text
stringlengths
4
267
“ባስልኤል ከኤልያብና ጥሩ ችሎታ ካላቸው ወንዶች ሁሉ ጋር ይሠራል፤ እነዚህ ወንዶች ቅዱስ ከሆነው አገልግሎት ጋር የተያያዘው ሥራ በሙሉ ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት እንዴት እንደሚከናወን ማወቅ ይችሉ ዘንድ ይሖዋ ጥበብና ማስተዋል የሰጣቸው ናቸው።”
ከዚያም ሙሴ ባስልኤልንና ኤልያብን እንዲሁም ይሖዋ በልባቸው ጥበብን ያኖረላቸውን ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ወንዶች ሁሉ ይኸውም ሥራውን ለመሥራት በፈቃደኝነት ራሳቸውን እንዲያቀርቡ ልባቸው ያነሳሳቸውን ሁሉ ጠራ።
እነሱም እስራኤላውያን ለቅዱሱ አገልግሎት ሥራ ያመጡትን መዋጮ በሙሉ ከሙሴ ወሰዱ። ሕዝቡ ግን በየማለዳው የፈቃደኝነት መባ ወደ እሱ ያመጣ ነበር።
ቅዱሱን ሥራ ከጀመሩም በኋላ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሠራተኞች ሁሉ አንድ በአንድ ይመጡ ነበር፤
ሙሴንም “ሕዝቡ፣ ይሖዋ እንዲሠራ ላዘዘው ሥራ ከሚፈለገው በላይ እያመጣ ነው” አሉት።
ስለዚህ ሙሴ በሰፈሩ ሁሉ እንዲህ የሚል ማስታወቂያ እንዲነገር አዘዘ፦ “ወንዶችም ሆናችሁ ሴቶች፣ ከእንግዲህ ለቅዱሱ መዋጮ የሚሆን ተጨማሪ ነገር አታምጡ።” በመሆኑም ሕዝቡ ምንም ነገር ከማምጣት ተገታ።
የመጣውም ነገር ሥራውን ሁሉ ለማከናወን በቂ፣ እንዲያውም ከበቂ በላይ ነበር።
ጥሩ ችሎታ ያላቸውም ሰዎች ሁሉ በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ የበፍታ ድር፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍና ከደማቅ ቀይ ማግ ከተሠሩ አሥር የድንኳን ጨርቆች የማደሪያ ድንኳኑን ሠሩ፤ እሱም በጨርቆቹ ላይ ኪሩቦችን ጠለፈባቸው።
የእያንዳንዱ የድንኳን ጨርቅ ርዝመት 28 ክንድ ወርዱ ደግሞ 4 ክንድ ነበር። ሁሉም የድንኳን ጨርቆች መጠናቸው እኩል ነበር።
ከዚያም አምስቱን የድንኳን ጨርቆች አንድ ላይ ቀጣጠላቸው፤ ሌሎቹን አምስት የድንኳን ጨርቆችም እንዲሁ አንድ ላይ ቀጣጠላቸው።
ከዚህ በኋላ አንደኛው የድንኳን ጨርቅ ከሌላኛው ጋር በሚጋጠምበት ጠርዝ ላይ ከሰማያዊ ክር ማቆላለፊያዎችን ሠራ። ሌላኛው የድንኳን ጨርቅ ከዚህኛው ጋር በሚጋጠምበት በመጨረሻው የድንኳን ጨርቅ ጠርዝ ላይም እንዲሁ አደረገ።
በአንደኛው የድንኳን ጨርቅ ላይ 50 ማቆላለፊያዎችን ሠራ፤ ማቆላለፊያዎቹም ትይዩ እንዲሆኑ ሌላኛው የድንኳን ጨርቅ ከዚህኛው ጋር በሚጋጠምበት የድንኳኑ ጨርቅ ጠርዝ ላይ 50 ማቆላለፊያዎችን ሠራ።
በመጨረሻም 50 የወርቅ ማያያዣዎችን ሠርቶ የድንኳኑን ጨርቆች በማያያዣዎቹ አማካኝነት እርስ በርስ አጋጠማቸው፤ በዚህም መንገድ የማደሪያ ድንኳኑ አንድ ወጥ ሆነ።
ከዚያም ለማደሪያ ድንኳኑ ልባስ የሚሆኑ የድንኳን ጨርቆችን ከፍየል ፀጉር ሠራ። አሥራ አንድ የድንኳን ጨርቆችን ሠራ።
የእያንዳንዱ የድንኳን ጨርቅ ርዝመት 30 ክንድ ወርዱ ደግሞ 4 ክንድ ነበር። አሥራ አንዱም የድንኳን ጨርቆች መጠናቸው እኩል ነበር።
ከዚያም አምስቱን የድንኳን ጨርቆች አንድ ላይ፣ ሌሎቹን ስድስት የድንኳን ጨርቆች ደግሞ አንድ ላይ ቀጣጠላቸው።
በመቀጠልም አንደኛው የድንኳን ጨርቅ ከሌላኛው ጋር በሚጋጠምበት በመጨረሻው የድንኳን ጨርቅ ጠርዝ ላይ 50 ማቆላለፊያዎችን ሠራ፤ እንዲሁም ከዚህኛው ጋር በሚጋጠመው በሌላኛው የድንኳን ጨርቅ ጠርዝ ላይ 50 ማቆላለፊያዎችን ሠራ።
ከዚያም ድንኳኑን በማያያዝ አንድ ወጥ እንዲሆን ለማድረግ 50 የመዳብ ማያያዣዎችን ሠራ።
እሱም ቀይ ቀለም ከተነከረ የአውራ በግ ቆዳ ለድንኳኑ መደረቢያ ሠራ፤ እንዲሁም ከአቆስጣ ቆዳ በላዩ ላይ የሚደረብ መደረቢያ ሠራ።
ከዚያም የግራር እንጨት ጣውላዎችን በማገጣጠም የማደሪያ ድንኳኑን ቋሚዎች ሠራ።
እያንዳንዱ ቋሚ ቁመቱ አሥር ክንድ ወርዱ ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ነበር።
እያንዳንዱ ቋሚም እርስ በርስ የተያያዙ ሁለት ጉጦች ነበሩት። ሁሉንም የማደሪያ ድንኳኑን ቋሚዎች የሠራው በዚህ መንገድ ነበር።
በመሆኑም በስተ ደቡብ በኩል ለሚገኘው፣ ፊቱ በደቡብ አቅጣጫ ላለው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን ቋሚዎችን ይኸውም 20 ቋሚዎችን ሠራ።
ከዚያም በ20ዎቹ ቋሚዎች ሥር የሚሆኑ 40 የብር መሰኪያዎችን ሠራ፤ በአንዱ ቋሚ ሥር ላሉት ሁለት ጉጦች የሚሆኑ ሁለት መሰኪያዎችን፣ ቀጥሎ ባለው በእያንዳንዱም ቋሚ ሥር ላሉት ሁለት ጉጦች የሚሆኑ ሁለት መሰኪያዎችን አደረገ።
በስተ ሰሜን በኩል ላለው ለሌላኛውም የማደሪያ ድንኳኑ ጎን 20 ቋሚዎችን ሠራ፤
እንዲሁም 40 የብር መሰኪያዎቻቸውን ሠራ፤ በአንዱ ቋሚ ሥር ሁለት መሰኪያዎችን፣ በተቀረው በእያንዳንዱም ቋሚ ሥር ሁለት መሰኪያዎችን አደረገ።
በስተ ምዕራብ በኩል ለሚገኘው ለኋለኛው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን ስድስት ቋሚዎችን ሠራ።
በማደሪያ ድንኳኑ በስተ ኋላ በኩል ባሉት ሁለት ማዕዘኖች ላይ የማዕዘን ቋሚዎች የሚሆኑ ሁለት ቋሚዎችን ሠራ።
ቋሚዎቹም ከታች አንስቶ የመጀመሪያው ቀለበት እስከሚገኝበት እስከ ላይ ድረስ ድርብ ነበሩ። ሁለቱን የማዕዘን ቋሚዎች የሠራቸው በዚህ መንገድ ነበር።
በመሆኑም ስምንት ቋሚዎች የነበሩ ሲሆን እነሱም ከብር የተሠሩ 16 መሰኪያዎች ነበሯቸው፤ ይህም በእያንዳንዱ ቋሚ ሥር ሁለት መሰኪያ ማለት ነው።
ከዚያም ከግራር እንጨት አግዳሚ እንጨቶችን ሠራ፤ በአንዱ ጎን ላሉት የማደሪያ ድንኳኑ ቋሚዎች አምስት አግዳሚ እንጨቶችን፣
በሌላኛው ጎን ላሉት የማደሪያ ድንኳኑ ቋሚዎች ደግሞ አምስት አግዳሚ እንጨቶችን እንዲሁም በስተ ምዕራብ በሚገኘው በኋለኛው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን ላሉት ቋሚዎች አምስት አግዳሚ እንጨቶችን ሠራ።
ከዚያም በቋሚዎቹ መሃል ላይ ከጫፍ እስከ ጫፍ እንዲዘልቅ መካከለኛውን አግዳሚ እንጨት ሠራ።
ቋሚዎቹንም በወርቅ ለበጣቸው፤ አግዳሚ እንጨቶቹን የሚሸከሙትን ቀለበቶችም ከወርቅ ሠራቸው። አግዳሚ እንጨቶቹንም በወርቅ ለበጣቸው።
ከዚያም ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ የበፍታ ድር መጋረጃ ሠራ። በላዩም ላይ ኪሩቦች እንዲጠለፉበት አደረገ።
ከዚያም ለመጋረጃው ከግራር እንጨት አራት ዓምዶችን ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው፤ ማንጠልጠያዎቻቸውም ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ ለዓምዶቹም ከብር የተሠሩ አራት መሰኪያዎችን አዘጋጀ።
በመቀጠልም ለድንኳኑ መግቢያ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ የበፍታ ድር የተሸመነ መከለያ ሠራ፤
እንዲሁም አምስቱን ዓምዶችና ማንጠልጠያዎቹን ሠራ። አናታቸውንና ማያያዣዎቻቸውንም በወርቅ ለበጣቸው፤ አምስቱ መሰኪያዎቻቸው ግን ከመዳብ የተሠሩ ነበሩ።
ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ አንተን ለፈርዖን እንደ አምላክ አድርጌሃለሁ፤ የገዛ ወንድምህ አሮን ደግሞ የአንተ ነቢይ ይሆናል።
አንተም የማዝህን ሁሉ ደግመህ ትናገራለህ፤ ወንድምህ አሮንም ለፈርዖን ይነግረዋል፤ እሱም እስራኤላውያን ከምድሩ እንዲወጡ ይለቃቸዋል።
እኔ ደግሞ የፈርዖን ልብ እንዲደነድን እፈቅዳለሁ፤ በግብፅ ምድርም ምልክቶቼንና ተአምራቴን አበዛለሁ።
ፈርዖን ግን አይሰማችሁም፤ እኔም በግብፅ ምድር ላይ እጄን አሳርፋለሁ፤ ሠራዊቴን ይኸውም ሕዝቤ የሆኑትን እስራኤላውያንን በታላቅ ፍርድ ከግብፅ ምድር አወጣቸዋለሁ።
በግብፅ ላይ እጄን ስዘረጋና እስራኤላውያንን ከመካከላቸው ሳወጣ ግብፃውያን እኔ ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ያውቃሉ።”
ሙሴና አሮን ይሖዋ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ልክ እንደተባሉት አደረጉ።
ከፈርዖን ጋር በተነጋገሩበት ጊዜ ሙሴ የ80 ዓመት ሰው፣ አሮን ደግሞ የ83 ዓመት ሰው ነበር።
በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦
“ምናልባት ፈርዖን ‘እስቲ ተአምር አሳዩ’ ቢላችሁ አሮንን ‘በትርህን ወስደህ በፈርዖን ፊት ጣለው’ በለው። በትሩም ትልቅ እባብ ይሆናል።”
ስለሆነም ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ገብተው ልክ ይሖዋ እንዳዘዛቸው አደረጉ። አሮንም በትሩን በፈርዖንና በአገልጋዮቹ ፊት ጣለው፤ በትሩም ትልቅ እባብ ሆነ።
ይሁንና ፈርዖን ጠቢባኑንና መተተኞቹን ጠራ፤ አስማት የሚሠሩ የግብፅ ካህናትም በአስማታቸው ተመሳሳይ ነገር አደረጉ።
እያንዳንዳቸውም በትራቸውን ጣሉ፤ በትሮቹም ትላልቅ እባቦች ሆኑ፤ ይሁን እንጂ የአሮን በትር የእነሱን በትሮች ዋጠ።
ያም ሆኖ የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ ልክ ይሖዋ እንዳለውም ያሉትን ነገር አልሰማቸውም።
ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የፈርዖን ልብ ደንድኗል። እሱም ሕዝቡን ለመልቀቅ እንቢተኛ ሆኗል።
በማለዳ ወደ ፈርዖን ሂድ። እሱም ወደ ውኃው ይወርዳል! አንተም እሱን ለማግኘት በአባይ ወንዝ ዳር ቁም፤ ወደ እባብ ተለውጦ የነበረውንም በትር በእጅህ ያዝ።
እንዲህም በለው፦ ‘የዕብራውያን አምላክ ይሖዋ ወደ አንተ ልኮኛል፤ እሱም “በምድረ በዳ እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ” ብሎሃል፤ ይኸው አንተ ግን እስካሁን ድረስ አልታዘዝክም።
እንግዲህ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ በዚህ ታውቃለህ። ይኸው በበትሬ በአባይ ወንዝ ውስጥ ያለውን ውኃ እመታለሁ፤ ውኃውም ወደ ደም ይለወጣል።
በአባይ ውስጥ ያሉት ዓሣዎች ይሞታሉ፤ አባይም ይከረፋል፤ ግብፃውያንም ከአባይ ወንዝ ውኃ መጠጣት አይችሉም።”’”
ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አሮንን እንዲህ በለው፦ ‘የግብፅ ውኃዎች ይኸውም ወንዞቿ፣ የመስኖ ቦዮቿ፣ ረግረጋማ ቦታዎቿና የተጠራቀሙት ውኃዎቿ ሁሉ ወደ ደም እንዲለወጡ በትርህን ወስደህ በእነሱ ላይ እጅህን ዘርጋ።’ በመላው የግብፅ ምድር ላይ ሌላው ቀርቶ ከእንጨትና ከድንጋይ በተሠሩ ዕቃዎች ውስጥ ደም ይሆናል።”
ሙሴና አሮን ወዲያውኑ ልክ ይሖዋ እንዳዘዛቸው አደረጉ። እሱም ፈርዖንና አገልጋዮቹ እያዩ በትሩን አንስቶ በአባይ ወንዝ ውስጥ ያለውን ውኃ መታ፤ በወንዙ ውስጥ የነበረውም ውኃ በሙሉ ወደ ደም ተለወጠ።
በወንዙ ውስጥ የነበሩት ዓሣዎች ሞቱ፤ ወንዙም መከርፋት ጀመረ፤ ግብፃውያንም ከአባይ ወንዝ ውኃ መጠጣት አልቻሉም፤ በመላው የግብፅ ምድር ላይም ደም ነበር።
ይሁንና አስማት የሚሠሩ የግብፅ ካህናትም በሚስጥራዊ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር አደረጉ፤ በመሆኑም የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ ልክ ይሖዋ እንዳለውም እነሱን ለመስማት እንቢተኛ ሆነ።
ከዚያም ፈርዖን ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ፤ ይህን ከቁም ነገር አልቆጠረውም።
ግብፃውያን ሁሉ ከአባይ ወንዝ ውኃ መጠጣት ስላልቻሉ የሚጠጣ ውኃ ለማግኘት የአባይን ዳርቻ ተከትለው ጉድጓዶችን ይቆፍሩ ነበር።
ይሖዋ አባይን ከመታ ሰባት ቀን አለፈ።
ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦
“ለእስራኤላውያን መዋጮ እንዲያመጡልኝ ንገራቸው፤ ለመስጠት ልቡ ካነሳሳው ከእያንዳንዱ ሰው መዋጮዬን ትቀበላላችሁ።
ከእነሱ የምትቀበሉት መዋጮም ይህ ነው፦ ወርቅ፣ ብር፣ መዳብ፣
ሰማያዊ ክር፣ ሐምራዊ ሱፍ፣ ደማቅ ቀይ ማግ፣ ጥሩ በፍታ፣ የፍየል ፀጉር፣
ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ፣ የአቆስጣ ቆዳ፣ የግራር እንጨት፣
ለመብራት የሚሆን ዘይት፣ ለቅብዓት ዘይትና ጥሩ መዓዛ ላለው ዕጣን የሚሆን በለሳን፣
ለኤፉዱ እንዲሁም ለደረት ኪሱ የሚሆኑ የኦኒክስ ድንጋዮችና ሌሎች ድንጋዮች።
ለእኔም መቅደስ ይሠሩልኛል፤ እኔም በመካከላቸው እኖራለሁ።
የማደሪያ ድንኳኑንም ሆነ በውስጡ የሚቀመጡትን ቁሳቁሶች ሁሉ እኔ በማሳይህ ንድፍ መሠረት ትሠሯቸዋላችሁ።
“ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል እንዲሁም ከፍታው አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ታቦት ከግራር እንጨት ይሠራሉ።
ከዚያም በንጹሕ ወርቅ ትለብጠዋለህ። ውስጡንና ውጭውን ትለብጠዋለህ፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ ትሠራለታለህ።
አራት የወርቅ ቀለበቶች ትሠራለታለህ፤ ከዚያም ሁለቱን ቀለበቶች በአንዱ በኩል ሁለቱን ቀለበቶች ደግሞ በሌላው በኩል በማድረግ ከአራቱ እግሮቹ በላይ ታያይዛቸዋለህ።
ከግራር እንጨት መሎጊያዎችን ትሠራለህ፤ በወርቅም ትለብጣቸዋለህ።
ታቦቱን ለመሸከም እንዲያገለግሉ መሎጊያዎቹን በታቦቱ ጎንና ጎን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ ታስገባቸዋለህ።
መሎጊያዎቹ በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ እንዳሉ ይቀመጣሉ፤ ከዚያ መውጣት የለባቸውም።
የምሰጥህንም ምሥክር በታቦቱ ውስጥ ታስቀምጠዋለህ።
“እንዲሁም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ መክደኛ ከንጹሕ ወርቅ ትሠራለህ።
ሁለት የወርቅ ኪሩቦችን ትሠራለህ፤ ወርቁን በመጠፍጠፍም በመክደኛው ጫፍና ጫፍ ላይ ወጥ አድርገህ ትሠራቸዋለህ።
በሁለቱ የመክደኛው ጫፎች ላይ ኪሩቦቹን ሥራ፤ አንዱን ኪሩብ በዚህኛው ጫፍ፣ ሌላኛውን ኪሩብ ደግሞ በዚያኛው ጫፍ ላይ ሥራ።
ኪሩቦቹ ሁለቱን ክንፎቻቸውን ወደ ላይ በመዘርጋት መክደኛውን በክንፎቻቸው ይከልሉታል፤ እነሱም ትይዩ ይሆናሉ። የኪሩቦቹ ፊት ወደ መክደኛው ያጎነበሰ ይሆናል።
መክደኛውንም በታቦቱ ላይ ትገጥመዋለህ፤ የምሰጥህንም ምሥክር በታቦቱ ውስጥ ታስቀምጠዋለህ።
እኔም በዚያ እገለጥልሃለሁ፤ ከመክደኛውም በላይ ሆኜ አነጋግርሃለሁ። በምሥክሩ ታቦት ላይ በሚገኙት በሁለቱ ኪሩቦች መካከል ሆኜ እስራኤላውያንን በተመለከተ የማዝህንም ሁሉ አሳውቅሃለሁ።
“በተጨማሪም ርዝመቱ ሁለት ክንድ፣ ወርዱ አንድ ክንድ፣ ከፍታው ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ጠረጴዛ ከግራር እንጨት ትሠራለህ።
በንጹሕ ወርቅ ትለብጠዋለህ፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ ትሠራለታለህ።
ዙሪያውንም አንድ ጋት ስፋት ያለው ጠርዝ ታበጅለታለህ፤ በጠርዙም ዙሪያ የወርቅ ክፈፍ ታደርግለታለህ።
አራት የወርቅ ቀለበቶች ትሠራለታለህ፤ ከዚያም ቀለበቶቹን አራቱ እግሮቹ በሚገኙባቸው አራት ማዕዘኖች ላይ ታደርጋቸዋለህ።
ጠረጴዛውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች እንዲይዙ ቀለበቶቹ በጠርዙ አጠገብ ይሆናሉ።
መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ትለብጣቸዋለህ፤ ጠረጴዛውንም በእነሱ አማካኝነት ትሸከማለህ።
“ለመጠጥ መባ ማፍሰሻ የሚያገለግሉትን ሳህኖቹን፣ ጽዋዎቹን፣ ማንቆርቆሪያዎቹንና ጎድጓዳ ሳህኖቹን ትሠራለህ። ከንጹሕ ወርቅ ትሠራቸዋለህ።
ገጸ ኅብስቱን በጠረጴዛው ላይ ሁልጊዜ በፊቴ ታስቀምጣለህ።
“ከንጹሕ ወርቅ መቅረዝ ትሠራለህ። መቅረዙም ወጥ ከሆነ ወርቅ ተጠፍጥፎ የተሠራ ይሁን። የመቅረዙ መቆሚያ፣ ግንድ፣ ቅርንጫፎች፣ አበባ አቃፊዎች፣ እንቡጦችና የፈኩት አበቦች ወጥ ሆነው የተሠሩ ይሆናሉ።
በመቅረዙ ጎንና ጎን ስድስት ቅርንጫፎች ይኖራሉ፤ ሦስቱ የመቅረዙ ቅርንጫፎች ከአንዱ ጎን፣ ሦስቱ የመቅረዙ ቅርንጫፎች ደግሞ ከሌላው ጎን የወጡ ይሆናሉ።
በአንዱ በኩል ባሉት ቅርንጫፎች በእያንዳንዳቸው ላይ የአልሞንድ አበባ የሚመስሉ ሦስት የአበባ አቃፊዎችን ከእንቡጦቹና ከፈኩት አበቦች ጋር እያፈራረቅክ ትሠራለህ፤ በሌላኛው በኩል ባሉት ቅርንጫፎችም በእያንዳንዳቸው ላይ የአልሞንድ አበባ የሚመስሉ ሦስት የአበባ አቃፊዎችን ከእንቡጦቹና ከፈኩት አበቦች ጋር እያፈራረቅክ ትሠራለህ። ስድስቱ ቅርንጫፎች ከመቅረዙ ግንድ የሚወጡት በዚህ መንገድ ይሆናል።
በግንዱ ላይም የአልሞንድ አበባ የሚመስሉ አራት የአበባ አቃፊዎችን ከእንቡጦቹና ከፈኩት አበቦች ጋር እያፈራረቅክ ትሠራለህ።
ከግንዱ በሚወጡት በመጀመሪያዎቹ ሁለት ቅርንጫፎች ሥር አንድ እንቡጥ ይኖራል፤ በቀጣዮቹ ሁለት ቅርንጫፎች ሥርም አንድ እንቡጥ ይኖራል፤ በቀጣዮቹ ሁለት ቅርንጫፎች ሥርም እንዲሁ አንድ እንቡጥ ይኖራል፤ ከግንዱ የሚወጡት ስድስቱም ቅርንጫፎች በዚሁ መንገድ ይሠራሉ።
እንቡጦቹና ቅርንጫፎቻቸው እንዲሁም የመቅረዙ ሁለመና ንጹሕ ከሆነ አንድ ወጥ ወርቅ ተጠፍጥፈው የተሠሩ ይሆናሉ።
ሰባት መብራቶች ትሠራለታለህ፤ መብራቶቹ በሚለኮሱበት ጊዜ ከፊት ለፊቱ ላለው አካባቢ ብርሃን ይሰጣሉ።