text
stringlengths
4
267
በኤዶምም የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ። በመላው ኤዶም የጦር ሰፈሮችን ከማቋቋሙም ሌላ ኤዶማውያን ሁሉ የዳዊት አገልጋዮች ሆኑ። ይሖዋም ዳዊትን በሄደበት ሁሉ ድል አቀዳጀው።
ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ መግዛቱን ቀጠለ፤ ለሕዝቡም ሁሉ ፍትሕንና ጽድቅን አሰፈነላቸው።
የጽሩያ ልጅ ኢዮዓብ የሠራዊቱ አዛዥ ነበር፤ የአሂሉድ ልጅ ኢዮሳፍጥ ታሪክ ጸሐፊ ነበር።
የአኪጡብ ልጅ ሳዶቅና የአብያታር ልጅ አሂሜሌክ ካህናት ነበሩ፤ ሰራያህ ደግሞ ጸሐፊ ነበር።
የዮዳሄ ልጅ በናያህ የከሪታውያንና የጴሌታውያን አዛዥ ነበር። የዳዊት ወንዶች ልጆችም ዋና ኃላፊዎች ሆኑ።
በዚህ ጊዜ ከጊልያድ ነዋሪዎች አንዱ የሆነው ቲሽባዊው ኤልያስ አክዓብን “በማገለግለውና ሕያው በሆነው በእስራኤል አምላክ በይሖዋ እምላለሁ፣ በእኔ ትእዛዝ ካልሆነ በቀር በእነዚህ ዓመታት ጠል ወይም ዝናብ አይኖርም!” አለው።
የይሖዋም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እሱ መጣ፦
“ከዚህ ተነስተህ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ሂድ፤ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በሚገኘው በከሪት ሸለቆም ተደበቅ።
ከጅረቱ ትጠጣለህ፤ ቁራዎችም እዚያ ምግብ እንዲያመጡልህ አዛለሁ።”
እሱም ወዲያውኑ ሄዶ ይሖዋ እንዳዘዘው አደረገ፤ ሄዶም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በሚገኘው በከሪት ሸለቆ ተቀመጠ።
ቁራዎቹም ጠዋትና ማታ ምግብና ሥጋ ያመጡለት ነበር፤ እሱም ከጅረቱ ይጠጣ ነበር።
ሆኖም በምድሪቱ ላይ ዝናብ ስላልዘነበ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ጅረቱ ደረቀ።
ከዚያም የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እሱ መጣ፦
“ተነስተህ በሲዶና ወደምትገኘው ወደ ሰራፕታ ሂድ፤ እዚያም ተቀመጥ። እኔም በዚያ አንዲት መበለት እንድትመግብህ አዛለሁ።”
ኤልያስም ተነስቶ ወደ ሰራፕታ ሄደ። ወደ ከተማዋ መግቢያ በደረሰም ጊዜ አንዲት መበለት ጭራሮ ስትለቅም አገኘ። መበለቲቱንም ጠርቶ “እባክሽ የምጠጣው ትንሽ ውኃ በዕቃ ስጪኝ” አላት።
ልታመጣለት ስትሄድም ጠራትና “እባክሽ ቁራሽ ዳቦም ይዘሽልኝ ነይ” አላት።
በዚህ ጊዜ እንዲህ አለችው፦ “ሕያው በሆነው አምላክህ በይሖዋ እምላለሁ፣ በማድጋው ውስጥ ካለው አንድ እፍኝ ዱቄትና በማሰሮው ውስጥ ካለው ጥቂት ዘይት በስተቀር ምንም ዳቦ የለኝም። ለእኔና ለልጄ የሆነች ነገር ለማዘጋጀት ጭራሮ እየለቀምኩ ነው። እኛም እሷን ቀምሰን እንሞታለን።”
ከዚያም ኤልያስ እንዲህ አላት፦ “አይዞሽ ስጋት አይግባሽ። ወደ ቤት ገብተሽ እንዳልሽው አድርጊ። ብቻ በመጀመሪያ ከዚያችው ካለችሽ ላይ ትንሽ ቂጣ ጋግረሽ አምጪልኝ። ከዚያ በኋላ ለአንቺና ለልጅሽ የሆነ ነገር ማዘጋጀት ትችያለሽ።
ምክንያቱም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ይሖዋ በምድሪቱ ላይ ዝናብ እስከሚያዘንብበት ዕለት ድረስ ከማድጋው ዱቄት አይጠፋም፤ ከማሰሮውም ዘይት አያልቅም።’”
ስለሆነም ሄዳ ኤልያስ እንዳላት አደረገች፤ እሷም ሆነች እሱ እንዲሁም ቤተሰቧ ለብዙ ቀናት ሲመገቡ ቆዩ።
ይሖዋ በኤልያስ አማካኝነት በተናገረው ቃል መሠረት ከማድጋው ዱቄት አልጠፋም፤ ከማሰሮውም ዘይት አላለቀም።
ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ የቤቱ ባለቤት፣ ልጇ ታመመ፤ ሕመሙም እጅግ ስለጠናበት እስትንፋሱ ቀጥ አለ።
በዚህ ጊዜ ሴትየዋ ኤልያስን “የእውነተኛው አምላክ ሰው ሆይ፣ ምን አደረግኩህ? የመጣኸው በደሌን ልታስታውሰኝና ልጄን ልትገድል ነው?” አለችው።
እሱ ግን “ልጅሽን ስጪኝ” አላት። ከዚያም ልጁን ከእቅፏ ወስዶ እሱ ወዳረፈበት በሰገነቱ ላይ ወዳለው ክፍል ይዞት ወጣ፤ ልጁንም በራሱ አልጋ ላይ አስተኛው።
እሱም “አምላኬ ይሖዋ ሆይ፣ እኔን ያሳረፈችኝ የዚህች መበለት ልጅ እንዲሞት በማድረግ በእሷም ላይ መከራ ታመጣባታለህ?” በማለት ወደ ይሖዋ ጮኸ።
ከዚያም ልጁ ላይ ሦስት ጊዜ ከተዘረጋበት በኋላ “አምላኬ ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ የዚህ ልጅ ሕይወት ይመለስለት” ብሎ ወደ ይሖዋ ጮኸ።
ይሖዋም የኤልያስን ልመና ሰማ፤ የልጁም ሕይወት ተመለሰለት፤ እሱም ሕያው ሆነ።
ከዚያም ኤልያስ ልጁን ይዞት ሰገነት ላይ ካለው ክፍል ወደ ቤት ከወረደ በኋላ ለእናቱ ሰጣት፤ ኤልያስም “ይኸው፣ ልጅሽ ሕያው ሆኗል” አላት።
በዚህ ጊዜ ሴትየዋ ኤልያስን “አንተ በእርግጥ የአምላክ ሰው እንደሆንክ በአንደበትህም ያለው የይሖዋ ቃል እውነት እንደሆነ አሁን አወቅኩ” አለችው።
ከዚያም አክዓብ ኤልያስ ያደረገውን ሁሉና ነቢያቱን በሙሉ እንዴት በሰይፍ እንደገደለ ለኤልዛቤል ነገራት።
በዚህ ጊዜ ኤልዛቤል “ነገ በዚህ ሰዓት ከእነሱ እንደ አንዱ ሳላደርግህ ብቀር አማልክት እንዲህ ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ!” ብሎ ለኤልያስ እንዲነግረው መልእክተኛ ላከችበት።
በዚህ ጊዜ ኤልያስ ፈራ፤ በመሆኑም ሕይወቱን ለማትረፍ ሸሸ። በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ቤርሳቤህም መጣ፤ አገልጋዩንም እዚያ ተወው።
ከዚያም በምድረ በዳው የአንድ ቀን መንገድ ከተጓዘ በኋላ ወደ አንድ የክትክታ ዛፍ ሲደርስ ሥሩ ተቀመጠ፤ እንዲሞትም መለመን ጀመረ። እንዲህም አለ፦ “አሁንስ በቅቶኛል! ይሖዋ ሆይ፣ እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ሕይወቴን ውሰዳት።”
ከዚያም በክትክታው ዛፍ ሥር ጋደም አለ፤ እንቅልፍም ወሰደው። ሆኖም ድንገት አንድ መልአክ ነካ አደረገውና “ተነስና ብላ” አለው።
እሱም ቀና ብሎ ሲመለከት ራስጌው አጠገብ በጋሉ ድንጋዮች ላይ የተቀመጠ ዳቦ እንዲሁም በውኃ መያዣ ዕቃ ውስጥ ያለ ውኃ አየ። እሱም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተመልሶ ተኛ።
በኋላም የይሖዋ መልአክ ለሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ነካ አደረገውና “ሩቅ መንገድ ስለምትጓዝ ተነስና ብላ” አለው።
ስለሆነም ተነስቶ በላ፤ ጠጣም፤ ከምግቡም ባገኘው ብርታት እስከ እውነተኛው አምላክ ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ ለ40 ቀንና ለ40 ሌሊት ተጓዘ።
እዚያም ሲደርስ ወደ አንድ ዋሻ ገብቶ አደረ፤ በዚህ ጊዜ የይሖዋ ቃል ወደ እሱ መጥቶ “ኤልያስ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” አለው።
እሱም እንዲህ አለ፦ “እኔ ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ እጅግ ቀንቻለሁ፤ ምክንያቱም የእስራኤል ሰዎች ቃል ኪዳንህን ትተዋል፤ መሠዊያዎችህንም አፈራርሰዋል፤ ነቢያትህን በሰይፍ ገድለዋል፤ እንግዲህ የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ። ይኸው አሁን ደግሞ የእኔንም ሕይወት ለማጥፋት እየፈለጉ ነው።”
እሱ ግን “ውጣና ተራራው ላይ ይሖዋ ፊት ቁም” አለው። በዚህ ጊዜ ይሖዋ እያለፈ ነበር፤ ታላቅና ኃይለኛ ነፋስም በይሖዋ ፊት ተራሮቹን ሰነጣጠቀ፤ ዓለቶቹንም ፈረካከሰ፤ ይሖዋ ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱ ቀጥሎ ደግሞ የምድር መናወጥ ተከሰተ፤ ይሖዋ ግን በምድር መናወጡ ውስጥ አልነበረም።
ከምድር መናወጡ በኋላም እሳት መጣ፤ ይሖዋ ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱ በኋላ ደግሞ ዝግ ያለና ለስለስ ያለ ድምፅ ተሰማ።
ኤልያስ ይህን ድምፅ ሲሰማ ወዲያውኑ በለበሰው የነቢይ ልብስ ፊቱን ሸፈነ፤ ወጥቶም ዋሻው ደጃፍ ላይ ቆመ። ከዚያም አንድ ድምፅ “ኤልያስ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው።
እሱም እንዲህ አለ፦ “እኔ ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ እጅግ ቀንቻለሁ፤ ምክንያቱም የእስራኤል ሰዎች ቃል ኪዳንህን ትተዋል፤ መሠዊያዎችህንም አፈራርሰዋል፤ ነቢያትህን በሰይፍ ገድለዋል፤ እንግዲህ የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ። ይኸው አሁን ደግሞ የእኔንም ሕይወት ለማጥፋት እየፈለጉ ነው።”
ይሖዋም እንዲህ አለው፦ “ወደ ደማስቆ ምድረ በዳ ተመልሰህ ሂድ። እዚያም ስትደርስ ሃዛኤልን በሶርያ ላይ ንጉሥ አድርገህ ቀባው።
እንዲሁም የኒምሺን የልጅ ልጅ ኢዩን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርገህ ቀባው፤ የአቤልምሆላ ሰው የሆነውን የሻፋጥን ልጅ ኤልሳዕን ደግሞ በአንተ ምትክ ነቢይ አድርገህ ቀባው።
ከሃዛኤል ሰይፍ ያመለጠውን ኢዩ ይገድለዋል፤ ከኢዩ ሰይፍ ያመለጠውን ደግሞ ኤልሳዕ ይገድለዋል።
እኔም ለባአል ያልተንበረከኩና እሱን ያልሳሙ በእስራኤል ውስጥ የቀሩ 7,000 ሰዎች አሉኝ።”
ኤልያስም ከዚያ ወጥቶ ሄደ፤ የሻፋጥንም ልጅ ኤልሳዕን ከፊቱ 12 ጥማድ በሬዎች እያረሱ፣ እሱም በ12ኛው ጥማድ በሬ እያረሰ አገኘው። ኤልያስም ወደ እሱ በመሄድ የራሱን የነቢይ ልብስ አውልቆ ላዩ ላይ ጣል አደረገበት።
በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ በሬዎቹን እዚያው በመተው ኤልያስን ተከትሎ እየሮጠ “እባክህ፣ አባቴንና እናቴን ስሜ እንድመጣ ፍቀድልኝ። ከዚያ በኋላ እከተልሃለሁ” አለው። እሱም “ሂድ ተመለስ፤ እኔ መቼ ከለከልኩህ?” አለው።
በመሆኑም ተመለሰ፤ ከዚያም አንድ ጥማድ በሬ ወስዶ መሥዋዕት አደረገ፤ በእርሻ መሣሪያዎቹም የበሬዎቹን ሥጋ በመቀቀል ለሕዝቡ ሰጠ፤ እነሱም በሉ። ይህን ካደረገ በኋላም ተነስቶ ኤልያስን ተከተለው፤ እሱንም ያገለግለው ጀመር።
ይሁንና ንጉሥ ሰለሞን ከፈርዖን ልጅ ሌላ ብዙ የባዕድ አገር ሴቶችን ማለትም ሞዓባውያን፣ አሞናውያን፣ ኤዶማውያን፣ ሲዶናውያንና ሂታውያን ሴቶችን አፈቀረ።
እነሱም ይሖዋ ለእስራኤላውያን “ከእነሱ ጋር አትቀላቀሉ፤ እነሱም ከእናንተ ጋር አይቀላቀሉ፤ አለዚያ ያለምንም ጥርጥር ልባችሁ አማልክታቸውን ወደ መከተል እንዲያዘነብል ያደርጉታል” ብሎ ከነገራቸው ብሔራት ወገን ነበሩ። ሆኖም ሰለሞን ከእነሱ ጋር ተጣበቀ፤ ደግሞም አፈቀራቸው።
እሱም ልዕልቶች የሆኑ 700 ሚስቶች እንዲሁም 300 ቁባቶች ነበሩት፤ ሚስቶቹም ቀስ በቀስ ልቡ ወደ ሌላ እንዲያዘነብል አደረጉት።
ሰለሞን በሸመገለ ጊዜ ሚስቶቹ ልቡ ሌሎች አማልክትን ወደ መከተል እንዲያዘነብል አደረጉት፤ ልቡ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ልብ በአምላኩ በይሖዋ ዘንድ ሙሉ አልነበረም።
ሰለሞን የሲዶናውያንን እንስት አምላክ አስታሮትንና አስጸያፊ የሆነውን የአሞናውያንን አምላክ ሚልኮምን ተከተለ።
ሰለሞንም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ፤ አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ይሖዋን ሙሉ በሙሉ አልተከተለም።
ሰለሞን አስጸያፊ ለሆነው የሞዓብ አምላክ ለከሞሽና አስጸያፊ ለሆነው ለአሞናውያን አምላክ ለሞሎክ ኢየሩሳሌም ፊት ለፊት በሚገኘው ተራራ ላይ ከፍ ያለ የማምለኪያ ቦታ የሠራው በዚህ ጊዜ ነበር።
ለአማልክታቸው የሚጨስ መሥዋዕት ለሚያቀርቡትና ለሚሠዉት የባዕድ አገር ሚስቶቹ ሁሉ ልክ እንደዚሁ አደረገ።
ሰለሞን ሁለት ጊዜ ከተገለጠለት ከእስራኤል አምላክ ከይሖዋ ልቡ ስለሸፈተ ይሖዋ በሰለሞን ላይ ተቆጣ፤
ደግሞም ሌሎች አማልክትን እንዳይከተል በማዘዝ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ አስጠንቅቆት ነበር። እሱ ግን ይሖዋ ያዘዘውን ነገር አልጠበቀም።
በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሰለሞንን እንዲህ አለው፦ “ይህን ስላደረግክ እንዲሁም ባዘዝኩህ መሠረት ቃል ኪዳኔንና ደንቦቼን ስላልጠበቅክ መንግሥትህን ቀድጄ ከአንተ እወስደዋለሁ፤ ከአገልጋዮችህም መካከል ለአንዱ እሰጠዋለሁ።
ሆኖም ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ስል በአንተ ዘመን ይህን አላደርግም። መንግሥትህን ከልጅህ እጅ ላይ እቀደዋለሁ፤
ይሁንና መንግሥቱን በሙሉ ቀድጄ አልወስድም። ስለ አገልጋዬ ስለ ዳዊትና ስለመረጥኳት ስለ ኢየሩሳሌም ስል ለልጅህ አንድ ነገድ እሰጠዋለሁ።”
ከዚያም ይሖዋ ከኤዶም ንጉሣዊ ቤተሰብ የሆነውን ኤዶማዊውን ሃዳድን በሰለሞን ላይ ተቃዋሚ አድርጎ አስነሳው።
ዳዊት ኤዶምን ድል ባደረገበት ጊዜ የሠራዊቱ አለቃ የሆነው ኢዮዓብ የተገደሉትን ለመቅበር ወጥቶ የነበረ ሲሆን በኤዶም የሚገኘውን እያንዳንዱን ወንድ ለመግደል ሞክሮ ነበር።
(ምክንያቱም ኢዮዓብ በኤዶም የሚገኘውን እያንዳንዱን ወንድ ገድሎ እስኪጨርስ ድረስ ከመላው እስራኤል ጋር በዚያ ለስድስት ወር ተቀምጦ ነበር።)
ሆኖም ሃዳድ የአባቱ አገልጋዮች ከሆኑ የተወሰኑ ኤዶማውያን ጋር ሸሸ፤ እነሱም ወደ ግብፅ ሄዱ፤ በወቅቱ ሃዳድ ገና ትንሽ ልጅ ነበር።
እነሱም ከምድያም ተነስተው ወደ ፋራን ሄዱ። ከፋራንም ሰዎች ይዘው ወደ ግብፅ ይኸውም ወደ ግብፁ ንጉሥ ወደ ፈርዖን መጡ፤ ፈርዖንም ቤትና መሬት ሰጠው፤ ቀለብም እንዲሰፈርለት አደረገ።
ሃዳድም በፈርዖን ፊት ሞገስ ስላገኘ ፈርዖን የገዛ ሚስቱን እህት ማለትም የንግሥት ጣፍኔስን እህት ዳረለት።
ከጊዜ በኋላ የጣፍኔስ እህት፣ ጌኑባት የተባለ ልጅ ወለደችለት፤ ጣፍኔስም ልጁን በፈርዖን ቤት ውስጥ አሳደገችው፤ ጌኑባት በፈርዖን ቤት ከፈርዖን ልጆች ጋር ኖረ።
ሃዳድ በግብፅ ሳለ ዳዊት ከአባቶቹ ጋር እንዳንቀላፋ እንዲሁም የሠራዊቱ አለቃ ኢዮዓብ እንደሞተ ሰማ። በመሆኑም ሃዳድ ፈርዖንን “ወደ አገሬ እንድሄድ አሰናብተኝ” አለው።
ፈርዖን ግን “እዚህ እኔ ጋር እያለህ ምን ጎደለብህና ነው ወደ አገርህ መሄድ የፈለግከው?” አለው። እሱም “ምንም የጎደለብኝ ነገር የለም፤ ብቻ እንድሄድ አሰናብተኝ” አለው።
በተጨማሪም አምላክ ከጌታው ከጾባህ ንጉሥ ከሃዳድኤዜር የኮበለለውን የኤሊያዳን ልጅ ረዞንን በሰለሞን ላይ ተቃዋሚ አድርጎ አስነሳው።
እሱም ዳዊት የጾባህን ሰዎች ድል ባደረገበት ጊዜ ሰዎችን አሰባስቦ የአንድ ወራሪ ቡድን አለቃ ሆነ። በመሆኑም ወደ ደማስቆ ሄደው በዚያ ሰፈሩ፤ በደማስቆም መግዛት ጀመሩ።
ሃዳድ በእስራኤል ላይ ካስከተለው ጉዳት በተጨማሪ ረዞንም በሰለሞን ዘመን ሁሉ የእስራኤል ተቃዋሚ ሆነ፤ በሶርያ ላይ በነገሠበትም ዘመን ሁሉ ለእስራኤል ከፍተኛ ጥላቻ ነበረው።
እንዲሁም የሰለሞን አገልጋይ የሆነ ኢዮርብዓም የተባለ አንድ ኤፍሬማዊ ነበር፤ እሱም ከጸሬዳህ ወገን ሲሆን የናባጥ ልጅ ነበር፤ እናቱም ጽሩዓ የምትባል መበለት ነበረች። እሱም በንጉሡ ላይ ማመፅ ጀመረ።
በንጉሡ ላይ ያመፀውም በዚህ የተነሳ ነው፦ ሰለሞን ጉብታውን ሠርቶ እንዲሁም በአባቱ በዳዊት ከተማ ቅጥር ላይ የነበረውን ክፍተት ዘግቶ ነበር።
ኢዮርብዓም ከፍተኛ ችሎታ ያለው ሰው ነበር። ሰለሞንም ወጣቱ ጠንካራ ሠራተኛ መሆኑን ሲያይ በዮሴፍ ቤት በሚከናወነው የግዳጅ ሥራ ሁሉ ላይ የበላይ ተመልካች አደረገው።
በዚህ ጊዜ ኢዮርብዓም ከኢየሩሳሌም ወጣ፤ ሴሎናዊው ነቢዩ አኪያህም መንገድ ላይ አገኘው። አኪያህ አዲስ ልብስ ለብሶ ነበር፤ በሜዳውም ላይ ሁለቱ ብቻቸውን ነበሩ።
አኪያህም ለብሶት የነበረውን አዲስ ልብስ ይዞ 12 ቦታ ቀደደው።
ከዚያም ኢዮርብዓምን እንዲህ አለው፦ “አሥሩን ቁራጭ ለራስህ ውሰድ፤ ምክንያቱም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እንግዲህ መንግሥቱን ከሰለሞን እጅ እቀደዋለሁ፤ ለአንተም አሥር ነገዶችን እሰጥሃለሁ።
ሆኖም ስለ አገልጋዬ ስለ ዳዊትና ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል ስለመረጥኳት ከተማ ስለ ኢየሩሳሌም ስል አንዱ ነገድ የእሱ እንደሆነ ይቀጥላል።
ይህን የማደርገው እኔን ትተው ለሲዶናውያን እንስት አምላክ ለአስታሮት፣ ለሞዓብ አምላክ ለከሞሽና ለአሞናውያን አምላክ ለሚልኮም ስለሰገዱ ነው፤ አባቱ ዳዊት እንዳደረገው በፊቴ ትክክል የሆነውን ነገር በማድረግ እንዲሁም ደንቦቼንና ድንጋጌዎቼን በመጠበቅ በመንገዴ አልሄዱም።
ሆኖም ትእዛዛቴንና ደንቦቼን ስለጠበቀው ስለመረጥኩት አገልጋዬ ስለ ዳዊት ስል መንግሥቱን በሙሉ ከእጁ አልወስድም፤ ደግሞም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ አለቃ አደርገዋለሁ።
ይሁን እንጂ መንግሥቱን ይኸውም አሥሩን ነገድ ከልጁ እጅ ወስጄ ለአንተ እሰጥሃለሁ።
አገልጋዬ ዳዊት ስሜ እንዲኖርባት ለራሴ በመረጥኳት ከተማ በኢየሩሳሌም ዘወትር በፊቴ መብራት እንዲኖረው ለልጁ አንድ ነገድ እሰጠዋለሁ።
እኔም እወስድሃለሁ፤ አንተም በተመኘኸው ሁሉ ላይ ትገዛለህ፤ በእስራኤልም ላይ ንጉሥ ትሆናለህ።
አገልጋዬ ዳዊት እንዳደረገው ያዘዝኩህን ሁሉ ብትፈጽም እንዲሁም ደንቦቼንና ትእዛዛቴን በመጠበቅ በመንገዶቼ ብትሄድና በፊቴ ትክክል የሆነውን ነገር ብታደርግ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ። ለዳዊት እንዳደረግኩለት ሁሉ ለአንተም ጸንቶ የሚኖር ቤት እሠራልሃለሁ፤ እስራኤልንም እሰጥሃለሁ።
በዚህም የተነሳ የዳዊትን ዘር አዋርዳለሁ፤ ይህን የማደርገው ግን ለሁልጊዜ አይደለም።’”
በመሆኑም ሰለሞን ኢዮርብዓምን ሊገድለው ሞከረ፤ ሆኖም ኢዮርብዓም ተነስቶ ወደ ግብፅ፣ ወደ ንጉሥ ሺሻቅ ሸሸ፤ ሰለሞን እስኪሞትም ድረስ በግብፅ ተቀመጠ።
የቀረው የሰለሞን ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉና ጥበቡ በሰለሞን የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?
ሰለሞን በኢየሩሳሌም ሆኖ በመላው እስራኤል ላይ የገዛበት የጊዜ ርዝመት 40 ዓመት ነበር።
ከዚያም ሰለሞን ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ በእሱም ምትክ ልጁ ሮብዓም ነገሠ።
ንጉሥ ዳዊት አረጀ፤ ዕድሜውም እየገፋ ሄደ፤ ልብስ ቢደራርቡለትም እንኳ ሊሞቀው አልቻለም።
በመሆኑም አገልጋዮቹ “ለጌታዬ ለንጉሡ አንዲት ልጃገረድ ትፈለግለት፤ እሷም ንጉሡን እንደ ሞግዚት ሆና ትንከባከበው። ጌታዬ ንጉሡ እንዲሞቀው በእቅፉ ትተኛለች” አሉት።
ስለዚህ በመላው የእስራኤል ግዛት በመዘዋወር ቆንጆ ልጃገረድ ፈለጉ፤ ሹነማዊቷን አቢሻግንም አገኙ፤ ወደ ንጉሡም አመጧት።
እሷም እጅግ ውብ ነበረች፤ የንጉሡም ሞግዚት ሆነች፤ ትንከባከበውም ጀመር፤ ሆኖም ንጉሡ ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት አልፈጸመም።
በዚህ ጊዜ የሃጊት ልጅ አዶንያስ “ንጉሥ እሆናለሁ!” በማለት ራሱን ከፍ ከፍ ያደርግ ጀመር። ለራሱም ሠረገላ ከነፈረሰኞቹ እንዲሁም ከፊት ከፊቱ የሚሮጡ 50 ሰዎች እንዲዘጋጁለት አደረገ።
አባቱ ግን አንድም ቀን “ይህን ያደረግከው ለምንድን ነው?” በማለት ተቃውሞት አያውቅም ነበር። በተጨማሪም አዶንያስ እጅግ መልከ መልካም ነበር፤ እናቱ እሱን የወለደችው ከአቢሴሎም በኋላ ነበር።
እሱም ከጽሩያ ልጅ ከኢዮዓብና ከካህኑ ከአብያታር ጋር ተመካከረ፤ እነሱም እርዳታና ድጋፍ አደረጉለት።