text
stringlengths
4
267
በባካ ቁጥቋጦዎቹ አናት ላይ የሰልፍ ድምፅ ስትሰማ ቆራጥ እርምጃ ውሰድ፤ ምክንያቱም ይህ በሚሆንበት ጊዜ ይሖዋ የፍልስጤማውያንን ሠራዊት ለመምታት በፊትህ ወጥቷል ማለት ነው።”
በመሆኑም ዳዊት ልክ ይሖዋ እንዳዘዘው አደረገ፤ ፍልስጤማውያንንም ከጌባ አንስቶ እስከ ጌዜር ድረስ መታቸው።
የጽሩያ ልጅ ኢዮዓብ የንጉሡ ልብ አቢሴሎምን እንደናፈቀ ተረዳ።
በመሆኑም ኢዮአብ ወደ ተቆአ፣ ሰው ልኮ አንዲት ብልህ ሴት አስመጣ፤ እንዲህም አላት፦ “እባክሽ፣ ሐዘንተኛ ምሰዪ፤ የሐዘን ልብስ ልበሺ፤ ዘይትም አትቀቢ። ሰው ሞቶባት ለረጅም ጊዜ እንዳዘነች ሴት ሁኚ።
ወደ ንጉሡም ገብተሽ እንዲህ በይው።” ከዚያም ኢዮዓብ ምን እንደምትል ነገራት።
ተቆአዊቷም ሴት ወደ ንጉሡ ከገባች በኋላ በግንባሯ ተደፍታ በመስገድ “ንጉሥ ሆይ፣ እርዳኝ!” አለች።
ንጉሡም “ምን ሆነሽ ነው?” አላት። እሷም እንዲህ አለችው፦ “እኔ ባሌ የሞተብኝ መበለት ነኝ።
እኔ አገልጋይህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፤ እነሱም ሜዳ ላይ ተደባደቡ። ገላጋይም ስላልነበረ አንደኛው ሌላኛውን መትቶ ገደለው።
በኋላም ቤተ ዘመድ ሁሉ በእኔ በአገልጋይህ ላይ ተነስቶ ‘ወራሹን ማጥፋት ቢሆንብንም እንኳ የወንድሙን ሕይወት ስላጠፋ እሱን እንድንገድለው ገዳዩን አሳልፈሽ ስጪን’ ይለኝ ጀመር። በመሆኑም የቀረችኝን አንዲት ፍም በማጥፋት ባሌን በምድር ላይ ያለስምና ያለዘር ሊያስቀሩት ነው።”
ከዚያም ንጉሡ ሴትየዋን “በቃ አንቺ ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ የአንቺን ጉዳይ በተመለከተ ትእዛዝ እሰጣለሁ” አላት።
በዚህ ጊዜ ተቆአዊቷ ሴት ንጉሡን “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ ንጉሡና ዙፋኑ ንጹሐን ስለሆኑ በደሉ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ይሁን” አለችው።
ከዚያም ንጉሡ “ከዚህ በኋላ ማንም ሰው ቢናገርሽ ወደ እኔ አምጪው፤ ዳግመኛም አያስቸግርሽም” አላት።
እሷ ግን “ደም ተበቃዩ በልጄ ላይ ጉዳት እንዳያደርስበትና እንዳይገድለው እባክህ ንጉሡ አምላኩን ይሖዋን ያስብ” አለችው። እሱም “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ ከልጅሽ ራስ ላይ አንዲት ፀጉር እንኳ መሬት ላይ አትወድቅም” አላት።
ሴትየዋም “እባክህ አገልጋይህ ለጌታዬ ለንጉሡ አንዲት ቃል እንድትናገር ፍቀድላት” አለች። እሱም “እሺ፣ ተናገሪ!” አላት።
ከዚያም ሴትየዋ እንዲህ አለች፦ “ታዲያ አንተ በአምላክ ሕዝብ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ለማድረግ ያሰብከው ለምንድን ነው? ንጉሡ የተሰደደውን የገዛ ልጁን ባለመመለሱ እንዲህ ብሎ ሲናገር ራሱን በደለኛ እያደረገ ነው።
ሁላችንም መሞታችን አይቀርም፤ የፈሰሰ ውኃ እንደማይታፈስ ሁሉ እኛም እንደዚሁ እንሆናለን። ሆኖም አምላክ ሕይወት አያጠፋም፤ እንዲሁም የተሰደደ ሰው ከእሱ ርቆ በዚያው ተሰዶ እንዳይቀር እሱን ለመመለስ ምክንያት ይፈልጋል።
አሁንም ለጌታዬ ለንጉሡ ይህን ነገር ለመናገር የመጣሁት ሕዝቡ ስላስፈራኝ ነው። በመሆኑም አገልጋይህ እንዲህ ብላ አሰበች፦ ‘እንግዲህ አሁን ንጉሡን ላነጋግረው። ምናልባትም ንጉሡ ባሪያው የጠየቀችውን ነገር ይፈጽምላት ይሆናል።
ንጉሡ ቃሌን ሰምቶ እኔንም ሆነ አንድ ልጄን አምላክ ከሰጠን ርስት ላይ ሊያጠፋን ከሚፈልገው ሰው እጅ ባሪያውን ይታደጋት ይሆናል።’
ከዚያም አገልጋይህ ‘የጌታዬ የንጉሡ ቃል እረፍት ይስጠኝ’ አለች፤ ምክንያቱም ጌታዬ ንጉሡ ጥሩውን ከመጥፎው በመለየት ረገድ እንደ እውነተኛው አምላክ መልአክ ነው። አምላክህ ይሖዋም ከአንተ ጋር ይሁን።”
ንጉሡም መልሶ ሴትየዋን “እባክሽ፣ የምጠይቅሽን ነገር አንድም ሳትደብቂ ንገሪኝ” አላት። ሴትየዋም “እሺ፣ ንጉሡ ጌታዬ ይናገር” አለች።
ከዚያም ንጉሡ “በዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ የኢዮዓብ እጅ አለበት?” ሲል ጠየቃት። ሴትየዋም እንዲህ ስትል መለሰች፦ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ በሕያውነትህ እምላለሁ፣ ጌታዬ ንጉሡ እንደተናገረው ነው፤ ይህን እንዳደርግ ያዘዘኝና አገልጋይህ የተናገረችውን ነገር ሁሉ የነገራት አገልጋይህ ኢዮዓብ ነው።
አገልጋይህ ኢዮዓብ ይህን ያደረገው ሁኔታውን ለመለወጥ ሲል ነው፤ ሆኖም ጌታዬ እንደ እውነተኛው አምላክ መልአክ ዓይነት ጥበብ አለው፤ በምድሪቱ ላይ የሚከናወነውንም ነገር ሁሉ ያውቃል።”
ከዚያም ንጉሡ ኢዮዓብን “እሺ፣ ይህን አደርጋለሁ። በል ሂድና ወጣቱን አቢሴሎምን መልሰህ አምጣው” አለው።
በዚህ ጊዜ ኢዮዓብ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ በመስገድ ንጉሡን አመሰገነ። ከዚያም “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ ንጉሡ አገልጋዩ የጠየቀውን ነገር ስለፈጸመለት ዛሬ እኔ አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ እንዳገኘሁ አወቅኩ” አለ።
ኢዮዓብም ተነስቶ ወደ ገሹር ሄደ፤ አቢሴሎምንም ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው።
ሆኖም ንጉሡ “ወደ ራሱ ቤት ይመለስ፤ ፊቴን እንዳያይ” አለ። በመሆኑም አቢሴሎም ወደ ራሱ ቤት ተመለሰ፤ የንጉሡንም ፊት አላየም።
መቼም በመልኩ ማማር የአቢሴሎምን ያህል የተወደሰ አንድም ወንድ በመላው እስራኤል አልነበረም። ከእግር ጥፍሩ አንስቶ እስከ ራስ ፀጉሩ ድረስ ምንም እንከን አይወጣለትም ነበር።
የራስ ፀጉሩን ሲቆረጠው ፀጉሩ በቤተ መንግሥቱ የድንጋይ ሚዛን 200 ሰቅል ይመዝን ነበር፤ ፀጉሩም በጣም ስለሚከብደው ሁልጊዜ በዓመቱ መጨረሻ ላይ መቆረጥ ነበረበት።
አቢሴሎም ትዕማር የምትባል አንዲት ሴት ልጅና ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት። ትዕማር በጣም ቆንጆ ነበረች።
አቢሴሎምም በኢየሩሳሌም ድፍን ሁለት ዓመት ተቀመጠ፤ ሆኖም የንጉሡን ፊት አላየም።
በመሆኑም አቢሴሎም ወደ ንጉሡ ሊልከው ስለፈለገ ኢዮዓብን አስጠራው፤ ኢዮዓብ ግን ወደ እሱ ሳይመጣ ቀረ። ለሁለተኛ ጊዜም ሰው ላከበት፤ እሱ ግን አሁንም ለመምጣት ፈቃደኛ አልሆነም።
በመጨረሻም አቢሴሎም አገልጋዮቹን “የኢዮዓብ እርሻ የሚገኘው ከእኔ እርሻ አጠገብ ነው፤ በእርሻው ላይም የገብስ አዝመራ አለ። ሂዱና እሳት ልቀቁበት” አላቸው። በመሆኑም የአቢሴሎም አገልጋዮች በእርሻው ላይ እሳት ለቀቁበት።
በዚህ ጊዜ ኢዮዓብ ተነስቶ ወደ አቢሴሎም ቤት በመምጣት “አገልጋዮችህ እርሻዬን በእሳት ያቃጠሉት ለምንድን ነው?” አለው።
አቢሴሎምም ኢዮዓብን እንዲህ አለው፦ “ወደ እኔ ናና ለንጉሡ ‘“ከገሹር የመጣሁት ለምንድን ነው? እዚያው ብሆን ይሻለኝ ነበር። አሁንም ቢሆን የንጉሡን ፊት ማየት እፈልጋለሁ፤ ጥፋት ከተገኘብኝም ይግደለኝ” ብለህ እንድትነግርልኝ ልላክህ’ ብዬ መልእክት ላክሁብህ።”
በመሆኑም ኢዮዓብ ወደ ንጉሡ ገብቶ ይህንኑ ነገረው። ንጉሡም አቢሴሎምን ጠራው፤ አቢሴሎምም ወደ ንጉሡ ገብቶ በንጉሡ ፊት በግንባሩ መሬት ላይ በመደፋት ሰገደ። ንጉሡም አቢሴሎምን ሳመው።
ዳዊት፣ ይሖዋ ከጠላቶቹ ሁሉ እጅና ከሳኦል እጅ በታደገው ቀን የዚህን መዝሙር ቃል ለይሖዋ ዘመረ።
እንዲህም አለ፦ “ይሖዋ ቋጥኜ፣ ምሽጌና ታዳጊዬ ነው።
አምላኬ የምሸሸግበት ዓለቴ ነው፤ጋሻዬ፣ የመዳኔ ቀንድና አስተማማኝ መጠጊያዬ ነው፤መሸሻዬና አዳኜ ነው፤ አንተ ከዓመፅ ታድነኛለህ።
ውዳሴ የሚገባውን ይሖዋን እጠራለሁ፤ከጠላቶቼም እድናለሁ።
የሞት ማዕበል ዙሪያዬን ከቦኛል፤የማይረቡ ሰዎች የለቀቁት ድንገተኛ ጎርፍ አሸበረኝ።
የመቃብር ገመድ ተጠመጠመብኝ፤የሞት ወጥመድ ተጋረጠብኝ።
በጭንቅ ውስጥ ሳለሁ ይሖዋን ጠራሁት፤አምላኬን ደጋግሜ ጠራሁት። እሱም በመቅደሱ ሆኖ ድምፄን ሰማ፣እርዳታ ለማግኘት የማሰማውም ጩኸት ወደ ጆሮው ደረሰ።
ምድርም ወዲያና ወዲህ ትናወጥና ትንቀጠቀጥ ጀመር፤የሰማያት መሠረቶች ተንቀጠቀጡ፤እሱ ስለተቆጣም ራዱ።
ከአፍንጫው ጭስ ወጣ፤የሚባላም እሳት ከአፉ ወጣ፤ፍምም ከእሱ ፈለቀ።
ወደ ታች ሲወርድ ሰማያት እንዲያጎነብሱ አደረገ፤ከእግሮቹም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበር።
በኪሩብ ላይ ተቀምጦ እየበረረ መጣ። በመንፈስ ክንፎችም ላይ ሆኖ ይታይ ነበር።
ከዚያም ጨለማን በዙሪያው እንደ መጠለያ አደረገ፣ጨለማውም ጥቁር ውኃና ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበረው።
በፊቱ ካለው ብርሃን ፍም ፈለቀ።
ከዚያም ይሖዋ ከሰማይ ያንጎደጉድ ጀመር፤ልዑሉ አምላክ ድምፁን አሰማ።
ፍላጻዎቹን አስፈንጥሮ በታተናቸው፤መብረቁን አብርቆ ግራ አጋባቸው።
በይሖዋ ተግሣጽ፣ ከአፍንጫውም በሚወጣው ኃይለኛ እስትንፋስየባሕር ወለሎች ታዩ፤የምድር መሠረቶችም ተገለጡ።
ከላይ ሆኖ እጁን ሰደደ፤ከጥልቅ ውኃ ውስጥም አወጣኝ።
ከብርቱ ጠላቴ አዳነኝ፤ከእኔ ይበልጥ ብርቱዎች ከሆኑት፣ ከሚጠሉኝ ሰዎች ታደገኝ።
ችግር ላይ በወደቅኩበት ቀን ተነሱብኝ፤ይሖዋ ግን ድጋፍ ሆነልኝ።
ደህንነት ወደሚገኝበት ስፍራ አመጣኝ፤በእኔ ስለተደሰተ ታደገኝ።
ይሖዋ እንደ ጽድቄ ወሮታ ይከፍለኛል፤እንደ እጄ ንጽሕና ብድራት ይመልስልኛል።
የይሖዋን መንገድ ጠብቄአለሁና፤አምላኬን በመተው ክፉ ድርጊት አልፈጸምኩም።
ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነው፤ደንቦቹን አልተላለፍም።
በፊቱ እንከን የለሽ ሆኜ እኖራለሁ፤ራሴንም ከስህተት እጠብቃለሁ።
ይሖዋ እንደ ጽድቄ፣በፊቱም እንዳለኝ ንጽሕና ብድራት ይመልስልኝ።
ታማኝ ለሆነ ሰው ታማኝ ትሆናለህ፤እንከን የለሽ ለሆነ ኃያል ሰው እንከን የለሽ ትሆናለህ፤
ከንጹሕ ሰው ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ጠማማ ለሆነ ሰው ግን ብልህ መሆንህን ታሳያለህ።
ትሑት የሆኑትን ታድናለህና፤ዓይኖችህ ግን በትዕቢተኞች ላይ ናቸው፤ አንተም ታዋርዳቸዋለህ።
ይሖዋ ሆይ፣ አንተ መብራቴ ነህና፤ጨለማዬን ብርሃን የሚያደርገው ይሖዋ ነው።
በአንተ እርዳታ ወራሪውን ቡድን መጋፈጥ እችላለሁ፤በአምላክ ኃይል ቅጥር መውጣት እችላለሁ።
የእውነተኛው አምላክ መንገድ ፍጹም ነው፤የይሖዋ ቃል የነጠረ ነው። እሱ መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ ጋሻቸው ነው።
ደግሞስ ከይሖዋ ሌላ አምላክ ማን ነው? ከአምላካችንስ በቀር ዓለት ማን ነው?
እውነተኛው አምላክ ጠንካራ ምሽጌ ነው፤መንገዴንም ፍጹም ያደርግልኛል።
እግሮቼን እንደ ዋልያ እግሮች ያደርጋል፤በከፍታ ቦታዎች ላይ ያቆመኛል።
እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናል፤ክንዶቼ የመዳብ ደጋን ማጠፍ ይችላሉ።
የመዳን ጋሻህን ትሰጠኛለህ፤ትሕትናህም ታላቅ ያደርገኛል።
ለእርምጃዬ መንገዱን ታሰፋልኛለህ፤እግሮቼ አያዳልጣቸውም።
ጠላቶቼን አሳድጄ አጠፋቸዋለሁ፤ተጠራርገው እስኪጠፉ ድረስ ወደ ኋላ አልመለስም።
እንዳያንሰራሩም ጠራርጌ አጠፋቸዋለሁ፣ አደቃቸዋለሁ፤እግሬ ሥር ይወድቃሉ።
ለውጊያው ብርታት ታስታጥቀኛለህ፤ጠላቶቼ ሥሬ እንዲወድቁ ታደርጋለህ።
ጠላቶቼ ከእኔ እንዲሸሹ ታደርጋለህ፤እኔም የሚጠሉኝን አጠፋለሁ።
እርዳታ ለማግኘት ይጮኻሉ፤ ሆኖም የሚያድናቸው የለም፤ወደ ይሖዋም ይጮኻሉ፤ እሱ ግን አይመልስላቸውም።
በምድር ላይ እንዳለ አቧራ አደቃቸዋለሁ፤በመንገድ ላይ እንዳለ ጭቃ እረግጣቸዋለሁ፤ አደቃቸዋለሁ።
ስህተት ከሚለቃቅሙት ሕዝቦቼ ታድነኛለህ። የብሔራት መሪ እንድሆን ትጠብቀኛለህ፤የማላውቀው ሕዝብ ያገለግለኛል።
ባዕዳንም ተሸማቀው ወደ ፊቴ ይቀርባሉ፤ስለ እኔ የሚሰሙትም እንዲታዘዙኝ ያደርጋቸዋል።
የባዕድ አገር ሰዎች ወኔ ይከዳቸዋል፤ከምሽጎቻቸው እየተንቀጠቀጡ ይወጣሉ።
ይሖዋ ሕያው ነው! ዓለቴ ይወደስ! የመዳኔ ዓለት የሆነው አምላክ ከፍ ከፍ ይበል።
እውነተኛው አምላክ ይበቀልልኛል፤ሕዝቦችንም ከበታቼ ያስገዛልኛል፤
እሱ ከጠላቶቼ ያድነኛል። ከሚያጠቁኝ ሰዎች በላይ ከፍ ከፍ ታደርገኛለህ፤ከዓመፀኛ ሰው ታድነኛለህ።
ይሖዋ ሆይ፣ በብሔራት መካከል የማመሰግንህ ለዚህ ነው፤ለስምህም እንዲህ ብዬ የውዳሴ መዝሙር እዘምራለሁ፦
ለንጉሡ ታላላቅ የማዳን ሥራዎችን ያከናውናል፤ለቀባውም ታማኝ ፍቅር ያሳያል፤ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም ይህን ያደርጋል።”
ከዚህ ሁሉ በኋላ አቢሴሎም ሠረገላ፣ ፈረሶችና ከፊቱ የሚሮጡ 50 ሰዎች አዘጋጀ።
አቢሴሎምም በጠዋት ተነስቶ ወደ ከተማዋ በር በሚወስደው መንገድ ዳር ይቆም ነበር። ማንም ሰው ሙግት ኖሮት ፍርድ ለማግኘት ወደ ንጉሡ በሚመጣበት ጊዜ አቢሴሎም ይጠራውና “ለመሆኑ አንተ የየትኛው ከተማ ሰው ነህ?” ይለው ነበር፤ እሱም “አገልጋይህ ከእስራኤል ነገዶች መካከል ከአንዱ ነው” ይለዋል።
አቢሴሎምም “አቤቱታህ ትክክልና ተገቢ ነው፤ ግን ምን ያደርጋል፣ ከንጉሡ ዘንድ ጉዳይህን የሚሰማልህ አንድም ሰው አታገኝም” ይለው ነበር።
ከዚያም አቢሴሎም “ምነው በምድሪቱ ላይ ዳኛ ሆኜ በተሾምኩ! ሙግት ያለው ወይም ፍርድ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ወደ እኔ መጥቶ ፍትሕ ማግኘት ይችል ነበር” ይል ነበር።
እንዲሁም አንድ ሰው ሊሰግድለት ወደ እሱ በሚቀርብበት ጊዜ አቢሴሎም እጁን ዘርግቶ ይይዘውና ይስመው ነበር።
አቢሴሎምም ፍርድ ለማግኘት ወደ ንጉሡ ለሚመጣው እስራኤላዊ በሙሉ እንዲህ ያደርግ ነበር፤ በዚህ መንገድ አቢሴሎም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ።
በአራቱ ዓመት ማብቂያ ላይ አቢሴሎም ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “እባክህ፣ ለይሖዋ የተሳልኩትን ስእለት ለማድረስ ወደ ኬብሮን ልሂድ።
ምክንያቱም እኔ አገልጋይህ በሶርያ ባለችው በገሹር በነበርኩበት ጊዜ ‘ይሖዋ ወደ ኢየሩሳሌም ከመለሰኝ ለይሖዋ መባ አቀርባለሁ’ በማለት ተስዬ ነበር።”
በመሆኑም ንጉሡ “በሰላም ሂድ” አለው። እሱም ተነስቶ ወደ ኬብሮን ሄደ።
አቢሴሎምም “የቀንደ መለከት ድምፅ ስትሰሙ ‘አቢሴሎም በኬብሮን ነገሠ!’ ብላችሁ አውጁ” በማለት በመላው የእስራኤል ነገዶች መካከል ሰላዮችን አሰማራ።
በዚህ ጊዜ ከኢየሩሳሌም 200 ሰዎች ከአቢሴሎም ጋር ወደዚያ ሄደው ነበር፤ ጥሪ ቀርቦላቸው የሄዱት እነዚህ ሰዎች ምንም የጠረጠሩትና የሚያውቁት ነገር አልነበረም።
በተጨማሪም አቢሴሎም መሥዋዕቶቹን በሚያቀርብበት ጊዜ የዳዊትን አማካሪ ጊሎአዊውን አኪጦፌልን ከከተማው ከጊሎ ልኮ አስጠራው። አቢሴሎም የጠነሰሰው ሴራ እየተጠናከረ ሄደ፤ ከአቢሴሎም ጎን የተሰለፈውም ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መጣ።
በኋላም አንድ ሰው ወደ ዳዊት መጥቶ “የእስራኤል ሰዎች ልብ ወደ አቢሴሎም ሸፍቷል” ሲል ነገረው።
ዳዊትም በኢየሩሳሌም አብረውት የነበሩትን አገልጋዮቹን በሙሉ ወዲያውኑ እንዲህ አላቸው፦ “ተነሱ፣ እንሽሽ፤ አለዚያ አንዳችንም ከአቢሴሎም እጅ አናመልጥም! በፍጥነት መጥቶ እንዳይዘንና እንዳያጠፋን፣ ከተማዋንም በሰይፍ እንዳይመታ ቶሎ ብለን ከዚህ እንሂድ!”