text stringlengths 4 267 |
|---|
ንጉሡ ኢዮርብዓምም የእውነተኛው አምላክ ሰው በቤቴል የሚገኘውን መሠዊያ በመቃወም የተናገረውን ቃል ሲሰማ እጁን ከመሠዊያው ላይ አንስቶ በመዘርጋት “ያዙት!” አላቸው። ወዲያውኑም ወደ እሱ የዘረጋው እጁ ደረቀ፤ እጁንም ሊያጥፈው አልቻለም። |
ከዚያም የእውነተኛው አምላክ ሰው በይሖዋ ቃል ታዞ በሰጠው ምልክት መሠረት መሠዊያው ተሰነጠቀ፤ አመዱም ከመሠዊያው ላይ ፈሰሰ። |
በዚህ ጊዜ ንጉሡ የእውነተኛውን አምላክ ሰው “እባክህ፣ የአምላክህን የይሖዋን ሞገስ እንዳገኝ ለምንልኝ፤ እጄም ወደ ቦታው እንዲመለስ ጸልይልኝ” አለው። በዚህ ጊዜ የእውነተኛው አምላክ ሰው የይሖዋን ሞገስ እንዲያገኝ ለመነለት፤ የንጉሡም እጅ ተመልሶ እንደቀድሞው ሆነ። |
ከዚያም ንጉሡ የእውነተኛውን አምላክ ሰው “አብረኸኝ ወደ ቤት ሂድና ምግብ ብላ፤ ስጦታም ልስጥህ” አለው። |
ሆኖም የእውነተኛው አምላክ ሰው ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “የቤትህን ግማሽ ብትሰጠኝ እንኳ ከአንተ ጋር አልሄድም፤ በዚህም ቦታ ምግብ አልበላም፤ ውኃም አልጠጣም። |
ምክንያቱም የይሖዋ ቃል ‘ምግብ እንዳትበላ፤ ውኃም እንዳትጠጣ፤ በሄድክበትም መንገድ እንዳትመለስ’ ሲል አዞኛል።” |
በመሆኑም በሌላ መንገድ ሄደ፤ ወደ ቤቴል በመጣበትም መንገድ አልተመለሰም። |
በዚህ ጊዜ በቤቴል የሚኖር አንድ አረጋዊ ነቢይ ነበር፤ ልጆቹም ወደ ቤት መጥተው የእውነተኛው አምላክ ሰው በዚያ ቀን በቤቴል ያደረገውን ነገር ሁሉና ለንጉሡ የተናገረውን ቃል ነገሩት። ይህን ለአባታቸው ከተረኩለት በኋላ |
አባታቸው “ለመሆኑ የሄደው በየት በኩል ነው?” ሲል ጠየቃቸው። ልጆቹም ከይሁዳ የመጣው የእውነተኛው አምላክ ሰው የሄደበትን መንገድ አሳዩት። |
እሱም ልጆቹን “በሉ አህያውን ጫኑልኝ” አላቸው። እነሱም አህያውን ጫኑለት፤ እሱም አህያው ላይ ተቀመጠ። |
ከዚያም የእውነተኛውን አምላክ ሰው ተከተለው፤ በአንድ ትልቅ ዛፍ ሥር ተቀምጦም አገኘው። እሱም “ከይሁዳ የመጣኸው የእውነተኛው አምላክ ሰው አንተ ነህ?” አለው፤ እሱም “አዎ፣ እኔ ነኝ” ሲል መለሰለት። |
ከዚያም “አብረን ወደ ቤት እንሂድና ምግብ ብላ” አለው። |
እሱ ግን እንዲህ አለው፦ “ከአንተ ጋር ተመልሼ ልሄድ ወይም ያቀረብክልኝን ግብዣ ልቀበል አልችልም፤ ደግሞም በዚህ ቦታ ከአንተ ጋር ምግብም ሆነ ውኃ አልቀምስም። |
ምክንያቱም የይሖዋ ቃል ‘እዚያ ምግብ እንዳትበላ፤ ውኃም እንዳትጠጣ። በመጣህበትም መንገድ እንዳትመለስ’ በማለት አዞኛል።” |
በዚህ ጊዜ አረጋዊው ሰው “እኔም እኮ እንደ አንተው ነቢይ ነኝ፤ አንድ መልአክ ‘ምግብ እንዲበላና ውኃ እንዲጠጣ መልሰህ ወደ ቤትህ አምጣው’ በማለት የይሖዋን ቃል ነግሮኛል” አለው። (እሱም አታለለው።) |
በመሆኑም እሱ ቤት ምግብ ለመብላትና ውኃ ለመጠጣት አብሮት ተመለሰ። |
እነሱም በማዕድ ተቀምጠው ሳሉ የይሖዋ ቃል የእውነተኛውን አምላክ ሰው መልሶ ወዳመጣው ነቢይ መጣ፤ |
ከዚያም ከይሁዳ የመጣውን የእውነተኛውን አምላክ ሰው ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በይሖዋ መመሪያ ላይ ስላመፅክና አምላክህ ይሖዋ የሰጠህን ትእዛዝ ስላልጠበቅክ፣ |
ከዚህ ይልቅ ምግብ ለመብላትና ውኃ ለመጠጣት ስትል “ምግብ እንዳትበላ፤ ውኃም እንዳትጠጣ” ወደተባልክበት ቦታ ስለተመለስክ ሬሳህ በአባቶችህ የመቃብር ቦታ አይቀበርም።’” |
የእውነተኛው አምላክ ሰውም ከበላና ከጠጣ በኋላ አረጋዊው ነቢይ ከመንገድ መልሶ ላመጣው ለዚያ ነቢይ አህያውን ጫነለት። |
ከዚያም መንገዱን ቀጠለ፤ ሆኖም አንድ አንበሳ መንገድ ላይ አግኝቶ ገደለው። ሬሳውም መንገዱ ላይ ተጋድሞ፣ አህያው ደግሞ አጠገቡ ቆሞ ነበር፤ አንበሳውም ሬሳው አጠገብ ቆሞ ነበር። |
በዚያ የሚያልፉ ሰዎችም ሬሳው መንገድ ላይ ተጋድሞ፣ አንበሳው ደግሞ አጠገቡ ቆሞ አዩ። ከዚያም መጥተው ይህን ነገር አረጋዊው ነቢይ በሚኖርበት ከተማ አወሩ። |
ከመንገድ መልሶ ያመጣውም ነቢይ ይህን ሲሰማ ወዲያውኑ “ይህ ሰው በይሖዋ መመሪያ ላይ ያመፀው የእውነተኛው አምላክ ሰው ነው፤ ይሖዋ በነገረው ቃል መሠረት እንዲቦጫጭቀውና እንዲገድለው ይሖዋ ለአንበሳ አሳልፎ ሰጥቶታል” አለ። |
እሱም ልጆቹን “በሉ አህያውን ጫኑልኝ” አላቸው። እነሱም ጫኑለት። |
ከዚያም ሄደ፤ ሬሳው መንገድ ላይ ተጋድሞ፣ አህያውና አንበሳውም አጠገቡ ቆመው አገኛቸው። አንበሳው ሬሳውን አልበላውም፤ አህያውንም ቢሆን አልቦጫጨቀውም። |
ነቢዩም የእውነተኛውን አምላክ ሰው ሬሳ አንስቶ አህያው ላይ ከጫነ በኋላ አልቅሶ ሊቀብረው ስላሰበ ወደሚኖርበት ከተማ ይዞት ተመለሰ። |
ከዚያም ሬሳውን በራሱ የመቃብር ቦታ ቀበረው፤ እነሱም “ወይኔ ወንድሜን!” እያሉ አለቀሱለት። |
እሱንም ከቀበረው በኋላ ልጆቹን እንዲህ አላቸው፦ “እኔም ስሞት የእውነተኛው አምላክ ሰው በተቀበረበት የመቃብር ቦታ ቅበሩኝ። አጥንቶቼንም ከአጥንቶቹ አጠገብ ቅበሯቸው። |
በይሖዋ ቃል በታዘዘው መሠረት በቤቴል በሚገኘው መሠዊያና በሰማርያ ከተሞች በሚገኙት ኮረብቶች ላይ ባሉት የአምልኮ ቤቶች ሁሉ ላይ የተናገረው ቃል ያለጥርጥር ይፈጸማል።” |
ይህ ሁሉ ከሆነም በኋላ ቢሆን ኢዮርብዓም ከመጥፎ መንገዱ አልተመለሰም፤ ከዚህ ይልቅ ከፍ ላሉት የማምለኪያ ቦታዎች ከሕዝቡ መካከል ካህናት መሾሙን ቀጠለ። እንዲሁም ካህን ለመሆን የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው “ከፍ ላሉት የማምለኪያ ቦታዎች ካህን ይሁን” በማለት ይሾመው ነበር። |
ይህም ኃጢአት የኢዮርብዓም ቤት ከምድር ገጽ እንዲጠፋና እንዲደመሰስ ምክንያት ሆነ። |
እነዚህ ነገሮች ከተከናወኑ በኋላ ከኢይዝራኤላዊው ከናቡቴ የወይን እርሻ ጋር በተያያዘ አንድ ሁኔታ ተከሰተ፤ የወይን እርሻው የሚገኘው በኢይዝራኤል ውስጥ ከሰማርያው ንጉሥ ከአክዓብ ቤተ መንግሥት አጠገብ ነበር። |
አክዓብ ናቡቴን እንዲህ አለው፦ “የወይን እርሻህ ከቤቴ አጠገብ ስለሚገኝ የአትክልት ቦታ እንዳደርገው ስጠኝ። እኔም በምትኩ ከዚህ የተሻለ የወይን እርሻ እሰጥሃለሁ። ከፈለግክ ደግሞ የቦታውን ዋጋ እሰጥሃለሁ።” |
ናቡቴ ግን አክዓብን “የአባቶቼን ርስት ለአንተ መስጠት በይሖዋ ፊት ተገቢ ስላልሆነ ፈጽሞ የማላስበው ነገር ነው” አለው። |
በመሆኑም አክዓብ ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ “የአባቶቼን ርስት አልሰጥህም” ስላለው ፊቱ ጠቁሮና አዝኖ ወደ ቤቱ ገባ። ከዚያም ፊቱን ወደ ግድግዳ አዙሮ ተኛ፤ ምግብ ለመብላትም ፈቃደኛ አልሆነም። |
ሚስቱ ኤልዛቤልም ወደ እሱ ገብታ “ምግብ አልበላ እስኪልህ ድረስ እንዲህ ያዘንከው ለምንድን ነው?” አለችው። |
እሱም እንዲህ አላት፦ “ኢይዝራኤላዊውን ናቡቴን ‘የወይን እርሻህን በገንዘብ ሽጥልኝ። ከፈለግክ ደግሞ በምትኩ ሌላ የወይን እርሻ ልስጥህ’ ብዬው ነበር። እሱ ግን ‘የወይን እርሻዬን አልሰጥህም’ አለኝ።” |
ሚስቱ ኤልዛቤልም “በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆነህ የምትገዛው አንተ አይደለህም? በል ተነስና እህል ቅመስ፤ ልብህም ደስ ይበለው። የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን እርሻ እኔ እሰጥሃለሁ” አለችው። |
ስለሆነም በአክዓብ ስም ደብዳቤዎች ጽፋ በእሱ ማኅተም አተመቻቸው፤ ደብዳቤዎቹንም ናቡቴ በሚኖርበት ከተማ ወደሚገኙት ሽማግሌዎችና ታላላቅ ሰዎች ላከቻቸው። |
በደብዳቤዎቹም ላይ እንዲህ ስትል ጻፈች፦ “ጾም አውጁ፤ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት በክብር ቦታ ላይ አስቀምጡት። |
ሁለት የማይረቡ ሰዎችንም አምጥታችሁ ከፊት ለፊቱ አስቀምጡና ‘አምላክንና ንጉሡን ተራግመሃል!’ በማለት እንዲመሠክሩበት አድርጉ። ከዚያም አውጥታችሁ በድንጋይ በመውገር ግደሉት።” |
በመሆኑም የከተማዋ ሰዎች ማለትም እሱ በሚኖርበት ከተማ ያሉት ሽማግሌዎችና ታላላቅ ሰዎች ኤልዛቤል በላከችላቸው ደብዳቤዎች ላይ በተጻፈው መሠረት አደረጉ። |
እነሱም ጾም አወጁ፤ ናቡቴም በሕዝቡ ፊት በክብር ቦታ ላይ እንዲቀመጥ አደረጉ። |
ከዚያም ሁለት የማይረቡ ሰዎች መጥተው ፊት ለፊቱ ተቀመጡ፤ እነሱም በሕዝቡ ፊት ‘ናቡቴ አምላክንና ንጉሡን ተራግሟል!’ እያሉ በናቡቴ ላይ ይመሠክሩበት ጀመር። ከዚያም ወደ ከተማዋ ዳርቻ በመውሰድ በድንጋይ ወግረው ገደሉት። |
እነሱም “ናቡቴ በድንጋይ ተወግሮ ሞቷል” በማለት ወደ ኤልዛቤል መልእክት ላኩባት። |
ኤልዛቤልም ናቡቴ በድንጋይ ተወግሮ መሞቱን እንደሰማች አክዓብን “ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ በገንዘብ ሊሸጥልህ ያልፈለገውን የወይን እርሻውን ተነስና ውረስ፤ ምክንያቱም ናቡቴ በሕይወት የለም፤ ሞቷል” አለችው። |
አክዓብም ናቡቴ መሞቱን እንደሰማ ተነስቶ የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን እርሻ ለመውረስ ወደዚያ ወረደ። |
ሆኖም የይሖዋ ቃል ወደ ቲሽባዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ |
“በሰማርያ የሚገኘውን የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ለማግኘት ተነስተህ ወደዚያ ውረድ። እሱም የናቡቴን የወይን እርሻ ለመውረስ ሄዶ እዚያ ይገኛል። |
እንዲህም በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ሰው ገድለህ ንብረቱን ወሰድክ አይደል?”’ ከዚያም እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ቦታ የአንተንም ደም ይልሱታል።”’” |
አክዓብም ኤልያስን “ጠላቴ ሆይ፣ አገኘኸኝ?” አለው፤ እሱም እንዲህ አለው፦ “አዎ፣ አግኝቼሃለሁ። ‘እንግዲህ አንተ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ቆርጠህ ስለተነሳህ |
ጥፋት አመጣብሃለሁ፤ እየተከታተልኩም ሙልጭ አድርጌ እጠርግሃለሁ፤ እንዲሁም በእስራኤል ውስጥ የሚገኘውን ምስኪኑንና ደካማውን ጨምሮ የአክዓብ የሆነውን ወንድ ሁሉ አጠፋለሁ። |
ቁጣዬን ስላነሳሳህና እስራኤላውያን ኃጢአት እንዲፈጽሙ ስላደረግክ ቤትህን እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤትና እንደ አኪያህ ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ።’ |
ኤልዛቤልን በተመለከተም ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ ‘ውሾች በኢይዝራኤል በሚገኘው ቁራሽ መሬት ላይ ኤልዛቤልን ይበሏታል። |
ከአክዓብ ወገን የሆነውን፣ በከተማ ውስጥ የሚሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳ ላይ የሚሞተውን ደግሞ የሰማይ አሞሮች ይበሉታል። |
በእርግጥም በሚስቱ በኤልዛቤል ተነድቶ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ቆርጦ የተነሳ እንደ አክዓብ ያለ አንድም ሰው የለም። |
ይሖዋ ከእስራኤላውያን ፊት ያሳደዳቸው አሞራውያን እንዳደረጉት ሁሉ እሱም አስጸያፊ የሆኑ ጣዖቶችን በመከተል እጅግ አስነዋሪ ነገር አደረገ።’” |
አክዓብም ይህን እንደሰማ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅም ለበሰ፤ ጾመ፤ እንዲሁም ማቅ ላይ ይተኛና በሐዘን ተኮራምቶ ይሄድ ነበር። |
ከዚያም የይሖዋ ቃል ወደ ቲሽባዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ |
“አክዓብ ስለ እሱ በተናገርኩት ነገር የተነሳ ራሱን እንዴት እንዳዋረደ ተመለከትክ? ራሱን በፊቴ ስላዋረደ ላመጣበት የነበረውን ጥፋት በእሱ ዘመን አላመጣም። ከዚህ ይልቅ በእሱ ቤት ላይ ጥፋት የማመጣው በልጁ ዘመን ነው።” |
ሰለሞን ከግብፁ ንጉሥ ከፈርዖን ጋር በጋብቻ ተዛመደ። የፈርዖንን ሴት ልጅ አገባ፤ እሷንም የራሱን ቤት፣ የይሖዋን ቤትና በኢየሩሳሌም ዙሪያ ያለውን ቅጥር ገንብቶ እስኪጨርስ ድረስ ወደ ዳዊት ከተማ አመጣት። |
ሆኖም እስከዚያን ጊዜ ድረስ ለይሖዋ ስም የተሠራ ቤት ስላልነበረ ሕዝቡ መሥዋዕት ያቀርብ የነበረው ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች ላይ ነበር። |
ሰለሞን መሥዋዕቶችንና የሚቃጠሉ መባዎችን ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች ላይ ከማቅረቡ በስተቀር በአባቱ በዳዊት ደንቦች መሠረት በመሄድ ይሖዋን እንደሚወድ አሳይቷል። |
ይበልጥ ታዋቂ የሆነው ከፍ ያለ የማምለኪያ ቦታ ገባኦን ስለነበር ንጉሡ መሥዋዕት ለማቅረብ ወደዚያ ሄደ። ሰለሞን በዚያ መሠዊያ ላይ 1,000 የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችን አቀረበ። |
በገባኦንም ይሖዋ ለሰለሞን ሌሊት በሕልም ተገለጠለት፤ አምላክም “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ጠይቅ” አለው። |
በዚህ ጊዜ ሰለሞን እንዲህ አለ፦ “አገልጋይህ አባቴ ዳዊት በፊትህ በታማኝነት፣ በጽድቅና በቅን ልቦና ስለሄደ ጥልቅ የሆነ ታማኝ ፍቅር አሳይተኸዋል። በዙፋኑ ላይ የሚቀመጥ ልጅ በመስጠት እስከ ዛሬም ድረስ ለእሱ ይህን ጥልቅ የሆነ ታማኝ ፍቅር አሳይተሃል። |
አሁንም አምላኬ ይሖዋ ሆይ፣ እኔ ገና አንድ ፍሬ ልጅና ተሞክሮ የሌለኝ ብሆንም አገልጋይህን በአባቴ በዳዊት ምትክ አንግሠኸዋል። |
አገልጋይህ አንተ በመረጥከው፣ ከብዛቱም የተነሳ ሊቆጠር በማይችለው ሕዝብ መካከል ይገኛል። |
ስለሆነም አገልጋይህ ሕዝብህን መዳኘት እንዲሁም መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር መለየት እንዲችል ታዛዥ ልብ ስጠው፤ አለዚያማ ስፍር ቁጥር የሌለውን ይህን ሕዝብህን ማን ሊዳኝ ይችላል?” |
ሰለሞን ይህን መጠየቁ ይሖዋን ደስ አሰኘው። |
ከዚያም አምላክ እንዲህ አለው፦ “ይህን ነገር ስለጠየቅክ እንዲሁም ለራስህ ረጅም ዕድሜ ወይም ብልጽግና አሊያም የጠላቶችህን ሞት ሳይሆን የፍርድ ጉዳዮችን መዳኘት እንድትችል ማስተዋልን ስለጠየቅክ |
የጠየቅከውን አደርግልሃለሁ። ከአንተ በፊት ማንም ሰው ያልነበረውን ከአንተ በኋላም ማንም ሰው የማያገኘውን ጥበበኛና አስተዋይ ልብ እሰጥሃለሁ። |
በተጨማሪም በሕይወት ዘመንህ ሁሉ ከነገሥታት መካከል አንተን የሚተካከል እንዳይኖር አንተ ያልጠየቅከውን ብልጽግናና ክብር እሰጥሃለሁ። |
አባትህ ዳዊት እንዳደረገው ሥርዓቶቼንና ትእዛዛቴን በመጠበቅ በመንገዶቼ ከሄድክ ረጅም ዕድሜም እሰጥሃለሁ።” |
ሰለሞንም ከእንቅልፉ ሲነቃ ሕልም መሆኑን ተረዳ። ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ በይሖዋ የቃል ኪዳን ታቦት ፊት ቆመ፤ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችንና የኅብረት መባዎችን አቀረበ፤ ለአገልጋዮቹም በሙሉ ግብዣ አዘጋጀ። |
በዚህ ጊዜ ሁለት ዝሙት አዳሪዎች ወደ ንጉሡ መጥተው ፊቱ ቆሙ። |
የመጀመሪያዋም ሴት እንዲህ አለች፦ “ጌታዬ ሆይ፣ እኔና ይህች ሴት የምንኖረው አንድ ቤት ውስጥ ነው፤ እሷም ቤት ውስጥ እያለች ልጅ ወለድኩ። |
እኔ ከወለድኩ ከሦስት ቀን በኋላ ይህችም ሴት ልጅ ወለደች። ሁለታችን አብረን ነበርን፤ ከሁለታችን በስተቀር ቤቱ ውስጥ ማንም አብሮን አልነበረም። |
ሌሊት ላይ ይህች ሴት ልጇ ላይ ስለተኛችበት ልጇ ሞተ። |
ስለሆነም እኩለ ሌሊት ላይ ተነስታ እኔ አገልጋይህ ተኝቼ እያለሁ ልጄን ከአጠገቤ በመውሰድ በእቅፏ አስተኛችው፤ የሞተውን ልጇን ደግሞ በእኔ እቅፍ ውስጥ አስተኛችው። |
እኔም በማለዳ ልጄን ለማጥባት ስነሳ ልጁ ሞቷል። ስለሆነም በማለዳ ብርሃን ልጁን ትክ ብዬ ስመለከተው እኔ የወለድኩት ልጅ አለመሆኑን ተረዳሁ።” |
ሆኖም ሌላኛዋ ሴት “በፍጹም፣ በሕይወት ያለው የእኔ ልጅ ነው፤ የሞተው የአንቺ ልጅ ነው!” አለች። በዚህ ጊዜ የመጀመሪያዋ ሴት “በጭራሽ፣ የሞተው የአንቺ ልጅ ነው፤ በሕይወት ያለው የእኔ ልጅ ነው” አለች። እነሱም እንዲህ እያሉ በንጉሡ ፊት ተጨቃጨቁ። |
በመጨረሻም ንጉሡ “ይህችኛዋ ‘ይህ በሕይወት ያለው ልጅ የእኔ ነው፤ የሞተው የአንቺ ልጅ ነው!’ ትላለች፤ ያቺኛዋ ደግሞ ‘በፍጹም፣ የሞተው የአንቺ ልጅ ነው፤ በሕይወት ያለው የእኔ ልጅ ነው!’ ትላለች” አለ። |
ከዚያም ንጉሡ “እንግዲያውስ ሰይፍ አምጡልኝ” አለ። በመሆኑም ለንጉሡ ሰይፍ አመጡለት። |
ንጉሡም “በሉ በሕይወት ያለውን ልጅ ለሁለት ሰንጥቁትና ግማሹን ለአንደኛዋ ሴት ግማሹን ደግሞ ለሌላኛዋ ስጡ” አለ። |
በሕይወት ያለው ልጅ እናት ለልጇ ስለራራች ወዲያውኑ ንጉሡን “እባክህ ጌታዬ! በሕይወት ያለውን ልጅ ለእሷ ስጧት! በፍጹም አትግደሉት!” በማለት ተማጸነችው። ሌላኛዋ ሴት ግን “ልጁ የእኔም የአንቺም አይሆንም! ለሁለት ይሰንጥቁት!” ትል ነበር። |
ንጉሡም መልሶ “በሕይወት ያለውን ልጅ ለመጀመሪያዋ ሴት ስጧት! እናቱ እሷ ስለሆነች በፍጹም አትግደሉት” አለ። |
እስራኤላውያንም ሁሉ ንጉሡ የሰጠውን ፍርድ ሰሙ፤ ንጉሡ ፍትሐዊ ፍርድ መስጠት ይችል ዘንድ የአምላክን ጥበብ እንደታደለ ስለተመለከቱ ለንጉሡ አክብሮታዊ ፍርሃት አደረባቸው። |
ሰለሞን የይሖዋን ቤትና የንጉሡን ቤት እንዲሁም ለመሥራት የፈለገውን ነገር ሁሉ ገንብቶ እንደጨረሰ |
ይሖዋ በገባኦን እንደተገለጠለት አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ ተገለጠለት። |
ይሖዋም እንዲህ አለው፦ “በፊቴ የጸለይከውን ጸሎትና ሞገስ ለማግኘት ያቀረብከውን ልመና ሰምቻለሁ። የገነባኸውን ይህን ቤት ስሜ ለዘለቄታው እንዲጠራበት በማድረግ ቀድሼዋለሁ፤ ዓይኔም ሆነ ልቤ ሁልጊዜ በዚያ ይሆናል። |
አንተም አባትህ ዳዊት እንዳደረገው ያዘዝኩህን ሁሉ በመፈጸም በንጹሕ ልብና በቅንነት በፊቴ ብትሄድ እንዲሁም ሥርዓቶቼንና ፍርዴን ብትጠብቅ |
ለአባትህ ለዳዊት ‘ከዘር ሐረግህ በእስራኤል ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው አይታጣም’ በማለት በገባሁለት ቃል መሠረት የመንግሥትህን ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ። |
ሆኖም እናንተም ሆናችሁ ልጆቻችሁ እኔን ከመከተል ዞር ብትሉ እንዲሁም በፊታችሁ ያስቀመጥኳቸውን ትእዛዛቴንና ደንቦቼን ባትጠብቁ፣ ሄዳችሁም ሌሎች አማልክትን ብታገለግሉና ለእነሱ ብትሰግዱ |
እስራኤላውያንን ከሰጠኋቸው ምድር ላይ አጠፋቸዋለሁ፤ ለስሜ የቀደስኩትንም ቤት ከፊቴ አስወግደዋለሁ፤ እስራኤላውያንም በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ መቀለጃና መሳለቂያ ይሆናሉ። |
ይህም ቤት የፍርስራሽ ክምር ይሆናል። በዚያም የሚያልፉ ሰዎች ሁሉ በመገረም ትኩር ብለው እየተመለከቱ ‘ይሖዋ በዚህች ምድርና በዚህ ቤት ላይ እንዲህ ያለ ነገር ያደረገው ለምንድን ነው?’ በማለት ያፏጫሉ። |
ከዚያም እንዲህ ይላሉ፦ ‘ይህ የደረሰባቸው አባቶቻቸውን ከግብፅ ምድር ያወጣውን አምላካቸውን ይሖዋን ትተው ሌሎች አማልክትን ስለተከተሉና ለእነሱ ስለሰገዱ እንዲሁም እነሱን ስላገለገሉ ነው። ይሖዋ ይህን ሁሉ መከራ ያመጣባቸው ለዚህ ነው።’” |
ሰለሞን ሁለቱን ቤቶች ይኸውም የይሖዋን ቤትና የንጉሡን ቤት ገንብቶ በጨረሰበት በ20ኛው ዓመት ማብቂያ ላይ |
የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለሰለሞን የሚፈልገውን ያህል የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎች፣ የጥድ ዛፍ ሳንቃዎችና ወርቅ ሰጠው፤ ንጉሥ ሰለሞን ደግሞ ለኪራም በገሊላ ምድር የሚገኙ 20 ከተሞችን ሰጠው። |
ስለሆነም ኪራም ሰለሞን የሰጠውን ከተሞች ለማየት ከጢሮስ ወጥቶ ሄደ፤ ሆኖም በከተሞቹ አልተደሰተም። |
Subsets and Splits
No community queries yet
The top public SQL queries from the community will appear here once available.