text
stringlengths
4
267
እንግዲህ እነዚህ ይቅር ከተባሉ፣ ከዚህ በኋላ ለኃጢአት መባ ማቅረብ አያስፈልግም።
ስለዚህ ወንድሞች፣ በኢየሱስ ደም አማካኝነት ወደ ቅዱሱ ስፍራ በሚወስደው መንገድ ለመግባት የሚያስችል ድፍረት አግኝተናል፤
እሱ የከፈተልን ይህ መንገድ ወደ ሕይወት የሚመራ አዲስ መንገድ ነው። ይህን ያደረገው በመጋረጃው ማለትም በሥጋው በኩል በማለፍ ነው፤
በተጨማሪም በአምላክ ቤት ላይ የተሾመ ታላቅ ሊቀ ካህናት ስላለን
ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን እንዲሁም ሰውነታችንን በንጹሕ ውኃ ታጥበን በቅን ልቦና እና በሙሉ እምነት ወደ አምላክ እንቅረብ።
የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ስለሆነ ተስፋችንን በይፋ ለማወጅ የሚያስችለንን አጋጣሚ ያላንዳች ማወላወል አጥብቀን እንያዝ።
እንዲሁም እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤
አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት መሰብሰባችንን ቸል አንበል፤ ከዚህ ይልቅ እርስ በርስ እንበረታታ፤ ደግሞም ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ ይህን እናድርግ።
የእውነትን ትክክለኛ እውቀት ካገኘን በኋላ ሆን ብለን በኃጢአት ጎዳና ብንመላለስ ለኃጢአታችን የሚቀርብ ሌላ መሥዋዕት አይኖርም፤
ከዚህ ይልቅ አስፈሪ ፍርድ ይጠብቀናል፤ አምላክን የሚቃወሙትን የሚበላ የሚነድ ቁጣም ይኖራል።
የሙሴን ሕግ የጣሰ ማንኛውም ሰው ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ከመሠከሩበት ያለርኅራኄ ይገደል ነበር።
ታዲያ የአምላክን ልጅ የረገጠ፣ የተቀደሰበትን የቃል ኪዳኑን ደም እንደ ተራ ነገር የቆጠረና የጸጋን መንፈስ በንቀት ያጥላላ ሰው ምን ያህል የከፋ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል?
“በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” ያለውን እናውቀዋለንና። ደግሞም “ይሖዋ ሕዝቡን ይዳኛል።”
በሕያው አምላክ እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነገር ነው።
ይሁን እንጂ ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ በመከራ ውስጥ በከፍተኛ ተጋድሎ የጸናችሁበትን የቀድሞውን ጊዜ ዘወትር አስታውሱ።
በአደባባይ ለነቀፋና ለመከራ የተጋለጣችሁባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ ደግሞም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የደረሰባቸውን ሰዎች መከራ የተጋራችሁባቸው ጊዜያት ነበሩ።
እናንተ ራሳችሁ የተሻለና ዘላቂ የሆነ ንብረት እንዳላችሁ ስለምታውቁ በእስር ላይ ላሉት ራራችሁላቸው፤ እንዲሁም ንብረታችሁ ሲዘረፍ ሁኔታውን በደስታ ተቀበላችሁ።
እንግዲህ ትልቅ ወሮታ የሚያስገኘውን በድፍረት የመናገር ነፃነታችሁን አሽቀንጥራችሁ አትጣሉት።
የአምላክን ፈቃድ ከፈጸማችሁ በኋላ የተስፋው ቃል ሲፈጸም ማየት እንድትችሉ መጽናት ያስፈልጋችኋልና።
ምክንያቱም “ለጥቂት ጊዜ ነው” እንጂ “የሚመጣው እሱ ይመጣል፤ ደግሞም አይዘገይም።”
“ሆኖም ጻድቅ አገልጋዬ በእምነት ይኖራል”፤ ደግሞም “ወደኋላ ቢያፈገፍግ በእሱ ደስ አልሰኝም።”
እንግዲህ እኛ በሕይወት የሚያኖር እምነት እንዳላቸው ሰዎች ነን እንጂ ወደ ጥፋት እንደሚያፈገፍጉ ሰዎች አይደለንም።
ከሰዎች መካከል የተመረጠ እያንዳንዱ ሊቀ ካህናት ለኃጢአት መባና መሥዋዕት ያቀርብ ዘንድ እነሱን በመወከል የአምላክን አገልግሎት ለማከናወን ይሾማል።
እሱ ራሱ ድክመት ስላለበት አላዋቂ የሆኑትንና የሚሳሳቱትን በርኅራኄ ሊይዛቸው ይችላል፤
በዚህም የተነሳ ለሕዝቡ የኃጢአት መባ እንደሚያቀርብ ሁሉ ለራሱም ለማቅረብ ይገደዳል።
አንድ ሰው ይህን የክብር ቦታ የሚያገኘው እንደ አሮን፣ አምላክ ሲጠራው ብቻ ነው እንጂ በራሱ ፈቃድ አይደለም።
ክርስቶስም ሊቀ ካህናት በመሆን ራሱን ከፍ ከፍ አላደረገም፤ ከዚህ ይልቅ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድኩህ” ብሎ ስለ እሱ የተናገረው፣ ከፍ ከፍ አደረገው።
ደግሞም በሌላ ቦታ ላይ “እንደ መልከጼዴቅ፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ብሏል።
ክርስቶስ በምድር ላይ በኖረበት ዘመን ከሞት ሊያድነው ለሚችለው በከፍተኛ ለቅሶና እንባ ምልጃና ልመና አቀረበ፤ አምላካዊ ፍርሃት ስለነበረውም ጸሎቱ ተሰማለት።
ልጅ ቢሆንም እንኳ ከደረሰበት መከራ መታዘዝን ተማረ።
በዚህም ፍጹም ከሆነ በኋላ የሚታዘዙት ሁሉ ዘላለማዊ መዳን እንዲያገኙ ምክንያት ሆነላቸው፤
ምክንያቱም ከመልከጼዴቅ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ አምላክ ሊቀ ካህናት አድርጎ ሾሞታል።
እሱን በተመለከተ ብዙ የምንናገረው ነገር አለን፤ ይሁንና ጆሯችሁ ስለደነዘዘ ለማስረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው።
በአሁኑ ጊዜ አስተማሪዎች ልትሆኑ ይገባችሁ የነበረ ቢሆንም የአምላክን ቅዱስ መልእክት መሠረታዊ ነገሮች እንደገና ከመጀመሪያ ጀምሮ የሚያስተምራችሁ ሰው ትፈልጋላችሁ፤ ደግሞም ጠንካራ ምግብ ከመመገብ ይልቅ እንደገና ወተት መፈለግ ጀምራችኋል።
ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለሆነ ከጽድቅ ቃል ጋር ትውውቅ የለውም።
ጠንካራ ምግብ ግን ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት ላሠለጠኑ ጎልማሳ ሰዎች ነው።
ስለዚህ ወደ እረፍቱ የመግባት ተስፋ አሁንም ስላለ ከእናንተ መካከል ማንም ለዚያ የማይበቃ ሆኖ እንዳይገኝ እንጠንቀቅ።
ለአባቶቻችን ተሰብኮ እንደነበረው ሁሉ ምሥራቹ ለእኛም ተሰብኳልና፤ እነሱ ግን ሰምተው የታዘዙት ሰዎች የነበራቸው ዓይነት እምነት ስላልነበራቸው የሰሙት ቃል አልጠቀማቸውም።
እኛ ግን እምነት በማሳየታችን ወደዚህ እረፍት እንገባለን። ምንም እንኳ የእሱ ሥራ ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የተጠናቀቀ ቢሆንም “‘ወደ እረፍቴ አይገቡም’ ብዬ በቁጣዬ ማልኩ” ብሏል።
በአንድ ቦታ ላይ ሰባተኛውን ቀን አስመልክቶ “አምላክም በሰባተኛው ቀን ከሥራው ሁሉ አረፈ” ብሏልና፤
እንደገና እዚህ ላይ “ወደ እረፍቴ አይገቡም” ብሏል።
ስለዚህ ገና ወደ እረፍቱ የሚገቡ ስላሉና መጀመሪያ ምሥራቹ የተሰበከላቸው ባለመታዘዛቸው ምክንያት ሳይገቡ ስለቀሩ
ከረጅም ጊዜ በኋላ በዳዊት መዝሙር ላይ “ዛሬ” በማለት እንደገና አንድን ቀን መደበ፤ ይህም ቀደም ሲል “ዛሬ ድምፁን የምትሰሙ ከሆነ ልባችሁን አታደንድኑ” እንደተባለው ነው።
ኢያሱ ወደ እረፍት ቦታ እየመራ አስገብቷቸው ቢሆን ኖሮ አምላክ ከዚያ በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር።
ስለዚህ የአምላክ ሕዝብ የሰንበት እረፍት ገና ይቀረዋል።
ወደ አምላክ እረፍት የገባ ሰው አምላክ ከሥራው እንዳረፈ ሁሉ እሱም ከሥራው አርፏልና።
ስለዚህ ማንም የእነዚያን ያለመታዘዝ ምሳሌ ተከትሎ እንዳይወድቅ ወደዚያ እረፍት ለመግባት የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።
የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ከየትኛውም ሰይፍ የበለጠ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን እንዲሁም መገጣጠሚያንና መቅኒን እስኪለያይ ድረስ ሰንጥቆ ይገባል፤ የልብንም ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል።
ደግሞም ከአምላክ እይታ የተሰወረ አንድም ፍጥረት የለም፤ ይልቁንም ተጠያቂዎች በሆንበት በእሱ ዓይኖች ፊት ሁሉም ነገር የተራቆተና ገሃድ የወጣ ነው።
እንግዲህ ወደ ሰማያት የገባ ታላቅ ሊቀ ካህናት ይኸውም የአምላክ ልጅ ኢየሱስ እንዳለን ስለምናውቅ በእሱ ላይ እምነት እንዳለን ምንጊዜም በይፋ እንናገር።
ያለን ሊቀ ካህናት በድካማችን ሊራራልን የማይችል አይደለምና፤ ከዚህ ይልቅ እንደ እኛው በሁሉም ረገድ የተፈተነ ሊቀ ካህናት አለን፤ ይሁንና እሱ ኃጢአት የለበትም።
እንግዲህ እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ምሕረትና ጸጋ እናገኝ ዘንድ ያለምንም ፍርሃት ወደ ጸጋው ዙፋን እንቅረብ።
እንግዲያው እንዲህ ያለ ታላቅ የምሥክሮች ደመና በዙሪያችን ስላለልን እኛም ማንኛውንም ሸክምና በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘንን ኃጢአት ከላያችን አንስተን እንጣል፤ ከፊታችን የሚጠብቀንን ሩጫም በጽናት እንሩጥ፤
የምንሮጠውም የእምነታችን “ዋና ወኪል” እና “ፍጹም አድራጊ” የሆነውን ኢየሱስን በትኩረት በመመልከት ነው። እሱ ከፊቱ ለሚጠብቀው ደስታ ሲል፣ የሚደርስበትን ውርደት ከምንም ሳይቆጥር በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ጸንቷል፤ እንዲሁም በአምላክ ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል።
እንግዲህ እንዳትደክሙና ተስፋ እንዳትቆርጡ ኃጢአተኞች የራሳቸውን ጥቅም በመጻረር የሚያሰሙትን እንዲህ ዓይነቱን የተቃውሞ ንግግር በጽናት የተቋቋመውን እሱን በጥሞና አስቡ።
እናንተ ከዚህ ኃጢአት ጋር እያደረጋችሁ ባላችሁት ትግል ደማችሁ እስኪፈስ ድረስ ገና አልታገላችሁም።
ደግሞም ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን የተሰጣችሁን የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሙሉ በሙሉ ረስታችኋል፦ “ልጄ ሆይ፣ ይሖዋ የሚሰጥህን ተግሣጽ አቅልለህ አትመልከት፤ በሚያርምህም ጊዜ ተስፋ አትቁረጥ፤
ይሖዋ የሚወዳቸውን ይገሥጻልና፤ እንዲያውም እንደ ልጁ አድርጎ የሚቀበለውን ሁሉ ይቀጣል።”
ተግሣጽ የምትቀበሉበት አንዱ መንገድ ይህ ስለሆነ መከራ ሲደርስባችሁ መጽናት ያስፈልጋችኋል። አምላክ የያዛችሁ እንደ ልጆቹ አድርጎ ነው። ለመሆኑ አባቱ የማይገሥጸው ልጅ ማን ነው?
ሆኖም ሁላችሁም ይህን ተግሣጽ ካልተቀበላችሁ ዲቃላዎች ናችሁ እንጂ ልጆች አይደላችሁም።
ከዚህም በላይ ሰብዓዊ አባቶቻችን ይገሥጹን ነበር፤ እኛም እናከብራቸው ነበር። ታዲያ የመንፈሳዊ ሕይወታችን አባት ለሆነው ይበልጥ በፈቃደኝነት በመገዛት በሕይወት ልንኖር አይገባም?
እነሱ መልካም መስሎ በታያቸው መንገድ ለጥቂት ጊዜ ገሥጸውናል፤ እሱ ግን ከቅድስናው ተካፋዮች እንድንሆን ለጥቅማችን ሲል ይገሥጸናል።
እርግጥ ነው፣ ማንኛውም ተግሣጽ ለጊዜው የሚያስደስት አይመስልም፤ ይልቁንም ያስከፋል፤ በኋላ ግን በተግሣጽ ሥልጠና ላገኙ ሰዎች የጽድቅን ሰላማዊ ፍሬ ያፈራላቸዋል።
ስለዚህ የዛሉትን እጆችና የተብረከረኩትን ጉልበቶች አበርቱ፤
የተጎዳው የአካል ክፍል እንዲፈወስ እንጂ እንዳይናጋ እግራችሁ ዘወትር ቀና በሆነ መንገድ እንዲጓዝ አድርጉ።
ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር ጥረት አድርጉ፤ ቅድስናንም ፈልጉ፤ ያለቅድስና ማንም ሰው ጌታን ማየት አይችልም።
ማንም የአምላክን ጸጋ እንዳያጣ ብሎም መርዛማ ሥር በቅሎ ችግር እንዳይፈጥርና ብዙዎችን እንዳይበክል ተጠንቀቁ፤
በተጨማሪም በመካከላችሁ ሴሰኛ ሰውም ሆነ ለአንድ ጊዜ መብል ሲል የብኩርና መብቱን አሳልፎ እንደሰጠው እንደ ኤሳው ቅዱስ ነገሮችን የማያደንቅ ሰው እንዳይገኝ ተጠንቀቁ።
ኤሳው የኋላ ኋላ በረከቱን ለመውረስ በፈለገ ጊዜ እንደተከለከለ ታውቃላችሁና፤ ሐሳብ ለማስቀየር እያለቀሰ ብርቱ ጥረት ቢያደርግም እንኳ አልተሳካለትም።
እናንተ እኮ የቀረባችሁት ሊዳሰስ ወደሚችለውና በእሳት ወደተያያዘው ተራራ፣ ወደ ጥቁሩ ደመና፣ ወደ ድቅድቁ ጨለማ፣ ወደ አውሎ ነፋሱ፣
ወደ መለከት ድምፁና ቃል ያሰማ ወደነበረው ድምፅ አይደለም፤ ሕዝቡ ይህን ሲሰሙ ሌላ ተጨማሪ ነገር እንዳይነገራቸው ለምነው ነበር።
“እንስሳ እንኳ ተራራውን ቢነካ በድንጋይ ተወግሮ ይሙት” የሚለው ትእዛዝ በጣም አስፈርቷቸው ነበርና።
በተጨማሪም በዚያ ይታይ የነበረው ነገር በጣም አስፈሪ ስለነበረ ሙሴ “ፈራሁ፤ ተንቀጠቀጥኩም” ሲል ተናግሯል።
እናንተ ግን የቀረባችሁት ወደ ጽዮን ተራራና የሕያው አምላክ ከተማ ወደሆነችው ወደ ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም፣ አንድ ላይ ወደተሰበሰቡ አእላፋት መላእክት፣
በሰማያት ወደተመዘገበው የበኩራት ጉባኤ፣ የሁሉ ፈራጅ ወደሆነው አምላክ፣ ፍጽምና እንዲያገኙ ወደተደረጉት ጻድቃን መንፈሳዊ ሕይወት፣
የአዲስ ቃል ኪዳን መካከለኛ ወደሆነው ወደ ኢየሱስና ከአቤል ደም በተሻለ ሁኔታ ወደሚናገረው ወደተረጨው ደም ነው።
እየተናገረ ያለውን እሱን ከመስማት ወደኋላ እንዳትሉ ተጠንቀቁ። በምድር ላይ መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸው የነበረውን ከመስማት ወደኋላ ያሉት ሰዎች ከቅጣት ካላመለጡ ታዲያ እኛ ከሰማይ የሚናገረውን እሱን ከመስማት ዞር ብንል እንዴት እናመልጣለን?
በዚያን ጊዜ ድምፁ ምድርን አናውጦ ነበር፤ አሁን ግን “ምድርን ብቻ ሳይሆን ሰማይን ጭምር እንደገና አናውጣለሁ” ሲል ቃል ገብቷል።
እንግዲህ “እንደገና” የሚለው አባባል የማይናወጡት ነገሮች ጸንተው ይኖሩ ዘንድ የሚናወጡት ይኸውም የተሠሩት ነገሮች የሚወገዱ መሆናቸውን ያመለክታል።
ስለዚህ እኛ ሊናወጥ የማይችል መንግሥት ልንቀበል እንደሆነ ስለምናውቅ ጸጋውን መቀበላችንን እንቀጥል፤ ይህም በጸጋው አማካኝነት በአምላካዊ ፍርሃትና በጥልቅ አክብሮት፣ ተቀባይነት ባለው መንገድ ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ እንችል ዘንድ ነው።
አምላካችን የሚባላ እሳት ነውና።
ስለዚህ ስለ ክርስቶስ ከተማርነው መሠረታዊ ትምህርት አልፈን ስለሄድን ወደ ጉልምስና ለመድረስ እንጣጣር፤ መሠረትን ደግመን አንመሥርት፤ ይኸውም ከሞቱ ሥራዎች ንስሐ ስለ መግባት፣ በአምላክ ስለ ማመን፣
እንዲሁም ስለ ጥምቀቶች፣ እጆችን ስለ መጫን፣ ስለ ሙታን ትንሣኤና ስለ ዘላለማዊ ፍርድ የሚገልጹ ትምህርቶችን ደግመን አንማር።
አምላክ ከፈቀደ ይህን እናደርጋለን።
ቀደም ሲል ብርሃን በርቶላቸው የነበሩትን፣ ሰማያዊውን ነፃ ስጦታ የቀመሱትን፣ መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉትን፣
መልካም የሆነውን የአምላክ ቃልና በሚመጣው ሥርዓት የሚገኙትን በረከቶች የቀመሱትን፣
በኋላ ግን ከእምነት ጎዳና የራቁትን እንደገና ወደ ንስሐ መመለስ አይቻልም፤ ምክንያቱም የአምላክን ልጅ ለራሳቸው እንደገና በእንጨት ላይ ይቸነክሩታል፤ እንዲሁም በአደባባይ ያዋርዱታል።
በየጊዜው በላዩ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የሚጠጣና ለአራሾቹ መብል የሚሆን አትክልት የሚያፈራ መሬት ከአምላክ በረከትን ያገኛልና።
እሾህና አሜኬላ የሚያበቅል ከሆነ ግን የተተወና ለመረገም የተቃረበ ይሆናል፤ በመጨረሻም በእሳት ይቃጠላል።
ይሁን እንጂ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ምንም እንኳ እንደዚህ ብለን ብንናገርም እናንተ በተሻለ ሁኔታ ላይ ይኸውም ወደ መዳን በሚያደርስ ሁኔታ ላይ እንደምትገኙ እርግጠኞች ነን።
አምላክ ቅዱሳንን በማገልገልም ሆነ ወደፊትም ማገልገላችሁን በመቀጠል የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም።
ይሁንና ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ የሆነውን ተስፋ እስከ መጨረሻው መያዝ እንድትችሉ እያንዳንዳችሁ ያንኑ ትጋት እንድታሳዩ እንመኛለን፤
ይህም አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች በእምነትና በትዕግሥት የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ ነው።
አምላክ ለአብርሃም ቃል በገባለት ጊዜ ሊምልበት የሚችል ከእሱ የሚበልጥ ሌላ ማንም ስለሌለ በራሱ ስም ማለ፤
እንዲህም አለ፦ “በእርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም በእርግጥ አበዛዋለሁ።”
በመሆኑም አብርሃም በትዕግሥት ከጠበቀ በኋላ ይህን የተስፋ ቃል አገኘ።
ሰዎች ከእነሱ በሚበልጥ ይምላሉ፤ መሐላቸውም እንደ ሕጋዊ ዋስትና ስለሆነ ማንኛውም ሙግት በመሐላው ይቋጫል።
በተመሳሳይም አምላክ ዓላማው ፈጽሞ የማይለወጥ መሆኑን ለተስፋው ቃል ወራሾች ይበልጥ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ለማሳየት በወሰነ ጊዜ የተስፋውን ቃል በመሐላ አረጋገጠ።
ይህን ያደረገው መጠጊያ ለማግኘት ወደ እሱ የሸሸን እኛ፣ አምላክ ሊዋሽ በማይችልባቸው፣ ፈጽሞ በማይለወጡት በእነዚህ ሁለት ነገሮች አማካኝነት በፊታችን ያለውን ተስፋ አጥብቀን እንድንይዝ የሚረዳንን ከፍተኛ ማበረታቻ እንድናገኝ ነው።
እኛ ለነፍሳችን እንደ መልሕቅ አስተማማኝና ጽኑ የሆነ ይህ ተስፋ አለን፤ ተስፋውም መጋረጃውን አልፈን ወደ ውስጥ እንድንገባ ያስችለናል፤