text
stringlengths
4
267
ስለዚህ ማቱሳላ በአጠቃላይ 969 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።
ላሜህ 182 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ወንድ ልጅ ወለደ።
እሱም “ይህ ልጅ፣ ይሖዋ በረገማት ምድር የተነሳ ከምንለፋው ልፋትና ከምንደክመው ድካም በማሳረፍ ያጽናናናል” በማለት ስሙን ኖኅ ብሎ ጠራው።
ላሜህም ኖኅን ከወለደ በኋላ 595 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።
ስለዚህ ላሜህ በአጠቃላይ 777 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።
ኖኅ 500 ዓመት ከሆነው በኋላ ሴምን፣ ካምንና ያፌትን ወለደ።
በመሆኑም እስራኤል ያለውን ሁሉ ይዞ ተነሳ። ቤርሳቤህ በደረሰ ጊዜም ለአባቱ ለይስሐቅ አምላክ መሥዋዕቶችን አቀረበ።
ከዚያም አምላክ ለእስራኤል ሌሊት በራእይ ተገልጦለት “ያዕቆብ፣ ያዕቆብ!” ሲል ጠራው፤ እሱም “አቤት!” አለ።
አምላክም እንዲህ አለው፦ “እኔ የአባትህ አምላክ የሆንኩት እውነተኛው አምላክ ነኝ። ወደ ግብፅ ለመውረድ አትፍራ፤ ምክንያቱም በዚያ ታላቅ ብሔር አደርግሃለሁ።
እኔ ራሴ ከአንተ ጋር ወደ ግብፅ እወርዳለሁ፤ ደግሞም እኔ ራሴ ከዚያ አወጣሃለሁ፤ ዮሴፍም ዓይኖችህን በእጁ ይከድናል።”
ከዚያ በኋላ ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነሳ፤ የእስራኤል ወንዶች ልጆችም አባታቸውን ያዕቆብን፣ ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን ፈርዖን በላከለት ሠረገሎች ላይ አሳፍረው ጉዞ ጀመሩ።
እነሱም በከነአን ምድር ያፈሩትን ንብረትና መንጎቻቸውን ይዘው ሄዱ። ከዚያም ያዕቆብና ከእሱ ጋር የነበሩት ልጆቹ በሙሉ ወደ ግብፅ መጡ።
እሱም ወንዶች ልጆቹንና ወንዶች የልጅ ልጆቹን እንዲሁም ሴቶች ልጆቹንና ሴቶች የልጅ ልጆቹን ይኸውም ዘሮቹን ሁሉ ይዞ ወደ ግብፅ መጣ።
ወደ ግብፅ የመጡት የእስራኤል ማለትም የያዕቆብ ወንዶች ልጆች ስም ይህ ነው፦ የያዕቆብ የበኩር ልጅ ሮቤል።
የሮቤል ወንዶች ልጆች ሃኖክ፣ ፓሉ፣ ኤስሮን እና ካርሚ ነበሩ።
የስምዖን ወንዶች ልጆች የሙኤል፣ ያሚን፣ ኦሃድ፣ ያኪን፣ ጾሃር እንዲሁም ከአንዲት ከነአናዊት የወለደው ሻኡል ነበሩ።
የሌዊ ወንዶች ልጆች ጌድሶን፣ ቀአት እና ሜራሪ ነበሩ።
የይሁዳ ወንዶች ልጆች ኤር፣ ኦናን፣ ሴሎም፣ ፋሬስ እና ዛራ ነበሩ፤ ይሁንና ኤር እና ኦናን በከነአን ምድር ሞቱ። የፋሬስ ወንዶች ልጆች ኤስሮን እና ሃሙል ነበሩ።
የይሳኮር ወንዶች ልጆች ቶላ፣ ፑዋ፣ ዮብ እና ሺምሮን ነበሩ።
የዛብሎን ወንዶች ልጆች ሰሬድ፣ ኤሎን እና ያህልኤል ነበሩ።
ሴት ልጁን ዲናን ጨምሮ እነዚህ ሊያ በጳዳንአራም ለያዕቆብ የወለደችለት ልጆች ናቸው። በአጠቃላይ ወንዶች ልጆቹና ሴቶች ልጆቹ 33 ነበሩ።
የጋድ ወንዶች ልጆች ጺፍዮን፣ ሃጊ፣ ሹኒ፣ ኤጽቦን፣ ኤሪ፣ አሮድ እና አርዔላይ ነበሩ።
የአሴር ወንዶች ልጆች ይምናህ፣ ይሽዋ፣ ይሽዊ እና በሪአ ሲሆኑ እህታቸውም ሴራህ ትባላለች። የበሪአ ወንዶች ልጆች ሄቤር እና ማልኪኤል ነበሩ።
ላባ ለልጁ ለሊያ የሰጣት ዚልጳ የተባለችው አገልጋይ የወለደቻቸው ወንዶች ልጆች እነዚህ ናቸው። እሷም ለያዕቆብ እነዚህን ወለደችለት፤ እነሱም በአጠቃላይ 16 ነበሩ።
የያዕቆብ ሚስት የራሔል ወንዶች ልጆች ዮሴፍና ቢንያም ነበሩ።
ዮሴፍ በግብፅ ምድር ሳለ ምናሴንና ኤፍሬምን ወለደ፤ እነዚህም የኦን ካህን የሆነው የጶጥፌራ ልጅ አስናት የወለደችለት ናቸው።
የቢንያም ወንዶች ልጆች ቤላ፣ ቤኬር፣ አሽቤል፣ ጌራ፣ ንዕማን፣ ኤሂ፣ ሮሽ፣ ሙጲም፣ ሁፒም እና አርድ ነበሩ።
እነዚህ ራሔል ለያዕቆብ የወለደችለት ወንዶች ልጆች ናቸው፤ እነሱም በአጠቃላይ 14 ነበሩ።
የዳን ልጅ ሁሺም ነበር።
የንፍታሌም ወንዶች ልጆች ያህጽኤል፣ ጉኒ፣ የጼር እና ሺሌም ነበሩ።
ላባ ለልጁ ለራሔል የሰጣት ባላ የተባለችው አገልጋይ የወለደቻቸው ወንዶች ልጆች እነዚህ ናቸው። እሷም ለያዕቆብ እነዚህን ወለደችለት፤ እነሱም በአጠቃላይ ሰባት ነበሩ።
የያዕቆብ ዝርያዎች የሆኑትና ከእሱ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት ሰዎች፣ የልጆቹን ሚስቶች ሳይጨምር በአጠቃላይ 66 ነበሩ።
ዮሴፍ በግብፅ የወለዳቸው ወንዶች ልጆች ሁለት ነበሩ። ወደ ግብፅ የገቡት የያዕቆብ ቤተሰቦች በአጠቃላይ 70 ነበሩ።
ያዕቆብ ወደ ጎሸን እየሄደ መሆኑን ለዮሴፍ እንዲነግረው ይሁዳን ከእሱ አስቀድሞ ላከው። ወደ ጎሸን ምድር በደረሱም ጊዜ
ዮሴፍ ሠረገላው እንዲዘጋጅለት ካደረገ በኋላ አባቱን እስራኤልን ለመቀበል ወደ ጎሸን ሄደ። ባገኘውም ጊዜ አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ረዘም ላለ ጊዜ አለቀሰ።
ከዚያም እስራኤል ዮሴፍን “ከእንግዲህ ብሞት አይቆጨኝም፤ ዓይንህን ለማየት በቅቻለሁ፤ በሕይወት መኖርህንም አረጋግጫለሁ” አለው።
ከዚያም ዮሴፍ ወንድሞቹንና የአባቱን ቤተሰቦች እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ፈርዖን ወጥቼ ሁኔታውን ልንገረው፤ እንዲህም ልበለው፦ ‘በከነአን ምድር ይኖሩ የነበሩት ወንድሞቼና የአባቴ ቤተሰቦች ወደ እኔ መጥተዋል።
እነሱ እረኞችና ከብት አርቢዎች ናቸው፤ መንጎቻቸውን፣ ከብቶቻቸውንና ያላቸውን ሁሉ ይዘው መጥተዋል።’
እንግዲህ ፈርዖን ጠርቶ ‘ሥራችሁ ምንድን ነው?’ ብሎ ሲጠይቃችሁ
‘እኛ አገልጋዮችህም ሆን የቀድሞ አባቶቻችን ከልጅነታችን ጀምሮ ከብት አርቢዎች ነን’ በሉት። ግብፃውያን በግ ጠባቂዎችን ስለሚጸየፉ በጎሸን ምድር እንድትኖሩ ይፈቅድላችኋል።”
በዚያን ጊዜ የሰናኦር ንጉሥ አምራፌል፣ የኤላሳር ንጉሥ አርዮክ፣ የኤላም ንጉሥ ኮሎዶጎምር እና የጎይም ንጉሥ ቲድአል
ከሰዶም ንጉሥ ከቤራ፣ ከገሞራ ንጉሥ ከቢርሻ፣ ከአድማህ ንጉሥ ከሺንአብ፣ ከጸቦይም ንጉሥ ከሸሜበር እና ከቤላ ማለትም ከዞአር ንጉሥ ጋር ጦርነት ገጠሙ።
እነዚህ ሁሉ በሲዲም ሸለቆ ማለትም በጨው ባሕር ሠራዊታቸውን አሰባሰቡ።
እነሱም ኮሎዶጎምርን 12 ዓመት አገለገሉት፤ በ13ኛው ዓመት ግን ዓመፁ።
ስለሆነም በ14ኛው ዓመት ኮሎዶጎምርና አብረውት የነበሩት ነገሥታት መጥተው ረፋይምን በአስተሮትቃርናይም፣ ዙዚምን በሃም፣ ኤሚምን በሻዌቂሪያታይም፣
ሆራውያንን ደግሞ ሴይር ከሚባለው ተራራቸው አንስቶ በምድረ በዳ እስከሚገኘው እስከ ኤልጳራን ድረስ በሚዘልቀው ስፍራ ድል አደረጓቸው።
ከዚያም ቃዴስ ወደምትባለው ወደ ኤንሚሽጳጥ ተመልሰው በመምጣት መላውን የአማሌቃውያን ግዛትና በሃጻጾንታማር ይኖሩ የነበሩትን አሞራውያንን ድል አደረጉ።
በዚህ ጊዜ የሰዶም ንጉሥ፣ የገሞራ ንጉሥ፣ የአድማህ ንጉሥ፣ የጸቦይም ንጉሥ እንዲሁም የቤላ ማለትም የዞአር ንጉሥ ከእነሱ ጋር ለመዋጋት ሠራዊታቸውን አስተባብረው በሲዲም ሸለቆ ውስጥ ለጦርነት ተሰለፉ፤
የኤላምን ንጉሥ ኮሎዶጎምርን፣ የጎይምን ንጉሥ ቲድአልን፣ የሰናኦርን ንጉሥ አምራፌልን እንዲሁም የኤላሳርን ንጉሥ አርዮክን ለመውጋት ተነሱ፤ አራቱ ነገሥታት ከአምስቱ ጋር ተዋጉ።
የሲዲም ሸለቆ በቅጥራን ጉድጓዶች የተሞላ ነበር፤ የሰዶምና የገሞራ ነገሥታት ሸሽተው ለማምለጥ ሲሞክሩ እነዚህ ጉድጓዶች ውስጥ ወደቁ፤ የቀሩት ደግሞ ወደ ተራራማው አካባቢ ሸሹ።
ከዚያም ድል አድራጊዎቹ የሰዶምንና የገሞራን ንብረት በሙሉ እንዲሁም ምግባቸውን ሁሉ ይዘው ሄዱ።
በተጨማሪም በሰዶም ይኖር የነበረውን የአብራምን የወንድም ልጅ ሎጥን ከነንብረቱ ይዘውት ሄዱ።
ከዚያም አንድ ያመለጠ ሰው መጥቶ ለዕብራዊው ለአብራም ነገረው። በዚያን ጊዜ አብራም የኤሽኮል እና የአኔር ወንድም በሆነው በአሞራዊው በማምሬ ትላልቅ ዛፎች አጠገብ ይኖር ነበር። እነዚህ ሰዎች የአብራም አጋሮች ነበሩ።
በዚህ መንገድ አብራም ዘመዱ በምርኮ መወሰዱን ሰማ። ስለሆነም በቤቱ የተወለዱትን 318 የሠለጠኑ አገልጋዮች ሰብስቦ ተነሳ፤ ወራሪዎቹንም ተከትሎ እስከ ዳን ድረስ ሄደ።
በሌሊትም ሠራዊቱን ከፋፈለ፤ እሱና አገልጋዮቹም በወራሪዎቹ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ድል አደረጓቸው። እሱም ከደማስቆ በስተ ሰሜን እስከምትገኘው እስከ ሆባ ድረስ አሳደዳቸው።
የወሰዷቸውን ንብረቶችም ሁሉ አስመለሰ፤ በተጨማሪም ዘመዱን ሎጥንና ንብረቶቹን እንዲሁም ሴቶቹንና ሌሎቹን ሰዎች አስመለሰ።
አብራም ኮሎዶጎምርንና ከእሱ ጋር የነበሩትን ነገሥታት ድል አድርጎ ከተመለሰ በኋላ የሰዶም ንጉሥ ከአብራም ጋር ለመገናኘት ወደ ሻዌ ሸለቆ ማለትም ወደ ንጉሡ ሸለቆ ወጣ።
የሳሌም ንጉሥ መልከጼዴቅም ምግብና የወይን ጠጅ ይዞ ወጣ፤ እሱም የልዑሉ አምላክ ካህን ነበር።
አብራምንም ባረከው፤ እንዲህም አለው፦ “ሰማይንና ምድርን የሠራውልዑሉ አምላክ አብራምን ይባርክ፤
የሚጨቁኑህን በእጅህ አሳልፎ የሰጠህ፣ልዑሉ አምላክ ይወደስ!” አብራምም ከሁሉም ነገር ላይ አንድ አሥረኛውን ሰጠው።
ከዚያም የሰዶም ንጉሥ አብራምን “ሰዎቹን ስጠኝ፤ ንብረቶቹን ግን ለራስህ ውሰድ” አለው።
አብራም ግን የሰዶምን ንጉሥ እንዲህ አለው፦ “ሰማይንና ምድርን ወደሠራው ወደ ልዑሉ አምላክ ወደ ይሖዋ እጄን አንስቼ እምላለሁ፣
‘አብራምን አበለጸግኩት’ እንዳትል የአንተ ከሆነው ነገር ምንም አልወስድም፤ ሌላው ቀርቶ ብጣሽ ክርም ሆነ የጫማ ማሰሪያ አልወስድም።
ወጣቶቹ ከበሉት ምግብ በስተቀር ምንም ነገር አልወስድም። ከእኔ ጋር የዘመቱት አኔር፣ ኤሽኮልና ማምሬ ግን ድርሻቸውን ይውሰዱ።”
በመሆኑም ይስሐቅ ያዕቆብን ጠርቶ ባረከውና እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “ከከነአን ሴቶች ልጆች ሚስት እንዳታገባ።
በጳዳንአራም ወደሚገኘው ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ሂድና ከእናትህ ወንድም ከላባ ሴቶች ልጆች መካከል አንዷን አግባ።
ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ይባርክሃል፤ ፍሬያማም ያደርግሃል፤ እንዲሁም ያበዛሃል፤ አንተም በእርግጥ ብዙ ሕዝብ ያቀፈ ጉባኤ ትሆናለህ።
አምላክ ለአብርሃም የሰጠውን፣ አንተም እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆነህ የምትኖርበትን ምድር እንድትወርስ የአብርሃምን በረከት ለአንተና ከአንተ ጋር ላለው ዘርህ ይሰጣል።”
ስለሆነም ይስሐቅ ያዕቆብን አሰናበተው፤ እሱም የያዕቆብና የኤሳው እናት የርብቃ ወንድም እንዲሁም የአራማዊው የባቱኤል ልጅ ወደሆነው ወደ ላባ ለመሄድ ወደ ጳዳንአራም ጉዞ ጀመረ።
ኤሳው፣ ይስሐቅ ያዕቆብን እንደባረከውና ሚስት እንዲያገባ ወደ ጳዳንአራም እንደላከው እንዲሁም በባረከው ጊዜ “ከከነአን ሴቶች ልጆች ሚስት እንዳታገባ” ብሎ እንዳዘዘውና
ያዕቆብም አባቱንና እናቱን በመታዘዝ ወደ ጳዳንአራም እንደሄደ አወቀ።
በዚህ ጊዜ ኤሳው የከነአን ሴቶች ልጆች በአባቱ በይስሐቅ ዘንድ የተጠሉ መሆናቸውን ተገነዘበ፤
ስለዚህ ኤሳው ወደ እስማኤል ሄደ፤ ካሉትም ሚስቶች በተጨማሪ የአብርሃም ልጅ እስማኤል የወለዳትን የነባዮትን እህት ማሃላትን አገባ።
ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነስቶ ወደ ካራን አቀና።
ከዚያም ወደ አንድ ስፍራ ደረሰ፤ ፀሐይ ጠልቃ ስለነበረም እዚያ ለማደር አሰበ። በመሆኑም በአካባቢው ካሉት ድንጋዮች አንዱን አንስቶ በመንተራስ እዚያው ተኛ።
እሱም ሕልም አለመ፤ በሕልሙም በምድር ላይ የተተከለ ደረጃ አየ፤ የደረጃውም ጫፍ እስከ ሰማያት ይደርስ ነበር፤ በላዩም ላይ የአምላክ መላእክት ይወጡና ይወርዱ ነበር።
ከደረጃውም በላይ ይሖዋ ነበር፤ እሱም እንዲህ አለ፦ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክና የይስሐቅ አምላክ ይሖዋ ነኝ። የተኛህበትን ምድር ለአንተና ለዘርህ እሰጣለሁ።
ዘርህም በእርግጥ እንደ ምድር አፈር ብዙ ይሆናል፤ ወደ ምዕራብ፣ ወደ ምሥራቅ፣ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ ትስፋፋለህ። የምድር ቤተሰቦች ሁሉ በአንተና በዘርህ አማካኝነት በእርግጥ ይባረካሉ።
እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፤ በምትሄድበት ሁሉ እጠብቅሃለሁ፤ ወደዚህችም ምድር እመልስሃለሁ። የገባሁልህን ቃል እስክፈጽምልህ ድረስ አልተውህም።”
ከዚያም ያዕቆብ ከእንቅልፉ ነቅቶ “በእርግጥም በዚህ ስፍራ ይሖዋ አለ፤ እኔ ግን ይህን አላወቅኩም ነበር” አለ።
እሱም በፍርሃት ተዋጠ፤ እንዲህም አለ፦ “ይህ ስፍራ እንዴት የሚያስፈራ ነው! ይህ የአምላክ ቤት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፤ ይህ የሰማያት በር ነው።”
በመሆኑም ያዕቆብ በማለዳ ተነሳ፤ ተንተርሶት የነበረውን ድንጋይ ወስዶ እንደ ዓምድ አቆመው፤ በአናቱም ላይ ዘይት አፈሰሰበት።
ስለዚህ ያን ቦታ ቤቴል አለው፤ የከተማዋ የቀድሞ ስም ግን ሎዛ ነበር።
ከዚያም ያዕቆብ እንዲህ ሲል ስእለት ተሳለ፦ “አምላክ ከእኔ ባይለይና በመንገዴ ቢጠብቀኝ እንዲሁም የምበላው ምግብና የምለብሰው ልብስ ቢሰጠኝ፣
ወደ አባቴም ቤት በሰላም ብመለስ ይሖዋ አምላኬ መሆኑን አስመሠከረ ማለት ነው።
እንደ ዓምድ ያቆምኩት ይህ ድንጋይም የአምላክ ቤት ይሆናል፤ አምላክ ሆይ፣ እኔም ከምትሰጠኝ ከማንኛውም ነገር አንድ አሥረኛውን ለአንተ እሰጣለሁ።”
ከዚህ በኋላ እውነተኛው አምላክ አብርሃምን ፈተነው፤ “አብርሃም!” ሲል ጠራው፤ እሱም መልሶ “አቤት!” አለ።
ከዚያም አምላክ እንዲህ አለው፦ “እባክህ ልጅህን፣ በጣም የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ፤ በዚያም እኔ በማሳይህ በአንዱ ተራራ ላይ የሚቃጠል መባ አድርገህ አቅርበው።”
ስለዚህ አብርሃም በማለዳ ተነስቶ አህያውን ከጫነ በኋላ ከአገልጋዮቹ መካከል ሁለቱን ከልጁ ከይስሐቅ ጋር ይዞ ለመሄድ ተነሳ። ለሚቃጠል መባ የሚሆን እንጨትም ፈለጠ፤ ከዚያም ተነስቶ እውነተኛው አምላክ ወዳሳየው ስፍራ ተጓዘ።
በሦስተኛውም ቀን አብርሃም ቀና ብሎ ቦታውን ከሩቅ ተመለከተ።
በዚህ ጊዜ አብርሃም አገልጋዮቹን “እናንተ አህያውን ይዛችሁ እዚህ ቆዩ፤ እኔና ልጄ ግን ወደዚያ በመሄድ በአምላክ ፊት ሰግደን ወደ እናንተ እንመለሳለን” አላቸው።
ስለዚህ አብርሃም ለሚቃጠል መባ የሚሆነውን እንጨት ወስዶ ልጁን ይስሐቅን አሸከመው። እሱ ደግሞ እሳቱንና ቢላውን ያዘ፤ ሁለቱም አብረው ሄዱ።
ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን “አባዬ!” ሲል ጠራው። እሱም መልሶ “አቤት ልጄ!” አለው። ይስሐቅም “እሳቱና እንጨቱ ይኸውና፤ ለሚቃጠል መባ የሚሆነው በግ ግን የት አለ?” አለው።
በዚህ ጊዜ አብርሃም “ልጄ፣ ለሚቃጠል መባ የሚሆነውን በግ አምላክ ራሱ ያዘጋጃል” አለው። ሁለቱም አብረው ጉዟቸውን ቀጠሉ።
በመጨረሻም እውነተኛው አምላክ ወዳሳየው ስፍራ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሠዊያ ሠርቶ እንጨቱን ረበረበበት። ልጁን ይስሐቅንም እጁንና እግሩን አስሮ በመሠዊያው ላይ በተረበረበው እንጨት ላይ አጋደመው።
ከዚያም አብርሃም ልጁን ለማረድ እጁን ዘርግቶ ቢላውን አነሳ።
ሆኖም የይሖዋ መልአክ ከሰማይ ጠርቶት “አብርሃም፣ አብርሃም!” አለው፤ እሱም መልሶ “አቤት!” አለ።
መልአኩም እንዲህ አለው፦ “በልጁ ላይ እጅህን አታሳርፍበት፤ ምንም ነገር አታድርግበት፤ ምክንያቱም ልጅህን፣ አንድ ልጅህን ለእኔ ለመስጠት ስላልሳሳህ አምላክን የምትፈራ ሰው እንደሆንክ አሁን በእርግጥ አውቄአለሁ።”
በዚህ ጊዜ አብርሃም ቀና ብሎ ሲመለከት ከእሱ ትንሽ እልፍ ብሎ ቀንዶቹ በጥሻ የተያዙ አውራ በግ አየ። በመሆኑም አብርሃም አውራውን በግ ካመጣ በኋላ በልጁ ምትክ የሚቃጠል መባ አድርጎ አቀረበው።
አብርሃምም ያን ስፍራ ይሖዋ ይርኤ ብሎ ጠራው። እስከ ዛሬም ድረስ “ይሖዋ በተራራው ላይ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ያቀርባል” የሚባለው በዚህ የተነሳ ነው።