text stringlengths 4 267 |
|---|
“እጅጌ የሌለውን የኤፉዱን ቀሚስ ሙሉ በሙሉ ከሰማያዊ ክር ትሠራዋለህ። |
ከላይ በኩል መሃል ላይ የአንገት ማስገቢያ ይኖረዋል። የአንገት ማስገቢያውም ዙሪያውን በሽመና ባለሙያ የተሠራ ቅምቅማት ይኑረው። የአንገት ማስገቢያውም እንዳይቀደድ እንደ ጥሩር አንገትጌ ሆኖ ይሠራ። |
በታችኛው ጠርዝ ዙሪያ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍና ከደማቅ ቀይ ማግ የተሠሩ ሮማኖችን አድርግ፤ በመሃል በመሃላቸውም የወርቅ ቃጭሎች አድርግ። |
እጅጌ በሌለው ቀሚስ በታችኛው ጠርዝ ዙሪያ የወርቅ ቃጭል ከዚያም ሮማን፣ የወርቅ ቃጭል ከዚያም ሮማን እያፈራረቅክ አንጠልጥልበት። |
አሮን በሚያገለግልበት ጊዜ ይህን ልብስ መልበስ አለበት፤ በይሖዋ ፊት ለመቅረብ ወደ መቅደሱ በሚገባበትና ከዚያ በሚወጣበት ጊዜ እንዳይሞት የቃጭሎቹ ድምፅ መሰማት አለበት። |
“ከንጹሕ ወርቅም የሚያብረቀርቅ ጠፍጣፋ ወርቅ ሠርተህ ልክ ማኅተም በሚቀረጽበት መንገድ ‘ቅድስና የይሖዋ ነው’ ብለህ ትቀርጽበታለህ። |
እሱንም በሰማያዊ ገመድ በጥምጥሙ ላይ እሰረው፤ በጥምጥሙ ላይ ከፊት በኩል ይሆናል። |
በአሮን ግንባር ላይ ይሆናል፤ አሮንም አንድ ሰው ቅዱስ ከሆኑ ነገሮች ይኸውም እስራኤላውያን ቅዱስ ስጦታ አድርገው በሚያቀርቧቸው ጊዜ ከሚቀድሷቸው ነገሮች ጋር በተያያዘ ለሚፈጽመው ስህተት ተጠያቂ ይሆናል። በይሖዋም ፊት ተቀባይነት እንዲያገኙ ዘወትር በግንባሩ ላይ መሆን ይኖርበታል። |
“ከጥሩ በፍታ ረጅም ቀሚስ በካሬ ንድፍ ትሸምንለታለህ፤ እንዲሁም ከጥሩ በፍታ ጥምጥም ትሠራለህ፤ በተጨማሪም በሽመና የተሠራ መቀነት ትሠራለህ። |
“ለአሮን ወንዶች ልጆችም ክብርና ውበት የሚያጎናጽፏቸውን ረጃጅም ቀሚሶች፣ መቀነቶችና የራስ ቆቦች ትሠራላቸዋለህ። |
ወንድምህን አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ታለብሳቸዋለህ፤ እንዲሁም ትቀባቸዋለህ፣ ትሾማቸዋለህ ደግሞም ትቀድሳቸዋለህ፤ እነሱም ካህናት ሆነው ያገለግሉኛል። |
እርቃናቸውን የሚሸፍኑበት የበፍታ ቁምጣም ትሠራላቸዋለህ። ቁምጣውም ከወገባቸው እስከ ጭናቸው የሚደርስ ይሆናል። |
በደል እንዳይሆንባቸውና እንዳይሞቱ አሮንና ወንዶች ልጆቹ ወደ መገናኛ ድንኳኑ በሚገቡበት ጊዜ ወይም ቅዱስ በሆነው ስፍራ ለማገልገል ወደ መሠዊያው በሚቀርቡበት ጊዜ እነዚህን ልብሶች መልበስ አለባቸው። ይህ ለእሱም ሆነ ከእሱ በኋላ ለሚመጡት ዘሮቹ ዘላለማዊ ደንብ ነው። |
“አንድ ሰው በሬ ወይም በግ ቢሰርቅና ቢያርደው ወይም ቢሸጠው ለበሬው አምስት በሬዎችን ለበጉ ደግሞ አራት በጎችን ካሳ መክፈል አለበት። |
(“አንድ ሌባ ሰብሮ ሲገባ ቢያዝና ተመቶ ቢሞት ማንም ስለ እሱ በደም ዕዳ ተጠያቂ አይሆንም። |
ይህ የሆነው ግን ፀሐይ ከወጣች በኋላ ከሆነ ገዳዩ በደም ዕዳ ተጠያቂ ይሆናል።) “ሌባው ካሳ መክፈል አለበት። ምንም የሚከፍለው ነገር ከሌለው ግን ለሰረቃቸው ነገሮች ካሳ እንዲከፍል እሱ ራሱ ይሸጥ። |
የሰረቀው ነገር በሬም ሆነ አህያ ወይም በግ በሕይወት እንዳለ በእጁ ላይ ከተገኘ እጥፍ አድርጎ ካሳ መክፈል አለበት። |
“አንድ ሰው ከብቶቹን በእርሻ ወይም በወይን ቦታ አሰማርቶ የሌላ ሰው እርሻ ውስጥ ገብተው ሲግጡ ዝም ቢላቸው ይህ ሰው ምርጥ ከሆነው ከራሱ እርሻ ወይም ምርጥ ከሆነው ከራሱ የወይን ቦታ ካሳ መክፈል አለበት። |
“እሳት ተነስቶ ወደ ቁጥቋጦ ቢዛመትና ነዶዎችን ወይም ያልታጨደን እህል አሊያም አዝመራን ቢያወድም እሳቱን ያስነሳው ሰው ለተቃጠለው ነገር ካሳ መክፈል አለበት። |
“አንድ ሰው ገንዘብ ወይም ንብረት እንዲያስቀምጥለት ለባልንጀራው ቢሰጠውና ገንዘቡ ወይም ንብረቱ ከባልንጀራው ቤት ቢሰረቅ፣ ሌባው ከተያዘ እጥፍ አድርጎ ካሳ መክፈል አለበት። |
ሌባው ካልተያዘ ግን የቤቱ ባለቤት በባልንጀራው ንብረት ላይ እጁን አሳርፎ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማረጋገጥ በእውነተኛው አምላክ ፊት እንዲቀርብ መደረግ አለበት። |
አላግባብ በባለቤትነት የተያዘን ንብረት ይኸውም በሬን፣ አህያን፣ በግን፣ ልብስን ወይም ጠፍቶ የነበረን ማንኛውንም ነገር በተመለከተ ‘ይህ ንብረት የእኔ ነው!’ በሚል ክርክር ቢነሳ፣ ሁለቱም ሰዎች ጉዳያቸውን በእውነተኛው አምላክ ፊት ያቅርቡ። አምላክ ጥፋተኛ ነው ብሎ የሚፈርድበት ግለሰብ እጥፍ አድርጎ ለባልንጀራው ካሳ መክፈል አለበት። |
“አንድ ሰው አህያ ወይም በሬ ወይም በግ አሊያም ሌላ ማንኛውንም የቤት እንስሳ ለባልንጀራው በአደራ ቢሰጥና እንስሳው ቢሞት ወይም ከባድ ጉዳት ቢደርስበት አሊያም ማንም ሰው ሳያይ ተነድቶ ቢወሰድ |
አደራ ተቀባዩ በባልንጀራው ንብረት ላይ እጁን እንዳላሳረፈ ለማረጋገጥ በይሖዋ ፊት ይማልለት፤ የንብረቱ ባለቤትም መሐላውን መቀበል አለበት። ያም ሰው ካሳ እንዲከፍል አይጠየቅም። |
እንስሳው ተሰርቆበት ከሆነ ግን ለባለቤቱ ካሳ መክፈል አለበት። |
በአውሬ ተበልቶ ከሆነ ደግሞ ከአውሬ የተረፈውን ማስረጃ አድርጎ ያቅርብ። አውሬ ለበላው ካሳ መክፈል አይጠበቅበትም። |
“ሆኖም ማንኛውም ሰው ከባልንጀራው እንስሳ ቢዋስና እንስሳው ባለቤቱ በሌለበት ከባድ ጉዳት ቢደርስበት ወይም ቢሞት የተዋሰው ሰው ካሳ መክፈል አለበት። |
ጉዳቱ የደረሰው ባለቤቱ አብሮ እያለ ከሆነ ግን ካሳ መክፈል የለበትም። እንስሳው በኪራይ መልክ የተወሰደ ከሆነ የደረሰው ጉዳት በኪራዩ ዋጋ ይሸፈናል። |
“አንድ ወንድ አንዲትን ያልታጨች ድንግል አባብሎ አብሯት ቢተኛ የማጫዋን ዋጋ ከፍሎ ሚስቱ ሊያደርጋት ይገባል። |
የልጅቷ አባት ልጁን ለእሱ ለመስጠት ፈጽሞ ፈቃደኛ ሳይሆን ቢቀር ይህ ሰው ለደናግል የሚከፈለውን የማጫ ዋጋ መክፈል አለበት። |
“መተተኛ ሴት በሕይወት እንድትኖር አትፍቀድ። |
“ከእንስሳ ጋር የፆታ ግንኙነት የሚፈጽም ማንም ሰው ያለጥርጥር ይገደል። |
“ለይሖዋ ካልሆነ በቀር ለሌሎች አማልክት መሥዋዕት የሚያቀርብ ማንኛውም ሰው ይገደል። |
“የባዕድ አገር ሰውን አትበድል ወይም አትጨቁን፤ ምክንያቱም እናንተ ራሳችሁ በግብፅ ምድር ሳላችሁ የባዕድ አገር ሰው ነበራችሁ። |
“መበለቲቱን ወይም አባት የሌለውን ልጅ አታጎሳቁሉ። |
ብታጎሳቁለውና ወደ እኔ ቢጮኽ እኔ በእርግጥ ጩኸቱን እሰማለሁ፤ |
ቁጣዬም ይነድዳል። እናንተንም በሰይፍ እገድላችኋለሁ፤ ሚስቶቻችሁ መበለቶች፣ ልጆቻችሁም አባት የሌላቸው ልጆች ይሆናሉ። |
“ከሕዝቤ መካከል አብሮህ ላለ ችግረኛ ገንዘብ ብታበድር እንደ አራጣ አበዳሪ አትሁንበት። ወለድም አትጠይቁት። |
“የባልንጀራህን ልብስ መያዣ አድርገህ ብትይዝ ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ልትመልስለት ይገባል። |
ምክንያቱም የሚለብሰው ልብስ ይኸውም ሰውነቱ ላይ የሚጥለው ልብስ እሱ ብቻ ነው፤ አለዚያ ምን ለብሶ ይተኛል? እሱም ወደ እኔ በሚጮኽበት ጊዜ በእርግጥ እሰማዋለሁ፤ ምክንያቱም እኔ ሩኅሩኅ ነኝ። |
“አምላክን አትራገም፤ በሕዝብህ መካከል ያለውን አለቃም አትራገም። |
“ከተትረፈረፈው ምርትህና ሞልቶ ከሚፈሰው መጭመቂያህ መባ ለማቅረብ አትሳሳ። የወንዶች ልጆችህን በኩር ለእኔ መስጠት አለብህ። |
የበሬህንና የበግህን በኩር በተመለከተ ልታደርገው የሚገባህ ነገር ይህ ነው፦ ለሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቆይ። በስምንተኛው ቀን ለእኔ መስጠት አለብህ። |
“እናንተ ለእኔ ቅዱስ ሕዝብ ሆናችሁ መገኘት አለባችሁ፤ አውሬ ዘንጥሎት ሜዳ ላይ የተገኘን የማንኛውንም እንስሳ ሥጋ አትብሉ። ለውሾች ጣሉት። |
በዚያን ጊዜ ሙሴና እስራኤላውያን የሚከተለውን መዝሙር ለይሖዋ ዘመሩ፦ “በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ስላለ ለይሖዋ እዘምራለሁ። ፈረሱንና ፈረሰኛውን ባሕር ውስጥ ጣላቸው። |
አዳኜ ስለሆነልኝ ያህ ብርታቴና ኃይሌ ነው። እሱ አምላኬ ነው፤ አወድሰዋለሁ፤ የአባቴ አምላክ ነው፤ እኔም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ። |
ይሖዋ ኃያል ተዋጊ ነው። ስሙ ይሖዋ ነው። |
የፈርዖንን ሠረገሎችና ሠራዊቱን ባሕር ውስጥ ወረወራቸው፣ ምርጥ የሆኑ ተዋጊዎቹም ቀይ ባሕር ውስጥ ሰመጡ። |
ማዕበሉም ከደናቸው፤ እነሱም እንደ ድንጋይ ወደ ጥልቁ ሰመጡ። |
ይሖዋ ሆይ፣ ቀኝ እጅህ እጅግ ኃያል ነው፤ ይሖዋ ሆይ፣ ቀኝ እጅህ ጠላትን ያደቃል። |
እጅግ ታላቅ በሆነው ግርማህ በአንተ ላይ የሚነሱትን ሁሉ ቁልቁል ታሽቀነጥራቸዋለህ፤ የሚነደውን ቁጣህን ትልካለህ፤ እነሱንም እንደ ገለባ ይበላቸዋል። |
በአፍንጫህ እስትንፋስ ውኃዎች ተቆለሉ፤ ወራጁንም ውኃ ገድበው ቀጥ ብለው ቆሙ፤ ማዕበሉም በባሕሩ ልብ ውስጥ ረጋ። |
ጠላትም ‘አሳድዳቸዋለሁ! አሳድጄ እደርስባቸዋለሁ! እስክጠግብም ድረስ ምርኮን እከፋፈላለሁ! ሰይፌን እመዛለሁ! እጄም ታንበረክካቸዋለች!’ አለ። |
አንተም እስትንፋስህን እፍ አልክ፤ ባሕሩም ከደናቸው፤ እነሱም ኃያል በሆኑ ውኃዎች ውስጥ እንደ አረር ሰመጡ። |
ይሖዋ ሆይ፣ ከአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በቅድስናው ኃያል መሆኑን የሚያሳይ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? የምትፈራና የምትወደስ፣ ድንቅ ነገሮችን የምታደርግ አንተ ነህ። |
ቀኝ እጅህን ዘረጋህ፤ ምድርም ዋጠቻቸው። |
የታደግካቸውን ሕዝቦች በታማኝ ፍቅርህ መራሃቸው፤ በብርታትህም ወደ ቅዱስ መኖሪያህ ትመራቸዋለህ። |
ሕዝቦችም ይሰማሉ፤ ይንቀጠቀጣሉ፤ የፍልስጤም ነዋሪዎችም ምጥ ይይዛቸዋል። |
በዚያን ጊዜ የኤዶም አለቆች ይሸበራሉ፤ የሞዓብ ኃያላን ገዢዎች ብርክ ይይዛቸዋል። የከነአን ነዋሪዎችም ሁሉ ልባቸው ይከዳቸዋል። |
ፍርሃትና ድንጋጤ ይወድቅባቸዋል። ይሖዋ ሆይ፣ ሕዝቦችህ አልፈው እስኪሄዱ ድረስ፣ አንተ የፈጠርካቸው ሕዝቦች አልፈው እስኪሄዱ ድረስ፣ ከክንድህ ታላቅነት የተነሳ እንደ ድንጋይ ደርቀው ይቀራሉ። |
አምጥተህ በርስትህ ተራራ ላይ ትተክላቸዋለህ፤ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ራስህ ልትኖርበት ባዘጋጀኸው ጸንቶ የተመሠረተ ቦታ፣ ይሖዋ ሆይ፣ እጆችህ በመሠረቱት መቅደስ ትተክላቸዋለህ። |
ይሖዋ ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይገዛል። |
የፈርዖን ፈረሶች፣ የጦር ሠረገሎቹና ፈረሰኞቹ ወደ ባሕሩ በገቡ ጊዜ፣ ይሖዋ የባሕሩን ውኃ ላያቸው ላይ መለሰባቸው፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን በባሕሩ መሃል በደረቅ መሬት ተሻገረ።” |
ከዚያም የአሮን እህት ነቢዪቱ ሚርያም አታሞ አነሳች፤ ሴቶቹም ሁሉ አታሞ እየመቱና እየጨፈሩ ተከተሏት። |
ሚርያምም ከወንዶቹ ጋር እየተቀባበለች እንዲህ ስትል ዘመረች፦ “በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ስላለ ለይሖዋ ዘምሩ። ፈረሱንና ፈረሰኛውን ባሕር ውስጥ ጣላቸው።” |
ከዚያም ሙሴ እስራኤላውያንን ከቀይ ባሕር እየመራ ይዟቸው ወጣ፤ እነሱም ወደ ሹር ምድረ በዳ ሄዱ፤ በምድረ በዳውም ለሦስት ቀን ያህል ተጓዙ፤ ሆኖም ውኃ አላገኙም ነበር። |
በኋላም ወደ ማራ መጡ፤ ያም ሆኖ በማራ ያለው ውኃ መራራ ስለነበር ሊጠጡት አልቻሉም። የቦታውን ስም ማራ ያለውም በዚህ የተነሳ ነው። |
በመሆኑም ሕዝቡ “እንግዲህ ምን ልንጠጣ ነው?” እያለ በሙሴ ላይ ማጉረምረም ጀመረ። |
እሱም ወደ ይሖዋ ጮኸ፤ ይሖዋም ወደ አንዲት ዛፍ መራው። ሙሴም ዛፏን ውኃው ውስጥ ሲጥላት ውኃው ጣፋጭ ሆነ። እሱም በዚያ የሚመሩበት ሥርዓትና ለፍርድ መሠረት የሚሆን መመሪያ አወጣላቸው፤ በዚያም ፈተናቸው። |
እንዲህም አላቸው፦ “የአምላካችሁን የይሖዋን ቃል በጥንቃቄ ብታዳምጡ፣ በእሱ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ብታደርጉ፣ ለትእዛዛቱ ጆሯችሁን ብትሰጡና ሥርዓቶቹን በሙሉ ብታከብሩ በግብፃውያን ላይ ካመጣሁባቸው በሽታዎች አንዱንም በእናንተ ላይ አላመጣም፤ ምክንያቱም እኔ ይሖዋ እፈውሳችኋለሁ።” |
ከዚያም 12 የውኃ ምንጮችና 70 የዘንባባ ዛፎች ወዳሉበት ወደ ኤሊም መጡ። በዚያም በውኃው አጠገብ ሰፈሩ። |
በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሙሴ ከተራራው ላይ ሳይወርድ እንደቆየ አየ። በመሆኑም አሮንን ከበው እንዲህ አሉት፦ “እንግዲህ ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣን ያ ሙሴ ምን እንደደረሰበት ስለማናውቅ በል ተነስተህ ከፊት ከፊታችን የሚሄድ አምላክ ሥራልን።” |
አሮንም “በሚስቶቻችሁ እንዲሁም በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁ ጆሮዎች ላይ ያሉትን የወርቅ ጉትቻዎች አውልቃችሁ አምጡልኝ” አላቸው። |
በመሆኑም ሕዝቡ ሁሉ በጆሮዎቻቸው ላይ የነበሩትን የወርቅ ጉትቻዎች እያወለቁ ወደ አሮን ያመጡ ጀመር። |
እሱም ወርቁን ከእነሱ ወስዶ በቅርጽ ማውጫ ቅርጽ አወጣለት፤ የጥጃ ሐውልትም አድርጎ ሠራው። እነሱም “እስራኤል ሆይ፣ ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣህ አምላክህ ይህ ነው” ይሉ ጀመር። |
አሮንም ይህን ሲያይ በምስሉ ፊት መሠዊያ ሠራ። ከዚያም ድምፁን ከፍ አድርጎ “ነገ ለይሖዋ የሚከበር በዓል አለ” ሲል ተናገረ። |
በመሆኑም በማግስቱ በማለዳ ተነስተው የሚቃጠል መባና የኅብረት መሥዋዕት ያቀርቡ ጀመር። ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ። ከዚያም ሊጨፍሩ ተነሱ። |
በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከግብፅ ምድር መርተህ ያወጣኸው ሕዝብህ ምግባረ ብልሹ ስለሆነ ሂድ፣ ውረድ። |
እንዲሄዱበት ካዘዝኳቸው መንገድ ፈጥነው ዞር ብለዋል። ለራሳቸውም የጥጃ ሐውልት ሠርተዋል፤ ለእሱም እየሰገዱና መሥዋዕት እያቀረቡ ‘እስራኤል ሆይ፣ ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣህ አምላክህ ይህ ነው’ እያሉ ነው።” |
ይሖዋም በመቀጠል ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ይህ ሕዝብ ግትር መሆኑን ተመልክቻለሁ። |
እንግዲህ አሁን ቁጣዬ እንዲነድባቸውና እንዳጠፋቸው ተወኝ፤ አንተን በእነሱ ምትክ ታላቅ ብሔር አደርግሃለሁ።” |
ሙሴም አምላኩን ይሖዋን ተማጸነ፤ እንዲህም አለ፦ “ይሖዋ ሆይ፣ በታላቅ ኃይልና በብርቱ እጅ ከግብፅ ምድር ካወጣሃቸው በኋላ በሕዝብህ ላይ ቁጣህ የሚነደው ለምንድን ነው? |
ግብፃውያንስ ‘ቀድሞውንም ቢሆን መርቶ ያወጣቸው ተንኮል አስቦ ነው። በተራሮች ላይ ሊገድላቸውና ከምድር ገጽ ሊያጠፋቸው ፈልጎ ነው’ ለምን ይበሉ? ከሚነደው ቁጣህ ተመለስ፤ በሕዝብህ ላይ ይህን ጥፋት ለማምጣት ያደረግከውን ውሳኔ እስቲ እንደገና አስበው። |
‘ዘራችሁን በሰማያት ላይ እንዳሉት ከዋክብት አበዛዋለሁ፤ ለዘላለም ርስት አድርጎ እንዲወርሰውም ለዘራችሁ ለመስጠት ያሰብኩትን ይህን ምድር በሙሉ እሰጠዋለሁ’ በማለት በራስህ የማልክላቸውን አገልጋዮችህን አብርሃምን፣ ይስሐቅንና እስራኤልን አስታውስ።” |
በመሆኑም ይሖዋ በሕዝቡ ላይ እንደሚያመጣ የተናገረውን ጥፋት እንደገና አሰበበት። |
ከዚያም ሙሴ ሁለቱን የምሥክር ጽላቶች በእጁ እንደያዘ ተመልሶ ከተራራው ወረደ። ጽላቶቹም በሁለቱም በኩል ተቀርጾባቸው ነበር፤ በፊትም ሆነ በጀርባ ተጽፎባቸው ነበር። |
ጽላቶቹ የአምላክ ሥራ ነበሩ፤ በጽላቶቹ ላይ የተቀረጸው ጽሑፍም የአምላክ ጽሑፍ ነበር። |
ኢያሱም ሕዝቡ ይጮኽ ስለነበር ጫጫታውን ሲሰማ ሙሴን “በሰፈሩ ውስጥ የጦርነት ሁካታ ይሰማል” አለው። |
ሙሴ ግን እንዲህ አለው፦ “ይህ ድምፅ የድል መዝሙር አይደለም፤ ይህ ድምፅ በሽንፈት ምክንያት የሚሰማ የለቅሶ ድምፅም አይደለም፤ ይህ የምሰማው ድምፅ የተለየ መዝሙር ድምፅ ነው።” |
ሙሴም ወደ ሰፈሩ ሲቃረብ ጥጃውንና ጭፈራውን አየ፤ በዚህ ጊዜ ቁጣው ነደደ። ጽላቶቹንም ከእጁ ወርውሮ በተራራው ግርጌ ሰባበራቸው። |
የሠሩትንም ጥጃ ወስዶ በእሳት አቃጠለው፤ ሰባብሮም ዱቄት አደረገው፤ ከዚያም በውኃው ላይ በመበተን እስራኤላውያን እንዲጠጡት አደረገ። |
ሙሴም አሮንን “ይህን ከባድ ኃጢአት ያመጣህበት ይህ ሕዝብ ምን ቢያደርግህ ነው?” አለው። |
በዚህ ጊዜ አሮን እንዲህ አለ፦ “ጌታዬ አትቆጣ። መቼም ይህ ሕዝብ ወደ ክፋት ያዘነበለ እንደሆነ አንተ ራስህ በሚገባ ታውቃለህ። |
ስለዚህ ‘ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣን ያ ሙሴ ምን እንደደረሰበት ስለማናውቅ ከፊት ከፊታችን የሚሄድ አምላክ ሥራልን’ አሉኝ። |
በመሆኑም ‘ወርቅ ያለው ሁሉ አውልቆ ይስጠኝ’ አልኳቸው። ከዚያም ወርቁን እሳቱ ውስጥ ጣልኩት፤ ይህም ጥጃ ወጣ።” |
በተቃዋሚዎቻቸው ፊት መሳለቂያ እንዲሆኑ አሮን ሕዝቡን መረን ስለለቀቃቸው ሙሴ ሕዝቡ መረን እንደተለቀቀ አስተዋለ። |
ከዚያም ሙሴ በሰፈሩ መግቢያ ላይ ቆሞ “ከይሖዋ ጎን የሚቆም ማን ነው? ወደ እኔ ይምጣ!” አለ። በዚህ ጊዜ ሌዋውያን በሙሉ በዙሪያው ተሰበሰቡ። |
እሱም እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እያንዳንዳችሁ ሰይፋችሁን ታጠቁ፤ ከአንዱ በር ወደ ሌላው በር በመሄድና በሰፈሩ ውስጥ በማለፍ እያንዳንዱ ሰው ወንድሙን፣ ጎረቤቱንና የቅርብ ጓደኛውን ይግደል።’” |
ሌዋውያኑም ሙሴ እንዳላቸው አደረጉ። በመሆኑም በዚያ ዕለት 3,000 ገደማ የሚሆኑ ወንዶች ተገደሉ። |
ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለ፦ “እያንዳንዳችሁ በገዛ ልጃችሁና በገዛ ወንድማችሁ ላይ ስለተነሳችሁ ዛሬ ራሳችሁን ለይሖዋ ለዩ፤ እሱም ዛሬ በረከትን ያፈስላችኋል።” |
Subsets and Splits
No community queries yet
The top public SQL queries from the community will appear here once available.