text
stringlengths
4
267
በጣም የሚያስጨንቅ ሁኔታ በሚያጋጥማቸው ጊዜም እንኳ ጉዳዩን ለይሖዋ ይተዉት ነበር።
ይህም በይሖዋ መታመንን አስተምሮኛል።
ከልጆቻችሁ ጋር ስትጸልዩ ስለ እነሱ ብቻ አትጸልዩ።
ይሖዋ እናንተንም እንዲረዳችሁ ጠይቁት፤ ለምሳሌ በትልቅ ስብሰባ ላይ መገኘት እንድትችሉ አሠሪያችሁ ፈቃድ እንዲሰጣችሁ ለማነጋገር ወይም ለጎረቤታችሁ ለመመሥከር ይሖዋ ድፍረት እንዲሰጣችሁ አሊያም በሌሎች ጉዳዮች እንዲረዳችሁ ጸልዩ።
ትሑት በመሆን በአምላክ እንደምትታመኑ ካሳያችሁ ልጆቻችሁም ይህን ማድረግ ይማራሉ።
ወላጆች እንደመሆናችሁ መጠን በይሖዋ ላይ እምነት በማሳደር ረገድ እናንተ ራሳችሁ ምሳሌ ሆናችሁ መገኘታችሁ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው።
ልጆቻችሁ የምታደርጉትን ነገር ያስተውላሉ፤ ይህም በእነሱ ላይ በጎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ጥርጥር የለውም።
ስለዚህ ወላጆች የራሳችሁን እምነት መገንባታችሁን ቀጥሉ።
ልጆቻችሁ ይሖዋ ለእናንተ ምን ያህል እውን እንደሆነ እንዲመለከቱ አድርጉ።
በቤርሙዳ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት፣ የሚያስጨንቅ ሁኔታ በሚያጋጥማቸው ወቅት ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጣቸው ከልጆቻቸው ጋር ሆነው የሚጸልዩ ሲሆን ልጆቻቸውንም እንዲጸልዩ ያበረታቷቸዋል።
በተጨማሪም ትልቋ ልጃችንን ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ታመኚ፤ ራስሽን በአገልግሎት አስጠምጂ እንዲሁም ከልክ በላይ አትጨነቂ እንላታለን።
እንዲህ ማድረግ የሚያስገኘውን ውጤት ስትመለከት ይሖዋ እየረዳን እንዳለ ትገነዘባለች።
ይህም በአምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላት እምነት እንዲጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል በማለት ተናግረዋል።
እርግጥ ነው፣ እናንተ ምንም ያህል ጥረት ብታደርጉም እምነት ማዳበር ያለባቸው ልጆቹ ራሳቸው ናቸው።
የእናንተ ድርሻ መትከልና ውኃ ማጠጣት ነው።
ሊያሳድገው የሚችለው አምላክ ብቻ ነው።
እንግዲያው ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጣችሁ ጸልዩ፤ እንዲሁም ውድ የሆኑ ልጆቻችሁን ለማስተማር ከፍተኛ ጥረት አድርጉ፤ ይህን ካደረጋችሁ ይሖዋ ይባርካችኋል።
በ1914 በአውሮፓ በሚገኙ አገራት መካከል ጦርነት ተቀሰቀሰ፤ ጦርነቱም በመስፋፋቱ በመላው ዓለም ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።
በ1918 ጦርነቱ ሲያበቃ ከባድ የምግብ እጥረት ተከሰተ፤ ቀጥሎም በጦርነቱ ከሞቱት የሚበልጥ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች የጨረሰ የኢንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ ተነሳ።
በመሆኑም ኢየሱስ የምድር አዲሱ ንጉሥ ሆኖ በማይታይ ሁኔታ መገኘቱን እንደሚጠቁም የሚያሳየው ምልክት መፈጸም ጀመረ።
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አክሊል የተሰጠው በ1914 መሆኑን የሚያረጋግጥ በቂ ማስረጃ አለ።
እሱም ድል እያደረገ ወጣ፤ ድሉንም ለማጠናቀቅ ወደ ፊት ገሰገሰ።
ኢየሱስ በሰይጣንና በአጋንንቱ ላይ ጦርነት በማወጅ ሰማይን ያጸዳ ሲሆን እነሱንም ወደ ምድር አካባቢ ወረወራቸው።
ከዚያ ጊዜ ወዲህ የሰው ልጆች፣ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ሐሳብ እውነተኝነት እየተመለከቱ ነው።
የይሖዋ አገልጋዮች በመሆናችን ሰይጣን የለም በሚለው አመለካከት አልተታለልንም።
ሔዋንን በእባቡ ተጠቅሞ ያነጋገራት ሰይጣን ስለሆነ ዲያብሎስ በእውን ያለ አካል መሆኑን እናውቃለን።
ሰይጣን ከኢዮብ ጋር በተያያዘ በይሖዋ ላይ ተሳልቋል።
ኢየሱስን ሊፈትነው የሞከረውም ሰይጣን ነው።
እንዲሁም በ1914 የአምላክ መንግሥት ከተወለደ በኋላ ከቅቡዓን ቀሪዎች ጋር መዋጋት የጀመረው ሰይጣን ነው።
ሰይጣን የ144,000ዎቹን ቀሪዎችና የሌሎች በጎችን እምነት ለማጥፋት እየጣረ በመሆኑ ይህ ጦርነት አሁንም ቀጥሏል።
በዚህ ጦርነት ለማሸነፍ፣ በእምነት ጸንተን በመቆም ሰይጣንን መቃወም ይኖርብናል።
ሰይጣን ፈጽሞ ሊያንጸባርቀው የማይችለው ባሕርይ ቢኖር ትሕትና ነው።
ለነገሩ ይህ መንፈሳዊ ፍጡር የይሖዋን ሉዓላዊ ገዢነት መገዳደሩና ራሱን አምላክ ለማድረግ መድፈሩ ምን ያህል በኩራትና በትዕቢት እንደተወጠረ የሚያሳይ ነው።
በመሆኑም ሰይጣንን መቃወም የምንችልበት አንዱ መንገድ ከኩራት መራቅና ትሕትናን ማዳበር ነው።
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች፣ በብዙ ጉባኤዎች ውስጥ ወጣቶችንም ሆነ በዕድሜ ከፍ ያሉትን ወንድሞች አሠልጥኖ ለኃላፊነት በማብቃት ረገድ ብዙ የሚቀር ነገር እንዳለ አስተውለዋል።
ይሁንና ይህን ኃላፊነት መወጣት የራሱ ተፈታታኝ ነገሮች አሉት።
እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
ክርስቲያን ሽማግሌ ከሆንክ ሌሎችን በግለሰብ ደረጃ ማሠልጠን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ሳትገነዘብ አትቀርም።
አሁን ያሉት ጉባኤዎች በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነው እንዲቀጥሉ ብሎም አዳዲስ ጉባኤዎች እንዲቋቋሙ ከተፈለገ ተጨማሪ ወንድሞች እንደሚያስፈልጉ የታወቀ ነው።
በተጨማሪም የአምላክ ቃል ሌሎችን እንድታስተምር ማሳሰቢያ እንደሰጠህ ታውቃለህ።
ያም ሆኖ ሌሎችን ማሠልጠን ከብዶህ ሊሆን ይችላል።
የቤተሰብህን ፍላጎት ማሟላትን፣ ሰብዓዊ ሥራ መሥራትንና የጉባኤ ኃላፊነት መወጣትን ጨምሮ ሌሎች አጣዳፊ ሥራዎች እንዳሉብህ ስታስብ ሌሎችን ለማሠልጠን ጊዜ እንደሌለህ ይሰማህ ይሆናል።
ይሁንና የተጠመቁ ወንዶች በጉባኤ ውስጥ ለበለጠ ኃላፊነት እንዲበቁ ሥልጠና ማግኘታቸው አስፈላጊ ነው።
እንዲህ ከሆነ ሁሉም ጥቅም ማግኘት ይችላሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች የወንድማማች መዋደድ ሊኖረን እንደሚገባና አንዳችን ሌላውን ማገልገል እንዳለብን ጎላ አድርገው ይገልጻሉ።
የአምላክ ልጅ፣ ሌሎችን ለማገልገል ሲል ሕይወቱን ጨምሮ ሁሉ ነገሩን ሰጥቷል።
ዶርቃ መልካም በማድረግና ምጽዋት በመስጠት የምትታወቅ ሴት ነበረች።
በሮም ትገኝ የነበረችው ማርያም የተባለች እህትም ለጉባኤው ብዙ ደክማለች።
ታዲያ አዲሶች፣ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን መርዳት አስፈላጊ መሆኑን እንዲገነዘቡ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
የጎለመሱ ክርስቲያኖች፣ የታመሙና በዕድሜ የገፉ ሰዎችን በሚጠይቁበት ወቅት አብረዋቸው እንዲሄዱ አዲሶችን ሊጋብዟቸው ይችላሉ።
ወላጆችም እንዲህ ያሉትን ወንድሞች ለመጠየቅ ሲሄዱ፣ ተገቢ እንደሆነ ከተሰማቸው ልጆቻቸውን ይዘው መሄድ ይችላሉ።
ሽማግሌዎች፣ በዕድሜ የገፉ ውድ ወንድሞቻችን ተስማሚ ምግብ እንዲያገኙና ቤታቸው በሚገባ እንዲያዝ ዝግጅት በሚያደርጉበት ጊዜ ሌሎች እንዲያግዟቸው መጠየቅ ይችላሉ።
በዚህ መልኩ ወጣቶችና አዲሶች ለሌሎች ደግነት እንዲሁም ለሁሉም የጉባኤ አባላት ፍቅር ማሳየት ስለሚቻልባቸው መንገዶች ይማራሉ።
በጉባኤ ውስጥ አንድ ዓይነት ኃላፊነት በቅርቡ የተቀበለ ወንድም ቶሎ ብሎ የራሱን መንገድ ለመከተል መሞከር የለበትም፤ በሌላ አባባል ከዚህ በፊት የነበረውን አሠራር ሙሉ በሙሉ መቀየር እንዳለበት ሊሰማው አይገባም።
አንድ አሠራር መለወጥ ያለበት በአንድ ሰው ፍላጎት መሆን የለበትም፤ ከዚህ ይልቅ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የጉባኤው ጥቅምና ከይሖዋ ድርጅት የምናገኘው መመሪያ ነው።
አንተም ኃላፊነት ከተሰጠህ ሽማግሌዎቹ ሲጠቀሙባቸው የነበሩትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ዘዴዎች ተግባራዊ ማድረግህን በመቀጠል የእምነት ባልንጀሮችህ እንዲተማመኑብህ ማድረግ እንዲሁም ተሞክሮ ላካበቱ ሽማግሌዎች አክብሮት እንዳለህ ማሳየት ትችላለህ።
ተሞክሮ እያገኘህ ስትሄድ ጉባኤው ወደፊት እየገሰገሰ ከሚሄደው የይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል እንዲራመድ አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ እንደሚያስፈልግህ ግልጽ ነው።
እንዲያውም ይሖዋ ታማኝ እስከሆናችሁ ድረስ ውሎ አድሮ አስተማሪዎቻችሁ ካከናወኑት የበለጠ ነገር እንድትሠሩ ሊጠቀምባችሁ ይችላል።
ይህ ነገር ካጋጠማቸው ደቀ መዛሙርት አንዱ ብትሆን በዚያ ዕለት የተከናወነውን ነገር መቼም አትረሳውም።
በመንፈስ ቅዱስ መቀባትህን ፈጽሞ አትጠራጠርም፤ በተለይ ደግሞ በማታውቀው ቋንቋ የመናገር ተአምራዊ ስጦታም ተሰጥቶህ ከሆነ መቀባትህን እርግጠኛ ትሆናለህ።
ይሁንና በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ሁሉ፣ የተቀቡት ልክ እንደ መጀመሪያዎቹ 120 ደቀ መዛሙርት አስደናቂ በሆነ መንገድ ነው?
አይደለም።
በኢየሩሳሌም በዚያን ዕለት የነበሩት ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት በመንፈስ የተቀቡት ሲጠመቁ ነው።
የእሳት ምላሶች የሚመስሉ ነገሮች ጭንቅላታቸው ላይ አላረፉም።
በሌላ በኩል ደግሞ በተጠመቁበት ወቅት በመንፈስ የተቀቡት ሁሉም ክርስቲያኖች አይደሉም።
ሳምራውያን በመንፈስ የተቀቡት ከተጠመቁ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነው።
ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ የተቀቡበት መንገድም ለየት ያለ ነው፤ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡት ገና ከመጠመቃቸው በፊት ነው።
ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ ምድራዊ ተስፋ ካላቸው የበለጠ መንፈስ ቅዱስ እንዳልተቀበሉ በመገንዘብ ትሕትና ያሳያሉ።
ልዩ እውቀት እንዳላቸው ወይም ራእይ እንደሚገለጥላቸው አይናገሩም፤ አሊያም በሆነ መንገድ ከሌሎች እንደሚበልጡ ለማሳየት አይሞክሩም።
ከዚህም በተጨማሪ ለማንም ሰው፣ በመንፈስ እንደተቀባና ከምሳሌያዊው ቂጣና የወይን ጠጅ መውሰድ እንደሚገባው የሚገልጽ ሐሳብ ፈጽሞ አይሰነዝሩም፤ ከዚህ ይልቅ ቅቡዓንን የሚጠራው ይሖዋ እንደሆነ በትሕትና አምነው ይቀበላሉ።
ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሌሎች የተለየ ክብር እንዲሰጧቸው አይጠብቁም።
የይሖዋ መንፈስ የመሠከረላቸው በግለሰብ ደረጃ ነው።
ለሌሎች ሰዎች የተነገረ ማስታወቂያ የለም።
በመሆኑም አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን፣ በእርግጥ በመንፈስ ቅዱስ መቀባቱን አንዳንዶች ቢጠራጠሩ ሊገረም አይገባም።
እንዲያውም ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ከአምላክ ልዩ ሹመት እንዳገኘ የሚናገርን ሰው ቶሎ ማመንን አያበረታቱም።
አንድ ሰው ቅር የሚያሰኝ ነገር በሚናገርበት ጊዜም እንኳ የለዘበ መልስ መስጠት ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል።
አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ የአንዲት ነጠላ እህት ልጅ ሁለት ዓይነት ሕይወት እየመራ ነበር።
አንዲት ሌላ እህት ይህችን እናት ልጅሽን በማሠልጠን ረገድ ሳይሳካልሽ መቅረቱ በጣም ያሳዝናል አለቻት፤ ይህን ያለችው ስላዘነችላት ነው።
እናትየው ቆም ብላ ካሰበች በኋላ እንዲህ በማለት መለሰችላት፦ ነገሮች በትክክለኛው አቅጣጫ እየሄዱ እንዳልሆነ አልክድም፤ ሆኖም ልጄ ሥልጠናውን ገና አልጨረሰም።
እርግጠኛ መሆን የምንችለው ከአርማጌዶን በኋላ ነው።
ይህች እናት የሰጠችው የለዘበ መልስ በሁለቱ እህቶች መካከል ያለው ሰላም እንዳይደፈርስ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ ጭውውታቸውን ይሰማ የነበረውን የእህትን ልጅ አበረታቶታል።
ልጁ፣ እናቱ በእሱ ተስፋ እንዳልቆረጠች ተገነዘበ።
ይህም ከመጥፎ ጓደኞች እንዲርቅ አነሳሳው።
ከጊዜ በኋላ የተጠመቀ ሲሆን ውሎ አድሮም ቤቴል ገባ።
ከወንድሞቻችን፣ ከቤተሰባችን አባላት ወይም ከማናውቃቸው ሰዎች ጋር ስንሆን ንግግራችን ምንጊዜም በጨው የተቀመመ ያህል ለዛ ያለው ሊሆን ይገባል።
በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች ይጠመቃሉ።
ክርስቲያን ወላጆችና የጉባኤ ሽማግሌዎች እነዚህ ወጣቶች ለመጠመቅ የወሰኑት በራሳቸው ተነሳሽነት መሆኑን ብቻ ሳይሆን በሚገባ አስበውበት ጭምር መሆኑን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ።
አንድ ክርስቲያን ራሱን ወስኖ በሚጠመቅበት ጊዜ በሕይወቱ ውስጥ የይሖዋን በረከት እንደሚያገኝ ብቻ ሳይሆን ከሰይጣን ዲያብሎስ ተቃውሞ እንደሚደርስበትም መጠበቅ ይኖርበታል።
በመሆኑም ክርስቲያን ወላጆች የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ምን ነገሮችን እንደሚያካትት ጊዜ ወስደው ልጆቻቸውን ያስተምራሉ።
ወላጆቻቸው የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ወጣቶችን ደግሞ የጉባኤው ሽማግሌዎች የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ምን ወጪ እንደሚያስከፍላቸው እንዲያሰሉ በፍቅር ይረዷቸዋል።
አንድን ሕንፃ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ዕቅድ ማውጣት እንደሚጠይቅ ሁሉ ይሖዋን በታማኝነት እስከ መጨረሻው ለማገልገልም ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል።
የሙሴ ሕግ የተሰጠው ለአንድ ብሔር ይኸውም ለሥጋዊ እስራኤላውያን ነበር።
በአንጻሩ ግን መንፈሳዊ እስራኤል የተለያየ ብሔርና አኗኗር ከነበራቸው ሰዎች የተውጣጣ ነው።
ሥጋዊ እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር በነበሩበት ጊዜ ይጠቀሙበት የነበረው የሙሴ ሕግ የተቀረጸው በድንጋይ ላይ ነበር።
በሌላ በኩል መንፈሳዊ እስራኤላውያን የሚመሩበት የክርስቶስ ሕግ በዋነኝነት የተመሠረተው በልብ ላይ በተቀረጹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ነው።
ክርስቲያኖች የሚኖሩት የትም ይሁን የት በክርስቶስ ሕግ ሥር ናቸው፤ ከሕጉም ጥቅም አግኝተዋል።
መንፈሳዊ እስራኤላውያን አምላክ በልጁ በኩል ከሚሰጠው አመራር በእጅጉ ይጠቀማሉ።
አዲሱ ቃል ኪዳን ከመቋቋሙ በፊት ኢየሱስ ከፍተኛ ትርጉም ያላቸው ሁለት ትእዛዛት ሰጠ።
አንዱ ከስብከቱ ሥራ ጋር የተያያዘ ነው።
ሌላኛው ደግሞ የኢየሱስ ተከታዮች ከሚያሳዩት ምግባርና የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ከሚይዙበት መንገድ ጋር የሚያያዝ ነው።