text
stringlengths
4
267
ቃየንንና ያቀረበውን መባ ግን በጥሩ ፊት አልተመለከተም። በመሆኑም ቃየን በጣም ተናደደ፤ እጅግ አዘነ።
ከዚያም ይሖዋ ቃየንን እንዲህ አለው፦ “ለምን ተናደድክ? ለምንስ አዘንክ?
መልካም ወደ ማድረግ ብታዘነብል ኖሮ ሞገስ አታገኝም ነበር? መልካም ወደ ማድረግ ካላዘነበልክ ግን ኃጢአት በደጅህ እያደባ ነው፤ ሊቆጣጠርህም ይፈልጋል፤ ታዲያ አንተ ትቆጣጠረው ይሆን?”
ከዚያ በኋላ ቃየን ወንድሙን አቤልን “ና ወደ ሜዳ እንሂድ” አለው። በሜዳው ላይ ሳሉም ቃየን ወንድሙን አቤልን ደብድቦ ገደለው።
በኋላም ይሖዋ ቃየንን “ወንድምህ አቤል የት ነው?” አለው፤ እሱም “እኔ አላውቅም። እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝ?” አለ።
በዚህ ጊዜ እንዲህ አለው፦ “ያደረግከው ነገር ምንድን ነው? ስማ! የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ እየጮኸ ነው።
እንግዲህ የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፏን ከከፈተችው ምድር እንድትሰደድ ተረግመሃል።
ምድርን በምታርስበትም ጊዜ ምርቷን አትሰጥህም። በምድር ላይ ተንከራታችና ስደተኛ ትሆናለህ።”
በዚህ ጊዜ ቃየን ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “ለሠራሁት ጥፋት የምቀበለው ቅጣት ልሸከመው ከምችለው በላይ ነው።
ይኸው በዚህ ቀን ከምድሪቱ ልታባርረኝ ነው፤ ከፊትህም እሰወራለሁ፤ እንዲሁም በምድር ላይ ተንከራታችና ስደተኛ እሆናለሁ፤ እንግዲህ በቃ፣ ያገኘኝ ሁሉ ይገድለኛል።”
ስለሆነም ይሖዋ “እንግዲያው ቃየንን የሚገድል ማንኛውም ሰው ሰባት እጥፍ የበቀል ቅጣት ይቀበላል” አለው። በመሆኑም ያገኘው ማንም እንዳይገድለው ይሖዋ ለቃየን ምልክት አደረገለት።
ከዚያም ቃየን ከይሖዋ ፊት ርቆ ሄደ፤ ከኤደን በስተ ምሥራቅ በሚገኘው በግዞት ምድር መኖር ጀመረ።
ከዚህ በኋላ ቃየን ከሚስቱ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጸመ፤ እሷም ፀነሰች፤ ሄኖክንም ወለደች። ከዚያም ቃየን ከተማ መገንባት ጀመረ፤ ከተማዋንም በልጁ በሄኖክ ስም ሰየማት።
ከጊዜ በኋላም ሄኖክ ኢራድን ወለደ። ኢራድም መሁያኤልን ወለደ፤ መሁያኤልም መቱሻኤልን ወለደ፤ መቱሻኤል ደግሞ ላሜህን ወለደ።
ላሜህም ሁለት ሚስቶች አገባ፤ የመጀመሪያዋ ስም አዳ ሲሆን የሁለተኛዋ ስም ደግሞ ጺላ ነበር።
አዳ ያባልን ወለደች። ያባል በድንኳን የሚኖሩና ከብት የሚያረቡ ሰዎች አባት ነበር።
የወንድሙ ስም ዩባል ነበር። እሱም የበገና ደርዳሪዎችና የእምቢልታ ነፊዎች አባት ነበር።
ጺላ ደግሞ ቱባልቃይንን ወለደች፤ እሱም መዳብና ብረት እየቀጠቀጠ የተለያዩ መሣሪያዎችን ይሠራ ነበር። የቱባልቃይን እህት ናዕማ ትባል ነበር።
ከዚያም ላሜህ ለሚስቶቹ ለአዳና ለጺላ የሚከተለውን ተቀኘ፦ “እናንተ የላሜህ ሚስቶች፣ ቃሌን ስሙ፤የምላችሁንም አዳምጡ፦ አንድ ሰው ስላቆሰለኝ፣አዎ፣ አንድ ወጣት ስለመታኝ ገደልኩት።
ቃየንን የሚገድል 7 እጥፍ የበቀል ቅጣት የሚደርስበት ከሆነላሜህን የገደለማ 77 ጊዜ የበቀል ቅጣት ይደርስበታል።”
አዳም ከሚስቱ ጋር በድጋሚ የፆታ ግንኙነት ፈጸመ፤ እሷም ወንድ ልጅ ወለደች። ስሙንም “ቃየን አቤልን ስለገደለው በእሱ ፋንታ አምላክ ሌላ ዘር ተክቶልኛል” በማለት ሴት አለችው።
ሴት ደግሞ ወንድ ልጅ ወለደ፤ ስሙንም ሄኖስ አለው። በዚያን ዘመን ሰዎች የይሖዋን ስም መጥራት ጀመሩ።
ዮሴፍም ወደ ግብፅ ተወሰደ፤ የፈርዖን የቤተ መንግሥት ባለሥልጣንና የዘቦች አለቃ የሆነ ጶጢፋር የሚባል አንድ ግብፃዊ ወደዚያ ይዘውት ከወረዱት እስማኤላውያን እጅ ዮሴፍን ገዛው።
ሆኖም ይሖዋ ከዮሴፍ ጋር ነበር። በዚህም የተነሳ ስኬታማ ሆነ፤ በግብፃዊው ጌታው ቤትም ላይ ኃላፊ ሆኖ ተሾመ።
ጌታውም ይሖዋ ከዮሴፍ ጋር እንደሆነና የሚሠራውንም ነገር ሁሉ ይሖዋ እንደሚያሳካለት አየ።
ዮሴፍም በፊቱ ሞገስ እያገኘ ሄደ፤ የቅርብ አገልጋዩም ሆነ። በመሆኑም በቤቱ ላይ ሾመው፤ የእሱ የሆነውንም ነገር ሁሉ በኃላፊነት ሰጠው።
በቤቱና ባለው ነገር ሁሉ ላይ ከሾመው ጊዜ አንስቶ ይሖዋ በዮሴፍ ምክንያት የግብፃዊውን ቤት ባረከ፤ ይሖዋም በቤትና በመስክ ያለውን ነገር ሁሉ ባረከለት።
ከጊዜ በኋላም ያለውን ነገር ሁሉ ለዮሴፍ በኃላፊነት ሰጠው፤ እሱም ከሚመገበው ምግብ በስተቀር ስለሌላው ነገር ምንም አይጨነቅም ነበር። ደግሞም ዮሴፍ ሰውነቱ እየዳበረና መልኩ እያማረ ሄደ።
በኋላም የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዓይኗን ጣለችበት፤ እሷም “ከእኔ ጋር ተኛ” ትለው ጀመር።
እሱ ግን ፈቃደኛ አለመሆኑን በመግለጽ የጌታውን ሚስት እንዲህ አላት፦ “ጌታዬ በዚህ ቤት በእኔ እጅ ስላለው ነገር ምንም የሚያውቀው ነገር የለም፤ ያለውንም ነገር ሁሉ በአደራ ሰጥቶኛል።
በዚህ ቤት ውስጥ ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፤ ጌታዬ ከአንቺ በስተቀር ምንም ያልሰጠኝ ነገር የለም፤ ይህን ያደረገውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው። ታዲያ እንዲህ ያለውን እጅግ መጥፎ ድርጊት በመፈጸም በአምላክ ላይ እንዴት ኃጢአት እሠራለሁ?”
እሷም ዮሴፍን በየቀኑ ትወተውተው ነበር፤ እሱ ግን ከእሷ ጋር ለመተኛትም ሆነ አብሯት ለመሆን ፈጽሞ ፈቃደኛ አልሆነም።
ይሁንና አንድ ቀን ዮሴፍ ሥራውን ለማከናወን ወደ ቤት ሲገባ ከቤቱ አገልጋዮች መካከል አንዳቸውም በዚያ አልነበሩም።
እሷም ልብሱን አፈፍ አድርጋ ይዛ “አብረኸኝ ተኛ!” አለችው። እሱ ግን ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ወደ ውጭ ሸሽቶ ወጣ።
እሷም ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ወደ ውጭ እንደሸሸ ባየች ጊዜ
የቤቷን ሰዎች ጮኻ በመጣራት እንዲህ አለቻቸው፦ “አያችሁ! ባለቤቴ ያመጣው ይህ ዕብራዊ መሳለቂያ ሊያደርገን ነው። መጥቶ አብሬሽ ካልተኛሁ አለኝ፤ እኔ ግን ጩኸቴን አቀለጥኩት።
ድምፄን ከፍ አድርጌ ስጮኽ ልብሱን አጠገቤ ጥሎ ወደ ውጭ ሸሽቶ ወጣ።”
ከዚያም ጌታው ወደ ቤቱ እስኪመለስ ድረስ ልብሱን አጠገቧ አቆየችው።
ከዚያም እንዲህ ስትል ያንኑ ነገር ነገረችው፦ “ይህ ያመጣህብን ዕብራዊ አገልጋይ እኔ ወዳለሁበት ገብቶ መሳለቂያ ሊያደርገኝ ነበር።
ሆኖም ድምፄን ከፍ አድርጌ ስጮኽ ልብሱን አጠገቤ ጥሎ ወደ ውጭ ሸሽቶ ወጣ።”
ጌታውም “ይኸውልህ፣ አገልጋይህ እንዲህ አደረገኝ” ብላ ሚስቱ የነገረችውን ሲሰማ ቁጣው ነደደ።
በመሆኑም የዮሴፍ ጌታ ዮሴፍን ወስዶ የንጉሡ እስረኞች የታሰሩበት እስር ቤት አስገባው፤ ዮሴፍም እዚያው እስር ቤት ውስጥ ቆየ።
ይሁን እንጂ ይሖዋ ከዮሴፍ አልተለየም፤ እንደወትሮው ሁሉ ለእሱ ታማኝ ፍቅር ከማሳየት ወደኋላ አላለም፤ በእስር ቤቱ አለቃም ፊት ሞገስ ሰጠው።
በመሆኑም የእስር ቤቱ አለቃ ዮሴፍን በእስር ቤቱ ውስጥ ባሉት እስረኞች ሁሉ ላይ ኃላፊ አደረገው፤ በእስር ቤቱ ውስጥ እስረኞቹ የሚያከናውኑትን ማንኛውንም ሥራ የሚቆጣጠረው እሱ ነበር።
ይሖዋ ከዮሴፍ ጋር ስለነበርና የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ይሖዋ ስለሚያሳካለት የእስር ቤቱ አለቃ በዮሴፍ ኃላፊነት ሥር ስላለው ስለ ማንኛውም ነገር ምንም አይጨነቅም ነበር።
አብርሃም ድንኳኑን ከዚያ ነቅሎ ወደ ኔጌብ ምድር ሄደ፤ በቃዴስና በሹር መካከልም መኖር ጀመረ። በጌራራ እየኖረ ሳለ
በድጋሚ ሚስቱን ሣራን “እህቴ ናት” አለ። በመሆኑም የጌራራ ንጉሥ አቢሜሌክ ሰዎችን ልኮ ሣራን አስመጣት፤ ከዚያም ወሰዳት።
ከዚያም አምላክ ለአቢሜሌክ ሌሊት በሕልም ተገልጦለት “በወሰድካት ሴት የተነሳ ትሞታለህ፤ ምክንያቱም እሷ ያገባችና ባለቤት ያላት ሴት ናት” አለው።
ሆኖም አቢሜሌክ ወደ እሷ አልቀረበም ነበር። በመሆኑም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ፣ ምንም በደል ያልፈጸመን ብሔር ታጠፋለህ?
እሱ ‘እህቴ ናት’ አላለኝም? እሷስ ብትሆን ‘ወንድሜ ነው’ አላለችም? ይህን ያደረግኩት በቅን ልቦናና በንጹሕ እጅ ነው።”
ከዚያም እውነተኛው አምላክ በሕልም ተገልጦለት እንዲህ አለው፦ “ይህን ያደረግከው በቅን ልቦና ተነሳስተህ እንደሆነ አውቃለሁ፤ በእኔም ላይ ኃጢአት እንዳትሠራ ጠብቄሃለሁ። እንድትነካት ያልፈቀድኩልህም ለዚህ ነው።
በል አሁን የሰውየውን ሚስት መልስ፤ እሱ ነቢይ ነውና፤ ስለ አንተም ልመና ያቀርባል፤ አንተም በሕይወት ትኖራለህ። እሷን ባትመልስ ግን በእርግጥ እንደምትሞት እወቅ፤ አንተም ሆንክ የአንተ የሆነው ሁሉ ትሞታላችሁ።”
አቢሜሌክ በማለዳ ተነሳ፤ አገልጋዮቹንም በሙሉ ጠርቶ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፤ እነሱም በጣም ፈሩ።
ከዚያም አቢሜሌክ አብርሃምን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ይህ ያደረግክብን ነገር ምንድን ነው? በእኔም ሆነ በግዛቴ ላይ እንዲህ ያለውን ታላቅ ኃጢአት ያመጣህብን ለመሆኑ ምን በድዬህ ነው? ያደረግክብኝ ነገር ትክክል አይደለም።”
በመቀጠልም አቢሜሌክ አብርሃምን “ለመሆኑ ይህን ያደረግከው ምን አስበህ ነው?” አለው።
አብርሃምም እንዲህ አለው፦ “ይህን ያደረግኩት ‘በዚህ ስፍራ እንደሆነ ፈሪሃ አምላክ የሚባል ነገር የለም፤ ሰዎቹ ለሚስቴ ሲሉ ሊገድሉኝ ይችላሉ’ ብዬ ስለሰጋሁ ነው።
ደግሞም እኮ በእርግጥ እህቴ ናት፤ የእናቴ ልጅ ባትሆንም የአባቴ ልጅ ናት፤ እሷም ሚስቴ ሆነች።
በመሆኑም አምላክ ከአባቴ ቤት ወጥቼ ከአገር አገር እየዞርኩ እንድኖር በነገረኝ ጊዜ ‘በምንሄድበት ስፍራ ሁሉ “ወንድሜ ነው” ብለሽ በመናገር ታማኝ ፍቅር አሳዪኝ’ ብያት ነበር።”
ከዚያም አቢሜሌክ በጎችን፣ ከብቶችን እንዲሁም ወንድና ሴት አገልጋዮችን ለአብርሃም ሰጠው፤ ሚስቱን ሣራንም መለሰለት።
በተጨማሪም አቢሜሌክ “አገሬ አገርህ ናት፤ ደስ ባለህ ቦታ መኖር ትችላለህ” አለው።
ሣራንም እንዲህ አላት፦ “ይኸው ለወንድምሽ 1,000 የብር ሰቅል እሰጠዋለሁ። ይህም አንቺ ንጹሕ ሰው መሆንሽን ከአንቺ ጋር ባሉት ሰዎች ሁሉ ፊትም ሆነ በሌሎች ሰዎች ፊት የሚያሳውቅ ምልክት ነው፤ አንቺም ከማንኛውም ነቀፋ ነፃ ነሽ።”
አብርሃምም ወደ እውነተኛው አምላክ ልመና አቀረበ፤ አምላክም አቢሜሌክን፣ ሚስቱንና ሴት ባሪያዎቹን ፈወሳቸው፤ እነሱም ልጆች መውለድ ጀመሩ፤
ምክንያቱም ይሖዋ በአብርሃም ሚስት በሣራ የተነሳ በአቢሜሌክ ቤት ያሉትን ሴቶች ሁሉ መሃን አድርጎ ነበር።
ይሖዋም አብራምን እንዲህ አለው፦ “ከአገርህ፣ ከዘመዶችህና ከአባትህ ቤት ወጥተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ።
አንተን ታላቅ ብሔር አደርግሃለሁ፤ እንዲሁም እባርክሃለሁ፤ ስምህንም ታላቅ አደርገዋለሁ፤ አንተም በረከት ትሆናለህ።
የሚባርኩህን እባርካለሁ፤ የሚረግምህንም እረግማለሁ፤ የምድር ሕዝቦችም ሁሉ በአንተ አማካኝነት ይባረካሉ።”
ስለዚህ አብራም ልክ ይሖዋ በነገረው መሠረት ወጣ፤ ሎጥም አብሮት ሄደ። አብራም ከካራን በወጣበት ጊዜ ዕድሜው 75 ዓመት ነበር።
አብራም ሚስቱን ሦራን፣ የወንድሙን ልጅ ሎጥን እንዲሁም ያፈሩትን ንብረት ሁሉና በካራን አብረዋቸው የነበሩትን ሰዎች በሙሉ ይዞ ተነሳ፤ እነሱም ወደ ከነአን ምድር አቀኑ። ከነአን ምድር በደረሱም ጊዜ
አብራም በሞሬ ትላልቅ ዛፎች አቅራቢያ እስከሚገኘው ሴኬም እስከሚባለው አካባቢ ድረስ ወደ ምድሪቱ ዘልቆ ገባ። በዚያን ጊዜ ከነአናውያን በምድሪቱ ይኖሩ ነበር።
ይሖዋም ለአብራም ተገለጠለትና “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” አለው። ስለዚህ አብራም ተገልጦለት ለነበረው ለይሖዋ በዚያ መሠዊያ ሠራ።
በኋላም ከዚያ ተነስቶ ከቤቴል በስተ ምሥራቅ ወደሚገኘው ተራራማ አካባቢ ተጓዘ፤ እሱም ቤቴልን በስተ ምዕራብ፣ ጋይን ደግሞ በስተ ምሥራቅ አድርጎ ድንኳኑን ተከለ። በዚያም ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ፤ የይሖዋንም ስም ጠራ።
ከዚያ በኋላ አብራም ድንኳኑን ነቅሎ በየቦታው እየሰፈረ ወደ ኔጌብ ተጓዘ።
በምድሪቱም ላይ ረሃብ ተከሰተ፤ ረሃቡ በጣም አስከፊ ስለነበር አብራም ለተወሰነ ጊዜ በግብፅ ለመኖር ወደዚያ ወረደ።
ወደ ግብፅ ለመግባት ሲቃረብም ሚስቱን ሦራን እንዲህ አላት፦ “እባክሽ ስሚኝ፤ አንቺ በጣም ውብ ሴት ነሽ።
ስለሆነም ግብፃውያን አንቺን ሲያዩ ‘ይህች ሚስቱ ናት’ ማለታቸው አይቀርም። ከዚያም እኔን ይገድሉኛል፤ አንቺን ግን ይተዉሻል።
በአንቺ የተነሳ መልካም እንዲሆንልኝ እባክሽ፣ እህቴ እንደሆንሽ አድርገሽ ተናገሪ፤ እንዲህ ካደረግሽ ሕይወቴ ይተርፋል።”
አብራምም ግብፅ እንደደረሰ ግብፃውያኑ ሴቲቱ እጅግ ውብ እንደሆነች ተመለከቱ።
የፈርዖንም መኳንንት ሴቲቱን አዩአት፤ ስለ እሷም ለፈርዖን በአድናቆት ነገሩት። በመሆኑም ሴቲቱ ወደ ፈርዖን ቤት ተወሰደች።
ፈርዖንም በእሷ ምክንያት አብራምን ተንከባከበው፤ በጎችን፣ ከብቶችን፣ ተባዕትና እንስት አህዮችን፣ ግመሎችን እንዲሁም ወንድና ሴት አገልጋዮችን ሰጠው።
ከዚያም ይሖዋ በአብራም ሚስት በሦራ የተነሳ ፈርዖንንና ቤተሰቡን በታላቅ መቅሰፍት መታ።
በመሆኑም ፈርዖን አብራምን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ይህ ያደረግክብኝ ነገር ምንድን ነው? ሚስትህ እንደሆነች ያልነገርከኝ ለምንድን ነው?
‘እህቴ ናት’ ያልከውስ ለምንድን ነው? እኔ እኮ ወስጄ ሚስቴ ላደርጋት ነበር። በል፣ ሚስትህ ይችውልህ፤ ይዘሃት ሂድ!”
ስለዚህ ፈርዖን አብራምን በተመለከተ ለአገልጋዮቹ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ እነሱም አብራምን ከሚስቱና ከንብረቱ ሁሉ ጋር አሰናበቱት።
ይህ ከሆነ በኋላ ዮሴፍ “አባትህ ደክሟል” ተብሎ ተነገረው። ዮሴፍም ሁለቱን ወንዶች ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ሄደ።
ከዚያም ያዕቆብ “ልጅህ ዮሴፍ ወደ አንተ መጥቷል” ተብሎ ተነገረው። በመሆኑም እስራኤል እንደ ምንም ቀና ብሎ አልጋው ላይ ተቀመጠ።
ያዕቆብም ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በከነአን ምድር በምትገኘው በሎዛ ተገልጦልኝ ባረከኝ።
እሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘ፍሬያማ እያደረግኩህ ነው፤ ደግሞም አበዛሃለሁ፤ ብዙ ሕዝብ ያቀፈ ጉባኤም አደርግሃለሁ፤ ይህችን ምድር ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ዘሮችህ ዘላቂ ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ።’
አንተ ወዳለህበት ወደ ግብፅ ከመምጣቴ በፊት በግብፅ ምድር የወለድካቸው ሁለት ወንዶች ልጆች የእኔ ናቸው። ሮቤልና ስምዖን የእኔ እንደሆኑ ሁሉ ኤፍሬምና ምናሴም የእኔ ይሆናሉ።
ከእነሱ በኋላ የምትወልዳቸው ልጆች ግን የአንተ ይሆናሉ። እነሱም ርስት በሚሰጣቸው ጊዜ በወንድሞቻቸው ስም ይጠራሉ።
እኔም ከጳዳን ስመጣ ኤፍራታ ለመድረስ ረዘም ያለ መንገድ ሲቀረኝ ራሔል በከነአን ምድር ሞተችብኝ። በመሆኑም ወደ ኤፍራታ ማለትም ወደ ቤተልሔም በሚወስደው መንገድ ላይ ቀበርኳት።”
ከዚያም እስራኤል የዮሴፍን ወንዶች ልጆች ሲያይ “እነዚህ እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀው።
ዮሴፍም አባቱን “እነዚህ አምላክ በዚህ ስፍራ የሰጠኝ ወንዶች ልጆቼ ናቸው” አለው። በዚህ ጊዜ “እባክህ እንድባርካቸው ወደ እኔ አቅርባቸው” አለው።
የእስራኤል ዓይኖች በእርጅና የተነሳ ደክመው ነበር፤ እሱም ማየት ተስኖት ነበር። ስለዚህ ዮሴፍ ልጆቹን ወደ እሱ አቀረባቸው። እሱም ሳማቸው፤ እንዲሁም አቀፋቸው።
እስራኤልም ዮሴፍን “ዓይንህን አያለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ አምላክ ግን ልጆችህንም ጭምር ለማየት አበቃኝ” አለው።
ከዚያም ዮሴፍ ልጆቹን ከእስራኤል ጉልበቶች መካከል አውጥቶ ፈቀቅ ካደረጋቸው በኋላ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ ሰገደ።
ዮሴፍም ሁለቱን ልጆች ወስዶ ኤፍሬምን ከራሱ በስተ ቀኝ ከእስራኤል በስተ ግራ፣ ምናሴን ደግሞ ከራሱ በስተ ግራ ከእስራኤል በስተ ቀኝ አድርጎ ወደ እሱ አቀረባቸው።
ይሁን እንጂ እስራኤል ታናሽየው ኤፍሬም ቢሆንም ቀኝ እጁን በእሱ ራስ ላይ አደረገ፤ ግራ እጁን ደግሞ በምናሴ ራስ ላይ አደረገ። እንዲህ ያደረገው ሆን ብሎ ነው፤ ምክንያቱም ምናሴ የበኩር ልጅ ነበር።
ከዚያም ዮሴፍን ባረከው፤ እንዲህም አለው፦ “አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ የተመላለሱት እውነተኛው አምላክ፣እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ እረኛ የሆነልኝ እውነተኛው አምላክ፣
ከአደጋ ሁሉ ያዳነኝ መልአክ እነዚህን ልጆች ይባርክ። የእኔም ሆነ የአባቶቼ የአብርሃምና የይስሐቅ ስም በእነሱ ይጠራ። በምድርም ላይ ቁጥራቸው እየበዛ ይሂድ።”
ዮሴፍም አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ እንዳደረገ ሲያይ ቅር ተሰኘ፤ ስለዚህ የአባቱን እጅ ከኤፍሬም ራስ ላይ አንስቶ በምናሴ ራስ ላይ ሊያደርገው ሞከረ።