text
stringlengths
4
267
መልእክተኛውንም እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “አጠቃላይ የጦርነቱን ሁኔታ ለንጉሡ ነግረህ ስትጨርስ
ንጉሡ ሊቆጣና እንዲህ ሊልህ ይችላል፦ ‘ከተማዋን ለመውጋት ይህን ያህል የተጠጋችሁት ለምንድን ነው? ቅጥሩ አናት ላይ ሆነው እንደሚወነጭፉባችሁ አታውቁም?
የየሩቤሼትን ልጅ አቢሜሌክን የገደለው ማን ሆነና ነው? በቅጥሩ አናት ላይ ሆና መጅ በመልቀቅ በቴቤጽ የገደለችው አንዲት ሴት አይደለችም? ታዲያ እናንተ ይህን ያህል ወደ ቅጥሩ የተጠጋችሁት ለምንድን ነው?’ በዚህ ጊዜ ‘አገልጋይህ ሂታዊው ኦርዮም ሞቷል’ በለው።”
በመሆኑም መልእክተኛው ተነስቶ ሄደ፤ ኢዮዓብ የላከውንም መልእክት ሁሉ ለዳዊት ነገረው።
መልእክተኛውም ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ሰዎቹ አየሉብን፤ እኛንም ለመውጋት ወደ ሜዳው ወጡ፤ እኛ ግን እስከ ከተማው መግቢያ ድረስ እንዲያፈገፍጉ አደረግናቸው።
ቀስተኞቹም ቅጥሩ አናት ላይ ሆነው በአገልጋዮችህ ላይ ቀስት ያስወነጭፉ ጀመር፤ በዚህም የተነሳ ከንጉሡ አገልጋዮች መካከል አንዳንዶቹ ተገደሉ፤ አገልጋይህ ሂታዊው ኦርዮም ሞተ።”
በዚህ ጊዜ ዳዊት መልእክተኛውን “ኢዮዓብን እንዲህ በለው፦ ‘መቼም ሰይፍ አንዱን እንደሚበላ ሁሉ ሌላውንም ስለሚበላ ይህ ሁኔታ አይረብሽህ። ብቻ አንተ በከተማዋ ላይ ውጊያህን በማፋፋም በቁጥጥር ሥር አውላት።’ አንተም አበረታታው” አለው።
የኦርዮ ሚስት ባሏ መሞቱን ስትሰማ ለባለቤቷ አለቀሰችለት።
የሐዘኑ ጊዜ እንዳበቃም ዳዊት ልኮ ወደ ቤቱ አስመጣት፤ እሷም ሚስቱ ሆነች፤ ወንድ ልጅም ወለደችለት። ሆኖም ዳዊት ያደረገው ነገር ይሖዋን በጣም አሳዝኖት ነበር።
ሳኦል ከሞተ በኋላ ዳዊት አማሌቃውያንን ድል አድርጎ ሲመለስ በጺቅላግ ሁለት ቀን ቆየ።
በሦስተኛውም ቀን አንድ ሰው ልብሱን ቀዶና በራሱ ላይ አቧራ ነስንሶ ከሳኦል ሰፈር መጣ። እሱም ዳዊት ጋ ሲደርስ መሬት ላይ ተደፍቶ ሰገደ።
ዳዊትም “ከየት ነው የመጣኸው?” ሲል ጠየቀው፤ እሱም “ከእስራኤል ሰፈር አምልጬ ነው” በማለት መለሰለት።
ዳዊትም “እስቲ የሆነውን ነገር ንገረኝ” አለው። እሱም “ሰዎቹ ከውጊያው ሸሽተዋል፤ ብዙዎቹም ወድቀዋል፤ ሞተዋል። ሳኦልና ልጁ ዮናታንም እንኳ ሞተዋል” አለው።
ከዚያም ዳዊት ወሬውን ያመጣለትን ወጣት “ለመሆኑ ሳኦልና ልጁ ዮናታን መሞታቸውን እንዴት አወቅክ?” ሲል ጠየቀው።
ወጣቱም እንዲህ አለው፦ “እንደ አጋጣሚ ሆኖ ጊልቦአ ተራራ ላይ ነበርኩ፤ እዚያም ሳኦል ጦሩን ተመርኩዞ ቆሞ ነበር፤ ሠረገሎቹና ፈረሰኞቹም ደረሱበት።
ወደ ኋላም ዞር ብሎ ሲያየኝ ጠራኝ፤ እኔም ‘አቤት!’ አልኩት።
እሱም ‘አንተ ማን ነህ?’ አለኝ፤ እኔም ‘አማሌቃዊ ነኝ’ አልኩት።
ከዚያም ‘ሕይወቴ ያላለፈች ቢሆንም ከባድ ሥቃይ ላይ ስለሆንኩ እባክህ ላዬ ላይ ቁምና ግደለኝ’ አለኝ።
በመሆኑም መቼም ቆስሎ ከወደቀ በኋላ እንደማይተርፍ ስላወቅኩ ላዩ ላይ ቆሜ ገደልኩት። ከዚያም ራሱ ላይ ያለውን ዘውድና ክንዱ ላይ የነበረውን አምባር ወስጄ ወደ ጌታዬ ይዤ መጣሁ።”
በዚህ ጊዜ ዳዊት ልብሱን ቀደደ፤ አብረውት ያሉትም ሰዎች ሁሉ እንደዚሁ አደረጉ።
ከዚያም ለሳኦል፣ ለልጁ ለዮናታን፣ ለይሖዋ ሕዝብና ለእስራኤል ቤት እስከ ማታ ድረስ ጮኹ፣ አለቀሱ እንዲሁም ጾሙ፤ በሰይፍ ወድቀዋልና።
ዳዊትም ወሬውን ያመጣለትን ወጣት “የየት አገር ሰው ነህ?” አለው። እሱም “የባዕድ አገር ሰው የሆነ የአንድ አማሌቃዊ ልጅ ነኝ” አለው።
ከዚያም ዳዊት “ይሖዋ የቀባውን ለመግደል እጅህን ስታነሳ እንዴት አልፈራህም?” አለው።
ዳዊትም ከወጣቶቹ መካከል አንዱን ጠርቶ “በል ቅረብና ምታው” አለው። እሱም መታው፤ ወጣቱም ሞተ።
ከዚያም ዳዊት “‘ይሖዋ የቀባውን እኔ ራሴ ገድዬዋለሁ’ በማለት የገዛ አፍህ ስለመሠከረብህ ደምህ በራስህ ላይ ነው” አለው።
ዳዊትም ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን ይህን የሐዘን እንጉርጉሮ ተቀኘ፤
እንዲሁም በያሻር መጽሐፍ ተጽፎ የሚገኘውን “ቀስት” የተባለውን ሙሾ የይሁዳ ልጆች እንዲማሩ አዘዘ።
“እስራኤል ሆይ፣ ውበት በኮረብቶችህ ላይ ተገድሎ ተጋድሟል። ኃያላኑ እንዴት እንዲህ ይውደቁ!
ይህን በጌት አትናገሩ፤በአስቀሎን ጎዳናዎችም ላይ አታውጁ፤አለዚያ የፍልስጤም ሴቶች ልጆች ይደሰታሉ፣የእነዚያ ያልተገረዙ ሰዎች ሴቶች ልጆችም ይፈነድቃሉ።
እናንተ የጊልቦአ ተራሮች፣ጠል አያረስርሳችሁ ወይም ዝናብ አይዝነብባችሁ፣ለቅዱስ መዋጮዎች የሚሆን እህል የሚያበቅሉ ማሳዎችም አይገኙባችሁ፣በዚያ የኃያላኑ ጋሻ ረክሷልና፣የሳኦልም ጋሻ ከእንግዲህ በዘይት አይወለወልም።
ከተገደሉት ሰዎች ደም፣ ከኃያላኑ ስብ፣የዮናታን ቀስት አልተመለሰም፤የሳኦልም ሰይፍ ድል ሳያደርግ አይመለስም።
ሳኦልና ዮናታን በሕይወት ሳሉ የሚወደዱና የሚደነቁ ነበሩ፤ሲሞቱም አልተለያዩም። ከንስር ይልቅ ፈጣኖች፣ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ።
እናንተ የእስራኤል ሴቶች ልጆች፣የተንቆጠቆጡ ደማቅ ቀይ ልብሶችን ላለበሳችሁ፣ልብሶቻችሁንም በወርቅ ላስጌጠላችሁ ለሳኦል አልቅሱ።
ኃያላኑ በጦርነት ላይ እንዴት እንዲህ ይውደቁ! ዮናታን በኮረብቶችህ ላይ ተገድሎ ተጋድሟል!
ወንድሜ ዮናታን፣ በአንተ የተነሳ ተጨንቄአለሁ፤አንተ በእኔ ዘንድ እጅግ የተወደድክ ነበርክ። የአንተ ፍቅር ለእኔ ከሴት ፍቅር ይበልጥ ነበር።
ኃያላኑ እንዴት እንዲህ ይውደቁ፤የጦር መሣሪያዎቹስ እንዴት እንዲህ ይጥፉ!”
ንጉሡ በራሱ ቤት መኖር በጀመረና ይሖዋም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ እረፍት በሰጠው ጊዜ
ነቢዩ ናታንን “የእውነተኛው አምላክ ታቦት በድንኳን ውስጥ ተቀምጦ ሳለ ይኸው እኔ ከአርዘ ሊባኖስ በተሠራ ቤት ውስጥ እየኖርኩ ነው” አለው።
ናታንም ንጉሡን “ይሖዋ ከአንተ ጋር ስለሆነ ሄደህ በልብህ ያለውን ነገር ሁሉ አድርግ” አለው።
በዚያው ሌሊት የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ናታን መጣ፦
“ሂድና አገልጋዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “አንተ የምኖርበትን ቤት መሥራት ይኖርብሃል?
እስራኤላውያንን ከግብፅ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳንና በማደሪያ ድንኳን እጓዝ ነበር እንጂ በቤት ውስጥ አልኖርኩም።
ከእስራኤላውያን ሁሉ ጋር በተጓዝኩበት ጊዜ በሙሉ ሕዝቤን እስራኤልን እረኛ ሆነው እንዲጠብቁ ከሾምኳቸው የነገድ መሪዎች መካከል ‘በአርዘ ሊባኖስ ቤት ያልሠራህልኝ ለምንድን ነው?’ ያልኩት ማን አለ?”’
አሁንም አገልጋዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ እንድትሆን መንጋ ከምትጠብቅበት ስፍራ ወሰድኩህ።
እኔም በምትሄድበት ሁሉ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋለሁ፤ ስምህንም በምድር ላይ እንዳሉ ታላላቅ ሰዎች ስም ገናና አደርገዋለሁ።
ለሕዝቤ ለእስራኤል ቦታ እሰጣቸዋለሁ፤ ተረጋግተው እንዲቀመጡም አደርጋለሁ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ከእንግዲህም የሚረብሻቸው አይኖርም፤ ክፉዎች እንደቀድሞው ዳግመኛ አይጨቁኗቸውም፤
በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሳፍንትን ከሾምኩበት ጊዜ አንስቶ ሲያደርጉ እንደነበሩት አያደርጉባቸውም። እኔም ከጠላቶችህ ሁሉ እረፍት እሰጥሃለሁ። “‘“በተጨማሪም ይሖዋ ቤት እንደሚሠራልህ ይሖዋ ራሱ ነግሮሃል።
የሕይወት ዘመንህ አብቅቶ ከአባቶችህ ጋር በምታንቀላፋበት ጊዜ ከአንተ በኋላ ከአብራክህ የሚወጣውን ዘርህን አስነሳለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ።
ለስሜ የሚሆን ቤት የሚሠራልኝ እሱ ነው፤ እኔም የመንግሥቱን ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ።
አባት እሆነዋለሁ፤ እሱም ልጄ ይሆናል። ጥፋት በሚያጠፋበት ጊዜም በሰዎች በትር፣ በሰው ልጆች አለንጋ እቀጣዋለሁ።
ከፊትህ ካስወገድኩት ከሳኦል ላይ ታማኝ ፍቅሬን እንደወሰድኩ ከእሱ ላይ አይወሰድም።
ቤትህና መንግሥትህ ለዘላለም በፊትህ ጸንቶ ይኖራል፤ ዙፋንህም ለዘላለም የጸና ይሆናል።”’”
ናታንም ይህን ቃል ሁሉና ይህን ራእይ በሙሉ ለዳዊት ነገረው።
በዚህ ጊዜ ንጉሥ ዳዊት ገብቶ በይሖዋ ፊት ተቀመጠ፤ እንዲህም አለ፦ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ኧረ ለመሆኑ እኔ ማን ነኝ? እስከዚህ ድረስ ያደረስከኝስ ቤቴ ምን ስለሆነ ነው?
ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ይህ ሳያንስ ስለ አገልጋይህ ቤት ገና ወደፊት የሚሆነውንም ነገር ተናገርክ፤ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ይህ ለሰው ዘር ሁሉ የተሰጠ መመሪያ ነው።
ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ታዲያ አገልጋይህ ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ሊልህ ይችላል? አንተ በሚገባ ታውቀኝ የለ?
ለቃልህ ስትል፣ ከልብህ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እነዚህን ሁሉ ታላላቅ ነገሮች ፈጽመሃል፤ እንዲሁም ለአገልጋይህ ገልጠህለታል።
ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ በእርግጥም ታላቅ የሆንከው ለዚህ ነው። እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤ ከአንተ በቀር አምላክ የለም፤ በጆሯችን የሰማነው ነገር ሁሉ ይህን ያረጋግጣል።
በምድር ላይ እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ ሌላ ብሔር ማን አለ? አምላክ ሄዶ ለእነሱ ሲል ታላላቅና አስፈሪ ነገሮችን በመፈጸም እንዲሁም ስሙን በማስጠራት ሕዝቡ አድርጎ ዋጃቸው። ከግብፅ ለዋጀኸው ሕዝብ ስትል ብሔራትንና አማልክታቸውን አባረርክ።
ሕዝብህን እስራኤልን እስከ ወዲያኛው የራስህ ሕዝብ አድርገህ አጸናኸው፤ ይሖዋ ሆይ፣ አንተም አምላኩ ሆንክ።
“አሁንም ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ አገልጋይህንና ቤቱን በተመለከተ የገባኸውን ቃል እስከ ወዲያኛው ፈጽም፤ ቃል እንደገባኸውም አድርግ።
ሰዎች ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በእስራኤል ላይ አምላክ ነው’ እንዲሉ ስምህ ለዘላለም ከፍ ከፍ ይበል፤ የአገልጋይህም የዳዊት ቤት በፊትህ የጸና ይሁን።
የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ‘ለአንተ ቤት እሠራልሃለሁ’ በማለት ለአገልጋይህ ራእይ ገልጠህለታል። አገልጋይህ ይህን ጸሎት ወደ አንተ ለማቅረብ ድፍረት ያገኘው በዚህ ምክንያት ነው።
አሁንም ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ እውነተኛው አምላክ አንተ ነህ፤ ቃልህ እውነት ነው፤ ለአገልጋይህም እነዚህን መልካም ነገሮች ለማድረግ ቃል ገብተህለታል።
በመሆኑም የአገልጋይህን ቤት እባክህ ባርክ፤ በፊትህም ለዘላለም የጸና ይሁን፤ ምክንያቱም ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ራስህ ቃል ገብተሃል፤ በአንተም በረከት የአገልጋይህ ቤት ለዘላለም የተባረከ ይሁን።”
የዳዊት ልጅ አቢሴሎም ትዕማር የምትባል ቆንጆ እህት ነበረችው፤ የዳዊት ልጅ አምኖንም ወደዳት።
አምኖን በእህቱ በትዕማር ምክንያት በጣም ከመጨነቁ የተነሳ ታመመ፤ ምክንያቱም ድንግል ስለነበረች በእሷ ላይ ምንም ነገር ማድረግ እንደማይችል ሆኖ ተሰምቶት ነበር።
አምኖን፣ ኢዮናዳብ የተባለ ጓደኛ ነበረው፤ እሱም የዳዊት ወንድም የሆነው የሺምአህ ልጅ ነው፤ ኢዮናዳብም ብልህ ሰው ነበር።
እሱም አምኖንን “አንተ የንጉሥ ልጅ፣ በየቀኑ እንዲህ የምትጨነቀው ለምንድን ነው? ለምን አትነግረኝም?” አለው። አምኖንም “የወንድሜን የአቢሴሎምን እህት ትዕማርን አፍቅሬ ነው” አለው።
በዚህ ጊዜ ኢዮናዳብ እንዲህ አለው፦ “የታመምክ መስለህ አልጋህ ላይ ተኛ። አባትህም ሊጠይቅህ ሲመጣ ‘እባክህ፣ እህቴ ትዕማር መጥታ ምግብ ትስጠኝ። ለታመመ ሰው የሚሆነውን ምግብ እዚሁ እያየኋት ታዘጋጅልኝና በእጇ ታጉርሰኝ’ በለው።”
ስለዚህ አምኖን የታመመ መስሎ ተኛ፤ ንጉሡም ሊጠይቀው መጣ። ከዚያም አምኖን ንጉሡን “እባክህ፣ እህቴ ትዕማር ትምጣና እዚሁ እያየኋት ሁለት ቂጣ ጋግራ በእጇ ታጉርሰኝ” አለው።
ዳዊትም “እባክሽ፣ ወደ ወንድምሽ ወደ አምኖን ቤት ሄደሽ ምግብ አዘጋጂለት” ብለው ለትዕማር እንዲነግሯት ወደ ቤት መልእክት ላከ።
በመሆኑም ትዕማር ወደ ወንድሟ ወደ አምኖን ቤት ሄደች፤ እሱም እዚያ ተኝቶ ነበር። እሷም ሊጥ ካቦካች በኋላ እዚያው እያየ ጠፍጥፋ ጋገረችው።
ከዚያም መጋገሪያውን አውጥታ ቂጣውን አቀረበችለት። አምኖን ግን ለመብላት ፈቃደኛ አልሆነም፤ እሱም “ሁሉንም ሰው ከዚህ አስወጡልኝ!” አለ። ስለዚህ ሁሉም ሰው ትቶት ወጣ።
በዚህ ጊዜ አምኖን ትዕማርን “በእጅሽ እንድታጎርሺኝ ምግቡን ወደ መኝታ ክፍል አምጪልኝ” አላት። ትዕማርም የጋገረችውን ቂጣ ይዛ ወንድሟ አምኖን ወደነበረበት መኝታ ክፍል ገባች።
እሷም ምግቡን እንዲበላ ስታቀርብለት አፈፍ አድርጎ ያዛትና “እህቴ ሆይ፣ ነይ፣ አብረሽኝ ተኚ” አላት።
እሷ ግን እንዲህ አለችው፦ “ወንድሜ ሆይ፣ ይሄማ ፈጽሞ አይሆንም! እባክህ አታዋርደኝ፤ በእስራኤል ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር ተደርጎ አያውቅም። ይህን አሳፋሪ ድርጊት አትፈጽም።
እኔስ ብሆን ይህን ነውሬን ተሸክሜ እንዴት እኖራለሁ? አንተም ብትሆን በእስራኤል ውስጥ ካሉት ወራዳ ሰዎች እንደ አንዱ ትቆጠራለህ። ስለዚህ አሁን፣ እባክህ ንጉሡን አነጋግረው፤ እሱም ቢሆን እኔን አይከለክልህም።”
እሱ ግን ሊሰማት ፈቃደኛ አልሆነም፤ ከዚህ ይልቅ ኃይል ተጠቅሞ በማስነወር አዋረዳት።
ከዚያም አምኖን እጅግ በጣም ጠላት፤ ለእሷ ያደረበት ጥላቻም ለእሷ ከነበረው ፍቅር በለጠ። አምኖንም “ተነሽ ውጭልኝ!” አላት።
በዚህ ጊዜ “ወንድሜ ሆይ፣ ይሄማ አይሆንም፤ አሁን እኔን ማባረርህ ቀደም ሲል ከፈጸምክብኝ ነገር የከፋ ይሆናል!” አለችው። እሱ ግን ሊሰማት ፈቃደኛ አልሆነም።
ከዚያም አምኖን የሚያገለግለውን ወጣት ጠርቶ “እባክህ ይህችን ሴት ከፊቴ አስወጣና በሩን ዝጋባት” አለው።
(እሷም የሚያምር ልብስ ለብሳ ነበር፤ ምክንያቱም ድንግል የሆኑት የንጉሡ ሴቶች ልጆች እንዲህ ዓይነት ልብስ ይለብሱ ነበር።) በመሆኑም አገልጋዩ ወደ ውጭ አስወጥቶ በሩን ዘጋባት።
ከዚያም ትዕማር ራሷ ላይ አመድ ነሰነሰች፤ የለበሰችውንም የሚያምር ቀሚስ ቀደደች፤ በእጇም ራሷን ይዛ እያለቀሰች ሄደች።
በዚህ ጊዜ ወንድሟ አቢሴሎም “ወንድምሽ አምኖን ከአንቺ ጋር ነበር? እህቴ ሆይ፣ በቃ አሁን ዝም በይ። እንግዲህ እሱ ወንድምሽ ነው። ይህን ነገር በልብሽ አታብሰልስዪው” አላት። ከዚያም ትዕማር ከሌሎች ተገልላ በወንድሟ በአቢሴሎም ቤት ተቀመጠች።
ንጉሥ ዳዊት የሆነውን ነገር ሁሉ ሲሰማ እጅግ ተቆጣ። ሆኖም አምኖን የበኩር ልጁ በመሆኑ በጣም ይወደው ስለነበር ሊያስቀይመው አልፈለገም።
አቢሴሎምም አምኖንን ክፉም ሆነ ደግ አልተናገረውም፤ ምክንያቱም አቢሴሎም፣ አምኖን እህቱን ትዕማርን ስላዋረዳት ጠልቶት ነበር።
ድፍን ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ እንዲህ ሆነ፤ አቢሴሎም በኤፍሬም አቅራቢያ ባለችው በበዓልሃጾር በጎቹን ያሸልት ነበር፤ አቢሴሎምም የንጉሡን ወንዶች ልጆች በሙሉ ጋበዘ።
በመሆኑም አቢሴሎም ወደ ንጉሡ ገብቶ “አገልጋይህ በጎቹን እያሸለተ ነው። እባክህ፣ ንጉሡና አገልጋዮቹ ከእኔ ጋር ይሂዱ” አለው።
ንጉሡ ግን አቢሴሎምን “የእኔ ልጅ፣ ይሄማ አይሆንም! ሁላችንም ከሄድን ሸክም እንሆንብሃለን” አለው። አቢሴሎም አጥብቆ ቢለምነውም ንጉሡ ለመሄድ ፈቃደኛ አልሆነም፤ ከዚህ ይልቅ ባረከው።
ከዚያም አቢሴሎም “እሺ አንተ ካልሄድክ እባክህ ወንድሜ አምኖን አብሮን ይሂድ” አለው። ንጉሡም “ከአንተ ጋር የሚሄደው ለምንድን ነው?” አለው።
አቢሴሎም ግን አጥብቆ ለመነው፤ በመሆኑም ዳዊት አምኖንንና የንጉሡን ወንዶች ልጆች በሙሉ ላካቸው።
ከዚያም አቢሴሎም አገልጋዮቹን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፣ እኔም አምኖን የወይን ጠጅ ጠጥቶ ሞቅ ሲለው ‘አምኖንን ምቱት!’ እላችኋለሁ። እናንተም ትገድሉታላችሁ። አትፍሩ፤ የማዛችሁ እኔ አይደለሁም? በርቱ! ደፋሮች ሁኑ!”
በመሆኑም የአቢሴሎም አገልጋዮች በአምኖን ላይ ልክ አቢሴሎም እንዳዘዛቸው አደረጉበት፤ ከዚያም ሌሎቹ የንጉሡ ልጆች በሙሉ ተነስተው በየበቅሏቸው ላይ በመቀመጥ ሸሹ።
ገና በመንገድ ላይ ሳሉም ዳዊት “አቢሴሎም የንጉሡን ልጆች በሙሉ ፈጃቸው፤ አንድም የተረፈ ሰው የለም” የሚል ወሬ ደረሰው።
በዚህ ጊዜ ንጉሡ ተነሳ፤ ልብሱንም ቀዶ መሬት ላይ ተዘረረ፤ አገልጋዮቹም በሙሉ ልብሳቸውን ቀደው አጠገቡ ቆመው ነበር።
ሆኖም የዳዊት ወንድም የሺምአህ ልጅ የሆነው ኢዮናዳብ እንዲህ አለ፦ “ጌታዬ ወጣቶቹን የንጉሡን ወንዶች ልጆች በሙሉ እንደገደሏቸው አድርጎ አያስብ፤ ምክንያቱም የሞተው አምኖን ብቻ ነው። ይህም በአቢሴሎም ትእዛዝ የተፈጸመ ነው፤ እሱ፣ አምኖን እህቱን ትዕማርን ካስነወረበት ቀን አንስቶ ይህን ነገር ለማድረግ ወስኖ ነበር።
አሁንም ጌታዬ ንጉሡ ‘የንጉሡ ወንዶች ልጆች በሙሉ አልቀዋል’ ለሚለው ወሬ ጆሮ አይስጥ፤ የሞተው አምኖን ብቻ ነው።”
ይህ በእንዲህ እንዳለ አቢሴሎም ሸሸ። በኋላም ጠባቂው ቀና ብሎ ሲመለከት ከበስተኋላው ባለው ከተራራው አጠገብ በሚገኘው መንገድ ላይ ብዙ ሰዎች ሲመጡ አየ።
በዚህ ጊዜ ኢዮናዳብ ንጉሡን “ይኸው፣ የንጉሡ ወንዶች ልጆች ተመልሰው መጥተዋል። የሆነውም ነገር ልክ አገልጋይህ እንደተናገረው ነው” አለው።