text
stringlengths
4
267
በማግስቱም ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “ከባድ ኃጢአት ሠርታችኋል፤ እንግዲህ አሁን ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ አንድ ነገር ማድረግ እችል እንደሆነ ለማየት ወደ ይሖዋ እወጣለሁ።”
በመሆኑም ሙሴ ወደ ይሖዋ ተመልሶ እንዲህ አለ፦ “ይህ ሕዝብ የፈጸመው ኃጢአት ምንኛ ከባድ ነው! የወርቅ አምላክ ሠርተዋል።
ሆኖም አሁን ፈቃድህ ከሆነ ኃጢአታቸውን ይቅር በል፤ ካልሆነ ግን እባክህ እኔን ከጻፍከው መጽሐፍህ ላይ ደምስሰኝ።”
ይሁንና ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በእኔ ላይ ኃጢአት የሠራውን ሁሉ ከመጽሐፌ ላይ እደመስሰዋለሁ።
በል አሁን ሄደህ ሕዝቡን ወደነገርኩህ ስፍራ እየመራህ ውሰዳቸው። እነሆ መልአኬ ከፊት ከፊትህ ይሄዳል፤ ሕዝቡን በምመረምርበትም ቀን ስለሠሩት ኃጢአት ቅጣት አመጣባቸዋለሁ።”
ከዚያም ይሖዋ፣ በሠሩት ጥጃ ይኸውም አሮን በሠራላቸው ጥጃ ምክንያት ሕዝቡን በመቅሰፍት መታ።
ሆኖም ሙሴ “‘ይሖዋ አልተገለጠልህም’ ቢሉኝና ባያምኑኝስ? ቃሌንስ ባይሰሙ?” አለው።
ይሖዋም “በእጅህ የያዝከው ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። እሱም መልሶ “በትር ነው” አለ።
እሱም “መሬት ላይ ጣለው” አለው። እሱም መሬት ላይ ጣለው፤ በትሩም እባብ ሆነ፤ ሙሴም ከእባቡ ሸሸ።
በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን “እጅህን ዘርግተህ ጅራቱን ያዘው” አለው። እሱም እጁን ዘርግቶ ያዘው፤ እባቡም በእጁ ላይ እንደገና በትር ሆነ።
ከዚያም አምላክ “ይህ የሆነው የአባቶቻቸው አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ይሖዋ እንደተገለጠልህ እንዲያምኑ ነው” አለው።
ይሖዋም በድጋሚ “እባክህ እጅህን ወዳጣፋኸው ልብስ ውስጥ አስገባ” አለው። እሱም እጁን ወዳጣፋው ልብስ ውስጥ አስገባ። ባወጣውም ጊዜ እጁ በለምጽ ተመቶ ልክ እንደ በረዶ ነጭ ሆኖ ነበር!
ከዚያም “እጅህን ወዳጣፋኸው ልብስ ውስጥ መልሰህ አስገባው” አለው። እሱም እጁን መልሶ ልብሱ ውስጥ አስገባው። እጁንም ከልብሱ ውስጥ ባወጣው ጊዜ እጁ ተመልሶ እንደ ሌላው የሰውነቱ ክፍል ሆነ!
እሱም እንዲህ አለው፦ “ባያምኑህ ወይም የመጀመሪያውን ተአምራዊ ምልክት ችላ ቢሉ እንኳ የኋለኛውን ተአምራዊ ምልክት በእርግጥ አምነው ይቀበላሉ።
እንደዛም ሆኖ እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑና ቃልህን ለመስማት ፈቃደኛ ባይሆኑ ከአባይ ወንዝ ውኃ ቀድተህ በደረቁ መሬት ላይ አፍስሰው፤ ከአባይ የቀዳኸው ውኃ በደረቁ መሬት ላይ ደም ይሆናል።”
ሙሴም ይሖዋን “ይሖዋ ሆይ፣ ይቅርታ አድርግልኝ፤ እኔ ከዚህ በፊትም ሆነ አንተ አገልጋይህን ካነጋገርክበት ጊዜ ጀምሮ ፈጽሞ አንደበተ ርቱዕ አይደለሁም፤ ንግግር የማልችልና ተብታባ ሰው ነኝ” አለው።
ይሖዋም እንዲህ አለው፦ “ለሰው አፍ የፈጠረለት ማን ነው? ሰዎችን ዱዳ፣ ደንቆሮ ወይም ዕውር የሚያደርግ አሊያም ለሰዎች የዓይን ብርሃን የሚሰጥ ማን ነው? እኔ ይሖዋ አይደለሁም?
በል አሁን ሂድ፤ በምትናገርበት ጊዜ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ የምትናገረውንም ነገር አስተምርሃለሁ።”
እሱ ግን “ይሖዋ ሆይ፣ ይቅርታ አድርግልኝ፤ እባክህ መላክ የፈለግከውን ሌላ ማንኛውንም ሰው ላክ” አለው።
በዚህ ጊዜ የይሖዋ ቁጣ በሙሴ ላይ ነደደ፤ እንዲህም አለው፦ “እሺ ሌዋዊው ወንድምህ አሮንስ? እሱ በደንብ መናገር እንደሚችል አውቃለሁ። ደግሞም አንተን ለማግኘት አሁን ወደዚህ እየመጣ ነው። በሚያይህም ጊዜ ልቡ በደስታ ይሞላል።
ስለሆነም እሱን አነጋግረው፤ ቃላቱንም በአንደበቱ አኑር፤ በምትናገሩበትም ጊዜ ከአንተና ከእሱ ጋር እሆናለሁ፤ ምን ማድረግ እንዳለባችሁም አስተምራችኋለሁ።
እሱም አንተን ወክሎ ለሕዝቡ ይናገራል፤ እንደ ቃል አቀባይም ይሆንልሃል፤ አንተም ለእሱ እንደ አምላክ ትሆናለህ።
ይህን በትር በእጅህ ይዘህ ትሄዳለህ፤ በእሱም ተአምራዊ ምልክቶቹን ትፈጽማለህ።”
ስለዚህ ሙሴ ወደ አማቱ ወደ ዮቶር ተመልሶ በመሄድ “እስካሁን በሕይወት መኖር አለመኖራቸውን አይ ዘንድ እባክህ በግብፅ ወዳሉት ወንድሞቼ ተመልሼ ልሂድ” አለው። ዮቶርም ሙሴን “በሰላም ሂድ” አለው።
ከዚያ በኋላ ይሖዋ ሙሴን በምድያም ሳለ “ሂድ፤ ወደ ግብፅ ተመለስ፤ ነፍስህን ለማጥፋት የሚፈልጉት ሰዎች በሙሉ ሞተዋል” አለው።
ከዚያም ሙሴ ሚስቱንና ልጆቹን በአህያ ላይ አስቀምጦ ወደ ግብፅ ምድር ለመመለስ ጉዞ ጀመረ። የእውነተኛውን አምላክ በትርም በእጁ ይዞ ነበር።
ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ግብፅ ከተመለስክ በኋላ፣ በሰጠሁህ ኃይል የምታከናውናቸውን ተአምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት መፈጸም እንዳለብህ አትዘንጋ። እኔ ግን ልቡ እንዲደነድን እፈቅዳለሁ፤ እሱም ሕዝቡን አይለቅም።
ፈርዖንንም እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እስራኤል ልጄ ነው፤ አዎ፣ የበኩር ልጄ ነው።
እንግዲህ ‘እንዲያገለግለኝ ልጄን ልቀቅ’ ብዬሃለሁ። ለመልቀቅ ፈቃደኛ ካልሆንክ ግን ልጅህን፣ አዎ የበኩር ልጅህን እገድላለሁ።”’”
ይሖዋም በመንገድ ላይ ባለው የእንግዳ ማረፊያ ስፍራ አገኘው፤ እሱንም ሊገድለው ፈልጎ ነበር።
በመጨረሻም ሲፓራ ባልጩት ወስዳ ልጇን ገረዘችው፤ ሸለፈቱን እግሩን ካስነካች በኋላም “ይህ የሆነው አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ስለሆንክ ነው” አለች።
ስለሆነም እንዲሄድ ፈቀደለት። እሷም በዚህ ጊዜ በግርዛቱ የተነሳ “የደም ሙሽራ” አለች።
ይሖዋም አሮንን “ሙሴን ለማግኘት ወደ ምድረ በዳ ሂድ” አለው። እሱም ሄደ፤ በእውነተኛውም አምላክ ተራራ ላይ አገኘው፤ ከዚያም ሳመው።
ሙሴም ይሖዋ እንዲናገር የላከውን ቃል ሁሉ እንዲሁም እንዲፈጽማቸው ያዘዘውን ተአምራዊ ምልክቶች ሁሉ ለአሮን ነገረው።
ከዚህ በኋላ ሙሴና አሮን ሄደው የእስራኤልን ሽማግሌዎች በሙሉ ሰበሰቡ።
አሮንም ይሖዋ ለሙሴ የነገረውን ቃል ሁሉ ነገራቸው፤ እሱም በሕዝቡ ፊት ተአምራዊ ምልክቶቹን አደረገ።
በዚህ ጊዜ ሕዝቡ አመነ። ይሖዋ ፊቱን ወደ እስራኤላውያን እንደመለሰና ሥቃያቸውንም እንዳየ ሲሰሙ ተደፍተው ሰገዱ።
በቅዱሱ ስፍራ ለማገልገል የሚለበሱትን በጥሩ ሁኔታ የተሸመኑትን ልብሶች ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍና ከደማቅ ቀይ ማግ ሠሩ። ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረትም የአሮንን ቅዱስ ልብሶች ሠሩ።
እሱም ኤፉዱን ከወርቅ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ሠራው።
እነሱም ወርቁን በመቀጥቀጥ በስሱ ጠፈጠፉት፤ እሱም ከሰማያዊው ክር፣ ከሐምራዊው ሱፍ፣ ከደማቁ ቀይ ማግና ከጥሩው በፍታ ጋር አብሮ እንዲሠራው ወርቁን እንደ ክር በቀጫጭኑ ሰነጣጠቀው፤ ከዚያም በወርቁ ጥልፍ ጠለፈበት።
ለኤፉዱም ላዩ ላይ የሚጣበቁ የትከሻ ጥብጣቦች የሠሩለት ሲሆን ኤፉዱም ከትከሻ ጥብጣቦቹ ጋር የሚያያዘው በሁለቱ ጫፎቹ ላይ ነበር።
ኤፉዱ ወዲያ ወዲህ እንዳይንቀሳቀስ ለማሰር የሚያገለግለው ከኤፉዱ ጋር የተያያዘው በሽመና የተሠራው መቀነትም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት እንደ ኤፉዱ ሁሉ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ተሠራ።
ከዚያም የኦኒክስ ድንጋዮቹን በወርቅ አቃፊዎቹ ውስጥ አስቀመጧቸው፤ የእስራኤልን ወንዶች ልጆች ስሞችም ልክ ማኅተም በሚቀረጽበት መንገድ ቀረጹባቸው።
እሱም ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ለእስራኤል ልጆች እንደ መታሰቢያ ድንጋዮች ሆነው እንዲያገለግሉ በኤፉዱ የትከሻ ጥብጣቦች ላይ አስቀመጣቸው።
ከዚያም የደረት ኪሱን የጥልፍ ባለሙያ እንደሚሠራው አድርጎ ልክ ኤፉዱ በተሠራበት መንገድ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ሠራው።
ለሁለት በሚታጠፍበት ጊዜም አራቱም ጎኖቹ እኩል ነበሩ። ለሁለት በሚታጠፍበት ጊዜ ቁመቱም ሆነ ወርዱ አንድ ስንዝር የሆነውን የደረት ኪስ ሠሩ።
በላዩም ላይ አራት ረድፍ ድንጋዮችን አደረጉበት። በመጀመሪያው ረድፍ ሩቢ፣ ቶጳዝዮንና መረግድ ተደረደረ።
በሁለተኛው ረድፍ ደግሞ በሉር፣ ሰንፔርና ኢያስጲድ ተደረደረ።
በሦስተኛው ረድፍ ለሼም፣ አካትምና አሜቴስጢኖስ ተደረደረ።
በአራተኛውም ረድፍ ክርስቲሎቤ፣ ኦኒክስና ጄድ ተደረደረ። በወርቅ አቃፊዎችም ውስጥ ተቀመጡ።
ድንጋዮቹም 12ቱን የእስራኤል ወንዶች ልጆች ስሞች የሚወክሉ ነበሩ፤ ስሞቹም ልክ ማኅተም በሚቀረጽበት መንገድ ተቀረጹ፤ እያንዳንዱ ስም ከ12ቱ ነገዶች አንዱን የሚወክል ነበር።
ከዚያም በደረት ኪሱ ላይ እንደ ገመድ የተጎነጎነ ሰንሰለት ከንጹሕ ወርቅ ሠሩ።
በመቀጠልም ሁለት የወርቅ አቃፊዎችንና ሁለት ቀለበቶችን ሠሩ፤ ሁለቱን ቀለበቶችም በደረት ኪሱ ሁለት ማዕዘኖች ላይ አያያዟቸው።
በኋላም ሁለቱን የወርቅ ገመዶች በደረት ኪሱ ማዕዘኖች ላይ በሚገኙት ሁለት ቀለበቶች ውስጥ አስገቧቸው።
ከዚያም የሁለቱን ገመዶች ሁለት ጫፎች በሁለቱ አቃፊዎች ውስጥ አስገቧቸው፤ በኤፉዱ በፊት በኩል በትከሻ ጥብጣቦቹ ላይ አያያዟቸው።
በመቀጠልም ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተው በኤፉዱ በኩል በሚውለው በደረት ኪሱ ውስጠኛ ጠርዝ ሁለት ጫፎች ላይ አደረጓቸው።
ከዚያም ሁለት ተጨማሪ የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተው በኤፉዱ ላይ ከፊት በኩል ከሁለቱ የትከሻ ጥብጣቦች በታች፣ መጋጠሚያው አጠገብ፣ በሽመና ከተሠራው የኤፉዱ መቀነት በላይ አደረጓቸው።
በመጨረሻም ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት የደረት ኪሱ ከኤፉዱ ላይ ሳይንቀሳቀስ፣ ተሸምኖ ከተሠራው መቀነት በላይ እንዲውል የደረት ኪሱን ቀለበቶች ከኤፉዱ ቀለበቶች ጋር በሰማያዊ ገመድ አያያዟቸው።
ከዚያም እጅጌ የሌለውን የኤፉዱን ቀሚስ የሽመና ባለሙያ ሙሉ በሙሉ በሰማያዊ ክር ሸምኖ እንዲሠራው አደረገ።
የቀሚሱ አንገት ማስገቢያ ልክ እንደ ጥሩር አንገት ማስገቢያ መሃል ላይ ነበር። የአንገት ማስገቢያውም እንዳይቀደድ ዙሪያውን ተቀምቅሞ ነበር።
ከዚያም ሰማያዊ ክር፣ ሐምራዊ ሱፍና ደማቅ ቀይ ማግ አንድ ላይ በመግመድ በታችኛው የቀሚሱ ጠርዝ ዙሪያ ዘርፍ የሚሆኑ ሮማኖችን ሠሩ።
በተጨማሪም ከንጹሕ ወርቅ ቃጭሎችን ሠሩ፤ ቃጭሎቹንም በቀሚሱ ጠርዝ ዙሪያ በሮማኖቹ መሃል መሃል አደረጓቸው።
ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረትም ለአገልግሎት በሚውለው ቀሚስ የታችኛው ጠርዝ ዙሪያ ቃጭል ከዚያም ሮማን፣ ቃጭል ከዚያም ሮማን እያፈራረቁ አደረጉበት።
ከዚያም ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ ከጥሩ በፍታ ረጅም ቀሚስ በሽመና ባለሙያ አሠሩላቸው፤
በተጨማሪም ጥምጥሙን ከጥሩ በፍታ፣ ጌጠኛ የራስ ቆቦቹንም ከጥሩ በፍታ፣ የበፍታ ቁምጣውን በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ
እንዲሁም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት መቀነቱን በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍና ከደማቅ ቀይ ማግ ሸምነው ሠሩት።
በመጨረሻም የሚያብረቀርቀውን ጠፍጣፋ ወርቅ ይኸውም ለአምላክ የተወሰኑ መሆንን የሚያሳየውን ቅዱስ ምልክት ከንጹሕ ወርቅ ሠሩ፤ አንድ ሰው ማኅተም በሚቀርጽበት መንገድ “ቅድስና የይሖዋ ነው” የሚል ጽሑፍ በላዩ ላይ ቀረጹበት።
ከዚያም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት በጥምጥሙ ላይ እንዲውል ለማድረግ ሰማያዊ ገመድ አሰሩበት።
የማደሪያ ድንኳኑ ይኸውም የመገናኛ ድንኳኑ ሥራ በሙሉ ተጠናቀቀ፤ እስራኤላውያን ይሖዋ ሙሴን ያዘዘውን ነገር ሁሉ ሠሩ። ልክ እንደታዘዙትም አደረጉ።
እነሱም የማደሪያ ድንኳኑን ወደ ሙሴ አመጡ፤ ድንኳኑንና ዕቃዎቹን በሙሉ ማለትም ማያያዣዎቹን፣ አራት ማዕዘን ቋሚዎቹን፣ አግዳሚ እንጨቶቹን፣ ዓምዶቹን፣ መሰኪያዎቹን፣
ለመደረቢያ የሚሆነውን ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳና ለመደረቢያ የሚሆነውን የአቆስጣ ቆዳ፣ ለመግቢያው መከለያ የሚሆነውን መጋረጃ፣
የምሥክሩን ታቦት እንዲሁም መሎጊያዎቹንና መክደኛውን፣
ጠረጴዛውን እንዲሁም ዕቃዎቹን በሙሉና ገጸ ኅብስቱን፣
ከንጹሕ ወርቅ የተሠራውን መቅረዝ እንዲሁም በመደዳ የተደረደሩትን መብራቶቹንና ዕቃዎቹን በሙሉ፣ የመብራቱን ዘይት፣
የወርቅ መሠዊያውን፣ የቅብዓት ዘይቱን፣ ጥሩ መዓዛ ያለውን ዕጣን፣ ለድንኳኑ መግቢያ የሚሆነውን መከለያ፣
የመዳብ መሠዊያውንና የመዳብ ፍርግርጉን እንዲሁም መሎጊያዎቹንና ዕቃዎቹን በሙሉ፣ ገንዳውንና ማስቀመጫውን፣
የግቢውን መጋረጃዎች እንዲሁም ቋሚዎቹን፣ መሰኪያዎቹን፣ ለግቢው መግቢያ የሚሆነውን መከለያ፣ የድንኳኑን ገመዶች፣ የድንኳኑን ካስማዎችና በማደሪያ ድንኳኑ ይኸውም በመገናኛ ድንኳኑ ለሚከናወነው አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች በሙሉ፣
በመቅደሱ ለማገልገል የሚለበሱትን በጥሩ ሁኔታ ተሸምነው የተሠሩትን ልብሶች፣ የካህኑን የአሮንን ቅዱስ ልብሶች እንዲሁም ወንዶች ልጆቹ ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸውን ልብሶች አመጡ።
እስራኤላውያን ሥራውን በሙሉ ያከናወኑት ይሖዋ ለሙሴ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ነበር።
ሙሴም ሥራቸውን በሙሉ ሲመለከት ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት እንደሠሩ አየ፤ ከዚያም ባረካቸው።
ከዚያም አምላክ ይህን ቃል ሁሉ ተናገረ፦
“ከግብፅ ምድር፣ ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እኔ አምላክህ ይሖዋ ነኝ።
ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ።
“በላይ በሰማያት ወይም በታች በምድር አሊያም ከምድር በታች በውኃ ውስጥ ባለ በማንኛውም ነገር አምሳል የተቀረጸን ቅርጽ ወይም የተሠራን ምስል ለራስህ አታድርግ።
አትስገድላቸው፤ ተታለህም እነሱን አታገልግል፤ ምክንያቱም እኔ አምላክህ ይሖዋ እኔ ብቻ እንድመለክ የምፈልግና በሚጠሉኝ ሁሉ ላይ በአባቶች ስህተት የተነሳ በልጆቻቸው እንዲሁም በሦስተኛና በአራተኛ ትውልዶቻቸው ላይ ቅጣት የማመጣ አምላክ ነኝ፤
ሆኖም ለሚወዱኝና ትእዛዛቴን ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ታማኝ ፍቅር የማሳይ አምላክ ነኝ።
“የአምላክህን የይሖዋን ስም በከንቱ አታንሳ፤ ምክንያቱም ይሖዋ ስሙን በከንቱ የሚያነሳውን ሳይቀጣ አይተወውም።
“የሰንበትን ቀን ቅዱስ አድርገህ መጠበቅ እንዳለብህ አትርሳ።
ሥራህንና የምታከናውናቸውን ነገሮች በሙሉ በስድስት ቀን ሠርተህ አጠናቅ፤
ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለይሖዋ ሰንበት ነው። በዚህ ቀን አንተም ሆንክ ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ ባሪያህም ሆነ ሴት ባሪያህ፣ የቤት እንስሳህም ሆነ በሰፈርህ ውስጥ ያለ የባዕድ አገር ሰው ምንም ሥራ አትሥሩ።
ምክንያቱም ይሖዋ ሰማያትን፣ ምድርን፣ ባሕርንና በውስጣቸው ያሉትን ነገሮች ሁሉ በስድስት ቀናት ውስጥ ሠርቶ ካጠናቀቀ በኋላ በሰባተኛው ቀን ማረፍ ጀምሯል። ይሖዋ የሰንበትን ቀን የባረከውና የቀደሰው ለዚህ ነው።
“አምላክህ ይሖዋ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር።
“አትግደል።
“አታመንዝር።
“አትስረቅ።
“በባልንጀራህ ላይ ምሥክር ሆነህ ስትቀርብ በሐሰት አትመሥክር።
“የባልንጀራህን ቤት አትመኝ። የባልንጀራህን ሚስት፣ ወንድ ባሪያውን፣ ሴት ባሪያውን፣ በሬውን ወይም አህያውን አሊያም የባልንጀራህ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትመኝ።”
ሕዝቡም ሁሉ የነጎድጓዱንና የቀንደ መለከቱን ድምፅ ሰሙ፤ እንዲሁም የመብረቁን ብልጭታና የተራራውን ጭስ ተመለከቱ፤ ይህም በፍርሃት እንዲንቀጠቀጡና ርቀው እንዲቆሙ አደረጋቸው።
በመሆኑም ሙሴን “አንተ አነጋግረን፤ እኛም እናዳምጥሃለን፤ ሆኖም እንዳንሞት ስለምንፈራ አምላክ አያነጋግረን” አሉት።
ሙሴም ሕዝቡን “አትፍሩ፤ ምክንያቱም እውነተኛው አምላክ የመጣው እናንተን ለመፈተን ይኸውም ዘወትር እሱን በመፍራት ኃጢአት ከመሥራት እንድትቆጠቡ ለማድረግ ነው” አላቸው።