text
stringlengths
4
267
ከዚያም ዮናታን ለብሶት የነበረውን መደረቢያ አውልቆ ለዳዊት ሰጠው፤ እንዲሁም ልብሶቹን ሌላው ቀርቶ ሰይፉን፣ ቀስቱንና ቀበቶውን ሰጠው።
ዳዊትም ለውጊያ ይወጣ ጀመር፤ ሳኦል በሚልከው በማንኛውም ቦታ ተልእኮውን በተሳካ ሁኔታ ይፈጽም ነበር። በመሆኑም ሳኦል በሠራዊቱ ላይ ሾመው፤ ይህም ሕዝቡንና የሳኦልን አገልጋዮች በሙሉ አስደሰታቸው።
ዳዊትና አብረውት ያሉት ሰዎች ፍልስጤማውያንን መትተው በተመለሱ ጊዜ በመላው የእስራኤል ከተሞች የሚገኙ ሴቶች አታሞና ባለ ሦስት አውታር መሣሪያ ይዘው በደስታ እየዘፈኑና እየጨፈሩ ንጉሥ ሳኦልን ለመቀበል ወጡ።
እየጨፈሩ የነበሩት ሴቶችም እንዲህ እያሉ ዘፈኑ፦ “ሳኦል ሺዎችን ገደለ፤ዳዊት ደግሞ አሥር ሺዎችን ገደለ።”
ሳኦልም እጅግ ተቆጣ፤ ዘፈኑም አላስደሰተውም፤ በመሆኑም “ለዳዊት አሥር ሺህ አሉለት፤ ለእኔ ግን ሺህ ብቻ፤ ያልተሰጠው ነገር እኮ መንግሥት ብቻ ነው!” አለ።
ከዚያች ዕለት አንስቶ ሳኦል ዳዊትን በጥርጣሬ ዓይን ይመለከተው ጀመር።
በማግስቱም ከአምላክ የመጣ መጥፎ መንፈስ ሳኦልን ያዘው፤ ዳዊት በፊት እንደሚያደርገው ሁሉ በገና እየደረደረ ሳለ ሳኦል ቤቱ ውስጥ እንግዳ ባሕርይ ያሳይ ጀመር። ሳኦልም በእጁ ጦር ይዞ ነበር፤
እሱም ‘ዳዊትን ከግድግዳው ጋር አጣብቀዋለሁ!’ ብሎ በማሰብ ጦሩን በኃይል ወረወረው። ዳዊት ግን ሁለት ጊዜ ከእሱ አመለጠ።
ይሖዋ ከሳኦል ተለይቶ ከዳዊት ጋር ስለነበር ሳኦል ዳዊትን ፈራው።
በመሆኑም ሳኦል ከፊቱ እንዲርቅ አደረገው፤ የሺህ አለቃ አድርጎም ሾመው፤ ዳዊትም ሠራዊቱን እየመራ ወደ ጦርነት ይሄድ ነበር።
ዳዊት የሚያከናውነው ነገር ሁሉ ይሳካለት ነበር፤ ይሖዋም ከእሱ ጋር ነበር።
ሳኦልም ዳዊት ስኬታማ እንደሆነ ሲያይ ፈራው።
መላው እስራኤልና ይሁዳ ግን ዳዊትን ወደዱት፤ ምክንያቱም ወደ ጦርነት ሲወጡ የሚመራቸው እሱ ነበር።
በኋላም ሳኦል ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ ትልቋ ልጄ ሜሮብ አለች። እሷን እድርልሃለሁ። ሆኖም ጀግንነትህን ለእኔ ከማሳየት ወደኋላ ማለት የለብህም፤ የይሖዋንም ጦርነቶች መዋጋት ይኖርብሃል።” ሳኦል ይህን ያለው ‘እጄን በዚህ ሰው ላይ አላሳርፍም። ከዚህ ይልቅ በፍልስጤማውያን እጅ ይሙት’ ብሎ ስላሰበ ነው።
በዚህ ጊዜ ዳዊት ሳኦልን “ለንጉሡ አማች እሆን ዘንድ እኔም ሆንኩ የአባቴ ቤተሰቦች የሆኑት ዘመዶቼ በእስራኤል ውስጥ ከቶ ማን ሆነን ነው?” አለው።
ሆኖም የሳኦል ልጅ ሜሮብ ለዳዊት ልትሰጥ የነበረበት ጊዜ ሲደርስ እሷ ቀድሞውኑ ለመሆላታዊው ለአድሪዔል ተድራ ነበር።
የሳኦል ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ትወደው ነበር፤ ይህን ለሳኦል ነገሩት፤ እሱም ነገሩ ደስ አሰኘው።
በመሆኑም ሳኦል “ወጥመድ እንድትሆነውና የፍልስጤማውያን እጅ በእሱ ላይ እንዲሆን እሷን እሰጠዋለሁ” አለ። ከዚያም ሳኦል ለሁለተኛ ጊዜ ዳዊትን “በዛሬዋ ዕለት በዚህች በሁለተኛዋ ሴት አማካኝነት ከእኔ ጋር በጋብቻ ትዛመዳለህ” አለው።
በተጨማሪም ሳኦል አገልጋዮቹን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “ለዳዊት እንዲህ ብላችሁ በሚስጥር ንገሩት፦ ‘ንጉሡ በአንተ ደስ ብሎታል፤ አገልጋዮቹም በሙሉ ይወዱሃል። ስለሆነም አሁን ከንጉሡ ጋር በጋብቻ ተዛመድ።’”
የሳኦልም አገልጋዮች ይህን በነገሩት ጊዜ ዳዊት “እዚህ ግባ ለማልባል ለእንደኔ ዓይነቱ ድሃ ከንጉሡ ጋር በጋብቻ መዛመድ እንዲህ ቀላል ነገር ይመስላችኋል?” አላቸው።
ከዚያም የሳኦል አገልጋዮች “ዳዊት እኮ እንዲህ እንዲህ አለ” ብለው ነገሩት።
በዚህ ጊዜ ሳኦል እንዲህ አለ፦ “ዳዊትን እንዲህ በሉት፦ ‘ንጉሡ ከአንተ የሚፈልገው ጥሎሽ ሳይሆን ጠላቶቹን መበቀል እንዲችል የ100 ፍልስጤማውያንን ሸለፈት ብቻ ነው።’” ሳኦል ይህን ያለው ዳዊት በፍልስጤማውያን እጅ እንዲወድቅ ተንኮል አስቦ ስለነበር ነው።
በመሆኑም አገልጋዮቹ ይህንኑ ለዳዊት ነገሩት፤ ዳዊትም ከንጉሡ ጋር በጋብቻ የመዛመዱ ጉዳይ አስደሰተው። ስለሆነም የተሰጠው ጊዜ ከማብቃቱ በፊት
ዳዊት አብረውት ከነበሩት ሰዎች ጋር በመሄድ 200 ፍልስጤማውያንን መታ፤ ዳዊት ከንጉሡ ጋር በጋብቻ ለመዛመድ የገደላቸውን ሰዎች ሸለፈት በሙሉ አምጥቶ ለንጉሡ ሰጠው። በመሆኑም ሳኦል ልጁን ሜልኮልን ዳረለት።
ሳኦል ይሖዋ ከዳዊት ጋር እንደነበርና ልጁ ሜልኮልም ዳዊትን እንደወደደችው ተረዳ።
በዚህም ምክንያት ሳኦል ዳዊትን ከበፊቱ ይልቅ ፈራው፤ በመሆኑም ዕድሜውን ሙሉ የዳዊት ጠላት ሆነ።
የፍልስጤም መኳንንትም ለውጊያ ይወጡ ነበር፤ ሆኖም ለውጊያ በወጡ ቁጥር ዳዊት ከሳኦል አገልጋዮች ሁሉ ይበልጥ ይሳካለት ነበር፤ ስሙም እየገነነ መጣ።
ከጊዜ በኋላም ዳዊት “ፍልስጤማውያን በቀኢላ ላይ ውጊያ ከፍተው በየአውድማው ያለውን እህል እየዘረፉ ነው” ተብሎ ተነገረው።
ስለሆነም ዳዊት “ሄጄ እነዚህን ፍልስጤማውያን ልምታ?” በማለት ይሖዋን ጠየቀ። ይሖዋም ዳዊትን “ሂድ፣ ፍልስጤማውያንን ምታ፤ ቀኢላንም አድናት” አለው።
የዳዊት ሰዎች ግን “እዚህ በይሁዳ እያለን እንኳ ፈርተናል፤ የፍልስጤማውያንን ሠራዊት ለመውጋት ወደ ቀኢላ ከሄድንማ ምን ያህል እንፈራ!” አሉት።
በመሆኑም ዳዊት እንደገና ይሖዋን ጠየቀ። ይሖዋም “ፍልስጤማውያንን በእጅህ አሳልፌ ስለምሰጥህ ተነስተህ ወደ ቀኢላ ውረድ” ሲል መለሰለት።
ስለዚህ ዳዊት ከሰዎቹ ጋር በመሆን ወደ ቀኢላ ሄዶ ከፍልስጤማውያን ጋር ተዋጋ፤ ከብቶቻቸውን እየነዳ ወሰደ፤ ብዙ ሰውም ገደለባቸው፤ በዚህ መንገድ ዳዊት የቀኢላን ነዋሪዎች ታደጋቸው።
የአሂሜሌክ ልጅ አብያታር በቀኢላ ወደነበረው ወደ ዳዊት በሸሸ ጊዜ ኤፉድ ይዞ ነበር።
ሳኦል “ዳዊት ወደ ቀኢላ መጥቷል” የሚል ወሬ ደረሰው። ሳኦልም “ዳዊት በሮችና መቀርቀሪያዎች ወዳሏት ከተማ በመግባት ራሱን ወጥመድ ውስጥ ከቷል፤ ስለሆነም አምላክ እሱን በእጄ አሳልፎ ሰጥቶታል” አለ።
በመሆኑም ሳኦል ወደ ቀኢላ በመውረድ ዳዊትንና ሰዎቹን ከቦ ለመያዝ ሕዝቡን ሁሉ ለጦርነት አሰባሰበ።
ዳዊትም ሳኦል ሴራ እየጠነሰሰበት መሆኑን ሲያውቅ ካህኑን አብያታርን “ኤፉዱን ወደዚህ አምጣው” አለው።
ከዚያም ዳዊት እንዲህ አለ፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ ሳኦል ወደ ቀኢላ መጥቶ በእኔ የተነሳ ከተማዋን ለማጥፋት ማሰቡን አገልጋይህ በእርግጥ ሰምቷል።
ታዲያ የቀኢላ መሪዎች ለእሱ አሳልፈው ይሰጡኝ ይሆን? አገልጋይህ እንደሰማውስ ሳኦል ወደዚህ ይወርድ ይሆን? የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ ለአገልጋይህ አሳውቀው።” በዚህ ጊዜ ይሖዋ “አዎ፣ ይወርዳል” አለው።
ዳዊትም “የቀኢላ መሪዎች እኔንና ሰዎቼን ለሳኦል አሳልፈው ይሰጡን ይሆን?” በማለት ጠየቀ። ይሖዋም “አዎ፣ አሳልፈው ይሰጧችኋል” ሲል መለሰለት።
ዳዊትም 600 ገደማ ከሚሆኑት የራሱ ሰዎች ጋር ወዲያውኑ ተነሳ፤ ከቀኢላም ወጥተው መሄድ ወደሚችሉበት ቦታ ሁሉ ሄዱ። ሳኦልም ዳዊት ከቀኢላ መሸሹ ሲነገረው እሱን ለማሳደድ መውጣቱን ተወው።
ዳዊትም በምድረ በዳው ውስጥ በሚገኙ በቀላሉ በማይደረስባቸው ቦታዎች፣ በዚፍ ምድረ በዳ ባለው ተራራማ አካባቢ ተቀመጠ። ሳኦል ሁልጊዜ ይፈልገው ነበር፤ ይሖዋ ግን በእጁ አሳልፎ አልሰጠውም።
ዳዊት በሆሬሽ በሚገኘው በዚፍ ምድረ በዳ ሳለ ሳኦል የእሱን ሕይወት ለመፈለግ መውጣቱን አውቆ ነበር።
የሳኦል ልጅ ዮናታንም በሆሬሽ ወደሚገኘው ወደ ዳዊት ሄደ፤ እሱም በይሖዋ ላይ ያለው ትምክህት እንዲጠናከር ረዳው።
እንዲህም አለው፦ “አባቴ ሳኦል ስለማያገኝህ አትፍራ፤ አንተ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆናለህ፤ እኔ ደግሞ ከአንተ ቀጥዬ ሁለተኛ ሰው እሆናለሁ፤ አባቴ ሳኦልም ቢሆን ይህን ያውቃል።”
ከዚያም ሁለቱም በይሖዋ ፊት ቃል ኪዳን ተጋቡ፤ ዳዊትም በሆሬሽ ተቀመጠ፤ ዮናታን ደግሞ ወደ ቤቱ ተመለሰ።
በኋላም የዚፍ ሰዎች በጊብዓ ወደነበረው ወደ ሳኦል ወጥተው እንዲህ አሉት፦ “ዳዊት እዚሁ አጠገባችን ከየሺሞን በስተ ደቡብ፣ በሃኪላ ኮረብታ ላይ በሆሬሽ በሚገኙት በቀላሉ የማይደረስባቸው ስፍራዎች ተደብቆ የለም?
አሁንም ንጉሥ ሆይ፣ ወደዚህ ለመውረድ በምትፈልግበት በማንኛውም ጊዜ ወደዚህ ና፤ እኛም እሱን ለንጉሡ አሳልፈን እንሰጣለን።”
በዚህ ጊዜ ሳኦል እንዲህ አላቸው፦ “ለእኔ ስለተቆረቆራችሁ ይሖዋ ይባርካችሁ።
አሁንም እባካችሁ ሂዱና ያለበትን ትክክለኛ ቦታም ሆነ በዚያ ያየውን ሰው ማንነት ለይታችሁ ለማወቅ ጥረት አድርጉ፤ ምክንያቱም እሱ በጣም ተንኮለኛ ሰው እንደሆነ ሰምቻለሁ።
የሚደበቅባቸውን ቦታዎች በሙሉ በደንብ አጣሩ፤ ከዚያም ተጨባጭ ማስረጃ ይዛችሁልኝ ኑ። እኔም አብሬያችሁ እሄዳለሁ፤ በዚያ አገር የሚገኝ ከሆነ ከይሁዳ ሺዎች ሁሉ መካከል የገባበት ገብቼ አወጣዋለሁ።”
በመሆኑም ሰዎቹ ተነሱ፤ ከሳኦልም ቀድመው ወደ ዚፍ ሄዱ፤ በዚህ ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ ከየሺሞን በስተ ደቡብ በሚገኘው በአረባ፣ በማኦን ምድረ በዳ ነበሩ።
ሳኦልም ዳዊትን ለመፈለግ ከሰዎቹ ጋር መጣ። ዳዊትም ይህ በተነገረው ጊዜ ወዲያውኑ ወደ ዓለቱ ወርዶ በማኦን ምድረ በዳ ተቀመጠ። ሳኦል ይህን ሲሰማ ዳዊትን እያሳደደ ወደ ማኦን ምድረ በዳ ሄደ።
ከዚያም ሳኦል ከተራራው በአንደኛው በኩል ሲሆን ዳዊትና ሰዎቹ ደግሞ ከተራራው በሌላኛው በኩል ሆኑ። ዳዊት ከሳኦል ለማምለጥ እየተጣደፈ ነበር፤ ይሁን እንጂ ሳኦልና አብረውት የነበሩት ሰዎች ዳዊትንና ሰዎቹን ለመያዝ ተቃርበው ነበር።
ሆኖም አንድ መልእክተኛ ወደ ሳኦል መጥቶ “ፍልስጤማውያን ምድሪቱን ስለወረሯት ቶሎ ድረስ!” አለው።
በዚህ ጊዜ ሳኦል ዳዊትን ማሳደዱን ትቶ ፍልስጤማውያንን ለመግጠም ሄደ። ያ ቦታ ‘የመለያያ ዓለት’ የተባለው በዚህ የተነሳ ነው።
ዳዊትም ከዚያ ወጥቶ በኤንገዲ በሚገኙ በቀላሉ በማይደረስባቸው ስፍራዎች ተቀመጠ።
የይሖዋ ታቦት በፍልስጤማውያን ምድር ሰባት ወር ቆየ።
ፍልስጤማውያኑም ካህናትንና ሟርተኞችን ጠርተው “የይሖዋን ታቦት ምን ብናደርገው ይሻላል? ወደ ስፍራው እንዴት እንደምንመልሰው አሳውቁን” አሏቸው።
እነሱም እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፦ “የእስራኤልን አምላክ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት የምትመልሱ ከሆነ ያለመባ እንዳትመልሱት። ከበደል መባ ጋር አድርጋችሁ ወደ እሱ መመለስ ይኖርባችኋል። የምትፈወሱት እንዲህ ካደረጋችሁ ብቻ ነው፤ ደግሞም እጁ ከእናንተ ላይ ያልተመለሰው ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ።”
ስለዚህ “ወደ እሱ መላክ የሚኖርብን የበደል መባ ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁ። እነሱም እንዲህ አሏቸው፦ “እናንተንም ሆነ ገዢዎቻችሁን ያሠቃየው መቅሰፍት ተመሳሳይ ስለሆነ በፍልስጤም ገዢዎች ቁጥር ልክ አምስት የወርቅ ኪንታሮቶችንና አምስት የወርቅ አይጦችን ላኩ።
ምድሪቱን እያጠፉ ባሉት ኪንታሮቶቻችሁና አይጦቻችሁ አምሳያ ምስሎችን ሥሩ፤ የእስራኤልንም አምላክ አክብሩ። ምናልባትም በእናንተ፣ በአምላካችሁና በምድራችሁ ላይ የከበደውን እጁን ያቀልላችሁ ይሆናል።
ግብፅና ፈርዖን ልባቸውን እንዳደነደኑት እናንተም ለምን ልባችሁን ታደነድናላችሁ? እሱ ክፉኛ በቀጣቸው ጊዜ እስራኤላውያንን ለቀቋቸው፤ እነሱም ሄዱ።
ስለዚህ አሁን አዲስ ሠረገላ እንዲሁም እንቦሶች ያሏቸውና ቀንበር ያልተጫነባቸው ሁለት ላሞች አዘጋጁ። ከዚያም ሠረገላውን ጥመዱባቸው፤ እንቦሶቻቸውን ግን ከእነሱ ነጥላችሁ ወደ ቤት መልሷቸው።
የይሖዋን ታቦት ወስዳችሁ ሠረገላው ላይ አስቀምጡት፤ እንዲሁም ለእሱ የበደል መባ አድርጋችሁ የምትልኳቸውን የወርቅ ምስሎች በሣጥን አድርጋችሁ ታቦቱ አጠገብ አስቀምጡ። ከዚያም መንገዱን ይዞ እንዲሄድ ላኩት፤
ልብ ብላችሁም ተመልከቱ፦ ታቦቱ ወደ አገሩ ወደ ቤትሼሜሽ የሚወስደውን መንገድ ተከትሎ ከሄደ ይህን ታላቅ መከራ ያመጣብን እሱ ነው ማለት ነው። ካልሆነ ግን የእሱ እጅ እንዳልመታን እናውቃለን፤ ይህ የደረሰብንም እንዲያው በአጋጣሚ ነው።”
ሰዎቹም እንዲሁ አደረጉ። እንቦሶች ያሏቸውን ሁለት ላሞች ወስደው ሠረገላውን ጠመዱባቸው፤ እንቦሶቹንም በረት ውስጥ ዘጉባቸው።
ከዚያም የይሖዋን ታቦት እንዲሁም የወርቅ አይጦቹንና የኪንታሮቶቻቸውን ምስል የያዘውን ሣጥን ሠረገላው ላይ ጫኑ።
ላሞቹም ወደ ቤትሼሜሽ በሚወስደው መንገድ ቀጥ ብለው ሄዱ። ወደ ቀኝም ወደ ግራም ሳይሉ አንዱን ጎዳና ተከትለው ‘እምቧ’ እያሉ ተጓዙ፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ የፍልስጤም ገዢዎች እስከ ቤትሼሜሽ ድንበር ድረስ ከኋላ ከኋላቸው ይከተሏቸው ነበር።
የቤትሼሜሽ ሰዎች በሸለቋማው ሜዳ ላይ ስንዴ እያጨዱ ነበር። እነሱም ቀና ብለው ታቦቱን ተመለከቱ፤ እሱን በማየታቸውም በጣም ተደሰቱ።
ሠረገላውም ወደ ቤትሼሜሻዊው ኢያሱ ማሳ ገብቶ እዚያ በሚገኝ አንድ ትልቅ ዓለት አጠገብ ቆመ። ሰዎቹም የሠረገላውን እንጨት ፈልጠው ላሞቹን ለይሖዋ የሚቃጠል መባ አድርገው አቀረቡ።
ሌዋውያኑም የይሖዋን ታቦትና አብሮት የነበረውን የወርቅ ምስሎቹን የያዘውን ሣጥን አውርደው በትልቁ ዓለት ላይ አስቀመጧቸው። በዚያም ቀን የቤትሼሜሽ ሰዎች ለይሖዋ የሚቃጠሉ መባዎችን አቀረቡ፤ መሥዋዕቶችንም ሠዉ።
አምስቱ የፍልስጤም ገዢዎችም ይህን ሲያዩ በዚያው ቀን ወደ ኤቅሮን ተመለሱ።
ፍልስጤማውያን ለይሖዋ የበደል መባ አድርገው የላኳቸው የወርቅ ኪንታሮቶች እነዚህ ናቸው፦ ለአሽዶድ አንድ፣ ለጋዛ አንድ፣ ለአስቀሎን አንድ፣ ለጌት አንድ እንዲሁም ለኤቅሮን አንድ።
የወርቅ አይጦቹ ቁጥር አምስቱ የፍልስጤም ገዢዎች በሚያስተዳድሯቸው ከተሞች ሁሉ ይኸውም በተመሸጉት ከተሞችና በሥራቸው በሚገኙ አውላላ ሜዳ ላይ ባሉ መንደሮች ቁጥር ልክ ነበር። የይሖዋን ታቦት ያስቀመጡበት በቤትሼሜሻዊው ኢያሱ ማሳ ውስጥ የሚገኘው ትልቅ ዓለት እስከ ዛሬ ድረስ ምሥክር ሆኖ ያገለግላል።
ይሁንና አምላክ የይሖዋን ታቦት ስለተመለከቱ የቤትሼሜሽን ሰዎች መታቸው። ከሕዝቡ መካከል 50,070 ሰዎችን መታ፤ ሰዎቹም ይሖዋ ብዙ ሕዝብ ስለፈጀባቸው ያለቅሱ ጀመር።
በመሆኑም የቤትሼሜሽ ሰዎች “ታዲያ በዚህ ቅዱስ አምላክ በይሖዋ ፊት ማን ሊቆም ይችላል? ምናለ ከእኛ ላይ ዞር ቢልና ወደ ሌሎች ቢሄድ?” አሉ።
ስለዚህ ወደ ቂርያትየአሪም ነዋሪዎች መልእክተኞችን ልከው “ፍልስጤማውያን የይሖዋን ታቦት መልሰዋል። ወደዚህ ውረዱና ይዛችሁት ውጡ” አሏቸው።
ፍልስጤማውያን ሠራዊታቸውን በሙሉ በአፌቅ አሰባሰቡ፤ እስራኤላውያን ደግሞ በኢይዝራኤል በሚገኘው ምንጭ አጠገብ ሰፍረው ነበር።
የፍልስጤም ገዢዎችም በመቶዎችና በሺዎች እየሆኑ አለፉ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ከአንኩስ ጋር ሆነው ከኋላ ተሰልፈው ይሄዱ ነበር።
የፍልስጤም መኳንንት ግን “እነዚህ ዕብራውያን እዚህ ምን ያደርጋሉ?” አሉ። በዚህ ጊዜ አንኩስ የፍልስጤምን መኳንንት “ይህ ሰው ከእኔ ጋር ለአንድ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ አብሮኝ የኖረው የእስራኤል ንጉሥ የሳኦል አገልጋይ የሆነው ዳዊት ነው። ወደ እኔ ከተጠጋበት ቀን አንስቶ እስከዚህች ዕለት ድረስ ምንም ስህተት አላገኘሁበትም” አላቸው።
የፍልስጤም መኳንንት ግን በእሱ ላይ ተቆጥተው እንዲህ አሉት፦ “ይህ ሰው እንዲመለስ አድርግ። ወደሰጠኸውም ስፍራ ይመለስ። በውጊያው ወቅት እኛኑ ዞሮ እንዳይወጋን አብሮን ወደ ጦርነቱ እንዲሄድ ማድረግ የለብህም። ደግሞስ ከጌታው ጋር ለመታረቅ የእኛን ሰዎች ራስ ቆርጦ ከመውሰድ በስተቀር ምን የተሻለ ነገር ሊያደርግ ይችላል?
ይህ ሰው ‘ሳኦል ሺዎችን ገደለ፤ዳዊት ደግሞ አሥር ሺዎችን ገደለ’ በማለት እየዘፈኑ የጨፈሩለት ዳዊት አይደለም?”
በመሆኑም አንኩስ ዳዊትን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ አንተ ቅን ሰው ነህ፤ በእኔ በኩል ከሠራዊቴ ጋር አብረህ ብትዘምት ደስ ባለኝ፤ ምክንያቱም ወደ እኔ ከመጣህበት ቀን አንስቶ እስከዚህች ዕለት ድረስ ምንም ስህተት አላገኘሁብህም። ሆኖም ገዢዎቹ አላመኑህም።
ስለዚህ በሰላም ተመለስ፤ የፍልስጤም ገዢዎችን ቅር የሚያሰኝ ምንም ነገር አታድርግ።”
ዳዊት ግን አንኩስን “ምን አደረግኩ? ወደ አንተ ከመጣሁበት ጊዜ አንስቶ እስከዚህች ዕለት ድረስ በአገልጋይህ ላይ ምን ጥፋት አግኝተህበታል? ከአንተ ጋር የማልሄደውና ከንጉሡ ከጌታዬ ጠላቶች ጋር የማልዋጋው ለምንድን ነው?” አለው።
አንኩስም ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “በእኔ በኩል አንተ እንደ አምላክ መልአክ ጥሩ ሰው ነህ። የፍልስጤም መኳንንት ግን ‘ከእኛ ጋር ለጦርነት እንዲወጣ አታድርግ’ አሉኝ።
አሁንም አብረውህ ከመጡት የጌታህ አገልጋዮች ጋር በማለዳ ተነሱ፤ ልክ ጎህ ሲቀድ ጉዞ ጀምሩ።”
በመሆኑም ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ፍልስጤማውያን ምድር ለመመለስ በጠዋት ተነሱ፤ ፍልስጤማውያንም ወደ ኢይዝራኤል ወጡ።
ሳሙኤል በሸመገለ ጊዜ ልጆቹን በእስራኤል ውስጥ ፈራጆች ሆነው እንዲያገለግሉ ሾማቸው።
የበኩር ልጁ ስም ኢዩኤል ሲሆን የሁለተኛው ልጁ ስም ደግሞ አቢያህ ነበር፤ እነሱም በቤርሳቤህ ፈራጆች ነበሩ።
ይሁንና ልጆቹ የእሱን ፈለግ አልተከተሉም፤ ከዚህ ይልቅ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ይጥሩ፣ ጉቦ ይቀበሉ እንዲሁም ፍርድ ያጣምሙ ነበር።
ከጊዜ በኋላ የእስራኤል ሽማግሌዎች በሙሉ አንድ ላይ ተሰብስበው በራማ ወደሚገኘው ወደ ሳሙኤል መጡ።
እንዲህም አሉት፦ “እንግዲህ አንተ አርጅተሃል፤ ልጆችህ ደግሞ የአንተን ፈለግ እየተከተሉ አይደለም። ስለዚህ እንደ ሌሎቹ ብሔራት ሁሉ በእኛ ላይ ፈራጅ የሚሆን ንጉሥ ሹምልን።”
ይሁንና “በእኛ ላይ ፈራጅ የሚሆን ንጉሥ ሹምልን” ማለታቸው ሳሙኤልን አላስደሰተውም። ሳሙኤልም ወደ ይሖዋ ጸለየ፤
ይሖዋም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “ሕዝቡ የሚልህን ሁሉ ስማ፤ አልቀበልም ያሉት አንተን አይደለም፤ ይልቁንም ንጉሣቸው አድርገው መቀበል ያልፈለጉት እኔን ነው።
እየፈጸሙ ያሉት ነገር ከግብፅ ካወጣኋቸው ቀን ጀምሮ እስከዚህች ዕለት ድረስ ሲያደርጉ የነበሩትን ነው፤ እኔን ትተው ሌሎች አማልክትን አገለገሉ፤ በአንተም ላይ እያደረጉ ያሉት ይህንኑ ነው።
ስለዚህ የሚሉህን ስማ። ይሁን እንጂ በጥብቅ አስጠንቅቃቸው፤ በላያቸው የሚነግሠው ንጉሥ ምን እንዲደረግለት የመጠየቅ መብት እንዳለው ንገራቸው።”
በመሆኑም ሳሙኤል ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው ለጠየቁት ሰዎች የይሖዋን ቃል ሁሉ ነገራቸው።
እንዲህ አላቸው፦ “በእናንተ ላይ የሚነግሠው ንጉሥ እንዲህ እንዲደረግለት የመጠየቅ መብት አለው፦ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሠረገላው ውስጥ ያስቀምጣቸዋል፤ ፈረሰኞችም ያደርጋቸዋል፤ የተወሰኑትንም ከሠረገሎቹ ፊት ፊት እንዲሮጡ ያደርጋል።
ለራሱም የሺህ አለቆችንና የሃምሳ አለቆችን ይሾማል፤ አንዳንዶቹም መሬቱን ያርሳሉ፣ እህሉን ያጭዳሉ እንዲሁም የጦር መሣሪያዎቹንና ለሠረገሎቹ የሚሆኑትን ዕቃዎች ይሠራሉ።