text
stringlengths
4
267
ንጉሥ ሆይ፣ አረውና እነዚህን ሁሉ ለንጉሡ ሰጥቷል።” አክሎም አረውና ንጉሡን “አምላክህ ይሖዋ ሞገስ ያሳይህ” አለው።
ሆኖም ንጉሡ አረውናን “በፍጹም አይሆንም! ዋጋውን ልከፍልህ ይገባል። ደግሞም ምንም ያልከፈልኩበትን ነገር ለአምላኬ ለይሖዋ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አላቀርብም” አለው። ስለዚህ ዳዊት አውድማውንና ከብቶቹን በ50 የብር ሰቅል ገዛ።
ዳዊትም በዚያ ለይሖዋ መሠዊያ ሠርቶ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችንና የኅብረት መሥዋዕቶችን አቀረበ። ይሖዋም ስለ ምድሪቱ የቀረበውን ልመና ሰማ፤ በእስራኤል ላይ ይወርድ የነበረው መቅሰፍትም ቆመ።
ከዚህ በኋላ ዳዊት “ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዱ ልውጣ?” በማለት ይሖዋን ጠየቀ። ይሖዋም “ውጣ” አለው። ዳዊትም “ወዴት ብሄድ ይሻላል?” አለ። እሱም “ወደ ኬብሮን” አለው።
በመሆኑም ዳዊት ከሁለቱ ሚስቶቹ ማለትም ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪኖዓም እና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢጋኤል ጋር ወደዚያ ወጣ።
በተጨማሪም ዳዊት አብረውት የነበሩትን ሰዎች እያንዳንዳቸውን ከነቤተሰባቸው ይዞ ወጣ፤ እነሱም በኬብሮን ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች ውስጥ መኖር ጀመሩ።
ከዚያም የይሁዳ ሰዎች መጥተው በዚያ ዳዊትን በይሁዳ ቤት ላይ ንጉሥ አድርገው ቀቡት። ለዳዊትም “ሳኦልን የቀበሩት የኢያቢስጊልያድ ሰዎች ናቸው” ብለው ነገሩት።
በመሆኑም ዳዊት ወደ ኢያቢስጊልያድ ሰዎች መልእክተኞችን በመላክ እንዲህ አላቸው፦ “ጌታችሁን ሳኦልን በመቅበር ለእሱ ታማኝ ፍቅር ስላሳያችሁ ይሖዋ ይባርካችሁ።
ይሖዋ ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት ያሳያችሁ። እኔም ይህን ስላደረጋችሁ ደግነት አደርግላችኋለሁ።
እንግዲህ አሁን ጌታችሁ ሳኦል ስለሞተና የይሁዳም ቤት እኔን በላያቸው ንጉሥ አድርገው ስለቀቡኝ እጆቻችሁን አበርቱ፤ ደፋሮችም ሁኑ።”
የሳኦል ሠራዊት አለቃ የሆነው የኔር ልጅ አበኔር ግን የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ወደ ማሃናይም አሻገረው፤
እሱንም በጊልያድ፣ በአሱራውያን፣ በኢይዝራኤል፣ በኤፍሬምና በቢንያም እንዲሁም በእስራኤል ሁሉ ላይ አነገሠው።
የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ በእስራኤል ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 40 ዓመት ነበር፤ እሱም ለሁለት ዓመት ገዛ። የይሁዳ ቤት ግን ዳዊትን ደገፈ።
ዳዊት በኬብሮን ንጉሥ ሆኖ በይሁዳ ቤት ላይ የገዛበት ጊዜ ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበር።
ከጊዜ በኋላ የኔር ልጅ አበኔርና የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ አገልጋዮች ከማሃናይም ወደ ገባኦን ወጡ።
የጽሩያ ልጅ ኢዮዓብና የዳዊት አገልጋዮችም ወጥተው በገባኦን ኩሬ አጠገብ አገኟቸው፤ አንደኛው ቡድን ከኩሬው በዚህኛው በኩል ሌላኛው ቡድን ደግሞ ከኩሬው በዚያኛው በኩል ተቀመጠ።
በመጨረሻም አበኔር ኢዮዓብን “እስቲ ወጣቶቹ ይነሱና በፊታችን ይፋለሙ” አለው። ኢዮዓብም “እሺ ይነሱ” አለ።
በመሆኑም ተነሱ፤ ከሳኦል ልጅ ከኢያቡስቴ 12 ቢንያማውያን፣ ከዳዊት አገልጋዮችም 12 ሰዎች ተቆጥረው ተሻገሩ።
ከዚያም አንዱ የሌላውን ራስ በመያዝ ሰይፉን በባላጋራው ጎን እየሻጠ ሁሉም ተያይዘው ወደቁ። ስለዚህ በገባኦን የሚገኘው ያ ቦታ ሄልቃትሃጽጹሪም ተባለ።
በዚያን ዕለት የተነሳው ውጊያ እጅግ ከባድ ነበር፤ በመጨረሻም አበኔርና የእስራኤል ሰዎች በዳዊት አገልጋዮች ፊት ተሸነፉ።
ሦስቱ የጽሩያ ልጆች ኢዮዓብ፣ አቢሳ እና አሳሄል እዚያ ነበሩ፤ አሳሄል በመስክ ላይ እንዳለች የሜዳ ፍየል ፈጣን ሯጭ ነበር።
አሳሄልም አበኔርን ማሳደዱን ተያያዘው፤ እሱን ከማሳደድ ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዞር አላለም።
አበኔርም ወደ ኋላ ዞር ብሎ ተመለከተና “አሳሄል፣ አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀ፤ እሱም “አዎ፣ እኔ ነኝ” አለው።
ከዚያም አበኔር “ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ዞር ብለህ ከወጣቶቹ መካከል አንዱን ያዝና ያለውን ነጥቀህ ለራስህ ውሰድ” አለው። አሳሄል ግን እሱን ማሳደዱን መተው አልፈለገም።
በመሆኑም አበኔር አሳሄልን እንደገና “እኔን ማሳደድህን ተው። እኔስ ለምን ልግደልህ? የወንድምህን የኢዮዓብንስ ፊት እንዴት ብዬ አያለሁ?” አለው።
እሱ ግን ለመተው ፈቃደኛ አልሆነም፤ በመሆኑም አበኔር በጦሩ የኋላ ጫፍ ሆዱን ወጋው፤ ጦሩም በጀርባው ዘልቆ ወጣ፤ እሱም እዚያው ወድቆ ወዲያውኑ ሞተ። በዚያ የሚያልፍ ሰው ሁሉ አሳሄል ወድቆ የሞተበት ስፍራ ሲደርስ ቆም ይል ነበር።
ከዚያም ኢዮዓብና አቢሳ አበኔርን ማሳደድ ጀመሩ። ወደ ገባኦን ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ ላይ ከጊያህ ፊት ለፊት ያለው የአማ ኮረብታ ጋ ሲደርሱ ፀሐይ ጠለቀች።
በዚያም ቢንያማውያን በአበኔር ዙሪያ ተሰበሰቡ፤ እነሱም ግንባር በመፍጠር በአንድ ኮረብታ አናት ላይ ቆሙ።
ከዚያም አበኔር ኢዮዓብን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ይህ ሰይፍ ያለገደብ ሰው መብላት አለበት? ውጤቱስ መራራ እንደሚሆን አንተ ራስህ ሳታውቀው ቀርተህ ነው? ሰዎቹ ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ እንዲመለሱ የማትነግራቸው እስከ መቼ ነው?”
በዚህ ጊዜ ኢዮዓብ “ሕያው በሆነው በእውነተኛው አምላክ እምላለሁ፣ አንተ ይህን ባትናገር ኖሮ ሰዎቹ እስኪነጋ ድረስ ወንድሞቻቸውን ማሳደዳቸውን አያቆሙም ነበር” አለ።
ኢዮዓብም ቀንደ መለከት ነፋ፤ የእሱ ሰዎችም እስራኤልን ማሳደዳቸውን ተዉ፤ ውጊያውም አቆመ።
ከዚያም አበኔርና ሰዎቹ ሌሊቱን ሙሉ በአረባ ሲጓዙ አደሩ፤ ዮርዳኖስንም በመሻገር ሸለቆውን ሁሉ አቋርጠው በመጨረሻ ማሃናይምደረሱ።
ኢዮዓብም አበኔርን ከማሳደድ ተመልሶ ሕዝቡን በሙሉ አንድ ላይ ሰበሰበ። ከዳዊትም አገልጋዮች መካከል አሳሄልን ጨምሮ 19 ሰዎች መጉደላቸው ታወቀ።
የዳዊት አገልጋዮች ግን ቢንያማውያንንና የአበኔርን ሰዎች ድል ያደረጓቸው ከመሆኑም ሌላ ከእነሱ መካከል 360 ሰዎችን ገድለው ነበር።
እነሱም አሳሄልን ወስደው በቤተልሔም በሚገኘው በአባቱ የመቃብር ቦታ ቀበሩት። ከዚያም ኢዮዓብና ሰዎቹ ሌሊቱን ሙሉ ሲገሰግሱ አድረው ንጋት ላይ ኬብሮን ደረሱ።
ከጊዜ በኋላ የአሞናውያን ንጉሥ ሞተ፤ ልጁ ሃኑንም በእሱ ፋንታ ነገሠ።
በዚህ ጊዜ ዳዊት “አባቱ ታማኝ ፍቅር እንዳሳየኝ ሁሉ እኔም ለናሃሽ ልጅ ለሃኑን ታማኝ ፍቅር አሳየዋለሁ” አለ። ስለሆነም ዳዊት፣ በአባቱ ሞት ከደረሰበት ሐዘን እንዲያጽናኑት አገልጋዮቹን ወደ ሃኑን ላከ። ሆኖም የዳዊት አገልጋዮች ወደ አሞናውያን ምድር ሲደርሱ
የአሞናውያን መኳንንት ጌታቸውን ሃኑንን “ዳዊት አጽናኞችን ወደ አንተ የላከው አባትህን አክብሮ ይመስልሃል? ዳዊት አገልጋዮቹን ወደ አንተ የላከው ከተማዋን በሚገባ ለማጥናት፣ ለመሰለልና ለመገልበጥ አይደለም?” አሉት።
በመሆኑም ሃኑን የዳዊትን አገልጋዮች ወስዶ ግማሹን ጢማቸውን ላጫቸው፤ ልብሳቸውንም እስከ መቀመጫቸው ድረስ አሳጥሮ በመቁረጥ መልሶ ላካቸው።
ዳዊትም ይህን ሲሰማ ወዲያውኑ መልእክተኞችን ወደ ሰዎቹ ላከ፤ ምክንያቱም በኀፍረት ተውጠው ነበር፤ ንጉሡም “ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ቆዩ፤ ከዚያ በኋላ ተመለሱ” አላቸው።
ውሎ አድሮ አሞናውያን በዳዊት ዘንድ እንደ ጥንብ እንደተቆጠሩ ተገነዘቡ፤ በመሆኑም አሞናውያን፣ ሰዎችን በመላክ ከቤትሬሆብ ሶርያውያንና ከጾባህ ሶርያውያን 20,000 እግረኛ ተዋጊዎችን፣ የማአካን ንጉሥ ከ1,000 ሰዎች ጋር እንዲሁም ከኢሽጦብ 12,000 ሰዎችን ቀጠሩ።
ዳዊትም ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮአብን እንዲሁም እጅግ ኃያላን የሆኑትን ተዋጊዎቹን ጨምሮ መላውን ሠራዊት ላከ።
አሞናውያንም ወጥተው በከተማዋ መግቢያ ላይ ለውጊያ ተሰለፉ፤ የጾባህና የሬሆብ ሶርያውያን ደግሞ ከኢሽጦብና ከማአካ ጋር ሆነው ለብቻቸው ሜዳ ላይ ተሰለፉ።
ኢዮዓብ ወታደሮቹ ከፊትና ከኋላ ጥቃት ለመሰንዘር ወደ እሱ እየገሰገሱ መምጣታቸውን ሲያይ በእስራኤል ካሉት ምርጥ የሆኑ ተዋጊዎች መካከል የተወሰኑትን መርጦ ሶርያውያንን እንዲገጥሙ አሰለፋቸው።
የቀሩትን ሰዎች ደግሞ በወንድሙ በአቢሳ አመራር ሥር ሆነው አሞናውያንን እንዲገጥሙ አሰለፋቸው።
ከዚያም እንዲህ አለው፦ “ሶርያውያን ከበረቱብኝ አንተ ትደርስልኛለህ፤ አሞናውያን ከበረቱብህ ደግሞ እኔ እደርስልሃለሁ።
ለሕዝባችንና ለአምላካችን ከተሞች ስንል ብርቱና ደፋር መሆን አለብን፤ ይሖዋም በፊቱ መልካም የሆነውን ነገር ያደርጋል።”
ከዚያም ኢዮዓብና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሶርያውያንን ለመግጠም ወደ እነሱ ሲገሰግሱ ሶርያውያኑ ከፊታቸው ሸሹ።
አሞናውያንም ሶርያውያን እንደ ሸሹ ሲያዩ ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማዋ ገቡ። ከዚያም ኢዮዓብ አሞናውያንን ከመውጋት ተመልሶ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።
ሶርያውያንም በእስራኤላውያን ድል እንደተመቱ ሲያዩ በአዲስ መልክ ተደራጁ።
በመሆኑም ሃዳድኤዜር በወንዙ አካባቢ ወደነበሩት ሶርያውያን መልእክተኞችን ላከ፤ እነሱም የሃዳድኤዜር ሠራዊት አለቃ በሆነው በሾባክ መሪነት ወደ ሄላም መጡ።
ዳዊት ወሬው በተነገረው ጊዜ ወዲያውኑ እስራኤላውያንን ሁሉ ሰብስቦ ዮርዳኖስን በመሻገር ወደ ሄላም መጣ። ሶርያውያንም ዳዊትን ለመግጠም ተሰለፉ፤ ከእሱም ጋር ተዋጉ።
ሆኖም ሶርያውያን ከእስራኤላውያን ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን መካከል 700 ሠረገለኞችንና 40,000 ፈረሰኞችን ገደለ፤ የሠራዊታቸው አለቃ የሆነውን ሾባክንም መታው፤ እሱም እዚያው ሞተ።
የሃዳድኤዜር አገልጋዮች የሆኑት ነገሥታት በሙሉ እስራኤላውያን እንዳሸነፏቸው ባዩ ጊዜ ወዲያውኑ ከእስራኤላውያን ጋር እርቅ በመፍጠር ለእነሱ ተገዙ፤ ሶርያውያንም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አሞናውያንን መርዳት ፈሩ።
ዳዊት የተራራውን ጫፍ አልፎ ጥቂት እንደሄደ ሲባ የተባለው የሜፊቦስቴ አገልጋይ 200 ዳቦዎች፣ 100 የዘቢብ ቂጣዎች፣ ከበጋ ፍሬ የተዘጋጁ 100 ቂጣዎችና አንድ እንስራ የወይን ጠጅ የተጫነባቸው ሁለት አህዮች እየነዳ ሊያገኘው መጣ።
ንጉሡም ሲባን “እነዚህን ነገሮች ያመጣኸው ለምንድን ነው?” አለው። ሲባም “አህዮቹን የንጉሡ ቤተሰብ እንዲቀመጥባቸው፣ ዳቦውንና የበጋ ፍሬውን ደግሞ ወጣቶቹ እንዲበሏቸው፣ የወይን ጠጁንም በምድረ በዳ የደከሙ ሰዎች እንዲጠጡት ነው” ሲል መለሰ።
ንጉሡም “የጌታህ ልጅ የት አለ?” አለው። በዚህ ጊዜ ሲባ ንጉሡን “‘ዛሬ የእስራኤል ቤት የአባቴን ንጉሣዊ ሥልጣን ይመልስልኛል’ ብሎ ስላሰበ ኢየሩሳሌም ቀርቷል” አለው።
ንጉሡም ሲባን “እንግዲህ የሜፊቦስቴ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው” አለው። ሲባም “በፊትህ እሰግዳለሁ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ በአንተ ዘንድ ሞገስ ላግኝ” ሲል መለሰ።
ንጉሥ ዳዊትም ባሁሪም ሲደርስ ከሳኦል ቤት የሆነ ሺምአይ የተባለ ሰው ከዚያ ወጥቶ እየተራገመ ወደ እነሱ ቀረበ፤ እሱም የጌራ ልጅ ነበር።
ሺምአይ በንጉሥ ዳዊትና በአገልጋዮቹ ሁሉ ላይ እንዲሁም በንጉሡ ግራና ቀኝ በነበረው ሕዝብ ሁሉና በኃያላኑ ላይ ድንጋይ ይወረውር ነበር።
ሺምአይም እንዲህ እያለ ይራገም ነበር፦ “ውጣ፣ ከዚህ ውጣ፣ አንተ የደም ሰው! አንተ የማትረባ ሰው!
ንግሥናውን በወሰድክበት በሳኦል ቤት የተነሳ ያለብህን የደም ዕዳ በሙሉ ይሖዋ በአንተ ላይ እያመጣብህ ነው፤ ይሖዋም መንግሥትህን ለልጅህ ለአቢሴሎም አሳልፎ ይሰጠዋል። የደም ሰው ስለሆንክ ይኸው መከራህን እያየህ ነው!”
ከዚያም የጽሩያ ልጅ አቢሳ ንጉሡን “ይህ የሞተ ውሻ ጌታዬን ንጉሡን የሚራገመው ለምንድን ነው? እባክህ ልሂድና ራሱን ልቁረጠው” አለው።
ንጉሡ ግን “እናንተ የጽሩያ ልጆች፣ ከእናንተ ጋር ምን የሚያገናኘኝ ጉዳይ አለ? ተዉት ይርገመኝ፤ ምክንያቱም ይሖዋ ‘ዳዊትን እርገመው!’ ብሎታል። ታዲያ ‘ለምን እንዲህ ታደርጋለህ?’ ማን ሊለው ይችላል?” አለው።
ከዚያም ዳዊት አቢሳንና አገልጋዮቹን በሙሉ እንዲህ አላቸው፦ “ከአብራኬ የወጣው የገዛ ልጄ እንኳ ይኸው ሕይወቴን እየፈለገ አይደል? ታዲያ አንድ ቢንያማዊ እንዲህ ቢያደርግ ምን ያስደንቃል! ተዉት ይርገመኝ፤ ይሖዋ እርገመው ብሎት ነው!
ምናልባትም ይሖዋ መከራዬን ያይልኝና በዛሬው እርግማን ፋንታ ይሖዋ መልካም ነገር ያደርግልኝ ይሆናል።”
ከዚያም ዳዊትና ሰዎቹ መንገዱን ይዘው ቁልቁል ወረዱ፤ ሺምአይም በተራራው ጥግ ከዳዊት ጎን ጎን እየሄደ ይራገም፣ ድንጋይ ይወረውርና አቧራ ይበትን ነበር።
በኋላም ንጉሡና አብሮት የነበረው ሕዝብ በሙሉ ወዳሰቡበት ቦታ ደረሱ፤ እነሱም በጣም ደክሟቸው ነበር፤ በዚያም አረፉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አቢሴሎምና የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ኢየሩሳሌም ደረሱ፤ አኪጦፌልም አብሮት ነበር።
የዳዊት ወዳጅ አርካዊው ኩሲም ልክ ወደ አቢሴሎም እንደገባ አቢሴሎምን “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር! ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!” አለው።
በዚህ ጊዜ አቢሴሎም ኩሲን “ለወዳጅህ ታማኝ ፍቅር የምታሳየው በዚህ መንገድ ነው? ከወዳጅህ ጋር አብረህ ያልሄድከው ለምንድን ነው?” አለው።
ኩሲም አቢሴሎምን እንዲህ አለው፦ “በጭራሽ፣ እንዲህማ አላደርግም፤ ይሖዋ፣ ይህ ሕዝብና የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ከመረጡት ሰው ጎን እቆማለሁ። ከእሱም ጋር እቀመጣለሁ።
ደግሜ ይህን እናገራለሁ፣ ማገልገል ያለብኝ ማንን ነው? ልጁን አይደለም? አባትህን እንዳገለገልኩ ሁሉ አንተንም አገለግላለሁ።”
ከዚያም አቢሴሎም አኪጦፌልን “እስቲ ምክር ስጡኝ። ምን ብናደርግ ይሻላል?” አለው።
አኪጦፌልም አቢሴሎምን “አባትህ፣ ቤቱን እንዲጠብቁ ከተዋቸው ቁባቶቹ ጋር ግንኙነት ፈጽም። ከዚያም እስራኤላውያን ሁሉ ራስህን በአባትህ ዘንድ እንደ ጥንብ እንዳስቆጠርክ ይሰማሉ፤ አንተንም የሚደግፉ ብርታት ያገኛሉ” አለው።
በመሆኑም ለአቢሴሎም በጣሪያው ላይ ድንኳን ተከሉለት፤ አቢሴሎምም እስራኤላውያን ሁሉ እያዩት ከአባቱ ቁባቶች ጋር ግንኙነት ፈጸመ።
በዚያ ዘመን አኪጦፌል የሚሰጠው ምክር እንደ እውነተኛው አምላክ ቃል ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ዳዊትም ሆነ አቢሴሎም የአኪጦፌልን ምክር ሁሉ የሚያዩት እንደዚያ ነበር።
ከጊዜ በኋላ የእስራኤል ነገዶች በሙሉ በኬብሮን ወደሚገኘው ወደ ዳዊት መጥተው እንዲህ አሉት፦ “እንግዲህ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ፣ የሥጋህም ቁራጭ ነን።
ባለፉት ዘመናት ሳኦል ንጉሣችን በነበረበት ጊዜ እስራኤል ወደ ጦርነት ሲወጣ የምትመራው አንተ ነበርክ። ይሖዋም ‘ሕዝቤን እስራኤልን እረኛ ሆነህ ትጠብቃለህ፣ በእስራኤልም ላይ መሪ ትሆናለህ’ ብሎህ ነበር።”
በመሆኑም የእስራኤል ሽማግሌዎች በሙሉ ንጉሡ ወዳለበት ወደ ኬብሮን መጡ፤ ንጉሥ ዳዊትም በኬብሮን ከእነሱ ጋር በይሖዋ ፊት ቃል ኪዳን ገባ። እነሱም ዳዊትን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርገው ቀቡት።
ዳዊት በነገሠ ጊዜ 30 ዓመቱ ነበር፤ ለ40 ዓመትም ገዛ።
በኬብሮን ተቀምጦ በይሁዳ ላይ ለ7 ዓመት ከ6 ወር ገዛ፤ በኢየሩሳሌም ሆኖ ደግሞ በመላው እስራኤልና ይሁዳ ላይ ለ33 ዓመት ገዛ።
ዳዊትና ሰዎቹም በምድሪቱ የሚኖሩትን ኢያቡሳውያን ለመውጋት ወደ ኢየሩሳሌም ዘመቱ። እነሱም ዳዊትን “ፈጽሞ ወደዚህ አትገባም! ዕውሮችና ሽባዎች እንኳ ያባርሩሃል” በማለት ተሳለቁበት። ይህን ያሉት ‘ዳዊት ፈጽሞ ወደዚህ አይገባም’ ብለው ስላሰቡ ነበር።
ይሁን እንጂ ዳዊት በአሁኑ ጊዜ የዳዊት ከተማ ተብላ የምትጠራውን የጽዮንን ምሽግ ያዘ።
ስለሆነም በዚያን ቀን ዳዊት “በኢያቡሳውያን ላይ ጥቃት የሚሰነዝር ማንኛውም ሰው ዳዊት የሚጠላቸውን ‘ሽባዎችንና ዕውሮችን’ ለመምታት በውኃ መውረጃው ቦይ በኩል ማለፍ አለበት!” አለ። “ዕውርና ሽባ ፈጽሞ ወደ ቤት አይገቡም” የሚባለውም በዚህ የተነሳ ነው።
ከዚያም ዳዊት በምሽጉ ውስጥ መኖር ጀመረ፤ ስፍራውም የዳዊት ከተማ ተብሎ ይጠራ ነበር፤ እሱም ከጉብታው አንስቶ ወደ ውስጥ ዙሪያውን መገንባት ጀመረ።
በዚህ ሁኔታ ዳዊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ሄደ፤ የሠራዊት አምላክ ይሖዋም ከእሱ ጋር ነበር።
የጢሮስ ንጉሥ ኪራም መልእክተኞችን ወደ ዳዊት ላከ፤ እንዲሁም የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎችን፣ አናጺዎችንና ለቅጥር የሚሆን ድንጋይ የሚጠርቡ ሰዎችን ላከ፤ እነሱም ለዳዊት ቤት መሥራት ጀመሩ።
ዳዊትም ይሖዋ በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናውና ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤል ሲል መንግሥቱን ከፍ ከፍ እንዳደረገለት አወቀ።
ዳዊት ከኬብሮን ከመጣ በኋላ በኢየሩሳሌም ተጨማሪ ቁባቶችን አስቀመጠ፤ እንዲሁም ሌሎች ሚስቶችን አገባ፤ ተጨማሪ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ተወለዱለት።
በኢየሩሳሌም ሳለ የተወለዱለት ልጆች ስም ይህ ነው፦ ሻሙአ፣ ሾባብ፣ ናታን፣ ሰለሞን፣
ይብሃር፣ ኤሊሹዓ፣ ኔፌግ፣ ያፊአ፣
ኤሊሻማ፣ ኤሊያዳ እና ኤሊፌሌት።
ፍልስጤማውያንም በሙሉ ዳዊት በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ መቀባቱን ሲሰሙ እሱን ፍለጋ ወጡ። ዳዊትም ይህን ሲሰማ ወደ ምሽጉ ወረደ።
ከዚያም ፍልስጤማውያን መጥተው በረፋይም ሸለቆ ተበታትነው ሰፈሩ።
ዳዊትም “ወጥቼ ፍልስጤማውያንን ልግጠም? አንተስ በእጄ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህ?” ሲል ይሖዋን ጠየቀ። ይሖዋም ዳዊትን “አዎ ውጣ፤ እኔም በእርግጥ ፍልስጤማውያንን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ” አለው።
በመሆኑም ዳዊት ወደ በዓልጰራጺም መጥቶ በዚያ መታቸው። እሱም “ይሖዋ፣ ውኃ እንደጣሰው ግድብ ጠላቶቼን በፊቴ ደረማመሳቸው” አለ። ከዚህም የተነሳ ያን ቦታ በዓልጰራጺም ብሎ ጠራው።
ፍልስጤማውያንም ጣዖቶቻቸውን በዚያ ጥለው ሸሹ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ወሰዷቸው።
ከጊዜ በኋላ ፍልስጤማውያን እንደገና ወደ ረፋይም ሸለቆ መጥተው ተበታትነው ሰፈሩ።
ዳዊትም ይሖዋን ጠየቀ፤ እሱ ግን እንዲህ አለው፦ “በቀጥታ አትውጣ። ይልቁንም ከኋላቸው ዞረህ በባካ ቁጥቋጦዎቹ ፊት ለፊት ግጠማቸው።