text
stringlengths
4
267
“የወንድምህ በሬ ወይም በግ ጠፍቶ ሲባዝን ካየህ እንዳላየ ሆነህ አትለፍ። ከዚህ ይልቅ ወደ ወንድምህ መልሰህ ልትወስደው ይገባል።
ሆኖም ወንድምህ በአቅራቢያህ የማይኖር ወይም እሱን የማታውቀው ከሆነ እንስሳውን ወደ ቤትህ አምጣው፤ ወንድምህ እሱን ፈልጎ እስኪመጣም ድረስ አንተ ጋ ይቆይ። ከዚያም መልስለት።
አህያውንም ሆነ ልብሱን ወይም ወንድምህ ጠፍቶበት ያገኘኸውን ማንኛውንም ነገር በተመለከተ እንዲሁ ማድረግ ይኖርብሃል። አይተህ ዝም ብለህ ማለፍ የለብህም።
“የወንድምህ አህያ ወይም በሬ መንገድ ላይ ወድቆ ብታይ እንዳላየ ሆነህ አትለፍ። ከዚህ ይልቅ እንስሳው ተነስቶ እንዲቆም በማድረግ ሰውየውን ልትረዳው ይገባል።
“ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ፤ ወንድ ደግሞ የሴት ልብስ አይልበስ። ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ ማንኛውም ሰው በአምላክህ በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ነው።
“መንገድ ላይ ስትሄድ ጫጩቶች ወይም እንቁላሎች ያሉበት የወፍ ጎጆ፣ ዛፍ ላይ ወይም መሬት ላይ ብታገኝና እናትየው ጫጩቶቹን ወይም እንቁላሎቹን ታቅፋ ቢሆን እናትየውን ከጫጩቶቿ ጋር አብረህ አትውሰድ።
እናትየውን ልቀቃት፤ ጫጩቶቹን ግን መውሰድ ትችላለህ። ይህን የምታደርገው መልካም እንዲሆንልህና ዕድሜህ እንዲረዝም ነው።
“አዲስ ቤት በምትሠራበት ጊዜ አንድ ሰው ከጣሪያህ ላይ ወድቆ በቤትህ ላይ የደም ዕዳ እንዳታመጣ በጣሪያህ ዙሪያ መከታ ሥራ።
“በወይን እርሻህ ላይ ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ። እንዲህ ካደረግክ ከዘራኸው ዘር የሚገኘው ምርትም ሆነ የወይን እርሻህ ምርት በሙሉ በቤተ መቅደሱ ተቀባይነት ያጣል።
“በሬና አህያ አንድ ላይ ጠምደህ አትረስ።
“ከሱፍና ከበፍታ ተቀላቅሎ የተሠራ ልብስ አትልበስ።
“በምትለብሰው ልብስ ላይ በአራቱም ማዕዘን ዘርፍ አድርግ።
“አንድ ሰው ሚስት አግብቶ ከእሷ ጋር ግንኙነት ከፈጸመ በኋላ ቢጠላት፣
መጥፎ ምግባር እንዳላት አድርጎ ቢከሳትና ‘ይህችን ሴት አግብቼ ነበር፤ ሆኖም ከእሷ ጋር ግንኙነት ስፈጽም የድንግልናዋን ማስረጃ አላገኘሁም’ በማለት መጥፎ ስም ቢሰጣት
የልጅቷ አባትና እናት ድንግልናዋን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይዘው በከተማዋ በር ወደሚገኙት ሽማግሌዎች ይምጡ።
የልጅቷም አባት ሽማግሌዎቹን እንዲህ ይበላቸው፦ ‘ልጄን ለዚህ ሰው ድሬለት ነበር፤ እሱ ግን ጠላት፤
እንዲሁም “ልጅህን ከነድንግልናዋ አላገኘኋትም” በማለት መጥፎ ምግባር እንዳላት አድርጎ እየከሰሳት ነው። እንግዲህ የልጄ የድንግልና ማስረጃ ይኸውላችሁ።’ እነሱም ልብሱን በከተማዋ ሽማግሌዎች ፊት ይዘርጉት።
የዚያች ከተማ ሽማግሌዎችም ሰውየውን ወስደው ይቅጡት።
እነሱም 100 የብር ሰቅል ያስከፍሉታል፤ ከዚያም ገንዘቡን ለልጅቷ አባት ይስጡት፤ ምክንያቱም ይህ ሰው የአንዲትን እስራኤላዊት ድንግል ስም አጥፍቷል፤ እሷም ሚስቱ ሆና ትኖራለች። በሕይወት ዘመኑም ሁሉ እንዲፈታት አይፈቀድለትም።
“ሆኖም ክሱ እውነት ከሆነና ልጅቷ ድንግል እንደነበረች የሚያረጋግጥ ማስረጃ ካልተገኘ
ልጅቷን ወደ አባቷ ቤት ደጃፍ ያውጧት፤ በአባቷ ቤት የፆታ ብልግና በመፈጸም በእስራኤል ውስጥ አስነዋሪ ድርጊት ስለፈጸመች የከተማዋ ሰዎች እስክትሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሯት። በዚህ መንገድ ክፉ የሆነውን ከመካከልህ አስወግድ።
“አንድ ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ተኝቶ ቢገኝ ከሴትየዋ ጋር የተኛው ሰውም ሆነ ሴትየዋ ሁለቱም ይገደሉ። በዚህ መንገድ ክፉ የሆነውን ከእስራኤል መካከል አስወግድ።
“አንድ ሰው ለሌላ ሰው የታጨችን አንዲት ድንግል ከተማ ውስጥ አግኝቶ ከእሷ ጋር ቢተኛ
ልጅቷ በከተማው ውስጥ ስላልጮኸች፣ ሰውየው ደግሞ የባልንጀራውን ሚስት ስላዋረደ ሁለቱንም ወደ ከተማዋ በር አውጥታችሁ እስኪሞቱ ድረስ በድንጋይ ውገሯቸው። በዚህ መንገድ ክፉ የሆነውን ከመካከልህ አስወግድ።
“ይሁንና ሰውየው የታጨችውን ልጃገረድ ያገኛት ሜዳ ላይ ቢሆንና በጉልበት አስገድዶ አብሯት ቢተኛ እሱ ብቻ ይገደል፤
በልጅቷ ላይ ምንም አታድርግ። ልጅቷ ሞት የሚገባው ኃጢአት አልሠራችም። ይህ ጉዳይ በባልንጀራው ላይ ጥቃት ሰንዝሮ ከሚገድል ሰው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው።
ምክንያቱም ሰውየው ልጅቷን ያገኛት ሜዳ ላይ ሲሆን የታጨችው ልጅ ብትጮኽም እንኳ ማንም አልደረሰላትም።
“አንድ ሰው ያልታጨችን አንዲት ድንግል አግኝቶ ቢይዛትና አብሯት ቢተኛ፣ በኋላም ቢጋለጡ
ሰውየው ለልጅቷ አባት 50 የብር ሰቅል ይስጥ፤ እሷም ሚስቱ ትሆናለች። ስላዋረዳትም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እንዲፈታት አይፈቀድለትም።
“ማንም ሰው አባቱን እንዳያዋርድ የአባቱን ሚስት አያግባ።
“በየሰባት ዓመቱ መጨረሻ የሌሎችን ዕዳ መሰረዝ ይኖርብሃል።
ዕዳ የሚሰረዘው በሚከተለው መንገድ ነው፦ እያንዳንዱ አበዳሪ ባልንጀራው ያለበትን ዕዳ ይሰርዝለታል። ከባልንጀራው ወይም ከወንድሙ ክፍያ መጠየቅ የለበትም፤ ምክንያቱም ለይሖዋ ሲባል ዕዳ እንዲሰረዝ ይታወጃል።
ከባዕድ አገር ሰው ክፍያ መጠየቅ ትችላለህ፤ ወንድምህ ለአንተ መመለስ ያለበትን ማንኛውንም ነገር ግን ተውለት።
ይሁንና አምላክህ ይሖዋ ርስት አድርገህ እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር ላይ ይሖዋ ስለሚባርክህ ከእናንተ መካከል ማንም ድሃ አይሆንም፤
ይህ የሚሆነው ግን የአምላክህን የይሖዋን ቃል በትኩረት የምትሰማና እኔ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዛት በሙሉ በጥንቃቄ የምትፈጽም ከሆነ ነው።
አምላክህ ይሖዋ በገባልህ ቃል መሠረት ይባርክሃልና፤ አንተም ለብዙ ብሔራት ታበድራለህ እንጂ አትበደርም፤ ብዙ ብሔራትን ትገዛለህ እንጂ አንተን አይገዙህም።
“ከወንድሞችህ መካከል አንዱ አምላክህ ይሖዋ በሚሰጥህ ምድር ከሚገኙት ከተሞች በአንዱ ውስጥ ድሃ ቢሆን በድሃው ወንድምህ ላይ ልብህ አይጨክንበት ወይም እጅህን አትጠፍበት።
ከዚህ ይልቅ በልግስና እጅህን ዘርጋለት፤ በተቻለ መጠን፣ የሚያስፈልገውን ወይም የጎደለውን ማንኛውንም ነገር አበድረው።
‘ዕዳ የሚሰረዝበት ሰባተኛው ዓመት ቀርቧል’ የሚል ክፉ ሐሳብ በልብህ አድሮ ለድሃው ወንድምህ ከመለገስ ወደኋላ እንዳትልና ምንም ሳትሰጠው እንዳትቀር ተጠንቀቅ። እሱ በአንተ ላይ ቅር ተሰኝቶ ወደ ይሖዋ ቢጮኽ ኃጢአት ይሆንብሃል።
በልግስና ስጠው፤ ስትሰጠው ልብህ ቅር እያለው መሆን የለበትም፤ ምክንያቱም አምላክህ ይሖዋ በሥራህ ሁሉና በምታከናውነው በማንኛውም ነገር የሚባርክህ በዚህ የተነሳ ነው።
መቼም ቢሆን ከምድሪቱ ላይ ድሆች አይጠፉምና። ‘በምድርህ ላይ ለሚኖር ጎስቋላና ድሃ ወንድምህ በልግስና እጅህን ዘርጋለት’ በማለት ያዘዝኩህ ለዚህ ነው።
“ከወንድሞችህ አንዱ ይኸውም አንድ ዕብራዊ ወይም አንዲት ዕብራዊ፣ ለአንተ ቢሸጥና ስድስት ዓመት ቢያገለግልህ በሰባተኛው ዓመት ነፃ አውጣው።
ነፃ የምታወጣው ከሆነ ባዶ እጁን አትስደደው።
ከመንጋህና ከአውድማህ እንዲሁም ከዘይትና ከወይን መጭመቂያህ በልግስና ስጠው። አምላክህ ይሖዋ በባረከህ መጠን ስጠው።
አንተም በግብፅ ምድር ባሪያ እንደነበርክና አምላክህ ይሖዋ እንደተቤዠህ አስታውስ። እኔ ዛሬ ይህን እንድታደርግ የማዝህ ለዚህ ነው።
“ሆኖም ይህ ሰው ከአንተ ጋር በነበረበት ጊዜ ደስተኛ ስለነበር አንተንና ቤተሰብህን በመውደድ ‘ፈጽሞ ከአንተ አልለይም!’ ቢልህ
ጆሮውን በር ላይ አስደግፈህ በወስፌ ብሳው፤ እሱም ዕድሜ ልኩን የአንተ ባሪያ ይሆናል። ሴት ባሪያህንም በተመለከተ እንደዚሁ አድርግ።
ባሪያህን ነፃ አድርጎ ማሰናበት ሊከብድህ አይገባም፤ ምክንያቱም እሱ በስድስት ዓመት ውስጥ የሰጠህ አገልግሎት በቅጥር ሠራተኛ ደሞዝ ቢሰላ እጥፍ ዋጋ ያስወጣህ ነበር፤ ደግሞም አምላክህ ይሖዋ በምትሠራው ነገር ሁሉ ባርኮሃል።
“ከከብትህና ከመንጋህ መካከል በኩር የሆነውን ወንድ ሁሉ ለአምላክህ ለይሖዋ ቀድሰው። በከብትህ በኩር ምንም ሥራ አትሥራበት፤ የመንጋህንም በኩር አትሸልት።
አንተም ሆንክ ቤተሰብህ ይሖዋ በሚመርጠው ስፍራ በየዓመቱ በአምላክህ በይሖዋ ፊት ብሉት።
ይሁንና እንስሳው እንከን ካለበት ይኸውም አንካሳ ወይም ዕውር ከሆነ አሊያም ሌላ ዓይነት ከባድ ጉድለት ካለበት ለአምላክህ ለይሖዋ መሥዋዕት አድርገህ አታቅርበው።
በከተሞችህ ውስጥ ብላው፤ እንደ ሜዳ ፍየል ወይም እንደ ርኤም ሁሉ ንጹሕ ያልሆነውም ሆነ ንጹሕ የሆነው ሰው ሊበላው ይችላል።
ሆኖም ደሙን አትብላ፤ እንደ ውኃ መሬት ላይ አፍስሰው።
“ሰማያት ሆይ፣ ጆሯችሁን ስጡኝ፤ እኔም እናገራለሁ፤ምድርም የአፌን ቃል ትስማ።
ትምህርቴ እንደ ዝናብ ይወርዳል፤ካፊያ ሣር ላይ እንደሚወርድ፣የሚያረሰርስ ዝናብም ተክልን እንደሚያጠጣ፣ቃሌም እንደ ጤዛ ይንጠባጠባል።
የይሖዋን ስም አውጃለሁና። ስለ አምላካችን ታላቅነት ተናገሩ!
እሱ ዓለት፣ የሚያደርገውም ነገር ሁሉ ፍጹም ነው፤መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸውና። እሱ ፈጽሞ ፍትሕን የማያጓድል ታማኝ አምላክ ነው፤ጻድቅና ትክክለኛ ነው።
ምግባረ ብልሹ የሆኑት እነሱ ናቸው። ልጆቹ አይደሉም፤ ጉድለቱ የራሳቸው ነው። ጠማማና ወልጋዳ ትውልድ ናቸው!
እናንተ ሞኞችና ጥበብ የጎደላችሁ ሰዎች ሆይ፣በይሖዋ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ታደርጋላችሁ? ወደ ሕልውና ያመጣህ አባትህ እሱ አይደለም?የሠራህና አጽንቶ ያቆመህስ እሱ አይደለም?
የጥንቱን ዘመን አስታውስ፤ያለፉት ትውልዶች የኖሩባቸውን ዓመታት መለስ ብለህ አስብ። አባትህን ጠይቅ፤ ሊነግርህ ይችላል፤ሽማግሌዎችህንም ጠይቅ፤ ይነግሩሃል።
ልዑሉ ለብሔራት ርስታቸውን ሲሰጥ፣የአዳምን ልጆች አንዱን ከሌላው ሲለያይ፣በእስራኤል ልጆች ቁጥር ልክየሕዝቦችን ወሰን ደነገገ።
የይሖዋ ሕዝብ ድርሻው ነው፤ያዕቆብ ርስቱ ነው።
እሱን ምድረ በዳ በሆነ ምድር፣ነፋስ በሚያፏጭበት ጭው ያለ በረሃ አገኘው። ሊጠብቀውም ዙሪያውን ከበበው፤ ተንከባከበው፤እንደ ዓይኑም ብሌን ጠበቀው።
ንስር ጎጆዋን እንደምትነቀንቅናከጫጩቶቿ በላይ እንደምታንዣብብ፣ክንፎቿን ዘርግታ እንደምትይዛቸው፣በላባዎቿም እንደምትሸከማቸው ሁሉ
ይሖዋ ብቻውን መራው፤ከእሱም ጋር ምንም ባዕድ አምላክ አልነበረም።
በምድር ላይ በሚገኙ ከፍ ያሉ ቦታዎች እንዲሄድ አደረገው፤ስለሆነም የእርሻውን ምርት በላ። ከዓለት ማር አበላው፤ከባልጩትም ዘይት መገበው፤
የላሞቹን ቅቤና የመንጋውን ወተትምርጥ ከሆነው በግ ጋር ሰጠው፤የባሳንን አውራ በጎችና አውራ ፍየሎችከምርጥ ስንዴ ጋር ሰጠው፤አንተም ከወይን ፍሬው ደም የወይን ጠጅ ጠጣህ።
የሹሩን ሲወፍር በዓመፀኝነት ተራገጠ። ሰባህ፤ ፈረጠምክ፤ ደለብክ። ስለሆነም የሠራውን አምላክ ተወ፤አዳኝ የሆነለትን ዓለት ናቀ።
በባዕዳን አማልክት አስቆጡት፤በአስጸያፊ ነገሮችም አሳዘኑት።
ለአምላክ ሳይሆን ለአጋንንት፣ለማያውቋቸው አማልክት፣በቅርቡ ለተነሱ ለአዲሶች፣አባቶቻችሁ ለማያውቋቸው አማልክት ይሠዉ ነበር።
አባት የሆነህን ዓለት ረሳኸው፤የወለደህንም አምላክ አላስታወስክም።
ይሖዋ ይህን ሲያይ ተዋቸው፤ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ አሳዝነውት ነበርና።
ስለዚህ እንዲህ አለ፦ ‘ፊቴን ከእነሱ እሰውራለሁ፤ምን እንደሚሆኑም አያለሁ። ምክንያቱም እነሱ ጠማማ ትውልድ ናቸው፤ታማኝነት የሚባል ነገር የማያውቁ ልጆች ናቸው።
እነሱ አምላክ ባልሆነው አስቆጡኝ፤ከንቱ በሆኑ ጣዖቶቻቸው አሳዘኑኝ። በመሆኑም እኔ ሕዝብ ባልሆነው አስቀናቸዋለሁ፤ሞኝ በሆነ ብሔር አበሳጫቸዋለሁ።
ምክንያቱም ቁጣዬ እሳት አቀጣጥሏል፤እሱም እስከ መቃብር ጥልቀት ድረስ ዘልቆ ይነድዳል፤ምድርንና ምርቷን ይበላል፤የተራሮችንም መሠረት ያቃጥላል።
መከራቸውን አበዛዋለሁ፤ቀስቶቼን በእነሱ ላይ እጨርሳለሁ።
በረሃብ ይዳከማሉ፤በሚያቃጥል ትኩሳትና በመራራ ጥፋት ይበላሉ። የአራዊትን ጥርስ፣በምድር ላይ የሚሳቡ እንስሳትንም መርዝ እልክባቸዋለሁ።
ወጣቱንም ሆነ ልጃገረዲቱን፣ጨቅላውንም ሆነ ሽማግሌውን፣በውጭ፣ ሰይፍ ለሐዘን ይዳርጋቸዋል፤በቤት ውስጥ ደግሞ ሽብር አለ።
እኔም “እበትናቸዋለሁ፤መታሰቢያቸውም ከሰዎች ዘንድ እንዲጠፋ አደርጋለሁ” ባልኩ ነበር፤
ነገር ግን የጠላትን ምላሽ ፈራሁ፤ምክንያቱም ባላጋራዎቼ በተሳሳተ መንገድ ሊረዱት ይችላሉ። “ክንዳችን የበላይ ሆነ፤ይህን ሁሉ ያደረገው ይሖዋ አይደለም” ሊሉ ይችላሉ።
እነሱ ማመዛዘን የጎደለው ብሔር ናቸው፤በመካከላቸውም ማስተዋል የሚባል ነገር የለም።
ምነው ጥበበኛ በሆኑ ኖሮ! ይህን ሁሉ ያሰላስሉ ነበር። የሚደርስባቸውንም ያስቡ ነበር።
ዓለታቸው ካልሸጣቸውናይሖዋ ለምርኮ ካልዳረጋቸው በስተቀር አንድ ሰው 1,000 ሊያሳድድ፣ሁለት ሰው ደግሞ 10,000 ሊያባርር እንዴት ይችላል?
የእነሱ ዓለት እንደ እኛ ዓለት አይደለም፤ጠላቶቻችንም እንኳ ይህን ተረድተዋል።
ወይናቸው ከሰዶም የወይን ተክልናከገሞራ የእርሻ ቦታ የተገኘ ነው። የወይን ፍሬያቸው መርዛማ የወይን ፍሬ ነው፤ዘለላቸው መራራ ነው።
ወይናቸው የእባቦች መርዝ፣የጉበናም ምሕረት የለሽ መርዝ ነው።
ይህ እኔ ጋ ያለ፣በግምጃ ቤቴ ውስጥ ማኅተም ታትሞበት የተቀመጠ አይደለም?
በቀልም ሆነ ቅጣት የእኔ ነው፤አስቀድሞ የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ እግራቸው ይከዳቸዋል፤የሚጠፉበት ቀን ቀርቧልና፤የሚጠብቃቸውም ነገር በፍጥነት ይመጣል።’
ይሖዋ ሕዝቡን ይዳኛል፤አገልጋዮቹ አቅም እንዳነሳቸው፣ረዳት የለሽና ደካማ የሆኑት ብቻ እንደቀሩ ሲያይለእነሱ ያዝንላቸዋል።
ከዚያም እንዲህ ይላል፦ ‘አማልክታቸው የት አሉ?መሸሸጊያ እንዲሆናቸው የተጠጉት ዓለትስ የት አለ?
የመሥዋዕቶቻቸውን ስብ ይበላ፣የመጠጥ መባዎቻቸውንም የወይን ጠጅ ይጠጣ የነበረው የት አለ? እስቲ ተነስተው ይርዷችሁ። እስቲ መሸሸጊያ ስፍራ ይሁኑላችሁ።
እንግዲህ እኔ እሱ እንደሆንኩ እዩ፤ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት የሉም። እኔ እገድላለሁ፤ እኔ ሕያው አደርጋለሁ። እኔ አቆስላለሁ፤ እኔው እፈውሳለሁ፤ከእጄም ማዳን የሚችል የለም።
እጄን ወደ ሰማይ አንስቼ፣“በዘላለማዊ ሕያውነቴ” ብዬ እምላለሁ፤
የሚያብረቀርቅ ሰይፌን ከሳልኩናእጄን ለፍርድ ካዘጋጀሁ፣ተቃዋሚዎቼን እበቀላለሁ፤የሚጠሉኝንም እቀጣለሁ።
በታረዱና በተማረኩ ሰዎች ደም፣በጠላት መሪዎች ራስ፣ቀስቶቼን በደም አሰክራለሁ፤ሰይፌም ሥጋ ይበላል።’
እናንተ ብሔራት ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ፤እሱ የአገልጋዮቹን ደም ይመልሳልና፤ተቃዋሚዎቹንም ይበቀላል፤ለሕዝቡም ምድር ያስተሰርይለታል።”
ሙሴም ከነዌ ልጅ ከሆሺአ ጋር መጥቶ የዚህን መዝሙር ቃላት በሙሉ ሕዝቡ እየሰማ ተናገረ።
ሙሴ እነዚህን ቃላት በሙሉ ለመላው እስራኤል ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ
እንዲህ አላቸው፦ “የዚህን ሕግ ቃላት በሙሉ በጥንቃቄ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዟቸው እኔ በዛሬው ዕለት እናንተን ለማስጠንቀቅ የምነግራችሁን ቃል ሁሉ ልብ በሉ።
ይህ ቃል ለእናንተ ሕይወታችሁ እንጂ እንዲሁ ባዶ ቃል አይደለም፤ ይህ ቃል ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትወርሷት ምድር ላይ ዕድሜያችሁን ሊያረዝምላችሁ ይችላል።”