text stringlengths 4 267 |
|---|
እሱም ተናግሮ እንደጨረሰ የንጉሡ ወንዶች ልጆች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እያለቀሱ ገቡ፤ ንጉሡና አገልጋዮቹም በሙሉ አምርረው አለቀሱ። |
አቢሴሎም ግን ኮብልሎ የገሹር ንጉሥ ወደሆነው ወደ አሚሁድ ልጅ ወደ ታልማይ ሄደ። ዳዊትም ለልጁ ብዙ ቀናት አለቀሰ። |
አቢሴሎም ሸሽቶ ወደ ገሹር ከሄደ በኋላ በዚያ ሦስት ዓመት ተቀመጠ። |
በመጨረሻም የንጉሥ ዳዊት ነፍስ አቢሴሎምን ለማየት ናፈቀች፤ ምክንያቱም ዳዊት የአምኖን ሞት ካስከተለበት ሐዘን ተጽናንቶ ነበር። |
በዳዊት ዘመን ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ረሃብ ሆነ፤ ስለዚህ ዳዊት ይሖዋን ምክር ጠየቀ፤ ይሖዋም “ሳኦል ገባኦናውያንን ስለገደለ እሱም ሆነ ቤቱ የደም ዕዳ አለባቸው” አለ። |
በመሆኑም ንጉሡ ገባኦናውያንን ጠርቶ አነጋገራቸው። (እርግጥ ገባኦናውያን ከአሞራውያን የተረፉ ናቸው እንጂ እስራኤላውያን አልነበሩም፤ እስራኤላውያንም እንደማያጠፏቸው ምለውላቸው ነበር፤ ይሁንና ሳኦል ለእስራኤልና ለይሁዳ ሕዝብ ባለው ቅንዓት ተነሳስቶ ሊያጠፋቸው ፈልጎ ነበር።) |
ዳዊትም ገባኦናውያንን “የይሖዋን ርስት እንድትባርኩ ምን ላድርግላችሁ? ማስተሰረይስ የምችለው እንዴት ነው?” አላቸው። |
ገባኦናውያንም “ከሳኦልና ከእሱ ቤት ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ችግር በብርና በወርቅ የሚፈታ አይደለም፤ ደግሞም በእስራኤል ውስጥ ማንንም ሰው የመግደል መብት የለንም” አሉት። በዚህ ጊዜ ዳዊት “ያላችሁትን ሁሉ አደርግላችኋለሁ” አላቸው። |
እነሱም ንጉሡን እንዲህ አሉት፦ “ለጥፋት ከዳረገንና በየትኛውም የእስራኤል ግዛት ውስጥ እንዳንኖር እኛን ለመደምሰስ ሴራ ከጠነሰሰብን ሰው |
ወንዶች ልጆች መካከል ሰባቱ ይሰጡን። እኛም በይሖዋ የተመረጠው የሳኦል አገር በሆነችው በጊብዓ በድናቸውን በይሖዋ ፊት እንሰቅላለን።” ከዚያም ንጉሡ “እሺ፣ እሰጣችኋለሁ” አላቸው። |
ሆኖም ንጉሡ እሱና የሳኦል ልጅ ዮናታን በይሖዋ ፊት በተማማሉት መሐላ የተነሳ የሳኦል ልጅ ለሆነው ለዮናታን ልጅ ለሜፊቦስቴ ራራለት። |
በመሆኑም ንጉሡ የአያ ልጅ ሪጽፋ ለሳኦል የወለደችለትን ሁለት ወንዶች ልጆች ማለትም አርሞኒንና ሜፊቦስቴን እንዲሁም የሳኦል ልጅ ሜልኮል የመሆላታዊው የቤርዜሊ ልጅ ለሆነው ለአድሪዔል የወለደችለትን አምስት ወንዶች ልጆች ወሰደ። |
ከዚያም ለገባኦናውያኑ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነሱም በድናቸውን በተራራው ላይ በይሖዋ ፊት ሰቀሉ። ሰባቱም አንድ ላይ ሞቱ፤ የተገደሉትም አዝመራ በሚሰበሰብባቸው የመጀመሪያዎቹ ቀናት ይኸውም የገብስ አዝመራ መሰብሰብ በሚጀምርበት ጊዜ ነበር። |
ከዚያም የአያ ልጅ ሪጽፋ ከመከር ወቅት መጀመሪያ አንስቶ በበድኖቹ ላይ ከሰማይ ዝናብ እስከሚወርድበት ጊዜ ድረስ ማቅ ወስዳ በዓለቱ ላይ አነጠፈች፤ ቀን የሰማይ አሞሮች እንዲያርፉባቸው፣ ሌሊት ደግሞ የዱር አራዊት እንዲጠጓቸው አልፈቀደችም። |
በኋላም የሳኦል ቁባት የሆነችው የአያ ልጅ ሪጽፋ ያደረገችው ነገር ለዳዊት ተነገረው። |
ስለዚህ ዳዊት ሄዶ የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አፅም ከኢያቢስጊልያድ መሪዎች ላይ ወሰደ፤ እነዚህ ሰዎች አፅሙን ፍልስጤማውያን ሳኦልን በጊልቦአ በገደሉበት ቀን እሱንና ዮናታንን ከሰቀሉበት ከቤትሻን አደባባይ ሰርቀው ወስደው ነበር። |
እሱም የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አፅም ከዚያ አመጣ፤ በተጨማሪም የተገደሉትን ሰዎች አፅም ሰበሰቡ። |
ከዚያም የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አፅም በቢንያም ምድር በጸላ በሚገኘው በሳኦል አባት በቂስ የመቃብር ስፍራ ቀበሩት። ንጉሡ ያዘዘውን ነገር ሁሉ ከፈጸሙም በኋላ አምላክ ስለ ምድሪቱ ያቀረቡትን ልመና ሰማ። |
በፍልስጤማውያንና በእስራኤላውያን መካከል እንደገና ጦርነት ተነሳ። በመሆኑም ዳዊትና አገልጋዮቹ ወርደው ፍልስጤማውያንን ወጉ፤ በዚህ ጊዜ ዳዊት ዛለ። |
ከረፋይም ዘር የሆነው እንዲሁም 300 ሰቅል የሚመዝን የመዳብ ጦርና አዲስ ሰይፍ የታጠቀው ይሽቢብኖብ ዳዊትን ለመግደል አሰበ። |
የጽሩያ ልጅ አቢሳም ወዲያውኑ ደረሰለት፤ ፍልስጤማዊውንም መትቶ ገደለው። በዚያን ጊዜ የዳዊት ሰዎች “ከአሁን በኋላ ከእኛ ጋር ወደ ውጊያ መውጣት የለብህም! የእስራኤልን መብራት አታጥፋ!” በማለት ማሉለት። |
ከዚህም በኋላ እንደገና ከፍልስጤማውያን ጋር በጎብ ጦርነት ተከፈተ። በዚህ ጊዜ ሁሻዊው ሲበካይ የረፋይም ዘር የሆነውን ሳፍን ገደለው። |
ዳግመኛም ከፍልስጤማውያን ጋር በጎብ ጦርነት ተቀሰቀሰ፤ የቤተልሔማዊው የያአሬዖርጊም ልጅ ኤልሃናን የሸማኔ መጠቅለያ የሚመስል ዘንግ ያለው ጦር ይዞ የነበረውን ጌታዊውን ጎልያድን ገደለው። |
እንደገናም በጌት ጦርነት ተቀሰቀሰ፤ በዚያም በእጆቹ ላይ ስድስት ስድስት ጣቶች በእግሮቹም ላይ ስድስት ስድስት ጣቶች፣ በድምሩ 24 ጣቶች ያሉት በጣም ግዙፍ የሆነ ሰው ነበር፤ እሱም የረፋይም ዘር ነበር። |
ይህ ሰው እስራኤልን ይገዳደር ስለነበር የዳዊት ወንድም የሺምአይ ልጅ ዮናታን ገደለው። |
እነዚህ አራቱ በጌት የሚኖሩ የረፋይም ዘሮች ነበሩ፤ እነሱም በዳዊት እጅና በአገልጋዮቹ እጅ ወደቁ። |
በሳኦል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል የሚደረገው ውጊያ ለረጅም ጊዜ ዘለቀ፤ ዳዊት እየበረታ ሲሄድ የሳኦል ቤት ግን እየተዳከመ መጣ። |
በዚህ መሃል ዳዊት በኬብሮን ወንዶች ልጆች ተወለዱለት። የበኩር ልጁ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪኖዓም የወለደው አምኖን ነበር። |
ሁለተኛው ልጁ የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢጋኤል የወለደው ኪልአብ ሲሆን ሦስተኛው ልጁ ደግሞ የገሹር ንጉሥ የታልማይ ልጅ የሆነችው የማአካ ልጅ አቢሴሎም ነበር። |
አራተኛው ልጁ የሃጊት ልጅ አዶንያስ፣ አምስተኛው ልጁ ደግሞ የአቢጣል ልጅ ሰፋጥያህ ነበር። |
ስድስተኛው ልጁ ኤግላ ከተባለችው ሚስቱ የወለደው ይትረአም ነበር። እነዚህ ዳዊት በኬብሮን ሳለ የተወለዱለት ናቸው። |
በሳኦል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል የነበረው ጦርነት በቀጠለበት ወቅት አበኔር በሳኦል ቤት ውስጥ የነበረውን ቦታ እያጠናከረ ሄደ። |
ሳኦል የአያ ልጅ የሆነች ሪጽፋ የተባለች ቁባት ነበረችው። በኋላም ኢያቡስቴ አበኔርን “ከአባቴ ቁባት ጋር ግንኙነት የፈጸምከው ለምንድን ነው?” አለው። |
አበኔርም በኢያቡስቴ ንግግር እጅግ ተቆጥቶ እንዲህ አለ፦ “እኔ ከይሁዳ ወገን የሆንኩ የውሻ ጭንቅላት ነኝ? እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ ለአባትህ ለሳኦል ቤት፣ ለወንድሞቹና ለቅርብ ወዳጆቹ ታማኝ ፍቅር ከማሳየት ወደኋላ አላልኩም፤ አንተንም ለዳዊት አሳልፌ አልሰጠሁህም፤ ይኸው አንተ ግን ዛሬ በአንዲት ሴት የተነሳ ጥፋተኛ አድርገህ ትከሰኛለህ። |
ይሖዋ ለዳዊት እንደማለለት ሳላደርግለት ብቀር አምላክ በአበኔር ላይ ይህን ያድርግበት፤ ከዚህ የከፋም ያምጣበት፤ |
አምላክ መንግሥትን ከሳኦል ቤት እንደሚወስድ እንዲሁም የዳዊትን ዙፋን በእስራኤልና በይሁዳ ላይ ከዳን አንስቶ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እንደሚያጸና ምሏል።” |
ኢያቡስቴም አበኔርን ስለፈራው አንዲት ቃል እንኳ ሊመልስለት አልደፈረም። |
አበኔርም ወዲያውኑ ወደ ዳዊት መልእክተኞችን ልኮ “ምድሪቱ የማን ናት? ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን ግባ፤ መላው እስራኤል ከአንተ ጎን እንዲቆም የቻልኩትን ሁሉ አደርጋለሁ” አለው። |
እሱም እንዲህ አለው፦ “መልካም! ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ። ብቻ አንድ ነገር እንድታደርግልኝ እጠይቅሃለሁ፤ ወደ እኔ ስትመጣ የሳኦልን ልጅ ሜልኮልን ይዘህ ካልመጣህ በቀር ፊቴን እንደማታይ እወቅ” አለው። |
ከዚያም ዳዊት ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ “በ100 የፍልስጤማውያን ሸለፈት ያጨኋትን ሚስቴን ሜልኮልን ስጠኝ” ብለው እንዲነግሩት መልእክተኞችን ላከ። |
በመሆኑም ኢያቡስቴ መልእክተኛ ልኮ ሜልኮልን የላይሽ ልጅ ከሆነው ከባሏ ከፓልጢኤል ወሰዳት። |
ባሏ ግን እስከ ባሁሪም ድረስ እያለቀሰ ተከትሏት ሄደ። ከዚያም አበኔር “በቃ ሂድ፣ ተመለስ!” አለው። እሱም ተመለሰ። |
ይህ በእንዲህ እንዳለ አበኔር ለእስራኤል ሽማግሌዎች እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፦ “ቀድሞውንም ቢሆን ዳዊት በላያችሁ እንዲነግሥ ትፈልጉ ነበር። |
ይሖዋ ዳዊትን ‘ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጤማውያንና ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ የምታደገው በአገልጋዬ በዳዊት እጅ ነው’ ስላለው በሉ አሁን እርምጃ ውሰዱ።” |
ከዚያም አበኔር ቢንያማውያንን አነጋገራቸው። በተጨማሪም አበኔር እስራኤልና መላው የቢንያም ቤት ለማድረግ የተስማሙትን ነገር በኬብሮን ላለው ለዳዊት በግል ሊነግረው ወደ እሱ ሄደ። |
አበኔር ከ20 ሰዎች ጋር ሆኖ በኬብሮን ወዳለው ወደ ዳዊት ሲመጣ ዳዊት ለአበኔርና አብረውት ለነበሩት ሰዎች ግብዣ አደረገላቸው። |
ከዚያም አበኔር ዳዊትን “እስራኤላውያን ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እንዲገቡ ተነስቼ ልሂድና ሁሉንም ወደ ጌታዬ ወደ ንጉሡ ልሰብስባቸው፤ አንተም በፈለግከው ሁሉ ላይ ንጉሥ ትሆናለህ” አለው። በመሆኑም ዳዊት አበኔርን አሰናበተው፤ እሱም በሰላም ሄደ። |
በዚህ ጊዜ የዳዊት አገልጋዮችና ኢዮዓብ በጣም ብዙ ምርኮ ይዘው ከዘመቻ ተመለሱ። አበኔር ግን ዳዊት በሰላም አሰናብቶት ስለሄደ በኬብሮን ከእሱ ጋር አልነበረም። |
ኢዮዓብና አብሮት የነበረው ሠራዊት ሁሉ እዚያ ሲደርስ “የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሡ መጥቶ ነበር፤ ንጉሡም አሰናበተው፤ እሱም በሰላም ሄደ” ብለው ለኢዮዓብ ነገሩት። |
በመሆኑም ኢዮዓብ ወደ ንጉሡ ገብቶ እንዲህ አለው፦ “ምን ማድረግህ ነው? አበኔር ወደ አንተ መጥቶ ነበር። ታዲያ በሰላም እንዲሄድ ያሰናበትከው ለምንድን ነው? |
የኔርን ልጅ አበኔርን በሚገባ ታውቀዋለህ! ወደዚህ የመጣው አንተን ለማታለል እንዲሁም መውጫ መግቢያህን ለማወቅና የምታደርገውን ነገር ሁሉ ለመሰለል ነው።” |
በመሆኑም ኢዮዓብ ከዳዊት ዘንድ ወጥቶ መልእክተኞችን ወደ አበኔር ላከ፤ እነሱም ሲራ ከተባለው የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ጋ መለሱት፤ ዳዊት ግን ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም። |
አበኔር ወደ ኬብሮን በተመለሰ ጊዜ ኢዮዓብ ከእሱ ጋር በግል ለመነጋገር ነጠል አድርጎ ወደ ቅጥሩ በር ይዞት ገባ። ሆኖም በዚያ ሳሉ ሆዱ ላይ ወግቶ ገደለው፤ ይህን ያደረገው የወንድሙን የአሳሄልን ደም ለመበቀል ነው። |
ዳዊትም ይህን ሲሰማ እንዲህ አለ፦ “እኔም ሆንኩ መንግሥቴ በኔር ልጅ በአበኔር ደም በይሖዋ ፊት ለዘላለም ተጠያቂ አይደለንም። |
ደሙ በኢዮዓብ ራስና በመላው የአባቱ ቤት ራስ ላይ ይሁን። ከኢዮዓብም ቤት ፈሳሽ የሚወጣው ሰው ወይም የሥጋ ደዌ ያለበት አሊያም እንዝርት የሚያሾር ወንድ ወይም በሰይፍ የሚወድቅ አሊያም የሚበላው ያጣ ረሃብተኛ አይጥፋ!” |
በመሆኑም ኢዮዓብና ወንድሙ አቢሳ በገባኦን በተደረገው ውጊያ ላይ ወንድማቸውን አሳሄልን ስለገደለባቸው አበኔርን ገደሉት። |
ከዚያም ዳዊት ኢዮዓብንና አብረውት የነበሩትን ሰዎች በሙሉ “ልብሳችሁን ቀድዳችሁና ማቅ አሸርጣችሁ ለአበኔር አልቅሱለት” አላቸው። ንጉሥ ዳዊትም ራሱ ከቃሬዛው ኋላ ይሄድ ነበር። |
አበኔርንም በኬብሮን ቀበሩት፤ ንጉሡም በአበኔር መቃብር ላይ ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ አለቀሰ። |
ንጉሡም ለአበኔር ይህን የሐዘን እንጉርጉሮ ተቀኘ፦ “አበኔርም እንደማይረባ ሰው ይሙት? |
እጆችህ አልታሰሩም፤እግሮችህም እግር ብረት ውስጥ አልገቡም። በወንጀለኞች ፊት እንደሚወድቅ ሰው ወደቅክ።” በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ለእሱ እንደገና አለቀሱ። |
በኋላም ሕዝቡ ሁሉ ገና ቀን ሳለ፣ ዳዊትን ለማጽናናት ምግብ ይዞ መጣ፤ ሆኖም ዳዊት “ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ምግብ ወይም ማንኛውንም ነገር ብቀምስ አምላክ እንዲህ ያድርግብኝ፤ ከዚህ የከፋም ነገር ያምጣብኝ!” በማለት ማለ። |
ሕዝቡም ሁሉ የሆነውን ነገር ተመለከተ፤ ይህም ደስ አሰኛቸው። ንጉሡ ያደረገው ማንኛውም ነገር እንዳስደሰታቸው ሁሉ ይህም ደስ አሰኛቸው። |
በመሆኑም ሰዎቹ ሁሉና መላው እስራኤል ንጉሡ በኔር ልጅ በአበኔር ሞት እጁ እንደሌለበት በዚያ ቀን አወቁ። |
ከዚያም ንጉሡ አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፦ “በዛሬው ዕለት በእስራኤል ውስጥ አለቃና ታላቅ ሰው እንደወደቀ አታውቁም? |
ምንም እንኳ ንጉሥ ሆኜ የተቀባሁ ብሆንም እኔ ዛሬ ደካማ ነኝ፤ እነዚህ የጽሩያ ልጆች እጅግ ጨካኝ ሆነውብኛል። ይሖዋ ለክፉ አድራጊው እንደ ክፋቱ ይመልስለት።” |
ከዚያም ዳዊት “ለመሆኑ ለዮናታን ስል ታማኝ ፍቅር ላሳየው የምችል ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው ይኖራል?” አለ። |
በዚህ ጊዜ የሳኦል ቤት አገልጋይ የሆነ ሲባ የሚባል ሰው ነበር። እሱንም ወደ ዳዊት እንዲመጣ ጠሩት፤ ንጉሡም “ሲባ የምትባለው አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀው። እሱም “አዎ፣ እኔ አገልጋይህ ሲባ ነኝ” በማለት መለሰ። |
ከዚያም ንጉሡ “እንደው የአምላክን ታማኝ ፍቅር ላሳየው የምችል ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው ይኖራል?” አለው። ሲባም ንጉሡን “ሁለቱም እግሮቹ ሽባ የሆኑ አንድ የዮናታን ልጅ አለ” አለው። |
ንጉሡም “ለመሆኑ የት ነው ያለው?” አለው። ሲባም ንጉሡን “ሎደባር ባለው በአሚዔል ልጅ በማኪር ቤት ይገኛል” አለው። |
ንጉሥ ዳዊትም ወዲያውኑ መልእክተኞችን ልኮ ሎደባር ከሚገኘው ከአሚዔል ልጅ ከማኪር ቤት አስመጣው። |
የሳኦል ልጅ፣ የዮናታን ልጅ ሜፊቦስቴ ወደ ዳዊት ሲገባ ወዲያውኑ በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደ። ከዚያም ዳዊት “ሜፊቦስቴ!” ብሎ ጠራው፤ እሱም “አቤት ጌታዬ” አለ። |
ዳዊትም “ለአባትህ ለዮናታን ስል ታማኝ ፍቅር ስለማሳይህ አትፍራ፤ የአያትህን የሳኦልንም መሬት በሙሉ እመልስልሃለሁ፤ አንተም ዘወትር ከማዕዴ ትበላለህ” አለው። |
እሱም ከሰገደ በኋላ “እንደ እኔ ላለ የሞተ ውሻ ሞገስ ታሳይ ዘንድ ለመሆኑ እኔ አገልጋይህ ማን ነኝ?” አለው። |
ከዚያም ንጉሡ ለሳኦል አገልጋይ ለሲባ እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፦ “የሳኦልና የቤተሰቡ የሆነውን ነገር ሁሉ ለጌታህ የልጅ ልጅ ሰጥቼዋለሁ። |
አንተ፣ ልጆችህና አገልጋዮችህ መሬቱን ታርሱለታላችሁ፤ ምርቱንም ታስገቡለታላችሁ፤ ይህም ለጌታህ የልጅ ልጅ ቤተሰቦች መብል ይሆናል። የጌታህ የልጅ ልጅ ሜፊቦስቴ ግን ዘወትር ከማዕዴ ይመገባል።” ሲባ 15 ልጆችና 20 አገልጋዮች ነበሩት። |
ከዚያም ሲባ ንጉሡን “እኔ አገልጋይህ፣ ጌታዬ ንጉሡ ያዘዘኝን ሁሉ እፈጽማለሁ” አለው። ስለዚህ ሜፊቦስቴ ከንጉሡ ልጆች እንደ አንዱ ከዳዊት ማዕድ በላ። |
ሜፊቦስቴም ሚካ የሚባል ትንሽ ልጅ ነበረው፤ በሲባ ቤት የሚኖሩም ሁሉ የሜፊቦስቴ አገልጋዮች ሆኑ። |
ሜፊቦስቴም ዘወትር ከንጉሡ ማዕድ ይበላ ስለነበር የሚኖረው በኢየሩሳሌም ነበር፤ ሁለቱም እግሮቹ ሽባ ነበሩ። |
ዳዊትንም “ሂድ፣ እስራኤልንና ይሁዳን ቁጠር” ብሎ በእነሱ ላይ ባነሳሳው ጊዜ የይሖዋ ቁጣ እንደገና በእስራኤል ላይ ነደደ። |
ንጉሡም ከእሱ ጋር አብሮት የነበረውን የሠራዊቱን አለቃ ኢዮዓብን “የሕዝቡን ብዛት እንዳውቅ እስቲ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ባሉት በሁሉም የእስራኤል ነገዶች መካከል ተዘዋውራችሁ ሕዝቡን መዝግቡ” አለው። |
ኢዮዓብ ግን ንጉሡን “አምላክህ ይሖዋ ሕዝቡን 100 እጥፍ ያብዛው፤ የጌታዬ የንጉሡም ዓይኖች ይህን ይዩ፤ ሆኖም ጌታዬ ንጉሡ ይህን ማድረግ የፈለገው ለምንድን ነው?” አለው። |
ሆኖም የንጉሡ ቃል ኢዮዓብንና የሠራዊቱን አዛዦች አሸነፋቸው። በመሆኑም ኢዮዓብና የሠራዊቱ አዛዦች የእስራኤልን ሕዝብ ለመመዝገብ ከንጉሡ ፊት ወጥተው ሄዱ። |
እነሱም ዮርዳኖስን ተሻግረው በሸለቆ ውስጥ ከምትገኘው ከተማ በስተ ቀኝ ባለችው በአሮዔር ሰፈሩ፤ ከዚያም ወደ ጋዳውያን፣ ወደ ያዜር ሄዱ። |
በኋላም ወደ ጊልያድና ወደ ታህቲምሆድሺ ምድር ሄዱ፤ ከዚያም ወደ ዳንየዓን ቀጠሉ፤ ዞረውም ወደ ሲዶና ሄዱ። |
ከዚያም ወደ ጢሮስ ምሽግ እንዲሁም ወደ ሂዋውያንና ወደ ከነአናውያን ከተሞች በሙሉ ሄዱ፤ በመጨረሻም በይሁዳ ባለችው በኔጌብ ወደምትገኘው ወደ ቤርሳቤህ መጡ። |
በዚህ መንገድ በመላው ምድር ሲዘዋወሩ ቆይተው ከዘጠኝ ወር ከሃያ ቀን በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። |
ኢዮዓብም የተመዘገበውን የሕዝቡን ቁጥር ለንጉሡ ሰጠው። በእስራኤል ውስጥ ሰይፍ የታጠቁ 800,000 ተዋጊዎች ነበሩ፤ የይሁዳ ሰዎች ደግሞ 500,000 ነበሩ። |
ሆኖም ዳዊት ሕዝቡን ከቆጠረ በኋላ ልቡ ወቀሰው። ከዚያም ዳዊት ይሖዋን “ይህን በማድረጌ ከባድ ኃጢአት ሠርቻለሁ። አሁንም ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ የአገልጋይህን በደል ይቅር በል፤ ታላቅ የሞኝነት ድርጊት ፈጽሜአለሁና” አለው። |
ዳዊት ጠዋት ላይ ሲነሳ እንዲህ የሚል የይሖዋ ቃል የዳዊት ባለ ራእይ ወደሆነው ወደ ነቢዩ ጋድ መጣ፦ |
“ሂድና ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ “ሦስት ምርጫዎችን ሰጥቼሃለሁ። በአንተ ላይ አመጣብህ ዘንድ አንዱን ምረጥ” ይላል።’” |
ስለዚህ ጋድ ወደ ዳዊት ገብቶ እንዲህ አለው፦ “በምድርህ ላይ ለሰባት ዓመት ረሃብ ይሁን ወይስ ጠላቶችህ እያሳደዱህ ለሦስት ወር ከእነሱ ብትሸሽ ይሻልሃል? ወይስ ደግሞ በምድርህ ላይ ለሦስት ቀን ቸነፈር ይምጣ? እንግዲህ አሁን ለላከኝ ምን መልስ እንደምሰጥ በጥሞና አስብበት።” |
ስለዚህ ዳዊት ጋድን “ሁኔታው በጣም አስጨንቆኛል። ምሕረቱ ታላቅ ስለሆነ እባክህ በይሖዋ እጅ እንውደቅ፤ ሰው እጅ ላይ ግን አትጣለኝ” አለው። |
ከዚያም ይሖዋ ከጠዋት አንስቶ እስከተወሰነው ጊዜ ድረስ በእስራኤል ላይ ቸነፈር ላከ፤ በዚህም የተነሳ ከዳን አንስቶ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ካለው ሕዝብ መካከል 70,000 ሰዎች ሞቱ። |
መልአኩም ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት እጁን ወደ እሷ በዘረጋ ጊዜ ይሖዋ በደረሰው ጥፋት ተጸጸተ፤ በመሆኑም በሕዝቡ ላይ ጥፋት እያመጣ የነበረውን መልአክ “ይብቃ! አሁን እጅህን መልስ” አለው። የይሖዋ መልአክ በኢያቡሳዊው በአረውና አውድማ አጠገብ ነበር። |
ዳዊትም ሕዝቡን እየገደለ ያለውን መልአክ ሲያይ ይሖዋን “ኃጢአት የሠራሁት እኮ እኔ ነኝ፤ ያጠፋሁትም እኔ ነኝ፤ ታዲያ እነዚህ በጎች ምን አደረጉ? እባክህ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን” አለው። |
በመሆኑም ጋድ በዚያው ቀን ወደ ዳዊት መጥቶ “ውጣና በኢያቡሳዊው በአረውና አውድማ ላይ ለይሖዋ መሠዊያ ሥራ” አለው። |
ስለዚህ ዳዊት፣ ጋድ በነገረው መሠረት ይሖዋ እንዳዘዘው ተነስቶ ወጣ። |
አረውናም ቁልቁል ሲመለከት ንጉሡና አገልጋዮቹ ወደ እሱ ሲመጡ አየ፤ እሱም ወዲያውኑ ወጥቶ በግንባሩ መሬት ላይ በመደፋት ለንጉሡ ሰገደ። |
ከዚያም አረውና “ጌታዬ ንጉሡ ወደ አገልጋዩ የመጣው ለምንድን ነው?” አለው። ዳዊትም “በሕዝቡ ላይ እየወረደ ያለው መቅሰፍት እንዲቆም ለይሖዋ መሠዊያ ለመሥራት ይህን አውድማ ከአንተ ላይ ለመግዛት ነው” አለው። |
አረውና ግን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ጌታዬ ንጉሡ አውድማውን ወስዶ መልካም መስሎ የታየውን ነገር ያቅርብበት። ለሚቃጠል መባ የሚሆኑት ከብቶች እነዚሁልህ፣ ማሄጃውና ከብቶቹ ላይ የሚውሉት መሣሪያዎች ደግሞ ለማገዶ ይሁኑ። |
Subsets and Splits
No community queries yet
The top public SQL queries from the community will appear here once available.