text
stringlengths
4
267
የቀረው የመናሄምታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?
በመጨረሻም መናሄም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ፈቃህያህ በእሱ ምትክ ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ አዛርያስ በነገሠ በ50ኛው ዓመት የመናሄም ልጅ ፈቃህያህ በሰማርያ፣ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ለሁለት ዓመትም ገዛ።
እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሟቸው ካደረጋቸው ኃጢአቶች ዞር አላለም።
ከዚያም የረማልያህ ልጅ የሆነው የጦር መኮንኑ ፋቁሄ ከአርጎብ እና ከአርያ ጋር በማበር በእሱ ላይ አሴረ፤ በሰማርያ፣ በንጉሡ ቤት በሚገኘው የማይደፈር ማማ ላይ ሳለም መትቶ ገደለው። ከእሱ ጋር 50 የጊልያድ ሰዎች ነበሩ፤ እሱን ከገደለ በኋላም በምትኩ ነገሠ።
የቀረው የፈቃህያህ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈዋል።
የይሁዳ ንጉሥ አዛርያስ በነገሠ በ52ኛው ዓመት የረማልያህ ልጅ ፋቁሄ በሰማርያ፣ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ለ20 ዓመትም ገዛ።
እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሟቸው ካደረጋቸው ኃጢአቶች ዞር አላለም።
በእስራኤል ንጉሥ በፋቁሄ ዘመን የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር ወረራ በማካሄድ ኢዮንን፣ አቤልቤትማዓካን፣ ያኖአህን፣ ቃዴሽን፣ ሃጾርን፣ ጊልያድን እንዲሁም ገሊላን ይኸውም መላውን የንፍታሌም ምድር ያዘ፤ ነዋሪዎቹንም በግዞት ወደ አሦር ወሰደ።
በመጨረሻም የኤላህ ልጅ ሆሺአ በረማልያህ ልጅ በፋቁሄ ላይ በማሴር መትቶ ገደለው፤ እሱም የዖዝያ ልጅ ኢዮዓታም በነገሠ በ20ኛው ዓመት በፋቁሄ ምትክ ነገሠ።
የቀረው የፋቁሄ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈዋል።
የእስራኤል ንጉሥ የረማልያህ ልጅ ፋቁሄ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የዖዝያ ልጅ ኢዮዓታም ነገሠ።
እሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ16 ዓመት ገዛ። እናቱም የሩሻ ትባል ነበር፤ እሷም የሳዶቅ ልጅ ነበረች።
እሱም አባቱ ዖዝያ እንዳደረገው ሁሉ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።
ሆኖም ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች አልተወገዱም ነበር፤ ሕዝቡ አሁንም ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች ላይ ይሠዋ እንዲሁም የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር። የይሖዋን ቤት የላይኛውን በር የሠራው እሱ ነበር።
የቀረው የኢዮዓታም ታሪክና ያደረጋቸው ነገሮች በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?
በዚያ ዘመን ይሖዋ በይሁዳ ላይ የሶርያን ንጉሥ ረጺንን እና የረማልያህን ልጅ ፋቁሄን ላከ።
በመጨረሻም ኢዮዓታም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱ በዳዊት ከተማም ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። በእሱም ምትክ ልጁ አካዝ ነገሠ።
ከነቢያት ልጆች መካከል የአንዱ ሚስት ወደ ኤልሳዕ መጥታ እንዲህ ስትል ጮኸች፦ “አገልጋይህ ባለቤቴ ሞቷል፤ አገልጋይህ ምንጊዜም ይሖዋን የሚፈራ ሰው እንደነበር በሚገባ ታውቃለህ። አሁን ግን አንድ አበዳሪ መጥቶ ሁለቱንም ልጆቼን ባሪያዎቹ አድርጎ ሊወስዳቸው ነው።”
በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ “ታዲያ ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ? ንገሪኝ፣ ቤት ውስጥ ምን አለሽ?” አላት። እሷም “አገልጋይህ ከአንድ ማሰሮ ዘይት በስተቀር ቤት ውስጥ ምንም ነገር የላትም” ብላ መለሰችለት።
ከዚያም እንዲህ አላት፦ “እንግዲያው ሂጂና ከጎረቤቶችሽ ሁሉ ባዶ ዕቃዎች ለምኚ። የቻልሽውን ያህል ብዙ ዕቃ ለምኚ።
ከዚያም ገብተሽ በሩን በአንቺና በልጆችሽ ላይ ዝጊው። ዕቃዎቹንም ሁሉ በዘይት ሙዪ፤ የሞሉትንም ለብቻ አስቀምጫቸው።”
እሷም ወጥታ ሄደች። በሩን በራሷና በልጆቿ ላይ ከዘጋች በኋላ ልጆቿ ዕቃዎቹን ሲያቀርቡላት እሷ ትቀዳባቸው ጀመር።
ዕቃዎቹ ሲሞሉ ከልጆቿ መካከል አንዱን “ሌላ ዕቃ አምጣልኝ” አለችው። እሱ ግን “የቀረ ዕቃ የለም” አላት። በዚህ ጊዜ ዘይቱ መውረዱን አቆመ።
እሷም ሄዳ ለእውነተኛው አምላክ ሰው ነገረችው፤ እሱም “ሂጂ፤ ዘይቱን ሸጠሽ ዕዳሽን ክፈዪ፤ የተረፈው ደግሞ ለአንቺና ለልጆችሽ መተዳደሪያ ይሁን” አላት።
አንድ ቀን ኤልሳዕ ወደ ሹነም ሄደ፤ በዚያም አንዲት ታዋቂ ሴት ነበረች፤ እሷም ምግብ እንዲበላ አጥብቃ ለመነችው። እሱም በዚያ ባለፈ ቁጥር ምግብ ለመብላት ወደዚያ ጎራ ይል ነበር።
በመሆኑም ሴትየዋ ባሏን እንዲህ አለችው፦ “ይህ በየጊዜው በዚህ መንገድ የሚያልፈው ሰው ቅዱስ የአምላክ ሰው እንደሆነ አውቃለሁ።
እባክህ በሰገነቱ ላይ ትንሽ ክፍል ሠርተን አልጋ፣ ጠረጴዛ፣ ወንበርና መቅረዝ እናስገባለት። ከዚያም ወደ እኛ በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ እዚያ ማረፍ ይችላል።”
ኤልሳዕም አንድ ቀን ወደዚያ መጣ፤ ጋደም ለማለትም በሰገነቱ ላይ ወዳለው ክፍል ሄደ።
ከዚያም አገልጋዩን ግያዝን “እስቲ ሹነማዊቷን ሴት ጥራት” አለው። እሱም ጠራት፤ እሷም መጥታ ፊቱ ቆመች።
ከዚያም ኤልሳዕ ግያዝን እንዲህ አለው፦ “እባክህ እንዲህ በላት፦ ‘እንግዲህ ለእኛ ስትዪ ብዙ ተቸግረሻል። ታዲያ ምን እንዲደረግልሽ ትፈልጊያለሽ? ንጉሡን ወይም የሠራዊቱን አለቃ የማነጋግርልሽ ነገር አለ?’” እሷ ግን “እኔ እኮ የምኖረው በገዛ ወገኖቼ መካከል ነው” ብላ መለሰች።
እሱም “ታዲያ ምን ቢደረግላት ይሻላል?” አለ። ግያዝም “ለነገሩማ ሴትየዋ ወንድ ልጅ የላትም፤ ባሏ ደግሞ አርጅቷል” አለው።
ኤልሳዕም ወዲያውኑ “በል ጥራት” አለው። እሱም ጠራት፤ እሷም በራፉ ላይ ቆመች።
ከዚያም “የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ ወንድ ልጅ ትታቀፊያለሽ” አላት። እሷ ግን “የእውነተኛው አምላክ ሰው ጌታዬ ሆይ፣ ይሄማ አይሆንም! አገልጋይህን መዋሸት እንዳይሆንብህ” አለችው።
ይሁንና ሴትየዋ ፀነሰች፤ ኤልሳዕ በነገራትም መሠረት በቀጣዩ ዓመት በዚያው ጊዜ ወንድ ልጅ ወለደች።
ልጁም አደገ፤ ከዚያም አንድ ቀን ከአጫጆቹ ጋር ወደነበረው ወደ አባቱ ወጣ።
አባቱንም “ራሴን! ወይኔ ራሴን!” አለው። ከዚያም አባቱ አገልጋዩን “ተሸክመህ ወደ እናቱ ውሰደው” አለው።
እሱም ተሸክሞ ወደ እናቱ ወሰደው፤ ልጁም እስከ እኩለ ቀን ድረስ እናቱ ጭን ላይ ተቀመጠ፤ ከዚያም ሞተ።
እሷም ወደ ላይ ወጥታ ልጁን በእውነተኛው አምላክ ሰው አልጋ ላይ አስተኛችው፤ በሩንም ዘግታ ሄደች።
ባሏንም ጠርታ “እባክህ አንድ አገልጋይና አንድ አህያ ላክልኝና ወደ እውነተኛው አምላክ ሰው በፍጥነት ደርሼ ልመለስ” አለችው።
እሱ ግን “ዛሬ ወደ እሱ መሄድ ለምን አስፈለገሽ? አዲስ ጨረቃ ወይም ሰንበት አይደለም” አላት። እሷ ግን “ግድ የለም፣ ደርሼ ልምጣ” አለችው።
ስለዚህ አህያዋን ከጫነች በኋላ አገልጋይዋን “ቶሎ ቶሎ ሂድ። እኔ ቀስ በል እስካላልኩህ ድረስ ለእኔ ብለህ ፍጥነትህን እንዳትቀንስ” አለችው።
በመሆኑም በቀርሜሎስ ተራራ ወደሚገኘው ወደ እውነተኛው አምላክ ሰው ሄደች። የእውነተኛውም አምላክ ሰው ከሩቅ እንዳያት አገልጋዩን ግያዝን እንዲህ አለው፦ “ተመልከት! ሹነማዊቷ ሴት ያቻትና።
እባክህ ሮጠህ ወደ እሷ ሂድና ‘ምነው፣ ደህና አይደለሽም? ባልሽ ደህና አይደለም እንዴ? ልጁስ ደህና አይደለም?’ በላት።” እሷም “ሁሉም ነገር ደህና ነው” አለች።
ተራራው ላይ ወዳለው ወደ እውነተኛው አምላክ ሰው እንደደረሰች እግሩ ላይ ተጠመጠመች። በዚህ ጊዜ ግያዝ ሊያስለቅቃት ሲመጣ የእውነተኛው አምላክ ሰው “ተዋት፣ እጅግ ተጨንቃለች፤ ይሖዋም ነገሩን ከእኔ ደብቆታል፤ የነገረኝ ነገር የለም” አለው።
እሷም “ለመሆኑ ጌታዬ ልጅ እንዲሰጠኝ ጠይቄ ነበር? ደግሞስ ‘የማይሆን ተስፋ አትስጠኝ’ አላልኩም?” አለችው።
እሱም ወዲያውኑ ግያዝን “ልብስህን ወገብህ ላይ ታጠቅ፤ በትሬን ያዝና ሩጥ። መንገድ ላይ ሰው ብታገኝ ሰላም አትበል፤ ማንም ሰው ሰላም ቢልህም መልስ አትስጠው። ሂድና በትሬን በልጁ ፊት ላይ አድርገው” አለው።
በዚህ ጊዜ የልጁ እናት “ሕያው በሆነው በይሖዋና በሕያውነትህ እምላለሁ፣ ፈጽሞ ትቼህ አልሄድም” አለችው። ስለሆነም ተነስቶ አብሯት ሄደ።
ግያዝ ቀድሟቸው በመሄድ በትሩን በልጁ ፊት ላይ አደረገው፤ ሆኖም ድምፅም ሆነ ምላሽ አልነበረም። እሱም ወደ ኤልሳዕ ተመልሶ በመምጣት “ልጁ አልነቃም” አለው።
ኤልሳዕ ወደ ቤት ሲገባ ልጁ ሞቶ በእሱ አልጋ ላይ ተጋድሞ አገኘው።
ከዚያም ወደ ውስጥ ገብቶ በሩን በራሱና በልጁ ላይ ከዘጋ በኋላ ወደ ይሖዋ መጸለይ ጀመረ።
ከዚያም አልጋው ላይ ወጥቶ ልጁ ላይ በመተኛት አፉን በአፉ፣ ዓይኑን በዓይኑ እንዲሁም መዳፉን በመዳፉ ላይ አድርጎ ላዩ ላይ ተደፋበት፤ የልጁም ሰውነት መሞቅ ጀመረ።
ኤልሳዕ ተነስቶ ቤቱ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ይል ጀመር፤ ደግሞም እንደገና አልጋው ላይ ወጥቶ ላዩ ላይ ተደፋበት። ልጁም ሰባት ጊዜ ካስነጠሰው በኋላ ዓይኖቹን ገለጠ።
ኤልሳዕም ግያዝን ጠርቶ “ሹነማዊቷን ሴት ጥራት” አለው። እሱም ጠራት፤ እሷም ወደ እሱ ገባች። ከዚያም ኤልሳዕ “ልጅሽን አንሺው” አላት።
እሷም ገብታ እግሩ ሥር በመውደቅ ወደ መሬት ለጥ ብላ እጅ ነሳች፤ ልጇንም አንስታ ወጣች።
ኤልሳዕ ወደ ጊልጋል ሲመለስ በምድሪቱ ላይ ረሃብ ነበር። የነቢያት ልጆች በፊቱ ተቀምጠው ነበር፤ አገልጋዩንም “ትልቁን ድስት ጣደውና ለነቢያት ልጆች ወጥ ሥራላቸው” አለው።
አንድ ሰው ቅጠላ ቅጠል ለማምጣት ወደ ሜዳ ወጣ፤ እሱም ዱር በቀል ሐረግ አገኘ፤ ከሐረጉም ላይ የዱር ቅል ለቅሞ በልብሱ ሙሉ ይዞ ተመለሰ። ከዚያም ምንነታቸውን ሳያውቅ ከትፎ ድስቱ ውስጥ ጨመራቸው።
በኋላም ሰዎቹ እንዲበሉ አቀረቡላቸው፤ እነሱ ግን ወጡን ገና እንደቀመሱት “የእውነተኛው አምላክ ሰው ሆይ፣ ድስቱ ውስጥ ገዳይ መርዝ አለ” ብለው ጮኹ። ሊበሉትም አልቻሉም።
እሱም “ዱቄት አምጡልኝ” አለ። ዱቄቱንም ድስቱ ውስጥ ከጨመረው በኋላ “ለሰዎቹ አቅርቡላቸው” አለ። በድስቱም ውስጥ ጉዳት የሚያስከትል ምንም ነገር አልተገኘም።
ከበዓልሻሊሻ የመጣ አንድ ሰው ነበር፤ እሱም ለእውነተኛው አምላክ ሰው ከፍሬው በኩራት የተዘጋጁ 20 የገብስ ዳቦዎችና አንድ ከረጢት የእሸት ዛላዎች ይዞለት መጣ። ከዚያም ኤልሳዕ “ሰዎቹ እንዲበሉ ስጣቸው” አለው።
ሆኖም አገልጋዩ “ይህን እንዴት አድርጌ ለ100 ሰው አቀርባለሁ” አለው። በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ “ሰዎቹ እንዲበሉ ስጣቸው፤ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ ‘ይበላሉ፤ ደግሞም ይተርፋቸዋል’” አለው።
ከዚያም አቀረበላቸው፤ እነሱም በሉ፤ ይሖዋም በተናገረው መሠረት ተረፋቸው።
በዚያ ጊዜ ሕዝቅያስ በጠና ታሞ ሞት አፋፍ ደርሶ ነበር። የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ከሕመምህ አትድንም፤ መሞትህ ስለማይቀር ለቤተሰብህ መመሪያ ስጥ።’”
በዚህ ጊዜ ፊቱን ወደ ግድግዳው አዙሮ ወደ ይሖዋ መጸለይ ጀመረ፦
“እባክህ ይሖዋ ሆይ፣ በታማኝነትና በሙሉ ልብ በፊትህ እንዴት እንደተመላለስኩ እንዲሁም በዓይኖችህ ፊት መልካም የሆነውን ነገር እንዳደረግኩ እንድታስታውስ አጥብቄ እለምንሃለሁ።” ሕዝቅያስም ምርር ብሎ አለቀሰ።
ኢሳይያስ ገና ወደ መካከለኛው ግቢ ሳይወጣ የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እሱ መጣ፦
“ተመልሰህ ሂድና የሕዝቤ መሪ የሆነውን ሕዝቅያስን እንዲህ በለው፦ ‘የአባትህ የዳዊት አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ጸሎትህን ሰምቻለሁ። እንባህንም አይቻለሁ። ስለሆነም እፈውስሃለሁ። በሦስተኛው ቀን ወደ ይሖዋ ቤት ትወጣለህ።
እኔም በዕድሜህ ላይ 15 ዓመት እጨምርልሃለሁ፤ ደግሞም አንተንና ይህችን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤ ስለ ራሴና ስለ አገልጋዬ ስለ ዳዊት ስል ከተማዋን እጠብቃታለሁ።”’”
ከዚያም ኢሳይያስ “የደረቀ የበለስ ጥፍጥፍ አምጡ” አለ። ጥፍጥፉንም አምጥተው እባጩ ላይ አደረጉለት፤ እሱም ቀስ በቀስ እየተሻለው ሄደ።
ሕዝቅያስ ኢሳይያስን “ይሖዋ እንደሚፈውሰኝና በሦስተኛው ቀን ወደ ይሖዋ ቤት እንደምወጣ ማወቅ የምችልበት ምልክት ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።
ኢሳይያስም መልሶ “ይሖዋ የተናገረውን ቃል እንደሚፈጽም የሚያሳየው ይሖዋ የሰጠህ ምልክት ይህ ነው፦ ጥላው በደረጃው ላይ አሥር ደረጃ ወደ ፊት እንዲሄድ ትፈልጋለህ ወይስ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ?” አለው።
ሕዝቅያስም “ጥላው አሥር ደረጃ ወደ ፊት መሄዱ ቀላል ነገር ነው፤ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ መመለሱ ግን ቀላል አይደለም” አለ።
ስለዚህ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ይሖዋ ጮኸ፤ እሱም በአካዝ ደረጃ ላይ ወደ ታች ወርዶ የነበረው ጥላ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደረገ።
በዚያን ጊዜ የባላዳን ልጅ የሆነው የባቢሎን ንጉሥ ቤሮዳክባላዳን ሕዝቅያስ መታመሙን ሰምቶ ስለነበር ደብዳቤና ስጦታ ላከለት።
ሕዝቅያስም ለመልእክተኞቹ ጥሩ አቀባበል አደረገላቸው፤ ከዚያም ግምጃ ቤቱን ሁሉ ይኸውም ብሩን፣ ወርቁን፣ የበለሳን ዘይቱን፣ ሌላውን ምርጥ ዘይት፣ የጦር መሣሪያውንና በግምጃ ቤቶቹ ውስጥ ያለውን ንብረት በሙሉ አሳያቸው። ሕዝቅያስ በቤቱም ሆነ በግዛቱ ሁሉ ያላሳያቸው ምንም ነገር አልነበረም።
ከዚያ በኋላ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ መጥቶ “እነዚህ ሰዎች ምን አሉ? የመጡትስ ከየት ነው?” ሲል ጠየቀው። ሕዝቅያስም “የመጡት ከሩቅ አገር፣ ከባቢሎን ነው” አለው።
ቀጥሎም “በቤትህ ያዩት ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ሕዝቅያስም “በቤቴ ያለውን ነገር ሁሉ አይተዋል። በግምጃ ቤቶቼ ውስጥ ካለው ንብረት ሁሉ ያላሳየኋቸው ምንም ነገር የለም” ሲል መለሰለት።
በዚህ ጊዜ ኢሳይያስ ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፦ “የይሖዋን ቃል ስማ፦
‘እነሆ፣ በቤትህ ያለው ሁሉና አባቶችህ እስካሁን ድረስ ያከማቹት ነገር ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚጋዝበት ቀን ይመጣል። አንድም የሚቀር ነገር አይኖርም’ ይላል ይሖዋ።
‘ከአንተ ከሚወለዱት ከገዛ ልጆችህ መካከልም አንዳንዶቹ ይወሰዳሉ፤ በባቢሎን ንጉሥ ቤተ መንግሥትም ባለሥልጣናት ይሆናሉ።’”
በዚህ ጊዜ ሕዝቅያስ ኢሳይያስን “የተናገርከው የይሖዋ ቃል መልካም ነው” አለው። አክሎም “በእኔ የሕይወት ዘመን ሰላምና መረጋጋት መኖሩ መልካም ነው” አለ።
የቀረው የሕዝቅያስ ታሪክ፣ ኃያልነቱ ሁሉ እንዲሁም ኩሬውንና ቦዩን ሠርቶ ውኃው ወደ ከተማዋ እንዲመጣ ያደረገበት መንገድ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ ይገኝ የለም?
በመጨረሻም ሕዝቅያስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በእሱም ምትክ ልጁ ምናሴ ነገሠ።
ኢዩ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ኢዮዓስ ነገሠ፤ እሱም በኢየሩሳሌም ሆኖ 40 ዓመት ገዛ። እናቱ ጺብያ የተባለች የቤርሳቤህ ተወላጅ ነበረች።
ኢዮዓስ ካህኑ ዮዳሄ ያስተምረው በነበረበት ዘመን ሁሉ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።
ይሁን እንጂ ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች አልተወገዱም፤ ደግሞም ሕዝቡ አሁንም ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች ላይ ይሠዋ እንዲሁም የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር።
ኢዮዓስ ካህናቱን እንዲህ አላቸው፦ “ቅዱስ መባ ሆኖ ወደ ይሖዋ ቤት የሚመጣውን ገንዘብ በሙሉ ማለትም እያንዳንዱ ሰው የሚጠበቅበትን ገንዘብ፣ አንድ ሰው እንዲከፍል የተተመነበትን ገንዘብና እያንዳንዱ ሰው ልቡ አነሳስቶት ወደ ይሖዋ ቤት የሚያመጣውን ገንዘብ በሙሉ ውሰዱ።
ካህናቱ በግል ቀርበው ገንዘቡን ከለጋሾቻቸው ላይ መቀበል ይችላሉ፤ ከዚያም በቤቱ ውስጥ የፈረሰውን ሁሉ ለመጠገን ይጠቀሙበት።”
ንጉሥ ኢዮዓስ በነገሠ በ23ኛው ዓመት ካህናቱ በቤቱ ውስጥ የፈረሰውን ነገር ገና አልጠገኑም ነበር።
በመሆኑም ንጉሥ ኢዮዓስ ካህኑን ዮዳሄንና ሌሎቹን ካህናት ጠርቶ “በቤቱ ውስጥ የፈረሰውን ነገር ያልጠገናችሁት ለምንድን ነው? ስለዚህ ገንዘቡ ቤቱን ለማደስ ሥራ ላይ እስካልዋለ ድረስ ከለጋሾች ላይ ከዚህ በላይ ገንዘብ አትቀበሉ” አላቸው።
በዚህ ጊዜ ካህናቱ ከሕዝቡ ላይ ተጨማሪ ገንዘብ ላለመቀበልና ቤቱን የማደሱን ኃላፊነት ላለመውሰድ ተስማሙ።
ከዚያም ካህኑ ዮዳሄ አንድ ሣጥን ወስዶ መክደኛው ላይ ቀዳዳ አበጀ፤ ሣጥኑንም አንድ ሰው ወደ ይሖዋ ቤት ሲገባ በስተ ቀኝ በኩል በሚያገኘው መሠዊያ አጠገብ አስቀመጠው። በር ጠባቂዎች ሆነው የሚያገለግሉት ካህናት ወደ ይሖዋ ቤት የሚመጣውን ገንዘብ በሙሉ እዚያ ይጨምሩት ነበር።
እነሱም ሣጥኑ ውስጥ ብዙ ገንዘብ መኖሩን በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ የንጉሡ ጸሐፊና ሊቀ ካህናቱ መጥተው ይሰበስቡታል፤ ከዚያም ወደ ይሖዋ ቤት የመጣውን ገንዘብ ይቆጥሩታል።
የተቆጠረውን ገንዘብ በይሖዋ ቤት በሚከናወነው ሥራ ላይ ለተሾሙት ሰዎች ይሰጧቸዋል። እነሱ ደግሞ ገንዘቡን በይሖዋ ቤት ለሚሠሩት አናጺዎችና የግንባታ ባለሙያዎች ይከፍሉ ነበር፤
በተጨማሪም ለግንበኞችና ለድንጋይ ጠራቢዎች ይከፍሉ ነበር። ደግሞም በይሖዋ ቤት ውስጥ የፈረሰውን ለመጠገን የሚውሉ ሳንቃዎችንና ጥርብ ድንጋዮችን ለመግዛት እንዲሁም ቤቱን ለመጠገን የሚያስፈልጉትን ሌሎች ወጪዎች ለመሸፈን ያውሉት ነበር።
ይሁን እንጂ ወደ ይሖዋ ቤት ከገባው ገንዘብ ውስጥ ለይሖዋ ቤት የሚሆኑ የብር ገንዳዎችን፣ የእሳት ማጥፊያዎችን፣ ጎድጓዳ ሳህኖችን፣ መለከቶችን አሊያም ማንኛውንም ዓይነት የወርቅ ወይም የብር ዕቃ ለመሥራት የዋለ ገንዘብ አልነበረም።
ገንዘቡን የሚሰጡት ሥራውን ለሚሠሩት ሰዎች ብቻ ነበር፤ እነሱም በገንዘቡ የይሖዋን ቤት ጠገኑ።
ለሠራተኞቹ እንዲከፍሉ ገንዘብ በሚሰጧቸው ሰዎች ላይ ቁጥጥር አያደርጉም ነበር፤ ምክንያቱም ሰዎቹ እምነት የሚጣልባቸው ነበሩ።
ይሁን እንጂ ለበደል መባዎች የሚሰጠው ገንዘብና ለኃጢአት መባዎች የሚሰጠው ገንዘብ የካህናቱ ንብረት ስለሆነ ወደ ይሖዋ ቤት እንዲገባ አይደረግም ነበር።
የሶርያ ንጉሥ ሃዛኤል ጌትን ለመውጋት የወጣው በዚህ ጊዜ ነበር፤ እሱም በቁጥጥር ሥር አዋላት፤ ከዚያም በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ወሰነ።