text
stringlengths
4
267
ከዚያም ውኃው ቀስ በቀስ ከምድር ላይ እየቀነሰ ሄደ። ከ150 ቀናት በኋላም ውኃው ጎደለ።
በሰባተኛው ወር፣ ከወሩም በ17ኛው ቀን መርከቡ በአራራት ተራሮች ላይ አረፈ።
ውኃውም እስከ አሥረኛው ወር ድረስ ቀስ በቀስ እየቀነሰ ሄደ። በአሥረኛው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ አናት ታየ።
ከ40 ቀንም በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቡን መስኮት ከፍቶ
አንድ ቁራ ወደ ውጭ ላከ፤ ቁራው ከመርከቡ ውጭ ሲበር ይቆይና ተመልሶ ይመጣ ነበር፤ ውኃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ እንዲሁ ያደርግ ነበር።
በኋላም ውኃው ከምድር ላይ መጉደሉን ለማረጋገጥ አንዲት ርግብ ላከ።
ርግቧ ምንም የምታርፍበት ቦታ ስላላገኘች እሱ ወደነበረበት መርከብ ተመልሳ መጣች፤ ምክንያቱም ውኃው ገና መላውን ምድር እንደሸፈነው ነበር። በመሆኑም እጁን ወደ ውጭ ዘርግቶ ተቀበላትና ወደ መርከቡ አስገባት።
ከዚያም ሌላ ሰባት ቀን ከጠበቀ በኋላ ርግቧን በድጋሚ ከመርከቡ አውጥቶ ለቀቃት።
ርግቧም አመሻሹ ላይ ወደ እሱ በመጣች ጊዜ አዲስ የተቀጠፈ ለምለም የወይራ ቅጠል በአፏ እንደያዘች አየ! ስለዚህ ኖኅ ውኃው ከምድር ላይ መጉደሉን አወቀ።
እንደገና ሌላ ሰባት ቀን ጠበቀ። ከዚያም ርግቧን አውጥቶ ለቀቃት፤ በዚህ ጊዜ ግን ርግቧ ወደ እሱ ተመልሳ አልመጣችም።
ኖኅ በተወለደ በ601ኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ውኃው ከመሬቱ ላይ ሸሸ፤ ኖኅም የመርከቡን ሽፋን አንስቶ ተመለከተ፤ በዚህ ጊዜ መሬቱ ደርቆ ነበር።
በሁለተኛው ወር፣ ከወሩም በ27ኛው ቀን ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ ደረቀች።
ከዚያም አምላክ ኖኅን እንዲህ አለው፦
“አንተ፣ ሚስትህ፣ ወንዶች ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ከመርከቡ ውጡ።
በምድር ላይ እንዲዋለዱ፣ እንዲራቡና በምድር ላይ እንዲባዙ አብሮህ ያለውን እያንዳንዱን ዓይነት ሕያው ፍጡር ሁሉ ይኸውም የሚበርሩ ፍጥረታትን፣ እንስሳትን እንዲሁም በምድር ላይ መሬት ለመሬት የሚሄዱ እንስሳትን ይዘህ ውጣ።”
ስለዚህ ኖኅ ከወንዶች ልጆቹ፣ ከሚስቱና ከልጆቹ ሚስቶች ጋር አብሮ ወጣ።
እያንዳንዱ ሕያው ፍጡር፣ መሬት ለመሬት የሚሄድ እያንዳንዱ እንስሳና እያንዳንዱ የሚበር ፍጡር እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ነገር በወገን በወገኑ እየሆነ ከመርከቡ ወጣ።
ከዚያም ኖኅ ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ፤ ንጹሕ ከሆኑት እንስሳት ሁሉ እንዲሁም ንጹሕ ከሆኑት የሚበርሩ ፍጥረታት ሁሉ የተወሰኑትን ወስዶ በመሠዊያው ላይ የሚቃጠል መባ አቀረበ።
ይሖዋም ደስ የሚያሰኘውን መዓዛ አሸተተ። ስለዚህ ይሖዋ በልቡ እንዲህ አለ፦ “በሰው የተነሳ ከእንግዲህ ወዲህ ፈጽሞ ምድርን አልረግምም፤ ምክንያቱም የሰው የልብ ዝንባሌ ከልጅነቱ ጀምሮ መጥፎ ነው፤ ደግሞም አሁን እንዳደረግኩት ሕያው ፍጡርን ሁሉ ፈጽሞ ዳግመኛ አላጠፋም።
ከአሁን ጀምሮ በምድር ላይ ዘር መዝራትና ማጨድ፣ ቅዝቃዜና ሙቀት፣ በጋና ክረምት እንዲሁም ቀንና ሌሊት ፈጽሞ አይቋረጡም።”
መላው የእስራኤል ማኅበረሰብም ከሲን ምድረ በዳ ተነስቶ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት ከቦታ ወደ ቦታ ሲጓዝ ከቆየ በኋላ በረፊዲም ሰፈረ። ሆኖም ሕዝቡ የሚጠጣው ውኃ አልነበረም።
በመሆኑም ሕዝቡ “የሚጠጣ ውኃ ስጠን” በማለት ከሙሴ ጋር ይጣላ ጀመር። ሙሴ ግን “ከእኔ ጋር የምትጣሉት ለምንድን ነው? ይሖዋንስ ለምን ትፈታተኑታላችሁ?” አላቸው።
ሆኖም ሕዝቡ ውኃ በጣም ተጠምቶ ስለነበር “እኛና ልጆቻችን እንዲሁም ከብቶቻችን በውኃ ጥም እንድናልቅ ከግብፅ ያወጣኸን ለምንድን ነው?” በማለት በሙሴ ላይ ማጉረምረሙን ቀጠለ።
በመጨረሻም ሙሴ “ይህን ሕዝብ ምን ባደርገው ይሻለኛል? ትንሽ ቆይተው እኮ ይወግሩኛል!” በማለት ወደ ይሖዋ ጮኸ።
ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከእስራኤል ሽማግሌዎች መካከል የተወሰኑትን ምረጥና የአባይን ወንዝ የመታህበትን በትር ይዘህ ከሕዝቡ ፊት ፊት ሂድ። በትሩን በእጅህ ይዘህ ሂድ።
እኔም በዚያ በኮሬብ በሚገኘው ዓለት ላይ ፊትህ እቆማለሁ። አንተም ዓለቱን ትመታዋለህ፤ ውኃም ከውስጡ ይፈልቃል፤ ሕዝቡም ይጠጣሉ።” ሙሴም የእስራኤል ሽማግሌዎች እያዩ እንደተባለው አደረገ።
እሱም እስራኤላውያን ስለተጣሉትና “ለመሆኑ ይሖዋ በመካከላችን አለ ወይስ የለም?” በማለት ይሖዋን ስለተፈታተኑት የቦታውን ስም ማሳህ እና መሪባ አለው።
ከዚያም አማሌቃውያን መጥተው በረፊዲም እስራኤላውያንን ወጉ።
በዚህ ጊዜ ሙሴ ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ሰዎች ምረጥልንና ከአማሌቃውያን ጋር ለመዋጋት ውጣ። እኔም በነገው ዕለት የእውነተኛውን አምላክ በትር በእጄ ይዤ በኮረብታው አናት ላይ እቆማለሁ።”
ከዚያም ኢያሱ ልክ ሙሴ እንዳለው አደረገ፤ ከአማሌቃውያንም ጋር ተዋጋ። ሙሴ፣ አሮንና ሁርም ወደ ኮረብታው አናት ወጡ።
ሙሴ እጆቹን ወደ ላይ አንስቶ በሚቆይበት ጊዜ ሁሉ እስራኤላውያን ያይሉ፣ እጆቹን በሚያወርድበት ጊዜ ግን አማሌቃውያን ያይሉ ነበር።
የሙሴ እጆች በዛሉ ጊዜ ድንጋይ ወስደው ከሥሩ አስቀመጡለት፤ እሱም በድንጋዩ ላይ ተቀመጠ። ከዚያም አሮንና ሁር አንዱ በአንደኛው በኩል፣ ሌላው ደግሞ በሌላኛው በኩል ሆነው እጆቹን ደገፉለት፤ በመሆኑም ፀሐይ እስከምትጠልቅበት ጊዜ ድረስ እጆቹ ባሉበት ጸኑ።
በዚህ መንገድ ኢያሱ አማሌቅንና ሕዝቦቹን በሰይፍ ድል አደረገ።
ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “መታሰቢያ እንዲሆን ይህን በመጽሐፍ ጻፈው፤ ለኢያሱም ‘የአማሌቅን መታሰቢያ ከሰማይ በታች ሙሉ በሙሉ ጠራርጌ አጠፋለሁ’ በማለት ይህን ደግመህ ንገረው።”
ከዚያም ሙሴ መሠዊያ ሠርቶ ስሙን ‘ይሖዋ ንሲ’ ብሎ ሰየመው፤
እንዲህም ያለው “እጁ በያህ ዙፋን ላይ ስለተነሳ ይሖዋ ከአማሌቅ ጋር ከትውልድ እስከ ትውልድ ይዋጋል” በማለት ነው።
ይሖዋ እንዲህ በማለት ሙሴን ማነጋገሩን ቀጠለ፦
“እንግዲህ እኔ ከይሁዳ ነገድ የሆነው የሁር ልጅ ዖሪ የወለደውን ባስልኤልን መርጬዋለሁ።
ደግሞም ጥበብ፣ ማስተዋልና እውቀት በመስጠት በማንኛውም ዓይነት የእጅ ሙያ የተካነ እንዲሆን በአምላክ መንፈስ እሞላዋለሁ፤
ይህን የማደርገው የተለያዩ ንድፎችን እንዲያወጣ፣ በወርቅ፣ በብርና በመዳብ የተለያዩ ነገሮችን እንዲሠራ፣
ፈርጥ የሚሆኑትን ድንጋዮች እንዲቀርጽና በቦታቸው እንዲያስቀምጥ እንዲሁም ከእንጨት ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን እንዲሠራ ነው።
በተጨማሪም ከዳን ነገድ የሆነውን የአሂሳማክን ልጅ ኤልያብን ረዳት እንዲሆነው መርጬዋለሁ፤ እኔ ያዘዝኩህን የሚከተሉትን ነገሮች በሙሉ እንዲሠሩ ጥሩ ችሎታ ባላቸው ሰዎች ሁሉ ልብ ውስጥ ጥበብን አኖራለሁ፦
የመገናኛ ድንኳኑን፣ የምሥክሩን ታቦትና በላዩ ላይ ያለውን መክደኛ፣ የድንኳኑን ቁሳቁስ በሙሉ፣
ጠረጴዛውንና ዕቃዎቹን፣ ከንጹሕ ወርቅ የሚሠራውን መቅረዝና ዕቃዎቹን በሙሉ፣ የዕጣን መሠዊያውን፣
የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያና ዕቃዎቹን በሙሉ፣ መታጠቢያ ገንዳውንና መቆሚያውን፣
ጥሩ ሆነው የተሸመኑትን ልብሶች፣ የካህኑን የአሮንን ቅዱስ ልብሶች፣ ወንዶች ልጆቹ ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸውን ልብሶች፣
የቅብዓት ዘይቱንና ለመቅደሱ የሚሆነውን ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን። ማንኛውንም ነገር ልክ እኔ ባዘዝኩህ መሠረት ይሠሩታል።”
በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦
“ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘እናንተን የምቀድሳችሁ እኔ ይሖዋ መሆኔን እንድታውቁ የሚያደርግ፣ በትውልዶቻችሁ ሁሉ በእኔና በእናንተ መካከል ያለ ምልክት ስለሆነ በተለይ ሰንበቴን ማክበር አለባችሁ።
ለእናንተ የተቀደሰ ስለሆነ ሰንበትን አክብሩ። ሰንበትን የሚያረክስ ሰው ይገደል። ማንም ሰው በዚያ ቀን ሥራ ቢሠራ ያ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት።
ስድስት ቀን ሥራ መሥራት ይቻላል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ሙሉ በሙሉ የሚታረፍበት ሰንበት ነው። ለይሖዋ የተቀደሰ ነው። በሰንበት ቀን ሥራ የሚሠራ ማንም ሰው ይገደል።
እስራኤላውያን ሰንበትን መጠበቅ አለባቸው፤ በትውልዶቻቸው ሁሉ ሰንበትን ማክበር አለባቸው። ይህ ዘላቂ ቃል ኪዳን ነው።
በእኔና በእስራኤል ሕዝብ መካከል ያለ ዘላለማዊ ምልክት ነው፤ ምክንያቱም ይሖዋ ሰማያትንና ምድርን በስድስት ቀናት ውስጥ ሠርቶ በማጠናቀቅ ሥራውን ያቆመውና ያረፈው በሰባተኛው ቀን ነው።’”
በሲና ተራራ ላይ ከእሱ ጋር ተነጋግሮ እንደጨረሰ የምሥክሩን ሁለት ጽላቶች ይኸውም በአምላክ ጣት የተጻፈባቸውን የድንጋይ ጽላቶች ለሙሴ ሰጠው።
እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡ በሦስተኛው ወር በዚያው ቀን ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ።
ከረፊዲም ተነስተው ወደ ሲና ምድረ በዳ በመምጣት በምድረ በዳው ሰፈሩ። እስራኤላውያን በዚያ ከተራራው ፊት ለፊት ሰፈሩ።
ከዚያም ሙሴ ወደ እውነተኛው አምላክ ወጣ፤ ይሖዋም ከተራራው ጠርቶት እንዲህ አለው፦ “ለያዕቆብ ቤት የምትለው፣ ለእስራኤላውያንም የምትነግረው ይህ ነው፦
‘እናንተን በንስር ክንፎች ተሸክሜ ወደ እኔ ለማምጣት ስል በግብፃውያን ላይ ያደረግኩትን ሁሉ እናንተው ራሳችሁ አይታችኋል።
አሁንም ቃሌን በጥብቅ ብትታዘዙና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ መላው ምድር የእኔ ስለሆነ እናንተ ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የተመረጣችሁ ልዩ ንብረቶቼ ትሆናላችሁ።
እናንተ ለእኔ የካህናት መንግሥትና ቅዱስ ብሔር ትሆናላችሁ።’ ለእስራኤላውያን የምትነግራቸው ቃል ይህ ነው።”
በመሆኑም ሙሴ ሄዶ የሕዝቡን ሽማግሌዎች ጠራ፤ ይሖዋ ያዘዘውንም ይህን ቃል ነገራቸው።
ከዚያ በኋላ ሕዝቡ ሁሉ በአንድ ድምፅ “ይሖዋ የተናገረውን ሁሉ ለመፈጸም ፈቃደኞች ነን” ብለው መለሱ። ሙሴም ወዲያውኑ የሕዝቡን ምላሽ ይዞ ወደ ይሖዋ ሄደ።
ይሖዋም ሙሴን “ሕዝቡ ከአንተ ጋር ስነጋገር እንዲሰማና ምንጊዜም በአንተ ላይ እምነት እንዲጥል በጥቁር ደመና ወደ አንተ እመጣለሁ” አለው። ከዚያም ሙሴ የሕዝቡን ቃል ለይሖዋ ተናገረ።
ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ሕዝቡ ሄደህ ዛሬና ነገ ቀድሳቸው፤ እነሱም ልብሳቸውን ይጠቡ።
ለሦስተኛውም ቀን ይዘጋጁ፤ ምክንያቱም በሦስተኛው ቀን ይሖዋ ሕዝቡ ሁሉ እያዩ በሲና ተራራ ላይ ይወርዳል።
በተራራው ዙሪያ ለሕዝቡ ወሰን አብጅ፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘ወደ ተራራው እንዳትወጡ፣ ድንበሩንም እንኳ እንዳትነኩ ተጠንቀቁ። ተራራውን የሚነካ ማንኛውም ሰው ይገደላል።
ይህን ሰው ማንም እንዳይነካው፤ ከዚህ ይልቅ በድንጋይ ይወገር ወይም ደግሞ ይወጋ። እንስሳም ሆነ ሰው በሕይወት እንዲኖር አይተውም።’ ሆኖም የቀንደ መለከቱ ድምፅ በሚሰማበት ጊዜ ወደ ተራራው ሊወጡ ይችላሉ።”
ከዚያም ሙሴ ከተራራው ወርዶ ወደ ሕዝቡ ሄደ፤ ሕዝቡንም ይቀድስ ጀመር፤ እነሱም ልብሳቸውን አጠቡ።
ሕዝቡንም “ለሦስተኛው ቀን ተዘጋጁ። የፆታ ግንኙነት ከመፈጸምም ተቆጠቡ” አላቸው።
በሦስተኛውም ቀን ጠዋት ነጎድጓድ መሰማትና መብረቅ መታየት ጀመረ፤ በተራራውም ላይ ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበር፤ ከፍተኛ የቀንደ መለከት ድምፅም ተሰማ፤ በሰፈሩም ውስጥ ያለው ሕዝብ በሙሉ በፍርሃት ተንቀጠቀጠ።
በዚህ ጊዜ ሙሴ ከእውነተኛው አምላክ ጋር እንዲገናኙ ሕዝቡን ከሰፈሩ ይዞ ወጣ፤ እነሱም በተራራው ግርጌ ቆሙ።
የሲና ተራራ ይሖዋ በእሳት ስለወረደበት ዙሪያውን ጨሰ፤ ጭሱም እንደ እቶን ጭስ እየተትጎለጎለ ይወጣ ነበር፤ ተራራውም ሁሉ በኃይል ተናወጠ።
የቀንደ መለከቱም ድምፅ ይበልጥ እየጨመረ ሲመጣ ሙሴ ተናገረ፤ የእውነተኛውም አምላክ ድምፅ መለሰለት።
በመሆኑም ይሖዋ በሲና ተራራ አናት ላይ ወረደ። ከዚያም ይሖዋ ሙሴን ወደ ተራራው አናት ጠራው፤ ሙሴም ወጣ።
በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ሂድ ውረድ፤ ሕዝቡ ይሖዋን ለማየት ሲሉ አልፈው ለመምጣት እንዳይሞክሩ አስጠንቅቃቸው፤ ካልሆነ ግን ብዙዎቹ ለጥፋት ይዳረጋሉ።
ዘወትር ወደ ይሖዋ የሚቀርቡት ካህናትም ይሖዋ እንዳይቀስፋቸው ራሳቸውን ይቀድሱ።”
ከዚያም ሙሴ ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “አንተ ‘በተራራው ዙሪያ ወሰን አድርግ፤ እሱንም ቀድሰው’ በማለት ስላስጠነቀቅከን ሕዝቡ ወደ ሲና ተራራ መቅረብ አይችልም።”
ሆኖም ይሖዋ እንዲህ አለው፦ “ሂድ፣ ውረድና ከአሮን ጋር ተመልሰህ ወደዚህ ውጣ፤ ነገር ግን ካህናቱም ሆኑ ሕዝቡ አልፈው ወደ ይሖዋ ለመምጣት እንዳይሞክሩና እንዳይቀስፋቸው ከልክላቸው።”
ስለሆነም ሙሴ ወደ ሕዝቡ ወርዶ ነገራቸው።
በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከግብፅ መርተህ ካወጣኸው ሕዝብ ጋር ከዚህ ተነስተህ ሂድ። ‘ለዘርህ እሰጠዋለሁ’ በማለት ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ወደማልኩላቸውም ምድር ተጓዝ።
እኔም ከአንተ አስቀድሜ መልአክ በመላክ ከነአናውያንን፣ አሞራውያንን፣ ሂታውያንን፣ ፈሪዛውያንን፣ ሂዋውያንንና ኢያቡሳውያንን አስወጣለሁ።
ወተትና ማር ወደምታፈሰው ምድር ሂዱ። ሆኖም እናንተ ግትር ሕዝብ ስለሆናችሁ በመንገድ ላይ እንዳላጠፋችሁ በመካከላችሁ ሆኜ አብሬያችሁ አልሄድም።”
ሕዝቡም ይህን ኃይለኛ ንግግር ሲሰሙ በሐዘን ተዋጡ፤ ከመካከላቸውም ማንም ጌጡን አላደረገም።
ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘እናንተ ግትር ሕዝብ ናችሁ። ለአንድ አፍታ በመካከላችሁ አልፌ ላጠፋችሁ እችል ነበር። በእናንተ ላይ ምን ማድረግ እንዳለብኝ እስክወስን ድረስ ጌጣጌጣችሁን አውልቁ።’”
ስለዚህ እስራኤላውያን ከኮሬብ ተራራ አንስቶ ጌጣጌጣቸውን ማድረግ ተዉ።
ሙሴም የራሱን ድንኳን ወስዶ ከሰፈሩ ውጭ ማለትም ከሰፈሩ ትንሽ ራቅ አድርጎ ተከለው፤ ድንኳኑንም የመገናኛ ድንኳን ብሎ ጠራው። ይሖዋን የሚጠይቅ ማንኛውም ሰው ከሰፈሩ ውጭ ወዳለው የመገናኛ ድንኳን ይሄድ ነበር።
ሙሴ ወደ ድንኳኑ ሲሄድ ሕዝቡ በሙሉ ተነስተው በየድንኳናቸው መግቢያ ላይ በመቆም ሙሴ ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ ትክ ብለው ይመለከቱት ነበር።
ሙሴ ወደ ድንኳኑ ገብቶ አምላክ ከሙሴ ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ የደመናው ዓምድ ወርዶ በድንኳኑ መግቢያ ላይ ይቆማል።
ሕዝቡም ሁሉ የደመናው ዓምድ በድንኳኑ መግቢያ ላይ ቆሞ ሲመለከት እያንዳንዳቸው ተነስተው በየድንኳናቸው መግቢያ ላይ ይሰግዱ ነበር።
አንድ ሰው ከሌላ ሰው ጋር እንደሚነጋገር ይሖዋ ከሙሴ ጋር ፊት ለፊት ይነጋገር ነበር። ሙሴ ወደ ሰፈሩ በሚመለስበት ጊዜ አገልጋዩና ረዳቱ የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ ከድንኳኑ አይለይም ነበር።
ሙሴም ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ ‘ይህን ሕዝብ ምራ’ እያልከኝ ነው፤ ሆኖም ከእኔ ጋር ማንን እንደምትልክ አላሳወቅከኝም። ከዚህም በላይ ‘በስም አውቄሃለሁ፤ ደግሞም በፊቴ ሞገስ አግኝተሃል’ ብለኸኝ ነበር።
እባክህ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ እንዳውቅህና በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንድኖር መንገድህን አሳውቀኝ። እንዲሁም ይህ ብሔር ሕዝብህ እንደሆነ አስብ።”
በመሆኑም እሱ “እኔ ራሴ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ እረፍትም እሰጥሃለሁ” አለው።
ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለው፦ “አንተ ራስህ ከእኛ ጋር የማትሄድ ከሆነ ይህን ቦታ ለቅቀን እንድንሄድ አታድርገን።
ታዲያ እኔም ሆንኩ ሕዝብህ በፊትህ ሞገስ እንዳገኘን የሚታወቀው እንዴት ነው? እኔም ሆንኩ ሕዝብህ በምድር ላይ ካሉ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የተለየን እንድንሆን ስትል አብረኸን በመሄድህ አይደለም?”
ይሖዋም ሙሴን “በፊቴ ሞገስ ስላገኘህና በስም ስላወቅኩህ የጠየቅከውን ይህን ነገር እፈጽማለሁ” አለው።
እሱም በዚህ ጊዜ “እባክህ ክብርህን አሳየኝ” አለው።
ሆኖም እሱ እንዲህ አለው፦ “እኔ ራሴ ጥሩነቴ ሁሉ በፊትህ እንዲያልፍ አደርጋለሁ፤ ይሖዋ የተባለውንም ስሜን በፊትህ አውጃለሁ። ሞገስ ላሳየው የምፈልገውን ሞገስ አሳየዋለሁ፤ ልምረው የምፈልገውን ደግሞ እምረዋለሁ።”
ሆኖም “ማንም ሰው አይቶኝ በሕይወት መኖር ስለማይችል ፊቴን ማየት አትችልም” አለው።
በተጨማሪም ይሖዋ እንዲህ አለው፦ “ይኸው አጠገቤ ቦታ አለ። አንተም በዓለቱ ላይ ቁም።