text
stringlengths
4
267
ሴቶች ልጆቻችሁንም ወስዶ ቅባት ቀማሚዎች፣ ምግብ አብሳዮችና ዳቦ ጋጋሪዎች ያደርጋቸዋል።
እንዲሁም ከማሳችሁ፣ ከወይን እርሻችሁና ከወይራ ዛፎቻችሁ ምርጥ የሆነውን ይወስዳል፤ ለአገልጋዮቹም ይሰጣቸዋል።
ከእህል ማሳችሁና ከወይን እርሻችሁ ላይ አንድ አሥረኛውን ወስዶ ለቤተ መንግሥት ባለሥልጣናቱና ለአገልጋዮቹ ይሰጣል።
ወንድ አገልጋዮቻችሁንና ሴት አገልጋዮቻችሁን፣ ከከብቶቻችሁ መካከል ምርጥ የሆኑትን እንዲሁም አህዮቻችሁን ይወስዳል፤ ለራሱ ሥራም ይጠቀምባቸዋል።
ከመንጋችሁ መካከል አንድ አሥረኛውን ይወስዳል፤ እናንተም የእሱ አገልጋዮች ትሆናላችሁ።
ለራሳችሁ ከመረጣችሁት ንጉሥ የተነሳ የምትጮኹበት ቀን ይመጣል፤ ሆኖም በዚያ ቀን ይሖዋ አይመልስላችሁም።”
ሕዝቡ ግን ሳሙኤል የተናገረውን ለመስማት አሻፈረኝ አለ፤ እንዲህም አለ፦ “አይሆንም፣ ንጉሥ እንዲነግሥልን እንፈልጋለን።
ከዚያም እንደ ሌሎች ብሔራት እንሆናለን፤ ንጉሣችንም ፈራጅ ይሆንልናል፣ ይመራናል እንዲሁም ጦርነት ሲገጥመን ይዋጋልናል።”
ሳሙኤልም ሕዝቡ ያለውን ሁሉ ከሰማ በኋላ የተናገሩትን ነገር ይሖዋ እየሰማ በድጋሚ ተናገረ።
ይሖዋም ሳሙኤልን “የሚሉህን ስማ፤ በላያቸው የሚገዛ ንጉሥም አንግሥላቸው” አለው። ከዚያም ሳሙኤል የእስራኤልን ሰዎች “እያንዳንዳችሁ ወደ ከተማችሁ ተመለሱ” አላቸው።
ከዚያም አኪጦፌል አቢሴሎምን እንዲህ አለው፦ “እባክህ፣ 12,000 ሰዎች ልምረጥና ተነስቼ ዛሬ ማታ ዳዊትን ላሳደው።
በደከመውና አቅም ባጣ ጊዜ ድንገት እደርስበታለሁ፤ ሽብርም እለቅበታለሁ፤ አብረውት ያሉት ሰዎችም ሁሉ ይሸሻሉ፤ ንጉሡን ብቻ እመታለሁ።
ከዚያም ሕዝቡን ሁሉ ወደ አንተ እመልሳለሁ። የሕዝቡ ሁሉ መመለስ የተመካው አንተ የምትፈልገው ሰው በሚደርስበት ነገር ላይ ነው። ከዚያ በኋላ ሕዝቡ ሁሉ ሰላም ያገኛል።”
ይህ ሐሳብም በአቢሴሎምና በእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ ፊት መልካም ሆኖ ተገኘ።
ሆኖም አቢሴሎም “እስቲ አርካዊውን ኩሲን ጥሩትና እሱ ደግሞ የሚለውን እንስማ” አለ።
በመሆኑም ኩሲ ወደ አቢሴሎም ገባ። ከዚያም አቢሴሎም “አኪጦፌል እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል። ታዲያ እሱ እንዳለው እናድርግ? ካልሆነ የአንተን ሐሳብ ንገረን” አለው።
ኩሲም አቢሴሎምን “እዚህ ላይ እንኳ አኪጦፌል የሰጠው ምክር የሚያዋጣ አይደለም!” አለው።
አክሎም ኩሲ እንዲህ አለ፦ “መቼም አባትህም ሆነ አብረውት ያሉት ሰዎች ኃያል ተዋጊዎችና በሜዳ እንዳለች ግልገሎቿን ያጣች ድብ ምንም ነገር ከማድረግ የማይመለሱ መሆናቸውን በሚገባ ታውቃለህ። ደግሞም አባትህ ጦረኛ ነው፤ ሌሊት ከሕዝቡ ጋር አያድርም።
ይህን ጊዜ እኮ አንድ ዋሻ ውስጥ ወይም ሌላ ቦታ ተደብቋል፤ እሱ ቀድሞ ጥቃት ከሰነዘረ ይህን የሰሙ ሁሉ ‘አቢሴሎምን የተከተሉት ሰዎች ድል ተመቱ!’ ብለው ያወራሉ።
ልቡ እንደ አንበሳ የሆነ ደፋር ሰው እንኳ በፍርሃት መራዱ አይቀርም፤ ምክንያቱም አባትህ ኃያል ተዋጊ፣ አብረውት ያሉትም ሰዎች ጀግኖች መሆናቸውን መላው እስራኤል ያውቃል።
እንግዲህ እኔ የምመክርህ ይህ ነው፦ ከብዛቱ የተነሳ በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የሆነው ከዳን አንስቶ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ያለው የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ወደ አንተ ይሰብሰብ፤ አንተ ራስህም እየመራህ ወደ ውጊያ ውሰዳቸው።
እኛም የገባበት ገብተን ጥቃት እንሰነዝርበታለን፤ በመሬት ላይ እንደሚወርድ ጤዛም እንወርድበታለን፤ እሱም ሆነ ከእሱ ጋር ያሉት ሰዎች አንዳቸውም አያመልጡም።
ወደ አንድ ከተማ ቢሸሽ እንኳ መላው እስራኤል ወደ ከተማዋ ገመድ ይዞ በመሄድ፣ ከተማዋን ጎትተን አንዲት ጠጠር ሳናስቀር ሸለቆ ውስጥ እንከታታለን።”
ከዚያም አቢሴሎምና የእስራኤል ሰዎች በሙሉ “ከአኪጦፌል ምክር ይልቅ የአርካዊው የኩሲ ምክር ይሻላል!” አሉ። ምክንያቱም ይሖዋ በአቢሴሎም ላይ ጥፋት ለማምጣት ሲል ይሖዋ መልካም የሆነውን የአኪጦፌልን ምክር ለማክሸፍ ወስኖ ነበር።
በኋላም ኩሲ ካህናት የሆኑትን ሳዶቅንና አብያታርን እንዲህ አላቸው፦ “አኪጦፌል እንዲህ እንዲህ በማለት አቢሴሎምንና የእስራኤልን ሽማግሌዎች መክሯቸው ነበር፤ እኔ ደግሞ እንዲህ እንዲህ ብዬ መክሬያቸዋለሁ።
አሁንም ለዳዊት ፈጥናችሁ መልእክት በመላክ እንዲህ ብላችሁ አስጠንቅቁት፦ ‘ዛሬ ሌሊት በምድረ በዳው ባሉት መልካዎች እንዳታድር፤ የግድ መሻገር አለብህ፤ አለዚያ ንጉሡና አብሮት ያለው ሕዝብ በሙሉ ያልቃል።’”
ዮናታንና አኪማዓስም በኤንሮጌል ተቀምጠው ነበር፤ በመሆኑም አንዲት አገልጋይ ሄዳ መልእክቱን ነገረቻቸው፤ እነሱም ሁኔታውን ለንጉሥ ዳዊት ለመንገር ሄዱ። ምክንያቱም ወደ ከተማዋ ከገባን እንታያለን ብለው ፈርተው ነበር።
ይሁንና አንድ ወጣት አያቸውና ለአቢሴሎም ነገረው። ስለሆነም ሁለቱም በፍጥነት ከዚያ በመሄድ በባሁሪም ወደሚገኝ አንድ ሰው ቤት መጡ፤ እሱም ግቢው ውስጥ የውኃ ጉድጓድ ነበረው። እነሱም እዚያ ውስጥ ገቡ፤
የሰውየውም ሚስት በጉድጓዱ አፍ ላይ ማስጫ ዘርግታ የተከካ እህል አሰጣችበት፤ ይህን ያወቀ ማንም ሰው አልነበረም።
የአቢሴሎም አገልጋዮችም ወደ ሴትየዋ ቤት መጥተው “አኪማዓስና ዮናታን የት አሉ?” አሏት። እሷም “በዚህ አልፈው ወደ ወንዙ ሄደዋል” አለቻቸው። ሰዎቹም ፍለጋቸውን ቀጠሉ፤ ሆኖም ሊያገኟቸው አልቻሉም፤ ስለዚህ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
ሰዎቹ ከሄዱም በኋላ አኪማዓስና ዮናታን ከጉድጓዱ ወጥተው ወደ ንጉሥ ዳዊት በመሄድ “እናንተ ሰዎች፣ ተነስታችሁ በፍጥነት ወንዙን ተሻገሩ፤ ምክንያቱም አኪጦፌል ስለ እናንተ እንዲህ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል” አሉት።
ዳዊትና አብሮት የነበረው ሕዝብ በሙሉ ወዲያውኑ ተነስተው ዮርዳኖስን ተሻገሩ። ጎህ ሲቀድም ዮርዳኖስን ሳይሻገር የቀረ አንድም ሰው አልነበረም።
አኪጦፌል፣ የሰጠው ምክር ተቀባይነት እንዳላገኘ ሲያይ አህያውን ጭኖ በሚኖርባት ከተማ ወደሚገኘው ቤቱ ሄደ። ከዚያም ለቤተሰቡ አንዳንድ መመሪያዎችን ከሰጠ በኋላ ታንቆ ሞተ። በአባቶቹም የመቃብር ቦታ ተቀበረ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዳዊት ወደ ማሃናይም ሄደ፤ አቢሴሎም ደግሞ ከእስራኤል ሰዎች ሁሉ ጋር ዮርዳኖስን ተሻገረ።
አቢሴሎም በኢዮዓብ ቦታ አሜሳይን በሠራዊቱ ላይ ሾመው፤ አሜሳይ የእስራኤላዊው የይትራ ልጅ ነበር፤ ይትራ የኢዮዓብ እናት ከሆነችው ከጽሩያ እህት ከአቢጋኤል ጋር ግንኙነት ነበረው፤ አቢጋኤል የናሃሽ ልጅ ነበረች።
እስራኤላውያንና አቢሴሎም በጊልያድ ምድር ሰፈሩ።
ዳዊት ማሃናይም ሲደርስ የአሞናውያን ከተማ ከሆነችው ከራባ የመጣው የናሃሽ ልጅ ሾባይ፣ ከሎደባር የመጣው የአሚዔል ልጅ ማኪርና ከሮገሊም የመጣው ጊልያዳዊው ቤርዜሊ
ለመኝታ የሚሆኑ ነገሮች፣ ጎድጓዳ ሳህኖች፣ የሸክላ ዕቃዎች፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ዱቄት፣ ቆሎ፣ ባቄላ፣ ምስር፣ የተጠበሰ እሸት፣
ማር፣ ቅቤ፣ በግና አይብ ይዘው መጡ። ይህን ሁሉ ይዘው የመጡት “መቼም ሕዝቡ በምድረ በዳ ተርቧል፣ ደክሟል፣ ተጠምቷል” ብለው በማሰብ ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች እንዲበሉት ነው።
ለኢዮዓብ “ንጉሡ ለአቢሴሎም እያለቀሰና እያዘነ ነው” ተብሎ ተነገረው።
ሕዝቡ ሁሉ ንጉሡ በልጁ ምክንያት ማዘኑን ሲሰማ ያን ዕለት የተገኘው ድል ወደ ሐዘን ተለወጠ።
በዚያን ቀን ሕዝቡ ከጦርነት በመሸሹ ምክንያት በኀፍረት እንደተሸማቀቀ ሕዝብ ድምፁን አጥፍቶ ወደ ከተማዋ ገባ።
ንጉሡም ፊቱን ተከናንቦ “ልጄ አቢሴሎም! ልጄ አቢሴሎም፣ ልጄ!” እያለ ድምፁን ከፍ አድርጎ ያለቅስ ነበር።
ከዚያም ኢዮዓብ ቤቱ ውስጥ ወደነበረው ወደ ንጉሡ ገብቶ እንዲህ አለው፦ “በዛሬው ዕለት የአንተን፣ የወንዶች ልጆችህን፣ የሴቶች ልጆችህን፣ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን ሕይወት የታደጉትን አገልጋዮችህን ሁሉ አሳፍረሃቸዋል።
አንተ የሚጠሉህን ትወዳለህ፣ የሚወዱህን ደግሞ ትጠላለህ፤ የጦር አለቆችህም ሆኑ አገልጋዮችህ ለአንተ ምንህም እንዳይደሉ ይኸው ዛሬ በግልጽ አሳይተሃል፤ በዛሬው ቀን አቢሴሎም ብቻ በሕይወት ተርፎ እኛ ሁላችን አልቀን ቢሆን ኖሮ ደስ ይልህ እንደነበር እርግጠኛ ነኝ።
በል አሁን ተነስተህ ውጣና አገልጋዮችህን አበረታታቸው፤ ባትወጣ ግን በይሖዋ እምላለሁ፣ ዛሬ አንድም ሰው አብሮህ አያድርም። ይህ ደግሞ ከልጅነትህ አንስቶ እስካሁን ድረስ ከደረሰብህ ጉዳት ሁሉ የከፋ ይሆናል።”
በመሆኑም ንጉሡ ተነስቶ በከተማዋ በር አጠገብ ተቀመጠ፤ ለሕዝቡም ሁሉ “ንጉሡ በሩ አጠገብ ተቀምጧል” ተብሎ ተነገረው። ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ ወደ ንጉሡ መጣ። እስራኤላውያን ግን ወደየቤታቸው ሸሽተው ነበር።
በመላው የእስራኤል ነገዶች መካከል ያለው ሕዝብ እንዲህ በማለት ይከራከር ነበር፦ “ንጉሡ ከጠላቶቻችን አዳነን፤ ከፍልስጤማውያንም ታደገን፤ አሁን ግን በአቢሴሎም የተነሳ ከአገሩ ሸሽቶ ሄዷል።
በላያችን እንዲነግሥ የቀባነው አቢሴሎም እንደሆነ በውጊያው ሞቷል። ታዲያ ንጉሡን ለመመለስ አንድ ነገር የማታደርጉት ለምንድን ነው?”
ንጉሥ ዳዊት ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር እንዲህ የሚል መልእክት ላከባቸው፦ “የይሁዳን ሽማግሌዎች እንዲህ በሏቸው፦ ‘እስራኤላውያን በሙሉ የተናገሩት ነገር በቤቱ ውስጥ ወዳለው ወደ ንጉሡ ደርሶ ሳለ እናንተ ንጉሡን ወደ ቤቱ ለመመለስ እንዴት የመጨረሻዎቹ ሰዎች ትሆናላችሁ?
እናንተ ወንድሞቼ ናችሁ፤ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቁራጭ ናችሁ። ታዲያ ንጉሡን ለመመለስ እንዴት የመጨረሻዎቹ ሰዎች ትሆናላችሁ?’
አሜሳይንም ‘አንተ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቁራጭ አይደለህም? ከአሁን ጀምሮ በኢዮዓብ ምትክ የሠራዊቴ አለቃ ባትሆን አምላክ እንዲህ ያድርግብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጣብኝ’ በሉት።”
በመሆኑም የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ልብ ልክ እንደ አንድ ሰው ልብ ማረከ፤ እነሱም ወደ ንጉሡ “አንተም ሆንክ አገልጋዮችህ በሙሉ ተመለሱ” የሚል መልእክት ላኩበት።
ንጉሡም ለመመለስ ጉዞ ጀመረ፤ እስከ ዮርዳኖስም ድረስ መጣ፤ የይሁዳም ሰዎች ንጉሡን ለመቀበልና እስከ ዮርዳኖስ ማዶ ድረስ ለመሸኘት ወደ ጊልጋል መጡ።
የባሁሪም ሰው የሆነው ቢንያማዊው የጌራ ልጅ ሺምአይ ንጉሥ ዳዊትን ለማግኘት ከይሁዳ ሰዎች ጋር በፍጥነት ወረደ፤
ከእሱም ጋር ከቢንያም የመጡ 1,000 ሰዎች ነበሩ። በተጨማሪም የሳኦል ቤት አገልጋይ የሆነው ሲባ ከ15 ወንዶች ልጆቹና ከ20 አገልጋዮቹ ጋር በመሆን ከንጉሡ ቀድሞ በፍጥነት ወደ ዮርዳኖስ ወረደ።
እሱም የንጉሡን ቤተሰብ ለማሻገርና ንጉሡ ደስ የሚያሰኘውን ለማድረግ መልካውን ተሻገረ። የጌራ ልጅ ሺምአይ ግን ንጉሡ ዮርዳኖስን ሊሻገር ሲል በፊቱ ተደፋ።
ንጉሡንም እንዲህ አለው፦ “ጌታዬ በደሌን አይቁጠርብኝ፤ ጌታዬ ንጉሡ ከኢየሩሳሌም በወጣበት ቀን አገልጋይህ የፈጸመውን በደል አያስብ። ንጉሡም በልቡ አይያዘው፤
ምክንያቱም እኔ አገልጋይህ ኃጢአት እንደሠራሁ በሚገባ አውቃለሁ፤ በመሆኑም ዛሬ ጌታዬን ንጉሡን ወርጄ ለመቀበል ከመላው የዮሴፍ ቤት ቀድሜ መጥቻለሁ።”
በዚህ ጊዜ የጽሩያ ልጅ አቢሳ “ሺምአይ ይሖዋ የቀባውን በመራገም ለፈጸመው በደል ሞት አይገባውም?” አለ።
ዳዊት ግን እንዲህ አለ፦ “እናንተ የጽሩያ ልጆች፣ ይህ ጉዳይ ምን ይመለከታችኋልና ነው ዛሬ እኔን ተቃውማችሁ የተነሳችሁት? በዛሬው ዕለት እስራኤል ውስጥ ሰው መገደል ይገባዋል? በእስራኤል ላይ ንጉሥ መሆኔን ያወቅኩት ዛሬ አይደለም?”
ንጉሡ አክሎ ሺምአይን “አይዞህ፣ አትሞትም” አለው። ከዚያም ንጉሡ ማለለት።
የሳኦል የልጅ ልጅ የሆነው ሜፊቦስቴም ንጉሡን ለመቀበል ወረደ። እሱም ንጉሡ ከሄደበት ቀን አንስቶ በሰላም እስከተመለሰበት ዕለት ድረስ ለእግሩ ተገቢውን እንክብካቤ አላደረገም፣ ጢሙን አልተከረከመም፤ ልብሱንም አላጠበም።
እሱም ንጉሡን ለማግኘት ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ ንጉሡ “ሜፊቦስቴ፣ አብረኸኝ ያልሄድከው ለምንድን ነው?” አለው።
በዚህ ጊዜ እንዲህ አለው፦ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ አገልጋዬ አታለለኝ። እኔ አገልጋይህ ሽባ ስለሆንኩ ‘በአህያዬ ላይ ተቀምጬ ከንጉሡ ጋር እንድሄድ አህያዬን ጫኑልኝ’ ብዬ ነበር።
ሆኖም እሱ በጌታዬ በንጉሡ ፊት የእኔን የአገልጋይህን ስም አጥፍቷል። ይሁን እንጂ ጌታዬ ንጉሡ እንደ እውነተኛው አምላክ መልአክ ስለሆነ መልካም መስሎ የታየህን አድርግ።
የአባቴ ቤት በሙሉ በንጉሡ በጌታዬ ሞት ሊፈረድበት ይገባ ነበር፤ አንተ ግን አገልጋይህን ከማዕድህ ከሚበሉት አንዱ አደረግከው። ታዲያ ንጉሡን ተጨማሪ ነገር የመጠየቅ ምን መብት አለኝ?”
ሆኖም ንጉሡ “ለምን ዝም ብለህ ነገር ታስረዝማለህ? እርሻውን አንተና ሲባ እንድትካፈሉ ወስኛለሁ” አለው።
በዚህ ጊዜ ሜፊቦስቴ ንጉሡን “ጌታዬ ንጉሡ ወደ ቤቱ እንኳን በሰላም ተመለሰ እንጂ እሱ ሁሉንም ይውሰደው” አለው።
ከዚያም ጊልያዳዊው ቤርዜሊ ንጉሡን ወደ ዮርዳኖስ ለመሸኘት ከሮገሊም ወደ ዮርዳኖስ ወረደ።
ቤርዜሊ የ80 ዓመት አረጋዊ ነበር፤ እጅግ ባለጸጋም ስለነበር ንጉሡ በማሃናይም ይኖር በነበረበት ጊዜ ቀለብ አምጥቶለት ነበር።
በመሆኑም ንጉሡ ቤርዜሊን “አብረኸኝ ተሻገር፤ እኔም በኢየሩሳሌም ቀለብ እሰጥሃለሁ” አለው።
ቤርዜሊ ግን ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “ከንጉሡ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የምወጣው ለየትኛው ዕድሜዬ ብዬ ነው?
አሁን የ80 ዓመት ሰው ነኝ። ታዲያ መልካምና መጥፎውን መለየት እችላለሁ? እኔ አገልጋይህ የምበላውንና የምጠጣውን ማጣጣም እችላለሁ? ደግሞስ የወንድና የሴት ዘፋኞችን ድምፅ መስማት እችላለሁ? ታዲያ አገልጋይህ ለጌታዬ ለንጉሡ ለምን ተጨማሪ ሸክም ይሆናል?
አገልጋይህ ንጉሡን እስከ ዮርዳኖስ ድረስ መሸኘት ከቻለ ይበቃዋል። ታዲያ ንጉሡ ይህን ወሮታ የሚመልስልኝ ለምንድን ነው?
እባክህ እኔ አገልጋይህ ልመለስና በገዛ ከተማዬ በአባቴና በእናቴ መቃብር አጠገብ ልሙት። ሆኖም አገልጋይህ ኪምሃም ይኸውልህ። እሱ ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር ይሻገር፤ አንተም መልካም መስሎ የታየህን አድርግለት።”
በመሆኑም ንጉሡ “እንግዲያው ኪምሃም አብሮኝ ይሻገራል፤ እኔም መልካም መስሎ የታየህን አደርግለታለሁ፤ ለአንተም የምትጠይቀኝን ማንኛውንም ነገር አደርግልሃለሁ” አለው።
በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ዮርዳኖስን መሻገር ጀመረ፤ ንጉሡም ሊሻገር ሲል ቤርዜሊን ስሞ ባረከው፤ ቤርዜሊም ወደ ቤቱ ተመለሰ።
ንጉሡ ወደ ጊልጋል ሲሻገር ኪምሃምም አብሮት ተሻገረ። እንዲሁም የይሁዳ ሰዎች በሙሉና ግማሹ የእስራኤል ሕዝብ ንጉሡን አሻገሩት።
ከዚያም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ቀርበው “ወንድሞቻችን የሆኑት የይሁዳ ሰዎች ሹልክ ብለው ይዘውህ በመሄድ ንጉሡንና ቤተሰቡን ከዳዊት ሰዎች ሁሉ ጋር ዮርዳኖስን ያሻገሩት ለምንድን ነው?” አሉት።
በዚህ ጊዜ የይሁዳ ሰዎች ሁሉ የእስራኤልን ሰዎች “ይህን ያደረግነው ንጉሡ ዘመዳችን ስለሆነ ነው። ታዲያ ይህ እናንተን ያስቆጣችሁ ለምንድን ነው? በንጉሡ ወጪ የበላነው ነገር አለ? ወይስ ስጦታ መጥቶልን ያውቃል?” አሏቸው።
ሆኖም የእስራኤል ሰዎች የይሁዳን ሰዎች እንዲህ አሏቸው፦ “እኛ እኮ ከንጉሡ አሥር እጅ ድርሻ አለን፤ ስለሆነም በዳዊት ላይ ከእናንተ የበለጠ መብት ያለን እኛ ነን። ታዲያ የናቃችሁን ለምንድን ነው? ንጉሣችንን ለመመለስ ቅድሚያ ሊሰጠን አይገባም ነበር?” ይሁንና ከእስራኤል ሰዎች ቃል ይልቅ የይሁዳ ሰዎች ቃል አሸነፈ።
በዓመቱ መባቻ፣ ነገሥታት ለውጊያ በሚዘምቱበት ወቅት ዳዊት አሞናውያንን እንዲያጠፉ ኢዮዓብን፣ አገልጋዮቹንና መላውን የእስራኤል ሠራዊት ላከ፤ እነሱም ራባን ከበቡ፤ በዚህ ጊዜ ዳዊት ኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር።
አንድ ቀን ምሽት፣ ዳዊት ከአልጋው ተነስቶ በንጉሡ ቤት ሰገነት ላይ ይንጎራደድ ነበር። በሰገነቱ ላይ ሳለም አንዲት ሴት ገላዋን ስትታጠብ አየ፤ እሷም በጣም ውብ ነበረች።
ዳዊትም ስለ ሴትየዋ ማንነት እንዲጠይቅ አንድ ሰው ላከ፤ ሰውየውም “ሴቲቱ የኤሊያም ልጅ፣ የሂታዊው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ ናት” ብሎ ነገረው።
ከዚያም ዳዊት ሴትየዋን እንዲያመጧት መልእክተኞችን ላከ። እሷም ወደ እሱ ገባች፤ አብሯትም ተኛ። (ይህ የሆነው ራሷን ከርኩሰቷ እያነጻች ሳለ ነበር።) በኋላም ሴትየዋ ወደ ቤቷ ተመለሰች።
ሴትየዋም ፀነሰች፤ ለዳዊትም “አርግዣለሁ” የሚል መልእክት ላከችበት።
በዚህ ጊዜ ዳዊት “ሂታዊውን ኦርዮን ወደ እኔ ላከው” በማለት ወደ ኢዮዓብ መልእክት ላከበት። በመሆኑም ኢዮዓብ ኦርዮን ወደ ዳዊት ላከው።
ኦርዮም በመጣ ጊዜ ዳዊት ስለ ኢዮዓብ ደህንነት፣ ስለ ሠራዊቱ ሁኔታና ጦርነቱ እንዴት እየተካሄደ እንዳለ ጠየቀው።
ከዚያም ዳዊት ኦርዮን “እንግዲህ ወደ ቤትህ ውረድና ዘና በል” አለው። ኦርዮ ከንጉሡ ቤት ወጥቶ በሄደ ጊዜ የንጉሡ የደግነት ስጦታ ተላከለት።
ኦርዮ ግን ከሌሎቹ የጌታው አገልጋዮች ጋር በንጉሡ ቤት ደጃፍ ላይ ተኛ እንጂ ወደ ቤቱ አልወረደም።
በመሆኑም ለዳዊት “ኦርዮ እኮ ወደ ቤቱ አልወረደም” ብለው ነገሩት። በዚህ ጊዜ ዳዊት ኦርዮን “ከመንገድ ገና መግባትህ አይደለም እንዴ? ታዲያ ወደ ቤትህ ያልወረድከው ለምንድን ነው?” አለው።
ኦርዮም ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ታቦቱም ሆነ እስራኤልና ይሁዳ ያሉት ዳስ ውስጥ ነው፤ ጌታዬ ኢዮዓብና የጌታዬ አገልጋዮችም አውላላ ሜዳ ላይ ሰፍረዋል። ታዲያ እኔ ለመብላትና ለመጠጣት፣ ከሚስቴም ጋር ለመተኛት ወደ ቤቴ ልሂድ? በአንተና በሕያውነትህ እምላለሁ ይህን ፈጽሞ አላደርገውም!”
ከዚያም ዳዊት ኦርዮን “እንግዲያውስ ዛሬን እዚህ ቆይና ነገ አሰናብትሃለሁ” አለው። በመሆኑም ኦርዮ ያን ቀንና ቀጣዩን ቀን ኢየሩሳሌም ቆየ።
ዳዊትም አብሮት እንዲበላና እንዲጠጣ አስጠራው፤ አሰከረውም። ሆኖም ኦርዮ ምሽት ላይ ከጌታው አገልጋዮች ጋር ለመተኛት ወጥቶ ወደ መኝታው ሄደ እንጂ ወደ ቤቱ አልወረደም።
ሲነጋም ዳዊት ለኢዮዓብ ደብዳቤ ጽፎ በኦርዮ እጅ ላከለት።
በደብዳቤውም ላይ “ኦርዮን ውጊያው በተፋፋመበት ግንባር መድበው። እሱም ተመቶ እንዲሞት እናንተ ከኋላው አፈግፍጉ” ብሎ ጻፈ።
ኢዮዓብም ከተማዋን በጥንቃቄ ይመለከት ነበር፤ ኦርዮንም ኃይለኛ ተዋጊዎች እንዳሉበት በሚያውቀው ግንባር መደበው።
የከተማዋም ሰዎች ወጥተው ከኢዮዓብ ጋር ሲዋጉ ከዳዊት አገልጋዮች መካከል አንዳንዶቹ ወደቁ፤ ከሞቱትም ሰዎች መካከል ሂታዊው ኦርዮ ይገኝበታል።
ከዚያም ኢዮዓብ የጦርነቱን አጠቃላይ ሁኔታ የሚገልጽ ወሬ ለዳዊት ላከ።