text
stringlengths
4
267
ይሁንና የአካዝያስ እህት የሆነችው የንጉሥ ኢዮራም ልጅ የሆሼባ ሊገደሉ ከነበሩት የንጉሡ ልጆች መካከል የአካዝያስን ልጅ ኢዮዓስን ሰርቃ በመውሰድ እሱንና ሞግዚቱን በውስጠኛው መኝታ ክፍል አስቀመጠቻቸው። እነሱም ጎቶልያ እንዳታየው ደብቀው አቆዩት፤ በመሆኑም ሳይገደል ቀረ።
እሱም ከእሷ ጋር ለስድስት ዓመት በይሖዋ ቤት ተደብቆ ቆየ፤ በዚህ ጊዜ ጎቶልያ በምድሪቱ ላይ ትገዛ ነበር።
በሰባተኛው ዓመት ዮዳሄ መልእክት ልኮ ካራውያን ጠባቂዎቹንና የቤተ መንግሥቱን ዘቦች የሚያዙትን መቶ አለቆች እሱ ወዳለበት ወደ ይሖዋ ቤት አስመጣ። ከዚያም ከእነሱ ጋር ስምምነት አደረገ፤ እንዲሁም በይሖዋ ቤት ውስጥ አስማላቸው፤ ይህን ካደረገም በኋላ የንጉሡን ልጅ አሳያቸው።
እንዲህም ሲል አዘዛቸው፦ “እናንተም እንዲህ ታደርጋላችሁ፦ ከመካከላችሁ አንድ ሦስተኛ የምትሆኑት በሰንበት ቀን ገብታችሁ የንጉሡን ቤት በተጠንቀቅ ትጠብቃላችሁ፤
አንድ ሦስተኛ የምትሆኑት ደግሞ በመሠረት በር ላይ ትሆናላችሁ፤ ሌላው አንድ ሦስተኛ ከቤተ መንግሥቱ ዘቦች ኋላ ባለው በር ላይ ይሆናል። ቤቱን በየተራ ትጠብቃላችሁ።
ከመካከላችሁ በሰንበት ቀን ከሥራ ነፃ የሚሆኑት ሁለቱ ቡድኖች ንጉሡን ከጥቃት ለመከላከል የይሖዋን ቤት በተጠንቀቅ ይጠብቁ።
እያንዳንዳችሁ የጦር መሣሪያችሁን በእጃችሁ ይዛችሁ ንጉሡን ዙሪያውን ክበቡት። ረድፉን ጥሶ የገባ ማንኛውም ሰው ይገደላል። ንጉሡ በሚሄድበት ሁሉ አብራችሁት ሁኑ።”
መቶ አለቆቹ ልክ ካህኑ ዮዳሄ እንዳዘዛቸው አደረጉ። እያንዳንዳቸውም በሰንበት ቀን ተረኛ የሚሆኑትንና በሰንበት ቀን ከሥራ ነፃ የሚሆኑትን የራሳቸውን ሰዎች ይዘው ወደ ካህኑ ወደ ዮዳሄ መጡ።
ከዚያም ካህኑ በይሖዋ ቤት የነበሩትን የንጉሥ ዳዊት ጦሮችና ክብ ጋሻዎች ለመቶ አለቆቹ ሰጣቸው።
የቤተ መንግሥቱ ዘቦችም እያንዳንዳቸው የጦር መሣሪያቸውን ይዘው በስተ ቀኝ በኩል ካለው የቤቱ ጎን አንስቶ በስተ ግራ በኩል እስካለው የቤቱ ጎን ድረስ በመሠዊያውና በቤቱ አጠገብ በንጉሡ ዙሪያ ቆሙ።
ከዚያም ዮዳሄ የንጉሡን ልጅ አውጥቶ አክሊሉን ጫነበት፤ ምሥክሩንም ሰጠው፤ በዚህም መንገድ አነገሡት፤ ደግሞም ቀቡት። እያጨበጨቡም “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!” ይሉ ጀመር።
ጎቶልያ ሕዝቡ ሲሯሯጥ ስትሰማ ወዲያውኑ በይሖዋ ቤት ወዳለው ሕዝብ መጣች።
ከዚያም በነበረው ልማድ መሠረት ንጉሡ ዓምዱ አጠገብ ቆሞ አየች። አለቆቹና መለከት ነፊዎቹ ከንጉሡ ጋር ነበሩ፤ የምድሪቱም ሕዝብ ሁሉ እጅግ እየተደሰተና መለከት እየነፋ ነበር። በዚህ ጊዜ ጎቶልያ ልብሷን ቀዳ “ይህ ሴራ ነው! ሴራ ነው!” በማለት ጮኸች።
ካህኑ ዮዳሄ ግን በሠራዊቱ ላይ የተሾሙትን መቶ አለቆች “ከረድፉ መካከል አውጧት፤ እሷን ተከትሎ የሚመጣ ሰው ካለ በሰይፍ ግደሉት!” በማለት አዘዛቸው። ካህኑ “በይሖዋ ቤት ውስጥ እንዳትገድሏት” ብሎ ነበር።
በመሆኑም ያዟት፤ ፈረሶች ወደ ንጉሡ ቤት የሚገቡበት ቦታ ላይ ስትደርስ ተገደለች።
ከዚያም ዮዳሄ የይሖዋ ሕዝብ ሆነው እንዲቀጥሉ ይሖዋ፣ ንጉሡና ሕዝቡ ቃል ኪዳን እንዲጋቡ አደረገ፤ በተጨማሪም ንጉሡና ሕዝቡ ቃል ኪዳን እንዲጋቡ አደረገ።
ከዚህም በኋላ የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ ወደ ባአል ቤት መጥቶ መሠዊያዎቹን አፈራረሰ፤ ምስሎቹንም እንክትክት አድርጎ ሰባበረ፤ የባአል ካህን የነበረውን ማታንንም በመሠዊያዎቹ ፊት ገደሉት። ከዚያም ካህኑ በይሖዋ ቤት ላይ የበላይ ተመልካቾችን ሾመ።
በተጨማሪም ንጉሡን አጅበው ከይሖዋ ቤት ወደ ታች እንዲያመጡት መቶ አለቆቹን፣ ካራውያን ጠባቂዎቹን፣ የቤተ መንግሥት ዘቦቹንና የምድሪቱን ሕዝብ ሁሉ ሰበሰበ፤ እነሱም ወደ ቤተ መንግሥቱ ዘቦች በር በሚወስደው መንገድ በኩል ወደ ንጉሡ ቤት መጡ። እሱም በነገሥታቱ ዙፋን ላይ ተቀመጠ።
በመሆኑም የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ እጅግ ተደሰተ፤ ጎቶልያንም በንጉሡ ቤት በሰይፍ ስለገደሏት ከተማዋ ጸጥታ ሰፈነባት።
ኢዮዓስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር።
አክዓብ ከሞተ በኋላ ሞዓብ በእስራኤል ላይ ዓመፀ።
በዚህ ወቅት አካዝያስ በሰማርያ በሚገኘው ቤቱ ሰገነት ላይ ካለው ክፍል በርብራቡ ሾልኮ በመውደቁ ጉዳት ደርሶበት ነበር። በመሆኑም “ከደረሰብኝ ጉዳት እድን እንደሆነና እንዳልሆነ ማወቅ እንድችል ሄዳችሁ የኤቅሮንን አምላክ ባአልዜቡብን ጠይቁልኝ” በማለት መልእክተኞች ላከ።
የይሖዋ መልአክ ግን ቲሽባዊውን ኤልያስን እንዲህ አለው፦ “ተነስተህ የሰማርያን ንጉሥ መልእክተኞች ለማግኘት ውጣ፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘የኤቅሮንን አምላክ ባአልዜቡብን ለመጠየቅ የምትሄዱት በእስራኤል አምላክ ስለሌለ ነው?
ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ከተኛህበት አልጋ ላይ አትነሳም፤ በእርግጥ ትሞታለህ።”’” ከዚያም ኤልያስ ሄደ።
መልእክተኞቹ ወደ እሱ ተመልሰው ሲመጡ አካዝያስ “ለምን ተመልሳችሁ መጣችሁ?” አላቸው።
እነሱም እንዲህ አሉት፦ “እኛን ለማግኘት የመጣ አንድ ሰው ነበር፤ እሱም እንዲህ አለን፦ ‘ሂዱ፣ ወደላካችሁ ንጉሥ ተመልሳችሁ እንዲህ በሉት፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የኤቅሮንን አምላክ ባአልዜቡብን ለመጠየቅ መልእክተኛ የምትልከው በእስራኤል አምላክ ስለሌለ ነው? ስለዚህ ከተኛህበት አልጋ ላይ አትነሳም፤ በእርግጥ ትሞታለህ።’”’”
በዚህ ጊዜ አካዝያስ “እናንተን ለማግኘት የመጣውና ይህን የነገራችሁ ሰው ምን ይመስላል?” ብሎ ጠየቃቸው።
እነሱም “ሰውየው ፀጉራም ልብስ የለበሰ ሲሆን ወገቡም ላይ የቆዳ ቀበቶ ታጥቋል” አሉት። እሱም ወዲያውኑ “ይሄማ ቲሽባዊው ኤልያስ ነው” አለ።
ከዚያም ንጉሡ አንድ ሃምሳ አለቃ በሥሩ ካሉት 50 ሰዎች ጋር ላከ። ሃምሳ አለቃው ወደ እሱ ሲወጣ ኤልያስ ተራራው አናት ላይ ተቀምጦ ነበር። ሃምሳ አለቃውም “አንተ የእውነተኛው አምላክ ሰው፣ ንጉሡ ‘ና ውረድ’ ብሎሃል” አለው።
ኤልያስ ግን ሃምሳ አለቃውን “እኔ የአምላክ ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ አንተንና ከአንተ ጋር ያሉትን 50 ሰዎች ይብላ” አለው። ከዚያም እሳት ከሰማይ ወርዶ እሱንና 50ዎቹን ሰዎች በላ።
በመሆኑም ንጉሡ እንደገና ሌላ ሃምሳ አለቃ በሥሩ ካሉት 50 ሰዎች ጋር ወደ ኤልያስ ላከ። እሱም ሄዶ ኤልያስን “አንተ የእውነተኛው አምላክ ሰው፣ ንጉሡ ‘ና ፈጥነህ ውረድ’ ብሎሃል” አለው።
ኤልያስ ግን “እኔ የእውነተኛው አምላክ ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ አንተንና ከአንተ ጋር ያሉትን 50 ሰዎች ይብላ” አላቸው። ከዚያም የአምላክ እሳት ከሰማይ ወርዶ እሱንና 50ዎቹን ሰዎች በላ።
ከዚያም ንጉሡ እንደገና ለሦስተኛ ጊዜ አንድ ሃምሳ አለቃ በሥሩ ካሉት 50 ሰዎች ጋር ላከ። ሆኖም ሦስተኛው ሃምሳ አለቃ ወጥቶ በኤልያስ ፊት በጉልበቱ ተንበርክኮ ሰገደ፤ ሞገስ እንዲያሳየውም እየለመነ እንዲህ አለው፦ “አንተ የእውነተኛው አምላክ ሰው፣ እባክህ የእኔም ሕይወት ሆነ የእነዚህ 50 አገልጋዮችህ ሕይወት በፊትህ የከበረ ይሁን።
ከዚህ በፊት እሳት ከሰማይ ወርዶ ሁለቱን ሃምሳ አለቆችና አብረዋቸው የነበሩትን ሃምሳ ሃምሳ ሰዎች በልቷል፤ አሁን ግን ነፍሴ በፊትህ የከበረች ትሁን።”
በዚህ ጊዜ የይሖዋ መልአክ ኤልያስን “አብረኸው ውረድ። አትፍራው” አለው። በመሆኑም ኤልያስ ተነስቶ አብሮት ወደ ንጉሡ ወረደ።
ከዚያም ኤልያስ ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የኤቅሮንን አምላክ ባአልዜቡብን ለመጠየቅ መልእክተኞች ልከሃል። ይህን ያደረግከው በእስራኤል አምላክ ስለሌለ ነው? ለምን የእስራኤልን አምላክ አልጠየቅክም? ስለዚህ ከተኛህበት አልጋ ላይ አትነሳም፤ በእርግጥ ትሞታለህ።’”
በመሆኑም ይሖዋ በኤልያስ አማካኝነት በተናገረው ቃል መሠረት ሞተ፤ አካዝያስ ወንድ ልጅ ስላልነበረው ኢዮራም በምትኩ ነገሠ፤ ይህ የሆነው የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሳፍጥ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ነው።
የቀረው የአካዝያስ ታሪክ፣ ያደረገው ነገር በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ ይገኝ የለም?
ኤልሳዕም እንዲህ አለ፦ “የይሖዋን ቃል ስሙ። ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ነገ በዚህ ሰዓት ገደማ በሰማርያ በር ላይ አንድ የሲህ መስፈሪያ የላመ ዱቄት በአንድ ሰቅል እንዲሁም ሁለት የሲህ መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል ይሸጣል።’”
በዚህ ጊዜ ንጉሡ የሚተማመንበት የጦር መኮንን የእውነተኛውን አምላክ ሰው “ይሖዋ የሰማይን የውኃ በሮች ቢከፍት እንኳ እንዲህ ያለ ነገር ሊፈጸም ይችላል?” አለው። ኤልሳዕም “ይህን በገዛ ዓይኖችህ ታያለህ፤ ሆኖም ከዚያ ምንም አትቀምስም” አለው።
በከተማዋ መግቢያ በር ላይ በሥጋ ደዌ የተያዙ አራት ሰዎች ነበሩ፤ እነሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ “እስክንሞት ድረስ እዚህ ቁጭ የምንለው ለምንድን ነው?
‘ወደ ከተማዋ እንግባ’ ብንል ከተማዋ ውስጥ ረሃብ ስላለ እዚያ መሞታችን አይቀርም። እዚህም ብንቀመጥ ያው የሚጠብቀን ሞት ነው። ስለዚህ ዝም ብለን ወደ ሶርያውያን ሰፈር እንሂድ። ካልገደሉን ሕይወታችን ይተርፋል፤ ከገደሉንም ያው ሞቶ መገላገል ነው።”
ከዚያም ጨለምለም ሲል ተነስተው ወደ ሶርያውያን ሰፈር ሄዱ። ወደ ሶርያውያን ሰፈር ዳርቻ በደረሱ ጊዜ በዚያ አንድም ሰው አልነበረም።
ምክንያቱም ይሖዋ የሶርያውያን ሰፈር የጦር ሠረገሎችን ድምፅ፣ የፈረሶችን ድምፅና የታላቅ ሠራዊት ድምፅ እንዲሰማ አድርጎ ነበር። በመሆኑም እርስ በርሳቸው “የእስራኤል ንጉሥ እኛን ለመውጋት የሂታውያንንና የግብፅን ነገሥታት ቀጥሮብናል!” ተባባሉ።
እነሱም ወዲያውኑ ተነስተው በምሽት ሸሹ፤ ድንኳኖቻቸውን፣ ፈረሶቻቸውንና አህዮቻቸውን እንዲሁም ሰፈሩን እንዳለ ትተው ሕይወታቸውን ለማዳን እግሬ አውጪኝ አሉ።
በሥጋ ደዌ የተያዙት እነዚህ ሰዎች ወደ ሰፈሩ ዳርቻ ከደረሱ በኋላ ወደ አንዱ ድንኳን ገብተው መብላትና መጠጣት ጀመሩ። ከዚያም ብር፣ ወርቅና ልብስ ይዘው በመሄድ ደበቁት። ከዚያም ተመልሰው መጥተው ወደ ሌላ ድንኳን በመግባት የተለያዩ ነገሮችን ወሰዱ፤ እነዚህንም ይዘው በመሄድ ደበቁ።
በመጨረሻም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ “እያደረግን ያለነው ነገር ትክክል አይደለም። ይህ ቀን እኮ ምሥራች የሚነገርበት ቀን ነው! የምናመነታና እስኪነጋ ድረስ የምንጠብቅ ከሆነ መቀጣታችን አይቀርም። በመሆኑም አሁን ወደ ንጉሡ ቤት ሄደን ይህን ነገር እንናገር።”
ስለሆነም ሄደው የከተማዋን በር ጠባቂዎች በመጥራት እንዲህ አሏቸው፦ “ወደ ሶርያውያን ሰፈር ገብተን ነበር፤ ሆኖም በዚያ አንድም ሰው አልነበረም፤ የአንድም ሰው ድምፅ አልሰማንም። እዚያ የነበሩት የታሰሩ ፈረሶችና አህዮች ብቻ ናቸው፤ ድንኳኖቹም እንዳሉ ነበሩ።”
የከተማዋ በር ጠባቂዎችም ወዲያውኑ ይህን አስተጋቡ፤ ወሬውም በንጉሡ ቤት ተሰማ።
ንጉሡም ወዲያውኑ በሌሊት ተነስቶ አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፦ “ሶርያውያን ምን እንዳደረጉብን ልንገራችሁ። እንደተራብን ያውቃሉ፤ በመሆኑም ‘እነሱ ከተማዋን ለቀው ይወጣሉ፤ እኛም በሕይወት እንዳሉ እንይዛቸዋለን፤ ወደ ከተማዋም እንገባለን’ በማለት በዱር ለመደበቅ ከሰፈሩ ወጥተው ሄደዋል።”
ከዚያም ከአገልጋዮቹ አንዱ እንዲህ አለ፦ “የተወሰኑ ሰዎች በከተማዋ ውስጥ ከቀሩት ፈረሶች አምስቱን ይዘው ይሂዱ። እነዚህ ሰዎች እንደሆነ እዚህ ከሚቀረው የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የተለየ ምንም አይደርስባቸውም። የሚጠብቃቸው ነገር ቢኖር በዚህ እንዳለቁት እስራኤላውያን መሆን ነው። ስለሆነም እንላካቸውና የሚሆነውን እንይ።”
ስለዚህ ሁለት ሠረገሎችን ከፈረሶች ጋር ወሰዱ፤ ንጉሡም “ሄዳችሁ እዩ” በማለት ወደ ሶርያውያን ሰፈር ላካቸው።
እነሱም ዮርዳኖስ ድረስ ተከትለዋቸው ሄዱ፤ ሶርያውያን በድንጋጤ ሲሸሹ ጥለዋቸው የሄዱት ልብሶችና ዕቃዎች መንገዱን ሁሉ ሞልተውት ነበር። መልእክተኞቹም ተመልሰው በመምጣት ሁኔታውን ለንጉሡ ነገሩት።
ከዚያም ሕዝቡ ወጥቶ የሶርያውያንን ሰፈር በዘበዘ፤ በመሆኑም ይሖዋ በተናገረው መሠረት አንድ የሲህ መስፈሪያ የላመ ዱቄት በአንድ ሰቅል እንዲሁም ሁለት የሲህ መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል ተሸጠ።
ንጉሡ፣ የሚተማመንበትን የጦር መኮንን የከተማዋ በር ኃላፊ አድርጎ ሾመው፤ ይሁንና ሕዝቡ በሩ ላይ የጦር መኮንኑን ረጋገጠው፤ የእውነተኛው አምላክ ሰው ንጉሡ ወደ እሱ በወረደ ጊዜ በተናገረው መሠረት ሞተ።
የእውነተኛው አምላክ ሰው “ነገ በዚህ ሰዓት በሰማርያ በር ላይ ሁለት የሲህ መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል እንዲሁም አንድ የሲህ መስፈሪያ የላመ ዱቄት በአንድ ሰቅል ይሸጣል” በማለት ለንጉሡ የተናገረው ነገር ተፈጸመ።
የጦር መኮንኑ ግን የእውነተኛውን አምላክ ሰው “ይሖዋ የሰማይን የውኃ በሮች ቢከፍት እንኳ ይህ የተባለው ነገር ይፈጸማል?” ብሎት ነበር። በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ “ይህን በገዛ ዓይኖችህ ታያለህ፤ ሆኖም ከዚያ ምንም አትቀምስም” ብሎት ነበር።
የጦር መኮንኑ፣ ሕዝቡ በሩ ላይ ረጋግጦት ስለሞተ ልክ እንደተባለው ደረሰበት።
ሴዴቅያስ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት፣ በአሥረኛው ወር፣ ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር ሠራዊቱን ሁሉ አስከትሎ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ። በዙሪያዋም ሰፈረ፤ ደግሞም በዙሪያዋ የአፈር ቁልል ቆለለ፤
ከተማዋም እስከ ንጉሥ ሴዴቅያስ 11ኛ ዓመት ድረስ ተከበበች።
በአራተኛው ወር፣ ዘጠነኛ ቀን በከተማዋ ውስጥ ረሃቡ እጅግ ከፋ፤ በምድሪቱ የሚኖሩትም ሰዎች የሚላስ የሚቀመስ አጡ።
የከተማዋ ቅጥር ተደረመሰ፤ ከለዳውያን ከተማዋን ከበው ሳለም ወታደሮቹ ሁሉ በንጉሡ የአትክልት ቦታ አቅራቢያ ባለው መንገድ፣ በሁለቱ ቅጥሮች መካከል በሚገኘው በር በኩል በሌሊት ወጥተው ሸሹ፤ ንጉሡም ወደ አረባ በሚወስደው መንገድ ሄደ።
ይሁንና የከለዳውያን ሠራዊት ንጉሡን አሳደደ፤ እሱንም በኢያሪኮ በረሃማ ሜዳ ላይ ደረሱበት፤ ወታደሮቹም ሁሉ ጥለውት ተበታተኑ።
ከዚያም ንጉሡን ይዘው በሪብላ ወደነበረው የባቢሎን ንጉሥ አመጡት፤ ደግሞም ፈረዱበት።
የሴዴቅያስን ወንዶች ልጆች ዓይኑ እያየ አረዷቸው፤ ከዚያም ናቡከደነጾር የሴዴቅያስን ዓይን አሳወረ፤ በመዳብ የእግር ብረት አስሮም ወደ ባቢሎን ወሰደው።
በአምስተኛው ወር፣ ከወሩም በሰባተኛው ቀን ይኸውም ንጉሥ ናቡከደነጾር በነገሠ በ19ኛው ዓመት፣ የዘቦች አለቃና የባቢሎን ንጉሥ አገልጋይ የሆነው ናቡዛራዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።
እሱም የይሖዋን ቤት፣ የንጉሡን ቤትና በኢየሩሳሌም የሚገኙ ቤቶችን በሙሉ አቃጠለ፤ የታዋቂ ሰዎችንም ቤቶች ሁሉ በእሳት አጋየ።
ከዘቦቹ አለቃ ጋር የነበረው የከለዳውያን ሠራዊት በኢየሩሳሌም ዙሪያ ያለውን ቅጥር አፈረሰ።
የዘቦች አለቃ የሆነው ናቡዛራዳን በከተማዋ የቀሩትን በሕይወት የተረፉ ሰዎች፣ ከድተው ወደ ባቢሎን ንጉሥ የሄዱትን ሰዎችና የቀረውን ሕዝብ በግዞት ወሰደ።
ሆኖም የዘቦቹ አለቃ በምድሪቱ ከነበሩት ያጡ የነጡ ድሆች መካከል አንዳንዶቹ የወይን አትክልት ሠራተኞች ሆነው እንዲያገለግሉና የግዳጅ አገልግሎት እንዲሰጡ እዚያው ተዋቸው።
ከለዳውያኑም የይሖዋን ቤት የመዳብ ዓምዶች እንዲሁም በይሖዋ ቤት ውስጥ የነበሩትን የዕቃ ማጓጓዣ ጋሪዎችና የመዳብ ባሕር ሰባብረው መዳቡን ወደ ባቢሎን አጋዙ።
በተጨማሪም አመድ ማጠራቀሚያዎቹን፣ አካፋዎቹን፣ የእሳት ማጥፊያዎቹን፣ ጽዋዎቹንና ለቤተ መቅደስ አገልግሎት የሚውሉትን የመዳብ ዕቃዎች ሁሉ ወሰዱ።
የዘቦቹ አለቃ ከንጹሕ ወርቅና ብር የተሠሩትን መኮስተሪያዎችና ጎድጓዳ ሳህኖች ወሰደ።
ንጉሥ ሰለሞን ለይሖዋ ቤት ያሠራቸው ሁለቱ ዓምዶች፣ ባሕሩና የዕቃ ማጓጓዣ ጋሪዎቹ የተሠሩበት መዳብ ከብዛቱ የተነሳ ሊመዘን የሚችል አልነበረም።
የእያንዳንዱ ዓምድ ቁመት 18 ክንድ ነበር፤ በዓምዱ አናት ላይ ያለው ጌጥ ከመዳብ የተሠራ ሲሆን የጌጡ ርዝማኔ ሦስት ክንድ ነበር፤ በጌጡ ዙሪያ ያሉት ሮማኖችና መረቡ በሙሉ ከመዳብ የተሠሩ ነበሩ። ሁለተኛው ዓምድና መረቡም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነበር።
በተጨማሪም የዘቦቹ አለቃ የካህናት አለቃ የሆነውን ሰራያህን፣ ሁለተኛውን ካህን ሶፎንያስንና ሦስቱን የበር ጠባቂዎች ወሰዳቸው።
ደግሞም ከከተማዋ የወታደሮቹ ኃላፊ የሆነን አንድ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን፣ በከተማዋ ውስጥ የነበሩትን አምስቱን የንጉሡ የቅርብ ሰዎች፣ የምድሪቱን ሕዝብ የሚያሰልፈውን የሠራዊቱን አለቃ ጸሐፊ እንዲሁም ከተማዋ ውስጥ የተገኙትን በምድሪቱ የሚኖሩ 60 ተራ ሰዎች ወሰደ።
የዘቦች አለቃ የሆነው ናቡዛራዳን እነዚህን ሰዎች ይዞ በሪብላ ወዳለው ወደ ባቢሎን ንጉሥ አመጣቸው።
የባቢሎን ንጉሥ በሃማት ምድር ባለችው በሪብላ ሰዎቹን መትቶ ገደላቸው። በዚህ መንገድ ይሁዳ ከምድሩ በግዞት ተወሰደ።
የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር በይሁዳ ምድር በተዋቸው ሰዎች ላይ የሳፋን ልጅ፣ የአኪቃም ልጅ የሆነውን ጎዶልያስን አለቃ አድርጎ ሾመው።
የሠራዊቱ አለቆች በሙሉና አብረዋቸው ያሉት ሰዎች የባቢሎን ንጉሥ ጎዶልያስን አለቃ አድርጎ እንደሾመው ሲሰሙ ወዲያውኑ በምጽጳ ወደሚገኘው ወደ ጎዶልያስ መጡ። እነሱም የነታንያህ ልጅ እስማኤል፣ የቃሬሃ ልጅ ዮሃናን፣ የነጦፋዊው የታንሁመት ልጅ ሰራያህና የማአካታዊው ልጅ ያአዛንያህ እንዲሁም አብረዋቸው የነበሩት ሰዎች ናቸው።
ጎዶልያስ ለእነሱና አብረዋቸው ለነበሩት ሰዎች “የከለዳውያን አገልጋይ መሆን አያስፈራችሁ። በምድሪቱ ላይ ኑሩ፤ የባቢሎንንም ንጉሥ አገልግሉ፤ መልካምም ይሆንላችኋል” ሲል ማለላቸው።
በሰባተኛውም ወር፣ ከንጉሣውያን ቤተሰብ የሆነው የኤሊሻማ ልጅ፣ የነታንያህ ልጅ እስማኤል ከሌሎች አሥር ሰዎች ጋር መጣ፤ እነሱም ጎዶልያስን መቱት፤ እሱም በምጽጳ አብረውት ከነበሩት አይሁዳውያንና ከለዳውያን ጋር ሞተ።
ከዚያ በኋላ የሠራዊቱን አለቆች ጨምሮ ትልቅ ትንሽ ሳይባል ሕዝቡ ሁሉ ተነስተው ወደ ግብፅ ሄዱ፤ ከለዳውያንን ፈርተው ነበርና።
የባቢሎን ንጉሥ ኤዊልሜሮዳክ በነገሠበት ዓመት የይሁዳን ንጉሥ ዮአኪንን ከእስር ቤት ፈታው፤ ይህም የሆነው የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በግዞት በተወሰደ በ37ኛው ዓመት፣ በ12ኛው ወር፣ ከወሩም በ27ኛው ቀን ነበር።
በርኅራኄም አናገረው፤ ዙፋኑንም በባቢሎን ከእሱ ጋር ከነበሩት ከሌሎች ነገሥታት ዙፋን ይበልጥ ከፍ ከፍ አደረገለት።
በመሆኑም ዮአኪን የእስር ቤት ልብሱን አወለቀ፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ በቋሚነት ከንጉሡ ማዕድ ይመገብ ነበር።
ንጉሡም ለዮአኪን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሳያቋርጥ ቀለቡን በየዕለቱ ይሰጠው ነበር።
የይሁዳ ንጉሥ የአካዝያስ ልጅ ኢዮዓስ በነገሠ በ23ኛው ዓመት የኢዩ ልጅ ኢዮዓካዝ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በሰማርያም ሆኖ ለ17 ዓመት ገዛ።
እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ፤ እንዲሁም የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሙ ያደረገውን ኃጢአት መሥራቱን ቀጠለ። ከዚያም አልራቀም።
በመሆኑም የይሖዋ ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤ በዘመናቸውም ሁሉ በሶርያ ንጉሥ በሃዛኤል እጅና በሃዛኤል ልጅ በቤንሃዳድ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።
ከጊዜ በኋላ ኢዮዓካዝ የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ለመነ፤ ይሖዋም ሰማው፤ ምክንያቱም የሶርያ ንጉሥ በእስራኤላውያን ላይ ያደረሰውን ጭቆና አይቶ ነበር።
ስለሆነም ይሖዋ ለእስራኤላውያን ከሶርያውያን እጅ ነፃ የሚያወጣ አዳኝ ሰጣቸው፤ እስራኤላውያንም እንደቀድሟቸው በየቤታቸው መኖር ጀመሩ።
(እነሱ ግን የኢዮርብዓም ቤት እስራኤላውያን እንዲፈጽሙ ካደረገው ኃጢአት ዞር አላሉም። ይህን ኃጢአት መፈጸማቸውን ቀጠሉ፤ የማምለኪያ ዓምዱም በሰማርያ እንደቆመ ነበር።)
ኢዮዓካዝ የቀረው 50 ፈረሰኞች፣ 10 ሠረገሎችና 10,000 እግረኛ ወታደሮች ብቻ ያሉት ሠራዊት ነበር፤ ምክንያቱም የሶርያ ንጉሥ በአውድማ ላይ እንዳለ እብቅ ረጋግጦ ደምስሷቸው ነበር።
የቀረው የኢዮዓካዝ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉና ኃያልነቱ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?
በመጨረሻም ኢዮዓካዝ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮዓስ በምትኩ ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮዓስ በነገሠ በ37ኛው ዓመት የኢዮዓካዝ ልጅ ኢዮዓስ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በሰማርያም ሆኖ ለ16 ዓመት ገዛ።
እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሟቸው ካደረጋቸው ኃጢአቶች ሁሉ ዞር አላለም። እነዚህን ኃጢአቶች መፈጸሙን ቀጠለ።
የቀረው የኢዮዓስ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉና ኃያልነቱ እንዲሁም ከይሁዳ ንጉሥ ከአሜስያስ ጋር እንዴት እንደተዋጋ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?