text stringlengths 4 267 |
|---|
በዚህ ጊዜ ከሕዝቡ መካከል አንዱ “አባትህ እኮ ‘በዛሬው ዕለት እህል የሚቀምስ ሰው የተረገመ ይሁን!’ በማለት ሕዝቡን በጥብቅ አስምሏል። ሕዝቡ በጣም የተዳከመው ለዚህ ነው” አለው። |
ዮናታን ግን እንዲህ አለ፦ “አባቴ በምድሪቱ ላይ ከባድ ችግር አምጥቷል። እኔ ይህችን ማር በመቅመሴ ዓይኖቼ እንዴት እንደበሩ እስቲ ተመልከቱ። |
ሕዝቡ ከጠላቶቻቸው ከወሰዱት ምርኮ ዛሬ በነፃነት በልተው ቢሆን ኖሮ ምንኛ የተሻለ ይሆን ነበር! የተገደሉት ፍልስጤማውያንም ቁጥር ከዚህ እጅግ በበለጠ ነበር።” |
በዚያም ዕለት ፍልስጤማውያንን ከሚክማሽ አንስተው እስከ አይሎን ድረስ መቷቸው፤ ሕዝቡም በጣም ተዳከመ። |
ስለሆነም ሕዝቡ ምርኮውን በመስገብገብ ተሻምቶ ወሰደ፤ በጎችን፣ ከብቶችንና ጥጆችን ወስደው መሬት ላይ አረዷቸው፤ ሥጋውንም ከነደሙ በሉት። |
በመሆኑም ሳኦል “ይኸው ሕዝቡ ሥጋውን ከነደሙ በመብላት በይሖዋ ላይ ኃጢአት እየሠራ ነው” ተብሎ ተነገረው። እሱም በዚህ ጊዜ “እምነት እንደሌላችሁ የሚያሳይ ድርጊት ፈጽማችኋል። በሉ አሁኑኑ አንድ ትልቅ ድንጋይ አንከባላችሁ አምጡልኝ” አለ። |
አክሎም እንዲህ አለ፦ “በሕዝቡ መሃል ተበታትናችሁ እንዲህ በሏቸው፦ ‘እያንዳንዳችሁ በሬያችሁንና በጋችሁን አምጡ፤ በዚህም ስፍራ አርዳችሁ ብሉ። ሥጋውን ከነደሙ በመብላት በይሖዋ ላይ ኃጢአት አትሥሩ።’” በመሆኑም በዚያ ምሽት እያንዳንዱ ሰው በሬውን አምጥቶ በዚያ ስፍራ አረደው። |
ሳኦልም ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ። ይህ መሠዊያ ሳኦል ለይሖዋ የሠራው የመጀመሪያ መሠዊያ ነው። |
በኋላም ሳኦል “በሌሊት ፍልስጤማውያንን ተከታትለን በመውረድ እስኪነጋ ድረስ እንበዝብዛቸው። አንድም ሰው በሕይወት አናስተርፍም” አለ። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ “መልካም መስሎ የታየህን ማንኛውንም ነገር አድርግ” አሉት። ከዚያም ካህኑ “እዚሁ ወደ እውነተኛው አምላክ እንቅረብ” አለ። |
ሳኦልም “ፍልስጤማውያንን ተከትዬ ልውረድ? በእስራኤላውያን እጅ እንዲወድቁ ታደርጋለህ?” በማለት አምላክን ጠየቀ። አምላክ ግን በዚያ ዕለት አልመለሰለትም። |
በመሆኑም ሳኦል እንዲህ አለ፦ “እናንተ የሕዝቡ አለቆች ሁሉ ወደዚህ ቅረቡ፤ በዛሬው ዕለት ምን ኃጢአት እንደተፈጸመ አጣሩ። |
እስራኤልን ባዳነው ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ ይህን ኃጢአት የሠራው ልጄ ዮናታን ሆኖ ቢገኝ እንኳ መሞት አለበት።” ሆኖም ከሕዝቡ መካከል መልስ የሰጠው አንድም ሰው አልነበረም። |
ከዚያም እስራኤላውያንን በሙሉ “እናንተ በአንድ በኩል ትሆናላችሁ፤ እኔና ልጄ ዮናታን ደግሞ በሌላኛው በኩል እንሆናለን” አላቸው። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሳኦልን “መልካም መስሎ የታየህን ማንኛውንም ነገር አድርግ” አለው። |
ሳኦልም ይሖዋን “የእስራኤል አምላክ ሆይ፣ በቱሚም አማካኝነት መልስ ስጠን!” አለው። ከዚያም ዮናታንና ሳኦል ተመረጡ፤ ሕዝቡም ነፃ ሆነ። |
በዚህ ጊዜ ሳኦል “ከእኔና ከልጄ ከዮናታን ማን እንደሆነ ለመለየት ዕጣ ጣሉ” አለ። ዕጣውም በዮናታን ላይ ወጣ። |
ሳኦልም ዮናታንን “ንገረኝ፣ ያደረግከው ነገር ምንድን ነው?” አለው። በመሆኑም ዮናታን “በእጄ ይዤው በነበረው በትር ጫፍ ትንሽ ማር ቀምሻለሁ። እንግዲህ ይኸው ለመሞት ዝግጁ ነኝ!” በማለት መለሰለት። |
በዚህ ጊዜ ሳኦል “ዮናታን፣ እንደው አንተ ካልሞትክ አምላክ ይፍረድብኝ፤ የከፋም ነገር ያድርግብኝ” አለ። |
ሕዝቡ ግን ሳኦልን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ይህን ታላቅ ድል ያስገኘው ዮናታን መሞት ይገባዋል? ይሄማ ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው! ሕያው በሆነው በይሖዋ እንምላለን፣ ከራስ ፀጉሩ አንዷ እንኳ መሬት ላይ አትወድቅም፤ ምክንያቱም በዚህ ዕለት ይህን ያደረገው ከአምላክ ጋር ሆኖ ነው።” በዚህ መንገድ ሕዝቡ ዮናታንን ታደገው፤ እሱም ከሞት ዳነ። |
ሳኦልም ፍልስጤማውያንን ማሳደዱን ተወ፤ ፍልስጤማውያንም ወደ ክልላቸው ሄዱ። |
ሳኦልም በእስራኤል ላይ ንግሥናውን አጸና፤ በዙሪያው ከነበሩት ጠላቶቹ ማለትም ከሞዓባውያን፣ ከአሞናውያን፣ ከኤዶማውያን፣ ከጾባህ ነገሥታትና ከፍልስጤማውያን ጋር ተዋጋ፤ በሄደበትም ሁሉ ድል ያደርጋቸው ነበር። |
እንዲሁም በጀግንነት በመዋጋት አማሌቃውያንን ድል አደረገ፤ እስራኤላውያንንም ከዘራፊዎቻቸው እጅ አዳነ። |
የሳኦል ወንዶች ልጆች ዮናታን፣ ይሽዊ እና ሜልኪሳ ነበሩ። እሱም ሁለት ሴቶች ልጆች የነበሩት ሲሆን የትልቋ ስም ሜሮብ፣ የትንሿ ደግሞ ሜልኮል ነበር። |
የሳኦል ሚስት የአኪማዓስ ልጅ አኪኖዓም ነበረች። የሠራዊቱ አዛዥ ደግሞ አበኔር ሲሆን እሱም የሳኦል አጎት የኔር ልጅ ነበር። |
የሳኦል አባት ቂስ ነበር፤ የአበኔር አባት ኔር ደግሞ የአቢዔል ልጅ ነበር። |
በሳኦል ዘመን ሁሉ ከፍልስጤማውያን ጋር ከባድ ውጊያ ይደረግ ነበር። ሳኦልም ብርቱ ወይም ደፋር ሰው ሲያገኝ ወደ ሠራዊቱ እንዲቀላቀል ይመለምለው ነበር። |
በዚያም ዘመን ፍልስጤማውያን ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት ሠራዊታቸውን አሰባሰቡ። በመሆኑም አንኩስ ዳዊትን “መቼም አንተና ሰዎችህ አብራችሁኝ ወደ ጦርነት እንደምትወጡ ታውቃለህ” አለው። |
ዳዊትም አንኩስን “አገልጋይህ ምን እንደሚያደርግ አንተ በእርግጥ ታውቃለህ” አለው። ከዚያም አንኩስ ዳዊትን “እኔም በቋሚነት የግል ጠባቂዬ እንድትሆን የምሾምህ ለዚህ ነው” አለው። |
በዚህ ጊዜ ሳሙኤል ሞቶ ነበር፤ እስራኤላውያንም ሁሉ አልቅሰውለት በገዛ ከተማው በራማ ቀብረውት ነበር። ሳኦልም መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድሪቱ አስወግዶ ነበር። |
ፍልስጤማውያንም ተሰብስበው በመምጣት በሹነም ሰፈሩ። ሳኦል ደግሞ እስራኤላውያንን በሙሉ አሰባሰበ፤ እነሱም በጊልቦአ ሰፈሩ። |
ሳኦል የፍልስጤማውያንን ሠራዊት ባየ ጊዜ ፈራ፤ ልቡም እጅግ ተሸበረ። |
ሳኦል ይሖዋን ቢጠይቅም ይሖዋ በሕልምም ሆነ በኡሪም አሊያም በነቢያት በኩል መልስ አልሰጠውም። |
በመጨረሻም ሳኦል አገልጋዮቹን “መናፍስት ጠሪ ፈልጉልኝ፤ እኔም ሄጄ ምክር እጠይቃታለሁ” አላቸው። አገልጋዮቹም “በኤንዶር አንዲት መናፍስት ጠሪ አለች” በማለት መለሱለት። |
በመሆኑም ሳኦል ማንነቱን ሰውሮና ሌላ ልብስ ለብሶ ከሁለት ሰዎች ጋር በመሆን በሌሊት ወደ ሴትየዋ ሄደ። እሱም “እባክሽ፣ መናፍስትን ጠርተሽ ጠንቁይልኝ፤ የምነግርሽንም ሰው አስነሺልኝ” አላት። |
ሆኖም ሴትየዋ እንዲህ አለችው፦ “ሳኦል መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድሪቱ በማስወገድ ምን እንዳደረገ አንተ ራስህ በሚገባ ታውቃለህ። ታዲያ እኔ እንድገደል ልታጠምደኝ የምትሞክረው ለምንድን ነው?” |
ከዚያም ሳኦል “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ በዚህ ጉዳይ በጥፋተኝነት አትጠየቂም!” በማለት በይሖዋ ማለላት። |
በዚህ ጊዜ ሴትየዋ “እሺ ማንን ላስነሳልህ?” አለችው። እሱም “ሳሙኤልን አስነሺልኝ” አላት። |
ሴትየዋም “ሳሙኤልን” ስታየው በኃይል ጮኸች፤ ከዚያም ሳኦልን “ያታለልከኝ ለምንድን ነው? አንተ ሳኦል አይደለህ!” አለችው። |
ንጉሡም “አትፍሪ፤ ለመሆኑ ምን እያየሽ ነው?” አላት። ሴትየዋም ለሳኦል “አማልክትን የሚመስል ከምድር ሲወጣ አያለሁ” ስትል መለሰችለት። |
እሱም ወዲያውኑ “ምን ይመስላል?” አላት፤ እሷም “የወጣው አንድ አረጋዊ ሰው ነው፤ እጅጌ የሌለው ቀሚስ ለብሷል” አለችው። በዚህ ጊዜ ሳኦል የወጣው “ሳሙኤል” እንደሆነ ተገነዘበ፤ በግንባሩም መሬት ላይ ተደፍቶ ሰገደ። |
ከዚያም “ሳሙኤል” ሳኦልን “እንድነሳ በማድረግ ለምን ትረብሸኛለህ?” አለው። ሳኦልም እንዲህ አለው፦ “ከባድ ጭንቅ ውስጥ ገብቻለሁ። ፍልስጤማውያን እየወጉኝ ነው፤ አምላክም ከእኔ ርቋል፤ በነቢያትም ሆነ በሕልም አማካኝነት መልስ አይሰጠኝም፤ ስለሆነም ምን ማድረግ እንዳለብኝ እንድትነግረኝ ጠራሁህ።” |
“ሳሙኤልም” እንዲህ አለው፦ “ታዲያ ይሖዋ ከራቀህና ጠላት ከሆነብህ እኔን ለምን ትጠይቀኛለህ? |
ይሖዋ በእኔ በኩል አስቀድሞ የተናገረውን ይፈጽማል፦ ይሖዋ መንግሥትን ከእጅህ ነጥቆ ከባልንጀሮችህ አንዱ ለሆነው ለዳዊት ይሰጠዋል። |
የይሖዋን ቃል ስላልሰማህና በአማሌቃውያን ላይ የነደደውን ቁጣውን ስላላስፈጸምክ ይሖዋ በዚህ ቀን ይህን ያደርግብሃል። |
ይሖዋ አንተንም ሆነ እስራኤላውያንን ለፍልስጤማውያን አሳልፎ ይሰጣችኋል፤ ነገ አንተና ልጆችህ ከእኔ ጋር ትሆናላችሁ። በተጨማሪም ይሖዋ የእስራኤልን ሠራዊት ለፍልስጤማውያን አሳልፎ ይሰጣል።” |
በዚህ ጊዜ ሳኦል በቁመቱ መሬት ላይ ተዘረረ፤ “ሳሙኤል” በተናገረውም ቃል የተነሳ በከፍተኛ ፍርሃት ተዋጠ። ደግሞም ሙሉ ቀንና ሙሉ ሌሊት እህል ስላልቀመሰ አቅሙ ተሟጠጠ። |
ሴትየዋም ወደ ሳኦል መጥታ በጣም እንደተረበሸ ስታይ እንዲህ አለችው፦ “እንግዲህ እኔ አገልጋይህ ቃልህን ሰምቻለሁ፤ ሕይወቴን አደጋ ላይ ጥዬም እንዳደርገው የነገርከኝን ፈጽሜአለሁ። |
አሁንም እባክህ፣ የአገልጋይህን ቃል ስማ። ትንሽ ምግብ ላቅርብልህና ብላ፤ ከዚያም ለመሄድ የሚያስችል ብርታት ታገኛለህ።” |
እሱ ግን “አልበላም” በማለት እንቢ አለ። ሆኖም አገልጋዮቹና ሴትየዋ አጥብቀው ለመኑት። በመጨረሻም ቃላቸውን በመስማት ከመሬት ተነስቶ አልጋ ላይ ተቀመጠ። |
ሴትየዋም ቤት ውስጥ አንድ የሰባ ጥጃ ነበራት፤ ስለዚህ ፈጠን ብላ ጥጃውን አረደችው፤ ከዚያም ዱቄት ወስዳ ካቦካች በኋላ ቂጣ ጋገረች። |
ለሳኦልና ለአገልጋዮቹም አቀረበችላቸው፤ እነሱም በሉ። ከዚያም ተነስተው በሌሊት ሄዱ። |
ዳዊትም ከዚያ ተነስቶ ወደ አዱላም ዋሻ ሸሸ። ወንድሞቹና መላው የአባቱ ቤት ይህን ሲሰሙ እሱ ወዳለበት ወደዚያ ወረዱ። |
ችግር ያጋጠማቸው፣ ዕዳ ያለባቸውና የተከፉ ሰዎች ሁሉ ወደ እሱ ተሰበሰቡ፤ እሱም አለቃቸው ሆነ። ከእሱም ጋር 400 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ነበሩ። |
በኋላም ዳዊት ከዚያ ተነስቶ በሞዓብ ወዳለችው ወደ ምጽጳ ሄደ፤ የሞዓብንም ንጉሥ “አምላክ የሚያደርግልኝን ነገር እስካውቅ ድረስ እባክህ አባቴና እናቴ አንተ ጋ ይሁኑ” አለው። |
በመሆኑም የሞዓብ ንጉሥ ጋ አስቀመጣቸው፤ እነሱም ዳዊት በተራራው ላይ ምሽግ ውስጥ በነበረበት ጊዜ ሁሉ እዚያ ተቀመጡ። |
ከጊዜ በኋላም ነቢዩ ጋድ ዳዊትን “እዚህ ምሽግ ውስጥ መቆየት የለብህም። ሄደህ ወደ ይሁዳ ምድር ግባ” አለው። በመሆኑም ዳዊት ሄዶ ወደ ሄሬት ጫካ ገባ። |
ሳኦልም ዳዊትና ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች መገኘታቸውን ሰማ። በዚህ ጊዜ ሳኦል በጊብዓ በኮረብታው ላይ ባለው የታማሪስክ ዛፍ ሥር ጦሩን ይዞ ተቀምጦ ነበር፤ አገልጋዮቹም ሁሉ በዙሪያው ቆመው ነበር። |
ከዚያም ሳኦል በዙሪያው የቆሙትን አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ቢንያማውያን፣ እስቲ ስሙኝ፤ ለመሆኑ የእሴይ ልጅ እንደ እኔ፣ እርሻና የወይን ቦታ ለሁላችሁም ይሰጣችኋል? ሁላችሁንስ የሺህ አለቆችና የመቶ አለቆች አድርጎ ይሾማችኋል? |
እናንተ ሁላችሁ በእኔ ላይ ደባ ፈጽማችሁብኛል! የገዛ ልጄ ከእሴይ ልጅ ጋር ቃል ኪዳን ሲጋባ አንድም ሰው አልነገረኝም! ይኸው አሁን እንደምታዩት የገዛ ልጄ፣ አገልጋዬን በእኔ ላይ እንዲያደባብኝ ማነሳሳቱን አንዳችሁም ብትሆኑ ስለ እኔ ተቆርቁራችሁ አልነገራችሁኝም።” |
ከዚያም በሳኦል አገልጋዮች ላይ ተሹሞ የነበረው ኤዶማዊው ዶይቅ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የእሴይ ልጅ በኖብ ወደሚገኘው ወደ አኪጡብ ልጅ ወደ አሂሜሌክ ሲመጣ አይቻለሁ። |
አሂሜሌክም ይሖዋን ጠየቀለት፤ ስንቅም ሰጠው። ሌላው ቀርቶ የፍልስጤማዊውን የጎልያድን ሰይፍ ሰጠው።” |
ንጉሡም ወዲያውኑ ሰዎች ልኮ የካህኑን የአኪጡብን ልጅ አሂሜሌክንና በኖብ በአባቱ ቤት የነበሩትን ካህናት በሙሉ አስጠራ። በመሆኑም ሁሉም ወደ ንጉሡ መጡ። |
ሳኦልም “አንተ የአኪጡብ ልጅ፣ እስቲ ስማኝ!” አለው፤ እሱም መልሶ “እሺ ጌታዬ፣ እየሰማሁ ነው” አለ። |
ከዚያም ሳኦል “ለእሴይ ልጅ ምግብና ሰይፍ በመስጠት እንዲሁም ስለ እሱ አምላክን በመጠየቅ አንተም ሆንክ እሱ ደባ የፈጸማችሁብኝ ለምንድን ነው? ይኸው አሁን እንደሚታየው እየተቃወመኝና እያደባብኝ ነው” አለው። |
በዚህ ጊዜ አሂሜሌክ ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “እንደው ለመሆኑ ከአገልጋዮችህ ሁሉ መካከል እንደ ዳዊት ያለ እምነት የሚጣልበት ማን አለ? እሱ የንጉሡ አማች፣ የክብር ዘቦችህ አለቃና በቤትህ የተከበረ ሰው ነው። |
ስለ እሱ አምላክን ስጠይቅ ዛሬ የመጀመሪያዬ ነው? የምትናገረው ነገር ፈጽሞ ያላሰብኩትን ነው! ንጉሡ አገልጋዩንም ሆነ የአባቴን ቤት በሙሉ ጥፋተኛ አያድርግ፤ ምክንያቱም አገልጋይህ ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም።” |
ንጉሡ ግን “አሂሜሌክ፣ አንተም ሆንክ የአባትህ ቤት በሙሉ በእርግጥ ትሞታላችሁ” አለው። |
ከዚያም ንጉሡ በዙሪያው ቆመው የነበሩትን ጠባቂዎች “ከዳዊት ጋር ስላበሩ ዙሩና የይሖዋን ካህናት ግደሉ! ዳዊት መኮብለሉን እያወቁ አልነገሩኝም!” አላቸው። የንጉሡ አገልጋዮች ግን የይሖዋን ካህናት ለመግደል እጃቸውን ማንሳት አልፈለጉም። |
ንጉሡም ዶይቅን “እንግዲያውስ አንተ ዙርና ካህናቱን ግደላቸው!” አለው። ኤዶማዊው ዶይቅም ወዲያውኑ ሄዶ ካህናቱን ገደላቸው። በዚያን ቀን፣ ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ የለበሱ 85 ሰዎችን ገደለ። |
እንዲሁም የካህናቱን ከተማ ኖብን በሰይፍ መታ፤ ወንድም ሆነ ሴት፣ ልጅም ሆነ ጨቅላ ሕፃን፣ በሬም ሆነ አህያ ወይም በግ አንድም ሳያስቀር ሁሉንም በሰይፍ ገደለ። |
ሆኖም ከአኪጡብ ልጅ ከአሂሜሌክ ልጆች አንዱ የሆነው አብያታር አምልጦ ዳዊትን ለመከተል እሱ ወዳለበት እየሮጠ ሄደ። |
አብያታር ለዳዊት “ሳኦል እኮ የይሖዋን ካህናት ገደላቸው” ሲል ነገረው። |
በዚህ ጊዜ ዳዊት አብያታርን እንዲህ አለው፦ “ያን ቀን ኤዶማዊው ዶይቅ እዚያ ስለነበር ይህን ለሳኦል እንደሚነግረው አውቄአለሁ። በአባትህ ቤት ላሉት ሰዎች ሁሉ ሞት ተጠያቂው እኔ ራሴ ነኝ። |
አሁን እኔ ጋ ቆይ። የአንተን ሕይወት የሚፈልግ የእኔን ሕይወት የሚፈልግ ስለሆነ አትፍራ፤ እኔ ከለላ እሆንሃለሁ።” |
ከዚያም ሳሙኤል ሳኦልን እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጌ እንድቀባህ የላከው እኔን ነበር፤ እንግዲህ አሁን ይሖዋ ምን እንደሚል ስማ። |
የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡ ጊዜ በመንገድ ላይ እነሱን በመቃወም ለፈጸሙት ድርጊት አማሌቃውያንን እቀጣቸዋለሁ። |
በል አሁን ሂድ፤ አማሌቃውያንን ምታቸው፤ እነሱንም ካላቸው ነገር ሁሉ ጋር ፈጽመህ አጥፋቸው። አንዳቸውንም አታስቀር፤ ወንድም ሆነ ሴት፣ ልጅም ሆነ ሕፃን፣ በሬም ሆነ በግ፣ ግመልም ሆነ አህያ ሁሉንም ግደል።’” |
ሳኦልም ሕዝቡን በጤላይም ሰብስቦ ቆጠረ፤ በዚያም 200,000 እግረኛ ወታደሮችና 10,000 የይሁዳ ሰዎች ነበሩ። |
ከዚያም ሳኦል እስከ አማሌቃውያን ከተማ ድረስ በመጠጋት በሸለቆው ውስጥ አደፈጠ። |
ሳኦልም ቄናውያንን “ከአማሌቃውያን ጋር አብሬ እንዳላጠፋችሁ ሂዱ፣ ከእነሱ መካከል ውጡ። ምክንያቱም እናንተ እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡበት ጊዜ ለሕዝቡ በሙሉ ታማኝ ፍቅር አሳይታችኋል” አላቸው። በመሆኑም ቄናውያን ከአማሌቃውያን መካከል ወጡ። |
ከዚያም ሳኦል አማሌቃውያንን ከሃዊላ አንስቶ በግብፅ አጠገብ እስከምትገኘው እስከ ሹር ድረስ መታቸው። |
እሱም የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን ከነሕይወቱ ማረከው፤ የቀረውን ሕዝብ ሁሉ ግን በሰይፍ ፈጽሞ አጠፋ። |
ሆኖም ሳኦልና ሕዝቡ አጋግን እንዲሁም ከመንጋው፣ ከከብቱ፣ ከደለቡት እንስሳትና ከአውራ በጎቹ መካከል ምርጥ የሆኑትንና ጥሩ ጥሩ የሆነውን ነገር ሁሉ ሳያጠፉ ተዉ። እነዚህን ሊያጠፏቸው አልፈለጉም። የማይረባውንና የማይፈለገውን ነገር ሁሉ ግን ፈጽመው አጠፉ። |
ከዚያም የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሳሙኤል መጣ፦ |
“ሳኦልን ንጉሥ በማድረጌ ተጸጽቻለሁ፤ ምክንያቱም እሱ እኔን ከመከተል ዞር ብሏል፤ ቃሌንም አልፈጸመም።” ሳሙኤልም በጣም ስለተረበሸ ሌሊቱን ሙሉ ወደ ይሖዋ ሲጮኽ አደረ። |
ሳሙኤል ሳኦልን ለማግኘት በማለዳ ተነስቶ ሲሄድ “ሳኦል ወደ ቀርሜሎስ ሄዶ በዚያ ለራሱ የመታሰቢያ ሐውልት አቁሟል። ከዚያም ተመልሶ ወደ ጊልጋል ወርዷል” ተብሎ ተነገረው። |
በመጨረሻም ሳሙኤል ወደ ሳኦል ሲመጣ ሳኦል “ይሖዋ ይባርክህ። የይሖዋን ቃል ፈጽሜአለሁ” አለው። |
ሳሙኤል ግን “ታዲያ ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎችና የከብቶች ድምፅ ምንድን ነው?” አለው። |
በዚህ ጊዜ ሳኦል “ሕዝቡ ከአማሌቃውያን ላይ ወስዶ ያመጣቸው ናቸው፤ ከመንጋውና ከከብቶቹ መካከል ምርጥ የሆኑትን ለአምላክህ ለይሖዋ መሥዋዕት እንዲሆኑ ሳያጠፉ ተዉአቸው፤ የቀረውን ግን ሙሉ በሙሉ አጥፍተናል” አለው። |
ሳሙኤልም ሳኦልን “ተው በቃ! ትናንት ማታ ይሖዋ ምን እንዳለኝ ልንገርህ” አለው። እሱም “እሺ ንገረኝ!” አለው። |
ሳሙኤልም እንዲህ አለው፦ “በእስራኤል ነገዶች ላይ መሪ ሆነህ በተሾምክበትና ይሖዋ በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ በቀባህ ጊዜ አንተ ራስህ እዚህ ግባ የማትባል ሰው እንደሆንክ ተሰምቶህ አልነበረም? |
በኋላም ይሖዋ ‘ሄደህ ኃጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው። ጨርሰህ እስክታጠፋቸውም ድረስ ከእነሱ ጋር ተዋጋ’ በማለት ላከህ። |
ታዲያ የይሖዋን ቃል ያልታዘዝከው ለምንድን ነው? ከዚህ ይልቅ ለምርኮው በመስገብገብ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አድርገሃል!” |
ሳኦል ግን ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “እኔ እኮ የይሖዋን ቃል ታዝዣለሁ! ይሖዋ የሰጠኝን ተልእኮ ለመፈጸም ሄጃለሁ፤ የአማሌቃውያንን ንጉሥ አጋግን ይዤ አምጥቻለሁ፤ አማሌቃውያንንም ፈጽሜ አጥፍቻለሁ። |
ሕዝቡ ግን በጊልጋል ለአምላክህ ለይሖዋ ለመሠዋት ከምርኮው ላይ በጎችንና ከብቶችን ይኸውም ለጥፋት ከተለየው ነገር ላይ ምርጥ የሆነውን ወሰደ።” |
ከዚያም ሳሙኤል እንዲህ አለ፦ “ይሖዋን ይበልጥ የሚያስደስተው የትኛው ነው? የሚቃጠሉ መባዎችንና መሥዋዕቶችን ማቅረብ ወይስ የይሖዋን ቃል መታዘዝ? እነሆ፣ መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ መስማትም ከአውራ በግ ስብ ይበልጣል፤ |
ምክንያቱም ዓመፀኝነት ሟርት ከመፈጸም አይተናነስም፤ እብሪተኝነትም ቢሆን ከጥንቆላና ከጣዖት አምልኮ ተለይቶ አይታይም። አንተ የይሖዋን ቃል ስላልተቀበልክ እሱም የአንተን ንግሥና አልተቀበለውም።” |
ከዚያም ሳኦል ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “ኃጢአት ሠርቻለሁ፤ ሕዝቡን በመፍራትና ቃላቸውን በመስማት የይሖዋን ትእዛዝም ሆነ የአንተን ቃል ጥሻለሁ። |
አሁንም እባክህ ኃጢአቴን ይቅር በል፤ ለይሖዋም እንድሰግድ አብረኸኝ ተመለስ።” |
ሳሙኤል ግን ሳኦልን “አንተ የይሖዋን ቃል ስላልተቀበልክና ይሖዋም በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆነህ እንድትቀጥል ስላልፈቀደ ከአንተ ጋር አልመለስም” አለው። |
ሳሙኤል ለመሄድ ዞር ሲል ሳኦል የሳሙኤልን ልብስ ጫፍ አፈፍ አድርጎ ያዘ፤ ልብሱም ተቀደደ። |
Subsets and Splits
No community queries yet
The top public SQL queries from the community will appear here once available.