text stringlengths 4 267 |
|---|
ከአባቶች ቤት መሪዎች መካከል ለሥራው መዋጮ ያደረጉ ነበሩ። ገዢው 1,000 የወርቅ ድራክማ፣ 50 ጎድጓዳ ሳህኖችና 530 የካህናት ቀሚሶች ለግምጃ ቤቱ ሰጠ። |
ከአባቶች ቤት መሪዎች መካከል አንዳንዶቹ ለሥራው ማስኬጃ የሚሆን 20,000 የወርቅ ድራክማና 2,200 የብር ምናን ለግምጃ ቤቱ ሰጡ። |
የቀረው ሕዝብ ደግሞ 20,000 የወርቅ ድራክማ፣ 2,000 የብር ምናን እና 67 የካህናት ቀሚሶች ሰጠ። |
ካህናቱ፣ ሌዋውያኑ፣ በር ጠባቂዎቹ፣ ዘማሪዎቹ፣ ከሕዝቡ መካከል አንዳንዶቹ፣ የቤተ መቅደስ አገልጋዮቹና የቀሩት እስራኤላውያን በሙሉ በየከተሞቻቸው ሰፈሩ። በሰባተኛውም ወር እስራኤላውያን በየከተሞቻቸው ይኖሩ ነበር። |
በዚያን ቀን ሕዝቡ እየሰማ የሙሴ መጽሐፍ ይነበብ ነበር፤ በዚህ ጊዜ አሞናዊ ወይም ሞዓባዊ የሆነ ማንኛውም ሰው ወደ እውነተኛው አምላክ ጉባኤ ፈጽሞ መግባት እንደሌለበት የሚገልጽ ሐሳብ ተጽፎ ተገኘ፤ |
ይህም የሆነው ለእስራኤላውያን ምግብና ውኃ በመስጠት ፋንታ እነሱን እንዲረግምላቸው በለዓምን ቀጥረው ስለነበር ነው። ይሁንና አምላካችን እርግማኑን ወደ በረከት ለወጠው። |
እነሱም ይህን ሕግ እንደሰሙ የባዕድ አገር ሰዎችን ሁሉ ከእስራኤላውያን መለየት ጀመሩ። |
ይህ ከመሆኑ ቀደም ብሎ የአምላካችን ቤት ግምጃ ቤቶች ኃላፊ፣ የጦብያ ዘመድ የሆነው ካህኑ ኤልያሺብ ነበር። |
እሱም ቀደም ሲል የእህል መባውን፣ ነጩን ዕጣን፣ ዕቃዎቹን እንዲሁም ለሌዋውያኑ፣ ለዘማሪዎቹና ለበር ጠባቂዎቹ እንዲሰጥ የታዘዘውን የእህሉን፣ የአዲሱን የወይን ጠጅና የዘይቱን አንድ አሥረኛ እንዲሁም ለካህናቱ የሚዋጣውን መዋጮ ያስቀምጡበት የነበረውን ቦታ ትልቅ ግምጃ ቤት አድርጎ አዘጋጀለት። |
ይህ ሁሉ ሲሆን እኔ በኢየሩሳሌም አልነበርኩም፤ ምክንያቱም የባቢሎን ንጉሥ አርጤክስስ በነገሠ በ32ኛው ዓመት ወደ ንጉሡ ሄጄ ነበር፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ንጉሡን ፈቃድ እንዲሰጠኝ ጠየቅኩ። |
ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ስመጣ ኤልያሺብ በእውነተኛው አምላክ ቤት ግቢ ውስጥ ለጦብያ ግምጃ ቤት በማዘጋጀት የፈጸመውን መጥፎ ድርጊት አስተዋልኩ። |
እኔም በዚህ በጣም አዘንኩ፤ በመሆኑም የጦብያን የቤት ዕቃዎች በሙሉ ከግምጃ ቤቱ አውጥቼ ወረወርኳቸው። |
ከዚያም ትእዛዝ ሰጠሁ፤ እነሱም ግምጃ ቤቶቹን አጸዱ፤ እኔም የእውነተኛውን አምላክ ቤት ዕቃዎች ከእህሉ መባና ከነጩ ዕጣን ጋር እዚያው መልሼ አስቀመጥኩ። |
በተጨማሪም ሌዋውያኑ የሚገባቸው ድርሻ ስለማይሰጣቸው ሥራውን ያከናውኑ የነበሩት ሌዋውያንም ሆኑ ዘማሪዎች እያንዳንዳቸው ወደየእርሻቸው መሄዳቸውን ተረዳሁ። |
እኔም የበታች ገዢዎቹን “ለመሆኑ የእውነተኛው አምላክ ቤት እንዲህ ቸል የተባለው ለምንድን ነው?” በማለት ገሠጽኳቸው። ከዚያም ሁሉንም አንድ ላይ ከሰበሰብኳቸው በኋላ ወደየሥራ ምድባቸው እንዲመለሱ አደረግኩ። |
የይሁዳ ሰዎችም ሁሉ የእህሉን፣ የአዲሱን የወይን ጠጅና የዘይቱን አንድ አሥረኛ ወደ ግምጃ ቤቶቹ አስገቡ። |
ከዚያም ካህኑን ሸሌምያህን፣ የቅዱሳን መጻሕፍት ገልባጭ የሆነውን ሳዶቅን እንዲሁም ከሌዋውያን መካከል ፐዳያህን በግምጃ ቤቶቹ ላይ ኃላፊዎች አደረግኳቸው፤ የማታንያህ ልጅ፣ የዛኩር ልጅ ሃናን ደግሞ የእነሱ ረዳት ነበር፤ እነዚህ ሰዎች እምነት የሚጣልባቸው ነበሩ። ለወንድሞቻቸው የማከፋፈሉ ኃላፊነት የእነሱ ነበር። |
አምላኬ ሆይ፣ ስለዚህ ነገር አስበኝ፤ ለአምላኬ ቤትና በዚያ ለሚከናወነው አገልግሎት ስል የፈጸምኩትን ታማኝ ፍቅር የተንጸባረቀበት ተግባር አትርሳ። |
በእነዚያ ቀናት በይሁዳ በሰንበት ቀን በመጭመቂያ ውስጥ ወይን የሚረግጡና እህል አምጥተው በአህያ ላይ የሚጭኑ እንዲሁም የወይን ጠጅ፣ የወይን ዘለላ፣ በለስና የተለያዩ ነገሮችን ጭነው በሰንበት ቀን ወደ ኢየሩሳሌም የሚያመጡ ሰዎችን አየሁ። በመሆኑም በዚያን ቀን ሸቀጣ ሸቀጦችን እንዳይሸጡ አስጠነቀቅኳቸው። |
በከተማዋ የሚኖሩ የጢሮስ ሰዎችም ዓሣና የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን እያመጡ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ የይሁዳ ሰዎች በሰንበት ቀን ይሸጡ ነበር። |
ስለሆነም በይሁዳ ያሉትን የተከበሩ ሰዎች እንዲህ በማለት ገሠጽኳቸው፦ “ሰንበትን በማርከስ የምትፈጽሙት ይህ መጥፎ ድርጊት ምንድን ነው? |
አምላካችን በእኛም ሆነ በዚህች ከተማ ላይ ይህን ሁሉ መከራ ያመጣው አባቶቻችሁ እንዲህ ዓይነት ድርጊት በመፈጸማቸው አይደለም? አሁንም እናንተ ሰንበትን በማርከስ በእስራኤል ላይ የሚነደውን ቁጣ እያባባሳችሁ ነው።” |
በመሆኑም በሰንበት ዋዜማ የምሽቱ ጥላ በኢየሩሳሌም በሮች ላይ ማረፍ ሲጀምር በሮቹ እንዲዘጉ ትእዛዝ ሰጠሁ። ሰንበት እስኪያልፍም ድረስ እንዳይከፍቷቸው ነገርኳቸው፤ በሰንበት ቀን ምንም ዓይነት ጭነት እንዳይገባም ከአገልጋዮቼ የተወሰኑትን በበሮቹ ላይ አቆምኩ። |
ስለዚህ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን የሚነግዱትና የሚሸጡት ሰዎች ከአንዴም ሁለቴ ከኢየሩሳሌም ውጭ አደሩ። |
ከዚያም እኔ “ቅጥሩ አጠገብ የምታድሩት ለምንድን ነው? ዳግመኛ እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ የኃይል እርምጃ እወስድባችኋለሁ” በማለት አስጠነቀቅኳቸው። ከዚያን ጊዜ ወዲህ በሰንበት መጥተው አያውቁም። |
ለሌዋውያኑም የሰንበት ቀን ምንጊዜም የተቀደሰ እንዲሆን ዘወትር ራሳቸውን እንዲያነጹና መጥተው በሮቹን እንዲጠብቁ ነገርኳቸው። አምላኬ ሆይ፣ ይህንም አስብልኝ፤ ማለቂያ ከሌለው ታማኝ ፍቅርህም የተነሳ እዘንልኝ። |
በተጨማሪም በእነዚያ ቀናት አሽዶዳውያን፣ አሞናውያንና ሞዓባውያን ሴቶችን ያገቡ አይሁዳውያን መኖራቸውን አወቅኩ። |
ከልጆቻቸውም መካከል ግማሾቹ የአሽዶድን ቋንቋና ከተለያየ አገር የመጡትን ሰዎች ቋንቋ ይናገሩ የነበረ ቢሆንም ማንኛቸውም የአይሁዳውያንን ቋንቋ መናገር አይችሉም ነበር። |
ስለሆነም ገሠጽኳቸው፤ እርግማንም አወረድኩባቸው፤ አንዳንዶቹንም መታኋቸው፤ ፀጉራቸውንም ነጨሁ፤ እንዲሁም እንደሚከተለው በማለት በአምላክ አስማልኳቸው፦ “ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው መስጠት የለባችሁም፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁም ሆነ ለራሳችሁ መውሰድ የለባችሁም። |
የእስራኤል ንጉሥ ሰለሞን ኃጢአት የሠራው በእነሱ ምክንያት አይደለም? በብዙ ብሔራት መካከል እንደ እሱ ያለ ንጉሥ አልነበረም፤ ደግሞም በአምላኩ ዘንድ የተወደደ ስለነበር አምላክ በመላው እስራኤል ላይ ንጉሥ አደረገው። ይሁንና ባዕዳን ሚስቶች እሱን እንኳ ኃጢአት እንዲሠራ አደረጉት። |
እናንተም ባዕዳን ሴቶችን በማግባት በአምላካችን ላይ ታማኝነት የጎደለው ተግባር ፈጸማችሁ፤ ታዲያ እንዲህ ያለውን ተሰምቶ የማያውቅ እጅግ መጥፎ ድርጊት እንዴት ትፈጽማላችሁ?” |
ከሊቀ ካህናቱ ከኤልያሺብ ልጅ ከዮያዳ ወንዶች ልጆች መካከል አንዱ የሆሮናዊው የሳንባላጥ አማች ሆኖ ነበር። በመሆኑም ከአጠገቤ አባረርኩት። |
አምላኬ ሆይ፣ ክህነቱን እንዲሁም ከካህናቱና ከሌዋውያኑ ጋር የተገባውን ቃል ኪዳን ስላረከሱ አትርሳቸው። |
እኔም ርኩስ ከሆነ ከማንኛውም ባዕድ ነገር አነጻኋቸው፤ ለካህናቱና ለሌዋውያኑም ለእያንዳንዳቸው በየምድባቸው መሠረት ሥራ ሰጠኋቸው፤ |
እንዲሁም በተወሰነው ጊዜ መቅረብ ያለበትን እንጨትና መጀመሪያ የሚደርሰውን ፍሬ በተመለከተ ዝግጅት አደረግኩ። አምላኬ ሆይ፣ በመልካም አስበኝ። |
ሊቀ ካህናቱ ኤልያሺብና ካህናት የሆኑት ወንድሞቹ የበግ በርን ለመገንባት ተነሱ። እነሱም ቀደሱት፤ መዝጊያዎቹንም ገጠሙለት፤ እስከ መአህ ማማና እስከ ሃናንኤል ማማ ድረስ ቀደሱት። |
ከእነሱ ቀጥሎ ያለውን ደግሞ የኢያሪኮ ሰዎች እየገነቡ ነበር፤ ከእነሱ ቀጥሎ ያለውን የኢምሪ ልጅ ዛኩር እየገነባ ነበር። |
የሃስናአ ልጆች የዓሣ በርን ገነቡ፤ የጣውላ መቃኑንም ሠሩ፤ ከዚያም መዝጊያዎቹን፣ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹን ገጠሙለት። |
ከእነሱ ቀጥሎ ያለውን ደግሞ የሃቆጽ ልጅ የሆነው የዑሪያህ ልጅ መሬሞት ጠገነ፤ ቀጥሎ ያለውን የመሺዛቤል ልጅ የሆነው የቤራክያህ ልጅ መሹላም ጠገነ፤ ከዚያ ቀጥሎ ያለውን የባአና ልጅ ሳዶቅ ጠገነ። |
ከእነሱ ቀጥሎ ያለውን ደግሞ የተቆአ ሰዎች ጠገኑ፤ ሆኖም ከእነሱ መካከል ታዋቂ የሆኑት ሰዎች ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ አለቆቻቸው በሚያሠሩት ሥራ መካፈል አልፈለጉም። |
የፓሰአህ ልጅ ዮያዳ እና የቤሶድያህ ልጅ መሹላም የአሮጌ ከተማ በርን ጠገኑ፤ የጣውላ መቃኑንም ሠሩ፤ ከዚያም መዝጊያዎቹን፣ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹን ገጠሙለት። |
ከእነሱ ቀጥሎ ያለውን ደግሞ ከወንዙ ባሻገር ባለው ክልል ገዢ ሥልጣን ሥር የሚገኙት የገባኦንና የምጽጳ ሰዎች የሆኑት ገባኦናዊው መላጥያህና መሮኖታዊው ያዶን ጠገኑ። |
ከእነሱ ቀጥሎ ያለውን ከወርቅ አንጥረኞቹ አንዱ የሆነው የሃርሐያህ ልጅ ዑዚኤል ጠገነ፤ ከእሱ ቀጥሎ ያለውን ከቅባት ቀማሚዎች አንዱ የሆነው ሃናንያህ ጠገነ፤ ኢየሩሳሌምንም እስከ ሰፊ ቅጥር ድረስ ድንጋይ አነጠፉባት። |
ከእነሱ ቀጥሎ ያለውን ደግሞ የኢየሩሳሌም አውራጃ እኩሌታ ገዢ የሆነው የሁር ልጅ ረፋያህ ጠገነ። |
የሃሩማፍ ልጅ የዳያህ ከእነሱ ቀጥሎ የሚገኘውን ከራሱ ቤት ፊት ለፊት ያለውን ጠገነ፤ ከእሱ ቀጥሎ ያለውን ደግሞ የሃሻበንያህ ልጅ ሃጡሽ ጠገነ። |
የሃሪም ልጅ ማልኪያህና የፓሃትሞአብ ልጅ ሃሹብ ሌላኛውን ክፍል ጠገኑ፤ እንዲሁም የምድጃዎች ማማን ጠገኑ። |
ከእነሱ ቀጥሎ ያለውን ደግሞ የኢየሩሳሌም አውራጃ እኩሌታ ገዢ የሆነው የሃሎሔሽ ልጅ ሻሉም እና ሴቶች ልጆቹ ጠገኑ። |
ሃኑን እና የዛኖሃ ነዋሪዎች የሸለቆ በርን ጠገኑ፤ እነሱም ከሠሩት በኋላ መዝጊያዎቹን፣ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹን ገጠሙለት፤ በተጨማሪም እስከ አመድ ቁልል በር ድረስ ያለውን 1,000 ክንድ ቅጥር ጠገኑ። |
የቤትሃኬሬም አውራጃ ገዢ የሆነው የሬካብ ልጅ ማልኪያህ የአመድ ቁልል በርን ጠገነ፤ እሱም ከሠራው በኋላ መዝጊያዎቹን፣ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹን ገጠመለት። |
የምጽጳ አውራጃ ገዢ የሆነው የኮልሆዜ ልጅ ሻሉን የምንጭ በርን ጠገነ፤ እሱም ከሠራው በኋላ ጣሪያ አበጀለት፤ ከዚያም መዝጊያዎቹን፣ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹን ገጠመ፤ በተጨማሪም በንጉሡ የአትክልት ስፍራ ያለውን የሼላ የውኃ ገንዳ ግንብ ከዳዊት ከተማ ተነስቶ ቁልቁል እስከሚወርደው ደረጃ ድረስ ጠገነ። |
ከእሱ ቀጥሎ ደግሞ የቤትጹር አውራጃ እኩሌታ ገዢ የሆነው የአዝቡቅ ልጅ ነህምያ ከዳዊት የመቃብር ስፍራ ፊት ለፊት አንስቶ እስከ ሰው ሠራሹ ኩሬና እስከ ኃያላኑ ቤት ድረስ ገነባ። |
ከእሱ ቀጥሎ ያለውን በባኒ ልጅ በረሁም ሥር ያሉት ሌዋውያን ጠገኑት፤ ከእሱ ቀጥሎ ደግሞ የቀኢላ አውራጃ እኩሌታ ገዢ የሆነው ሃሻብያህ የራሱን አውራጃ ጠገነ። |
ከእሱ ቀጥሎ ያለውን የቀኢላ አውራጃ እኩሌታ ገዢ በሆነው በሄናዳድ ልጅ በባዋይ ሥር ያሉት ወንድሞቻቸው ጠገኑ። |
ከእሱ ቀጥሎ ደግሞ የምጽጳ ገዢ የሆነው የኤጼር ልጅ የሹዋ በቅጥሩ ቅስት አጠገብ ወደሚገኘው የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት ከሚያስወጣው አቀበት ፊት ለፊት ያለውን ሌላኛውን ክፍል ጠገነ። |
ከእሱ ቀጥሎ ደግሞ የዛባይ ልጅ ባሮክ የቅጥሩ ቅስት ከሚገኝበት አንስቶ እስከ ሊቀ ካህናቱ ኤልያሺብ ቤት መግቢያ ድረስ ያለውን ሌላኛውን ክፍል በቅንዓት ጠገነ። |
ከእሱ ቀጥሎ የሃቆጽ ልጅ የሆነው የዑሪያህ ልጅ መሬሞት ከኤልያሺብ ቤት መግቢያ አንስቶ እስከ ኤልያሺብ ቤት መጨረሻ ድረስ ያለውን ሌላኛውን ክፍል ጠገነ። |
ከእሱ ቀጥሎ ያለውን ደግሞ ካህናቱ ይኸውም የዮርዳኖስ አውራጃ ሰዎች ጠገኑት። |
ከእነሱ ቀጥሎ ቢንያምና ሃሹብ ከቤታቸው ፊት ለፊት ያለውን ጠገኑ። ከእነሱ ቀጥሎ ደግሞ የአናንያ ልጅ የሆነው የማአሴያህ ልጅ አዛርያስ ከራሱ ቤት አጠገብ ያለውን ጠገነ። |
ከእሱ ቀጥሎ የሄናዳድ ልጅ ቢኑይ ከአዛርያስ ቤት አንስቶ እስከ ቅጥሩ ቅስትና እስከ ማዕዘኑ ድረስ ያለውን ሌላኛውን ክፍል ጠገነ። |
ከእሱ ቀጥሎ የዑዛይ ልጅ ፓላል ከቅስቱ ፊት ለፊት ያለውን ቅጥርና በንጉሡ ቤት አጠገብ በክብር ዘቦቹ ግቢ ውስጥ የሚገኘውን የላይኛውን ማማ ጠገነ። ከእሱ ቀጥሎ የፓሮሽ ልጅ ፐዳያህ ነበር። |
እንዲሁም በኦፌል የሚኖሩት የቤተ መቅደስ አገልጋዮች በስተ ምሥራቅ እስከ ውኃ በር ፊት ለፊት ድረስ ያለውን ቅጥርና ወጣ ያለውን ማማ ጠገኑ። |
ከእነሱ ቀጥሎ የተቆአ ሰዎች ወጣ ካለው ትልቅ ማማ ፊት ለፊት አንስቶ እስከ ኦፌል ቅጥር ድረስ ያለውን ሌላኛውን ክፍል ጠገኑ። |
ካህናቱ ከፈረስ በር በላይ ያለውን ጠገኑ፤ እያንዳንዳቸውም ከቤታቸው ፊት ለፊት ያለውን ጠገኑ። |
ከእነሱ ቀጥሎ የኢሜር ልጅ ሳዶቅ ከራሱ ቤት ፊት ለፊት ያለውን ጠገነ። ከእሱ ቀጥሎ ደግሞ የምሥራቅ በር ጠባቂ የሆነው የሸካንያህ ልጅ ሸማያህ ጠገነ። |
ከእሱ ቀጥሎ የሸሌምያህ ልጅ ሃናንያህና የጻላፍ ስድስተኛ ልጅ ሃኑን ሌላኛውን ክፍል ጠገኑ። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የቤራክያህ ልጅ መሹላም ከራሱ አዳራሽ ፊት ለፊት ያለውን ጠገነ። |
ከእሱ ቀጥሎ ደግሞ የወርቅ አንጥረኞች ማኅበር አባል የሆነው ማልኪያህ በመቆጣጠሪያ በር አጠገብ እስከሚገኘው እስከ ቤተ መቅደስ አገልጋዮቹና እስከ ነጋዴዎቹ ቤት እንዲሁም በማዕዘኑ ላይ እስካለው ሰገነት ድረስ ያለውን ጠገነ። |
የወርቅ አንጥረኞቹና ነጋዴዎቹም በሰገነቱ ማዕዘን ላይ በሚገኘው ክፍልና በበግ በር መካከል ያለውን ጠገኑ። |
በዚህ ወር በ24ኛው ቀን እስራኤላውያን ተሰበሰቡ፤ ማቅ ለብሰውና በላያቸው ላይ አቧራ ነስንሰው ጾሙ። |
ከዚያም የእስራኤል ዘሮች ከባዕዳን ሁሉ ራሳቸውን ለዩ፤ ቆመውም ኃጢአታቸውንና አባቶቻቸው የፈጸሙትን ስህተት ሁሉ ተናዘዙ። |
ከዚያም ባሉበት ስፍራ ቆሙ፤ በቀኑ አንድ አራተኛም ከአምላካቸው ከይሖዋ የሕግ መጽሐፍ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያነብቡ፣ በቀኑ አንድ አራተኛ ደግሞ ለአምላካቸው ለይሖዋ ይናዘዙና ይሰግዱ ነበር። |
የሹዋ፣ ባኒ፣ ቃድሚኤል፣ ሸባንያህ፣ ቡኒ፣ ሸረበያህ፣ ባኒ እና ኬናኒ ለሌዋውያኑ በተሠራው ከፍ ያለ መድረክ ላይ ቆመው ወደ አምላካቸው ወደ ይሖዋ ጮኹ። |
እንዲሁም ሌዋውያኑ የሹዋ፣ ቃድሚኤል፣ ባኒ፣ ሃሻበንያህ፣ ሸረበያህ፣ ሆዲያህ፣ ሸባንያህ እና ፐታያህ እንዲህ አሉ፦ “ተነሱ፤ አምላካችሁን ይሖዋን ከዘላለም እስከ ዘላለም አመስግኑ። ከምስጋናና ከውዳሴ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያለውን ክብራማ ስምህን ያመስግኑ። |
“አንተ ብቻ ይሖዋ ነህ፤ አንተ ሰማያትን፣ አዎ ሰማየ ሰማያትንና ሠራዊታቸውን ሁሉ፣ ምድርንና በላይዋ ያሉትን ሁሉ፣ ባሕርንና በውስጡ ያሉትን ሁሉ ሠርተሃል። ሁሉንም ሕያው አድርገህ ታኖራቸዋለህ፤ የሰማይ ሠራዊትም ለአንተ ይሰግዳል። |
አብራምን መርጠህ ከከለዳውያን ዑር ያወጣኸውና አብርሃም ብለህ የጠራኸው እውነተኛው አምላክ ይሖዋ አንተ ነህ። |
ልቡ በፊትህ ታማኝ ሆኖ ስላገኘኸው የከነአናውያንን፣ የሂታውያንን፣ የአሞራውያንን፣ የፈሪዛውያንን፣ የኢያቡሳውያንንና የገርጌሻውያንን ምድር ለእሱ ይኸውም ለዘሩ ለመስጠት ከእሱ ጋር ቃል ኪዳን ተጋባህ፤ ጻድቅ ስለሆንክም ቃልህን ጠበቅክ። |
“በመሆኑም አባቶቻችን በግብፅ ሳሉ የደረሰባቸውን ሥቃይ አየህ፤ በቀይ ባሕር ያሰሙትንም ጩኸት ሰማህ። |
ከዚያም በፈርዖን፣ በአገልጋዮቹ ሁሉና በምድሩ በሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ፊት ምልክቶችንና ተአምራትን አሳየህ፤ ይህን ያደረግከው በእነሱ ላይ የእብሪት ድርጊት እንደፈጸሙ ስላወቅክ ነው። ለራስህም እስከ ዛሬ ጸንቶ የኖረ ስም አተረፍክ። |
በባሕሩ መሃል በደረቅ ምድር እንዲሻገሩ ባሕሩን በፊታቸው ከፈልክ፤ አሳዳጆቻቸውንም የሚናወጥ ባሕር ውስጥ እንደተጣለ ድንጋይ ወደ ጥልቁ ወረወርካቸው። |
ቀን በደመና ዓምድ፣ ሌሊት ደግሞ የሚሄዱበት መንገድ ብርሃን እንዲሆንላቸው ለማድረግ ስትል በእሳት ዓምድ መራሃቸው። |
በሲና ተራራ ላይ ወርደህ ከሰማይ አነጋገርካቸው፤ እንዲሁም የጽድቅ ፍርዶችን፣ የእውነት ሕጎችን፣ መልካም ሥርዓቶችንና ትእዛዛትን ሰጠሃቸው። |
ቅዱስ ሰንበትህን አሳወቅካቸው፤ እንዲሁም በአገልጋይህ በሙሴ አማካኝነት ትእዛዛትህን፣ ሥርዓቶችህንና ሕግህን ሰጠሃቸው። |
በተራቡ ጊዜ ከሰማይ ምግብ ሰጠሃቸው፤ በተጠሙም ጊዜ ከዓለቱ ውኃ አፈለቅክላቸው፤ ልትሰጣቸው የማልክላቸውን ምድር ገብተው እንዲወርሱም ነገርካቸው። |
“ይሁንና እነሱ ማለትም አባቶቻችን የእብሪት ድርጊት ፈጸሙ፤ ግትሮችም ሆኑ፤ ትእዛዛትህንም አልሰሙም። |
ለመስማትም አሻፈረኝ አሉ፤ በመካከላቸው የፈጸምካቸውን እጅግ አስደናቂ የሆኑ ነገሮች ረሱ፤ ከዚህ ይልቅ ግትሮች ሆኑ፤ በግብፅ ወደነበሩበት የባርነት ሕይወት ለመመለስም መሪ ሾሙ። አንተ ግን ይቅር ለማለት ዝግጁ የሆንክ፣ ሩኅሩኅ፣ መሐሪ፣ ለቁጣ የዘገየህና ታማኝ ፍቅርህ የበዛ አምላክ ነህ፤ እነሱንም አልተውካቸውም። |
ሌላው ቀርቶ ለራሳቸው የብረት ጥጃ ሐውልት ሠርተው ‘ከግብፅ መርቶ ያወጣህ አምላክህ ይህ ነው’ በማለት ከፍተኛ የንቀት ተግባር በፈጸሙ ጊዜም |
አንተ ምሕረትህ ታላቅ ስለሆነ በምድረ በዳ አልተውካቸውም። ቀን ቀን በመንገዳቸው ይመራቸው የነበረው የደመና ዓምድም ሆነ የሚሄዱበትን መንገድ የሚያበራላቸው ሌሊት ሌሊት ይታይ የነበረው የእሳት ዓምድ ከላያቸው አልተነሳም ነበር። |
ጥልቅ ማስተዋል እንዲያገኙ መልካም መንፈስህን ሰጠሃቸው፤ መናህንም ከአፋቸው አልከለከልክም፤ በተጠሙም ጊዜ ውኃ ሰጠሃቸው። |
በምድረ በዳም ለ40 ዓመት መገብካቸው። ምንም ያጡት ነገር አልነበረም። ልብሶቻቸው አላለቁም፤ እግሮቻቸውም አላበጡም። |
“መንግሥታትንና ሕዝቦችን እየከፋፈልክ ሰጠሃቸው፤ በመሆኑም የሲሖንን ምድር ይኸውም የሃሽቦንን ንጉሥ ምድር እንዲሁም የባሳንን ንጉሥ የኦግን ምድር ወረሱ። |
ወንዶች ልጆቻቸውንም በሰማያት ላይ እንዳሉ ከዋክብት አበዛሃቸው። ከዚያም ገብተው እንዲወርሷት ለአባቶቻቸው ቃል ወደገባህላቸው ምድር አመጣሃቸው። |
በመሆኑም ወንዶች ልጆቻቸው ገብተው ምድሪቱን ወረሱ፤ አንተም የምድሪቱ ነዋሪዎች የሆኑትን ከነአናውያን በፊታቸው እንዲንበረከኩ አደረግክ፤ በነገሥታታቸውና በምድሪቱ ሕዝቦች ላይም ያሻቸውን እንዲያደርጉ በእጃቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። |
የተመሸጉ ከተሞችንና ለም የሆነውን መሬት ያዙ፤ መልካም ነገሮች ሁሉ የሞሉባቸውን ቤቶች፣ የተቆፈሩ የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶችን፣ የወይን እርሻዎችን፣ የወይራ ዛፎችንና ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የፍራፍሬ ዛፎች ወረሱ። በመሆኑም እስኪጠግቡ ድረስ በሉ፤ ሰቡም፤ ታላቅ በሆነው ጥሩነትህም ተንደላቀቁ። |
“ይሁንና ለመታዘዝ እንቢተኞች በመሆን በአንተ ላይ ዓመፁ፤ ለሕግህም ጀርባቸውን ሰጡ። ወደ አንተ እንዲመለሱ ሲያስጠነቅቋቸው የነበሩትን ነቢያትህን ገደሉ፤ ከፍተኛ ንቀት የሚንጸባረቅባቸውንም ተግባሮች ፈጸሙ። |
በዚህም የተነሳ መከራ ለሚያሳዩአቸው ጠላቶቻቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። በተጨነቁ ጊዜ ግን ወደ አንተ ጮኹ፤ አንተም ከሰማያት ሆነህ ሰማሃቸው፤ ከታላቅ ምሕረትህ የተነሳም ከጠላቶቻቸው እጅ የሚታደጓቸውን አዳኞች ሰጠሃቸው። |
“ሆኖም ፋታ ሲያገኙ እንደገና በፊትህ መጥፎ ነገር አደረጉ፤ አንተም በሚጨቁኗቸው ጠላቶቻቸው እጅ ጣልካቸው። ከዚያም ተመልሰው ለእርዳታ ወደ አንተ ጮኹ፤ አንተም በሰማያት ሆነህ ሰማሃቸው፤ ከታላቅ ምሕረትህም የተነሳ በተደጋጋሚ አዳንካቸው። |
ወደ ሕግህ እንዲመለሱ ለማድረግ ብታስጠነቅቃቸውም እነሱ ግን እብሪተኞች በመሆን ትእዛዛትህን ለመስማት አሻፈረኝ አሉ፤ ለሚጠብቃቸው ሰው ሁሉ ሕይወት በሚያስገኙት ድንጋጌዎችህ ላይ ኃጢአት ሠሩ። ደግሞም በግትርነት ጀርባቸውን ሰጡ፤ አንገታቸውን አደነደኑ፤ ለመስማትም አሻፈረኝ አሉ። |
አንተ ግን ለብዙ ዓመታት ታገሥካቸው፤ በነቢያትህም አማካኝነት በመንፈስህ አስጠነቀቅካቸው፤ እነሱ ግን ለመስማት አሻፈረኝ አሉ። በመጨረሻም በምድሪቱ ለሚኖሩት ሕዝቦች አሳልፈህ ሰጠሃቸው። |
ከታላቅ ምሕረትህ የተነሳ ፈጽመህ አላጠፋሃቸውም ወይም አልተውካቸውም፤ ምክንያቱም አንተ ሩኅሩኅና መሐሪ አምላክ ነህ። |
“አምላካችን ሆይ፣ አንተ ታላቅ፣ ኃያል፣ የተፈራህ፣ ቃል ኪዳንህን የምትጠብቅና ታማኝ ፍቅር የምታሳይ አምላክ ነህ፤ ከአሦር ነገሥታት ዘመን አንስቶ እስካሁን ድረስ በእኛ፣ በነገሥታታችን፣ በመኳንንታችን፣ በካህናታችን፣ በነቢያታችን፣ በአባቶቻችንና በመላው ሕዝብህ ላይ እየደረሰ ያለውን ይህን ሁሉ መከራ አቅልለህ አትመልከተው። |
በእኛ ላይ በደረሰው ነገር ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ምክንያቱም አንተ ማንኛውንም ነገር ያደረግከው በታማኝነት ነው፤ ክፉ ነገር የፈጸምነው እኛ ነን። |
Subsets and Splits
No community queries yet
The top public SQL queries from the community will appear here once available.