text stringlengths 4 267 |
|---|
የካህናቱ አለቃ አዛርያስና ካህናቱ ሁሉ ባዩት ጊዜ ግንባሩ በሥጋ ደዌ ተመቶ ነበር! በመሆኑም ከዚያ አጣድፈው አስወጡት፤ እሱ ራሱም ይሖዋ ስለመታው ለመውጣት ቸኩሎ ነበር። |
ንጉሥ ዖዝያ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የሥጋ ደዌ በሽተኛ ሆኖ ኖረ፤ የሥጋ ደዌ በሽተኛ በመሆኑ በአንድ የተለየ ቤት ውስጥ ተገልሎ ተቀመጠ፤ ወደ ይሖዋ ቤት እንዳይገባ ታግዶ ነበር። ልጁ ኢዮዓታም በንጉሡ ቤት ላይ ተሹሞ በምድሪቱ በሚኖረው ሕዝብ ላይ ይፈርድ ነበር። |
ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለውን የቀረውን የዖዝያ ታሪክ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ጽፎታል። |
በመጨረሻም ዖዝያ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ከአባቶቹም ጋር ቀበሩት፤ ሆኖም “የሥጋ ደዌ አለበት” ብለው ስላሰቡ የቀበሩት ከነገሥታቱ የመቃብር ቦታ ውጭ ባለ መሬት ላይ ነበር። በእሱም ምትክ ልጁ ኢዮዓታም ነገሠ። |
የዳዊት ልጅ ሰለሞን ንግሥናውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠናከረ ሄደ፤ አምላኩ ይሖዋም ከእሱ ጋር ስለነበር እጅግ ገናና አደረገው። |
ሰለሞን ለእስራኤል ሁሉ፣ ለሺህ አለቆች፣ ለመቶ አለቆች፣ ለፈራጆችና የአባቶች ቤቶች መሪዎች ለሆኑት በመላው እስራኤል ለሚገኙት አለቆች ሁሉ መልእክት ላከ። |
ከዚያም ሰለሞንና መላው ጉባኤ በገባኦን ወደሚገኘው ኮረብታ ሄዱ፤ ምክንያቱም የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የእውነተኛው አምላክ የመገናኛ ድንኳን የሚገኘው በዚያ ነበር። |
ይሁን እንጂ ዳዊት የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ከቂርያትየአሪም እሱ ወዳዘጋጀለት ስፍራ አምጥቶት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ድንኳን ተክሎለት ነበር። |
የሁር ልጅ የዖሪ ልጅ ባስልኤል የሠራው የመዳብ መሠዊያ በይሖዋ የማደሪያ ድንኳን ፊት ይገኝ ነበር፤ ሰለሞንና ጉባኤውም በመሠዊያው ፊት ይጸልዩ ነበር። |
ሰለሞንም በዚያ በይሖዋ ፊት መባ አቀረበ፤ በመገናኛው ድንኳን በሚገኘው የመዳብ መሠዊያ ላይ 1,000 የሚቃጠሉ መባዎችን አቀረበ። |
በዚያ ሌሊት አምላክ ለሰለሞን ተገልጦ “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ጠይቅ” አለው። |
በዚህ ጊዜ ሰለሞን አምላክን እንዲህ አለው፦ “ለአባቴ ለዳዊት ጥልቅ የሆነ ታማኝ ፍቅር አሳይተኸዋል፤ በእሱም ምትክ አንግሠኸኛል። |
አሁንም ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸው ቃል ይፈጸም፤ እንደ ምድር አፈር እጅግ ብዙ በሆነ ሕዝብ ላይ አንግሠኸኛልና። |
ይህን ሕዝብ መምራት እንድችል ጥበብና እውቀት ስጠኝ፤ አለዚያማ ይህን ታላቅ ሕዝብህን ማን ሊዳኝ ይችላል?” |
ከዚያም አምላክ ሰለሞንን እንዲህ አለው፦ “የልብህ መሻት ይህ ስለሆነ ደግሞም ብልጽግና፣ ሀብትና ክብር ወይም የሚጠሉህን ሰዎች ሞት አሊያም ረጅም ዕድሜ ስላልተመኘህ፣ ይልቁንም አንተን ንጉሥ አድርጌ የሾምኩበትን ሕዝቤን ማስተዳደር እንድትችል ጥበብና እውቀት ስለጠየቅክ፣ |
ጥበብና እውቀት ይሰጥሃል፤ ከዚህም ሌላ ከአንተ በፊት የነበረ ማንኛውም ንጉሥ ያላገኘውን፣ ከአንተም በኋላ የሚነሳ የትኛውም ንጉሥ የማያገኘውን ብልጽግና፣ ሀብትና ክብር እሰጥሃለሁ።” |
ሰለሞንም በገባኦን ኮረብታ ከሚገኘው ከመገናኛው ድንኳን ፊት ወጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ በእስራኤልም ላይ ነገሠ። |
ሰለሞን ሠረገሎችንና ፈረሶችን መሰብሰቡን ቀጠለ፤ እሱም 1,400 ሠረገሎችና 12,000 ፈረሶች ነበሩት፤ እነሱንም በሠረገላ ከተሞችና በኢየሩሳሌም በንጉሡ አቅራቢያ አኖራቸው። |
ንጉሡ ብርና ወርቅ በየቦታው እንደሚገኝ ድንጋይ እስኪሆን ድረስ በኢየሩሳሌም እንዲበዛ አደረገ፤ አርዘ ሊባኖሱንም ከብዛቱ የተነሳ በሸፌላ እንደሚገኘው የሾላ ዛፍ አደረገው። |
የሰለሞን ፈረሶች ከግብፅ ያስመጣቸው ነበሩ፤ የንጉሡ ነጋዴዎችም የፈረሶቹን መንጋ አንዴ በተተመነው ዋጋ ይገዙ ነበር። |
ከግብፅ የሚመጣው እያንዳንዱ ሠረገላ 600 የብር ሰቅል ያወጣ ነበር፤ አንድ ፈረስ ደግሞ 150 ሰቅል ያወጣል፤ እነሱ ደግሞ በተራቸው ለሂታውያን ነገሥታትና ለሶርያ ነገሥታት ሁሉ ሠረገሎችንና ፈረሶችን ይሸጡ ነበር። |
ከዚያም የምድሪቱ ሕዝብ የኢዮስያስን ልጅ ኢዮዓካዝን በአባቱ ምትክ በኢየሩሳሌም አነገሡት። |
ኢዮዓካዝ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 23 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለሦስት ወር ገዛ። |
ይሁን እንጂ የግብፅ ንጉሥ በኢየሩሳሌም ካለው ዙፋኑ አወረደው፤ በምድሪቱም ላይ 100 የብር ታላንትና አንድ የወርቅ ታላንት ቅጣት ጣለ። |
በተጨማሪም የግብፁ ንጉሥ ኒካዑ የኢዮዓካዝን ወንድም ኤልያቄምን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠው፤ ስሙንም ቀይሮ ኢዮዓቄም አለው፤ ወንድሙን ኢዮዓካዝን ግን ወደ ግብፅ ወሰደው። |
ኢዮዓቄም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ11 ዓመት ገዛ። እሱም በአምላኩ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። |
የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር ከመዳብ በተሠሩ ሁለት የእግር ብረቶች አስሮ ወደ ባቢሎን ለመውሰድ በእሱ ላይ ዘመተ። |
ናቡከደነጾርም በይሖዋ ቤት ያሉ የተወሰኑ ዕቃዎችን ወደ ባቢሎን ወስዶ በባቢሎን በሚገኘው ቤተ መንግሥቱ አስቀመጣቸው። |
የቀረው የኢዮአቄም ታሪክ፣ የፈጸማቸው አስጸያፊ ነገሮችና በእሱ ላይ የተገኘበት መጥፎ ነገር በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል፤ በእሱም ምትክ ልጁ ዮአኪን ነገሠ። |
ዮአኪን በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 18 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለሦስት ወር ከአሥር ቀን ገዛ፤ እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። |
በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ንጉሥ ናቡከደነጾር አገልጋዮቹን ልኮ በይሖዋ ቤት ካሉት ውድ ዕቃዎች ጋር ወደ ባቢሎን አመጣው። የአባቱን ወንድም ሴዴቅያስንም በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠው። |
ሴዴቅያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 21 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ11 ዓመት ገዛ። |
በአምላኩ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። በይሖዋ ትእዛዝ በተናገረው በነቢዩ ኤርምያስ ፊት ራሱን ዝቅ አላደረገም። |
ደግሞም በአምላክ ስም ባስማለው በንጉሥ ናቡከደነጾር ላይ ዓመፀ፤ ግትር ሆነ፤ ልቡንም አጠነከረ፤ ወደ እስራኤል አምላክ ወደ ይሖዋ ለመመለስ አሻፈረኝ አለ። |
ዋነኞቹ ካህናት ሁሉና ሕዝቡ፣ ብሔራት የሚፈጽሟቸውን አስጸያፊ ነገሮች በማድረግ እጅግ ከፍተኛ ክህደት ፈጸሙ፤ ይሖዋ በኢየሩሳሌም የቀደሰውንም ቤት አረከሱ። |
የአባቶቻቸው አምላክ ይሖዋ ለሕዝቡና ለማደሪያው ስፍራ ስለራራ መልእክተኞቹን እየላከ በተደጋጋሚ ያስጠነቅቃቸው ነበር። |
እነሱ ግን የይሖዋ ቁጣ በሕዝቡ ላይ እስኪነድና ፈውስ እስከማይገኝላቸው ድረስ በእውነተኛው አምላክ መልእክተኞች ላይ ያላግጡ፣ ቃሉን ይንቁና በነቢያቱ ላይ ያፌዙ ነበር። |
ስለዚህ የከለዳውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እሱም ወጣቶቻቸውን በቤተ መቅደሳቸው ውስጥ በሰይፍ ገደለ፤ ለወጣቱም ሆነ ለድንግሊቱ፣ ለሽማግሌውም ሆነ ለአቅመ ደካማው አልራራም። አምላክ ሁሉንም በእጁ አሳልፎ ሰጠው። |
በእውነተኛው አምላክ ቤት የነበሩትን ትላልቅም ሆኑ ትናንሽ ዕቃዎች በሙሉ፣ የይሖዋን ቤት ውድ ሀብት እንዲሁም የንጉሡንና የመኳንንቱን ውድ ሀብት ሁሉ ወደ ባቢሎን አጋዘ። |
የእውነተኛውን አምላክ ቤት አቃጠለ፤ የኢየሩሳሌምን ቅጥር አፈረሰ፤ የማይደፈሩ ማማዎቿን ሁሉ በእሳት አቃጠለ፤ እንዲሁም ውድ የሆኑትን ዕቃዎች በሙሉ አወደመ። |
ከሰይፍ የተረፉትንም ሁሉ ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፤ እነሱም የፋርስ መንግሥት መግዛት እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ የእሱና የወንዶች ልጆቹ አገልጋዮች ሆኑ፤ |
ይህም የሆነው ይሖዋ በኤርምያስ በኩል የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ ምድሪቱ የሰንበት ዕዳዋን እስክትከፍል ድረስ ነው። ፈራርሳ በቆየችባቸው ጊዜያት ሁሉ፣ 70 ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ሰንበትን አከበረች። |
በኤርምያስ በኩል የተነገረው የይሖዋ ቃል ይፈጸም ዘንድ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት የሚከተለውን አዋጅ በመላ ግዛቱ እንዲያውጅ ይሖዋ የፋርሱን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አነሳሳ፤ እሱም ይህ በጽሑፍ እንዲሰፍር አደረገ፦ |
“የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፦ ‘የሰማይ አምላክ ይሖዋ የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳ በምትገኘው በኢየሩሳሌምም ቤት እንድሠራለት አዞኛል። ከእሱ ሕዝብ መካከል የሆነ አብሯችሁ የሚኖር ማንኛውም ሰው አምላኩ ይሖዋ ከእሱ ጋር ይሁን፤ እሱም ወደዚያ ይውጣ።’” |
ሰለሞንም ጸሎቱን እንደጨረሰ እሳት ከሰማያት ወርዶ የሚቃጠለውን መባና መሥዋዕቶቹን በላ፤ የይሖዋም ክብር ቤቱን ሞላው። |
የይሖዋ ክብር የይሖዋን ቤት ሞልቶት ስለነበር ካህናቱ ወደ ይሖዋ ቤት መግባት አልቻሉም። |
የእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ እሳቱ ሲወርድና የይሖዋ ክብር ከቤቱ በላይ ሲሆን ይመለከቱ ነበር፤ ወደ መሬት አጎንብሰው ድንጋይ በተነጠፈበት ወለል ላይ በግንባራቸው ተደፍተው ሰገዱ፤ ደግሞም “እሱ ጥሩ ነውና፤ ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” እያሉ ይሖዋን አመሰገኑ። |
ከዚያም ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ በይሖዋ ፊት መሥዋዕት አቀረቡ። |
ንጉሥ ሰለሞን 22,000 ከብቶችና 120,000 በጎች መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። በዚህ መንገድ ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ የእውነተኛውን አምላክ ቤት መረቁ። |
ካህናቱም ሆኑ የይሖዋን መዝሙር ለማጀብ የሚያገለግሉ የሙዚቃ መሣሪያዎችን የያዙት ሌዋውያን እንዲያገለግሉ በተመደቡበት ስፍራ ቆመው ነበር። (ንጉሥ ዳዊት እነዚህን መሣሪያዎች የሠራው ከእነሱ ጋር ሆኖ ውዳሴ በሚያቀርብበት ጊዜ “ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና” በማለት ይሖዋን ለማመስገን ነው።) ካህናቱ በእነሱ ትይዩ ሆነው መለከቶቹን በኃይል ይነፉ ነበር፤ በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ሁሉ በዚያ ቆመው ነበር። |
ከዚያም ሰለሞን በይሖዋ ቤት ፊት የሚገኘውን የግቢውን መሃል ቀደሰው፤ ምክንያቱም ሰለሞን የሚቃጠለውን መባና የኅብረት መሥዋዕቱን ስብ በዚያ ማቅረብ ነበረበት፤ ይህም የሆነው ሰለሞን የሠራው የመዳብ መሠዊያ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ የእህሉን መባና ስቡን መያዝ ስላልቻለ ነው። |
በዚያን ጊዜ ሰለሞን ከመላው እስራኤል ጋር ይኸውም ከሌቦሃማት አንስቶ እስከ ግብፅ ደረቅ ወንዝ ድረስ ካለው ምድር ከመጣው ታላቅ ጉባኤ ጋር በመሆን ለሰባት ቀን በዓሉን አከበረ። |
ይሁንና የመሠዊያውን የምረቃ ሥነ ሥርዓት ለሰባት ቀን ስላከናወኑና በዓሉን ለሰባት ቀን ስላከበሩ በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አደረጉ። |
ከዚያም በሰባተኛው ወር፣ በ23ኛው ቀን ሕዝቡን ወደየቤታቸው አሰናበተ፤ እነሱም ይሖዋ ለዳዊት፣ ለሰለሞንና ለሕዝቡ ለእስራኤል ባሳየው ጥሩነት እየተደሰቱና ከልባቸው እየፈነደቁ ሄዱ። |
ሰለሞንም የይሖዋን ቤትና የንጉሡን ቤት ሠርቶ ጨረሰ፤ ከይሖዋ ቤትና ከራሱ ቤት ጋር በተያያዘ በልቡ ያሰበውን ሁሉ በተሳካ ሁኔታ አከናወነ። |
ከዚያም ይሖዋ በሌሊት ለሰለሞን ተገልጦለት እንዲህ አለው፦ “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ ይህን ቦታ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቤት እንዲሆን ለራሴ መርጬዋለሁ። |
ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማያትን ብዘጋ፣ ምድሪቱን እንዲበሉ አንበጦችን ብልክ፣ በሕዝቤ መካከል ቸነፈር ብሰድ፣ |
በስሜ የተጠሩትም ሕዝቤ ራሳቸውን ዝቅ ቢያደርጉ፣ ቢጸልዩ፣ ፊቴን ቢሹና ከክፉ መንገዳቸው ቢመለሱ፣ ከሰማያት ሆኜ እሰማለሁ፤ ኃጢአታቸውን ይቅር እላለሁ፤ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ። |
በዚህም ስፍራ ለሚቀርበው ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ፤ ጆሮዎቼም ይከፈታሉ። |
አሁንም ስሜ ለዘለቄታው በዚያ እንዲጠራ ይህን ቤት መርጬዋለሁ፤ ደግሞም ቀድሼዋለሁ፤ ዓይኔም ሆነ ልቤ ሁልጊዜ በዚያ ይሆናል። |
“አንተም አባትህ ዳዊት እንዳደረገው ያዘዝኩህን ሁሉ በመፈጸም በፊቴ ብትሄድ እንዲሁም ሥርዓቶቼንና ድንጋጌዎቼን ብትጠብቅ፣ |
ለአባትህ ለዳዊት ‘ከዘር ሐረግህ በእስራኤል ላይ ገዢ የሚሆን አይታጣም’ በማለት በገባሁለት ቃል ኪዳን መሠረት የንግሥና ዙፋንህን አጸናለሁ። |
ሆኖም ጀርባችሁን ብትሰጡ፣ በፊታችሁ ያስቀመጥኳቸውን ደንቦቼንና ትእዛዛቴን ብትተዉ፣ ሄዳችሁም ሌሎች አማልክትን ብታገለግሉና ለእነሱ ብትሰግዱ፣ |
እስራኤልን ከሰጠሁት ምድሬ ላይ እነቅለዋለሁ፤ ለስሜ የቀደስኩትንም ይህን ቤት ከፊቴ አስወግደዋለሁ፤ በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ መቀለጃና መሳለቂያ አደርገዋለሁ። |
ይህም ቤት የፍርስራሽ ክምር ይሆናል። በዚያም የሚያልፉ ሰዎች ሁሉ በመገረም ትኩር ብለው እየተመለከቱ ‘ይሖዋ በዚህች ምድርና በዚህ ቤት ላይ እንዲህ ያለ ነገር ያደረገው ለምንድን ነው?’ በማለት ይጠይቃሉ። |
ከዚያም እንዲህ ይላሉ፦ ‘ይህ የደረሰባቸው ከግብፅ ምድር ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ ይሖዋን ትተው ሌሎች አማልክትን ስለተከተሉና ለእነሱ ስለሰገዱ እንዲሁም እነሱን ስላገለገሉ ነው። ይህን ሁሉ መከራ ያመጣባቸው ለዚህ ነው።’” |
አሜስያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ29 ዓመት ገዛ። እናቱ ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ተወላጅ ነበረች። |
እሱም በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ፤ ሆኖም በሙሉ ልቡ አልነበረም። |
መንግሥቱ በእጁ እንደጸናለትም ንጉሥ የነበረውን አባቱን የገደሉትን አገልጋዮቹን ገደላቸው። |
ይሁንና “አባቶች በልጆቻቸው ኃጢአት መገደል የለባቸውም፤ ልጆችም በአባቶቻቸው ኃጢአት መገደል የለባቸውም፤ ይልቁንም እያንዳንዱ ሰው በገዛ ኃጢአቱ ይገደል” በሚለው በሙሴ የሕግ መጽሐፍ ላይ በተጻፈው የይሖዋ ትእዛዝ መሠረት የገዳዮቹን ልጆች አልገደላቸውም። |
አሜስያስም የይሁዳን ሰዎች ሰብስቦ በየአባቶቻቸው ቤት፣ በሺህ አለቆችና በመቶ አለቆች በመደልደል መላውን ይሁዳና ቢንያም ወክለው እንዲቆሙ አደረገ። ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸውን መዘገበ፤ በጦርና በትልቅ ጋሻ መጠቀምና በሠራዊቱ ውስጥ ማገልገል የሚችሉ 300,000 የሠለጠኑ ተዋጊዎችን አገኘ። |
በተጨማሪም በ100 የብር ታላንት፣ 100,000 ኃያላን ተዋጊዎችን ከእስራኤል ቀጠረ። |
ይሁንና አንድ የእውነተኛው አምላክ ሰው ወደ እሱ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ንጉሥ ሆይ፣ ይሖዋ ከእስራኤል፣ ከኤፍሬማውያን ሁሉ ጋር ስላልሆነ የእስራኤል ሠራዊት ከአንተ ጋር እንዲዘምት አታድርግ። |
ይልቁንም ብቻህን ዝመት፤ ወደኋላ አትበል፤ በቆራጥነትም ተዋጋ። እንዲህ ባታደርግ ግን እውነተኛው አምላክ በጠላቶችህ ፊት ሊጥልህ ይችላል፤ አምላክ ለመርዳትም ሆነ ለመጣል ኃይል አለውና።” |
በዚህ ጊዜ አሜስያስ የእውነተኛውን አምላክ ሰው “ታዲያ ለእስራኤል ወታደሮች የሰጠሁት 100 ታላንት ምን ይሁን?” አለው። የእውነተኛውም አምላክ ሰው “ይሖዋ ከዚህ እጅግ የሚበልጥ ሊሰጥህ ይችላል” ሲል መለሰለት። |
በመሆኑም አሜስያስ ከኤፍሬም ወደ እሱ የመጡትን ወታደሮች ወደ ስፍራቸው እንዲመለሱ አሰናበታቸው። እነሱ ግን በይሁዳ እጅግ ተበሳጭተው በታላቅ ቁጣ ወደ ገዛ አገራቸው ተመለሱ። |
ከዚያም አሜስያስ ተበረታታ፤ የራሱንም ወታደሮች እየመራ ወደ ጨው ሸለቆ ሄደ፤ ደግሞም 10,000 የሚሆኑ የሴይር ሰዎችን ገደለ። |
የይሁዳም ሰዎች 10,000 የሚሆኑ ሰዎችን ማረኩ። ከዚያም ወደ ገደል አፋፍ ወስደው፣ ከአፋፉ ላይ ቁልቁል ወረወሯቸው፤ ሁሉም ተፈጥፍጠው ብትንትናቸው ወጣ። |
ይሁንና አሜስያስ ከእሱ ጋር ወደ ጦርነት እንዳይሄዱ ያሰናበታቸው ወታደሮች ከሰማርያ አንስቶ እስከ ቤትሆሮን ድረስ ያሉትን የይሁዳ ከተሞች ወረሩ፤ 3,000 ሰዎችም ገደሉ፤ ብዙ ምርኮም ወሰዱ። |
አሜስያስ ኤዶማውያንን መትቶ ከተመለሰ በኋላ የሴይርን ሰዎች አማልክት ይዞ በመምጣት ለራሱ አማልክት አድርጎ አቆማቸው፤ በእነሱም ፊት ይሰግድ እንዲሁም የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብላቸው ጀመር። |
ስለሆነም የይሖዋ ቁጣ በአሜስያስ ላይ ነደደ፤ ነቢይም ልኮ “የገዛ ሕዝባቸውን ከእጅህ መታደግ ያልቻሉትን የሕዝቡን አማልክት የምትከተለው ለምንድን ነው?” አለው። |
በዚህ ጊዜ ንጉሡ ነቢዩን “የንጉሡ አማካሪ አድርገን ሾመንሃል? ዝም በል! መሞት ትፈልጋለህ?” አለው። ነቢዩም ዝም አለ፤ ሆኖም “ይህን በማድረግህና ምክሬን ባለመስማትህ አምላክ ሊያጠፋህ እንደወሰነ ተረዳሁ” አለ። |
የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ ከአማካሪዎቹ ጋር ከተማከረ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ ወደሆነው ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ኢዮዓካዝ ልጅ ወደ ኢዮዓስ “ና! ውጊያ እንግጠም” የሚል መልእክት ላከበት። |
የእስራኤል ንጉሥ ኢዮዓስ ደግሞ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ ይህን መልእክት ላከ፦ “በሊባኖስ የሚገኘው ኩርንችት በሊባኖስ ወደሚገኘው አርዘ ሊባኖስ ‘ሴት ልጅህን ለወንድ ልጄ ዳርለት’ የሚል መልእክት ላከ። ይሁን እንጂ በሊባኖስ የነበረ አንድ የዱር አውሬ በዚያ ሲያልፍ ያን ኩርንችት ረገጠው። |
አንተ ‘እኔ ኤዶምን መትቻለሁ’ ብለሃል። በመሆኑም ልብህ ክብር በመሻት ታብዮአል። አሁን ግን አርፈህ ቤትህ ተቀመጥ። በራስህ ላይ ለምን ጥፋት ትጋብዛለህ? ደግሞስ ራስህንም ሆነ ይሁዳን ለምን ለውድቀት ትዳርጋለህ?” |
አሜስያስ ግን አልሰማም፤ የኤዶምን አማልክት በመከተላቸው እውነተኛው አምላክ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ሊሰጣቸው ወስኗልና። |
በመሆኑም የእስራኤል ንጉሥ ኢዮዓስ ወጣ፤ እሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ በምትገኘው በቤትሼሜሽ ተጋጠሙ። |
ይሁዳ በእስራኤል ድል ተመታ፤ እያንዳንዳቸውም ወደየቤታቸው ሸሹ። |
የእስራኤል ንጉሥ ኢዮዓስ የኢዮአካዝ ልጅ፣ የኢዮዓስ ልጅ የሆነውን የይሁዳን ንጉሥ አሜስያስን ቤትሼሜሽ ላይ ያዘው። ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ የኢየሩሳሌምን ቅጥር፣ ከኤፍሬም በር አንስቶ እስከ ማዕዘን በር ድረስ አፈረሰ፤ ርዝመቱም 400 ክንድ ያህል ነበር። |
በእውነተኛው አምላክ ቤት በኦቤድዔዶም እጅና በንጉሡ ቤት ግምጃ ቤቶች የተገኘውን ወርቅ፣ ብርና ዕቃ ሁሉ እንዲሁም የታገቱትን ሰዎች ወሰደ። ከዚያም ወደ ሰማርያ ተመለሰ። |
የእስራኤል ንጉሥ የኢዮዓካዝ ልጅ ኢዮዓስ ከሞተ በኋላ፣ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮዓስ ልጅ አሜስያስ 15 ዓመት ኖረ። |
ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለው የቀረው የአሜስያስ ታሪክ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ የለም? |
አሜስያስ ይሖዋን መከተል ከተወበት ጊዜ ጀምሮ በኢየሩሳሌም በእሱ ላይ ሲያሴሩ ቆዩ፤ እሱም ወደ ለኪሶ ሸሸ፤ እነሱ ግን ተከታትለው እንዲይዙት ሰዎችን ወደ ለኪሶ ላኩ፤ በዚያም ገደሉት። |
ከዚያም በፈረሶች ላይ ጭነው አመጡት፤ ከአባቶቹም ጋር በይሁዳ ከተማ ቀበሩት። |
ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በ18ኛው ዓመት አቢያህ በይሁዳ ላይ ነገሠ። |
እሱም በኢየሩሳሌም ለሦስት ዓመት ገዛ። የእናቱ ስም ሚካያህ ነበር፤ እሷም የጊብዓዊው የዑሪኤል ልጅ ነበረች። በአቢያህና በኢዮርብዓም መካከልም ጦርነት ነበር። |
በመሆኑም አቢያህ 400,000 የሠለጠኑ ኃያላን ተዋጊዎችን ያቀፈ ሠራዊት ይዞ ዘመተ። ኢዮርብዓምም 800,000 የሠለጠኑ ኃያላን ተዋጊዎችን አስከትሎ እሱን ለመግጠም ተሰለፈ። |
አቢያህ በኤፍሬም ተራራማ ክልል በሚገኘው በጸማራይም ተራራ ላይ ቆሞ እንዲህ አለ፦ “ኢዮርብዓምና እስራኤላውያን ሁሉ፣ ስሙኝ። |
የእስራኤል አምላክ ይሖዋ፣ ዳዊትና ልጆቹ በእስራኤል ላይ ለዘላለም እንዲነግሡ በጨው ቃል ኪዳን መንግሥት እንደሰጣቸው አታውቁም? |
የዳዊት ልጅ የሰለሞን አገልጋይ የነበረው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ግን ተነስቶ በጌታው ላይ ዓመፀ። |
Subsets and Splits
No community queries yet
The top public SQL queries from the community will appear here once available.