text
stringlengths
4
267
በዚህ ጊዜ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮዓስ የይሁዳ ነገሥታት የነበሩት አባቶቹ ኢዮሳፍጥ፣ ኢዮራምና አካዝያስ የቀደሷቸውን ቅዱስ መባዎች ሁሉ፣ የራሱን ቅዱስ መባዎች እንዲሁም በይሖዋ ቤትና በንጉሡ ቤት ግምጃ ቤቶች የተገኘውን ወርቅ ሁሉ ወስዶ ለሶርያ ንጉሥ ለሃዛኤል ላከለት። በመሆኑም ሃዛኤል ኢየሩሳሌምን ከመውጋት ተመለሰ።
የቀረው የኢዮዓስ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?
ይሁንና አገልጋዮቹ በኢዮዓስ ላይ በማሴር ወደ ሲላ ቁልቁል በሚወስደው መንገድ ላይ በጉብታው ቤት ገደሉት።
ኢዮዓስን መትተው የገደሉት፣ አገልጋዮቹ የነበሩት የሺምዓት ልጅ ዮዛካር እና የሾሜር ልጅ የሆዛባድ ነበሩ። እነሱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት፤ በእሱም ምትክ ልጁ አሜስያስ ነገሠ።
የእስራኤል ንጉሥ የኤላህ ልጅ ሆሺአ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ ነገሠ።
እሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ29 ዓመት ገዛ። እናቱ አቢ ትባል ነበር፤ እሷም የዘካርያስ ልጅ ነበረች።
አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ እሱም በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።
ከፍ ያሉትን የማምለኪያ ቦታዎች ያስወገደው፣ የማምለኪያ ዓምዶቹን ያደቀቀውና የማምለኪያ ግንዱን የቆራረጠው እሱ ነበር። በተጨማሪም ሙሴ ሠርቶት የነበረውን የመዳብ እባብ አደቀቀ፤ የእስራኤል ሕዝብ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ለእባቡ የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ ነበርና፤ ይህም ጣዖት የመዳብ እባብ ተብሎ ይጠራ ነበር።
እሱም በእስራኤል አምላክ በይሖዋ ታመነ፤ ከእሱ በኋላም ሆነ ከእሱ በፊት ከተነሱት የይሁዳ ነገሥታት መካከል እንደ እሱ ያለ አልተገኘም።
ከይሖዋ ጋር ተጣበቀ። እሱንም ከመከተል ዞር አላለም፤ ይሖዋ ለሙሴ የሰጠውን ትእዛዝ ጠብቆ ኖረ።
ይሖዋም ከእሱ ጋር ነበር። የሚያደርገውንም ነገር ሁሉ በጥበብ ያከናውን ነበር። በኋላም በአሦር ንጉሥ ላይ ዓመፀ፤ እሱንም ለማገልገል ፈቃደኛ አልሆነም።
በተጨማሪም እስከ ጋዛና እስከ ክልሎቿ ድረስ በመዝለቅ ፍልስጤማውያንን ከመጠበቂያ ግንቡ አንስቶ እስከተመሸገው ከተማ ድረስ ድል አደረገ።
ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ማለትም የእስራኤል ንጉሥ የኤላህ ልጅ ሆሺአ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰልምናሶር በሰማርያ ላይ ዘምቶ ከበባት።
በሦስተኛው ዓመት ማብቂያ ላይ ከተማዋን ያዟት፤ ሕዝቅያስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት ይኸውም የእስራኤል ንጉሥ ሆሺአ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ሰማርያ ተያዘች።
ከዚያም የአሦር ንጉሥ እስራኤላውያንን ወደ አሦር በግዞት ወስዶ በሃላህ፣ በጎዛን ወንዝ አጠገብ በምትገኘው በሃቦርና በሜዶናውያን ከተሞች አሰፈራቸው።
ይህ የሆነው የአምላካቸውን የይሖዋን ድምፅ ከመስማት ይልቅ ቃል ኪዳኑን ስላፈረሱ ይኸውም የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ የሰጣቸውን ትእዛዝ በሙሉ ስላልጠበቁ ነው። አልሰሙም፤ ደግሞም አልታዘዙም።
ንጉሥ ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች ሁሉ ላይ ዘምቶ ያዛቸው።
በመሆኑም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ በለኪሶ ወደነበረው ወደ አሦር ንጉሥ “በድያለሁ። እባክህ ከእኔ ተመለስ፤ እኔም የምትጠይቀኝን ነገር ሁሉ እሰጣለሁ” የሚል መልእክት ላከ። የአሦርም ንጉሥ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ላይ 300 የብር ታላንትና 30 የወርቅ ታላንት ቅጣት ጣለበት።
በመሆኑም ሕዝቅያስ በይሖዋ ቤትና በንጉሡ ቤት ግምጃ ቤቶች የተገኘውን ብር ሁሉ ሰጠው።
በዚህ ጊዜ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ራሱ የለበጣቸውን የይሖዋን ቤተ መቅደስ በሮችና መቃኖች ነቃቅሎ ለአሦር ንጉሥ ሰጠው።
ከዚያም የአሦር ንጉሥ ታርታኑን፣ ራብሳሪሱንና ራብሻቁን ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ላካቸው። እነሱም ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው ወደ ልብስ አጣቢው እርሻ በሚወስደው አውራ ጎዳና ላይ በሚገኘው በላይኛው ኩሬ የውኃ መውረጃ ቦይ አጠገብ ቆሙ።
ንጉሡ እንዲመጣ በተጣሩ ጊዜ የንጉሡ ቤት ኃላፊ የሆነው የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሐፊው ሸብናህ እና ታሪክ ጸሐፊው የአሳፍ ልጅ ዮአህ ወደ እነሱ ወጡ።
ራብሻቁም እንዲህ አላቸው፦ “እስቲ ሕዝቅያስን እንዲህ በሉት፦ ‘ታላቁ ንጉሥ፣ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ “ለመሆኑ እንዲህ እንድትተማመን ያደረገህ ምንድን ነው?
‘የጦር ስልትና ለመዋጋት የሚያስችል ኃይል አለኝ’ ትላለህ፤ ይሁንና ይህ ከንቱ ወሬ ነው። ለመሆኑ በእኔ ላይ ለማመፅ የደፈርከው በማን ተማምነህ ነው?
እነሆ፣ ሰው ቢመረኮዘው እጁ ላይ ሊሰነቀርና ሊወጋው ከሚችለው ከዚህ የተቀጠቀጠ ሸምበቆ፣ ከግብፅ ድጋፍ አገኛለሁ ብለህ ተማምነሃል። የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው።
‘እኛ የምንታመነው በአምላካችን በይሖዋ ነው’ የምትሉኝ ከሆነ ደግሞ፣ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ‘መስገድ ያለባችሁ በኢየሩሳሌም በሚገኘው በዚህ መሠዊያ ፊት ነው’ ብሎ የእሱን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎችና መሠዊያዎች አስወግዶ የለም?”’
በል እስቲ፣ አሁን ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተወራረድ፦ ጋላቢዎች ማግኘት የምትችል ከሆነ 2,000 ፈረሶች እሰጥሃለሁ።
አንተ የምትታመነው በግብፅ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ነው፤ ታዲያ ከጌታዬ አገልጋዮች መካከል ዝቅተኛ ደረጃ ያለውን አንዱን አለቃ እንኳ እንዴት መመከት ትችላለህ?
ለመሆኑ ይህን አካባቢ ለማጥፋት የመጣሁት ይሖዋ ሳይፈቅድልኝ ይመስልሃል? ይሖዋ ራሱ ‘በዚህ ምድር ላይ ዘምተህ አጥፋው’ ብሎኛል።”
በዚህ ጊዜ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ሸብናህ እና ዮአህ ራብሻቁን እንዲህ አሉት፦ “እባክህ፣ እኛ አገልጋዮችህ ቋንቋውን ስለምናውቅ በአረማይክ ቋንቋ አናግረን፤ በቅጥሩ ላይ ያለው ሕዝብ በሚሰማው በአይሁዳውያን ቋንቋ አታነጋግረን።”
ራብሻቁ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ጌታዬ ይህን ቃል እንድናገር የላከኝ ለጌታህና ለአንተ ብቻ ነው? ከእናንተ ጋር የገዛ ራሳቸውን እዳሪ ለሚበሉትና የገዛ ራሳቸውን ሽንት ለሚጠጡት በቅጥሩ ላይ ለተቀመጡት ሰዎች ጭምር አይደለም?”
ከዚያም ራብሻቁ ቆሞ ከፍ ባለ ድምፅ በአይሁዳውያን ቋንቋ እንዲህ አለ፦ “የታላቁን ንጉሥ፣ የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ።
ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ ‘ሕዝቅያስ አያታላችሁ፤ እሱ ከእጄ ሊታደጋችሁ አይችልምና።
ደግሞም ሕዝቅያስ “ይሖዋ በእርግጥ ይታደገናል፤ ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትወድቅም” እያለ በይሖዋ እንድትታመኑ አያድርጋችሁ።
ሕዝቅያስን አትስሙት፤ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላልና፦ “ከእኔ ጋር ሰላም ፍጠሩ፤ እጃችሁንም ስጡ፤ እያንዳንዳችሁም ከራሳችሁ ወይንና ከራሳችሁ በለስ ትበላላችሁ፤ ከራሳችሁም የውኃ ጉድጓድ ትጠጣላችሁ፤
ይህም የሚሆነው መጥቼ የእናንተን ምድር ወደምትመስለው፣ እህልና አዲስ ወይን፣ ዳቦና የወይን እርሻ፣ የወይራ ዛፍና ማር ወደሚገኝባት ምድር እስክወስዳችሁ ድረስ ነው። በዚያን ጊዜ በሕይወት ትኖራላችሁ እንጂ አትሞቱም። ሕዝቅያስን አትስሙት፤ ‘ይሖዋ ይታደገናል’ እያለ ያታልላችኋልና።
ከብሔራት አማልክት መካከል ምድሩን ከአሦር ንጉሥ እጅ ያስጣለ አለ?
የሃማትና የአርጳድ አማልክት የት አሉ? የሰፋርዊም፣ የሄና እና የኢዋ አማልክትስ የት አሉ? ሰማርያን ከእጄ ማስጣል ችለዋል?
ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ ምድሩን ከእጄ ማስጣል የቻለ የትኛው ነው? ታዲያ ይሖዋ ኢየሩሳሌምን ከእጄ ሊያስጥላት ይችላል?”’”
ሕዝቡ ግን ንጉሡ “ምንም መልስ አትስጡት” ብሎ አዝዞ ስለነበር ዝም አለ፤ አንድም ቃል አልመለሰለትም።
ይሁንና የቤቱ አስተዳዳሪ የሆነው የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሐፊው ሸብናህ እና ታሪክ ጸሐፊው የአሳፍ ልጅ ዮአህ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፤ ራብሻቁ ያለውንም ነገሩት።
ንጉሡም መልእክት ላከ፤ እነሱም የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠሩ።
ከዚያ በኋላ ንጉሡ ከይሁዳ ሰዎች፣ ከኢየሩሳሌም ነዋሪዎች፣ ከካህናቱ፣ ከነቢያቱ እንዲሁም ትልቅ ትንሽ ሳይባል ከሕዝቡ ሁሉ ጋር ወደ ይሖዋ ቤት ወጣ። እሱም በይሖዋ ቤት የተገኘውን የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ የተሰበሰቡት ሰዎች እየሰሙ አነበበላቸው።
ንጉሡ ዓምዱ አጠገብ ቆሞ በዚህ መጽሐፍ ላይ የሰፈሩትን የዚህን ቃል ኪዳን ቃላት በመፈጸም በሙሉ ልቡና በሙሉ ነፍሱ ይሖዋን ለመከተል እንዲሁም ትእዛዛቱን፣ ማሳሰቢያዎቹንና ደንቦቹን ለመጠበቅ በይሖዋ ፊት ቃል ኪዳን ገባ። ሕዝቡም ሁሉ በቃል ኪዳኑ ተስማማ።
ከዚያም ንጉሡ ሊቀ ካህናቱን ኬልቅያስን፣ በሁለተኛ ማዕረግ ያሉትን ካህናትና በር ጠባቂዎቹን ለባአል፣ ለማምለኪያ ግንዱና ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ የተሠሩትን ዕቃዎች በሙሉ ከይሖዋ ቤተ መቅደስ እንዲያወጡ አዘዛቸው። ከዚያም ከኢየሩሳሌም ውጭ በቄድሮን ተዳፋት ላይ አቃጠላቸው፤ አመዱንም ወደ ቤቴል ወሰደው።
የይሁዳ ነገሥታት በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም ዙሪያ በነበሩት ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች ላይ የሚጨስ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ የሾሟቸውን የባዕድ አምላክ ካህናት አባረረ፤ በተጨማሪም ለባአል፣ ለፀሐይ፣ ለጨረቃ፣ ዞዲያክ ለተባለው ኅብረ ከዋክብትና ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርቡ የነበሩትን በሙሉ አባረረ።
የማምለኪያ ግንዱን ከይሖዋ ቤት አውጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም ዳርቻ ወደ ቄድሮን ሸለቆ በመውሰድ በዚያ አቃጠለው፤ አድቅቆም አመድ አደረገው፤ አመዱንም በሕዝቡ መቃብር ላይ በተነው።
እንዲሁም በይሖዋ ቤት ውስጥ የነበሩትንና ሴቶች ለማምለኪያ ግንዱ ቤተ መቅደስ የሚሆኑ ድንኳኖችን ይሸምኑባቸው የነበሩትን የቤተ መቅደስ ቀላጮች ቤቶች አፈራረሰ።
ከዚያም ካህናቱን ሁሉ ከይሁዳ ከተሞች አስወጣ፤ እንዲሁም ካህናቱ የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርቡባቸው የነበሩትን ከጌባ አንስቶ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ የሚገኙትን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች አረከሰ። በተጨማሪም የከተማዋ አለቃ በሆነው በኢያሱ መግቢያ በር ላይ ይኸውም አንድ ሰው በከተማዋ በር ሲገባ በስተ ግራ በኩል በሚያገኘው በር ላይ የነበሩትን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች አፈራረሰ።
ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች ካህናት፣ በኢየሩሳሌም በሚገኘው የይሖዋ መሠዊያ አያገልግሉ እንጂ ከወንድሞቻቸው ጋር ቂጣ ይበሉ ነበር።
እሱም በሂኖም ልጆች ሸለቆ ውስጥ የነበረውን ቶፌትን አረከሰ፤ ይህን ያደረገው ማንም ሰው በዚያ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን ለሞሎክ በእሳት አሳልፎ እንዳይሰጥ ነው።
ደግሞም የይሁዳ ነገሥታት ለፀሐይ የሰጧቸው ፈረሶች የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን በሆነው በናታንሜሌክ ክፍል ይኸውም በመተላለፊያዎቹ መሃል ባለው ክፍል በኩል አድርገው ወደ ይሖዋ ቤት እንዳይገቡ ከለከለ፤ የፀሐይንም ሠረገሎች በእሳት አቃጠለ።
እንዲሁም ንጉሡ የይሁዳ ነገሥታት በአካዝ ሰገነት ጣሪያ ላይ የሠሯቸውን መሠዊያዎችና ምናሴ በይሖዋ ቤት ሁለት ግቢዎች ውስጥ የሠራቸውን መሠዊያዎች አፈራረሰ። ከዚያም አደቀቃቸው፤ የደቀቀውንም በቄድሮን ሸለቆ ውስጥ በተነው።
በተጨማሪም ንጉሡ፣ የእስራኤል ንጉሥ ሰለሞን ለሲዶናውያን አስጸያፊ የሴት አምላክ ለአስታሮት፣ ለሞዓባውያን አስጸያፊ አምላክ ለከሞሽ እንዲሁም ለአሞናውያን አስጸያፊ አምላክ ለሚልኮም የሠራቸውን በኢየሩሳሌም ፊት ለፊት ከጥፋት ተራራ በስተ ደቡብ የነበሩትን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች አረከሰ።
የማምለኪያ ዓምዶቹን ሰባበረ፤ የማምለኪያ ግንዶቹንም ቆራረጠ፤ ቦታውንም በሰው አፅም ሞላው።
በቤቴል የነበረውንም መሠዊያ ይኸውም እስራኤላውያን ኃጢአት እንዲሠሩ ያደረገው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም የሠራውን ከፍ ያለ የማምለኪያ ቦታ አፈረሰ። ያን መሠዊያና ከፍ ያለ የማምለኪያ ቦታ ካፈረሰ በኋላ ቦታውን አቃጠለው፤ ፈጭቶም አመድ አደረገው፤ የማምለኪያ ግንዱንም አቃጠለ።
ኢዮስያስ ዞር ብሎ በተራራው ላይ ያሉትን መቃብሮች ባየ ጊዜ አፅሞቹን ከመቃብሮቹ ውስጥ አስወጥቶ በመሠዊያው ላይ በማቃጠል እነዚህ ነገሮች እንደሚሆኑ አስቀድሞ የተናገረው የእውነተኛው አምላክ ሰው ባወጀው የይሖዋ ቃል መሠረት መሠዊያውን አረከሰ።
ከዚያም “እዚያ ጋ የማየው የመቃብር ሐውልት የማን ነው?” አለ። በዚህ ጊዜ የከተማዋ ሰዎች “ከይሁዳ የመጣውና በቤቴል በሚገኘው መሠዊያ ላይ አንተ ያደረግካቸውን እነዚህን ነገሮች አስቀድሞ የተናገረው የእውነተኛው አምላክ ሰው መቃብር ነው” አሉት።
እሱም “በሉ ይረፍ ተዉት። ማንም ሰው አፅሙን አይረብሸው” አለ። በመሆኑም የእሱንም ሆነ ከሰማርያ የመጣውን ነቢይ አፅም ሳይነኩ ተዉት።
በተጨማሪም ኢዮስያስ የእስራኤል ነገሥታት አምላክን ለማስቆጣት በሰማርያ ከተሞች ውስጥ የሠሯቸውን ከፍ ባሉ የማምለኪያ ቦታዎች ላይ የሚገኙ የአምልኮ ቤቶች በሙሉ አስወገደ፤ በቤቴል ያደረገውንም ሁሉ በእነሱ ላይ አደረገ።
በዚህም መሠረት በዚያ የነበሩትን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች ካህናት በሙሉ በመሠዊያዎቹ ላይ ሠዋ፤ በላያቸውም ላይ የሰው አፅም አቃጠለ። ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
ንጉሡም ሕዝቡን ሁሉ “በዚህ የቃል ኪዳን መጽሐፍ ላይ በተጻፈው መሠረት ለአምላካችሁ ለይሖዋ ፋሲካን አክብሩ” ሲል አዘዘ።
መሳፍንት እስራኤልን ያስተዳድሩ በነበረበት ዘመንም ሆነ በእስራኤል ነገሥታትና በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ሁሉ እንዲህ ያለ ፋሲካ ተከብሮ አያውቅም።
ንጉሥ ኢዮስያስ በነገሠ በ18ኛው ዓመት ግን ይህ ፋሲካ በኢየሩሳሌም ለይሖዋ ተከበረ።
በተጨማሪም ኢዮስያስ ካህኑ ኬልቅያስ በይሖዋ ቤት ውስጥ ባገኘው መጽሐፍ ላይ የተጻፈውን የሕጉን ቃል ይፈጽም ዘንድ መናፍስት ጠሪዎችን፣ ጠንቋዮችን፣ የተራፊም ቅርጻ ቅርጾችን፣ አስጸያፊ የሆኑ ጣዖቶችን እንዲሁም በይሁዳ ምድርና በኢየሩሳሌም የነበሩ አስጸያፊ ነገሮችን በሙሉ አስወገደ።
በሙሴ ሕግ መሠረት በሙሉ ልቡ፣ በሙሉ ነፍሱና በሙሉ ኃይሉ ወደ ይሖዋ የተመለሰ እንደ እሱ ያለ ንጉሥ ከእሱ በፊት አልነበረም፤ ከእሱ በኋላም እንደ እሱ ያለ ንጉሥ አልተነሳም።
ይሁንና ይሖዋ፣ ምናሴ እሱን ያስቆጣው ዘንድ በፈጸማቸው አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ የተነሳ በይሁዳ ላይ ከነደደው ቁጣው አልተመለሰም ነበር።
ይሖዋ “እስራኤልን እንዳስወገድኩ ሁሉ ይሁዳንም ከፊቴ አስወግዳለሁ፤ የመረጥኳትን ይህችን ከተማ ኢየሩሳሌምን እንዲሁም ‘ስሜ በዚያ ይኖራል’ ብዬ የተናገርኩለትን ቤት እተዋለሁ” አለ።
የቀረው የኢዮስያስ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?
በእሱ ዘመን የግብፁ ንጉሥ ፈርዖን ኒካዑ ከአሦር ንጉሥ ጋር ለመገናኘት በኤፍራጥስ ወንዝ በኩል መጣ፤ ንጉሥ ኢዮስያስም ሊገጥመው ወጣ፤ ኒካዑም ባየው ጊዜ መጊዶ ላይ ገደለው።
በመሆኑም አገልጋዮቹ አስከሬኑን በሠረገላ ከመጊዶ ወደ ኢየሩሳሌም በማምጣት በራሱ መቃብር ውስጥ ቀበሩት። ከዚያም የምድሪቱ ሕዝብ የኢዮስያስን ልጅ ኢዮዓካዝን ቀብተው በአባቱ ምትክ አነገሡት።
ኢዮዓካዝ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 23 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለሦስት ወር ገዛ። እናቱ ሀሙጣል ትባል ነበር፤ እሷም የሊብና ሰው የሆነው የኤርምያስ ልጅ ነበረች።
አባቶቹ እንዳደረጉት ሁሉ እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።
ፈርዖን ኒካዑ፣ ኢዮዓካዝ በኢየሩሳሌም ሆኖ እንዳይገዛ በሃማት ምድር በምትገኘው በሪብላ አሰረው፤ በምድሪቱም ላይ 100 የብር ታላንትና አንድ የወርቅ ታላንት ቅጣት ጣለ።
በተጨማሪም ፈርዖን ኒካዑ የኢዮስያስን ልጅ ኤልያቄምን በአባቱ በኢዮስያስ ምትክ አነገሠው፤ ስሙንም ቀይሮ ኢዮዓቄም አለው፤ ኢዮዓካዝን ግን ወደ ግብፅ ወሰደው፤ እሱም በመጨረሻ በዚያ ሞተ።
ኢዮዓቄም ብሩንና ወርቁን ለፈርዖን ሰጠው፤ ይሁንና ፈርዖን የጠየቀውን ብር ለመስጠት በምድሪቱ ላይ ቀረጥ መጣል አስፈልጎት ነበር። እሱም እያንዳንዱ የምድሪቱ ነዋሪ ለፈርዖን ኒካዑ እንዲሰጥ ተገምቶ በተጣለበት ቀረጥ መሠረት ብርና ወርቅ እንዲከፍል አደረገ።
ኢዮዓቄም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ11 ዓመት ገዛ። እናቱ ዘቢዳ ትባል ነበር፤ እሷም የሩማ ሰው የሆነው የፐዳያህ ልጅ ነበረች።
አባቶቹ እንዳደረጉት ሁሉ እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።
የነቢያት ልጆች ኤልሳዕን እንዲህ አሉት፦ “ይኸው እንደምታየው አብረንህ የምንኖርበት ስፍራ በጣም ጠቦናል።
እባክህ ወደ ዮርዳኖስ እንሂድ። እያንዳንዳችን ከዚያ እንጨት እንቁረጥ፤ በዚያም የምንቀመጥበት መኖሪያ እንሥራ።” እሱም “እሺ ሂዱ” አላቸው።
ከመካከላቸው አንዱ “አንተስ ከአገልጋዮችህ ጋር ለመሄድ ፈቃደኛ ነህ?” አለው። እሱም “እሺ እሄዳለሁ” አለ።
ስለዚህ አብሯቸው ሄደ፤ ወደ ዮርዳኖስም መጥተው ዛፍ መቁረጥ ጀመሩ።
ከእነሱ አንዱ ዛፍ እየቆረጠ ሳለ የመጥረቢያው አናት ወልቆ ውኃው ውስጥ ወደቀ። ሰውየውም “ወየው ጌታዬ፣ ተውሼ ያመጣሁት መጥረቢያ እኮ ነው!” በማለት ጮኸ።
የእውነተኛው አምላክ ሰውም “የት ነው የወደቀው?” አለው። ሰውየውም ቦታውን አሳየው። እሱም እንጨት ቆርጦ ውኃው ውስጥ በመጣል የመጥረቢያው አናት እንዲንሳፈፍ አደረገ።
ከዚያም “በል አውጣው” አለው። ሰውየውም እጁን ዘርግቶ ወሰደው።
በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ እስራኤልን ለመውጋት ዘምቶ ነበር። ከአገልጋዮቹ ጋር ከተማከረ በኋላ “እዚህ እዚህ ቦታ አብሬያችሁ እሰፍራለሁ” አለ።
ከዚያም የእውነተኛው አምላክ ሰው “ሶርያውያን በዚህ እየወረዱ ስለሆነ በዚህ በኩል እንዳታልፍ ተጠንቀቅ” በማለት ወደ እስራኤል ንጉሥ መልእክት ላከ።
የእስራኤልም ንጉሥ፣ የእውነተኛው አምላክ ሰው እንዳይሄድ ወዳስጠነቀቀው ስፍራ መልእክት ላከ። በዚህ መንገድ ኤልሳዕ ንጉሡን በተደጋጋሚ ጊዜ ያስጠነቅቀው የነበረ ሲሆን ንጉሡም ከዚያ አካባቢ ይርቅ ነበር።
ይህ ጉዳይ የሶርያን ንጉሥ እጅግ አበሳጨው፤ በመሆኑም አገልጋዮቹን ጠርቶ “ከመካከላችን ከእስራኤል ንጉሥ ጋር የወገነ ካለ ንገሩኝ!” አላቸው።
ከዚያም ከአገልጋዮቹ መካከል አንዱ “ንጉሡ ጌታዬ ሆይ፣ ኧረ ማንም የለም! አንተ መኝታ ቤትህ ውስጥ ሆነህ የምትናገረውን ነገር ለእስራኤል ንጉሥ የሚነግረው በእስራኤል ያለው ነቢዩ ኤልሳዕ ነው” አለው።
ንጉሡም “በሉ ሰዎች ልኬ እንዳስይዘው ሄዳችሁ የት እንደሚገኝ አጣሩ” አላቸው። በኋላም “ዶታን ነው ያለው” የሚል ወሬ ደረሰው።
እሱም ወዲያውኑ ፈረሶችን፣ የጦር ሠረገሎችንና ብዙ ሠራዊት ወደዚያ ላከ፤ እነሱም በሌሊት መጥተው ከተማዋን ከበቡ።
የእውነተኛው አምላክ ሰው አገልጋይ በማለዳ ተነስቶ ወደ ውጭ ሲወጣ በፈረሶችና በጦር ሠረገሎች የተጠናከረ ሠራዊት ከተማዋን መክበቡን አየ። አገልጋዩም ወዲያውኑ “ወየው ጌታዬ! ምን ብናደርግ ይሻላል?” አለ።
ኤልሳዕ ግን “አይዞህ፣ አትፍራ! ከእነሱ ጋር ካሉት ከእኛ ጋር ያሉት ይበልጣሉ” አለው።
ከዚያም ኤልሳዕ “ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ ያይ ዘንድ ዓይኖቹን ክፈትለት” በማለት ጸለየ። ይሖዋም ወዲያውኑ የአገልጋዩን ዓይኖች ከፈተ፤ እሱም አየ፤ እነሆ የእሳት ፈረሶችና የጦር ሠረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ ተራራማውን አካባቢ ሞልተውት ነበር።
ሶርያውያኑ ወደ ኤልሳዕ መውረድ ሲጀምሩ ኤልሳዕ “እባክህ፣ ይህን ሕዝብ አሳውረው” በማለት ወደ ይሖዋ ጸለየ። እሱም ኤልሳዕ በጠየቀው መሠረት አሳወራቸው።
ኤልሳዕም “መንገዱ ይሄ አይደለም፤ ከተማዋም ይህች አይደለችም። ወደምትፈልጉት ሰው መርቼ እንዳደርሳችሁ እኔን ተከተሉኝ” አላቸው። ይሁን እንጂ ኤልሳዕ የወሰዳቸው ወደ ሰማርያ ነበር።
እነሱም ሰማርያ ሲደርሱ ኤልሳዕ “ይሖዋ ሆይ፣ እንዲያዩ ዓይኖቻቸውን ክፈት” አለ። ስለዚህ ይሖዋ ዓይኖቻቸውን ከፈተላቸው፤ እነሱም ሰማርያ ውስጥ መሆናቸውን አዩ።
የእስራኤል ንጉሥ ባያቸው ጊዜ ኤልሳዕን “አባቴ ሆይ፣ ልግደላቸው? ልፍጃቸው?” አለው።
እሱ ግን እንዲህ አለው፦ “አትግደላቸው። ለመሆኑ በሰይፍህ ወይም በቀስትህ ማርከህ የወሰድካቸውን ሰዎች ትገድላለህ? በል አሁን እንዲበሉና እንዲጠጡ ምግብና ውኃ ስጣቸው፤ ከዚያም ወደ ጌታቸው ይመለሱ።”