text
stringlengths
4
267
ኤቤርም ፋሌቅን ከወለደ በኋላ 430 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።
ፋሌቅ 30 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ረኡን ወለደ።
ፋሌቅ ረኡን ከወለደ በኋላ 209 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።
ረኡ 32 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሴሮህን ወለደ።
ረኡ ሴሮህን ከወለደ በኋላ 207 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።
ሴሮህ 30 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ናኮርን ወለደ።
ሴሮህ ናኮርን ከወለደ በኋላ 200 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።
ናኮር 29 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ታራን ወለደ።
ናኮር ታራን ከወለደ በኋላ 119 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።
ታራ 70 ዓመት ከኖረ በኋላ አብራምን፣ ናኮርን እና ካራንን ወለደ።
የታራ ታሪክ ይህ ነው። ታራ አብራምን፣ ናኮርን እና ካራንን ወለደ፤ ካራን ደግሞ ሎጥን ወለደ።
ካራንም አባቱ ታራ ገና በሕይወት እያለ፣ በተወለደበት አገር በከለዳውያን ዑር ሞተ።
አብራምና ናኮር ሚስት አገቡ። የአብራም ሚስት ስሟ ሦራ ሲሆን የናኮር ሚስት ደግሞ ስሟ ሚልካ ነበር፤ እሷም የሚልካ እና የዪስካ አባት የሆነው የካራን ልጅ ናት።
በዚህ ጊዜ ሦራ መሃን ነበረች፤ ልጅም አልነበራትም።
ከዚያም ታራ ልጁን አብራምንና የልጁ ልጅ የሆነውን የካራንን ልጅ ሎጥን እንዲሁም የልጁ የአብራም ሚስት የሆነችውን ምራቱን ሦራን ይዞ ወደ ከነአን ምድር ለመሄድ ከከለዳውያን ዑር ተነሳ። ከጊዜ በኋላም ወደ ካራን መጡ፤ በዚያም መኖር ጀመሩ።
ታራም 205 ዓመት ኖረ። ከዚያም በካራን ሞተ።
ያዕቆብ አባቱ የባዕድ አገር ሰው ሆኖ ይኖርበት በነበረው በከነአን ምድር ኖረ።
የያዕቆብ ታሪክ ይህ ነው። ዮሴፍ የ17 ዓመት ወጣት ሳለ ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዚልጳ ወንዶች ልጆች ጋር በጎች ይጠብቅ ነበር። እሱም ስለ ወንድሞቹ መጥፎ ድርጊት የሚገልጽ ወሬ ለአባታቸው ይዞለት መጣ።
እስራኤል ዮሴፍን የወለደው በስተርጅናው ስለነበር ከሌሎቹ ወንዶች ልጆቹ ሁሉ ይበልጥ ይወደው ነበር፤ ለእሱም ልዩ የሆነ ቀሚስ አሠራለት።
ወንድሞቹም አባታቸው ከእነሱ አስበልጦ እንደሚወደው ሲያዩ ይጠሉት ጀመር፤ በሰላምም ሊያናግሩት አልቻሉም።
በኋላም ዮሴፍ ሕልም አለመ፤ ሕልሙንም ለወንድሞቹ ነገራቸው፤ እነሱም እሱን የሚጠሉበት ተጨማሪ ምክንያት አገኙ።
እሱም እንዲህ አላቸው፦ “እባካችሁ ያየሁትን ሕልም ልንገራችሁ፣ ስሙኝ።
በእርሻ መካከል ነዶ እያሰርን ነበር፤ ከዚያም የእኔ ነዶ ተነስታ ቀጥ ብላ ስትቆም የእናንተ ነዶዎች ደግሞ የእኔን ነዶ ከበው ሰገዱላት።”
ወንድሞቹም “በእኛ ላይ ንጉሥ ልትሆንና ልትገዛን ታስባለህ ማለት ነው?” አሉት። በመሆኑም ያየው ሕልምና የተናገረው ነገር እሱን ይበልጥ እንዲጠሉት አደረጋቸው።
ከዚያም ሌላ ሕልም አለመ፤ ሕልሙንም ለወንድሞቹ እንዲህ ሲል ነገራቸው፦ “ሌላም ሕልም አለምኩ። አሁን ደግሞ ፀሐይ፣ ጨረቃና 11 ከዋክብት ሲሰግዱልኝ አየሁ።”
ሕልሙንም ለአባቱና ለወንድሞቹ ነገራቸው፤ አባቱም ገሠጸው፤ እንዲህም አለው፦ “ይህ ያለምከው ሕልም ፍቺ ምንድን ነው? እኔም ሆንኩ እናትህና ወንድሞችህ መጥተን መሬት ላይ ተደፍተን እንድንሰግድልህ ታስባለህ?”
ወንድሞቹም ይበልጥ ቀኑበት፤ አባቱ ግን ነገሩን በልቡ ያዘው።
ወንድሞቹ የአባታቸውን መንጋ ለማሰማራት ሴኬም አቅራቢያ ወደሚገኝ ቦታ ሄደው ነበር።
በኋላም እስራኤል ዮሴፍን “ወንድሞችህ በሴኬም አቅራቢያ መንጎቹን እየጠበቁ እንዳሉ አውቀሃል አይደል? በል ና፣ ወደ እነሱ ልላክህ” አለው። እሱም “እሺ፣ እሄዳለሁ!” አለ።
በመሆኑም “እባክህ ሂድና ወንድሞችህ ደህና መሆናቸውን እይ። መንጋውም ደህና መሆኑን እይና መጥተህ ትነግረኛለህ” አለው። በዚህም መሠረት ከኬብሮን ሸለቆ ወደዚያ ላከው፤ ዮሴፍም ወደ ሴኬም ሄደ።
በኋላም ዮሴፍ በሜዳ ላይ ሲባዝን አንድ ሰው አገኘው። ሰውየውም “ምን ፈልገህ ነው?” ሲል ጠየቀው።
እሱም “ወንድሞቼን እየፈለግኩ ነው። መንጎቹን እየጠበቁ ያሉት የት እንደሆነ እባክህ ንገረኝ” አለው።
ሰውየውም “ከዚህ ሄደዋል፤ ምክንያቱም ‘ወደ ዶታን እንሂድ’ ሲባባሉ ሰምቻቸዋለሁ” አለው። ስለዚህ ዮሴፍ ወንድሞቹን ፍለጋ ሄደ፤ ዶታን ላይም አገኛቸው።
እነሱም ከሩቅ ሲመጣ ተመለከቱት፤ አጠገባቸውም ከመድረሱ በፊት እሱን እንዴት እንደሚገድሉት ይመካከሩ ጀመር።
እነሱም እንዲህ ተባባሉ፦ “ያውና! ያ ሕልም አላሚ መጣ።
ኑ፣ እንግደለውና ከውኃ ጉድጓዶቹ በአንዱ ውስጥ እንጣለው፤ ከዚያም ኃይለኛ አውሬ በልቶታል እንላለን። እስቲ የሕልሞቹን መጨረሻ እናያለን።”
ሮቤል ይህን ሲሰማ ከእነሱ ሊያስጥለው አሰበ፤ በመሆኑም “ሕይወቱን እንኳ አናጥፋ” አለ።
ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “ደም አታፍስሱ። በምድረ በዳ በሚገኘው በዚህ የውኃ ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት እንጂ ጉዳት አታድርሱበት።” ይህን ያላቸው ከእነሱ ሊያስጥለውና ወደ አባቱ ሊመልሰው አስቦ ነበር።
ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ እንደደረሰም የለበሰውን ያን ልዩ ቀሚስ ገፈፉት፤
ወስደውም የውኃ ጉድጓዱ ውስጥ ጣሉት። ጉድጓዱም ባዶ ነበር፤ ውኃም አልነበረበትም።
ከዚያም ሊበሉ ተቀመጡ። ቀና ብለው ሲመለከቱም እስማኤላውያን ነጋዴዎች ግመሎቻቸውን አግተልትለው ከጊልያድ ሲመጡ አዩ። እነሱም በግመሎቻቸው ላይ ጥሩ መዓዛ ያለው ሙጫ፣ በለሳንና ከርቤ ጭነው ወደ ግብፅ እየወረዱ ነበር።
በዚህ ጊዜ ይሁዳ ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፦ “ወንድማችንን ብንገድለውና ደሙን ብንሸሽግ ምን እንጠቀማለን?
ኑ፣ ለእስማኤላውያን እንሽጠው፤ እጃችንን አንሰንዝርበት። ደግሞም እኮ እሱ ወንድማችን፣ የገዛ ሥጋችን ነው።” እነሱም በወንድማቸው ሐሳብ ተስማሙ።
ምድያማውያን ነጋዴዎች በአጠገባቸው ሲያልፉም ዮሴፍን ከውኃ ጉድጓዱ አውጥተው በ20 የብር ሰቅል ለእስማኤላውያን ሸጡት። እነሱም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት።
በኋላም ሮቤል ወደ ውኃ ጉድጓዱ ተመልሶ ዮሴፍ በዚያ አለመኖሩን ሲመለከት ልብሱን ቀደደ።
ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ “ልጁ የለም! እንግዲህ ምንድን ነው የማደርገው?” አላቸው።
ስለዚህ የዮሴፍን ቀሚስ ወሰዱ፤ አንድ ፍየል ካረዱ በኋላም ቀሚሱን ደሙ ውስጥ ነከሩት።
ከዚያም ያን ልዩ ቀሚስ እንዲህ ከሚል መልእክት ጋር ወደ አባታቸው ላኩት፦ “ይህን አገኘን፤ እባክህ ይህ የልጅህ ቀሚስ መሆን አለመሆኑን እስቲ እየው።”
እሱም ልብሱን አገላብጦ ካየው በኋላ “ይሄማ የልጄ ቀሚስ ነው! ኃይለኛ አውሬ በልቶት መሆን አለበት! በቃ ዮሴፍን አውሬ ቦጫጭቆታል ማለት ነው!” አለ።
ከዚያም ያዕቆብ ልብሱን ቀደደ፤ በወገቡም ላይ ማቅ ታጥቆ ለብዙ ቀናት ለልጁ አለቀሰ።
ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ ሁሉ ሊያጽናኑት ሞከሩ፤ እሱ ግን ፈጽሞ ሊጽናና አልቻለም፤ “በልጄ ሐዘን እንደተቆራመድኩ ወደ መቃብር እወርዳለሁ!” ይል ነበር። አባቱም ለልጁ ማልቀሱን አላቋረጠም።
በዚህ ጊዜ ምድያማውያን ዮሴፍን ግብፅ ውስጥ ጶጢፋር ለተባለ ሰው ሸጡት፤ ይህ ሰው የፈርዖን የቤተ መንግሥት ባለሥልጣንና የዘቦች አለቃ ነበር።
በአብርሃም ዘመን ከተከሰተው ከመጀመሪያው ረሃብ ሌላ በምድሪቱ ላይ ረሃብ ተከሰተ፤ ስለዚህ ይስሐቅ በጌራራ ወደሚገኘው ወደ ፍልስጤማውያን ንጉሥ ወደ አቢሜሌክ ሄደ።
ከዚያም ይሖዋ ተገለጠለትና እንዲህ አለው፦ “ወደ ግብፅ አትውረድ። እኔ በማሳይህ ምድር ተቀመጥ።
በዚህ ምድር እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆነህ ተቀመጥ፤ እኔም ከአንተ ጋር መሆኔን እቀጥላለሁ፤ እንዲሁም እባርክሃለሁ። ምክንያቱም ይህችን ምድር በሙሉ ለአንተና ለዘሮችህ እሰጣለሁ፤ ደግሞም ለአባትህ ለአብርሃም እንዲህ ስል የማልሁለትን መሐላ እፈጽማለሁ፦
‘ዘርህን በሰማያት ላይ እንዳሉ ከዋክብት አበዛዋለሁ፤ ይህችንም ምድር በሙሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ የምድርም ብሔራት ሁሉ በዘርህ አማካኝነት ለራሳቸው በረከት ያገኛሉ።’
ይህን የማደርገውም አብርሃም ቃሌን ስለሰማ እንዲሁም ሥርዓቶቼን፣ ትእዛዛቴን፣ ደንቦቼንና ሕጎቼን ጠብቆ ስለኖረ ነው።”
በመሆኑም ይስሐቅ በጌራራ መኖሩን ቀጠለ።
የዚያ አገር ሰዎች ስለ ሚስቱ በተደጋጋሚ ሲጠይቁት “እህቴ ናት” ይላቸው ነበር። “የዚህ አገር ሰዎች በርብቃ የተነሳ ሊገድሉኝ ይችላሉ” ብሎ ስላሰበ “ሚስቴ ናት” ለማለት ፈርቶ ነበር፤ ምክንያቱም ርብቃ ቆንጆ ነበረች።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላም የፍልስጤማውያን ንጉሥ አቢሜሌክ በመስኮት ወደ ውጭ ሲመለከት ይስሐቅ ለሚስቱ ለርብቃ ፍቅሩን ሲገልጽላት አየ።
አቢሜሌክም ወዲያው ይስሐቅን ጠርቶ “መቼም እሷ ሚስትህ እንደሆነች ግልጽ ነው! ታዲያ ‘እህቴ ናት’ ያልከው ለምንድን ነው?” አለው። በዚህ ጊዜ ይስሐቅ “እንዲህ ያልኩት በእሷ የተነሳ ሕይወቴን እንዳላጣ ስለፈራሁ ነው” አለው።
አቢሜሌክ ግን “እንዴት እንዲህ ያለ ነገር ታደርግብናለህ? ከእኛ ሰዎች አንዱ ከሚስትህ ጋር ሊተኛ ይችል ነበር፤ እኛንም በደለኞች አድርገህ ታስቆጥረን ነበር!” አለው።
ከዚያም አቢሜሌክ “ይህን ሰውም ሆነ ሚስቱን የነካ ማንኛውም ሰው ያለምንም ጥርጥር ይገደላል!” በማለት ለሕዝቡ ሁሉ ትእዛዝ አስተላለፈ።
ይስሐቅም በዚያ ምድር ዘር መዝራት ጀመረ፤ ይሖዋም ስለባረከው በዚያ ዓመት፣ የዘራውን 100 እጥፍ አመረተ።
ሰውየውም ባለጸጋ ሆነ፤ እጅግ ባለጸጋ እስኪሆንም ድረስ በሀብት ላይ ሀብት እየጨመረ ሄደ።
የበግና የከብት መንጋው በዛለት፤ አገልጋዮቹም ብዙ ሆኑ፤ ፍልስጤማውያንም ይቀኑበት ጀመር።
በመሆኑም ፍልስጤማውያን የአባቱ አገልጋዮች በአብርሃም ዘመን የቆፈሯቸውን የውኃ ጉድጓዶች በሙሉ አፈር በመሙላት ደፈኗቸው።
ከዚያም አቢሜሌክ ይስሐቅን “ከእኛ ይልቅ እየበረታህ ስለመጣህ አካባቢያችንን ለቅቀህ ሂድልን” አለው።
በመሆኑም ይስሐቅ ከዚያ ተነስቶ በመሄድ በጌራራ ሸለቆ ሰፈረ፤ በዚያም መኖር ጀመረ።
ይስሐቅም በአባቱ በአብርሃም ዘመን ተቆፍረው የነበሩትንና አብርሃም ከሞተ በኋላ ፍልስጤማውያን የደፈኗቸውን የውኃ ጉድጓዶች እንደገና ቆፈረ፤ ቀደም ሲል አባቱ ባወጣላቸው ስምም ጠራቸው።
የይስሐቅ አገልጋዮችም በሸለቆው ውስጥ ሲቆፍሩ ለመጠጥ የሚሆን ውኃ ያለበት አንድ ጉድጓድ አገኙ።
የጌራራ እረኞች “ውኃው የእኛ ነው!” በማለት ከይስሐቅ እረኞች ጋር ጠብ አነሱ። ከእሱ ጋር ስለተጣሉም የውኃ ጉድጓዱን ስም ኤሴቅ አለው።
እነሱም ሌላ የውኃ ጉድጓድ ቆፈሩ፤ በዚህም ጉድጓድ ጠብ አነሱ። በመሆኑም የጉድጓዱን ስም ሲጥና አለው።
ከዚያም ያን ቦታ ትቶ በመሄድ ሌላ የውኃ ጉድጓድ ቆፈረ፤ እነሱም በዚህ ጉድጓድ ጠብ አላነሱበትም። በመሆኑም “አሁን ይሖዋ ሰፊ ቦታ ሰጥቶናል፤ በምድርም ላይ እንድንበዛ አድርጎናል” በማለት የጉድጓዱን ስም ረሆቦት አለው።
በኋላም ከዚያ ተነስቶ ወደ ቤርሳቤህ ወጣ።
ይሖዋም በዚያ ሌሊት ተገለጠለትና እንዲህ አለው፦ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ። እኔ ከአንተ ጋር ስለሆንኩ አትፍራ፤ ስለ አገልጋዬ ስለ አብርሃም ስል እባርክሃለሁ እንዲሁም ዘርህን አበዛዋለሁ።”
በመሆኑም በዚያ መሠዊያ ሠራ፤ የይሖዋንም ስም ጠራ። እንዲሁም ይስሐቅ ድንኳኑን በዚያ ተከለ፤ አገልጋዮቹም በዚያ የውኃ ጉድጓድ ቆፈሩ።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አቢሜሌክ የግል አማካሪው ከሆነው ከአሁዛትና ከሠራዊቱ አዛዥ ከፊኮል ጋር በመሆን ከጌራራ ተነስቶ ወደ ይስሐቅ መጣ።
በዚህ ጊዜ ይስሐቅ “ጠልታችሁኝ ከአካባቢያችሁ ካባረራችሁኝ በኋላ አሁን ለምን ወደ እኔ መጣችሁ?” አላቸው።
እነሱም እንዲህ አሉት፦ “ይሖዋ ከአንተ ጋር እንደሆነ በግልጽ ማየት ችለናል። በመሆኑም እንዲህ አልን፦ ‘በእኛና በአንተ መካከል በመሐላ የጸና ስምምነት ይኑር፤ ከአንተም ጋር ቃል ኪዳን እንጋባ።
በአንተ ላይ ምንም ጉዳት እንዳላደረስንብህ ከዚህ ይልቅ በሰላም በማሰናበት መልካም እንዳደረግንልህ ሁሉ አንተም በእኛ ላይ ምንም መጥፎ ነገር እንደማታደርግብን ማልልን። አንተ አሁን ይሖዋ የባረከህ ሰው ነህ።’”
እሱም ግብዣ አዘጋጀላቸው፤ እነሱም በሉ፣ ጠጡም።
በማግስቱም በማለዳ ተነስተው እርስ በርሳቸው ተማማሉ። ከዚያም ይስሐቅ አሰናበታቸው፤ እነሱም ከእሱ ዘንድ በሰላም ሄዱ።
በዚያኑ ዕለት የይስሐቅ አገልጋዮች መጥተው ስለቆፈሩት የውኃ ጉድጓድ ነገሩት፤ እነሱም “ውኃ እኮ አገኘን!” አሉት።
በመሆኑም የጉድጓዱን ስም ሳቤህ አለው። የከተማዋ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ቤርሳቤህ ተብሎ የሚጠራው በዚህ የተነሳ ነው።
ኤሳው 40 ዓመት ሲሆነው የሂታዊውን የቤኤሪን ልጅ ዮዲትን እንዲሁም የሂታዊውን የኤሎንን ልጅ ባሴማትን አገባ።
እነሱም ይስሐቅንና ርብቃን ለከፍተኛ ሐዘን ዳረጓቸው።
በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ።
ምድርም ቅርጽ አልባና ባድማ ነበረች፤ ጥልቁም ውኃ በጨለማ ተሸፍኖ ነበር፤ የአምላክም ኃይል በውኃው ላይ ይንቀሳቀስ ነበር።
አምላክም “ብርሃን ይሁን” አለ። ብርሃንም ሆነ።
ከዚህ በኋላ አምላክ ብርሃኑ መልካም እንደሆነ አየ፤ አምላክም ብርሃኑን ከጨለማው ለየ።
አምላክም ብርሃኑን ‘ቀን’ ብሎ ጠራው፤ ጨለማውን ግን ‘ሌሊት’ ብሎ ጠራው። መሸ፣ ነጋም፤ የመጀመሪያ ቀን።
ከዚያም አምላክ “በውኃዎቹ መካከል ጠፈር ይሁን፣ ውኃዎቹም ከውኃዎቹ ይከፈሉ” አለ።
ከዚያም አምላክ ጠፈርን ሠራ፤ ከጠፈሩ በታች ያሉትንም ውኃዎች ከጠፈሩ በላይ ካሉት ውኃዎች ለየ። እንዳለውም ሆነ።
አምላክ ጠፈሩን ‘ሰማይ’ ብሎ ጠራው። መሸ፣ ነጋም፤ ሁለተኛ ቀን።
በመቀጠልም አምላክ “ከሰማያት በታች ያሉት ውኃዎች አንድ ቦታ ላይ ይሰብሰቡና ደረቁ መሬት ይገለጥ” አለ። እንዳለውም ሆነ።
አምላክ ደረቁን መሬት ‘የብስ’ ብሎ ጠራው፤ አንድ ላይ የተሰበሰቡትን ውኃዎች ግን ‘ባሕር’ ብሎ ጠራቸው። አምላክም ይህ መልካም እንደሆነ አየ።
ቀጥሎም አምላክ “ምድር ሣርን፣ ዘር የሚሰጡ ተክሎችን እንዲሁም ዘር ያለው ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን እንደየወገናቸው ታብቅል” አለ። እንዳለውም ሆነ።
ምድርም ሣርን፣ ዘር የሚሰጡ ተክሎችን እንዲሁም ዘር ያለው ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን እንደየወገናቸው ማብቀል ጀመረች። ከዚያም አምላክ ይህ መልካም እንደሆነ አየ።
መሸ፣ ነጋም፤ ሦስተኛ ቀን።