text
stringlengths
4
267
በኋላም ኤልያስ ሕዝቡን ሁሉ “ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ ወደ እሱ ቀረቡ። ከዚያም ፈርሶ የነበረውን የይሖዋን መሠዊያ ጠገነ።
በመቀጠልም ኤልያስ “ስምህ እስራኤል ይባላል” የሚል የይሖዋ ቃል በመጣለት በያዕቆብ ወንዶች ልጆች ነገዶች ቁጥር ልክ 12 ድንጋዮችን ወሰደ።
በድንጋዮቹም በይሖዋ ስም መሠዊያ ሠራ። በመሠዊያውም ዙሪያ ሁለት የሲህ መስፈሪያ ዘር ሊያዘራ የሚችል ስፋት ያለው ቦይ ቆፈረ።
ከዚያም እንጨቶቹን ረበረበ፤ ወይፈኑንም በየብልቱ ቆራርጦ በእንጨቶቹ ላይ አደረገ። ቀጥሎም “በአራት ጋኖች ውኃ ሞልታችሁ በሚቃጠለው መባና በእንጨቱ ላይ አፍስሱ” አለ።
ከዚያም “አሁንም ድገሙ” አለ። እነሱም ደገሙ። “ለሦስተኛ ጊዜ ድገሙ” አላቸው። እነሱም ለሦስተኛ ጊዜ ደገሙ።
ውኃውም መሠዊያውን ዙሪያውን አጥለቀለቀው፤ ቦዩንም በውኃ ሞላው።
ነቢዩ ኤልያስም የምሽቱ የእህል መባ በሚቀርብበት ጊዜ ገደማ ወደ ፊት ቀረብ ብሎ እንዲህ አለ፦ “የአብርሃም፣ የይስሐቅና የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ በእስራኤል ውስጥ አምላክ እንደሆንክ፣ እኔም አገልጋይህ እንደሆንኩና እነዚህን ሁሉ ነገሮች ያደረግኩት በአንተ ቃል እንደሆነ ዛሬ ይታወቅ።
ይሖዋ ሆይ፣ መልስልኝ! እነዚህ ሰዎች አንተ ይሖዋ እውነተኛው አምላክ እንደሆንክና ልባቸውን ወደ አንተ እየመለስክ መሆንህን እንዲያውቁ መልስልኝ።”
በዚህ ጊዜ የይሖዋ እሳት ወርዶ የሚቃጠለውን መባ፣ እንጨቱን፣ ድንጋዮቹንና አፈሩን በላ፤ በቦዩ ውስጥ የነበረውንም ውኃ ላሰ።
ሕዝቡ ሁሉ ይህን ሲያዩ ወዲያውኑ በግንባራቸው ተደፉ፤ ከዚያም “እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ነው! እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ነው!” አሉ።
በዚህ ጊዜ ኤልያስ “የባአልን ነቢያት ያዟቸው! አንዳቸውም እንዳያመልጡ!” አላቸው። እነሱም ወዲያውኑ ያዟቸው፤ ኤልያስም ወደ ቂሾን ጅረት ይዟቸው በመውረድ በዚያ አረዳቸው።
ኤልያስም አክዓብን “የከባድ ዝናብ ድምፅ እያጉረመረመ ስለሆነ ሂድ ብላ፤ ጠጣም” አለው።
በመሆኑም አክዓብ ሊበላና ሊጠጣ ሲወጣ ኤልያስ ደግሞ ወደ ቀርሜሎስ አናት ወጣ፤ ፊቱንም በጉልበቶቹ መካከል አድርጎ ወደ መሬት አቀረቀረ።
ከዚያም አገልጋዩን “እባክህ ውጣና ወደ ባሕሩ አቅጣጫ ተመልከት” አለው። እሱም ወጥቶ ተመለከተና “ኧረ ምንም የለም” አለ። ኤልያስም ሰባት ጊዜ “ተመልሰህ ሂድ” አለው።
በሰባተኛውም ጊዜ አገልጋዩ “እነሆ! የሰው እጅ የምታክል ትንሽ ደመና ከባሕሩ እየወጣች ነው” አለ። ኤልያስም “ሄደህ አክዓብን ‘ሠረገላህን አዘጋጅ! ዝናቡ እንዳያግድህ ወደዚያ ውረድ!’ በለው” አለው።
በዚህ ጊዜ ሰማዩ በደመና ጠቆረ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ከባድ ዝናብም ይጥል ጀመር፤ አክዓብም እየጋለበ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ።
ሆኖም የይሖዋ እጅ በኤልያስ ላይ መጣ፤ እሱም ልብሱን ጠቅልሎ መቀነቱ ውስጥ በመሸጎጥ ከአክዓብ ፊት ፊት እየሮጠ እስከ ኢይዝራኤል ድረስ ሄደ።
እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር በወጡ በ480ኛው ዓመት ይኸውም ሰለሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ዚፍ በተባለው በሁለተኛው ወር ሰለሞን የይሖዋን ቤት መሥራት ጀመረ።
ንጉሥ ሰለሞን ለይሖዋ የሠራው ቤት ርዝመቱ 60 ክንድ፣ ወርዱ 20 ክንድ፣ ቁመቱ ደግሞ 30 ክንድ ነበር።
ከቅድስቱ ፊት ለፊት ያለው በረንዳ ርዝመቱ 20 ክንድ ሲሆን ይህም ከቤቱ ወርድ ጋር እኩል ነው። በረንዳው ከቤቱ አሥር ክንድ ወደ ፊት ወጣ ያለ ነበር።
ለቤቱም እየጠበቡ የሚሄዱ ክፈፎች ያሏቸውን መስኮቶች ሠራ።
በተጨማሪም በቤቱ ግድግዳ ዙሪያ ተቀጥላ ቤት ሠራ። ቤቱ የተሠራው በቤቱ ግድግዳ ዙሪያ ይኸውም በቤተ መቅደሱና በውስጠኛው ክፍል ግድግዳ ዙሪያ ነበር፤ በዚህ መንገድ በዙሪያው ተቀጥላ ክፍሎችን ሠራ።
የታችኛው ተቀጥላ ክፍል ወርድ አምስት ክንድ፣ የመካከለኛው ወርድ ስድስት ክንድ፣ የላይኛው ወርድ ደግሞ ሰባት ክንድ ነበር፤ ከቤቱ ግድግዳ ጋር የሚያያዝ ምንም ነገር እንዳይኖር በቤቱ ግድግዳ ዙሪያ ተሸካሚዎችን ሠርቶ ነበር።
ቤቱ የተገነባው ሁሉ ነገር ባለቀለት ተፈልፍሎ በወጣ ድንጋይ ነበር፤ በመሆኑም ቤቱ በተገነባበት ጊዜ የመዶሻ ወይም የመጥረቢያ አሊያም የማንኛውም የብረት መሣሪያ ድምፅ ቤቱ ውስጥ አልተሰማም።
የታችኛው ተቀጥላ ክፍል መግቢያ የሚገኘው በስተ ደቡብ በኩል ባለው የቤቱ ጎን ነበር፤ በተጨማሪም ከታችኛው ወደ መካከለኛው ደርብ እንዲሁም ከመካከለኛው ወደ ላይኛው ደርብ የሚያስወጣ ጠመዝማዛ ደረጃ ነበር።
እሱም ቤቱን ገንብቶ አጠናቀቀ፤ ቤቱንም ከአርዘ ሊባኖስ በተሠሩ ተሸካሚዎችና ርብራቦች ከደነው።
በቤቱ ዙሪያ እያንዳንዳቸው ቁመታቸው አምስት ክንድ የሆነ ተቀጥላ ክፍሎችን ሠራ፤ ክፍሎቹም ከቤቱ ጋር በአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎች ተያይዘው ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሰለሞን መጣ፦
“በደንቦቼ ብትሄድ፣ ፍርዶቼን ብትፈጽምና በትእዛዛቴ መሠረት በመሄድ ሁሉንም ብትጠብቃቸው እኔም እየገነባህ ያለኸውን ይህን ቤት በተመለከተ ለአባትህ ለዳዊት የገባሁለትን ቃል እፈጽምልሃለሁ፤
እንዲሁም በእስራኤላውያን መካከል እኖራለሁ፤ ሕዝቤን እስራኤልንም አልተውም።”
ሰለሞንም ቤቱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ የግንባታ ሥራውን ገፋበት።
ውስጠኛውን የቤቱን ግድግዳ በአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎች ሠራ። ቤቱንም ከወለሉ አንስቶ እስከ ኮርኒሱ ወራጆች ድረስ በሳንቃ ለበጠ፤ የቤቱንም ወለል በጥድ ጣውላ ለበጠው።
እንዲሁም ከቤቱ በስተ ኋላ በኩል ከወለሉ አንስቶ እስከ ወራጁ ድረስ በአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎች የተሠራ ባለ 20 ክንድ ክፍል ገነባ፤ በውስጡም፣ የውስጠኛውን ክፍል ይኸውም ቅድስተ ቅዱሳኑን ሠራ።
ከፊቱ ያለው የቤቱ ክፍል ይኸውም ቤተ መቅደሱ 40 ክንድ ነበር።
በቤቱ በውስጠኛው በኩል ያለው አርዘ ሊባኖስ የቅሎችና የፈኩ አበቦች ምስል ተቀርጾበት ነበር። ሙሉ በሙሉ በአርዘ ሊባኖስ የተሠራ ነበር፤ ምንም የሚታይ ድንጋይ አልነበረም።
እሱም የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት በዚያ ለማስቀመጥ ቤቱ ውስጥ የውስጠኛውን ክፍል አዘጋጀ።
ውስጠኛው ክፍል ርዝመቱ 20 ክንድ፣ ወርዱ 20 ክንድ እንዲሁም ቁመቱ 20 ክንድ ነበር፤ በንጹሕ ወርቅም ለበጠው፤ መሠዊያውንም በአርዘ ሊባኖስ ለበጠው።
ሰለሞን ቤቱን ከውስጥ በኩል በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ በወርቅ በተለበጠው በውስጠኛው ክፍል ፊት ለፊትም የወርቅ ሰንሰለት ዘረጋ።
ቤቱ ሙሉ በሙሉ እስኪለበጥ ድረስ ቤቱን በሙሉ በወርቅ ለበጠው፤ በውስጠኛው ክፍል አጠገብ ያለውን መሠዊያም ሙሉ በሙሉ በወርቅ ለበጠው።
በውስጠኛው ክፍል ውስጥ እያንዳንዳቸው አሥር ክንድ ቁመት ያላቸውን ሁለት ኪሩቦች ከጥድ እንጨት ሠራ።
የኪሩቡ አንድ ክንፍ አምስት ክንድ ሲሆን ሌላኛውም ክንፉ አምስት ክንድ ነበር። ከአንዱ ክንፍ ጫፍ እስከ ሌላው ክንፍ ጫፍ አሥር ክንድ ነበር።
ሁለተኛውም ኪሩብ አሥር ክንድ ነበር። ሁለቱ ኪሩቦች ተመሳሳይ መጠንና ቅርጽ ነበራቸው።
የአንደኛው ኪሩብ ቁመት አሥር ክንድ ነበር፤ የሌላኛውም ኪሩብ እንደዚሁ ነበር።
ከዚያም ኪሩቦቹን ውስጠኛው ክፍል ውስጥ አስቀመጣቸው። የኪሩቦቹም ክንፎች ተዘርግተው ስለነበር የአንደኛው ኪሩብ ክንፍ አንደኛው ግድግዳ ጋ፣ የሌላኛው ኪሩብ ክንፍ ደግሞ ሌላኛው ግድግዳ ጋ ይደርስ ነበር፤ ወደ ቤቱ መሃል የተዘረጉት ክንፎቻቸው ደግሞ ይነካኩ ነበር።
ኪሩቦቹንም በወርቅ ለበጣቸው።
በቤቱ ግድግዳ ሁሉ ላይ ይኸውም በውስጠኛውና በውጨኛው ክፍሎች ዙሪያ ሁሉ የኪሩቦችን፣ የዘንባባ ዛፎችንና የፈኩ አበቦችን ምስል ቀረጸ፤
የቤቱን ወለል ይኸውም የውስጠኛውንም ሆነ የውጨኛውን ክፍሎች ወለል በወርቅ ለበጠው።
ለውስጠኛው ክፍል መግቢያ የሚሆኑ በሮችን፣ በጎንና በጎን የሚቆሙ ዓምዶችንና መቃኖችን አንድ አምስተኛ አድርጎ ከጥድ እንጨት ሠራ።
ሁለቱ በሮች ከጥድ እንጨት የተሠሩ ነበሩ፤ በበሮቹም ላይ የኪሩቦችን፣ የዘንባባ ዛፎችንና የፈኩ አበቦችን ምስል ቀረጸባቸው፤ በወርቅም ለበጣቸው፤ ደግሞም ወርቁን በኪሩቦቹና በዘንባባ ዛፎቹ ላይ ጠፈጠፈው።
ለቤተ መቅደሱ መግቢያ የሚሆኑትንና የአንድ አራተኛው ክፍል የሆኑትን የጥድ እንጨት መቃኖች የሠራው በዚሁ መንገድ ነበር።
እሱም ከጥድ እንጨት ሁለት በሮች ሠራ። ሁለት ታጣፊ ሳንቃዎች ያሉት አንዱ በር በመሽከርከሪያዎቹ ላይ፣ ሁለት ታጣፊ ሳንቃዎች ያሉት ሌላኛውም በር በመሽከርከሪያዎቹ ላይ ተገጥሞ ነበር።
እሱም ኪሩቦችን፣ የዘንባባ ዛፎችንና የፈኩ አበቦችን ምስል ቀረጸ፤ ቅርጾቹንም በወርቅ ለበጣቸው።
የውስጠኛውንም ግቢ ወደ ላይ በተነባበረ ሦስት ረድፍ ጥርብ ድንጋይና በአንድ ረድፍ የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃ ሠራው።
በ4ኛው ዓመት በዚፍ ወር የይሖዋ ቤት መሠረት ተጣለ፤
በ11ኛው ዓመት በቡል ወር (ማለትም በስምንተኛው ወር) የቤቱ እያንዳንዱ ነገር በንድፉ መሠረት ተሠርቶ ተጠናቀቀ። በመሆኑም ቤቱን ገንብቶ ለመጨረስ ሰባት ዓመት ፈጀበት።
በዚህ ጊዜ ሰለሞን የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ የነገዶቹን መሪዎች ሁሉና የእስራኤልን የአባቶች ቤት አለቆች ሰበሰበ። እነሱም የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ማለትም ከጽዮን ለማምጣት በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ ንጉሥ ሰለሞን መጡ።
የእስራኤል ሰዎች በሙሉ በሰባተኛው ወር ማለትም በኤታኒም ወር በሚከበረው በዓል ላይ ንጉሥ ሰለሞን ፊት ተሰበሰቡ።
የእስራኤል ሽማግሌዎችም በሙሉ መጡ፤ ካህናቱም ታቦቱን አነሱ።
የይሖዋን ታቦት፣ የመገናኛ ድንኳኑንና በድንኳኑ ውስጥ የነበሩትን ቅዱስ ዕቃዎች በሙሉ አመጡ። እነዚህንም ያመጡት ካህናቱና ሌዋውያኑ ናቸው።
ንጉሥ ሰለሞንና ወደ እሱ እንዲመጣ የተጠራው መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ታቦቱ ፊት ነበሩ። ከብዛታቸው የተነሳ ሊቆጠሩ የማይችሉ ብዙ በጎችና ከብቶች መሥዋዕት ሆነው ቀረቡ።
ከዚያም ካህናቱ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት አምጥተው ቦታው ላይ ማለትም በቤቱ ውስጠኛ ክፍል ይኸውም በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ከኪሩቦቹ ክንፎች በታች አስቀመጡት።
የኪሩቦቹ ክንፎች ታቦቱ ባለበት ቦታ ላይ ተዘርግተው ስለነበር ኪሩቦቹ ታቦቱንና መሎጊያዎቹን ከላይ ከልለዋቸው ነበር።
መሎጊያዎቹ ረጅም ስለነበሩ የመሎጊያዎቹን ጫፎች ከውስጠኛው ክፍል ፊት ለፊት ባለው በቅድስቱ ውስጥ ሆኖ ማየት ይቻል ነበር፤ ከውጭ ግን አይታዩም ነበር። እስከ ዛሬም ድረስ እዚያው ይገኛሉ።
የእስራኤል ሰዎች ከግብፅ ምድር ሲወጡ ይሖዋ ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን በገባበት ጊዜ ሙሴ በኮሬብ ታቦቱ ውስጥ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች በስተቀር በታቦቱ ውስጥ ምንም አልነበረም።
ካህናቱ ከቅዱሱ ስፍራ በወጡ ጊዜ ደመናው የይሖዋን ቤት ሞላው።
የይሖዋ ክብር የይሖዋን ቤት ሞልቶት ስለነበር ካህናቱ ከደመናው የተነሳ በዚያ ቆመው ማገልገል አልቻሉም።
በዚህ ጊዜ ሰለሞን እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደሚኖር ተናግሯል።
እኔም እጅግ ከፍ ያለ ቤት፣ ለዘላለም የምትኖርበት ጸንቶ የተመሠረተ ቦታ ገንብቼልሃለሁ።”
ከዚያም መላው የእስራኤል ጉባኤ ቆሞ ሳለ ንጉሡ ዞሮ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መባረክ ጀመረ።
እንዲህም አለ፦ “ለአባቴ ለዳዊት በገዛ አፉ እንዲህ ብሎ ቃል የገባውና ይህን በራሱ እጅ የፈጸመው የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ይወደስ፦
‘ሕዝቤን እስራኤልን ከግብፅ ካወጣሁበት ዕለት አንስቶ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል ስሜ የሚጠራበት ቤት እንዲሠራበት አንድም ከተማ አልመረጥኩም፤ ዳዊትን ግን በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ገዢ እንዲሆን መረጥኩ።’
አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ስም ቤት ለመሥራት ከልቡ ተመኝቶ ነበር።
ሆኖም ይሖዋ አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ ‘ለስሜ ቤት ለመሥራት ከልብህ ተመኝተህ ነበር፤ ይህን በልብህ መመኘትህም መልካም ነው።
ይሁንና ቤቱን የምትሠራው አንተ አይደለህም፤ ሆኖም ለስሜ ቤት የሚሠራልኝ የሚወለድልህ የገዛ ልጅህ ይሆናል።’
ይሖዋ የገባውን ቃል ፈጽሟል፤ ልክ ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት አባቴን ዳዊትን ተክቼ በእስራኤል ዙፋን ላይ ተቀምጫለሁና። በተጨማሪም ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ስም ቤት ሠርቻለሁ፤
እንዲሁም አባቶቻችንን ከግብፅ ምድር ባወጣቸው ጊዜ ይሖዋ ከእነሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን የያዘው ታቦት የሚያርፍበትን ቦታ በዚያ አዘጋጅቻለሁ።”
ከዚያም ሰለሞን በይሖዋ መሠዊያ ፊት፣ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ለፊት ቆሞ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤
እንዲህም አለ፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ በፊቱ በሙሉ ልባቸው ለሚመላለሱ አገልጋዮቹ ቃል ኪዳኑን የሚጠብቅና ታማኝ ፍቅር የሚያሳይ እንደ አንተ ያለ አምላክ በላይ በሰማይም ሆነ በታች በምድር የለም።
ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸውን ቃል ጠብቀሃል። በገዛ አፍህ ቃል ገባህ፤ ዛሬ ደግሞ በራስህ እጅ ፈጸምከው።
አሁንም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ ‘አንተ በፊቴ እንደተመላለስከው ሁሉ ልጆችህም በጥንቃቄ በፊቴ ከተመላለሱ ከዘርህ በእስራኤል ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ከፊቴ ፈጽሞ አይታጣም’ በማለት ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸውን ቃል ጠብቅ።
አሁንም የእስራኤል አምላክ ሆይ፣ እባክህ ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸው ቃል ይፈጸም።
“በእርግጥ አምላክ በምድር ላይ ይኖራል? እነሆ ሰማያት፣ አዎ ሰማየ ሰማያት እንኳ ሊይዙህ አይችሉም፤ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤትማ ምንኛ ያንስ!
እንግዲህ አምላኬ ይሖዋ ሆይ፣ የአገልጋይህን ጸሎትና ሞገስ ለማግኘት የሚያቀርበውን ልመና በትኩረት ስማ፤ አገልጋይህ እርዳታ ለማግኘት የሚያሰማውን ጩኸትና በዛሬው ዕለት በፊትህ የሚያቀርበውን ጸሎት አዳምጥ።
አገልጋይህ ወደዚህ ስፍራ የሚያቀርበውን ጸሎት ለመስማት ‘ስሜ በዚያ ይሆናል’ ወዳልከው ወደዚህ ቤት ዓይኖችህ ቀንና ሌሊት ይመልከቱ።
አገልጋይህ ሞገስ ለማግኘት የሚያቀርበውን ልመናና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ በመጸለይ የሚያቀርበውን ልመና አዳምጥ፤ በሰማያት ባለው ማደሪያህ ሆነህ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል።
“አንድ ሰው ባልንጀራውን በድሎ እንዲምል ቢደረግ፣ በመሐላውም ተጠያቂ ቢሆን፣ በዳዩም በዚህ መሐላ ሥር ሆኖ እዚህ ቤት ውስጥ ባለው መሠዊያህ ፊት ቢቀርብ፣
አንተ በሰማያት ሆነህ ስማ፤ ክፉውን ጥፋተኛ በማለትና እንደ ሥራው በመመለስ፣ ጻድቁንም ንጹሕ መሆኑን በማሳወቅና እንደ ጽድቁ ወሮታውን በመክፈል እርምጃ ውሰድ፤ አገልጋዮችህንም ዳኝ።
“ሕዝብህ እስራኤላውያን አንተን ከመበደላቸው የተነሳ በጠላት ድል ቢነሱና ወደ አንተ ተመልሰው ስምህን ቢያወድሱ እንዲሁም በዚህ ቤት ወደ አንተ ቢጸልዩና ሞገስ ለማግኘት ልመና ቢያቀርቡ
ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ የሕዝብህንም የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ለአባቶቻቸው ወደሰጠኸው ምድርም መልሳቸው።
“ሕዝቡ አንተን በመበደሉ የተነሳ ሰማያት ተዘግተው ዝናብ ቢጠፋ፣ እነሱም አንተ ስላዋረድካቸው ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩና ስምህን ቢያወድሱ እንዲሁም ከኃጢአታቸው ቢመለሱ
ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ የአገልጋዮችህን፣ የሕዝብህን የእስራኤላውያንን ኃጢአት ይቅር በል፤ ስለሚሄዱበት ቀና መንገድ ታስተምራቸዋለህና፤ ለሕዝብህ ርስት አድርገህ ባወረስከው ምድርህም ላይ ዝናብ አዝንብ።
“በምድሪቱ ላይ ረሃብ ወይም ቸነፈር፣ የሚለበልብና የሚያደርቅ ነፋስ ወይም ዋግ ቢከሰት፣ የአንበጣ መንጋ ወይም የማይጠግብ አንበጣ ቢመጣ አሊያም ጠላቶቻቸው በምድሪቱ ላይ ባለ በየትኛውም ከተማ ውስጥ ሳሉ ቢከቧቸው ወይም ደግሞ ማንኛውም ዓይነት መቅሰፍት አሊያም ማንኛውም ዓይነት በሽታ ቢከሰትና
ማንኛውም ሰው ወይም ሕዝብህ እስራኤል በሙሉ (እያንዳንዱ የልቡን ጭንቀት ያውቃልና) ወደ አንተ ለመጸለይ ወይም ሞገስ እንድታሳየው ልመና ለማቅረብ እጁን ወደዚህ ቤት ቢዘረጋ
አንተ ከመኖሪያ ቦታህ ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ ደግሞም ይቅር በል፤ እርምጃም ውሰድ፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው ብድራቱን ክፈለው፤ ምክንያቱም አንተ ልቡን ታውቃለህ (የሰውን ልብ በሚገባ የምታውቀው አንተ ብቻ ነህ)፤
ይህም ለአባቶቻችን በሰጠኸው ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ አንተን እንዲፈሩ ነው።
“በተጨማሪም ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ የባዕድ አገር ሰው በስምህ የተነሳ ከሩቅ አገር ቢመጣ፣
(መቼም ስለ ታላቁ ስምህ፣ ስለ ኃያሉ እጅህና ስለተዘረጋው ክንድህ መስማታቸው አይቀርም) ወደዚህም ቤት መጥቶ ቢጸልይ
ከመኖሪያ ቦታህ ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ስምህን እንዲያውቁና እንዲፈሩህ እንዲሁም ስምህ እኔ በሠራሁት በዚህ ቤት እንደሚጠራ እንዲያውቁ ያ የባዕድ አገር ሰው የጠየቀህን ሁሉ ፈጽምለት።
“ሕዝብህ ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ በምትልካቸው መንገድ ለጦርነት ቢወጡና አንተ ወደመረጥከው ከተማ እንዲሁም ለስምህ ወደሠራሁት ቤት አቅጣጫ ወደ ይሖዋ ቢጸልዩ
ከሰማያት ሆነህ ጸሎታቸውንና ሞገስ ለማግኘት የሚያቀርቡትን ልመና ስማ፤ ፍረድላቸውም።