ከእንግዲህ አያስተምሩም። ከትንሹ አንስቶ እስከ ትልቁ ድረስ ሁሉም ያውቁኛልና። |
ለክፉ ሥራቸው ምሕረት አደርግላቸዋለሁና፤ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስም።’” |
“አዲስ ቃል ኪዳን” ሲል የቀድሞውን ቃል ኪዳን ጊዜ ያለፈበት አድርጎታል። ስለዚህ ጊዜ ያለፈበትና እያረጀ ያለው ቃል ኪዳን ሊጠፋ ተቃርቧል። |
የአምላክና የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የሆነው ያዕቆብ፣ በየቦታው ለተበተኑት ለ12ቱ ነገዶች፦ ሰላምታ ይድረሳችሁ! |
ወንድሞቼ ሆይ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት፤ |
ይህን ስታደርጉ ተፈትኖ የተረጋገጠው እምነታችሁ ጽናት እንደሚያስገኝ ታውቃላችሁ። |
ይሁንና በሁሉም ረገድ ምንም የማይጎድላችሁ ፍጹማንና እንከን የለሽ እንድትሆኑ ጽናት ሥራውን ሙሉ በሙሉ ይፈጽም። |
እንግዲህ ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤ አምላክ ማንንም ሳይነቅፍ ለሁሉም በልግስና ይሰጣልና፤ ይህም ሰው ይሰጠዋል። |
ሆኖም ምንም ሳይጠራጠር በእምነት መለመኑን ይቀጥል፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ እንደሚገፋና እንደሚናወጥ የባሕር ማዕበል ነውና። |
እንዲያውም እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከይሖዋ አንዳች ነገር አገኛለሁ ብሎ መጠበቅ የለበትም፤ |
ይህ ሰው በሁለት ሐሳብ የሚዋልልና በመንገዱ ሁሉ የሚወላውል ነው። |
ይሁንና ዝቅ ያለው ወንድም ከፍ በመደረጉ ደስ ይበለው፤ |
እንዲሁም ባለጸጋ የሆነው ዝቅ በመደረጉ ደስ ይበለው፤ ምክንያቱም ባለጸጋ ሰው እንደ ሜዳ አበባ ይረግፋል። |
ፀሐይ ወጥታ በኃይለኛ ሙቀቷ ተክሉን ታጠወልጋለች፤ አበባውም ይረግፋል፤ ውበቱም ይጠፋል፤ ባለጸጋ ሰውም ልክ እንደዚሁ በዕለት ተዕለት ተግባሩ ሲዋትት ከስሞ ይጠፋል። |
ፈተናን በጽናት ተቋቁሞ የሚኖር ሰው ደስተኛ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ሰው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት በሚያገኝበት ጊዜ፣ ይሖዋ እሱን ለሚወዱት ቃል የገባውን የሕይወት አክሊል ይቀበላል። |
ማንም ሰው ፈተና ሲደርስበት “አምላክ እየፈተነኝ ነው” አይበል። አምላክ በክፉ ነገር ሊፈተን አይችልምና፤ እሱ ራሱም ማንንም በክፉ ነገር አይፈትንም። |
ሆኖም እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል። |
ከዚያም ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአት ሲፈጸም ደግሞ ሞት ያስከትላል። |
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ አትታለሉ። |
መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ ከላይ ነው፤ ይህ የሚወርደው ከሰማይ ብርሃናት አባት ሲሆን እሱ ደግሞ ቦታውን እንደሚቀያይር ጥላ አይለዋወጥም። |
ፈቃዱ ስለሆነም ከፍጥረታቱ መካከል እኛ እንደ በኩራት እንድንሆን በእውነት ቃል አማካኝነት ወለደን። |
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ይህን እወቁ፦ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና ለቁጣ የዘገየ መሆን አለበት፤ |
የሰው ቁጣ የአምላክ ጽድቅ እንዲፈጸም አያደርግምና። |
ስለዚህ ጸያፍ የሆነውን ነገር ሁሉና ክፋትን ሁሉ አስወግዳችሁ እናንተን ሊያድን የሚችለውን በውስጣችሁ የሚተከለውን ቃል በገርነት ተቀበሉ። |
ሆኖም ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ የውሸት ምክንያት እያቀረባችሁ ራሳችሁን በማታለል ሰሚዎች ብቻ አትሁኑ። |
ማንም ሰው ቃሉን የሚሰማ እንጂ የማያደርገው ከሆነ የገዛ ፊቱን በመስተዋት እያየ ካለ ሰው ጋር ይመሳሰላል። |
ይህ ሰው ራሱን ካየ በኋላ ይሄዳል፤ ወዲያውም ምን እንደሚመስል ይረሳል። |
ሆኖም ነፃ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ በትኩረት የሚመለከትና በዚያ የሚጸና ሰው ሰምቶ የሚረሳ ሳይሆን በሥራ ላይ የሚያውል ሰው ነው፤ በሚያደርገውም ነገር ደስተኛ ይሆናል። |
አንድ ሰው አምላክን እያመለከ እንዳለ ቢያስብም እንኳ አንደበቱን የማይገታ ከሆነ ይህ ሰው የገዛ ልቡን ያታልላል፤ አምልኮውም ከንቱ ነው። |
በአምላካችንና በአባታችን ዓይን ንጹሕና ያልረከሰ አምልኮ ‘ወላጅ አልባ የሆኑ ልጆችንና መበለቶችን በመከራቸው መርዳት እንዲሁም ከዓለም እድፍ ራስን መጠበቅ’ ነው። |
ወንድሞቼ ሆይ፣ ከእናንተ መካከል ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ፤ ምክንያቱም እኛ የባሰ ፍርድ እንደምንቀበል ታውቃላችሁ። |
ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለንና። በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር ይህ ሰው መላ ሰውነቱንም መቆጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው። |
ፈረሶች እንዲታዘዙልን አፋቸው ውስጥ ልጓም ካስገባን መላ ሰውነታቸውንም መምራት እንችላለን። |
መርከቦችንም ተመልከቱ፦ በጣም ትልቅና በኃይለኛ ነፋስ የሚነዱ ቢሆኑም የመርከቡ ነጂ በትንሽ መሪ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ሁሉ ይመራቸዋል። |
ልክ እንደዚሁም ምላስ ትንሽ የአካል ክፍል ሆና ሳለ ጉራዋን ትነዛለች። በጣም ሰፊ የሆነን ጫካ በእሳት ለማያያዝ ትንሽ እሳት ብቻ ይበቃል! |
ምላስም እሳት ናት። ምላስ በአካል ክፍሎቻችን መካከል የክፋትን ዓለም ትወክላለች፤ መላ ሰውነትን ታረክሳለችና፤ እንዲሁም መላውን የሕይወት ጎዳና ታቃጥላለች፤ እሷም በገሃነም ትቃጠላለች። |
ማንኛውም ዓይነት የዱር እንስሳ፣ ወፍ፣ በምድር ላይ የሚሳብ ፍጥረትና በባሕር ውስጥ የሚኖር ፍጥረት በሰዎች ሊገራ ይችላል፤ ደግሞም ተገርቷል። |
ምላስን ግን ሊገራ የሚችል አንድም ሰው የለም። ምላስ ገዳይ መርዝ የሞላባት፣ ለመቆጣጠር የምታስቸግር ጎጂ ነገር ናት። |
በምላሳችን አባት የሆነውን ይሖዋን እናወድሳለን፤ ይሁንና በዚህችው ምላሳችን “በአምላክ አምሳል” የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን። |
ከአንድ አፍ በረከትና እርግማን ይወጣሉ። ወንድሞቼ፣ ይህ መሆኑ ተገቢ አይደለም። |
አንድ ምንጭ ከዚያው ጉድጓድ ጣፋጭና መራራ ውኃ ያፈልቃል? |
ወንድሞቼ፣ የበለስ ዛፍ ወይራን ወይም ደግሞ የወይን ተክል በለስን ሊያፈራ ይችላል? ከጨዋማ ውኃም ጣፋጭ ውኃ ሊገኝ አይችልም። |
ከእናንተ መካከል ጥበበኛና አስተዋይ ሰው ማን ነው? ሥራውን የሚያከናውነው ከጥበብ በመነጨ ገርነት መሆኑን በመልካም ምግባሩ ያሳይ። |
ሆኖም በልባችሁ ውስጥ መራራ ቅናትና ጠበኝነት ካለ አትኩራሩ፤ እንዲሁም በእውነት ላይ አትዋሹ። |
ይህ ከሰማይ የሚመጣ ጥበብ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ምድራዊ፣ እንስሳዊና አጋንንታዊ ነው። |
ቅናትና ጠበኝነት ባለበት ሁሉ ብጥብጥና መጥፎ ነገሮችም ይኖራሉ። |
ከሰማይ የሆነው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት እንዲሁም አድልዎና ግብዝነት የሌለበት ነው። |
ከዚህም በላይ የጽድቅ ፍሬ ሰላም ፈጣሪ ለሆኑ ሰዎች ሰላማዊ በሆኑ ሁኔታዎች ይዘራል። |
ወንድሞቼ ሆይ፣ በአንድ በኩል ክብር በተጎናጸፈው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የምታምኑ ሆናችሁ በሌላ በኩል ደግሞ አድልዎ ታደርጋላችሁ? |
በጣቶቹ ላይ የወርቅ ቀለበቶች ያደረገና ያማረ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ስብሰባችሁ ቢመጣና ያደፈ ልብስ የለበሰ ድሃ ሰውም እንደዚሁ ወደ ስብሰባው ቢገባ |
ያማረ ልብስ ለለበሰው ሰው አክብሮት በማሳየት “እዚህ የተሻለው ቦታ ላይ ተቀመጥ” ድሃውን ደግሞ “አንተ እዚያ ቁም” ወይም “እዚህ ከእግሬ ማሳረፊያ በታች ተቀመጥ” ትሉታላችሁ? |
እንዲህ የምትሉ ከሆነ በመካከላችሁ የመደብ ልዩነት እንዲኖር ማድረጋችሁ አይደለም? ደግሞስ ክፉ ፍርድ የምትፈርዱ ፈራጆች መሆናችሁ አይደለም? |
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ስሙ። አምላክ በእምነት ባለጸጋ እንዲሆኑና እሱን ለሚወዱ ቃል የገባውን መንግሥት እንዲወርሱ ከዓለም አመለካከት አንጻር ድሆች የሆኑትን አልመረጠም? |
እናንተ ግን ድሃውን ሰው አዋረዳችሁ። እናንተን የሚጨቁኗችሁና ጎትተው ፍርድ ቤት የሚያቀርቧችሁ ሀብታሞች አይደሉም? |
እናንተ የተጠራችሁበትን መልካም ስም የሚሳደቡት እነሱ አይደሉም? |
እንግዲያው በቅዱስ መጽሐፉ መሠረት “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለውን ንጉሣዊ ሕግ ተግባራዊ የምታደርጉ ከሆነ መልካም እያደረጋችሁ ነው። |
ማዳላታችሁን የማትተዉ ከሆነ ግን ኃጢአት እየሠራችሁ ነው፤ ሕጉም ሕግ ተላላፊዎች ናችሁ ብሎ ይፈርድባችኋል። |
አንድ ሰው ሕጉን ሁሉ የሚጠብቅ ሆኖ ሳለ አንዱን ትእዛዝ ሳይጠብቅ ቢቀር ሁሉንም እንደጣሰ ይቆጠራል። |
“አታመንዝር” ያለው እሱ “አትግደል” የሚል ትእዛዝም ሰጥቷልና። እንግዲህ ምንዝር ባትፈጽምም እንኳ ከገደልክ ሕግ ተላላፊ ሆነሃል። |
ነፃ በሆኑ ግለሰቦች ሕግ የሚዳኙ ሰዎች በሚናገሩበት መንገድ መናገራችሁንና እነሱ እንደሚያደርጉት ማድረጋችሁን ቀጥሉ። |
ምሕረት የማያደርግ ሰው ያለምሕረት ይፈረድበታልና። ምሕረት በፍርድ ላይ ድል ይቀዳጃል። |
ወንድሞቼ ሆይ፣ አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ነገር ግን እምነቱ በሥራ የተደገፈ ባይሆን ምን ጥቅም ይኖረዋል? እምነቱ ሊያድነው ይችላል? |
አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት የሚለብሱት ቢያጡና ለዕለት የሚያስፈልጋቸውን በቂ ምግብ ባያገኙ |
ሆኖም ከመካከላችሁ አንዱ “በሰላም ሂዱ፤ ይሙቃችሁ፤ ጥገቡም” ቢላቸው ለሰውነታቸው የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ግን ባይሰጣቸው ምን ይጠቅማቸዋል? |
ስለዚህ በሥራ ያልተደገፈ እምነትም በራሱ የሞተ ነው። |
ይሁን እንጂ አንድ ሰው እንዲህ ይላል፦ “አንተ እምነት አለህ፤ እኔ ደግሞ ሥራ አለኝ። እምነትህን ከሥራ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔ ደግሞ እምነቴን በሥራ አሳይሃለሁ።” |
አንድ አምላክ እንዳለ ታምናለህ አይደል? ማመንህ መልካም ነው። ይሁንና አጋንንትም ያምናሉ፤ በፍርሃትም ይንቀጠቀጣሉ። |
አንተ ከንቱ ሰው፣ እምነት ያለሥራ እንደማይጠቅም ማረጋገጥ ትፈልጋለህ? |
አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያ ላይ ካቀረበ በኋላ የጸደቀው በሥራ አይደለም? |
እምነቱ ከሥራው ጋር አብሮ ይሠራ እንደነበረና ሥራው እምነቱን ፍጹም እንዳደረገው ትገነዘባለህ፤ |
ደግሞም “አብርሃም በይሖዋ አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት” የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል ተፈጸመ፤ እሱም የይሖዋ ወዳጅ ለመባል በቃ። |
እንግዲህ ሰው የሚጸድቀው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራም ጭምር እንደሆነ ትገነዘባላችሁ። |
ዝሙት አዳሪዋ ረዓብም መልእክተኞቹን በጥሩ ሁኔታ ተቀብላ ካስተናገደቻቸውና በሌላ መንገድ ከላከቻቸው በኋላ በሥራ አልጸደቀችም? |
በእርግጥም አካል ያለመንፈስ የሞተ እንደሆነ ሁሉ እምነትም ያለሥራ የሞተ ነው። |
እናንተ ሀብታሞች እንግዲህ ስሙ፤ እየመጣባችሁ ባለው መከራ አልቅሱ እንዲሁም ዋይ ዋይ በሉ። |
ሀብታችሁ በስብሷል፤ ልብሳችሁንም ብል በልቶታል። |
ወርቃችሁና ብራችሁ ሙሉ በሙሉ ዝጓል፤ ዝገቱም በእናንተ ላይ ይመሠክራል፤ ሥጋችሁንም ይበላል። ያከማቻችሁት ነገር በመጨረሻዎቹ ቀናት እንደ እሳት ይሆናል። |
እነሆ፣ በእርሻችሁ ላይ ያለውን ሰብል ለሰበሰቡት ሠራተኞች ሳትከፍሏቸው የቀራችሁት ደሞዝ ይጮኻል፤ አጫጆቹም ለእርዳታ የሚያሰሙት ጥሪ ወደ ሠራዊት ጌታ ወደ ይሖዋ ጆሮ ደርሷል። |
በምድር ላይ በቅንጦት ኖራችኋል፤ የራሳችሁንም ፍላጎት ለማርካት ትጥሩ ነበር። በእርድ ቀን ልባችሁን አወፍራችኋል። |
ጻድቁን ኮነናችሁት፤ ደግሞም ገደላችሁት። እሱ እየተቃወማችሁ አይደለም? |
እንግዲህ ወንድሞች፣ ጌታ እስከሚገኝበት ጊዜ ድረስ በትዕግሥት ጠብቁ። እነሆ፣ ገበሬ የመጀመሪያውና የኋለኛው ዝናብ እስኪመጣ ድረስ በመታገሥ የምድርን መልካም ፍሬ ይጠባበቃል። |
እናንተም በትዕግሥት ጠብቁ፤ ጌታ የሚገኝበት ጊዜ ስለተቃረበ ልባችሁን አጽኑ። |
ወንድሞች፣ እንዳይፈረድባችሁ አንዳችሁ በሌላው ላይ አታጉረምርሙ። እነሆ፣ ፈራጁ ደጃፍ ላይ ቆሟል። |
ወንድሞች፣ በይሖዋ ስም የተናገሩትን ነቢያት መከራ በመቀበልና ትዕግሥት በማሳየት ረገድ አርዓያ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው። |
እነሆ፣ የጸኑትን ደስተኞች እንደሆኑ አድርገን እንቆጥራቸዋለን። ስለ ኢዮብ ጽናት ሰምታችኋል፤ በውጤቱም ይሖዋ ያደረገለትን አይታችኋል፤ በዚህም ይሖዋ እጅግ አፍቃሪና መሐሪ እንደሆነ ተመልክታችኋል። |
ከሁሉም በላይ ወንድሞቼ፣ በሰማይም ሆነ በምድር ወይም በሌላ መሐላ መማላችሁን ተዉ። ከዚህ ይልቅ “አዎ” ካላችሁ አዎ ይሁን፤ “አይደለም” ካላችሁ አይደለም ይሁን፤ አለዚያ ለፍርድ ትዳረጋላችሁ። |
ከእናንተ መካከል መከራ እየደረሰበት ያለ ሰው አለ? መጸለዩን ይቀጥል። ደስ የተሰኘ አለ? የምስጋና መዝሙር ይዘምር። |
ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው አለ? የጉባኤ ሽማግሌዎችን ወደ እሱ ይጥራ፤ እነሱም በይሖዋ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። |
በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል፤ ይሖዋም ያስነሳዋል። በተጨማሪም ኃጢአት ሠርቶ ከሆነ ይቅር ይባላል። |
Subsets and Splits
No community queries yet
The top public SQL queries from the community will appear here once available.