text
stringlengths
4
267
በመሆኑም ታላቅ ግብዣ አደረገላቸው፤ እነሱም በሉ፣ ጠጡም፤ ከዚያም ወደ ጌታቸው እንዲመለሱ አሰናበታቸው። ከዚያ በኋላ የሶርያውያን ወራሪ ቡድን ወደ እስራኤል ምድር ተመልሶ አልመጣም።
ከጊዜ በኋላ የሶርያ ንጉሥ ቤንሃዳድ ሠራዊቱን ሁሉ ሰብስቦ በመውጣት ሰማርያን ከበበ።
በመሆኑም በሰማርያ ታላቅ ረሃብ ተከሰተ፤ ከተማዋን ከበው በነበረበት ጊዜም አንድ የአህያ ጭንቅላት 80 የብር ሰቅል እንዲሁም አንድ አራተኛ የቃብ መስፈሪያ የርግብ ኩስ 5 የብር ሰቅል እስኪያወጣ ድረስ ረሃቡ ጸንቶ ነበር።
የእስራኤል ንጉሥ በቅጥሩ ላይ ሲያልፍ አንዲት ሴት “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ እርዳን!” በማለት ወደ እሱ ጮኸች።
ንጉሡም “ይሖዋ ካልረዳሽ እኔ ከየት አምጥቼ ልረዳሽ እችላለሁ? ከአውድማው ነው ወይስ ከወይኑ ወይስ ከዘይት መጭመቂያው?” አላት።
ከዚያም “ለመሆኑ ችግርሽ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃት። እሷም እንዲህ ስትል መለሰች፦ “ይህች ሴት ‘ዛሬ የአንቺን ልጅ እንድንበላው አምጪው፤ ነገ ደግሞ የእኔን ልጅ እንበላለን’ አለችኝ።
በመሆኑም ልጄን ቀቅለን በላነው። በማግስቱ ‘የአንቺን ልጅ እንድንበላው አምጪው’ አልኳት። እሷ ግን ልጇን ደበቀችው።”
ንጉሡ ሴትየዋ ያለችውን ሲሰማ ልብሱን ቀደደ። በቅጥሩም ላይ በሚያልፍበት ጊዜ ሕዝቡ ንጉሡ ከልብሶቹ ሥር ማቅ መልበሱን አየ።
ከዚያም “የሻፋጥ ልጅ የኤልሳዕ ጭንቅላት ዛሬ አንገቱ ላይ ካደረ አምላክ እንዲህ ያድርግብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጣብኝ!” አለ።
ኤልሳዕ ቤቱ ውስጥ ተቀምጦ ነበር፤ ሽማግሌዎቹም አብረውት ተቀምጠው ነበር። ንጉሡ አንድ ሰው ከፊቱ አስቀድሞ ላከ፤ ሆኖም መልእክተኛው ከመድረሱ በፊት ኤልሳዕ ሽማግሌዎቹን እንዲህ አላቸው፦ “ይህ የነፍሰ ገዳይ ልጅ ጭንቅላቴን ሊያስቆርጥ ሰው እንደላከ ታያላችሁ? በሉ መልእክተኛው ሲመጣ በሩን ዝጉት፤ ደግሞም እንዳይገባ በሩን ዘግታችሁ ያዙት። የጌታው ኮቴ ድምፅ ከኋላው ይሰማ የለም?”
እሱም ገና ከእነሱ ጋር እየተነጋገረ ሳለ መልእክተኛው ወደ እሱ ደረሰ፤ ንጉሡም “ይህ ከይሖዋ የመጣ ጥፋት ነው። ታዲያ ከዚህ በላይ ይሖዋን ለምን እጠብቃለሁ?” አለ።
ኤልሳዕ፣ ልጇን ከሞት ያስነሳላትን ሴት “ተነስተሽ ከቤተሰብሽ ጋር የባዕድ አገር ሰው ሆነሽ መኖር ወደምትችዪበት ቦታ ሂጂ፤ ይሖዋ ረሃብ እንደሚከሰት ተናግሯልና፤ ደግሞም ረሃቡ በምድሪቱ ላይ ለሰባት ዓመት ይቆያል” አላት።
በመሆኑም ሴትየዋ ተነስታ የእውነተኛው አምላክ ሰው እንደነገራት አደረገች። እሷም ከመላ ቤተሰቧ ጋር ሄደች፤ በፍልስጤማውያንም ምድር ለሰባት ዓመት ተቀመጠች።
በሰባቱ ዓመት ማብቂያ ላይ ሴትየዋ ከፍልስጤማውያን ምድር ተመልሳ መጣች፤ ከዚያም ስለ ቤቷና ስለ መሬቷ ለንጉሡ አቤቱታ ለማቅረብ ሄደች።
በዚህ ጊዜ ንጉሡ የእውነተኛው አምላክ ሰው አገልጋይ የሆነውን ግያዝን “እስቲ ኤልሳዕ ያደረጋቸውን ታላላቅ ነገሮች በሙሉ ተርክልኝ” እያለው ነበር።
እሱም ኤልሳዕ የሞተውን ልጅ እንዴት እንዳስነሳው ለንጉሡ እየተረከለት ሳለ ኤልሳዕ ልጇን ከሞት ያስነሳላት ሴት ስለ ቤቷና ስለ መሬቷ ለንጉሡ አቤቱታ ለማቅረብ መጣች። ግያዝም ወዲያውኑ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ ሴትየዋ ይህች ናት፤ ኤልሳዕ ያስነሳው ልጇም ይሄ ነው” አለው።
በዚህ ጊዜ ንጉሡ ሴትየዋን ጠየቃት፤ እሷም ታሪኩን ነገረችው። ከዚያም ንጉሡ ከቤተ መንግሥት ባለሥልጣናቱ አንዱን “የእሷ የሆነውን በሙሉ እንዲሁም መሬቷን ከለቀቀችበት ቀን አንስቶ እስካሁን ድረስ መሬቱ ያፈራውን ምርት ሁሉ መልስላት” የሚል መመሪያ በመስጠት መደበላት።
የሶርያ ንጉሥ ቤንሃዳድ ታሞ ሳለ ኤልሳዕ ወደ ደማስቆ መጣ። በመሆኑም “የእውነተኛው አምላክ ሰው ወደዚህ መጥቷል” ተብሎ ተነገረው።
በዚህ ጊዜ ንጉሡ ሃዛኤልን “ስጦታ ይዘህ ወደ እውነተኛው አምላክ ሰው ሂድ። በእሱም አማካኝነት ይሖዋን ‘ከዚህ በሽታ እድናለሁ?’ ብለህ ጠይቀው” አለው።
ሃዛኤልም በደማስቆ ከሚገኘው ምርጥ ነገር ሁሉ 40 የግመል ጭነት ስጦታ ይዞ ሊያገኘው ሄደ። እሱም መጥቶ በፊቱ በመቆም “ልጅህ የሶርያ ንጉሥ ቤንሃዳድ ‘ከዚህ በሽታ እድናለሁ?’ በማለት ወደ አንተ ልኮኛል” አለው።
ኤልሳዕም “ሂድና ‘በእርግጥ ትድናለህ’ በለው፤ ሆኖም መሞቱ እንደማይቀር ይሖዋ አሳይቶኛል” ሲል መለሰለት።
ደግሞም እስኪያፍር ድረስ ትኩር ብሎ ተመለከተው። ከዚያም የእውነተኛው አምላክ ሰው አለቀሰ።
ሃዛኤልም “ጌታዬ የሚያለቅሰው ለምንድን ነው?” በማለት ጠየቀው። እሱም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “በእስራኤል ሕዝብ ላይ ምን ዓይነት ጉዳት እንደምታደርስ ስለማውቅ ነው። የተመሸጉ ስፍራዎቻቸውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ምርጥ የሆኑ ሰዎቻቸውን በሰይፍ ትገድላለህ፤ ልጆቻቸውንም ትፈጠፍጣለህ፤ ነፍሰ ጡር የሆኑ ሴቶቻቸውንም ሆድ ትቀድዳለህ።”
ሃዛኤልም “ለመሆኑ ተራ ውሻ የሆነው አገልጋይህ እንዲህ ያለ ነገር እንዴት ሊያደርግ ይችላል?” አለው። ኤልሳዕ ግን “አንተ በሶርያ ላይ ንጉሥ እንደምትሆን ይሖዋ አሳይቶኛል” አለው።
ከዚያም ከኤልሳዕ ተለይቶ በመሄድ ወደ ጌታው መጣ፤ ቤንሃዳድም “ለመሆኑ ኤልሳዕ ምን አለህ?” አለው። እሱም “በእርግጥ እንደምትድን ነግሮኛል” ሲል መለሰለት።
በማግስቱ ግን ሃዛኤል የአልጋ ልብስ ወስዶ ውኃ ውስጥ ከነከረ በኋላ የንጉሡን ፊት ሸፈነው፤ ንጉሡም ሞተ። ሃዛኤልም በምትኩ ነገሠ።
የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሳፍጥ ልጅ ኢዮራም ነገሠ፤ በዚህ ጊዜ ኢዮሳፍጥ በይሁዳ ንጉሥ ሆኖ ይገዛ ነበር።
ኢዮራም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 32 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ስምንት ዓመት ገዛ።
የአክዓብን ልጅ አግብቶ ስለነበር ከአክዓብ ቤት የሆኑት እንዳደረጉት ሁሉ እሱም በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ በይሖዋም ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።
ሆኖም ይሖዋ ለአገልጋዩ ለዳዊት ሲል ይሁዳን ማጥፋት አልፈለገም፤ ምክንያቱም ለእሱና ለልጆቹ ለሁልጊዜ የሚኖር መብራት እንደሚሰጥ ቃል ገብቶ ነበር።
በእሱ ዘመን ኤዶም በይሁዳ ላይ ዓምፆ የራሱን ንጉሥ አነገሠ።
በመሆኑም ኢዮራም ሠረገሎቹን ሁሉ ይዞ ወደ ጻኢር ተሻገረ፤ በሌሊትም ተነስቶ እሱንና የሠረገሎቹን አዛዦች ከበው የነበሩትን ኤዶማውያን ድል አደረገ፤ ሠራዊቱም ሸሽቶ ወደየድንኳኑ ሄደ።
ሆኖም ኤዶም እስከ ዛሬ ድረስ በይሁዳ ላይ እንዳመፀ ነው። ሊብናም በዚሁ ጊዜ ዓመፀ።
የቀረው የኢዮራም ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?
በመጨረሻም ኢዮራም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ከአባቶቹም ጋር በዳዊት ከተማ ተቀበረ። በእሱም ምትክ ልጁ አካዝያስ ነገሠ።
የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በ12ኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ነገሠ።
አካዝያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 22 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ አንድ ዓመት ገዛ። እናቱም ጎቶልያ የተባለች የእስራኤል ንጉሥ የኦምሪ የልጅ ልጅ ነበረች።
እሱም ከአክዓብ ቤተሰብ ጋር በጋብቻ ተሳስሮ ስለነበር የአክዓብን ቤት መንገድ ተከተለ፤ እንዲሁም የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።
በመሆኑም አካዝያስ ከአክዓብ ልጅ ከኢዮራም ጋር ሆኖ ከሶርያ ንጉሥ ከሃዛኤል ጋር ለመዋጋት ወደ ራሞትጊልያድ ሄደ፤ ሆኖም ሶርያውያን ኢዮራምን አቆሰሉት።
ስለዚህ ንጉሥ ኢዮራም ከሶርያ ንጉሥ ከሃዛኤል ጋር በተዋጋበት ጊዜ ሶርያውያን በራማ ካቆሰሉት ቁስል ለማገገም ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ። የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ፣ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም ቆስሎ ስለነበር እሱን ለማየት ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።
ዳዊት በራሱ ቤት መኖር እንደጀመረ ነቢዩ ናታንን “የይሖዋ የቃል ኪዳኑ ታቦት በድንኳን ውስጥ ተቀምጦ ሳለ ይኸው እኔ ከአርዘ ሊባኖስ በተሠራ ቤት ውስጥ እየኖርኩ ነው” አለው።
ናታንም ዳዊትን “እውነተኛው አምላክ ከአንተ ጋር ስለሆነ በልብህ ያለውን ነገር ሁሉ አድርግ” አለው።
በዚያው ሌሊት የአምላክ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ናታን መጣ፦
“ሂድና አገልጋዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የምኖርበትን ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም።
እስራኤልን ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ከአንዱ ድንኳን ወደ ሌላው ድንኳን፣ ከአንዱም የማደሪያ ድንኳን ወደ ሌላው የማደሪያ ድንኳን እሄድ ነበር እንጂ በቤት ውስጥ አልኖርኩም።
ከመላው እስራኤል ጋር በተጓዝኩበት ጊዜ ሁሉ ሕዝቤን እረኛ ሆነው እንዲጠብቁ ከሾምኳቸው የእስራኤል ፈራጆች መካከል ‘በአርዘ ሊባኖስ፣ ቤት ያልሠራህልኝ ለምንድን ነው?’ ያልኩት ማን አለ?” ’
“አሁንም አገልጋዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ እንድትሆን መንጋ ከምትጠብቅበት ስፍራ ወሰድኩህ።
እኔም በምትሄድበት ሁሉ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋለሁ፤ ስምህንም በምድር ላይ እንዳሉ ታላላቅ ሰዎች ስም አደርገዋለሁ።
ለሕዝቤ ለእስራኤል ቦታ እሰጣቸዋለሁ፤ ተረጋግተው እንዲቀመጡም አደርጋለሁ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ከእንግዲህም የሚረብሻቸው አይኖርም፤ ክፉዎችም እንደቀድሞው ዳግመኛ አይጨቁኗቸውም፤
በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሳፍንትን ከሾምኩበት ጊዜ አንስቶ ሲያደርጉ እንደነበሩት አያደርጉባቸውም። ጠላቶቻችሁም ሁሉ እንዲገዙላችሁ አደርጋለሁ። በተጨማሪም ‘ይሖዋ ቤት እንደሚሠራልህ’ እነግርሃለሁ።
“ ‘ “የሕይወት ዘመንህ አብቅቶ ከአባቶችህ ጋር ለመሆን በምትሄድበት ጊዜ ከአንተ በኋላ ዘርህን ይኸውም ከወንዶች ልጆችህ መካከል አንዱን አስነሳለሁ፤ ንግሥናውንም አጸናለሁ።
ቤት የሚሠራልኝ እሱ ነው፤ እኔም ዙፋኑን ለዘላለም አጸናለሁ።
አባት እሆነዋለሁ፤ እሱም ልጄ ይሆናል። ታማኝ ፍቅሬንም ከአንተ በፊት ከነበረው ላይ እንደወሰድኩ ከእሱ ላይ አልወስድም።
በቤቴና በንጉሣዊ ግዛቴ ላይ ለዘላለም ጸንቶ እንዲኖር አደርገዋለሁ፤ ዙፋኑም ለዘላለም ይዘልቃል።” ’ ”
ናታንም ይህን ቃል ሁሉና ይህን ራእይ በሙሉ ለዳዊት ነገረው።
በዚህ ጊዜ ንጉሥ ዳዊት ገብቶ በይሖዋ ፊት ተቀመጠ፤ እንዲህም አለ፦ “ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ኧረ ለመሆኑ እኔ ማን ነኝ? እስከዚህ ድረስ ያደረስከኝስ ቤቴ ምን ስለሆነ ነው?
አምላክ ሆይ፣ ይህ ሳያንስ ስለ አገልጋይህ ቤት ገና ወደፊት የሚሆነውንም ነገር ተናገርክ፤ ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ከዚህ በላይ ከፍ ከፍ ሊደረግ እንደሚገባ ሰው አድርገህ ተመልክተኸኛል።
ስለሰጠኸኝ ክብር አገልጋይህ ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ሊልህ ይችላል? አንተ አገልጋይህን በሚገባ ታውቀው የለ?
ይሖዋ ሆይ፣ ለአገልጋይህ ስትል፣ ከልብህ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ታላቅነትህን በመግለጥ እነዚህን ሁሉ ታላላቅ ነገሮች ፈጽመሃል።
ይሖዋ ሆይ፣ እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤ ከአንተ በቀር አምላክ የለም፤ በጆሯችን የሰማነው ነገር ሁሉ ይህን ያረጋግጣል።
በምድር ላይ እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ ሌላ ብሔር ማን አለ? እውነተኛው አምላክ ሄዶ ሕዝቡ አድርጎ ዋጀው። ብሔራትን ከግብፅ ከዋጀኸው ሕዝብህ ፊት አባረህ ታላላቅና አስፈሪ ነገሮችን በመፈጸም ስምህን አስጠራህ።
ሕዝብህን እስራኤልን እስከ ወዲያኛው የራስህ ሕዝብ አደረግከው፤ ይሖዋ ሆይ፣ አንተም አምላኩ ሆንክ።
አሁንም ይሖዋ ሆይ፣ አገልጋይህንና ቤቱን በተመለከተ የገባኸው ቃል እስከ ወዲያኛው የጸና ይሁን፤ ቃል እንደገባኸውም አድርግ።
ሰዎች ‘የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ለእስራኤል አምላክ ነው’ እንዲሉ ስምህ የጸና ይሁን፤ ደግሞም ለዘላለም ከፍ ከፍ ይበል፤ የአገልጋይህም የዳዊት ቤት በፊትህ የጸና ይሁን።
አምላኬ ሆይ፣ አንተ ለአገልጋይህ ቤት የመሥራት ዓላማ እንዳለህ አሳውቀኸዋልና። አገልጋይህ ይህን ጸሎት በልበ ሙሉነት ወደ አንተ የሚያቀርበው በዚህ ምክንያት ነው።
አሁንም ይሖዋ ሆይ፣ እውነተኛው አምላክ አንተ ነህ፤ ለአገልጋይህም እነዚህን መልካም ነገሮች ለማድረግ ቃል ገብተህለታል።
በመሆኑም የአገልጋይህን ቤት እባክህ ባርክ፤ በፊትህም ለዘላለም የጸና ይሁን፤ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ቀድሞውንም ባርከኸዋልና፤ ለዘላለምም የተባረከ ይሆናል።”
ከጊዜ በኋላ የአሞናውያን ንጉሥ ናሃሽ ሞተ፤ በእሱም ፋንታ ልጁ ነገሠ።
በዚህ ጊዜ ዳዊት “አባቱ ታማኝ ፍቅር ስላሳየኝ እኔም ለናሃሽ ልጅ ለሃኑን ታማኝ ፍቅር አሳየዋለሁ” አለ። በመሆኑም ዳዊት በአባቱ ሞት ከደረሰበት ሐዘን እንዲያጽናኑት መልእክተኞችን ላከ። ሆኖም የዳዊት አገልጋዮች ሃኑንን ለማጽናናት ወደ አሞናውያን ምድር ሲደርሱ
የአሞናውያን መኳንንት ሃኑንን እንዲህ አሉት፦ “ዳዊት አጽናኞችን ወደ አንተ የላከው አባትህን አክብሮ ይመስልሃል? አገልጋዮቹ ወደ አንተ የመጡት ምድሪቱን በሚገባ ለማጥናትና በውስጧ ያለውን ነገር ለመሰለል እንዲሁም አንተን ለመገልበጥ አይደለም?”
በመሆኑም ሃኑን የዳዊትን አገልጋዮች ወስዶ ላጫቸው፤ ልብሳቸውንም እስከ መቀመጫቸው ድረስ አሳጥሮ በመቁረጥ መልሶ ላካቸው።
በአገልጋዮቹ ላይ የደረሰውን ነገር ለዳዊት በነገሩት ጊዜ ሰዎቹ በኀፍረት ተውጠው ስለነበር ዳዊት ወዲያውኑ መልእክተኞችን ወደ እነሱ ላከ፤ ንጉሡም “ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ቆዩ፤ ከዚያ በኋላ ተመለሱ” አላቸው።
ውሎ አድሮ አሞናውያን በዳዊት ዘንድ እንደ ጥንብ እንደተቆጠሩ ተገነዘቡ፤ በመሆኑም ሃኑን እና አሞናውያን ከሜሶጶጣሚያ፣ ከአራምመዓካና ከጾባህ ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን ለመቅጠር 1,000 የብር ታላንት ላኩ።
በዚህ መንገድ 32,000 ሠረገሎችን፣ የማአካን ንጉሥና ሕዝቡን ለራሳቸው ቀጠሩ። እነሱም መጥተው በመደባ ፊት ለፊት ሰፈሩ። አሞናውያን ደግሞ ከየከተሞቻቸው ተሰብስበው ለጦርነት መጡ።
ዳዊት ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮአብን እንዲሁም እጅግ ኃያላን የሆኑትን ተዋጊዎቹን ጨምሮ መላውን ሠራዊት ላከ።
አሞናውያንም ወጥተው በከተማዋ መግቢያ ላይ ለውጊያ ተሰለፉ፤ የመጡት ነገሥታት ደግሞ ለብቻቸው ሜዳ ላይ ተሰለፉ።
ኢዮዓብ ወታደሮቹ ከፊትና ከኋላ ጥቃት ለመሰንዘር ወደ እሱ እየገሰገሱ መምጣታቸውን ሲያይ በእስራኤል ካሉት ምርጥ የሆኑ ተዋጊዎች መካከል የተወሰኑትን መርጦ ሶርያውያንን እንዲገጥሙ አሰለፋቸው።
የቀሩትን ሰዎች ደግሞ በወንድሙ በአቢሳ አመራር ሥር ሆነው አሞናውያንን እንዲገጥሙ አሰለፋቸው።
ከዚያም እንዲህ አለው፦ “ሶርያውያን ከበረቱብኝ አንተ ትደርስልኛለህ፤ አሞናውያን ከበረቱብህ ደግሞ እኔ እደርስልሃለሁ።
ለሕዝባችንና ለአምላካችን ከተሞች ስንል ብርቱና ደፋር መሆን አለብን፤ ይሖዋም በፊቱ መልካም የሆነውን ነገር ያደርጋል።”
ከዚያም ኢዮዓብና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሶርያውያንን ለመግጠም ወደ እነሱ ሲገሰግሱ ሶርያውያኑ ከፊቱ ሸሹ።
አሞናውያንም ሶርያውያን እንደ ሸሹ ሲያዩ እነሱም ከወንድሙ ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማዋ ገቡ። ከዚያም ኢዮዓብ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።
ሶርያውያን በእስራኤላውያን ድል እንደተመቱ ሲያዩ መልእክተኞች ልከው በወንዙ አካባቢ የነበሩትን ሶርያውያን አስጠሩ፤ የሃዳድኤዜር ሠራዊት አለቃ የሆነውም ሾፋክ ይመራቸው ነበር።
ዳዊት ወሬው በተነገረው ጊዜ ወዲያውኑ እስራኤልን ሁሉ ሰብስቦ ዮርዳኖስን በመሻገር ወደ እነሱ መጣ፤ ተዋጊዎቹንም በእነሱ ላይ አሰለፈ። ዳዊት ሶርያውያንን ለመግጠም ተዋጊዎቹን ባሰለፈ ጊዜ ከእሱ ጋር ተዋጉ።
ይሁንና ሶርያውያን ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን መካከል 7,000 ሠረገለኞችንና 40,000 እግረኛ ወታደሮችን ገደለ፤ የሠራዊቱ አዛዥ የሆነውን ሾፋክንም ገደለው።
የሃዳድኤዜር አገልጋዮች በእስራኤል እንደተሸነፉ ባዩ ጊዜ ወዲያውኑ ከዳዊት ጋር እርቅ በመፍጠር ለእሱ ተገዙ፤ ሶርያም ከዚህ በኋላ አሞናውያንን ለመርዳት ፈቃደኛ አልሆነችም።
ከጊዜ በኋላ እስራኤላውያን በሙሉ በኬብሮን ወደሚገኘው ወደ ዳዊት ተሰብስበው እንዲህ አሉት፦ “እንግዲህ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ፣ የሥጋህም ቁራጭ ነን።
ባለፉት ዘመናት ሳኦል ንጉሥ በነበረበት ጊዜ እስራኤል ወደ ጦርነት ሲወጣ የምትመራው አንተ ነበርክ። አምላክህ ይሖዋም ‘ሕዝቤን እስራኤልን እረኛ ሆነህ ትጠብቃለህ፤ በሕዝቤ በእስራኤልም ላይ መሪ ትሆናለህ’ ብሎህ ነበር።”
በመሆኑም የእስራኤል ሽማግሌዎች በሙሉ ንጉሡ ወዳለበት ወደ ኬብሮን መጡ፤ ዳዊትም በኬብሮን ከእነሱ ጋር በይሖዋ ፊት ቃል ኪዳን ገባ። ከዚያም በሳሙኤል አማካኝነት በተነገረው የይሖዋ ቃል መሠረት ዳዊትን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርገው ቀቡት።
በኋላም ዳዊትና መላው እስራኤል ወደ ኢየሩሳሌም ይኸውም ኢያቡሳውያን ይኖሩበት ወደነበረው ምድር ወደ ኢያቡስ ሄዱ።
የኢያቡስ ነዋሪዎችም ዳዊትን “ፈጽሞ ወደዚህ አትገባም!” በማለት ተሳለቁበት። ይሁን እንጂ ዳዊት በአሁኑ ጊዜ የዳዊት ከተማ ተብላ የምትጠራውን የጽዮንን ምሽግ ያዘ።
ስለሆነም ዳዊት “ኢያቡሳውያንን በመጀመሪያ የሚመታ ሰው አለቃና መኮንን ይሆናል” አለ። የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ በመጀመሪያ ወደዚያ ወጣ፤ እሱም አለቃ ሆነ።
ከዚያም ዳዊት በምሽጉ ውስጥ መኖር ጀመረ። ከዚህም የተነሳ ስፍራውን የዳዊት ከተማ አሉት።
እሱም ከጉብታው አንስቶ በዙሪያው እስካሉት ቦታዎች ድረስ ከተማዋን ዙሪያዋን ገነባ፤ ኢዮዓብ ደግሞ ቀሪውን የከተማዋን ክፍል መልሶ ሠራ።
በዚህ ሁኔታ ዳዊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ሄደ፤ የሠራዊት ጌታ ይሖዋም ከእሱ ጋር ነበር።
የዳዊት ኃያላን ተዋጊዎች መሪዎች እነዚህ ናቸው፤ እነሱም ከመላው የእስራኤል ሕዝብ ጋር ሆነው ይሖዋ ለእስራኤል ቃል በገባው መሠረት ንጉሥ እንዲሆን ብርቱ ድጋፍ አድርገውለታል።
የዳዊት ኃያላን ተዋጊዎች ስም ዝርዝር ይህ ነው፦ የሦስቱ መሪ የሆነው የሃክሞናዊው ልጅ ያሾብአም። እሱም ጦሩን ሰብቆ በአንድ ጊዜ 300 ሰው ገደለ።
ከእሱ ቀጥሎ የአሆሐያዊው የዶዶ ልጅ አልዓዛር ነበር። እሱም ከሦስቱ ኃያላን ተዋጊዎች መካከል አንዱ ነው።
ፍልስጤማውያን ለጦርነት ተሰብስበው በነበረበት ጊዜ በጳስዳሚም ከዳዊት ጋር አብሮ ነበር። በዚያም የገብስ ሰብል የሞላበት መሬት ነበር፤ ሕዝቡም ከፍልስጤማውያን የተነሳ ከአካባቢው ሸሹ።
እሱ ግን በእርሻው መካከል ካለበት ንቅንቅ ሳይል መሬቱ እንዳይያዝ አደረገ፤ ፍልስጤማውያንንም መታቸው፤ በመሆኑም ይሖዋ ታላቅ ድል አጎናጸፈ።