text
stringlengths
4
267
የእስማኤል ወንዶች ልጆች በየመንደራቸውና በየሰፈራቸው ሲዘረዘሩ ስማቸው ይህ ነው፤ እነሱም በየነገዳቸው 12 የነገድ አለቆች ናቸው።
እስማኤል 137 ዓመት ኖረ። ከዚያም እስትንፋሱ ቀጥ አለና ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ።
እነሱም ከግብፅ አጠገብ በሹር አቅራቢያ ከምትገኘው ከሃዊላ አንስቶ እስከ አሦር ድረስ ባለው አካባቢ ሰፍረው ነበር። በወንድሞቹም ሁሉ አቅራቢያ ሰፈረ።
የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ታሪክ ይህ ነው። አብርሃም ይስሐቅን ወለደ።
ይስሐቅ በጳዳንአራም የሚኖረውን የአራማዊውን የባቱኤልን ሴት ልጅ ማለትም የአራማዊውን የላባን እህት ርብቃን ሲያገባ ዕድሜው 40 ዓመት ነበር።
ይስሐቅ ሚስቱ መሃን ስለነበረች ስለ እሷ አዘውትሮ ይሖዋን ይለምን ነበር፤ ይሖዋም ልመናውን ሰማው፤ ሚስቱ ርብቃም ፀነሰች።
በሆዷ ውስጥ ያሉት ልጆችም እርስ በርስ ይታገሉ ጀመር፤ በመሆኑም “እንዲህ ከሆነስ ብሞት ይሻለኛል” አለች። ስለዚህ ይሖዋን ጠየቀች።
ይሖዋም እንዲህ አላት፦ “በማህፀንሽ ውስጥ ሁለት ብሔራት አሉ፤ ከውስጥሽም ሁለት ሕዝቦች ተለያይተው ይወጣሉ። አንደኛው ብሔር ከሌላኛው ብሔር ይበረታል፤ ታላቁም ታናሹን ያገለግላል።”
የመውለጃዋም ጊዜ ሲደርስ በማህፀኗ ውስጥ መንታ ልጆች ነበሩ።
መጀመሪያ የወጣው መልኩ ቀይ ሲሆን ፀጉራም ካባ የለበሰ ይመስል ሰውነቱ በሙሉ በፀጉር የተሸፈነ ነበር፤ በመሆኑም ስሙን ኤሳው አሉት።
ከዚያም ወንድሙ ወጣ፤ በእጁም የኤሳውን ተረከዝ ይዞ ነበር፤ በዚህም የተነሳ ስሙን ያዕቆብ አለው። ርብቃ እነሱን ስትወልድ ይስሐቅ 60 ዓመቱ ነበር።
ልጆቹም እያደጉ ሲሄዱ ኤሳው ውጭ መዋል የሚወድ የተዋጣለት አዳኝ ሆነ፤ ያዕቆብ ግን አብዛኛውን ጊዜውን በድንኳን የሚያሳልፍ ነቀፋ የሌለበት ሰው ነበር።
ይስሐቅ ኤሳውን ይወደው ነበር፤ ምክንያቱም እያደነ ያበላው ነበር፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወደው ነበር።
አንድ ቀን ኤሳው ውጭ ውሎ በጣም ደክሞት ሲመጣ ያዕቆብ ወጥ እየሠራ ነበር።
በመሆኑም ኤሳው ያዕቆብን “ቶሎ በል እባክህ፣ በጣም ስለደከመኝ ከዚያ ከቀዩ ወጥ የተወሰነ ስጠኝ!” አለው። ስሙ ኤዶም የተባለውም በዚህ የተነሳ ነው።
በዚህ ጊዜ ያዕቆብ “በመጀመሪያ የብኩርና መብትህን ሽጥልኝ!” አለው።
ኤሳውም “እኔ ለራሴ ልሞት ደርሻለሁ! ታዲያ የብኩርና መብት ምን ይጠቅመኛል?” አለው።
ያዕቆብም “በመጀመሪያ ማልልኝ!” አለው። እሱም ማለለት፤ የብኩርና መብቱንም ለያዕቆብ ሸጠለት።
ከዚያም ያዕቆብ ለኤሳው ዳቦና ምስር ወጥ ሰጠው፤ እሱም በላ፣ ጠጣም፤ ተነሥቶም ሄደ። በዚህ መንገድ ኤሳው የብኩርና መብቱን አቃለለ።
ከዚያም አብራም ሚስቱንና ያለውን ንብረት ሁሉ ይዞ ከሎጥ ጋር በመሆን ከግብፅ ወጥቶ ወደ ኔጌብ ሄደ።
አብራም በከብት፣ በብርና በወርቅ እጅግ በልጽጎ ነበር።
እሱም ከኔጌብ ተነስቶ ወደ ቤቴል በሚጓዝበት ጊዜ ድንኳኑን ተክሎበት ወደነበረው በቤቴልና በጋይ መካከል ወደሚገኘው ስፍራ እስኪደርስ ድረስ በየቦታው ይሰፍር ነበር፤
ይህም ቀደም ሲል መሠዊያ ሠርቶበት የነበረው ስፍራ ነው። በዚያም አብራም የይሖዋን ስም ጠራ።
ከአብራም ጋር ይጓዝ የነበረው ሎጥም በጎች፣ ከብቶችና ድንኳኖች ነበሩት።
በመሆኑም ሁሉም አንድ ላይ ለመኖር ምድሪቱ አልበቃቻቸውም፤ ንብረታቸው በጣም እየበዛ ስለመጣ አብረው መኖር አልቻሉም።
በዚህም ምክንያት በአብራም እረኞችና በሎጥ እረኞች መካከል ጠብ ተነሳ። (በወቅቱ ከነአናውያንና ፈሪዛውያን በምድሪቱ ይኖሩ ነበር።)
ስለዚህ አብራም ሎጥን እንዲህ አለው፦ “እባክህ በእኔና በአንተ እንዲሁም በእኔ እረኞችና በአንተ እረኞች መካከል ምንም ዓይነት ጠብ አይኑር፤ እኛ እኮ ወንድማማቾች ነን።
ምድሪቱ ሁሉ በእጅህ አይደለችም? እባክህ ከእኔ ተለይ። አንተ ወደ ግራ ብትሄድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ አንተ ወደ ቀኝ ብትሄድ ደግሞ እኔ ወደ ግራ እሄዳለሁ።”
ሎጥም ዓይኑን አቅንቶ መላውን የዮርዳኖስ አውራጃ እስከ ዞአር ድረስ ተመለከተ፤ (ይሖዋ ሰዶምንና ገሞራን ከማጥፋቱ በፊት) አካባቢው ልክ እንደ ይሖዋ የአትክልት ስፍራ፣ ልክ እንደ ግብፅ ምድር ውኃ የጠገበ ነበር።
ከዚያም ሎጥ መላውን የዮርዳኖስ አውራጃ ለራሱ መረጠ፤ ሎጥም ወደ ምሥራቅ ሄዶ ሰፈረ። በዚህ መንገድ አንዳቸው ከሌላው ተለዩ።
አብራም በከነአን ምድር ኖረ፤ ሎጥ ግን በአውራጃው በሚገኙ ከተሞች አቅራቢያ ኖረ። በመጨረሻም በሰዶም አቅራቢያ ድንኳን ተከለ።
የሰዶም ሰዎች በይሖዋ ፊት ከባድ ኃጢአት የሚፈጽሙ ክፉ ሰዎች ነበሩ።
ሎጥ ከአብራም ከተለየ በኋላ ይሖዋ አብራምን እንዲህ አለው፦ “እባክህ ካለህበት ቦታ ሆነህ ዓይንህን አቅንተህ ወደ ሰሜን፣ ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ተመልከት፤
ምክንያቱም የምታየውን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘለቄታው ርስት አድርጌ እሰጣለሁ።
ዘርህን እንደ ምድር አፈር አበዛዋለሁ፤ ማንም ሰው የምድርን አፈር መቁጠር ከቻለ የአንተም ዘር ሊቆጠር ይችላል።
ተነሳ፣ ይህችን ምድር ልሰጥህ ስለሆነ በምድሪቱ ስፋትና ርዝመት ሂድ።”
በመሆኑም አብራም ሄደ፤ በድንኳን መኖሩንም ቀጠለ። ከጊዜ በኋላም በኬብሮን ወደሚገኙት የማምሬ ትላልቅ ዛፎች መጥቶ መኖር ጀመረ፤ በዚያም ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ።
ይሖዋ ልክ በተናገረው መሠረት ሣራን አሰባት፤ ይሖዋም ለሣራ ቃል የገባላትን አደረገላት።
በመሆኑም ሣራ ፀነሰች፤ ለአብርሃምም አምላክ ቃል በገባለት በተወሰነው ጊዜ ላይ በስተርጅናው ወንድ ልጅ ወለደችለት።
አብርሃም ሣራ የወለደችለትን ልጅ ይስሐቅ ብሎ ጠራው።
አብርሃምም ልክ አምላክ ባዘዘው መሠረት ልጁ ይስሐቅ ስምንት ቀን ሲሆነው ገረዘው።
አብርሃም ልጁ ይስሐቅ ሲወለድ ዕድሜው 100 ዓመት ነበር።
ከዚያም ሣራ “አምላክ በደስታ እንድስቅ አድርጎኛል፤ ይህን የሰማም ሁሉ ከእኔ ጋር አብሮ ይስቃል” አለች።
አክላም “ለመሆኑ ለአብርሃም ‘ሣራ ልጆች ታጠባለች’ ማን ብሎት ያውቃል? እኔ ግን ይኸው በስተርጅናው ወንድ ልጅ ወለድኩለት” አለች።
ልጁም አደገ፤ ጡትም ጣለ፤ አብርሃምም ይስሐቅ ጡት በጣለበት ቀን ትልቅ ግብዣ አደረገ።
ሣራም ግብፃዊቷ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት ልጅ በይስሐቅ ላይ እንደሚያፌዝበት በተደጋጋሚ አስተዋለች።
ስለዚህ አብርሃምን “ይህችን ባሪያና ልጇን ከዚህ አባር፤ ምክንያቱም የዚህች ባሪያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር ወራሽ አይሆንም!” አለችው።
አብርሃም ግን ሣራ ስለ ልጁ የተናገረችው ነገር በጣም ቅር አሰኘው።
ከዚያም አምላክ አብርሃምን እንዲህ አለው፦ “ሣራ ስለ ልጁና ስለ ባሪያህ እየነገረችህ ያለው ነገር ምንም ቅር አያሰኝህ። ዘርህ የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ስለሆነ የምትልህን ስማ።
የባሪያይቱም ልጅ ቢሆን ልጅህ ስለሆነ ከእሱ አንድ ብሔር እንዲገኝ አደርጋለሁ።”
ስለዚህ አብርሃም በማለዳ ተነሳ፤ ለአጋርም ምግብና የውኃ አቁማዳ ሰጣት። እነዚህንም በትከሻዋ አሸከማት፤ ከዚያም ከልጁ ጋር አሰናበታት። እሷም ሄደች፤ በቤርሳቤህ ምድረ በዳም ትንከራተት ጀመር።
በመጨረሻም በአቁማዳው ውስጥ የነበረው ውኃ አለቀ፤ እሷም ልጁን አንዱ ቁጥቋጦ ሥር ጣለችው።
ከዚያም “ልጁ ሲሞት ማየት አልፈልግም” ብላ የቀስት ውርወራ ያህል ርቃ ተቀመጠች። እሷም ትጮኽና ታለቅስ ጀመር።
በዚህ ጊዜ አምላክ የልጁን ድምፅ ሰማ፤ የአምላክም መልአክ ከሰማይ አጋርን ጠርቶ እንዲህ አላት፦ “አጋር፣ ምን ሆነሻል? ልጁ ካለበት ቦታ ሆኖ ሲያለቅስ አምላክ ስለሰማ አይዞሽ አትፍሪ።
ተነሽ፣ ልጁንም አንስተሽ በእጅሽ ያዢው፤ ምክንያቱም እኔ ታላቅ ብሔር አደርገዋለሁ።”
ከዚያም አምላክ ዓይኖቿን ከፈተላት፤ የውኃ ጉድጓድም ተመለከተች። ወደዚያም ሄዳ በአቁማዳው ውኃ ሞላች፤ ልጁንም አጠጣችው።
ልጁም እያደገ ሄደ፤ አምላክም ከልጁ ጋር ነበር። እሱም የሚኖረው በምድረ በዳ ነበር፤ ቀስተኛም ሆነ።
እሱም በፋራን ምድረ በዳ ኖረ፤ እናቱም ከግብፅ ምድር ሚስት አመጣችለት።
በዚያን ጊዜ አቢሜሌክ ከሠራዊቱ አዛዥ ከፊኮል ጋር ሆኖ አብርሃምን እንዲህ አለው፦ “በምታደርገው ነገር ሁሉ አምላክ ከአንተ ጋር ነው።
ስለዚህ እኔንም ሆነ ልጆቼንና ዘሮቼን እንደማትክድ እንዲሁም ለእኔም ሆነ ለምትኖርባት ምድር እኔ ያሳየሁህ ዓይነት ታማኝ ፍቅር እንደምታሳይ በአምላክ ስም ማልልኝ።”
አብርሃምም “እሺ፣ እምላለሁ” አለ።
ሆኖም አብርሃም የአቢሜሌክ አገልጋዮች በጉልበት ስለወሰዱት የውኃ ጉድጓድ ለአቢሜሌክ ቅሬታውን ገለጸለት።
አቢሜሌክም መልሶ “ይህን ያደረገው ማን እንደሆነ አላውቅም፤ አንተም ብትሆን ስለዚህ ጉዳይ አልነገርከኝም፤ ስለዚህ ነገር ያለዛሬ አልሰማሁም” አለው።
በዚህ ጊዜ አብርሃም በጎችንና ከብቶችን ወስዶ ለአቢሜሌክ ሰጠው፤ ሁለቱም ቃል ኪዳን ገቡ።
አብርሃም ሰባት እንስት በጎችን ከመንጋው ለይቶ ለብቻቸው እንዲሆኑ ባደረገ ጊዜ
አቢሜሌክ አብርሃምን “እነዚህን ሰባት እንስት በጎች ለብቻቸው የለየኸው ለምንድን ነው?” አለው።
እሱም “ይህን ጉድጓድ የቆፈርኩት እኔ ለመሆኔ ምሥክር እንዲሆን እነዚህን ሰባት እንስት በጎች ከእጄ ውሰድ” አለው።
የቦታውን ስም ቤርሳቤህ ብሎ የጠራው በዚህ የተነሳ ነው፤ ምክንያቱም በዚያ ሁለቱ ተማምለዋል።
ስለዚህ በቤርሳቤህ ቃል ኪዳን ገቡ፤ ከዚያም አቢሜሌክ ከሠራዊቱ አዛዥ ከፊኮል ጋር ሆኖ ወደ ፍልስጤማውያን ምድር ተመለሰ።
ከዚያም በኋላ አብርሃም በቤርሳቤህ የታማሪስክ ዛፍ ተከለ፤ በዚያም የዘላለማዊውን አምላክ የይሖዋን ስም ጠራ።
አብርሃምም በፍልስጤማውያን ምድር ረዘም ላለ ጊዜ ኖረ።
እባብም ይሖዋ አምላክ ከሠራቸው የዱር እንስሳት ሁሉ እጅግ ጠንቃቃ ነበር። በመሆኑም ሴቲቱን “በእርግጥ አምላክ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም ዛፍ አትብሉ’ ብሏችኋል?” ሲል ጠየቃት።
በዚህ ጊዜ ሴቲቱ እባቡን እንዲህ አለችው፦ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን።
ይሁንና በአትክልቱ ስፍራ መካከል የሚገኘውን ዛፍ ፍሬ በተመለከተ አምላክ ‘ከእሱ አትብሉ፤ ፈጽሞም አትንኩት፤ አለዚያ ትሞታላችሁ’ ብሏል።”
በዚህ ጊዜ እባቡ ሴቲቱን እንዲህ አላት፦ “መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም።
አምላክ ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚገለጡና መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ እንደምትሆኑ ስለሚያውቅ ነው።”
በዚህም የተነሳ ሴቲቱ ዛፉ ለመብል መልካም፣ ሲያዩትም የሚያጓጓ እንደሆነ ተመለከተች፤ ዛፉ ለዓይን የሚማርክ ነበር። ስለሆነም ከዛፉ ፍሬ ወስዳ በላች። ባሏም አብሯት ሲሆን ለእሱም ሰጠችው፤ እሱም በላ።
ከዚያም የሁለቱም ዓይኖች ተገለጡ፤ ራቁታቸውን መሆናቸውንም አስተዋሉ። በመሆኑም የበለስ ቅጠል በመስፋት የሚያሸርጡት ነገር ለራሳቸው ሠሩ።
በኋላም ሰውየውና ሚስቱ ቀኑ ነፋሻማ በሆነበት ጊዜ ላይ ይሖዋ አምላክ በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ ሲሄድ ድምፁን ሰሙ፤ እነሱም በአትክልቱ ስፍራ ባሉት ዛፎች መካከል በመግባት ከይሖዋ አምላክ ፊት ተደበቁ።
ይሖዋ አምላክም ሰውየውን በተደጋጋሚ በመጣራት “የት ነህ?” አለው።
በመጨረሻም ሰውየው “በአትክልቱ ስፍራ ድምፅህን ሰማሁ፤ ሆኖም ራቁቴን ስለነበርኩ ፈራሁ፤ ስለሆነም ተደበቅኩ” አለ።
እሱም “ራቁትህን እንደሆንክ ማን ነገረህ? እንዳትበላ ብዬ ካዘዝኩህ ዛፍ በላህ?” አለው።
ሰውየውም “ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ይህች ሴት ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” አለ።
ከዚያም ይሖዋ አምላክ ሴቲቱን “ለመሆኑ ይህ ያደረግሽው ነገር ምንድን ነው?” አላት። ሴቲቱም “እባቡ አታለለኝና በላሁ” ስትል መለሰች።
ከዚያም ይሖዋ አምላክ እባቡን እንዲህ አለው፦ “ይህን ስላደረግክ ከቤት እንስሳት ሁሉ እንዲሁም ከዱር እንስሳት ሁሉ የተረገምክ ትሆናለህ። በሕይወትህ ዘመን ሁሉ በሆድህ እየተሳብክ ትሄዳለህ፤ እንዲሁም አፈር ትበላለህ።
በአንተና በሴቲቱ መካከል እንዲሁም በዘርህና በዘሯ መካከል ጠላትነት እንዲኖር አደርጋለሁ፤ እሱ ራስህን ይጨፈልቃል፤ አንተም ተረከዙን ታቆስላለህ።”
ሴቲቱንም እንዲህ አላት፦ “በእርግዝናሽ ወቅት የሚሰማሽን ሕመም በእጅጉ አበዛለሁ፤ ልጆች የምትወልጂውም በሥቃይ ይሆናል፤ ምኞትሽ ሁሉ ባልሽ ይሆናል፤ እሱ ደግሞ ይገዛሻል።”
አዳምንም እንዲህ አለው፦ “የሚስትህን ቃል ስለሰማህና ‘ከእሱ አትብላ’ ብዬ ካዘዝኩህ ዛፍ ወስደህ ስለበላህ በአንተ የተነሳ ምድር የተረገመች ትሁን። በሕይወትህ ዘመን ሁሉ የምድርን ፍሬ በሥቃይ ትበላለህ።
ምድርም እሾህና አሜኬላ ታበቅልብሃለች፤ አንተም በሜዳ ላይ የሚበቅለውን ተክል ትበላለህ።
ከመሬት ስለተገኘህ ወደ መሬት እስክትመለስ ድረስ ላብህን እያንጠፈጠፍክ ምግብ ትበላለህ። አፈር ስለሆንክ ወደ አፈር ትመለሳለህ።”
ከዚህ በኋላ አዳም ሚስቱን ሔዋን ብሎ ጠራት፤ ምክንያቱም እሷ የሕያዋን ሁሉ እናት ትሆናለች።
ይሖዋ አምላክም ረጅም ልብስ ከቆዳ ሠርቶ አዳምንና ሚስቱን አለበሳቸው።
ከዚያም ይሖዋ አምላክ እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ ሰውየው መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ ከእኛ እንደ አንዱ ሆኗል። አሁን ደግሞ እጁን በመዘርጋት ከሕይወት ዛፍ ፍሬ ወስዶ እንዳይበላና ለዘላለም እንዳይኖር አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ።”
ስለሆነም የተገኘበትን መሬት እንዲያርስ፣ ይሖዋ አምላክ አዳምን ከኤደን የአትክልት ስፍራ አባረረው።
ሰውየውንም አስወጣው፤ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ በኤደን የአትክልት ስፍራ በስተ ምሥራቅ በኩል ኪሩቤልና ያለማቋረጥ የሚሽከረከር የነበልባል ሰይፍ አስቀመጠ።
ራሔል ለያዕቆብ ምንም ልጅ እንዳልወለደችለት ባየች ጊዜ በእህቷ ቀናች፤ ያዕቆብንም “ልጆች ስጠኝ፤ አለዚያ እሞታለሁ” ትለው ጀመር።
በዚህ ጊዜ ያዕቆብ ራሔልን በጣም ተቆጥቶ “እኔ፣ እንዳትወልጂ ያደረገሽን አምላክ መሰልኩሽ እንዴ?” አላት።
እሷም በዚህ ጊዜ “ባሪያዬ ባላ ይችውልህ፤ ልጆች እንድትወልድልኝና እኔም በእሷ አማካኝነት ልጆች እንዳገኝ ከእሷ ጋር ግንኙነት ፈጽም” አለችው።
በዚህ መሠረት አገልጋይዋን ባላን ሚስት እንድትሆነው ሰጠችው፤ ያዕቆብም ከእሷ ጋር ግንኙነት ፈጸመ።
ባላም ፀነሰች፤ ከዚያም ለያዕቆብ ወንድ ልጅ ወለደችለት።