text stringlengths 4 267 |
|---|
ስለሆነም የእስራኤል ንጉሥ አንድ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን ጠርቶ “የይምላን ልጅ ሚካያህን በአስቸኳይ ይዘኸው ና” አለው። |
በዚህ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ የንግሥና ልብሳቸውን ለብሰው በየዙፋናቸው ተቀምጠው ነበር፤ የተቀመጡትም በሰማርያ መግቢያ በር በሚገኘው አውድማ ላይ ሲሆን ነቢያቱ ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር። |
ከዚያም የኬናአና ልጅ ሴዴቅያስ የብረት ቀንዶች ሠርቶ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ሶርያውያንን እስክታጠፋቸው ድረስ በእነዚህ ትወጋቸዋለህ’” አለ። |
ሌሎቹ ነቢያትም ሁሉ “ወደ ራሞትጊልያድ ውጣ፤ ይሳካልሃል፤ ይሖዋም እሷን በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል” በማለት ተመሳሳይ ትንቢት ይናገሩ ነበር። |
ሚካያህን ለመጥራት የሄደው መልእክተኛም “እነሆ፣ ነቢያቱ ሁሉ በአንድ ድምፅ ለንጉሡ የተናገሩት ነገር ጥሩ ነው። እባክህ፣ የአንተም ቃል እንደ እነሱ ይሁን፤ አንተም ጥሩ ነገር ተናገር” አለው። |
ሚካያህ ግን “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፤ የምናገረው አምላኬ የሚለውን ብቻ ነው” አለ። |
ከዚያም ወደ ንጉሡ ገባ፤ ንጉሡም “ሚካያህ፣ ራሞትጊልያድን ለመውጋት እንዝመት ወይስ ይቅርብኝ?” ሲል ጠየቀው። እሱም ወዲያውኑ “ውጡ፤ ይቀናችኋል፤ በእጃችሁም አልፈው ይሰጣሉ” በማለት መለሰለት። |
በዚህ ጊዜ ንጉሡ “በይሖዋ ስም ከእውነት በስተቀር ሌላ አንዳች ነገር እንዳትነግረኝ የማስምልህ ስንት ጊዜ ነው?” አለው። |
በመሆኑም ሚካያህ እንዲህ በማለት ተናገረ፦ “እስራኤላውያን ሁሉ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበታትነው አያለሁ። ይሖዋም ‘እነዚህ ጌታ የላቸውም። እያንዳንዳቸው በሰላም ወደየቤታቸው ይመለሱ’ ብሏል።” |
ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ ኢዮሳፍጥን “‘ስለ እኔ መጥፎ ነገር ብቻ እንጂ ጥሩ ነገር አይተነብይም’ ብዬህ አልነበረም?” አለው። |
በዚህ ጊዜ ሚካያህ እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ የይሖዋን ቃል ስሙ፦ ይሖዋ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ የሰማያት ሠራዊትም ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። |
ከዚያም ይሖዋ ‘በራሞትጊልያድ ላይ ዘምቶ እዚያው እንዲሞት የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ማን ያሞኘዋል?’ አለ። በዚህ ጊዜ አንዱ አንድ ነገር፣ ሌላው ደግሞ ሌላ ነገር ተናገረ። |
ከዚያም አንድ መንፈስ ወደ ፊት ወጥቶ ይሖዋ ፊት በመቆም ‘እኔ አሞኘዋለሁ’ አለ። ይሖዋም ‘እንዴት አድርገህ?’ አለው። |
‘እኔ እወጣና በነቢያቱ ሁሉ አፍ ላይ አሳሳች መንፈስ እሆናለሁ’ አለ። እሱም ‘እንግዲያው ታሞኘዋለህ፤ ደግሞም ይሳካልሃል። ውጣና እንዳልከው አድርግ’ አለው። |
ይሖዋም በእነዚህ ነቢያትህ አፍ ላይ አሳሳች መንፈስ አኑሯል፤ ሆኖም ይሖዋ ጥፋት እንደሚመጣብህ ተናግሯል።” |
የኬናአና ልጅ ሴዴቅያስም ወደ ሚካያህ ቀርቦ በጥፊ መታውና “ለመሆኑ የይሖዋ መንፈስ እኔን በየት በኩል አልፎ ነው አንተን ያናገረህ?” አለው። |
ሚካያህም “በየት በኩል እንዳለፈማ፣ ለመደበቅ ወደ ውስጠኛው ክፍል በምትገባበት ቀን ታውቀዋለህ” አለው። |
ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ አለ፦ “ሚካያህን ወስዳችሁ ለከተማው አለቃ ለአምዖን እና የንጉሡ ልጅ ለሆነው ለዮአስ አስረክቡት። |
እንዲህም በሏቸው፦ ‘ንጉሡ “በሰላም ተመልሼ እስክመጣ ድረስ ይህን ሰው እስር ቤት አቆዩት፤ ጥቂት ምግብና ውኃ ብቻ ስጡት” ብሏል።’” |
ሚካያህ ግን “እውነት አንተ በሰላም ከተመለስክ ይሖዋ በእኔ አልተናገረም ማለት ነው!” አለ። ከዚያም “እናንተ ሰዎች፣ ሁላችሁም ልብ በሉ” አለ። |
በመሆኑም የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ወደ ራሞትጊልያድ ወጡ። |
የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሳፍጥን “እኔ ማንነቴ እንዳይታወቅ ራሴን ለውጬ ወደ ውጊያው እገባለሁ፤ አንተ ግን ንጉሣዊ ልብስህን ልበስ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ማንነቱ እንዳይታወቅ ራሱን ለወጠ፤ ከዚያም ወደ ውጊያው ገቡ። |
በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ የሠረገሎቹን አዛዦች “ከእስራኤል ንጉሥ በስተቀር ከትንሹም ሆነ ከትልቁ፣ ከማንም ጋር እንዳትዋጉ” በማለት አዟቸው ነበር። |
የሠረገሎቹ አዛዦችም ኢዮሳፍጥን ባዩት ጊዜ “ይህ የእስራኤል ንጉሥ ነው” ብለው አሰቡ። በመሆኑም ሊወጉት ወደ እሱ ዞሩ፤ በዚህ ጊዜ ኢዮሳፍጥ እርዳታ ለማግኘት ጮኸ፤ ይሖዋም ረዳው፤ አምላክም ወዲያውኑ ከእሱ እንዲርቁ አደረገ። |
የሠረገሎቹ አዛዦችም የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን ሲያዩ ወዲያውኑ እሱን ማሳደዳቸውን ትተው ተመለሱ። |
ይሁንና አንድ ሰው በነሲብ ቀስቱን ሲያስወነጭፍ የእስራኤልን ንጉሥ የጥሩሩ መጋጠሚያ ላይ ወጋው። ስለሆነም ንጉሡ ሠረገላ ነጂውን “ክፉኛ ስለቆሰልኩ ሠረገላውን አዙረህ ከጦርነቱ ይዘኸኝ ውጣ” አለው። |
ያን ቀን ሙሉ የተፋፋመ ውጊያ ተካሄደ፤ የእስራኤልንም ንጉሥ ሠረገላው ውስጥ እንዳለ ፊቱን ወደ ሶርያውያን አዙረው እስከ ምሽት ድረስ ደግፈው አቆሙት፤ ፀሐይ ስትጠልቅም ሞተ። |
በሰባተኛው ዓመት ካህኑ ዮዳሄ ድፍረት የተሞላበት እርምጃ በመውሰድ ከመቶ አለቆቹ ይኸውም ከየሮሃም ልጅ ከአዛርያስ፣ ከየሆሃናን ልጅ ከእስማኤል፣ ከኢዮቤድ ልጅ ከአዛርያስ፣ ከአዳያህ ልጅ ከማአሴያህ እና ከዚክሪ ልጅ ከኤሊሻፋጥ ጋር ስምምነት አደረገ። |
ከዚያም በይሁዳ ሁሉ በመዘዋወር ከመላው የይሁዳ ከተሞች ሌዋውያንንና የእስራኤልን የአባቶች ቤት መሪዎች ሰበሰቡ። ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጡ |
መላው ጉባኤ በእውነተኛው አምላክ ቤት ከንጉሡ ጋር ቃል ኪዳን ገባ፤ ከዚያም ዮዳሄ እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፣ ይሖዋ የዳዊትን ወንዶች ልጆች አስመልክቶ ቃል በገባው መሠረት የንጉሡ ልጅ ይገዛል። |
እናንተም እንዲህ ታደርጋላችሁ፦ በሰንበት ቀን ተረኛ ከሚሆኑት ካህናትና ሌዋውያን መካከል አንድ ሦስተኛዎቹ በር ጠባቂዎች ይሆናሉ፤ |
አንድ ሦስተኛዎቹ ደግሞ በንጉሡ ቤት ይሆናሉ፤ ሌላው አንድ ሦስተኛ በመሠረት በር ላይ ይሆናል፤ ሕዝቡ ሁሉ ደግሞ በይሖዋ ቤት ግቢዎች ውስጥ ይሆናል። |
ከሚያገለግሉት ካህናትና ሌዋውያን በስተቀር ማንንም ወደ ይሖዋ ቤት እንዳታስገቡ። እነሱ የተቀደሱ ስለሆኑ ይግቡ፤ የቀረውም ሕዝብ ሁሉ ለይሖዋ ያለበትን ግዴታ ይፈጽማል። |
ሌዋውያኑም እያንዳንዳቸው የጦር መሣሪያቸውን በእጃቸው ይዘው ንጉሡን ዙሪያውን ይክበቡት። ወደ ቤቱም ውስጥ የሚገባ ማንኛውም ሰው ይገደላል። ንጉሡ በሚሄድበት ሁሉ አብራችሁት ሁኑ።” |
ሌዋውያኑና የይሁዳ ሰዎች በሙሉ ልክ ካህኑ ዮዳሄ እንዳዘዛቸው አደረጉ። እያንዳንዳቸውም በሰንበት ቀን ተረኛ የሚሆኑትንና በሰንበት ቀን ከሥራ ነፃ የሚሆኑትን የራሳቸውን ሰዎች ወሰዱ፤ ካህኑ ዮዳሄ ተራቸው ባይሆንም እንኳ በየምድቡ ያሉትን ከሥራ አላሰናበተም ነበርና። |
ካህኑ ዮዳሄም በእውነተኛው አምላክ ቤት የነበሩትን የንጉሥ ዳዊት ጦሮች፣ ትናንሽ ጋሻዎችና ክብ ጋሻዎች ለመቶ አለቆቹ ሰጣቸው። |
ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ እያንዳንዳቸው የጦር መሣሪያቸውን ይዘው በስተ ቀኝ በኩል ካለው የቤቱ ጎን አንስቶ በስተ ግራ በኩል እስካለው የቤቱ ጎን ድረስ በመሠዊያውና በቤቱ አጠገብ በንጉሡ ዙሪያ እንዲቆሙ አደረገ። |
የንጉሡንም ልጅ አውጥተው አክሊሉን ጫኑበት፤ ምሥክሩንም ሰጡት፤ በዚህም መንገድ አነገሡት፤ ዮዳሄና ወንዶች ልጆቹም ቀቡት። ከዚያም “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!” አሉ። |
ጎቶልያ ሕዝቡ ሲሯሯጥና ንጉሡን ሲያወድስ ስትሰማ ወዲያውኑ በይሖዋ ቤት ወዳለው ሕዝብ መጣች። |
ከዚያም ንጉሡ በመግቢያው ላይ ባለው በዓምዱ አጠገብ ቆሞ አየች። መኳንንቱና መለከት ነፊዎቹ ከንጉሡ ጋር ነበሩ፤ የምድሪቱም ሕዝብ ሁሉ እጅግ እየተደሰተና መለከት እየነፋ ነበር፤ የሙዚቃ መሣሪያ የያዙት ዘማሪዎችም ውዳሴውን ይመሩ ነበር። በዚህ ጊዜ ጎቶልያ ልብሷን ቀዳ “ይህ ሴራ ነው! ሴራ ነው!” በማለት ጮኸች። |
ካህኑ ዮዳሄ ግን በሠራዊቱ ላይ የተሾሙትን መቶ አለቆች ይዟቸው በመውጣት “ከረድፉ መካከል አውጧት፤ እሷን ተከትሎ የሚመጣ ሰው ካለ በሰይፍ ግደሉት!” አላቸው። ካህኑ “በይሖዋ ቤት ውስጥ እንዳትገድሏት” ብሎ ነበር። |
በመሆኑም ያዟት፤ በንጉሡም ቤት ወዳለው የፈረስ በር መግቢያ እንደደረሰች ገደሏት። |
ከዚያም ዮዳሄ የይሖዋ ሕዝብ ሆነው እንዲቀጥሉ እሱ፣ ሕዝቡ ሁሉና ንጉሡ ቃል ኪዳን እንዲጋቡ አደረገ። |
የምድሪቱም ሕዝብ ሁሉ ወደ ባአል ቤት መጥቶ አፈራረሰው፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹንም ሰባበረ፤ የባአል ካህን የነበረውን ማታንንም በመሠዊያዎቹ ፊት ገደሉት። |
ከዚያም ዮዳሄ በይሖዋ ቤት የሚከናወኑትን ሥራዎች እንዲቆጣጠሩ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ሾመ፤ እነሱም በሙሴ ሕግ ላይ በተጻፈው እንዲሁም ዳዊት ባዘዘው መሠረት በደስታና በመዝሙር ለይሖዋ የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ዳዊት በይሖዋ ቤት በየምድቡ የመደባቸው ናቸው። |
በተጨማሪም በማንኛውም ነገር የረከሰ ሰው እንዳይገባ በር ጠባቂዎቹን በይሖዋ ቤት በሮች ላይ አቆመ። |
ከዚያም መቶ አለቆቹን፣ መኳንንቱን፣ የሕዝቡን ገዢዎችና የምድሪቱን ሕዝብ ሁሉ ሰበሰበ፤ ንጉሡንም አጅበው ከይሖዋ ቤት ወደ ታች አመጡት። በላይኛውም በር በኩል ወደ ንጉሡ ቤት ገቡ፤ ንጉሡንም በመንግሥቱ ዙፋን ላይ አስቀመጡት። |
በመሆኑም የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ እጅግ ተደሰተ፤ ጎቶልያንም በሰይፍ ስለገደሏት ከተማዋ ጸጥታ ሰፈነባት። |
ኢዮስያስ በኢየሩሳሌም ለይሖዋ ፋሲካ አደረገ፤ በመጀመሪያው ወር በ14ኛው ቀን የፋሲካን መሥዋዕት አረዱ። |
ካህናቱን በየሥራቸው ላይ መደባቸው፤ የይሖዋንም ቤት አገልግሎት እንዲያከናውኑ አበረታታቸው። |
ከዚያም የመላው እስራኤል አስተማሪዎች የሆኑትንና ለይሖዋ የተቀደሱትን ሌዋውያን እንዲህ አላቸው፦ “ቅዱሱን ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰለሞን በሠራው ቤት ውስጥ አስቀምጡት፤ ከዚህ በኋላ ታቦቱን በትከሻችሁ መሸከም አያስፈልጋችሁም። አሁን አምላካችሁን ይሖዋንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ። |
የእስራኤል ንጉሥ ዳዊትና ልጁ ሰለሞን በጻፉት ትእዛዝ መሠረት በየአባቶቻችሁ ቤት እንደየምድባችሁ ራሳችሁን አዘጋጁ። |
ወንድሞቻችሁ የሆኑትን የቀሩትን ሰዎች ለማገልገል በየአባቶች ቤት ምድብ በተቀደሰው ስፍራ ቁሙ፤ እያንዳንዱም የሌዋውያን ቡድን ከሕዝቡ መካከል የሚደርሰውን የአባቶች ቤት ምድብ ያገልግል። |
የፋሲካውን መሥዋዕት እረዱ፤ ራሳችሁንም ቀድሱ፤ ይሖዋ በሙሴ በኩል የሰጠውን ትእዛዝ መፈጸም እንድትችሉ ለወንድሞቻችሁ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጉ።” |
ኢዮስያስም ለሕዝቡ ይኸውም በዚያ ለተገኙት ሁሉ ለፋሲካ መሥዋዕት እንዲሆኑ ከመንጋው መካከል በድምሩ 30,000 ተባዕት የበግና የፍየል ጠቦቶች እንዲሁም 3,000 ከብቶች ሰጠ። እነዚህ የተሰጡት ከንጉሡ ሀብት ላይ ነበር። |
መኳንንቱም ለሕዝቡ፣ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ በፈቃደኝነት የሚቀርብ መባ ሰጡ። የእውነተኛው አምላክ ቤት መሪዎች የሆኑት ኬልቅያስ፣ ዘካርያስና የሂኤል ለፋሲካ መሥዋዕት የሚሆኑ 2,600 በጎችና ፍየሎች እንዲሁም 300 ከብቶች ለካህናቱ ሰጡ። |
ኮናንያ፣ ወንድሞቹ ሸማያህ እና ናትናኤል እንዲሁም የሌዋውያኑ አለቆች ሃሻብያህ፣ የኢዔል እና ዮዛባድ ለፋሲካ መሥዋዕት የሚሆኑ 5,000 በጎችና ፍየሎች እንዲሁም 500 ከብቶች ለሌዋውያኑ ሰጡ። |
የአገልግሎቱ ዝግጅት ከተጠናቀቀ በኋላ ንጉሡ ባዘዘው መሠረት ካህናቱ በየቦታቸው፣ ሌዋውያኑም በየምድባቸው ቆሙ። |
የፋሲካውንም መሥዋዕት አረዱ፤ ሌዋውያኑ ቆዳውን ሲገፉ ካህናቱ ደግሞ ከእነሱ የተቀበሉትን ደም መሠዊያው ላይ ረጩ። |
ከዚያም በየአባቶች ቤት ለተመደቡት ለቀሩት ሰዎች ለማከፋፈል የሚቃጠለውን መባ አዘጋጁ፤ ይህም የሆነው በሙሴ መጽሐፍ ላይ በተጻፈው መሠረት መባው ለይሖዋ እንዲቀርብ ነው፤ ከብቶቹንም በዚሁ መንገድ አዘጋጁ። |
በልማዱም መሠረት የፋሲካን መባ በእሳት አበሰሉ፤ የተቀደሱትንም መባዎች በድስት፣ በሰታቴና በመጥበሻ አብስለው ወዲያውኑ ለቀሩት ሰዎች ሁሉ አቀረቡ። |
ከዚያም ለራሳቸውና ለካህናቱ አዘጋጁ፤ ምክንያቱም የአሮን ዘሮች የሆኑት ካህናቱ እስኪመሽ ድረስ፣ የሚቃጠሉትን መሥዋዕቶችና ስቡን ያቀርቡ ነበር፤ በመሆኑም ሌዋውያኑ ለራሳቸውና የአሮን ዘሮች ለሆኑት ለካህናቱ አዘጋጁ። |
ዳዊት፣ አሳፍ፣ ሄማንና የንጉሡ ባለ ራእይ የሆነው የዱቱን በሰጡት ትእዛዝ መሠረት የአሳፍ ልጆች የሆኑት ዘማሪዎቹ በየቦታቸው ላይ ነበሩ፤ በር ጠባቂዎቹም በየበሩ ላይ ነበሩ። ወንድሞቻቸው የሆኑት ሌዋውያን አዘጋጅተውላቸው ስለነበር ሥራቸውን ትተው መሄድ አላስፈለጋቸውም። |
በመሆኑም ንጉሥ ኢዮስያስ ባዘዘው መሠረት ፋሲካን ለማክበርና በይሖዋ መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መባ ለማቅረብ፣ ለይሖዋ አገልግሎት የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ በዚያን ቀን ተዘጋጅቶ ነበር። |
በስፍራው የተገኙት እስራኤላውያን በዚያ ጊዜ ፋሲካን አከበሩ፤ የቂጣንም በዓል ለሰባት ቀን አከበሩ። |
ከነቢዩ ሳሙኤል ዘመን ወዲህ እንደዚህ ያለ የፋሲካ በዓል በእስራኤል ተከብሮ አያውቅም፤ ኢዮስያስ፣ ካህናቱ፣ ሌዋውያኑ፣ በዚያ የተገኙት የይሁዳና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ እንዲሁም የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ያከበሩት ዓይነት ፋሲካ ያከበረ አንድም የእስራኤል ንጉሥ የለም። |
ይህ ፋሲካ የተከበረው ኢዮስያስ በነገሠ በ18ኛው ዓመት ነበር። |
ከዚህ ሁሉ በኋላ ኢዮስያስ ቤተ መቅደሱን አዘጋጅቶ ባጠናቀቀ ጊዜ የግብፁ ንጉሥ ኒካዑ በኤፍራጥስ አጠገብ ባለው በካርከሚሽ ለመዋጋት መጣ። በዚህ ጊዜ ኢዮስያስ ሊገጥመው ወጣ። |
ኒካዑም እንዲህ ሲል መልእክተኞችን ላከበት፦ “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፣ እኔን ልትወጋ የመጣኸው ለምንድን ነው? አሁን የመጣሁት ከሌላ ብሔር ጋር ልዋጋ እንጂ አንተን ልወጋ አይደለም፤ አምላክም እንድፈጥን አዞኛል። ከእኔ ጋር የሆነውን አምላክ መቃወም ቢቀርብህ ይሻላል፤ አለዚያ ያጠፋሃል።” |
ኢዮስያስ ግን ለመመለስ ፈቃደኛ አልሆነም፤ ይልቁንም ማንነቱ እንዳይታወቅ ራሱን ለውጦ ከእሱ ጋር ለመዋጋት ወጣ፤ በኒካዑ በኩል የተነገረውን የአምላክ ቃል አልሰማም። በመሆኑም ለመዋጋት ወደ መጊዶ ሜዳ መጣ። |
ቀስተኞችም ንጉሥ ኢዮስያስን ወጉት፤ ንጉሡም አገልጋዮቹን “ክፉኛ ስለቆሰልኩ ከዚህ አውጡኝ” አላቸው። |
በመሆኑም አገልጋዮቹ ከሠረገላው አውርደው በሁለተኛው የጦር ሠረገላው ላይ ካስቀመጡት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት። እሱም በዚህ ሁኔታ ሞተ፤ በአባቶቹም መቃብር ተቀበረ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሁሉ ለኢዮስያስ አለቀሱ። |
ኤርምያስም ለኢዮስያስ የሐዘን እንጉርጉሮ ተቀኘ፤ ወንዶችና ሴቶች ዘማሪዎችም ሁሉ እስከ ዛሬ ድረስ በሙሿቸው ላይ ስለ ኢዮስያስ ይዘምራሉ፤ ደግሞም በእስራኤል እንዲዘመርና ሌሎች ሙሾዎች በተጻፉበት መጽሐፍ ላይ እንዲሰፍር ተወሰነ። |
የቀረው የኢዮስያስ ታሪክና በይሖዋ ሕግ ላይ በተጻፈው መሠረት ያከናወናቸው ታማኝ ፍቅር የተንጸባረቀባቸው ተግባራት |
እንዲሁም ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያደረጋቸው ነገሮች በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል። |
ኢዮስያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ31 ዓመት ገዛ። |
ኢዮስያስም በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ፤ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሄደ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አላለም። |
በነገሠ በ8ኛው ዓመት፣ ገና ልጅ ሳለ የአባቱን የዳዊትን አምላክ መፈለግ ጀመረ፤ በ12ኛውም ዓመት ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ከፍ ካሉ የማምለኪያ ቦታዎች፣ ከማምለኪያ ግንዶች፣ ከተቀረጹ ምስሎችና ከብረት ከተሠሩ ሐውልቶች አነጻ። |
በተጨማሪም እሱ በተገኘበት የባአልን መሠዊያዎች አፈራረሱ፤ በላያቸው ላይ የነበሩትንም የዕጣን ማጨሻዎች ሰባበራቸው። ደግሞም የማምለኪያ ግንዶቹን፣ የተቀረጹትን ምስሎችና ከብረት የተሠሩትን ሐውልቶች ሰባብሮ አደቀቃቸው፤ ከዚያም ለእነሱ ይሠዉ በነበሩት ሰዎች መቃብር ላይ በተነው። |
የካህናቱንም አጥንቶች በመሠዊያዎቻቸው ላይ አቃጠለ። በዚህ መንገድ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አነጻ። |
በተጨማሪም ከምናሴ፣ ከኤፍሬምና ከስምዖን አንስቶ እስከ ንፍታሌም ባሉት ከተሞች እንዲሁም በዙሪያቸው ባሉ የወደሙ ስፍራዎች ሁሉ፣ |
መሠዊያዎችን አፈራረሰ፤ የማምለኪያ ግንዶችንና የተቀረጹትን ምስሎች ሰባብሮ አደቀቃቸው፤ በመላው የእስራኤል ምድር የሚገኙትንም የዕጣን ማጨሻዎች ሰባበረ፤ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። |
እሱም በነገሠ በ18ኛው ዓመት ምድሪቱንና ቤተ መቅደሱን ካነጻ በኋላ የአዜልያን ልጅ ሳፋንን፣ የከተማዋን አለቃ ማአሴያህንና ታሪክ ጸሐፊውን የዮአሃዝን ልጅ ዮአህን የአምላኩን የይሖዋን ቤት እንዲጠግኑ ላካቸው። |
እነሱም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ኬልቅያስ መጥተው ወደ አምላክ ቤት የመጣውን ገንዘብ አስረከቡት፤ ገንዘቡም በር ጠባቂዎች ሆነው የሚያገለግሉት ሌዋውያን ከምናሴ፣ ከኤፍሬም፣ ከቀረው የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እንዲሁም ከይሁዳ፣ ከቢንያምና ከኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የሰበሰቡት ነበር። |
ከዚያም በይሖዋ ቤት የሚከናወነውን ሥራ እንዲቆጣጠሩ ለተሾሙት ሠራተኞች ገንዘቡን ሰጧቸው። በይሖዋ ቤት የሚሠሩት ሠራተኞች ደግሞ ቤቱን ለመጠገንና ለማደስ አዋሉት። |
በመሆኑም ጥርብ ድንጋዮችንና ለማጠናከሪያ የሚያገለግሉ ሳንቃዎችን እንዲሁም የይሁዳ ነገሥታት ትተዋቸው የፈራረሱትን ቤቶች ለመጠገን የሚያስፈልጉ ወራጆችን እንዲገዙ ገንዘቡን ለእጅ ጥበብ ባለሙያዎቹና ለግንበኞቹ ሰጧቸው። |
ሰዎቹም ሥራውን በታማኝነት አከናወኑ። በእነሱም ላይ ከሜራራውያን ሌዋውያኑ ያሃት እና አብድዩ፣ ከቀአታውያን ደግሞ ዘካርያስ እና መሹላም የበላይ ተመልካቾች ሆነው እንዲያገለግሉ ተሹመው ነበር። የሙዚቃ መሣሪያዎችን በመጫወት የተካኑት ሌዋውያንም ሁሉ፣ |
በጉልበት ሠራተኞቹ ላይ ተሹመው ነበር፤ እንዲሁም በሁሉም ዓይነት አገልግሎት ላይ ተመድበው በሚሠሩት ሠራተኞች ላይ የበላይ ተመልካቾች ሆነው ያገለግሉ ነበር፤ ከሌዋውያኑም መካከል አንዳንዶቹ ጸሐፊዎች፣ አለቆችና በር ጠባቂዎች ነበሩ። |
ወደ ይሖዋ ቤት የመጣውን ገንዘብ በሚያወጡበት ጊዜ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ በኩል የተሰጠውን የይሖዋን ሕግ መጽሐፍ አገኘ። |
በመሆኑም ኬልቅያስ ጸሐፊውን ሳፋንን “የሕጉን መጽሐፍ በይሖዋ ቤት ውስጥ አገኘሁት” አለው። ከዚያም ኬልቅያስ መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው። |
ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ ወስዶ እንዲህ አለው፦ “አገልጋዮችህ የተመደበላቸውን ሥራ ሁሉ እያከናወኑ ነው። |
በይሖዋ ቤት የተገኘውን ገንዘብ አውጥተው ለተሾሙት ሰዎችና ለሠራተኞቹ አስረክበዋል።” |
በተጨማሪም ጸሐፊው ሳፋን ንጉሡን “ካህኑ ኬልቅያስ የሰጠኝ አንድ መጽሐፍ አለ” አለው። ከዚያም ሳፋን መጽሐፉን በንጉሡ ፊት ማንበብ ጀመረ። |
ንጉሡ የሕጉን ቃል ሲሰማ ልብሱን ቀደደ። |
ከዚያም ንጉሡ ኬልቅያስን፣ የሳፋንን ልጅ አኪቃምን፣ የሚክያስን ልጅ አብዶንን፣ ጸሐፊውን ሳፋንን እና የንጉሡን አገልጋይ አሳያህን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ |
“ሄዳችሁ በተገኘው መጽሐፍ ላይ የሰፈረውን ቃል በተመለከተ እኔን እንዲሁም በእስራኤልና በይሁዳ የቀረውን ሕዝብ ወክላችሁ ይሖዋን ጠይቁ፤ አባቶቻችን በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን ነገሮች ሁሉ ስላልፈጸሙና የይሖዋን ቃል ስላልጠበቁ በእኛ ላይ የሚወርደው የይሖዋ ቁጣ ታላቅ ነው።” |
በመሆኑም ኬልቅያስና ንጉሡ የላካቸው ሰዎች ወደ ነቢዪቱ ሕልዳና ሄዱ። ሕልዳና የሃርሐስ ልጅ፣ የቲቅዋ ልጅ፣ የአልባሳት ጠባቂው የሻሉም ሚስት ስትሆን ኢየሩሳሌም ውስጥ በሁለተኛው ክፍል ትኖር ነበር፤ እነሱም በዚያ አነጋገሯት። |
እሷም እንዲህ አለቻቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ወደ እኔ የላካችሁን ሰው እንዲህ በሉት፦ |
“ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በዚህ ቦታና በነዋሪዎቹ ላይ መከራ አመጣለሁ፤ በይሁዳ ንጉሥ ፊት ባነበቡት መጽሐፍ ላይ የሰፈረውን እርግማን ሁሉ አመጣለሁ። |
እኔን በመተው በእጆቻቸው ሥራ ሁሉ ያስቆጡኝ ዘንድ ለሌሎች አማልክት የሚጨስ መሥዋዕት ስለሚያቀርቡ በዚህ ቦታ ላይ ቁጣዬ ይፈስሳል፤ ደግሞም አይጠፋም።’” |
Subsets and Splits
No community queries yet
The top public SQL queries from the community will appear here once available.