text
stringlengths
4
267
ሆኖም ነገ በዚህ ሰዓት ገደማ አገልጋዮቼን ወደ አንተ እልካለሁ፤ እነሱም የአንተን ቤትና የአገልጋዮችህን ቤት አንድ በአንድ ይበረብራሉ፤ ለአንተ ትልቅ ዋጋ ያለውን ነገር ሁሉ እጃቸው በማስገባት ይወስዳሉ።’”
በዚህ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ በምድሪቱ ያሉትን ሽማግሌዎች በሙሉ ጠርቶ “እንግዲህ ይህ ሰው በእኛ ላይ መከራ ለማምጣት ቆርጦ እንደተነሳ ልብ በሉ፤ ሚስቶቼን፣ ልጆቼን፣ ብሬንና ወርቄን እንድሰጠው ላከብኝ፤ እኔም አልከለከልኩትም” አላቸው።
ከዚያም ሽማግሌዎቹ ሁሉና ሕዝቡ በሙሉ “እሺ አትበለው፤ በዚህ አትስማማ” አሉት።
በመሆኑም የቤንሃዳድን መልእክተኞች “ጌታዬ ንጉሡን እንዲህ በሉት፦ ‘እኔ አገልጋይህ መጀመሪያ ላይ የጠየቅከኝን ነገር ሁሉ እፈጽማለሁ፤ ይህን ግን መፈጸም አልችልም’” አላቸው። መልእክተኞቹም ይህን መልእክት ይዘው ወደ እሱ ሄዱ።
ቤንሃዳድም “የሰማርያ አፈር ለሚከተለኝ ሕዝብ ሁሉ አንድ አንድ እፍኝ እንኳ ቢደርሰው አማልክት እንዲህ ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የከፋም ያምጡብኝ!” የሚል መልእክት ላከበት።
የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ “ቤንሃዳድን እንዲህ በሉት፦ ‘ለጦርነት እየታጠቀ ያለ ሰው ጦርነቱን ድል አድርጎ ትጥቁን እንደሚፈታ ሰው መደንፋት የለበትም’” አለ።
ቤንሃዳድና ነገሥታቱ በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሆነው እየጠጡ ሳለ ቤንሃዳድ ይህን ምላሽ ሲሰማ አገልጋዮቹን “ጥቃት ለመሰንዘር ተዘጋጁ!” አላቸው። በመሆኑም በከተማዋ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ተዘጋጁ።
ሆኖም አንድ ነቢይ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ ቀርቦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ይህን እጅግ ብዙ ሕዝብ ትመለከታለህ? እኔ ዛሬ በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ አንተም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃለህ’” አለው።
አክዓብም “በማን አማካኝነት?” ሲል ጠየቀ፤ እሱም መልሶ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በአውራጃዎቹ መኳንንት አገልጋዮች አማካኝነት’” አለው። ስለሆነም አክዓብ “ታዲያ ውጊያውን የሚያስጀምረው ማን ነው?” አለ፤ እሱም “አንተ ነህ!” አለው።
ከዚያም አክዓብ የአውራጃዎቹን መኳንንት አገልጋዮች ቆጠረ፤ እነሱም 232 ነበሩ፤ በመቀጠልም የእስራኤልን ወንዶች በሙሉ ቆጠረ፤ እነሱም 7,000 ነበሩ።
እነሱም እኩለ ቀን ላይ ቤንሃዳድ ረዳቶቹ ከሆኑት 32 ነገሥታት ጋር በድንኳኖቹ ውስጥ ሆኖ ሰክሮ ሳለ ወደዚያ ሄዱ።
የአውራጃዎቹ መኳንንት አገልጋዮች ቀድመው በወጡ ጊዜ ቤንሃዳድ ወዲያውኑ መልእክተኞችን ላከ። እነሱም “ከሰማርያ የመጡ ሰዎች አሉ” ብለው ነገሩት።
በዚህ ጊዜ ቤንሃዳድ “ሰዎቹ የመጡት ለሰላም ከሆነ በሕይወት እንዳሉ ያዟቸው፤ የመጡት ለጦርነት ከሆነም በሕይወት እንዳሉ ያዟቸው” አለ።
ሆኖም እነዚህ ማለትም የአውራጃዎቹ መኳንንት አገልጋዮችና እነሱን ይከተላቸው የነበረው ሠራዊት ከከተማዋ ሲወጡ
እያንዳንዳቸው ሊገጥማቸው የመጣውን ሰው ገደሉ። ከዚያም ሶርያውያን ሸሹ፤ እስራኤላውያንም አሳደዷቸው፤ የሶርያ ንጉሥ ቤንሃዳድ ግን በፈረስ ላይ ሆኖ ከተወሰኑ ፈረሰኞች ጋር አመለጠ።
ሆኖም የእስራኤል ንጉሥ ወጥቶ ፈረሶቹንና ሠረገሎቹን መታ፤ በሶርያውያንም ላይ ታላቅ ድል ተቀዳጀ።
በኋላም ነቢዩ ወደ እስራኤል ንጉሥ ቀርቦ “የሶርያ ንጉሥ በሚቀጥለው ዓመት መባቻ ላይ ስለሚመጣብህ ሄደህ ራስህን አጠናክር፤ ምን ማድረግ እንደምትችልም አስብ” አለው።
በዚህ ጊዜ የሶርያን ንጉሥ አገልጋዮቹ እንዲህ አሉት፦ “አምላካቸው የተራሮች አምላክ ነው። በእኛ ላይ ያየሉብንም ለዚህ ነው። ሆኖም ሜዳ ላይ ብንገጥማቸው እናሸንፋቸዋለን።
በተጨማሪም እንዲህ አድርግ፦ ነገሥታቱን በሙሉ ከቦታቸው አንስተህ በምትካቸው አስተዳዳሪዎች አስቀምጥ።
ከዚያም ከተደመሰሰብህ ሠራዊት ጋር የሚመጣጠን ሠራዊት ሰብስብ፤ በፈረሱ ፋንታ ፈረስ፣ በሠረገላውም ፋንታ ሠረገላ ተካ። ከዚያም ሜዳ ላይ እንግጠማቸው፤ ያለምንም ጥርጥር እናሸንፋቸዋለን።” ንጉሡም የሰጡትን ምክር ሰማ፤ እንዳሉትም አደረገ።
በዓመቱ መባቻ ላይም ቤንሃዳድ ሶርያውያንን አሰባስቦ ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት ወደ አፌቅ ወጣ።
የእስራኤል ሰዎችም ከተሰባሰቡና ስንቅ ከተሰጣቸው በኋላ እነሱን ለመግጠም ወጡ። የእስራኤል ሰዎች ፊት ለፊታቸው ሰፍረው ሲታዩ ሁለት ትናንሽ የፍየል መንጋ ይመስሉ ነበር፤ ሶርያውያኑ ግን መላውን ምድር አጥለቅልቀውት ነበር።
ከዚያም የእውነተኛው አምላክ ሰው ወደ እስራኤል ንጉሥ ቀርቦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ሶርያውያን “ይሖዋ የተራሮች አምላክ እንጂ የሜዳ አምላክ አይደለም” ስላሉ ይህን እጅግ ብዙ ሕዝብ በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ እናንተም እኔ ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ታውቃላችሁ’” አለው።
እነሱም ለሰባት ቀን ያህል እንደተፋጠጡ ቆዩ። በሰባተኛውም ቀን ውጊያው ተጀመረ። የእስራኤል ሰዎችም በአንድ ቀን 100,000 ሶርያውያን እግረኛ ወታደሮችን ገደሉ።
የተረፉትም ወደ ከተማዋ ወደ አፌቅ ሸሹ። ሆኖም ከተረፉት ሰዎች መካከል በ27,000ዎቹ ላይ ቅጥሩ ተንዶ ወደቀባቸው። ቤንሃዳድም ሸሽቶ ወደ ከተማዋ ገባ፤ አንድ ክፍል ውስጥ ገብቶም ተሸሸገ።
በመሆኑም አገልጋዮቹ እንዲህ አሉት፦ “የእስራኤል ቤት ነገሥታት መሐሪዎች እንደሆኑ ሰምተናል። እንግዲህ ወገባችንን በማቅ ታጥቀንና ራሳችን ላይ ገመድ አስረን ወደ እስራኤል ንጉሥ እንውጣ። ምናልባት ሕይወትህን ያተርፍልህ ይሆናል።”
ስለሆነም ወገባቸውን በማቅ ታጥቀውና ራሳቸው ላይ ገመድ አስረው ወደ እስራኤል ንጉሥ በመምጣት “አገልጋይህ ቤንሃዳድ ‘እባክህ፣ ሕይወቴን አታጥፋ’ ይላል” አሉት። ንጉሡም “እስካሁን በሕይወት አለ? ወንድሜ እኮ ነው” አለ።
ሰዎቹ ይህን እንደ ጥሩ ገድ በመመልከትና ንጉሡ የተናገረውን በማመን “አዎ፣ ቤንሃዳድ እኮ ወንድምህ ነው” አሉ። ንጉሡም “በሉ ሄዳችሁ አምጡት” አለ። ከዚያም ቤንሃዳድ ወደ እሱ መጣ፤ እሱም ወዲያውኑ ሠረገላው ላይ እንዲወጣ አደረገው።
ቤንሃዳድም “አባቴ ከአባትህ ላይ የወሰዳቸውን ከተሞች እመልሳለሁ፤ አባቴ በሰማርያ እንዳደረገው ሁሉ አንተም በደማስቆ ለራስህ ገበያ ማቋቋም ትችላለህ” አለው። አክዓብም “በዚህ ስምምነት መሠረት አሰናብትሃለሁ” አለው። በዚህም መሠረት ከእሱ ጋር ስምምነት አድርጎ አሰናበተው።
ከነቢያት ልጆች አንዱ በይሖዋ ቃል ታዞ ጓደኛውን “እባክህ ምታኝ” አለው። ሰውየው ግን ሊመታው ፈቃደኛ አልሆነም።
ስለዚህ “የይሖዋን ቃል ስላልሰማህ ከእኔ ተለይተህ እንደሄድክ አንበሳ አግኝቶ ይገድልሃል” አለው። ከእሱ ተለይቶም ሲሄድ አንበሳ አግኝቶ ገደለው።
ከዚያም ሌላ ሰው አግኝቶ “እባክህ ምታኝ” አለው። በመሆኑም ሰውየው መትቶ አቆሰለው።
ከዚያም ይህ ነቢይ ሄዶ ንጉሡን መንገድ ዳር ቆሞ ጠበቀው፤ ማንነቱም እንዳይታወቅ ዓይኖቹን በመጠምጠሚያ ሸፍኖ ነበር።
ንጉሡም በዚያ ሲያልፍ ነቢዩ ጮክ ብሎ ንጉሡን በመጣራት እንዲህ አለ፦ “እኔ አገልጋይህ ወደተፋፋመው ጦርነት ገብቼ ነበር፤ በዚህ ጊዜ አንድ ሰው ከዚያ ወጥቶ የሆነ ሰው ወደ እኔ ይዞ መጣ፤ እንዲህም አለኝ፦ ‘ይህን ሰው ጠብቀው። ይህ ሰው ቢጠፋ በእሱ ሕይወት ፋንታ የአንተ ሕይወት ይተካል፤ ወይም ደግሞ አንድ ታላንት ብር ትከፍላለህ።’
ታዲያ እኔ አገልጋይህ ሥራ በዝቶብኝ ወዲያ ወዲህ ስል ሰውየው ድንገት አምልጦ ሄደ።” የእስራኤልም ንጉሥ “እንግዲህ በራስህ ላይ ፈርደሃል፤ አንተው ራስህ ውሳኔውን አስተላልፈሃል” አለው።
ከዚያም ፈጠን ብሎ መጠምጠሚያውን ከዓይኖቹ ላይ አነሳ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ይህ ሰው ከነቢያት አንዱ መሆኑን አወቀ።
ነቢዩም “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እኔ መጥፋት አለበት ያልኩት ሰው ከእጅህ እንዲያመልጥ ስላደረግክ በእሱ ሕይወት ፋንታ የአንተ ሕይወት ይተካል፤ በእሱም ሕዝብ ፋንታ የአንተ ሕዝብ ይተካል’” አለው።
በዚህ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ፊቱ ጠቁሮና አዝኖ ወደ ቤቱ ወደ ሰማርያ ሄደ።
ሮብዓም እስራኤላውያን በሙሉ ሊያነግሡት ወደ ሴኬም መጥተው ስለነበር እሱም ወደ ሴኬም ሄደ።
የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን እንደሰማ (ምክንያቱም ኢዮርብዓም ከንጉሥ ሰለሞን ሸሽቶ በግብፅ ይኖር ስለነበር በወቅቱ በዚያ ይገኝ ነበር)፣
ልከው አስጠሩት። ከዚያም ኢዮርብዓምና መላው የእስራኤል ጉባኤ መጥተው ሮብዓምን እንዲህ አሉት፦
“አባትህ ቀንበራችንን አክብዶብን ነበር። አንተ ግን አባትህ የሰጠንን አስቸጋሪ ሥራና በላያችን የጫነብንን ከባድ ቀንበር የምታቀልልን ከሆነ እናገለግልሃለን።”
በዚህ ጊዜ “እንግዲያው ሂዱና ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሳችሁ ኑ” አላቸው። በመሆኑም ሕዝቡ ሄደ።
ከዚያም ንጉሥ ሮብዓም አባቱ ሰለሞን በሕይወት በነበረበት ጊዜ ሲያገለግሉት የነበሩትን ሽማግሌዎች “ለዚህ ሕዝብ ምን ምላሽ እንድሰጥ ትመክሩኛላችሁ?” በማለት ምክር ጠየቀ።
እነሱም “ዛሬ አንተ የዚህ ሕዝብ አገልጋይ ብትሆንና የጠየቁህን ብትፈጽምላቸው እንዲሁም መልካም ምላሽ ብትሰጣቸው ምንጊዜም አገልጋዮችህ ይሆናሉ” በማለት መለሱለት።
ሆኖም ሮብዓም ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር ትቶ አብሮ አደጎቹ ከነበሩትና አሁን የእሱ አገልጋዮች ከሆኑት ወጣቶች ጋር ተማከረ።
እሱም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፦ “‘አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልልን’ ለሚለኝ ለዚህ ሕዝብ ምን ምላሽ እንድንሰጥ ትመክሩኛላችሁ?”
አብሮ አደጎቹ የሆኑት ወጣቶችም እንዲህ አሉት፦ “‘አባትህ ቀንበራችንን አክብዶብን ነበር፤ አንተ ግን ቀንበራችንን አቅልልልን’ ለሚልህ ለዚህ ሕዝብ እንዲህ በለው፦ ‘ትንሿ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች።
አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፤ እኔ ግን ቀንበራችሁን የባሰ አከብደዋለሁ። አባቴ በአለንጋ ገርፏችሁ ነበር፤ እኔ ግን በእሾህ አለንጋ እገርፋችኋለሁ።’”
ኢዮርብዓምና መላው ሕዝብ ንጉሡ “በሦስተኛው ቀን ተመልሳችሁ ኑ” ባላቸው መሠረት በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም መጡ።
ንጉሡ ግን ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር ትቶ ለሕዝቡ መጥፎ ምላሽ ሰጠ።
ወጣቶቹም በሰጡት ምክር መሠረት “አባቴ ቀንበራችሁን አክብዶባችሁ ነበር፤ እኔ ግን ቀንበራችሁን የባሰ አከብደዋለሁ። አባቴ በአለንጋ ገርፏችሁ ነበር፤ እኔ ግን በእሾህ አለንጋ እገርፋችኋለሁ” አላቸው።
በመሆኑም ንጉሡ ሕዝቡን ሳይሰማ ቀረ፤ ይህም የሆነው ይሖዋ በሴሎናዊው በአኪያህ አማካኝነት ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ይሖዋ እነዚህ ነገሮች በዚህ መንገድ እንዲከናወኑ ስላደረገ ነው።
እስራኤላውያን ሁሉ ንጉሡ ሊሰማቸው ፈቃደኛ አለመሆኑን ሲያዩ ንጉሡን እንዲህ አሉት፦ “ከዳዊት ምን ድርሻ አለን? ከእሴይ ልጅ ምንም ርስት የለንም። እስራኤል ሆይ፣ ወደ አማልክትህ ተመለስ። ዳዊት ሆይ፣ እንግዲህ የገዛ ቤትህን ጠብቅ!” ከዚያም እስራኤላውያን ወደየቤታቸው ተመለሱ።
ይሁንና ሮብዓም በይሁዳ ከተሞች በሚኖሩት እስራኤላውያን ላይ መግዛቱን ቀጠለ።
ከዚያም ንጉሥ ሮብዓም የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ የተመለመሉት ሰዎች አለቃ የነበረውን አዶራምን ላከው፤ ሆኖም እስራኤላውያን በሙሉ በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ንጉሥ ሮብዓም ግን እንደ ምንም ብሎ ሠረገላው ላይ በመውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሸሸ።
እስራኤላውያንም እስከዚህ ቀን ድረስ በዳዊት ቤት ላይ እንዳመፁ ናቸው።
እስራኤላውያን በሙሉ ኢዮርብዓም መመለሱን እንደሰሙ ወደ ማኅበረሰቡ ካስጠሩት በኋላ በመላው እስራኤል ላይ አነገሡት። ከይሁዳ ነገድ በስተቀር ከሕዝቡ መሃል የዳዊትን ቤት የተከተለ ማንም አልነበረም።
ሮብዓም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከእስራኤል ቤት ጋር ተዋግተው ንግሥናውን ለሰለሞን ልጅ ለሮብዓም እንዲያስመልሱ ከመላው የይሁዳ ቤትና ከቢንያም ነገድ የተውጣጡ 180,000 የሠለጠኑ ተዋጊዎች ወዲያውኑ ሰበሰበ።
ከዚያም የእውነተኛው አምላክ ቃል የእውነተኛው አምላክ ሰው ወደሆነው ወደ ሸማያህ እንዲህ ሲል መጣ፦
“ለይሁዳ ንጉሥ ለሰለሞን ልጅ ለሮብዓም፣ ለይሁዳ ቤት ሁሉ፣ ለቢንያምና ለቀረው ሕዝብ እንዲህ ብለህ ተናገር፦
‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ከወንድሞቻችሁ ከእስራኤላውያን ጋር ለመዋጋት አትውጡ። ይህ እንዲሆን ያደረግኩት እኔ ስለሆንኩ እያንዳንዳችሁ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ።”’” ስለዚህ የይሖዋን ቃል ሰሙ፤ ይሖዋ እንደነገራቸውም ወደየቤታቸው ተመለሱ።
ከዚያም ኢዮርብዓም በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ ሴኬምን ገንብቶ በዚያ መኖር ጀመረ። ከዚያ ወጥቶ በመሄድ ጰኑኤልን ገነባ።
ኢዮርብዓም በልቡ እንዲህ ሲል አሰበ፦ “እንግዲህ አሁን መንግሥቱ ወደ ዳዊት ቤት ይመለሳል።
ይህ ሕዝብ በኢየሩሳሌም በሚገኘው የይሖዋ ቤት መሥዋዕት ለማቅረብ ወደዚያ መውጣቱን ከቀጠለ የዚህ ሕዝብ ልብ ጌታው ወደሆነው ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሮብዓም ይመለሳል። እኔንም ይገድለኛል፤ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሮብዓምም ይመለሳል።”
በመሆኑም ንጉሡ ከተማከረ በኋላ ሁለት የወርቅ ጥጃዎችን ሠርቶ ሕዝቡን “ወደ ኢየሩሳሌም መውጣት መንገላታት ይሆንባችኋል። እስራኤል ሆይ፣ ከግብፅ ምድር ያወጣህ አምላክህ ይኸውልህ” አለ።
ከዚያም አንደኛውን በቤቴል ሌላኛውን ደግሞ በዳን አቆመው።
ይህም ለኃጢአት ዳረጋቸው፤ ሕዝቡም በዳን የሚገኘውን ጥጃ ለማምለክ እስከዚያ ድረስ ይሄድ ነበር።
እሱም በኮረብቶቹ ላይ የአምልኮ ቤቶችን ሠራ፤ ከሕዝቡም መካከል ሌዋውያን ያልሆኑ ሰዎችን ካህናት አድርጎ ሾመ።
በተጨማሪም ኢዮርብዓም በስምንተኛው ወር ከወሩም በ15ኛው ቀን በይሁዳ ይከበር የነበረው ዓይነት በዓል እንዲቋቋም አደረገ። ለሠራቸውም ጥጆች በቤቴል በሠራው መሠዊያ ላይ መሥዋዕት አቀረበ፤ በቤቴል ለሠራቸው ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎችም ካህናት መደበ።
በቤቴል በሠራው መሠዊያም ላይ ራሱ በመረጠው ወር ይኸውም በስምንተኛው ወር በ15ኛው ቀን መባዎችን ማቅረብ ጀመረ፤ ለእስራኤል ሰዎችም በዓል አቋቋመ፤ እንዲሁም መባዎችንና የሚጨሱ መሥዋዕቶችን ለማቅረብ ወደ መሠዊያው ወጣ።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላም በሦስተኛው ዓመት የይሖዋ ቃል “ሂድና አክዓብ ፊት ቅረብ፤ እኔም በምድሩ ላይ ዝናብ አዘንባለሁ” ሲል ወደ ኤልያስ መጣ።
ስለሆነም ኤልያስ አክዓብ ፊት ለመቅረብ ሄደ፤ በዚህ ወቅት ረሃቡ በሰማርያ ክፉኛ ጸንቶ ነበር።
በዚህ ጊዜ አክዓብ በቤቱ ላይ አዛዥ የነበረውን አብድዩን ጠራው። (አብድዩ ይሖዋን በጣም ይፈራ ነበር፤
ኤልዛቤል የይሖዋን ነቢያት እያጠፋች በነበረበት ጊዜም አብድዩ 100 ነቢያትን ወስዶ 50ውን በአንድ ዋሻ 50ውን ደግሞ በሌላ ዋሻ ውስጥ ከደበቃቸው በኋላ ምግብና ውኃ ይሰጣቸው ነበር።)
ከዚያም አክዓብ አብድዩን እንዲህ አለው፦ “በምድሪቱ ላይ ወደሚገኙት የውኃ ምንጮች ሁሉና ሸለቆዎች ሁሉ ሂድ። እንስሶቻችን በሙሉ እንዳያልቁ፣ ፈረሶቹንና በቅሎዎቹን በሕይወት ማቆየት የሚያስችል በቂ ሣር እናገኝ ይሆናል።”
በመሆኑም አቋርጠውት የሚሄዱትን ምድር ተከፋፈሉ። አክዓብ ለብቻው በአንድ በኩል፣ አብድዩም ለብቻው በሌላ በኩል ሄደ።
አብድዩ እየተጓዘ ሳለ ኤልያስን መንገዱ ላይ አገኘው። እሱም ወዲያውኑ ስላወቀው በግንባሩ ተደፋ፤ ከዚያም “ጌታዬ ኤልያስ ሆይ፣ በእርግጥ አንተ ነህ?” አለው።
ኤልያስም “አዎ፣ እኔ ነኝ። ሄደህ ለጌታህ ‘ኤልያስ እዚህ አለ’ ብለህ ንገረው” አለው።
እሱ ግን እንዲህ አለው፦ “እኔ አገልጋይህ እንድሞት ለአክዓብ አሳልፈህ የምትሰጠኝ ምን ኃጢአት ሠርቼ ነው?
ሕያው በሆነው አምላክህ በይሖዋ እምላለሁ፣ ጌታዬ አንተን ፍለጋ ሰው ያልላከበት አንድም ብሔር ሆነ መንግሥት የለም። እነሱም ‘እዚህ የለም’ ባሉት ጊዜ ያ መንግሥትም ሆነ ብሔር አንተን አለማግኘቱን በመሐላ እንዲያረጋግጥለት ያደርግ ነበር።
አንተ ደግሞ አሁን ‘ሄደህ ለጌታህ “ኤልያስ እዚህ አለ” ብለህ ንገረው’ ትለኛለህ።
ከአንተ ተለይቼ ስሄድ የይሖዋ መንፈስ ወደማላውቀው ቦታ ይወስድሃል፤ ለአክዓብ ብነግረውና ሳያገኝህ ቢቀር እንደሚገድለኝ የታወቀ ነው። ነገር ግን እኔ አገልጋይህ ከወጣትነቴ ጀምሮ ይሖዋን ስፈራ ኖሬአለሁ።
ኤልዛቤል የይሖዋን ነቢያት በገደለች ጊዜ ከይሖዋ ነቢያት መካከል 100ዎቹን ወስጄ ሃምሳ ሃምሳ በማድረግ ዋሻ ውስጥ እንደደበቅኳቸው እንዲሁም ምግብና ውኃ እሰጣቸው እንደነበር ጌታዬ አልሰማም?
አሁን ግን አንተ ‘ሄደህ ለጌታህ “ኤልያስ እዚህ አለ” ብለህ ንገረው’ ትለኛለህ። እሱም በእርግጠኝነት ይገድለኛል።”
ሆኖም ኤልያስ “በማገለግለው ሕያው በሆነው በሠራዊት ጌታ በይሖዋ እምላለሁ፣ ዛሬ እሱ ፊት እቀርባለሁ” አለ።
ስለዚህ አብድዩ ወደ አክዓብ ሄዶ ነገረው፤ አክዓብም ኤልያስን ለማግኘት ሄደ።
አክዓብም ልክ ኤልያስን ሲያየው “በእስራኤል ላይ ከፍተኛ ችግር የምትፈጥረው አንተ ነህ?” አለው።
በዚህ ጊዜ ኤልያስ እንዲህ አለው፦ “የይሖዋን ትእዛዛት በመተውና ባአልን በመከተል በእስራኤል ላይ ችግር የምትፈጥሩት አንተና የአባትህ ቤት እንጂ እኔ አይደለሁም።
ይልቅስ አሁን እስራኤላውያንን በሙሉ፣ ከኤልዛቤል ማዕድ ከሚበሉት 450 የባአል ነቢያትና 400 የማምለኪያ ግንድ ነቢያት ጋር በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ሰብስብልኝ።”
በመሆኑም አክዓብ ወደ እስራኤል ሰዎች ሁሉ መልእክት ላከ፤ ነቢያቱንም በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ሰበሰበ።
ከዚያም ኤልያስ ወደ ሕዝቡ ሁሉ ቀርቦ “በሁለት ሐሳብ የምታነክሱት እስከ መቼ ነው? እውነተኛው አምላክ፣ ይሖዋ ከሆነ እሱን ተከተሉ፤ ባአል ከሆነ ደግሞ እሱን ተከተሉ!” አላቸው። ሕዝቡ ግን አንዲት ቃል አልመለሰለትም።
ከዚያም ኤልያስ እንዲህ አላቸው፦ “ከይሖዋ ነቢያት መካከል የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ፤ የባአል ነቢያት ግን 450 ናቸው።
እንግዲህ አሁን ሁለት ወይፈኖች ይስጡን፤ እነሱም አንድ ወይፈን መርጠው በየብልቱ እየቆራረጡ በእንጨቱ ላይ ያድርጉት፤ ሆኖም እሳት አያንድዱበት። እኔ ደግሞ ሌላኛውን ወይፈን አዘጋጅቼ በእንጨቱ ላይ አደርገዋለሁ፤ ሆኖም እሳት አላነድበትም።
ከዚያም እናንተ የአምላካችሁን ስም ትጠራላችሁ፤ እኔም የይሖዋን ስም እጠራለሁ። እሳት በመላክ መልስ የሚሰጠው አምላክ እሱ እውነተኛው አምላክ እንደሆነ ያሳያል።” በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ “ያልከው ነገር ጥሩ ነው” አሉ።
ኤልያስም የባአል ነቢያትን “እናንተ ብዙ ስለሆናችሁ በቅድሚያ አንድ ወይፈን መርጣችሁ አዘጋጁ። ከዚያም የአምላካችሁን ስም ጥሩ፤ ሆኖም እሳት አታንድዱበት” አላቸው።
በመሆኑም የተሰጣቸውን ወይፈን ወስደው አዘጋጁ፤ ከጠዋት አንስቶ እስከ እኩለ ቀን ድረስም “ባአል ሆይ፣ መልስልን!” እያሉ የባአልን ስም ጠሩ። ሆኖም ድምፅ የለም፤ የሚመልስም አልነበረም። በሠሩትም መሠዊያ ዙሪያ እያነከሱ ዞሩ።
እኩለ ቀን ገደማም ኤልያስ እንዲህ በማለት ያፌዝባቸው ጀመር፦ “ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ እንጂ! አምላክ እኮ ነው! ምናልባት በሐሳብ ተውጦ ይሆናል፤ ወይም ሊጸዳዳ ሄዶ ይሆናል። አሊያም ደግሞ ተኝቶ ሊሆን ስለሚችል የሚቀሰቅሰው ያስፈልገው ይሆናል!”
እነሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ይጮኹ እንደ ልማዳቸውም ደም በደም እስኪሆኑ ድረስ ሰውነታቸውን በጩቤና በጦር ይተለትሉ ነበር።
እኩለ ቀን አልፎ የእህል መባ እስከሚቀርብበትም ጊዜ ድረስ እንደ እብድ ሲያደርጋቸው ቆየ፤ ሆኖም ምንም ድምፅ የለም፤ የሚመልስም የለም፤ ትኩረት የሰጠም አልነበረም።