text
stringlengths
4
267
ከእኛ ከባሪያዎችህ መካከል የተገኘበት ቢኖር ያ ሰው ይገደል፤ የቀረነውም ለጌታዬ ባሪያዎች እንሆናለን።”
እሱም “እሺ፣ እንዳላችሁት ይሁን፤ ጽዋው የተገኘበት ሰው ባሪያዬ ይሆናል፤ የቀራችሁት ግን ነፃ ትሆናላችሁ” አላቸው።
ከዚያም እያንዳንዳቸው ወዲያውኑ ከረጢታቸውን መሬት አውርደው መፍታት ጀመሩ።
እሱም ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ በጥንቃቄ ፈተሸ። በመጨረሻም ጽዋው በቢንያም ከረጢት ውስጥ ተገኘ።
በዚህ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ እያንዳንዳቸውም ጓዛቸውን መልሰው በአህዮቻቸው ላይ በመጫን ወደ ከተማዋ ተመለሱ።
ይሁዳና ወንድሞቹ ወደ ዮሴፍ ቤት ሲገቡ ዮሴፍ ገና ከቤት አልወጣም ነበር፤ እነሱም በፊቱ መሬት ላይ ተደፉ።
ዮሴፍም “ይህ ያደረጋችሁት ነገር ምንድን ነው? እንደ እኔ ያለ ሰው ማንኛውንም ነገር በጥንቆላ የማወቅ ችሎታ እንዳለው አታውቁም?” አላቸው።
በዚህ ጊዜ ይሁዳ እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ ለጌታዬ ምን ማለት እንችላለን? ምንስ አፍ አለን? ጻድቅ መሆናችንን እንዴት ማረጋገጥ እንችላለን? እውነተኛው አምላክ ባሪያዎችህ የፈጸሙትን ስህተት አጋልጧል። እንግዲህ እኛም ሆን ጽዋው የተገኘበት ሰው ለጌታዬ ባሪያዎች እንሆናለን!”
እሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ይህንማ ፈጽሞ አላደርገውም! ባሪያዬ የሚሆነው ጽዋው የተገኘበት ሰው ነው። የቀራችሁት ግን ወደ አባታችሁ በሰላም ሂዱ።”
ይሁዳም ወደ እሱ ቀርቦ እንዲህ አለው፦ “እባክህ ጌታዬ እማጸንሃለሁ፤ ባሪያህ አንዲት ቃል ብቻ ይናገር፤ ጌታዬም ይስማው፤ እባክህ በባሪያህ ላይ አትቆጣ፤ ምክንያቱም አንተ ልክ እንደ ፈርዖን ነህ።
ጌታዬ እኛን ባሪያዎቹን ‘አባት ወይም ወንድም አላችሁ?’ በማለት ጠይቆን ነበር።
እኛም ለጌታዬ እንዲህ ስንል መለስንለት፦ ‘አረጋዊ አባት አለን፤ እንዲሁም በስተርጅናው የወለደው የሁላችንም ታናሽ የሆነ ወንድም አለን። ወንድሙ ግን ሞቷል፤ በመሆኑም ከአንድ እናት ከተወለዱት መካከል የቀረው እሱ ብቻ ነው፤ አባቱም በጣም ይወደዋል።’
ከዚያም አንተ እኛን ባሪያዎችህን ‘እንዳየው ወደ እኔ አምጡት’ አልከን።
እኛ ግን ጌታዬን ‘ልጁ ከአባቱ ሊለይ አይችልም። ከተለየው ደግሞ አባቱ ያለጥርጥር ይሞታል’ አልነው።
አንተም እኛን ባሪያዎችህን ‘ትንሹን ወንድማችሁን ይዛችሁት ካልመጣችሁ ከእንግዲህ ፊቴን አታዩም’ አልከን።
“በመሆኑም ወደ ባሪያህ ወደ አባታችን ሄደን የጌታዬን ቃል ነገርነው።
ከጊዜ በኋላም አባታችን ‘ተመልሳችሁ ሂዱና ጥቂት እህል ግዙልን’ አለን።
እኛ ግን እንዲህ አልነው፦ ‘ወደዚያ መሄድ አንችልም። ትንሹ ወንድማችን ከእኛ ጋር ካልሄደ የሰውየውን ፊት ማየት ስለማንችል ትንሹ ወንድማችን አብሮን የሚሄድ ከሆነ ወደዚያ እንወርዳለን።’
በዚህ ጊዜ ባሪያህ አባታችን እንዲህ አለን፦ ‘ሚስቴ ከሁለት ወንዶች ልጆች ሌላ ምንም እንዳልወለደችልኝ እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁ።
ሆኖም አንዱ እንደወጣ በመቅረቱ “መቼም አውሬ ቦጫጭቆት መሆን አለበት!” አልኩ፤ ይኸው ከዚያን ጊዜ ወዲህ አይቼው አላውቅም።
ይሄኛውንም ልጅ ከእኔ ለይታችሁ ብትወስዱትና አደጋ ደርሶበት ቢሞት ሽበቴን በሥቃይ ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ።’
“እንግዲህ ወደ ባሪያህ ወደ አባቴ ስመለስ ልጁ ከእኛ ጋር ከሌለ፣ የአባታችን ሕይወት ከልጁ ሕይወት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ስለሆነ
አባታችን ልጁ አብሮን አለመኖሩን ሲያይ ይሞታል፤ ባሪያዎችህም የባሪያህን የአባታችንን ሽበት በሐዘን ወደ መቃብር ያወርዱታል።
እኔ ባሪያህ ‘ልጁን ወደ አንተ መልሼ ባላመጣው በአባቴ ፊት ለዘላለም በደለኛ ልሁን’ ብዬ ለአባቴ ቃል ገብቻለሁ።
ስለዚህ እባክህ ልጁ ከወንድሞቹ ጋር እንዲሄድ እኔ ባሪያህ በልጁ ፋንታ እዚሁ ቀርቼ ለጌታዬ ባሪያ ልሁን።
ልጁን ሳልይዝ እንዴት ወደ አባቴ እመለሳለሁ? በአባቴ ላይ እንዲህ ያለ መከራ ሲደርስ ማየት አልችልም!”
የኖኅ ወንዶች ልጆች የሆኑት የሴም፣ የካም እና የያፌት ታሪክ ይህ ነው። ከጥፋት ውኃ በኋላ ወንዶች ልጆች ወለዱ።
የያፌት ወንዶች ልጆች ጎሜር፣ ማጎግ፣ ማዳይ፣ ያዋን፣ ቱባል፣ መሼቅ እና ቲራስ ነበሩ።
የጎሜር ወንዶች ልጆች አሽከናዝ፣ ሪፋት እና ቶጋርማ ነበሩ።
የያዋን ወንዶች ልጆች ኤሊሻ፣ ተርሴስ፣ ኪቲም እና ዶዳኒም ነበሩ።
በደሴቶች ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች እንደየቋንቋቸውና እንደየቤተሰባቸው በየብሔራቸው በመሆን ወደየምድራቸው የተሰራጩት ከእነዚህ ነው።
የካም ወንዶች ልጆች ኩሽ፣ ሚጽራይም፣ ፑጥ እና ከነአን ነበሩ።
የኩሽ ወንዶች ልጆች ሴባ፣ ሃዊላ፣ ሳብታ፣ ራአማ እና ሳብተካ ነበሩ። የራአማ ወንዶች ልጆች ሳባ እና ዴዳን ነበሩ።
ኩሽ ናምሩድን ወለደ። እሱም በምድር ላይ የመጀመሪያው ኃያል ሰው ነበር።
እሱም ይሖዋን የሚቃወም ኃያል አዳኝ ሆነ። በዚህም የተነሳ “እንደ ናምሩድ ያለ ይሖዋን የሚቃወም ኃያል አዳኝ” ይባል ነበር።
የግዛቱ መጀመሪያም በሰናኦር ምድር የሚገኙት ባቤል፣ ኤሬክ፣ አካድ እና ካልኔ ነበሩ።
ከዚያ ምድር ተነስቶም ወደ አሦር በመሄድ ነነዌን፣ ረሆቦትኢርን እና ካላህን ቆረቆረ፤
እንዲሁም በነነዌና በካላህ መካከል የምትገኘውን ረሰንን ቆረቆረ፤ እሷም ታላቋ ከተማ ናት።
ሚጽራይም ሉድን፣ አናሚምን፣ ለሃቢምን፣ ናፊቱሂምን፣
ጳትሩሲምን፣ ካስሉሂምን (ፍልስጤማውያን የተገኙት ከእሱ ነው) እንዲሁም ካፍቶሪምን ወለደ።
ከነአን የበኩር ልጁን ሲዶናን፣ ሄትን
እንዲሁም ኢያቡሳዊውን፣ አሞራዊውን፣ ገርጌሻዊውን፣
ሂዋዊውን፣ አርቃዊውን፣ ሲናዊውን፣
አርዋዳዊውን፣ ጸማራዊውን እና ሃማታዊውን ወለደ። ከዚያ በኋላ የከነአናውያን ቤተሰቦች ተበተኑ።
በመሆኑም የከነአናውያን ወሰን ከሲዶና አንስቶ በጋዛ አቅራቢያ እስካለችው እስከ ጌራራ እንዲሁም እስከ ሰዶም፣ ገሞራ፣ አድማህ እና በላሻ አቅራቢያ እስካለችው እስከ ጸቦይም ድረስ ያለው ነበር።
የካም ወንዶች ልጆች እንደየቤተሰባቸውና እንደየቋንቋቸው በየአገራቸውና በየብሔራቸው እነዚህ ነበሩ።
የኤቤር ወንዶች ልጆች ሁሉ ቅድመ አያትና የታላቅየው የያፌት ወንድም የሆነው ሴምም ልጆች ወለደ።
የሴም ወንዶች ልጆች ኤላም፣ አሹር፣ አርፋክስድ፣ ሉድ እና አራም ነበሩ።
የአራም ወንዶች ልጆች ዑጽ፣ ሁል፣ ጌተር እና ማሽ ነበሩ።
አርፋክስድ ሴሎምን ወለደ፤ ሴሎምም ኤቤርን ወለደ።
ኤቤር ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ። የአንደኛው ስም ፋሌቅ ነበር፤ ምክንያቱም በእሱ የሕይወት ዘመን ምድር ተከፋፍላ ነበር። የወንድሙ ስም ደግሞ ዮቅጣን ነበር።
ዮቅጣን አልሞዳድን፣ ሸሌፍን፣ ሃጻርማዌትን፣ ያራህን፣
ሃዶራምን፣ ዑዛልን፣ ዲቅላን፣
ኦባልን፣ አቢማዔልን፣ ሳባን፣
ኦፊርን፣ ሃዊላን እና ዮባብን ወለደ፤ እነዚህ ሁሉ የዮቅጣን ወንዶች ልጆች ነበሩ።
መኖሪያ ስፍራቸውም ከሜሻ አንስቶ እስከ ሰፋር ይኸውም እስከ ምሥራቅ ተራራማ አካባቢ ድረስ ይዘልቃል።
የሴም ወንዶች ልጆች እንደየቤተሰባቸውና እንደየቋንቋቸው በየአገራቸውና በየብሔራቸው እነዚህ ነበሩ።
የኖኅ ወንዶች ልጆች ቤተሰቦች እንደየዘር ሐረጋቸው በየብሔራቸው እነዚህ ነበሩ። ከጥፋት ውኃው በኋላ ብሔራት ሁሉ በምድር ላይ የተሰራጩት ከእነዚህ ነበር።
የአብራም ሚስት ሦራ ለአብራም ልጆች አልወለደችለትም ነበር፤ ይሁንና አጋር የምትባል አንዲት ግብፃዊት አገልጋይ ነበረቻት።
በመሆኑም ሦራ አብራምን እንዲህ አለችው፦ “እንግዲህ እንደምታየው ይሖዋ ልጆች እንዳልወልድ አድርጎኛል። እባክህ ከአገልጋዬ ጋር ግንኙነት ፈጽም። ምናልባትም በእሷ አማካኝነት ልጆች ላገኝ እችላለሁ።” ስለሆነም አብራም የሦራን ቃል ሰማ።
አብራም በከነአን ምድር ለአሥር ዓመት ያህል ከኖረ በኋላ የአብራም ሚስት ሦራ ግብፃዊት አገልጋይዋን አጋርን ወስዳ ሚስት እንድትሆነው ለባሏ ለአብራም ሰጠችው።
በመሆኑም አብራም ከአጋር ጋር ግንኙነት ፈጸመ፤ እሷም ፀነሰች። መፀነሷን ባወቀች ጊዜም እመቤቷን መናቅ ጀመረች።
በዚህ ጊዜ ሦራ አብራምን እንዲህ አለችው፦ “ለደረሰብኝ በደል ተጠያቂው አንተ ነህ። አገልጋዬን በእቅፍህ ያደረግኩልህ እኔው ራሴ ነበርኩ፤ እሷ ግን መፀነሷን ባወቀች ጊዜ ትንቀኝ ጀመር። ይሖዋ በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ።”
በመሆኑም አብራም ሦራን “እንግዲህ አገልጋይሽ እንደሆነች በእጅሽ ናት። መልካም መስሎ የታየሽን ነገር አድርጊባት” አላት። ከዚያም ሦራ አገልጋይዋን አዋረደቻት፤ ስለዚህም ጥላት ኮበለለች።
በኋላም የይሖዋ መልአክ አጋርን በምድረ በዳ በሚገኝ አንድ የውኃ ምንጭ አጠገብ ማለትም ወደ ሹር በሚወስደው መንገድ ላይ ባለው ምንጭ አጠገብ አገኛት።
እሱም “የሦራ አገልጋይ አጋር፣ ለመሆኑ የመጣሽው ከየት ነው? ወዴትስ እየሄድሽ ነው?” አላት። እሷም መልሳ “ከእመቤቴ ከሦራ ኮብልዬ እየሄድኩ ነው” አለች።
የይሖዋም መልአክ “ወደ እመቤትሽ ተመለሽ፤ ለእሷም በትሕትና ተገዢላት” አላት።
ከዚያም የይሖዋ መልአክ “ከብዛቱ የተነሳ የማይቆጠር እስኪሆን ድረስ ዘርሽን እጅግ አበዛዋለሁ” አላት።
በተጨማሪም የይሖዋ መልአክ እንዲህ አላት፦ “እንግዲህ ይኸው ፀንሰሻል፤ ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ። ስሙንም እስማኤል ትይዋለሽ፤ ምክንያቱም ይሖዋ የሥቃይ ጩኸትሽን ሰምቷል።
እሱም እንደ ዱር አህያ ይሆናል። ባገኘው ሰው ሁሉ ላይ እጁን ያነሳል፤ ያገኘውም ሰው ሁሉ እጁን ያነሳበታል፤ ከወንድሞቹም ሁሉ ፊት ለፊት ይኖራል።”
ከዚያም አጋር “የሚያየኝን አሁን በእርግጥ አየሁት ማለት ነው?” ብላ ስላሰበች እያነጋገራት የነበረውን ይሖዋን ስሙን ጠርታ “አንተ የምታይ አምላክ ነህ” አለች።
የውኃ ጉድጓዱ ብኤርላሃይሮዒ ተብሎ የተጠራው በዚህ የተነሳ ነው። (ጉድጓዱም በቃዴስና በቤሬድ መካከል ይገኛል።)
ስለዚህ አጋር ለአብራም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ አብራምም አጋር የወለደችለትን ልጅ እስማኤል ብሎ ስም አወጣለት።
አጋር ለአብራም እስማኤልን በወለደችለት ጊዜ አብራም የ86 ዓመት ሰው ነበር።
የአዳምን ታሪክ የያዘው መጽሐፍ ይህ ነው። አምላክ አዳምን በፈጠረበት ቀን፣ በአምላክ አምሳል ሠራው።
ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። በተፈጠሩበትም ቀን ባረካቸው፤ እንዲሁም ሰው ብሎ ጠራቸው።
አዳም 130 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም እሱን የሚመስል ወንድ ልጅ በራሱ አምሳያ ወለደ፤ ስሙንም ሴት አለው።
አዳም ሴትን ከወለደ በኋላ 800 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።
ስለዚህ አዳም በአጠቃላይ 930 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።
ሴት 105 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሄኖስን ወለደ።
ሴትም ሄኖስን ከወለደ በኋላ 807 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።
ስለዚህ ሴት በአጠቃላይ 912 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።
ሄኖስ 90 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ቃይናንን ወለደ።
ሄኖስም ቃይናንን ከወለደ በኋላ 815 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።
ስለዚህ ሄኖስ በአጠቃላይ 905 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።
ቃይናን 70 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም መላልኤልን ወለደ።
ቃይናንም መላልኤልን ከወለደ በኋላ 840 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።
ስለዚህ ቃይናን በአጠቃላይ 910 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።
መላልኤል 65 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ያሬድን ወለደ።
መላልኤልም ያሬድን ከወለደ በኋላ 830 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።
ስለዚህ መላልኤል በአጠቃላይ 895 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።
ያሬድ 162 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሄኖክን ወለደ።
ያሬድም ሄኖክን ከወለደ በኋላ 800 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።
ስለዚህ ያሬድ በአጠቃላይ 962 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።
ሄኖክ 65 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ማቱሳላን ወለደ።
ሄኖክ ማቱሳላን ከወለደ በኋላ ለ300 ዓመት ከእውነተኛው አምላክ ጋር መሄዱን ቀጠለ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።
ስለዚህ ሄኖክ በአጠቃላይ 365 ዓመት ኖረ።
ሄኖክ ከእውነተኛው አምላክ ጋር መሄዱን ቀጠለ። አምላክ ስለወሰደውም ከዚያ በኋላ አልተገኘም።
ማቱሳላ 187 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ላሜህን ወለደ።
ማቱሳላም ላሜህን ከወለደ በኋላ 782 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።