text
stringlengths
4
267
እሱም “ወንድሜ ሆይ፣ የሰጠኸኝ ምን ዓይነት ከተሞችን ነው?” አለው። ስለዚህ እነዚህ ከተሞች እስከ ዛሬ ድረስ የካቡል ምድር ተብለው ይጠራሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኪራም ለንጉሡ 120 ታላንት ወርቅ ላከለት።
ንጉሥ ሰለሞን የይሖዋን ቤት፣ የራሱን ቤት፣ ጉብታውን፣ የኢየሩሳሌምን ቅጥር፣ ሃጾርን፣ መጊዶንና ጌዜርን እንዲገነቡ ስለመለመላቸው የግዳጅ ሥራ የሚሠሩ ሠራተኞች የሚገልጸው ዘገባ ይህ ነው።
(የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ወጥቶ ጌዜርን ያዘ፤ በእሳትም አቃጠላት፤ በተጨማሪም በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩትን ከነአናውያን ገደለ። ከተማዋንም የሰለሞን ሚስት ለሆነችው ለልጁ ጎጆ መውጫ አድርጎ ሰጣት።)
ሰለሞንም ጌዜርንና ታችኛውን ቤትሆሮንን ሠራ፤
በተጨማሪም ባዓላትን፣ በምድሩ በሚገኘው ምድረ በዳ ውስጥ ያለችውን ትዕማርን
እንዲሁም የሰለሞንን የእህልና የዕቃ ማከማቻ ከተሞች በሙሉ፣ የሠረገላ ከተሞቹን፣ የፈረሰኞቹን ከተሞች እንዲሁም ሰለሞን በኢየሩሳሌም፣ በሊባኖስና በእሱ ግዛት ውስጥ ባለው ምድር ሁሉ መገንባት የፈለጋቸውን ነገሮች በሙሉ ሠራ።
ከእስራኤላውያን ወገን ያልሆኑትን ከአሞራውያን፣ ከሂታውያን፣ ከፈሪዛውያን፣ ከሂዋውያንና ከኢያቡሳውያን የተረፉትን ሕዝቦች በሙሉ
ይኸውም እስራኤላውያን ፈጽመው ሊያጠፏቸው ያልቻሏቸውን በምድሪቱ ላይ የቀሩትን ዘሮቻቸውን ሰለሞን እንደ ባሪያ ሆነው የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ መልምሏቸው ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ ይሠራሉ።
ሆኖም ሰለሞን ከእስራኤላውያን መካከል አንዳቸውንም ባሪያ አላደረገም፤ ምክንያቱም እነሱ ተዋጊዎቹ፣ አገልጋዮቹ፣ መኳንንቱ፣ የጦር መኮንኖቹ እንዲሁም የሠረገለኞቹና የፈረሰኞቹ አለቆች ነበሩ።
ሰለሞን የሚያሠራውን ሥራ የሚከታተሉት ይኸውም ሥራውን የሚሠሩትን ሰዎች በቅርብ የሚቆጣጠሩት የበታች ተቆጣጣሪዎቹ አለቆች 550 ነበሩ።
የፈርዖን ሴት ልጅ ግን ከዳዊት ከተማ ወጥታ ሰለሞን ወዳሠራላት ወደ ራሷ ቤት መጣች፤ ከዚያም ጉብታውን ሠራ።
ሰለሞን በዓመት ሦስት ጊዜ ለይሖዋ በሠራው መሠዊያ ላይ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችንና የኅብረት መሥዋዕቶችን ያቀርብ ነበር፤ በተጨማሪም በይሖዋ ፊት በነበረው መሠዊያ ላይ የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር፤ ቤቱንም አጠናቀቀ።
እንዲሁም ንጉሥ ሰለሞን በኤዶም ምድር በቀይ ባሕር ዳርቻ በኤሎት አጠገብ በምትገኘው በዔጽዮንጋብር መርከቦችን ሠራ።
ኪራምም ከሰለሞን አገልጋዮች ጋር አብረው እንዲሠሩ አገልጋዮቹን ይኸውም ልምድ ያላቸውን ባሕረኞች ከእነዚህ መርከቦች ጋር ላከ።
እነሱም ወደ ኦፊር በመሄድ 420 ታላንት ወርቅ አምጥተው ለንጉሥ ሰለሞን ሰጡት።
ዳዊት የሚሞትበት ቀን ሲቃረብ ልጁን ሰለሞንን እንዲህ ሲል አዘዘው፦
“እንግዲህ እኔ የምሞትበት ጊዜ ቀርቧል። ስለሆነም በርታ፤ ወንድ ሁን።
በሙሴ ሕግ ላይ በተጻፈው መሠረት በመንገዶቹ በመሄድ እንዲሁም ደንቦቹን፣ ትእዛዛቱን፣ ፍርዶቹንና ማሳሰቢያዎቹን በመጠበቅ ለአምላክህ ለይሖዋ ያለብህን ግዴታ ፈጽም፤ ይህን ካደረግክ የምታከናውነው ሁሉ ይሳካልሃል፤ በምትሄድበትም ሁሉ ይቃናልሃል።
ይሖዋም እንዲህ በማለት የገባልኝን ቃል ይፈጽማል፦ ‘ልጆችህ፣ በሙሉ ልባቸውና በሙሉ ነፍሳቸው በፊቴ በታማኝነት በመመላለስ መንገዳቸውን ከጠበቁ ከዘር ሐረግህ በእስራኤል ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው አይታጣም።’
“የጽሩያ ልጅ ኢዮዓብ በእኔ ላይ ያደረገውን ነገር ይኸውም በሁለቱ የእስራኤል ሠራዊት አለቆች ማለትም በኔር ልጅ በአበኔርና በየቴር ልጅ በአሜሳይ ላይ ያደረገውን በሚገባ ታውቃለህ። ይህ ሰው እነዚህን ሰዎች በመግደል ጦርነት ሳይኖር በሰላሙ ጊዜ ደም አፍስሷል፤ እንዲሁም በወገቡ ላይ የታጠቀው ቀበቶና በእግሩ ላይ ያደረገው ጫማ በጦርነት ጊዜ በሚፈሰው ደም እንዲበከል አድርጓል።
እንግዲህ እንደ ጥበብህ አድርግ፤ ሽበቱ በሰላም ወደ መቃብር እንዲወርድ አታድርግ።
“ሆኖም ለቤርዜሊ ልጆች ታማኝ ፍቅር አሳያቸው፤ እነሱም ከማዕድህ ከሚበሉ ሰዎች መካከል ይሁኑ፤ ምክንያቱም ከወንድምህ ከአቢሴሎም ፊት በሸሸሁ ጊዜ እነሱም ከጎኔ ቆመው ነበር።
“በተጨማሪም ከባሁሪም የመጣው ቢንያማዊው የጌራ ልጅ ሺምአይ አብሮህ አለ። ወደ ማሃናይም በሄድኩበት ዕለት ከባድ እርግማን የረገመኝ እሱ ነው፤ ሆኖም እኔን ለማግኘት ወደ ዮርዳኖስ በወረደ ጊዜ ‘በሰይፍ አልገድልህም’ ብዬ በይሖዋ ማልኩለት።
አንተ ጥበበኛ ስለሆንክና በእሱ ላይ ምን ማድረግ እንዳለብህ ስለምታውቅ ሳትቀጣ አትተወው፤ ሽበቱ በደም ወደ መቃብር እንዲወርድ አድርግ።”
ከዚያም ዳዊት ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም ተቀበረ።
ዳዊት በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ የገዛው ለ40 ዓመት ነበር። በኬብሮን ለ7 ዓመት፣ በኢየሩሳሌም ደግሞ ለ33 ዓመት ነገሠ።
ከዚያም ሰለሞን በአባቱ በዳዊት ዙፋን ላይ ተቀመጠ፤ ቀስ በቀስም ንግሥናው እየጸና ሄደ።
ከጊዜ በኋላም የሃጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰለሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ መጣ። እሷም “የመጣኸው በሰላም ነው?” አለችው፤ እሱም “አዎ፣ በሰላም ነው” አላት።
ከዚያም “አንድ የምነግርሽ ጉዳይ አለኝ” አላት። እሷም “እሺ፣ ንገረኝ” አለችው።
እሱም እንዲህ አላት፦ “ንግሥናው የእኔ ሊሆን እንደነበረና እስራኤልም ሁሉ ይነግሣል ብለው ይጠብቁ እንደነበር በሚገባ ታውቂያለሽ፤ ይሁንና ንግሥናው የእኔ መሆኑ ቀርቶ የወንድሜ ሆነ፤ ምክንያቱም ይሖዋ ንግሥናው የእሱ እንዲሆን ወስኖ ነበር።
ሆኖም አሁን አንድ የምጠይቅሽ ነገር አለ። መቼም አታሳፍሪኝም።” እሷም “እሺ ንገረኝ” አለችው።
እሱም “እባክሽ፣ ንጉሥ ሰለሞን የጠየቅሽውን እንቢ ስለማይልሽ ሹነማዊቷን አቢሻግን እንዲድርልኝ ጠይቂው” አላት።
በዚህ ጊዜ ቤርሳቤህ “መልካም! ንጉሡን አነጋግርልሃለሁ” አለችው።
በመሆኑም ቤርሳቤህ የአዶንያስን ጉዳይ ልትነግረው ወደ ንጉሥ ሰለሞን ገባች። ንጉሡም ወዲያውኑ ሊቀበላት ተነሳ፤ ሰገደላትም። ከዚያም ዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ የንጉሡም እናት በቀኙ እንድትቀመጥ ዙፋን አስመጣላት።
እሷም “አንዲት ትንሽ ነገር ልጠይቅህ አስቤ ነበር። መቼም እንቢ አትለኝም” አለችው። ንጉሡም “እናቴ ሆይ፣ ንገሪኝ፤ የጠየቅሽኝን እንቢ አልልሽም” አላት።
እሷም “ሹነማዊቷ አቢሻግ ለወንድምህ ለአዶንያስ ትዳርለት” አለችው።
በዚህ ጊዜ ንጉሥ ሰለሞን ለእናቱ እንዲህ ሲል መለሰላት፦ “ለአዶንያስ ሹነማዊቷን አቢሻግን ብቻ ለምን ትጠይቂለታለሽ? ታላቅ ወንድሜ ስለሆነ ንግሥናም ጠይቂለት እንጂ፤ ካህኑ አብያታርና የጽሩያ ልጅ ኢዮዓብም እየደገፉት ነው።”
ከዚያም ንጉሥ ሰለሞን እንዲህ ሲል በይሖዋ ማለ፦ “አዶንያስ ይህን በመጠየቁ ሕይወቱን ሳያጣ ቢቀር አምላክ ይህን ያድርግብኝ፤ ከዚህ የከፋም ነገር ያምጣብኝ።
አሁንም በሚገባ ባጸናኝ፣ በአባቴ በዳዊት ዙፋን ላይ ባስቀመጠኝና በገባው ቃል መሠረት ቤት በሠራልኝ ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ አዶንያስ በዛሬዋ ዕለት ይገደላል።”
ንጉሥ ሰለሞንም ወዲያውኑ የዮዳሄን ልጅ በናያህን ላከው፤ እሱም ወጥቶ አዶንያስን መታው፤ እሱም ሞተ።
ንጉሡም ካህኑን አብያታርን እንዲህ አለው፦ “በአናቶት ወደሚገኘው እርሻህ ሂድ! አንተ ሞት የሚገባህ ሰው ነህ፤ ሆኖም በአባቴ በዳዊት ፊት የሉዓላዊውን ጌታ የይሖዋን ታቦት ስለተሸከምክና በአባቴ ላይ የደረሰውን መከራ ሁሉ ስለተጋራህ ዛሬ አልገድልህም።”
በመሆኑም ይሖዋ በሴሎ፣ በኤሊ ቤት ላይ እንደሚደርስ የተናገረው ነገር ይፈጸም ዘንድ ሰለሞን አብያታርን የይሖዋ ካህን ሆኖ እንዳያገለግል አባረረው።
ኢዮዓብ ቀደም ሲል ከአቢሴሎምጋር ወግኖ ያልነበረ ቢሆንም አዶንያስን ደግፎ ስለነበር ይህን ወሬ ሲሰማ ወደ ይሖዋ ድንኳን በመሸሽ የመሠዊያውን ቀንዶች ያዘ።
ከዚያም ንጉሥ ሰለሞን “ኢዮዓብ ወደ ይሖዋ ድንኳን ሸሽቶ እዚያ በመሠዊያው አጠገብ ይገኛል” ተብሎ ተነገረው። በመሆኑም ሰለሞን የዮዳሄን ልጅ በናያህን “ሂድና ግደለው!” ብሎ ላከው።
ስለዚህ በናያህ ወደ ይሖዋ ድንኳን ሄዶ ኢዮዓብን “ንጉሡ ‘ና ውጣ!’ ብሎሃል” አለው። እሱ ግን “እዚሁ እሞታታለሁ እንጂ በፍጹም አልወጣም!” አለ። በዚህ ጊዜ በናያህ “ኢዮዓብ እንዲህ እንዲህ ብሏል፤ እንዲህም ሲል መልሶልኛል” በማለት ለንጉሡ ተናገረ።
ከዚያም ንጉሡ እንዲህ አለው፦ “በል ልክ እንዳለው አድርግ፤ ግደለውና ቅበረው፤ ኢዮዓብ አላግባብ ካፈሰሰውም ደም እኔንና የአባቴን ቤት አንጻ።
ኢዮዓብ አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ከእሱ ይልቅ ጻድቅና የተሻሉ የነበሩትን ሁለት ሰዎች ማለትም የእስራኤል ሠራዊት አለቃ የነበረውን የኔርን ልጅ አበኔርንና የይሁዳ ሠራዊት አለቃ የነበረውን የየቴርን ልጅ አሜሳይን በሰይፍ መትቶ በመግደሉ ይሖዋ ደሙን በራሱ ላይ ይመልስበታል።
ደማቸውም ለዘላለም በኢዮዓብ ራስና በዘሮቹ ራስ ላይ ይሆናል፤ በዳዊት፣ በዘሮቹ፣ በቤቱና በዙፋኑ ላይ ግን የይሖዋ ሰላም ለዘላለም ይሁን።”
ከዚያም የዮዳሄ ልጅ በናያህ ወጥቶ ኢዮዓብን መትቶ ገደለው፤ እሱም በምድረ በዳ በሚገኘው በራሱ ቤት ተቀበረ።
ከዚያም ንጉሡ በኢዮዓብ ምትክ የዮዳሄን ልጅ በናያህን በሠራዊቱ ላይ ሾመው፤ በአብያታር ቦታ ደግሞ ካህኑን ሳዶቅን ሾመው።
ንጉሡም ሺምአይን አስጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ኢየሩሳሌም ውስጥ ቤት ሠርተህ በዚያ ኑር፤ ከዚያም ወጥተህ ወደ ሌላ ቦታ አትሂድ።
ከዚያ ወጥተህ የቄድሮንን ሸለቆ የተሻገርክ ቀን ግን እንደምትሞት እወቅ። ደምህ በራስህ ላይ ይሆናል።”
ሺምአይም ንጉሡን “ጥሩ ሐሳብ ነው። አገልጋይህ፣ ጌታዬ ንጉሡ እንዳለው ያደርጋል” አለው። ስለሆነም ሺምአይ በኢየሩሳሌም ለብዙ ጊዜ ተቀመጠ።
ሆኖም ከሦስት ዓመት በኋላ ከሺምአይ ባሪያዎች መካከል ሁለቱ የጌት ንጉሥ ወደሆነው ወደ ማአካ ልጅ ወደ አንኩስ ኮበለሉ። ሺምአይም “ባሪያዎችህ ያሉት ጌት ነው” ተብሎ ሲነገረው
ወዲያውኑ አህያውን ጭኖ ባሪያዎቹን ለመፈለግ በጌት ወዳለው ወደ አንኩስ አቀና። ሺምአይ ባሪያዎቹን ይዞ ከጌት ሲመለስ
ለሰለሞን “ሺምአይ ከኢየሩሳሌም ወጥቶ ወደ ጌት ሄዶ ነበር፤ አሁን ግን ተመልሷል” ተብሎ ተነገረው።
በዚህ ጊዜ ንጉሡ ሺምአይን አስጠርቶ እንዲህ አለው፦ “‘ከዚህ ወጥተህ ወደ ሌላ ቦታ በሄድክ ቀን እንደምትሞት እወቅ’ ብዬ በይሖዋ አስምዬህና አስጠንቅቄህ አልነበረም? አንተስ ብትሆን ‘ጥሩ ሐሳብ ነው፤ እንዳልከኝ አደርጋለሁ’ ብለኸኝ አልነበረም?
ታዲያ በይሖዋ ፊት የገባኸውን መሐላና የሰጠሁህን ትእዛዝ ያልጠበቅከው ለምንድን ነው?”
ከዚያም ንጉሡ፣ ሺምአይን እንዲህ አለው፦ “በአባቴ በዳዊት ላይ ያደረግከውን ክፉ ነገር ሁሉ ልብህ ያውቀዋል፤ ይሖዋም ያደረግከውን ክፉ ነገር በራስህ ላይ ይመልስብሃል።
ንጉሥ ሰለሞን ግን ይባረካል፤ የዳዊትም ዙፋን በይሖዋ ፊት ለዘላለም ይጸናል።”
ከዚያም ንጉሡ የዮዳሄን ልጅ በናያህን አዘዘው፤ እሱም ወጥቶ ሺምአይን መትቶ ገደለው። በዚህ መንገድ መንግሥቱ በሰለሞን እጅ ጸና።
የሳባ ንግሥት ስለ ሰለሞን ዝና እንዲሁም ከይሖዋ ስም ጋር ስላለው ግንኙነት ሰማች፤ በመሆኑም አስቸጋሪ በሆኑ ጥያቄዎች ልትፈትነው መጣች።
እሷም እጅግ ታላቅ አጀብ አስከትላ እንዲሁም የበለሳን ዘይት፣ በጣም ብዙ ወርቅና የከበሩ ድንጋዮች በግመል አስጭና ኢየሩሳሌም ደረሰች። ወደ ሰለሞንም ገብታ በልቧ ያለውን ሁሉ ነገረችው።
ሰለሞንም ጥያቄዎቿን ሁሉ መለሰላት። ንጉሡ ሊያብራራላት ያልቻለው ምንም ነገር አልነበረም።
የሳባ ንግሥት የሰለሞንን ጥበብ ሁሉና የሠራውን ቤት ስትመለከት፣
በገበታው ላይ የሚቀርበውን ምግብ፣ የአገልጋዮቹን አቀማመጥ፣ አስተናጋጆቹ በማዕድ ላይ የሚያስተናግዱበትን መንገድና አለባበሳቸውን፣ መጠጥ አሳላፊዎቹን እንዲሁም በይሖዋ ቤት ዘወትር የሚያቀርባቸውን የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች ስታይ በመገረም ፈዛ ቀረች።
በመሆኑም ንጉሡን እንዲህ አለችው፦ “ስላከናወንካቸው ነገሮችና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ነገር እውነት ነው።
ይሁንና እኔ ራሴ መጥቼ በገዛ ዓይኔ እስከማይ ድረስ የተነገረኝን ነገር አላመንኩም ነበር። እንደዚያም ሆኖ ግማሹ እንኳ አልተነገረኝም! በጥበብም ሆነ በብልጽግና ከሰማሁት ሁሉ እጅግ የላቅክ ነህ።
አብረውህ ያሉ ሰዎች ደስተኞች ናቸው፤ ዘወትር በፊትህ ቆመው ጥበብህን የሚሰሙት አገልጋዮችህም እጅግ ደስተኞች ናቸው!
አንተን በእስራኤል ዙፋን ላይ በማስቀመጥ በአንተ ደስ የተሰኘው አምላክህ ይሖዋ ይወደስ። ይሖዋ ለእስራኤል ካለው ዘላለማዊ ፍቅር የተነሳ ፍትሕንና ጽድቅን እንድታሰፍን ንጉሥ አድርጎ ሾሞሃል።”
ከዚያም ለንጉሡ 120 ታላንት ወርቅ እንዲሁም እጅግ ብዙ የበለሳን ዘይትና የከበሩ ድንጋዮች ሰጠችው። የሳባ ንግሥት ለንጉሥ ሰለሞን የሰጠችውን የሚያህል መጠን ያለው የበለሳን ዘይት ከዚያ በኋላ መጥቶ አያውቅም።
ከኦፊር ወርቅ ጭነው የመጡት የኪራም መርከቦች ከኦፊር እጅግ ብዙ የሰንደል ዛፍ ሳንቃዎችንና የከበሩ ድንጋዮችንም አምጥተው ነበር።
ንጉሡም ከሰንደል ዛፍ ሳንቃዎቹ ለይሖዋ ቤትና ለንጉሡ ቤት ድጋፎችን እንዲሁም ለዘማሪዎቹ የሚሆኑ በገናዎችንና ሌሎች ባለ አውታር መሣሪያዎችን ሠራ። ይህን ያህል ብዛት ያለው የሰንደል ዛፍ ሳንቃ እስከ ዛሬ ድረስ መጥቶም ሆነ ታይቶ አያውቅም።
ንጉሥ ሰለሞንም ለሳባ ንግሥት በልግስና ተነሳስቶ ከሰጣት ሌላ የፈለገችውንና የጠየቀችውን ነገር ሁሉ ሰጣት። ከዚያም ተነስታ አገልጋዮቿን በማስከተል ወደ አገሯ ተመለሰች።
ሰለሞን በየዓመቱ 666 ታላንት ወርቅ ይመጣለት ነበር፤
ይህም ከነጋዴዎች፣ ከሸቃጮች ከሚገኘው ትርፍ፣ ከዓረብ ነገሥታት ሁሉና ከአገረ ገዢዎች የሚሰበሰበውን ሳይጨምር ነው።
ንጉሥ ሰለሞን ከቅይጥ ወርቅ 200 ትላልቅ ጋሻዎችን ሠራ፤ (እያንዳንዱ ጋሻ በ600 ሰቅል ወርቅ ተለብጦ ነበር)፤
እንዲሁም ከቅይጥ ወርቅ 300 ትናንሽ ጋሻዎችን ሠራ፤ (እያንዳንዱ ትንሽ ጋሻ በሦስት ምናን ወርቅ ተለብጦ ነበር)። ከዚያም ንጉሡ የሊባኖስ ደን በተባለው ቤት አስቀመጣቸው።
በተጨማሪም ንጉሡ ከዝሆን ጥርስ ትልቅ ዙፋን ሠርቶ በተጣራ ወርቅ ለበጠው።
ወደ ዙፋኑ የሚያስወጡ ስድስት ደረጃዎች ነበሩ፤ ዙፋኑም ከኋላው በኩል ክብ ከለላ ነበረው፤ መቀመጫውም በጎንና በጎኑ የእጅ መደገፊያዎች ያሉት ሲሆን ከእጅ መደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር።
በስድስቱ ደረጃዎች ዳርና ዳር አንድ አንድ አንበሳ፣ በአጠቃላይ 12 አንበሶች ቆመው ነበር። እንዲህ ያለ ዙፋን የሠራ አንድም ሌላ መንግሥት አልነበረም።
የንጉሥ ሰለሞን የመጠጫ ዕቃዎች በሙሉ ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ የሊባኖስ ደን በተባለው ቤት የነበሩት ዕቃዎችም በሙሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ነበሩ። ከብር የተሠራ ምንም ነገር አልነበረም፤ በሰለሞን ዘመን ብር እንደ ተራ ነገር ይቆጠር ነበር።
ንጉሡ ከኪራም መርከቦች ጋር አብረው በባሕር ላይ የሚጓዙ የተርሴስ መርከቦች ነበሩት። እነዚህ የተርሴስ መርከቦች በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብር፣ የዝሆን ጥርስ፣ ጦጣና ጣዎስ ጭነው ይመጡ ነበር።
በመሆኑም ንጉሥ ሰለሞን በብልጽግናና በጥበብ ምድር ላይ ካሉ ሌሎች ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ ነበር።
የምድር ሕዝቦችም ሁሉ አምላክ በሰለሞን ልብ ውስጥ ያኖረውን ጥበብ ይሰሙ ዘንድ ከእሱ ጋር ለመገናኘት ይጓጉ ነበር።
ወደ እሱ የሚመጡትም ሰዎች በየዓመቱ የብር ዕቃዎች፣ የወርቅ ዕቃዎች፣ ልብሶች፣ የጦር ትጥቆች፣ የበለሳን ዘይት፣ ፈረሶችና በቅሎዎች ስጦታ አድርገው ያመጡ ነበር።
ሰለሞንም ሠረገሎችንና ፈረሶችን መሰብሰቡን ቀጠለ፤ እሱም 1,400 ሠረገሎችና 12,000 ፈረሶች ነበሩት፤ እነሱንም በሠረገላ ከተሞችና በኢየሩሳሌም በንጉሡ አቅራቢያ አኖራቸው።
ንጉሡ በኢየሩሳሌም ያለውን ብር ከብዛቱ የተነሳ በየቦታው እንደሚገኝ ድንጋይ አደረገው፤ አርዘ ሊባኖሱንም ከብዛቱ የተነሳ በሸፌላ እንደሚገኘው የሾላ ዛፍ አደረገው።
የሰለሞን ፈረሶች ከግብፅ ያስመጣቸው ነበሩ፤ የንጉሡ ነጋዴዎችም የፈረሶቹን መንጋ አንዴ በተተመነው ዋጋ ይገዙ ነበር።
ከግብፅ የሚመጣው እያንዳንዱ ሠረገላ 600 የብር ሰቅል ያወጣ ነበር፤ አንድ ፈረስ ደግሞ 150 ሰቅል ያወጣል፤ እነሱ ደግሞ በተራቸው ለሂታውያን ነገሥታትና ለሶርያ ነገሥታት ሁሉ ሠረገሎችንና ፈረሶችን ይሸጡ ነበር።
ከዚያም በባኦስ ላይ የተነገረው የይሖዋ ቃል የሃናኒ ልጅ ወደሆነው ወደ ኢዩ እንዲህ ሲል መጣ፦
“ከአቧራ ላይ አንስቼ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ አደረግኩህ፤ አንተ ግን የኢዮርብዓምን መንገድ ተከተልክ፤ ሕዝቤ እስራኤልም ኃጢአት እንዲሠራ አደረግክ፤ እነሱም በኃጢአታቸው አስቆጡኝ።
ስለሆነም ባኦስንና ቤቱን ሙልጭ አድርጌ እጠርጋለሁ፤ ቤቱንም እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት አደርገዋለሁ።
ከባኦስ ወገን የሆነውን በከተማ ውስጥ የሚሞተውን ሁሉ ውሾች ይበሉታል፤ ከእሱ ወገን የሆነውን በሜዳ ላይ የሚሞተውን ሁሉ ደግሞ የሰማይ አሞሮች ይበሉታል።”
የቀረው የባኦስ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮችና ኃያልነቱ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?
በመጨረሻም ባኦስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በቲርጻም ተቀበረ፤ በእሱም ምትክ ልጁ ኤላህ ነገሠ።
በተጨማሪም ባኦስ ልክ እንደ ኢዮርብዓም ቤት በእጁ በሠራቸው ነገሮች ይሖዋን በማስቆጣት በፊቱ መጥፎ የሆነውን ነገር ሁሉ ስለፈጸመ እንዲሁም እሱን ስለገደለ የይሖዋ ቃል የሃናኒ ልጅ በሆነው በነቢዩ ኢዩ አማካኝነት በባኦስና በቤቱ ላይ መጣ።
የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በ26ኛው ዓመት የባኦስ ልጅ ኤላህ በቲርጻ ሆኖ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ለሁለት ዓመትም ገዛ።
የግማሹ የሠረገላ ሠራዊት አለቃ የሆነው አገልጋዩ ዚምሪ በእሱ ላይ አሴረ፤ በዚህ ጊዜ ኤላህ በቲርጻ የሚገኘው የንጉሡ ቤት ኃላፊ በነበረው በአርጻ ቤት ጠጥቶ ሰክሮ ነበር።