text stringlengths 4 267 |
|---|
እነሱም በመካከላቸው እኖር ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው እኔ አምላካቸው ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ያውቃሉ። እኔ አምላካቸው ይሖዋ ነኝ። |
ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ፈርዖን ገብተህ እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ። |
እነሱን ለመልቀቅ አሁንም ፈቃደኛ የማትሆን ከሆነ ምድርህን በሙሉ በእንቁራሪት መቅሰፍት እመታለሁ። |
የአባይም ወንዝ በእንቁራሪቶች ይሞላል፤ እነሱም ወጥተው ወደ ቤትህ፣ ወደ መኝታ ክፍልህ ይገባሉ፤ አልጋህም ላይ ይወጣሉ፤ እንዲሁም ወደ አገልጋዮችህ ቤቶች ይገባሉ፤ ሕዝብህም ላይ ይወጣሉ፤ መጋገሪያ ምድጃዎችህና ቡሃቃዎችህም ውስጥ ይገባሉ። |
እንቁራሪቶቹ በአንተ፣ በሕዝብህና በአገልጋዮችህ ሁሉ ላይ ይወጡባችኋል።”’” |
በኋላም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አሮንን እንዲህ በለው፦ ‘እጅህን ሰንዝረህ ወንዞቹን፣ የአባይ ወንዝ የመስኖ ቦዮቹንና ረግረጋማ ቦታዎቹን በበትርህ በመምታት እንቁራሪቶቹ በግብፅ ምድር ላይ እንዲወጡ አድርግ።’” |
ስለዚህ አሮን በግብፅ ውኃዎች ላይ እጁን ሰነዘረ፤ እንቁራሪቶቹም እየወጡ የግብፅን ምድር መውረር ጀመሩ። |
ይሁን እንጂ አስማተኞቹ ካህናትም በሚስጥራዊ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር ፈጸሙ፤ እነሱም እንቁራሪቶች በግብፅ ምድር ላይ እንዲወጡ አደረጉ። |
ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን ጠርቶ “ሕዝቡ ለይሖዋ መሥዋዕት እንዲያቀርብ መልቀቅ ስለምፈልግ እንቁራሪቶቹን ከእኔም ሆነ ከሕዝቤ ላይ እንዲያስወግድ ይሖዋን ለምኑልኝ” አላቸው። |
ከዚያም ሙሴ ፈርዖንን እንዲህ አለው፦ “እንቁራሪቶቹ ከአንተ፣ ከአገልጋዮችህ፣ ከሕዝብህና ከቤቶችህ ይወገዱ ዘንድ አምላክን እንድለምንልህ የምትፈልገው መቼ እንደሆነ የመወሰኑን ጉዳይ ለአንተ ትቼዋለሁ። እንቁራሪቶቹ በአባይ ወንዝ ውስጥ ብቻ ተወስነው ይቀራሉ።” |
እሱም “ነገ ይሁን” አለው። በመሆኑም ሙሴ እንዲህ አለው፦ “እንደ አምላካችን እንደ ይሖዋ ያለ ማንም እንደሌለ እንድታውቅ ልክ እንዳልከው ይሆናል። |
እንቁራሪቶቹ ከአንተ፣ ከቤቶችህ፣ ከአገልጋዮችህና ከሕዝቦችህ ይወገዳሉ። በአባይ ወንዝ ውስጥ ብቻ ተወስነው ይቀራሉ።” |
ሙሴና አሮንም ከፈርዖን ፊት ወጥተው ሄዱ፤ ሙሴም ይሖዋ በፈርዖን ላይ ያመጣቸውን እንቁራሪቶች አስመልክቶ ወደ እሱ ጮኸ። |
ይሖዋም ሙሴ እንደጠየቀው አደረገ፤ እንቁራሪቶቹም በየቤቱ፣ በየግቢውና በየሜዳው መሞት ጀመሩ። |
እነሱም እንቁራሪቶቹን በየቦታው ከመሯቸው፤ ምድሪቱም መግማት ጀመረች። |
ፈርዖንም ችግሩ ጋብ ማለቱን ባየ ጊዜ ልቡን አደነደነ፤ ልክ ይሖዋ እንደተናገረውም እነሱን ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነም። |
በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አሮንን እንዲህ በለው፦ ‘በትርህን ሰንዝረህ የምድርን አቧራ ምታ፤ አቧራውም በመላው የግብፅ ምድር ላይ ትንኝ ይሆናል።’” |
እነሱም እንዲሁ አደረጉ። አሮን በእጁ የያዘውን በትር ሰንዝሮ የምድርን አቧራ መታ፤ ትንኞቹም ሰዉንም እንስሳውንም ወረሩ። በምድሪቱ ያለው አቧራ ሁሉ በመላው የግብፅ ምድር ላይ ትንኝ ሆነ። |
አስማተኞቹ ካህናትም ተመሳሳይ ነገር ለመፈጸምና በሚስጥራዊ ጥበባቸው ትንኞች እንዲፈሉ ለማድረግ ሞከሩ፤ ሆኖም አልቻሉም። ትንኞቹ ሰዉንም እንስሳውንም ወርረው ነበር። |
በመሆኑም አስማተኞቹ ካህናት ፈርዖንን “ይህ የአምላክ ጣት ነው!” አሉት። የፈርዖን ልብ ግን ደነደነ፤ ልክ ይሖዋ እንዳለውም እነሱን አልሰማቸውም። |
ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በማለዳ ተነስተህ ፈርዖን ፊት ቁም። እሱም ወደ ውኃው ይወርዳል! አንተም እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ። |
ሕዝቤን የማትለቅ ከሆነ ግን በአንተ፣ በአገልጋዮችህና በሕዝብህ ላይ እንዲሁም በቤቶችህ ውስጥ ተናካሽ ዝንብ እለቃለሁ፤ ዝንቦቹም በግብፅ ያሉትን ቤቶች ይሞላሉ፤ አልፎ ተርፎም የቆሙበትን መሬት ይሸፍናሉ። |
በዚያ ቀን ሕዝቤ የሚኖርበትን የጎሸንን ምድር እለያለሁ። በዚያ ምንም ተናካሽ ዝንብ አይኖርም፤ ይህን በማድረጌም እኔ ይሖዋ በምድሪቱ መካከል እንዳለሁ ታውቃለህ። |
እኔም በሕዝቤና በሕዝብህ መካከል ልዩነት እንዲኖር አደርጋለሁ። ይህ ምልክት ነገ ይፈጸማል።”’” |
ይሖዋም እንዳለው አደረገ፤ የተናካሽ ዝንብ መንጋም የፈርዖንን ቤትና የአገልጋዮቹን ቤቶች እንዲሁም መላውን የግብፅ ምድር መውረር ጀመረ። በተናካሽ ዝንቦቹም የተነሳ ምድሪቱ ክፉኛ ተበላሸች። |
በመጨረሻም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን ጠርቶ “ሂዱ፤ በምድሪቱም ለአምላካችሁ መሥዋዕት ሠዉ” አላቸው። |
ሙሴ ግን እንዲህ አለው፦ “ይሄማ ተገቢ አይደለም፤ ምክንያቱም እኛ ለአምላካችን ለይሖዋ መሥዋዕት የምናደርገው ነገር ለግብፃውያን አስጸያፊ ነው። ታዲያ ግብፃውያን የሚጸየፉትን መሥዋዕት እዚያው እነሱ እያዩን ብናቀርብ አይወግሩንም? |
ስለዚህ ወደ ምድረ በዳው የሦስት ቀን መንገድ እንጓዛለን፤ በዚያም አምላካችን ይሖዋ ባለን መሠረት ለእሱ መሥዋዕት እናቀርባለን።” |
በዚህ ጊዜ ፈርዖን እንዲህ አለ፦ “በምድረ በዳ ለአምላካችሁ ለይሖዋ መሥዋዕት እንድታቀርቡ እለቃችኋለሁ። ብቻ ብዙ ርቃችሁ መሄድ የለባችሁም። ስለ እኔም ለምኑልኝ።” |
ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ አሁን ከአንተ ተለይቼ እወጣለሁ፤ ይሖዋንም እለምናለሁ፤ ተናካሽ ዝንቦቹም በነገው ዕለት ከፈርዖን፣ ከአገልጋዮቹና ከሕዝቡ ይወገዳሉ። ሆኖም ፈርዖን፣ ሕዝቡ ለይሖዋ መሥዋዕት ለማቅረብ እንዳይሄድ በመከልከል ሊያታልለን መሞከሩን ይተው።” |
ከዚያም ሙሴ ከፈርዖን ፊት ወጥቶ በመሄድ ይሖዋን ለመነ። |
ይሖዋም ሙሴ እንዳለው አደረገ፤ ተናካሽ ዝንቦቹም ከፈርዖን፣ ከአገልጋዮቹና ከሕዝቡ ተወገዱ። አንድም ዝንብ አልቀረም። |
ሆኖም ፈርዖን እንደገና ልቡን አደነደነ፤ ሕዝቡንም ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም። |
ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ |
“አሮንንና ወንዶች ልጆቹን እንዲሁም እስራኤላውያንን በሙሉ እንዲህ በላቸው፦ ‘ይሖዋ ያዘዘው ይህ ነው፦ |
“‘“ከእስራኤል ቤት የሆነ ማንኛውም ሰው በሬ ወይም የበግ ጠቦት አሊያም ፍየል በሰፈሩ ውስጥ ወይም ከሰፈሩ ውጭ ቢያርድና |
በይሖዋ የማደሪያ ድንኳን ፊት ለይሖዋ መባ አድርጎ ለማቅረብ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ባያመጣ ያ ሰው በደም ዕዳ ይጠየቃል። ሰውየው ደም አፍስሷል፤ በመሆኑም ይህ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት። |
ይህም እስራኤላውያን በሜዳ ላይ እየሠዉ ያሉትን መሥዋዕት ወደ ይሖዋ፣ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያና ወደ ካህኑ እንዲያመጡ ነው። እነዚህንም ለይሖዋ የኅብረት መሥዋዕቶች አድርገው መሠዋት አለባቸው። |
ካህኑም ደሙን በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ባለው የይሖዋ መሠዊያ ላይ ይረጨዋል፤ ስቡንም ለይሖዋ ደስ የሚያሰኝ መዓዛ አድርጎ ያጨሰዋል። |
ከእንግዲህ ወዲህ፣ አብረዋቸው ምንዝር ለሚፈጽሙት ፍየል የሚመስሉ አጋንንት አይሠዉም። ይህም በመጪዎቹ ትውልዶቻችሁ ሁሉ ለእናንተ ዘላቂ ደንብ ሆኖ ያገለግላል።”’ |
“እንዲህም በላቸው፦ ‘የሚቃጠል መባ ወይም መሥዋዕት የሚያቀርብ ከእስራኤል ቤት የሆነ ማንኛውም ሰው ወይም በመካከላችሁ የሚኖር ማንኛውም የባዕድ አገር ሰው |
ይህን ለይሖዋ ለማቅረብ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ባያመጣ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት። |
“‘ከእስራኤል ቤት የሆነ ማንኛውም ሰው ወይም በመካከላችሁ የሚኖር የትኛውም የባዕድ አገር ሰው ምንም ዓይነት ደም ቢበላ፣ ደም በሚበላው ሰው ላይ በእርግጥ ፊቴን አጠቁርበታለሁ፤ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። |
ምክንያቱም የሥጋ ሕይወት ያለው በደሙ ውስጥ ነው፤ ለራሳችሁም ማስተሰረያ እንዲሆን እኔ ራሴ ደሙን ለእናንተ ስል ለመሠዊያው ሰጥቼዋለሁ፤ ምክንያቱም በውስጡ ባለው ሕይወት አማካኝነት የሚያስተሰርየው ደሙ ነው። |
እስራኤላውያንን “ማንኛችሁም ደም መብላት የለባችሁም፤ እንዲሁም በመካከላችሁ የሚኖር ማንኛውም የባዕድ አገር ሰው ደም አይብላ” ያልኳቸው ለዚህ ነው። |
“‘አንድ እስራኤላዊ ወይም በመካከላችሁ የሚኖር አንድ የባዕድ አገር ሰው ለመብልነት የተፈቀደ እንስሳ ወይም ወፍ አድኖ ቢይዝ ደሙን ያፍሰው፤ አፈርም ያልብሰው። |
የሥጋ ሁሉ ሕይወት ደሙ ነውና፤ ምክንያቱም በውስጡ ሕይወት አለ። በዚህም የተነሳ እስራኤላውያንን እንዲህ አልኳቸው፦ “የሥጋ ሁሉ ሕይወት ደሙ ስለሆነ የማንኛውንም ሥጋ ደም አትብሉ። ደም የሚበላ ማንኛውም ሰው ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረጋል።” |
የአገሬው ተወላጅም ይሁን የባዕድ አገር ሰው፣ ማንኛውም ሰው ሞቶ የተገኘን ወይም አውሬ የቦጫጨቀውን እንስሳ ሥጋ ቢበላ ልብሶቹን ይጠብ፤ በውኃም ይታጠብ፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሁን፤ ከዚያም ንጹሕ ይሆናል። |
ሆኖም ልብሶቹን ካላጠበና ሰውነቱን ካልታጠበ በሠራው ጥፋት ይጠየቅበታል።’” |
በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ |
“ለመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱስ ልትሆኑ ይገባል። |
“‘ከእናንተ እያንዳንዱ እናቱንና አባቱን ያክብር፤ ሰንበቶቼንም ይጠብቅ። እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ። |
ከንቱ ወደሆኑ አማልክት ዞር አትበሉ፤ ወይም ከቀለጠ ብረት ለራሳችሁ አማልክትን አትሥሩ። እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ። |
“‘ለይሖዋ የኅብረት መሥዋዕት የምታቀርቡ ከሆነ ተቀባይነት በሚያስገኝላችሁ መንገድ አቅርቡት። |
መሥዋዕቱም በዚያው ባቀረባችሁበት ዕለትና በቀጣዩ ቀን መበላት ይኖርበታል፤ ተርፎ እስከ ሦስተኛው ቀን የቆየ ካለ ግን በእሳት መቃጠል አለበት። |
ይሁንና ከተረፈው ላይ በሦስተኛው ቀን ከተበላ ተቀባይነት የሌለው አስጸያፊ ነገር ይሆናል። |
የበላውም ሰው የይሖዋን ቅዱስ ነገር ስላረከሰ በጥፋቱ ይጠየቃል፤ ያም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት። |
“‘የምድራችሁን አዝመራ በምትሰበስቡበት ጊዜ በእርሻችሁ ዳር ዳር ያለውን ሙልጭ አድርጋችሁ አትጨዱት፤ የእርሻችሁን ቃርሚያም አትልቀሙ። |
በተጨማሪም በወይን እርሻህ ላይ የተረፈውን አትሰብስብ፤ በወይን እርሻህ ላይ የወዳደቀውን የወይን ፍሬ አትልቀም። እነዚህን ለድሃውና ለባዕድ አገሩ ሰው ተውለት። እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ። |
“‘አትስረቁ፤ አታታሉ፤ አንዳችሁ በሌላው ላይ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት አትፈጽሙ። |
በስሜ በሐሰት አትማሉ፤ በዚህም የአምላካችሁን ስም አታርክሱ። እኔ ይሖዋ ነኝ። |
ባልንጀራህን አታጭበርብር፤ አትዝረፈውም። የቅጥር ሠራተኛውን ደሞዝ ሳትከፍል አታሳድር። |
“‘መስማት የተሳነውን አትርገም ወይም በዓይነ ስውሩ ፊት እንቅፋት አታስቀምጥ፤ አምላክህን ፍራ። እኔ ይሖዋ ነኝ። |
“‘ፍርድ አታዛቡ። ለድሃው አታዳላ ወይም ባለጸጋውን ከሌሎች አስበልጠህ አትመልከት። ለባልንጀራህ ፍትሐዊ ፍርድ ፍረድ። |
“‘በሕዝብህ መካከል እየዞርክ ስም አታጥፋ። የባልንጀራህን ሕይወት ለማጥፋት አትነሳ። እኔ ይሖዋ ነኝ። |
“‘ወንድምህን በልብህ አትጥላው። የባልንጀራህ ኃጢአት ተባባሪ እንዳትሆን ተግሣጽ በሚያስፈልገው ጊዜ ሁሉ ገሥጸው። |
“‘የሕዝብህን ልጆች አትበቀል፤ በእነሱም ላይ ቂም አትያዝ፤ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ። እኔ ይሖዋ ነኝ። |
“‘የሚከተሉትን ደንቦቼን ጠብቁ፦ ሁለት ዓይነት እንስሳትን አታዳቅል። በእርሻህ ላይ ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ፤ ከሁለት የተለያዩ የክር ዓይነቶች የተሠራ ልብስ አትልበስ። |
“‘አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር ቢተኛና ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት ቢፈጽም፣ ሴቲቱ ደግሞ ለሌላ ወንድ የታጨች ሆኖም ገና ያልተዋጀች ወይም ነፃ ያልወጣች ባሪያ ብትሆን የቅጣት እርምጃ መወሰድ አለበት። ይሁንና ይህች ሴት ገና ነፃ ስላልወጣች መገደል የለባቸውም። |
ሰውየው የበደል መባውን ይኸውም ለበደል መባ የሚሆነውን አውራ በግ ወደ ይሖዋ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ያምጣ። |
ካህኑም ሰውየው ለሠራው ኃጢአት የበደል መባ እንዲሆን በቀረበው አውራ በግ በይሖዋ ፊት ያስተሰርይለታል፤ የሠራውም ኃጢአት ይቅር ይባልለታል። |
“‘እናንተም ወደ ምድሪቱ ብትገቡና ለምግብ የሚሆን ዛፍ ብትተክሉ ፍሬውን ርኩስና የተከለከለ አድርጋችሁ ቁጠሩት። ለሦስት ዓመት ከእሱ መብላት የለባችሁም። ፍሬው መበላት የለበትም። |
በአራተኛው ዓመት ግን ፍሬው በሙሉ በይሖዋ ፊት የምትደሰቱበት ቅዱስ ነገር ይሆናል። |
ከዚያም በአምስተኛው ዓመት ፍሬውን መብላት ትችላላችሁ፤ ይህን ካደረጋችሁ ምርታችሁ ይበዛላችኋል። እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ። |
“‘ደም ያለበትን ማንኛውንም ነገር አትብሉ። “‘አታስጠንቁሉ ወይም አስማት አትሥሩ። |
“‘ጆሮ ግንዳችሁ አካባቢ ያለውን ፀጉር አትላጩ ወይም የጢማችሁን ዳር ዳር አትላጩ። |
“‘ለሞተ ሰው ብላችሁ አካላችሁን አትተልትሉ ወይም ሰውነታችሁን አትነቀሱ። እኔ ይሖዋ ነኝ። |
“‘ምድሪቱ ዝሙት እንዳትፈጽምና ልቅ በሆነ ምግባር እንዳትሞላ ሴት ልጅህን ዝሙት አዳሪ በማድረግ አታዋርዳት። |
“‘ሰንበቶቼን ጠብቁ፤ ለመቅደሴ አክብሮት ይኑራችሁ። እኔ ይሖዋ ነኝ። |
“‘ወደ መናፍስት ጠሪዎች አትሂዱ፤ ጠንቋዮችንም አትጠይቁ፤ እንዲህ ካደረጋችሁ በእነሱ ትረክሳላችሁ። እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ። |
“‘በሸበተው ሰው ፊት ተነስ፤ አረጋዊውንም አክብር፤ አምላክህን ፍራ። እኔ ይሖዋ ነኝ። |
“‘በምድራችሁ አብሯችሁ የሚኖር የባዕድ አገር ሰው ካለ አትበድሉት። |
አብሯችሁ የሚኖረውን የባዕድ አገር ሰው እንደ አገራችሁ ተወላጅ አድርጋችሁ ተመልከቱት፤ እንደ ራሳችሁ አድርጋችሁም ውደዱት፤ ምክንያቱም እናንተም በግብፅ ምድር ሳላችሁ የባዕድ አገር ሰው ነበራችሁ። እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ። |
“‘ርዝመትን፣ ክብደትን ወይም መጠንን ስትለኩ በተጭበረበረ መለኪያ አትጠቀሙ። |
ትክክለኛ ሚዛን፣ ትክክለኛ የሚዛን ድንጋዮች፣ ትክክለኛ የደረቅ ነገር መስፈሪያና ትክክለኛ የፈሳሽ ነገር መለኪያ ሊኖራችሁ ይገባል። ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ። |
ስለሆነም ደንቦቼን ሁሉና ድንጋጌዎቼን በሙሉ ጠብቁ፤ እንዲሁም ፈጽሟቸው። እኔ ይሖዋ ነኝ።’” |
ከዚያም ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ |
“እስራኤላውያንን እንዲህ በሏቸው፦ ‘በምድር ላይ ካሉ ሕያዋን ፍጥረታት መካከል እነዚህን መብላት ትችላላችሁ፦ |
ሰኮናው የተሰነጠቀውንና ስንጥቁም ሙሉ በሙሉ የተከፈለውን እንዲሁም የሚያመሰኳውን ማንኛውንም እንስሳ መብላት ትችላላችሁ። |
“‘ሆኖም የሚያመሰኩትን ወይም ሰኮናቸው የተሰነጠቀውን እነዚህን እንስሳት መብላት የለባችሁም፦ ግመል የሚያመሰኳ ቢሆንም ሰኮናው የተሰነጠቀ አይደለም። ለእናንተ ርኩስ ነው። |
ሽኮኮም መብላት የለባችሁም፤ ምክንያቱም የሚያመሰኳ ቢሆንም ሰኮናው የተሰነጠቀ አይደለም። ለእናንተ ርኩስ ነው። |
ጥንቸልም ብትሆን መብላት የለባችሁም፤ ምክንያቱም የምታመሰኳ ብትሆንም ሰኮናዋ የተሰነጠቀ አይደለም። ለእናንተ ርኩስ ነች። |
አሳማም መብላት የለባችሁም፤ ሰኮናው የተሰነጠቀና ስንጥቁ ሙሉ በሙሉ የተከፈለ ቢሆንም እንኳ አያመሰኳም። ለእናንተ ርኩስ ነው። |
የእነዚህን እንስሳት ሥጋ አትብሉ ወይም በድናቸውን አትንኩ። እነዚህ ለእናንተ ርኩስ ናቸው። |
“‘በውኃዎች ውስጥ ካሉት መካከል እነዚህን መብላት ትችላላችሁ፦ በባሕርም ሆነ በወንዞች፣ በውኃዎች ውስጥ ካሉት መካከል ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን ሁሉ መብላት ትችላላችሁ። |
በውኃዎች ውስጥ ካሉ የሚርመሰመሱ ፍጥረታትና ሌሎች ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት ሁሉ መካከል በባሕርና በወንዞች ውስጥ የሚገኙ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ሁሉ ግን ለእናንተ አስጸያፊ ናቸው። |
አዎ፣ እነዚህን ልትጸየፏቸው ይገባል፤ ሥጋቸውን ፈጽሞ አትብሉ፤ በድናቸውንም ተጸየፉት። |
በውኃዎች ውስጥ የሚኖሩ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ሁሉ ለእናንተ አስጸያፊ ናቸው። |
“‘ልትጸየፏቸው የሚገቡ በራሪ ፍጥረታት እነዚህ ናቸው፤ አስጸያፊ በመሆናቸው መበላት የለባቸውም፦ ንስር፣ ዓሣ በል ጭላት፣ ጥቁር ጥምብ አንሳ፣ |
ቀይ ጭልፊት፣ ማንኛውም ዓይነት ጥቁር ጭልፊት፣ |
Subsets and Splits
No community queries yet
The top public SQL queries from the community will appear here once available.