text
stringlengths
4
267
የኪራም አገልጋዮች የሰለሞንን መርከቦች እየነዱ ወደ ተርሴስ ይጓዙ ነበር። እነዚህ የተርሴስ መርከቦች በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብር፣ የዝሆን ጥርስ፣ ጦጣና ጣዎስ ጭነው ይመጡ ነበር።
በመሆኑም ንጉሥ ሰለሞን በብልጽግናና በጥበብ ምድር ላይ ካሉ ሌሎች ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ ነበር።
የምድር ነገሥታትም ሁሉ እውነተኛው አምላክ በሰለሞን ልብ ውስጥ ያኖረውን ጥበብ ይሰሙ ዘንድ ከእሱ ጋር ለመገናኘት ይጓጉ ነበር።
ወደ እሱ የሚመጡትም ሰዎች በየዓመቱ የብር ዕቃዎች፣ የወርቅ ዕቃዎች፣ ልብሶች፣ የጦር ትጥቆች፣ የበለሳን ዘይት፣ ፈረሶችና በቅሎዎች ስጦታ አድርገው ያመጡ ነበር።
ሰለሞንም ለፈረሶቹ የሚሆኑ 4,000 ጋጣዎች፣ ሠረገሎችና 12,000 ፈረሶች ነበሩት፤ እነሱንም በሠረገላ ከተሞችና በኢየሩሳሌም በንጉሡ አቅራቢያ አኖራቸው።
እሱም ከወንዙ አንስቶ እስከ ፍልስጤማውያን ምድርና እስከ ግብፅ ወሰን ድረስ ባሉት ነገሥታት ሁሉ ላይ ገዛ።
ንጉሡ በኢየሩሳሌም ያለውን ብር ከብዛቱ የተነሳ በየቦታው እንደሚገኝ ድንጋይ አደረገው፤ የአርዘ ሊባኖሱንም ብዛት በሸፌላ እንደሚገኘው የሾላ ዛፍ አደረገው።
ደግሞም ለሰለሞን ከግብፅና ከሌሎች አገሮች ሁሉ ፈረሶችን ያመጡለት ነበር።
ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለው የቀረው የሰለሞን ታሪክ ነቢዩ ናታን ባዘጋጀው ጽሑፍ፣ የሴሎ ሰው የሆነው አኪያህ በተናገረው ትንቢትና ባለ ራእዩ ኢዶ ስለ ናባጥ ልጅ ስለ ኢዮርብዓምያየው ራእይ በሰፈረበት ዘገባ ላይ ተጽፎ የለም?
ሰለሞን በኢየሩሳሌም ሆኖ በመላው እስራኤል ላይ ለ40 ዓመት ገዛ።
በመጨረሻም ሰለሞን ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ። በአባቱም በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤ በእሱም ምትክ ልጁ ሮብዓም ነገሠ።
ኢዮዓስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ሆኖ 40 ዓመት ገዛ። እናቱ ጺብያ የተባለች የቤርሳቤህ ተወላጅ ነበረች።
ኢዮዓስ ካህኑ ዮዳሄ በነበረበት ዘመን ሁሉ በይሖዋ ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ።
ዮዳሄ ሁለት ሚስቶች መረጠለት፤ እሱም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወለደ።
ከጊዜ በኋላ ኢዮዓስ የይሖዋን ቤት ለማደስ ልባዊ ፍላጎት አደረበት።
በመሆኑም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ሄዳችሁ የአምላካችሁን ቤት በየዓመቱ ለማደስ ከእስራኤል ሁሉ ገንዘብ ሰብስቡ፤ እናንተም በአስቸኳይ ይህንኑ አድርጉ።” ሌዋውያኑ ግን አፋጣኝ እርምጃ አልወሰዱም።
ስለዚህ ንጉሡ የካህናቱን አለቃ ዮዳሄን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “የይሖዋ አገልጋይ የሆነው ሙሴ ያዘዘውንና ለምሥክሩ ድንኳን የሚውለውን የተቀደሰ ግብር ይኸውም የእስራኤልን ጉባኤ የተቀደሰ ግብር ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም እንዲያመጡ ሌዋውያኑን ያላዘዝካቸው ለምንድን ነው?
የዚያች ክፉ ሴት የጎቶልያ ወንዶች ልጆች ወደ እውነተኛው አምላክ ቤት ሰብረው በመግባት በይሖዋ ቤት የነበሩትን የተቀደሱ ዕቃዎች በሙሉ ለባአል አገልግሎት እንዳዋሉ ታውቃለህ።”
ከዚያም በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት ሣጥን ተሠርቶ በይሖዋ ቤት በር አጠገብ በውጭ በኩል ተቀመጠ።
ከዚህ በኋላ የእውነተኛው አምላክ አገልጋይ ሙሴ በምድረ በዳ ሳሉ በእስራኤል ላይ የጣለው የተቀደሰ ግብር ለይሖዋ እንዲሰጥ በመላው ይሁዳና ኢየሩሳሌም አዋጅ ተነገረ።
መኳንንቱ ሁሉና ሕዝቡ ሁሉ ሐሴት አደረጉ፤ ሣጥኑ እስኪሞላም ድረስ መዋጮ እያመጡ ይጨምሩ ነበር።
ሌዋውያኑ ሣጥኑን ወደ ንጉሡ በሚያመጡበትና በውስጡ ብዙ ገንዘብ መኖሩን በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ የንጉሡ ጸሐፊና የካህናቱ አለቃ ሹም መጥተው ሣጥኑን ካጋቡ በኋላ ወደ ቦታው ይመልሱት ነበር። በየዕለቱ እንዲህ ያደርጉ ነበር፤ እጅግ ብዙ ገንዘብም ሰበሰቡ።
ከዚያም ንጉሡና ዮዳሄ ገንዘቡን በይሖዋ ቤት አገልግሎት የሚከናወነውን ሥራ ለሚቆጣጠሩት ሰዎች ይሰጧቸው ነበር፤ እነሱ ደግሞ የይሖዋን ቤት ለማደስ ድንጋይ ጠራቢዎችንና የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችን እንዲሁም የይሖዋን ቤት ለመጠገን የብረትና የመዳብ ሠራተኞችን ይቀጥሩ ነበር።
ሥራውን የሚቆጣጠሩት ሰዎችም ሥራው እንዲጀመር አደረጉ፤ የጥገናውም ሥራ በእነሱ አመራር ሥር ተፋጠነ፤ የእውነተኛውን አምላክ ቤት በማደስ ወደ ቀድሞው ሁኔታ መለሱት፤ ቤቱንም አጠናከሩት።
ሥራውን እንደጨረሱም የተረፈውን ገንዘብ ወደ ንጉሡና ወደ ዮዳሄ አመጡ፤ እነሱም ለይሖዋ ቤት የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን፣ ለአገልግሎትና መባ ለማቅረብ የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን፣ ጽዋዎችን እንዲሁም የወርቅና የብር ዕቃዎችን ለመሥራት ተጠቀሙበት። ዮዳሄ በነበረበት ዘመን ሁሉ በይሖዋ ቤት የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችን ዘወትር ያቀርቡ ነበር።
ዮዳሄ ሸምግሎና ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ በሞተ ጊዜ ዕድሜው 130 ዓመት ነበር።
ከእውነተኛው አምላክና ከአምላክ ቤት ጋር በተያያዘ በእስራኤል መልካም ነገር ስላደረገ በዳዊት ከተማ ከነገሥታት ጋር ቀበሩት።
ከዮዳሄ ሞት በኋላ የይሁዳ መኳንንት መጥተው ንጉሡን እጅ ነሱ፤ ንጉሡም እነሱ ያሉትን ሰማ።
እነሱም የአባቶቻቸውን አምላክ የይሖዋን ቤት ትተው የማምለኪያ ግንዶችንና ጣዖቶችን ማገልገል ጀመሩ፤ ከፈጸሙት በደል የተነሳ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ የአምላክ ቁጣ መጣ።
ይሖዋ ወደ እሱ እንዲመልሷቸው ነቢያትን ይልክላቸው ነበር፤ እነሱም ያስጠነቅቋቸው ነበር፤ ሕዝቡ ግን ለመስማት ፈቃደኛ አልነበረም።
የአምላክ መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ ልጅ በዘካርያስ ላይ ወረደ፤ እሱም በሕዝቡ ፊት ከፍ ያለ ቦታ ላይ ቆሞ እንዲህ አላቸው፦ “እውነተኛው አምላክ እንዲህ ይላል፦ ‘የይሖዋን ትእዛዛት የምትተላለፉት ለምንድን ነው? አይሳካላችሁም! ይሖዋን ስለተዋችሁ እሱም ይተዋችኋል።’”
እነሱ ግን በእሱ ላይ አሴሩ፤ ንጉሡም በሰጠው ትእዛዝ መሠረት በይሖዋ ቤት ግቢ ውስጥ በድንጋይ ወገሩት።
ንጉሥ ኢዮዓስ፣ አባቱ ዮዳሄ ያሳየውን ታማኝ ፍቅር አላሰበም፤ ልጁንም ገደለው፤ እሱም ሊሞት ሲል “ይሖዋ ይየው፤ የእጅህንም ይስጥህ” አለ።
በዓመቱ መጀመሪያ ላይ የሶርያ ሠራዊት በኢዮዓስ ላይ ዘመተ፤ እነሱም ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ወረሩ። ከዚያም የሕዝቡን መኳንንት ሁሉ አጠፉ፤ የማረኩትንም ሁሉ ወደ ደማስቆ ንጉሥ ላኩ።
ወራሪው የሶርያ ሠራዊት አነስተኛ ቁጥር የነበረው ቢሆንም ይሖዋ እጅግ ብዙ የሆነውን ሠራዊት በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤ ይህም የሆነው የአባቶቻቸውን አምላክ ይሖዋን በመተዋቸው ነው፤ እነሱም በኢዮዓስ ላይ የተላለፈውን ፍርድ ፈጸሙ።
እነሱም ጥለውት በሄዱ ጊዜ (ክፉኛ አቁስለውት ነበርና) የገዛ አገልጋዮቹ የካህኑን የዮዳሄን ልጆች ደም በማፍሰሱ አሴሩበት። አልጋው ላይ እንዳለ ገደሉት። ከሞተም በኋላ በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤ በነገሥታቱ የመቃብር ስፍራ ግን አልቀበሩትም።
በእሱ ላይ ያሴሩት የአሞናዊቷ የሺምዓት ልጅ ዛባድና የሞዓባዊቷ የሺምሪት ልጅ የሆዛባድ ነበሩ።
ስለ ወንዶች ልጆቹ፣ በእሱ ላይ ስለተላለፉት በርካታ የፍርድ መልእክቶችና የእውነተኛውን አምላክ ቤት ስለማደሱ የሚገልጸው ታሪክ ሁሉ በነገሥታቱ መጽሐፍ ዘገባዎች ላይ ሰፍሯል። በእሱም ምትክ ልጁ አሜስያስ ነገሠ።
ኢዮዓታም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ16 ዓመት ገዛ። እናቱም የሩሻህ ትባል ነበር፤ እሷም የሳዶቅ ልጅ ነበረች።
ኢዮዓታም አባቱ ዖዝያ እንዳደረገው ሁሉ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ፤ ይሁንና ሥርዓቱን ጥሶ ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ አልገባም። ሕዝቡ ግን ክፉ ድርጊት መፈጸሙን አልተወም ነበር።
እሱም የይሖዋን ቤት የላይኛውን በር ሠራ፤ በኦፌልም ቅጥር ላይ መጠነ ሰፊ የግንባታ ሥራ አከናወነ።
በተጨማሪም በተራራማው የይሁዳ ክልል ከተሞችን ሠራ፤ በደን በተሸፈኑት ስፍራዎችም ምሽጎችንና ማማዎችን ገነባ።
ከአሞናውያንም ንጉሥ ጋር ተዋጋ፤ በመጨረሻም አሸነፋቸው፤ በመሆኑም አሞናውያን በዚያ ዓመት 100 የብር ታላንት፣ 10,000 የቆሮስ መስፈሪያ ስንዴና 10,000 የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ ሰጡት። በተጨማሪም አሞናውያን በሁለተኛውና በሦስተኛው ዓመት ይህንኑ ግብር አመጡለት።
ኢዮዓታም በአምላኩ በይሖዋ ፊት መንገዱን ስላጸና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ሄደ።
የቀረው የኢዮዓታም ታሪክ፣ ያካሄዳቸው ጦርነቶችና የተከተለው መንገድ ሁሉ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈዋል።
እሱ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ16 ዓመት ገዛ።
በመጨረሻም ኢዮዓታም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም ቀበሩት። በእሱም ምትክ ልጁ አካዝ ነገሠ።
ሰለሞን ለይሖዋ ስም ቤት፣ ለመንግሥቱም ቤት እንዲሠራ አዘዘ።
ሰለሞን 70,000 ተራ የጉልበት ሠራተኞችና በተራሮቹ ላይ ድንጋይ የሚጠርቡ 80,000 ሰዎች መረጠ፤ በእነሱም ላይ 3,600 ሰዎችን የበላይ ተመልካቾች አድርጎ ሾመ።
ደግሞም ሰለሞን እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ጢሮስ ንጉሥ ወደ ኪራም ላከ፦ “አባቴ ዳዊት የሚኖርበትን ቤት ሲሠራ የአርዘ ሊባኖስ እንጨት እንደላክለት ሁሉ ለእኔም እንዲሁ አድርግልኝ።
እነሆ፣ በፊቱ ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን ለማጠን፣ የሚነባበረውን ዳቦ ዘወትር በዚያ ለማስቀመጥ እንዲሁም በየጠዋቱና በየማታው፣ በየሰንበቱ፣ በየወር መባቻውና በአምላካችን በይሖዋ የበዓላት ወቅቶች የሚቃጠል መባ ለማቅረብ ለአምላኬ ለይሖዋ ስም ቤት ልሠራና ለእሱ ልቀድሰው አስቤአለሁ። ይህም እስራኤላውያን ሁልጊዜ ሊፈጽሙት የሚገባ ግዴታ ነው።
አምላካችን ከሌሎች አማልክት ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ስለሆነ የምሠራውም ቤት ታላቅ ይሆናል።
ለእሱ ቤት መሥራት የሚችል ማነው? ሰማያትና የሰማያት ሰማይ ሊይዙት አይችሉምና፤ በፊቱ የሚጨስ መሥዋዕት የሚቀርብበት ስፍራ ካልሆነ በስተቀር ለእሱ ቤት እሠራለት ዘንድ እኔ ማን ነኝ?
አሁንም በወርቅ፣ በብር፣ በመዳብ፣ በብረት፣ በሐምራዊ ሱፍ፣ በደማቅ ቀይ ክርና በሰማያዊ ክር ሥራ የተካነ እንዲሁም ቅርጻ ቅርጽ የመሥራት ችሎታ ያለው የእጅ ጥበብ ባለሙያ ላክልኝ። እሱም አባቴ ዳዊት ካዘጋጃቸው የተካኑ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎቼ ጋር በይሁዳና በኢየሩሳሌም አብሮ ይሠራል።
የአርዘ ሊባኖስ፣ የጥድና የሰንደል ዛፍ ሳንቃ ከሊባኖስ ላክልኝ፤ አገልጋዮችህ የሊባኖስን ዛፎች በመቁረጥ ረገድ የተካኑ መሆናቸውን በሚገባ አውቃለሁ። አገልጋዮቼ ከአገልጋዮችህ ጋር አብረው በመሥራት
በርካታ ሳንቃዎችን ያዘጋጁልኛል፤ የምሠራው ቤት እጅግ ታላቅ ነውና።
እነሆ፣ ዛፍ ቆራጭና እንጨት ፈላጭ ለሆኑት አገልጋዮችህ ቀለብ እንዲሆናቸው 20,000 የቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ፣ 20,000 የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ፣ 20,000 የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅና 20,000 የባዶስ መስፈሪያ ዘይት እሰጣቸዋለሁ።”
በዚህ ጊዜ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም የሚከተለውን መልእክት በጽሑፍ ለሰለሞን ላከለት፦ “ይሖዋ ሕዝቡን ስለሚወድ አንተን በእነሱ ላይ ንጉሥ አድርጎ ሾመህ።”
ከዚያም ኪራም እንዲህ አለ፦ “ሰማያትንና ምድርን የሠራው የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ውዳሴ ይድረሰው፤ ምክንያቱም ለይሖዋ ቤት፣ ለመንግሥቱም ቤት የሚሠራ ልባምና አስተዋይ የሆነ ጥበበኛ ልጅ ለንጉሥ ዳዊት ሰጥቷል።
አሁንም አስተዋይ የሆነውን ኪራምአቢ የተባለውን የእጅ ጥበብ ባለሙያ ልኬልሃለሁ፤
እናቱ ከዳን ወገን ስትሆን አባቱ ግን የጢሮስ ሰው ነው፤ እሱም በወርቅ፣ በብር፣ በመዳብ፣ በብረት፣ በድንጋይ፣ በሳንቃ፣ በሐምራዊ ሱፍ፣ በሰማያዊ ክር፣ ጥራት ባለው ጨርቅና በደማቅ ቀይ ክር ሥራ ልምድ ያካበተ ነው። ማንኛውንም ቅርጻ ቅርጽ መቅረጽ እንዲሁም የተሰጠውን ማንኛውንም ንድፍ መሥራት ይችላል። አንተ ጋ ካሉትም ሆነ ከጌታዬ ይኸውም ከአባትህ ከዳዊት የተካኑ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ሆኖ ይሠራል።
አሁንም ጌታዬ ቃል በገባው መሠረት ስንዴውን፣ ገብሱን፣ ዘይቱንና የወይን ጠጁን ለአገልጋዮቹ ይላክ።
እኛም የምትፈልገውን ያህል ከሊባኖስ ዛፎች ቆርጠን አንድ ላይ በማሰር በባሕር ላይ እያንሳፈፍን ወደ ኢዮጴ እናመጣልሃለን፤ አንተም ወደ ኢየሩሳሌም ልትወስደው ትችላለህ።”
በዚህ ጊዜ ሰለሞን አባቱ ዳዊት ካደረገው ቆጠራ በኋላ በእስራኤል ምድር የሚኖሩትን የባዕድ አገር ወንዶች ሁሉ ቆጠረ፤ ቁጥራቸውም 153,600 ሆነ።
ከእነሱም መካከል 70,000ዎቹን ተራ የጉልበት ሠራተኞች፣ 80,000ዎቹን በተራሮቹ ላይ ድንጋይ ጠራቢዎች፣ 3,600ዎቹን ደግሞ ሰዎቹን የሚያሠሩ የበላይ ተመልካቾች አድርጎ ሾማቸው።
እስራኤላውያን በሙሉ ሮብዓምን ለማንገሥ ወደ ሴኬም መጥተው ስለነበር እሱም ወደ ሴኬም ሄደ።
የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን እንደሰማ (ምክንያቱም በወቅቱ ኢዮርብዓም ከንጉሥ ሰለሞን ሸሽቶ በግብፅ ይኖር ነበር)፣ ከግብፅ ተመልሶ መጣ።
ከዚያም ሰዎች ልከው አስጠሩት፤ ኢዮርብዓምና መላው እስራኤልም መጥተው ሮብዓምን እንዲህ አሉት፦
“አባትህ ቀንበራችንን አክብዶብን ነበር። አንተ ግን አባትህ የሰጠንን አስቸጋሪ ሥራና በላያችን የጫነብንን ከባድ ቀንበር የምታቀልልን ከሆነ እናገለግልሃለን።”
በዚህ ጊዜ “ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሳችሁ ኑ” አላቸው። በመሆኑም ሕዝቡ ሄደ።
ከዚያም ንጉሥ ሮብዓም አባቱ ሰለሞን በሕይወት በነበረበት ጊዜ ሲያገለግሉት የነበሩትን ሽማግሌዎች “ለዚህ ሕዝብ ምን ምላሽ እንድሰጥ ትመክሩኛላችሁ?” በማለት ምክር ጠየቀ።
እነሱም “ለዚህ ሕዝብ ጥሩ ብትሆንና ደስ ብታሰኛቸው እንዲሁም መልካም ምላሽ ብትሰጣቸው ምንጊዜም አገልጋዮችህ ይሆናሉ” በማለት መለሱለት።
ሆኖም ሮብዓም ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር ትቶ አብሮ አደጎቹ ከነበሩትና አሁን የእሱ አገልጋዮች ከሆኑት ወጣቶች ጋር ተማከረ።
እሱም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፦ “‘አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልልን’ ለሚለኝ ለዚህ ሕዝብ ምን ምላሽ እንድንሰጥ ትመክሩኛላችሁ?”
አብሮ አደጎቹ የሆኑት ወጣቶችም እንዲህ አሉት፦ “‘አባትህ ቀንበራችንን አክብዶብን ነበር፤ አንተ ግን ቀንበራችንን አቅልልልን’ ለሚልህ ሕዝብ እንዲህ በለው፦ ‘ትንሿ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች።
አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፤ እኔ ግን ቀንበራችሁን የባሰ አከብደዋለሁ። አባቴ በአለንጋ ገርፏችሁ ነበር፤ እኔ ግን በእሾህ አለንጋ እገርፋችኋለሁ።’”
ኢዮርብዓምና መላው ሕዝብ ንጉሡ “በሦስተኛው ቀን ተመልሳችሁ ኑ” ባላቸው መሠረት በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም መጡ።
ይሁንና ንጉሡ መጥፎ ምላሽ ሰጣቸው። በዚህ መንገድ ንጉሥ ሮብዓም ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር ሳይቀበል ቀረ።
ወጣቶቹ በሰጡት ምክር መሠረት “ቀንበራችሁን አከብደዋለሁ፤ ከቀድሞውም የከፋ አደርገዋለሁ። አባቴ በአለንጋ ገርፏችሁ ነበር፤ እኔ ግን በእሾህ አለንጋ እገርፋችኋለሁ” አላቸው።
በመሆኑም ንጉሡ ሕዝቡን ሳይሰማ ቀረ፤ ይህም የሆነው ይሖዋ በሴሎናዊው በአኪያህ አማካኝነት ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ እውነተኛው አምላክ እነዚህ ነገሮች በዚህ መንገድ እንዲከናወኑ ስላደረገ ነው።
እስራኤላውያን ሁሉ ንጉሡ ሊሰማቸው ፈቃደኛ አለመሆኑን ሲያዩ ንጉሡን እንዲህ አሉት፦ “ከዳዊት ምን ድርሻ አለን? ከእሴይ ልጅ ምንም ርስት የለንም። እስራኤል ሆይ፣ እያንዳንድህ ወደ አማልክትህ ተመለስ! ዳዊት ሆይ፣ እንግዲህ የገዛ ቤትህን ጠብቅ!” ከዚያም እስራኤላውያን ሁሉ ወደየቤታቸው ተመለሱ።
ይሁንና ሮብዓም በይሁዳ ከተሞች በሚኖሩት እስራኤላውያን ላይ መግዛቱን ቀጠለ።
ከዚያም ንጉሥ ሮብዓም የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ የተመለመሉት ሰዎች አለቃ የነበረውን ሃዶራምን ላከው፤ ሆኖም እስራኤላውያን በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ንጉሥ ሮብዓም ግን እንደ ምንም ብሎ ሠረገላው ላይ በመውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሸሸ።
እስራኤላውያንም እስከዚህ ቀን ድረስ በዳዊት ቤት ላይ እንዳመፁ ናቸው።
አሳ በነገሠ በ36ኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ዘመተ፤ እሱም ማንም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ እንዳይገባና እንዳይወጣ ለማድረግ ራማን መገንባት ጀመረ።
በዚህ ጊዜ አሳ ከይሖዋ ቤትና ከንጉሡ ቤት ግምጃ ቤቶች ብርና ወርቅ አውጥቶ በደማስቆ ወደሚገኘው የሶርያ ንጉሥ ወደ ቤንሃዳድ እንዲህ ሲል ላከ፦
“በእኔና በአንተ እንዲሁም በአባቴና በአባትህ መካከል ውል አለ። እኔ ብርና ወርቅ ልኬልሃለሁ። ስለዚህ ና፣ የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ከእኔ እንዲርቅ ከእሱ ጋር የገባኸውን ውል አፍርስ።”
ቤንሃዳድ የንጉሥ አሳን ሐሳብ ተቀብሎ የጦር ሠራዊቱን አለቆች በእስራኤል ከተሞች ላይ አዘመተ፤ እነሱም ኢዮንን፣ ዳንን፣ አቤልማይምን እና በንፍታሌም ከተሞች ውስጥ ያሉትን የማከማቻ ስፍራዎች ሁሉ መቱ።
ባኦስም ይህን ሲሰማ ወዲያውኑ ራማን መገንባቱን አቆመ፤ ሥራውንም አቋረጠ።
ከዚያም ንጉሡ አሳ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ይዞ ሄደ፤ እነሱም ባኦስ እየገነባባቸው የነበሩትን የራማን ድንጋዮችና ሳንቃዎች አጋዙ፤ እሱም በድንጋዮቹና በሳንቃዎቹ ጌባንና ምጽጳን ገነባ።
በዚህ ጊዜ ባለ ራእዩ ሃናኒ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “በአምላክህ በይሖዋ ከመታመን ይልቅ በሶርያ ንጉሥ ስለታመንክ የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት ከእጅህ አምልጧል።
ኢትዮጵያውያንና ሊቢያውያን ብዙ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ያሏቸው ታላቅ ሠራዊት አልነበሩም? ይሁንና በይሖዋ በመታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጣቸው።
አዎ፣ በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች ብርታቱን ያሳይ ዘንድ የይሖዋ ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመላለሳሉ። በዚህ ረገድ የሞኝነት ድርጊት ፈጽመሃል፤ ከእንግዲህ ወዲያ ጦርነት አይለይህም።”
ሆኖም አሳ በባለ ራእዩ ተቆጣ፤ በዚህ ጉዳይ በጣም ስለተናደደበትም እስር ቤት አስገባው። በዚያ ወቅት አሳ በሌሎች ሰዎችም ላይ በደል መፈጸም ጀመረ።
ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለው የአሳ ታሪክ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፏል።
አሳ በ39ኛው የግዛት ዘመኑ እግሩን ታመመ፤ ሕመሙም ጠናበት፤ ታሞ ሳለም እንኳ የባለ መድኃኒቶችን እንጂ የይሖዋን እርዳታ አልፈለገም።
በመጨረሻም አሳ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በ41ኛው የግዛት ዘመኑም ሞተ።
እነሱም በዳዊት ከተማ ለራሱ ባስቆፈረው ታላቅ የመቃብር ቦታ ቀበሩት፤ የበለሳን ዘይት እንዲሁም ከተለያዩ ቅመሞች የተዘጋጀ ልዩ ቅባት በሞላበት ቃሬዛ ላይ አኖሩት። በተጨማሪም ለክብሩ ታላቅ እሳት አነደዱለት።
በዚህ ሁኔታ ሰለሞን ከይሖዋ ቤት ጋር በተያያዘ መሥራት የሚገባውን ሥራ በሙሉ ሠርቶ አጠናቀቀ። ከዚያም ሰለሞን አባቱ ዳዊት የቀደሳቸውን ነገሮች ወደዚያ አስገባ፤ ብሩን፣ ወርቁንና ዕቃዎቹን በሙሉ በእውነተኛው አምላክ ቤት ግምጃ ቤቶች ውስጥ አስቀመጠ።
በዚህ ጊዜ ሰለሞን የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ የነገዶቹን መሪዎች ሁሉና የእስራኤልን የአባቶች ቤት አለቆች ሰበሰበ። እነሱም የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ማለትም ከጽዮን ለማምጣት ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።