text
stringlengths
4
267
ንግሥት አስጢንን የንግሥትነት አክሊሏን እንዳደረገች ወደ ንጉሡ ፊት እንዲያመጧት ነገራቸው፤ ይህን ያደረገው በጣም ቆንጆ ስለነበረች ሕዝቡና መኳንንቱ ውበቷን እንዲያዩ ነበር።
ንግሥት አስጢን ግን ንጉሡ በቤተ መንግሥት ባለሥልጣናቱ በኩል ያስተላለፈውን ትእዛዝ ባለመቀበል ፈጽሞ ለመምጣት ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች። በዚህ ጊዜ ንጉሡ በኃይል ተቆጣ፤ በጣም ተናደደ።
ከዚያም ንጉሡ ስለ ቀድሞው ዘመን ጥልቅ ማስተዋል ያላቸውን ጥበበኛ ሰዎች አማከረ (ንጉሡ የሚያጋጥሙት ነገሮች ሕግንና የፍርድ ጉዳዮችን ጠንቅቀው በሚያውቁ ሰዎች ሁሉ ፊት የሚቀርቡት በዚህ መንገድ ነበርና፤
የቅርብ ሰዎቹም ካርሼና፣ ሼታር፣ አድማታ፣ ተርሴስ፣ ሜሬስ፣ ማርሴና እና ሜሙካን ነበሩ፤ እነዚህ ንጉሡ ፊት መቅረብ የሚችሉና በመንግሥቱ ውስጥ ከፍተኛውን ቦታ የያዙ ሰባቱ የፋርስና የሜዶን መኳንንት ናቸው)።
ንጉሡም እንዲህ ሲል ጠየቀ፦ “ንጉሥ አሐሽዌሮስ በቤተ መንግሥት ባለሥልጣናቱ በኩል ያስተላለፈውን ትእዛዝ ባለማክበሯ በሕጉ መሠረት በንግሥት አስጢን ላይ ምን ቢደረግ ይሻላል?”
በዚህ ጊዜ ሜሙካን በንጉሡና በመኳንንቱ ፊት እንዲህ አለ፦ “ንግሥት አስጢን የበደለችው ንጉሡን ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ መኳንንቱን ሁሉና በመላው የንጉሥ አሐሽዌሮስ አውራጃዎች የሚኖሩትን ሕዝቦች ሁሉ ነው።
ሌሎች ሚስቶች ሁሉ ንግሥቲቱ ያደረገችውን ነገር ማወቃቸው ስለማይቀር ባሎቻቸውን ይንቃሉ፤ ደግሞም ‘ንጉሥ አሐሽዌሮስ ንግሥት አስጢንን በፊቱ እንዲያቀርቧት አዝዞ ነበር፤ እሷ ግን አልቀረበችም’ ይላሉ።
በዚህ ቀን ንግሥቲቱ ያደረገችውን ነገር የሰሙ የፋርስና የሜዶን ልዕልቶች ለንጉሡ መኳንንት ሁሉ ተመሳሳይ መልስ ሊሰጡ ነው፤ ይህም ከፍተኛ ንቀትና ቁጣ ያስከትላል።
በመሆኑም ንጉሡ መልካም መስሎ ከታየው አስጢን፣ ንጉሥ አሐሽዌሮስ ፊት ዳግመኛ እንዳትቀርብ የሚያዝዝ ንጉሣዊ አዋጅ ያውጣ፤ ይህም የማይሻር ሆኖ በፋርስና በሜዶን ሕጎች ውስጥ ይካተት፤ ንጉሡም የእቴጌነት ክብሯን ከእሷ ለተሻለች ሴት ይስጥ።
ንጉሡም የሚያወጣው አዋጅ ሰፊ በሆነው ግዛቱ ሁሉ ሲነገር ትልቅ ትንሽ ሳይል ሁሉም ሚስቶች ባሎቻቸውን ያከብራሉ።”
ይህ ሐሳብ ንጉሡንና መኳንንቱን ደስ አሰኛቸው፤ ንጉሡም ሜሙካን እንዳለው አደረገ።
በመሆኑም እያንዳንዱ ባል በቤቱ ውስጥ ጌታ እንዲሆንና በራሱ ሕዝብ ቋንቋ እንዲናገር የሚያዝዝ ደብዳቤ ለመላው የንጉሡ አውራጃዎች ላከ፤ ደብዳቤውም ለእያንዳንዱ አውራጃ በየራሱ ጽሑፍ፣ ለእያንዳንዱም ሕዝብ በገዛ ቋንቋው የተዘጋጀ ነበር።
ንጉሡና ሃማም ንግሥት አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ መጡ።
በሁለተኛው ቀን በወይን ጠጅ ግብዣው ላይ ንጉሡ አስቴርን በድጋሚ እንዲህ አላት፦ “ንግሥት አስቴር ሆይ፣ የምትጠይቂው ምንድን ነው? የጠየቅሽው ይሰጥሻል። የምትፈልጊውስ ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ብትጠይቂ ይሰጥሻል!”
ንግሥት አስቴርም እንዲህ ስትል መለሰች፦ “ንጉሥ ሆይ፣ በፊትህ ሞገስ ካገኘሁና ንጉሡን የሚያስደስተው ከሆነ ሕይወቴን እንድትታደግልኝ እማጸንሃለሁ፤ ሕዝቤንም እንድታድንልኝ እጠይቅሃለሁ።
እኔና ሕዝቤ ለጥፋት፣ ለመገደልና ለመደምሰስ ተሸጠናልና። የተሸጥነው ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች እንድንሆን ብቻ ቢሆን ኖሮ ዝም ባልኩ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ጥፋት በንጉሡም ላይ ጉዳት ስለሚያስከትል በቸልታ መታለፍ የለበትም።”
ንጉሥ አሐሽዌሮስም ንግሥት አስቴርን “ለመሆኑ ይህ ሰው ማን ነው? እንዲህ ያለውን ነገር ለማድረግ የደፈረውስ ሰው የታለ?” አላት።
አስቴርም “ባላጋራና ጠላት የሆነው ሰው ይህ ክፉው ሃማ ነው” አለች። ሃማም በንጉሡና በንግሥቲቱ ፊት በፍርሃት ተንቀጠቀጠ።
ንጉሡም ከወይን ጠጅ ግብዣው ላይ ተቆጥቶ ተነሳ፤ ወደ ቤተ መንግሥቱም የአትክልት ስፍራ ሄደ፤ ይሁንና ሃማ ንጉሡ ሊቀጣው ቆርጦ እንደተነሳ ስለተገነዘበ ንግሥት አስቴር ሕይወቱን እንድታድንለት ለመማጸን ቆመ።
ንጉሡ ከቤተ መንግሥቱ የአትክልት ስፍራ ወደ ወይን ጠጅ ግብዣው ተመልሶ ሲመጣ ሃማ አስቴር ባለችበት ድንክ አልጋ ላይ ተደፍቶ ተመለከተ። ንጉሡም “ብሎ ብሎ በገዛ ቤቴ ንግሥቲቱን ሊደፍራት ያስባል?” ብሎ ጮኸ። ይህ ቃል ከንጉሡ አፍ እንደወጣ የሃማን ፊት ሸፈኑት።
ከንጉሡ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት አንዱ የሆነው ሃርቦና እንዲህ አለ፦ “ሃማ፣ የንጉሡ ሕይወት እንዲተርፍ ሴራውን ላጋለጠው ለመርዶክዮስ የመሰቀያ እንጨትም አዘጋጅቷል። እንጨቱ 50 ክንድ ቁመት ያለው ሲሆን በሃማ ቤት ቆሟል።” በዚህ ጊዜ ንጉሡ “በዚያው እንጨት ላይ ስቀሉት” አለ።
በመሆኑም ሃማን ለመርዶክዮስ ባዘጋጀው እንጨት ላይ ሰቀሉት፤ የንጉሡም ቁጣ በረደ።
ከዚህ በኋላ ንጉሥ አሐሽዌሮስ የአጋጋዊውን የሃመዳታን ልጅ የሃማን ዙፋን አብረውት ካሉት ከሌሎቹ መኳንንት ሁሉ በላይ በማድረግ ላቅ ያለ ሹመት ሰጠው፤ ደግሞም ከፍ ከፍ አደረገው።
በንጉሡ በር የነበሩት የንጉሡ አገልጋዮች በሙሉ ሃማን እጅ ይነሱትና ለእሱ ይሰግዱለት ነበር፤ ንጉሡ እንዲህ እንዲደረግለት አዝዞ ነበርና። መርዶክዮስ ግን እጅ ለመንሳትም ሆነ ለመስገድ ፈቃደኛ አልሆነም።
በመሆኑም በንጉሡ በር የነበሩት የንጉሡ አገልጋዮች መርዶክዮስን “የንጉሡን ትእዛዝ የማታከብረው ለምንድን ነው?” አሉት።
በየቀኑ ይህን ጉዳይ ቢያነሱበትም እሱ ግን ሊሰማቸው ፈቃደኛ አልሆነም። ከዚያም የመርዶክዮስ አድራጎት በቸልታ የሚታለፍ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማየት ጉዳዩን ለሃማ ነገሩት፤ መርዶክዮስ አይሁዳዊ መሆኑን ነግሯቸው ነበርና።
ሃማም መርዶክዮስ እሱን እጅ ለመንሳትና ለእሱ ለመስገድ ፈቃደኛ አለመሆኑን ባስተዋለ ጊዜ እጅግ ተቆጣ።
ሆኖም ስለ መርዶክዮስ ወገኖች ነግረውት ስለነበር መርዶክዮስን ብቻ ማስገደሉ ተራ ነገር እንደሆነ ተሰማው። ስለዚህ ሃማ በመላው የአሐሽዌሮስ ግዛት የሚገኙትን አይሁዳውያን በሙሉ ማለትም የመርዶክዮስን ወገኖች በአጠቃላይ ለማጥፋት ዘዴ ይፈልግ ጀመር።
ንጉሥ አሐሽዌሮስ በነገሠ በ12ኛው ዓመት ኒሳን በተባለው የመጀመሪያ ወር ላይ፣ ቀኑንና ወሩን ለመወሰን በሃማ ፊት ፑር (ዕጣ ማለት ነው) ጣሉ፤ ዕጣውም በ12ኛው ወር ማለትም በአዳር ወር ላይ ወደቀ።
ከዚያም ሃማ ንጉሥ አሐሽዌሮስን እንዲህ አለው፦ “በግዛትህ ውስጥ ባሉት አውራጃዎች ሁሉ ተበታትኖና ተሰራጭቶ የሚገኝ፣ የሚመራበትም ሕግ ከሌሎቹ ሕዝቦች ሁሉ የተለየ አንድ ሕዝብ አለ፤ የንጉሡንም ሕጎች አያከብርም፤ ንጉሡም ይህን ሕዝብ ዝም ብሎ መመልከቱ ይጎዳዋል።
ለንጉሡ መልካም መስሎ ከታየው እነዚህ ሰዎች እንዲጠፉ የሚያዝዝ ድንጋጌ በጽሑፍ ይውጣ። እኔም ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት እንዲያስገቡ ለባለሥልጣናቱ 10,000 የብር ታላንት እከፍላለሁ።”
በዚህ ጊዜ ንጉሡ የማኅተም ቀለበቱን ከእጁ አውልቆ የአይሁዳውያን ጠላት ለነበረው ለአጋጋዊው ለሃመዳታ ልጅ ለሃማ ሰጠው።
ንጉሡም ሃማን “ተገቢ መስሎ የታየህን እንድታደርግበት ብሩም ሆነ ሕዝቡ ለአንተ ተሰጥቷል” አለው።
ከዚያም በመጀመሪያው ወር 13ኛ ቀን የንጉሡ ጸሐፊዎች ተጠሩ። የሃማን ትእዛዝ ሁሉ በተለያዩ አውራጃዎች ላይ ለተሾሙት የንጉሡ አስተዳዳሪዎችና ገዢዎች እንዲሁም ለተለያዩ ሕዝቦች መኳንንት ጻፉ፤ ለእያንዳንዱ አውራጃ በራሱ ጽሑፍ፣ ለእያንዳንዱም ሕዝብ በራሱ ቋንቋ ተጻፈ። ደብዳቤው የተጻፈው በንጉሥ አሐሽዌሮስ ስም ሲሆን በንጉሡ የማኅተም ቀለበትም ታተመ።
ወጣት ሽማግሌ፣ ሕፃንም ሆነ ሴት ሳይባል አይሁዳውያን በጠቅላላ በአንድ ቀን ይኸውም አዳር በተባለው በ12ኛው ወር 13ኛ ቀን ላይ እንዲጠፉ፣ እንዲገደሉ፣ እንዲደመሰሱና ንብረታቸው እንዲወረስ የሚያዝዙ ደብዳቤዎች በመልእክተኞች አማካኝነት ወደ ንጉሡ አውራጃዎች ሁሉ ተላኩ።
ሕዝቡም ሁሉ ለዚያ ቀን ዝግጁ እንዲሆን ሲባል በደብዳቤዎቹ ላይ የሰፈረው ሐሳብ በሁሉም አውራጃዎች ውስጥ ሕግ ሆኖ እንዲደነገግና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲታወጅ መመሪያ ተላለፈ።
መልእክተኞቹም ከንጉሡ ትእዛዝ የተነሳ ተጣድፈው ወጡ፤ ሕጉም በሹሻን ግንብ ታወጀ። ከዚያም ንጉሡና ሃማ ሊጠጡ ተቀመጡ፤ የሹሻን ከተማ ግን ግራ ተጋባች።
አዳር በተባለው በ12ኛው ወር፣ 13ኛ ቀን፣ የንጉሡ ቃልና ሕግ በሚፈጸምበት እንዲሁም የአይሁዳውያን ጠላቶች በአይሁዳውያን ላይ ድል እንደሚቀዳጁ ተስፋ አድርገው በነበረበት ቀን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆነ፤ አይሁዳውያኑ የሚጠሏቸውን ሰዎች ድል አደረጉ።
አይሁዳውያኑ እነሱን ለመጉዳት በሚሹ ሰዎች ላይ እጃቸውን ለማንሳት በንጉሥ አሐሽዌሮስ አውራጃዎች በሙሉ በሚገኙ ከተሞቻቸው ውስጥ ተሰባሰቡ፤ ሕዝቡም ሁሉ ፈርቷቸው ስለነበር ሊቃወማቸው የቻለ አንድም ሰው አልነበረም።
የአውራጃዎቹ መኳንንት በሙሉ፣ አስተዳዳሪዎቹ፣ ገዢዎቹና የንጉሡን ጉዳይ የሚያስፈጽሙ ሰዎችም መርዶክዮስን ፈርተውት ስለነበር አይሁዳውያኑን ይረዷቸው ነበር።
መርዶክዮስ በንጉሡ ቤት ውስጥ ገናና ሆኖ ነበር፤ ገናናነቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለመጣ ዝናው በየአውራጃው ተዳረሰ።
አይሁዳውያኑ ጠላቶቻቸውን በሙሉ በሰይፍ ጨፈጨፏቸው፤ ገደሏቸው፤ እንዲሁም ደመሰሷቸው፤ በሚጠሏቸውም ሰዎች ላይ የፈለጉትን አደረጉባቸው።
አይሁዳውያኑ በሹሻን ግንብ 500 ሰዎችን ገደሉ፤ ደግሞም አጠፉ።
በተጨማሪም ፓርሻንዳታ፣ ዳልፎን፣ አስፋታ፣
ፖራታ፣ አዳሊያ፣ አሪዳታ፣
ፓርማሽታ፣ አሪሳይ፣ አሪዳይ እና ዋይዛታ የተባሉትን፣
የአይሁዳውያን ጠላት የነበረውን የሃመዳታን ልጅ የሃማን አሥር ወንዶች ልጆች ገደሉ። ከገደሏቸው በኋላ ግን አንድም ምርኮ አልወሰዱም።
በዚያ ቀን በሹሻን ግንብ የተገደሉት ሰዎች ብዛት ለንጉሡ ተነገረው።
ንጉሡ ንግሥት አስቴርን እንዲህ አላት፦ “አይሁዳውያኑ በሹሻን ግንብ 500 ሰዎችንና አሥሩን የሃማ ወንዶች ልጆች ገድለዋል፤ ደግሞም አጥፍተዋል። በቀሩት የንጉሡ አውራጃዎችስ ምን አድርገው ይሆን? አሁንስ የምትጠይቂው ምንድን ነው? የጠየቅሽው ይሰጥሻል። ሌላስ የምትፈልጊው ነገር አለ? ይደረግልሻል።”
አስቴርም እንዲህ ስትል መለሰች፦ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ በሹሻን የሚኖሩት አይሁዳውያን ዛሬ ተግባራዊ ያደረጉትን ሕግ ነገም እንዲደግሙት ይፈቀድላቸው፤ አሥሩ የሃማ ልጆችም በእንጨት ላይ ይሰቀሉ።”
ንጉሡም እንዲሁ እንዲደረግ አዘዘ። ከዚያም በሹሻን ሕግ ወጣ፤ አሥሩ የሃማ ልጆችም ተሰቀሉ።
በሹሻን የሚኖሩት አይሁዳውያን አዳር በተባለው ወር 14ኛ ቀን ላይ በድጋሚ ተሰበሰቡ፤ በሹሻንም 300 ሰዎችን ገደሉ፤ ይሁንና አንድም ምርኮ አልወሰዱም።
በንጉሡ አውራጃዎች የሚኖሩት የቀሩት አይሁዳውያንም ተሰብስበው ሕይወታቸውን ከጥቃት ተከላከሉ። እነሱን ይጠሏቸው ከነበሩት ሰዎች መካከል 75,000 ሰዎችን በመግደል ጠላቶቻቸውን አጠፉ፤ ይሁንና አንድም ምርኮ አልወሰዱም።
ይህ የሆነው አዳር በተባለው ወር 13ኛ ቀን ላይ ነበር፤ እነሱም በ14ኛው ቀን አረፉ፤ ዕለቱንም የግብዣና የሐሴት ቀን አደረጉት።
በሹሻን የነበሩት አይሁዳውያን በ13ኛው ቀንና በ14ኛው ቀን ላይ ተሰበሰቡ፤ በ15ኛው ቀን ደግሞ አረፉ፤ ቀኑንም የግብዣና የሐሴት ቀን አደረጉት።
ከዋና ከተማዋ ውጭ በሚገኙ የገጠር ከተሞች የሚኖሩት አይሁዳውያን አዳር የተባለውን ወር 14ኛ ቀን የሐሴትና የግብዣ ቀን፣ የፈንጠዝያ ቀንና አንዳቸው ለሌላው ምግብ የሚልኩበት ጊዜ እንዲሆን ያደረጉት በዚህ የተነሳ ነው።
መርዶክዮስ እነዚህን ክንውኖች ከመዘገበ በኋላ በቅርብም ይሁን በሩቅ ስፍራ ላሉ፣ በመላው የንጉሥ አሐሽዌሮስ አውራጃዎች ለሚኖሩ አይሁዳውያን በሙሉ ሕጋዊ እውቅና ያላቸው ደብዳቤዎች ላከ።
በየዓመቱ የአዳርን ወር 14ኛና 15ኛ ቀን እንዲያከብሩ አዘዛቸው፤
ምክንያቱም እነዚህ ቀናት አይሁዳውያኑ ከጠላቶቻቸው ያረፉባቸውና ሐዘናቸው ወደ ሐሴት፣ ለቅሷቸውም ወደ ፈንጠዝያ የተለወጠባቸው ቀናት ናቸው። እነዚህን ቀናት የግብዣና የደስታ እንዲሁም አንዳቸው ለሌላው ምግብ የሚልኩባቸውና ለድሆች ምጽዋት የሚሰጡባቸው ቀናት አድርገው እንዲያከብሩ ታዘው ነበር።
አይሁዳውያንም ማክበር የጀመሩትን ይህን በዓል ማክበራቸውን ለመቀጠልና መርዶክዮስ የጻፈላቸውን ነገር ለመፈጸም ተስማሙ።
የአይሁዳውያን ሁሉ ጠላት የነበረው የአጋጋዊው የሃመዳታ ልጅ ሃማ አይሁዳውያንን ለማጥፋት ሴራ ሸርቦ ነበርና፤ እንዲሁም እነሱን ለማሸበርና ለመደምሰስ ፑር ወይም ዕጣ ጥሎ ነበር።
ሆኖም አስቴር ወደ ንጉሡ በገባች ጊዜ ንጉሡ “በአይሁዳውያን ላይ የሸረበው መጥፎ ሴራ በራሱ ላይ ይድረስበት” የሚል የጽሑፍ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ እነሱም እሱንና ልጆቹን በእንጨት ላይ ሰቀሏቸው።
በዚህም የተነሳ እነዚህን ቀናት ፑሪም አሏቸው፤ ይህ ስም የተወሰደው ፑር ከተባለው ቃል ነው። በመሆኑም በዚህ ደብዳቤ ላይ ከሰፈረው ሐሳብ እንዲሁም ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ካዩአቸውና ካጋጠሟቸው ነገሮች የተነሳ
አይሁዳውያኑ ራሳቸውም ሆኑ ዘሮቻቸው እንዲሁም ከእነሱ ጋር የተባበሩ ሁሉ በየዓመቱ እነዚህን ሁለት ቀናት በተወሰነላቸው ጊዜ ላይ ለማክበርና እነዚህን ቀናት አስመልክቶ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ አደረጉ።
እያንዳንዱ ትውልድ፣ እያንዳንዱ ቤተሰብ፣ እያንዳንዱ አውራጃና እያንዳንዱ ከተማ እነዚህን ቀናት ማሰብና ማክበር ይጠበቅበት ነበር፤ እነዚህን የፑሪም ቀናት አይሁዳውያኑ ማክበራቸውን መተው የለባቸውም፤ መታሰቢያቸውም ከዘሮቻቸው መካከል መጥፋት የለበትም።
ከዚያም የአቢሃይል ልጅ ንግሥት አስቴርና አይሁዳዊው መርዶክዮስ ፑሪምን በተመለከተ የተጻፈውን ሁለተኛ ደብዳቤ በሙሉ ሥልጣናቸው አጸኑት።
እሱም የሰላምና የእውነት ቃል የያዙ ሕጋዊ እውቅና ያላቸው ደብዳቤዎችን በአሐሽዌሮስ ግዛት ውስጥ በሚገኙት 127 አውራጃዎች ለሚኖሩት አይሁዳውያን በሙሉ ላከ፤
ይህም አይሁዳዊው መርዶክዮስና ንግሥት አስቴር ባዘዟቸው መሠረት እንዲሁም እነሱ ራሳቸው መጾምንና ምልጃ ማቅረብን ጨምሮ የሚጠበቅባቸውን ነገር ለመፈጸም ራሳቸውንና ዘሮቻቸውን ግዴታ ውስጥ ባስገቡት መሠረት የፑሪምን ቀናት በተወሰነው ጊዜ እንዲያከብሩ ለማድረግ ነው።
አስቴር ያስተላለፈችውም ትእዛዝ ከፑሪም ጋር የተያያዙትን እነዚህን ነገሮች አጸና፤ ደግሞም መጽሐፍ ላይ ሰፈረ።
ከዚህ በኋላ ንጉሥ አሐሽዌሮስ ቁጣው ሲበርድለት አስጢን ያደረገችውን ነገርና በእሷ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ አስታወሰ።
ከዚያም የንጉሡ የቅርብ አገልጋዮች እንዲህ አሉ፦ “ለንጉሡ ቆንጆ የሆኑ ወጣት ደናግል ይፈለጉለት።
ንጉሡም ቆንጆ የሆኑትን ወጣት ደናግል ሁሉ ሰብስበው በሹሻን ግንብ ወደሚገኘው፣ ሴቶች ወደሚኖሩበት ቤት እንዲያመጧቸው በግዛቱ ውስጥ በሚገኙት አውራጃዎች ሁሉ ሰዎችን ይሹም። እነሱም የንጉሡ ጃንደረባና የሴቶቹ ጠባቂ በሆነው በሄጌ ኃላፊነት ሥር ይሁኑ፤ የውበት እንክብካቤም ይደረግላቸው።
ንጉሡ እጅግ ደስ የተሰኘባት ወጣትም በአስጢን ምትክ ንግሥት ትሆናለች።” ንጉሡም በሐሳቡ ደስ ተሰኘ፤ እንደተባለውም አደረገ።
በዚህ ጊዜ መርዶክዮስ የተባለ አንድ አይሁዳዊ በሹሻን ግንብ ይኖር ነበር፤ እሱም የቢንያማዊው የቂስ ልጅ፣ የሺምአይ ልጅ የሆነው የያኢር ልጅ ነው፤
ይህ ሰው የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር በግዞት ከወሰደው ከይሁዳ ንጉሥ ከኢኮንያን ጋር ከኢየሩሳሌም በግዞት ከተወሰዱት ሰዎች አንዱ ነበር።
እሱም የአባቱ ወንድም ልጅ የሆነችው የሃዳሳ ማለትም የአስቴር አሳዳጊ ነበር፤ አስቴር አባትም ሆነ እናት አልነበራትም። ወጣቷ ቁመናዋ ያማረ፣ መልኳም ቆንጆ ነበር፤ መርዶክዮስም አባትና እናቷ ሲሞቱ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ ወሰዳት።
የንጉሡ ቃልና ያወጣው ሕግ ታውጆ በርካታ ወጣት ሴቶች በሄጌ ኃላፊነት ሥር እንዲሆኑ በሹሻን ግንብ ሲሰበሰቡ አስቴርም ወደ ንጉሡ ቤት ተወስዳ የሴቶች ጠባቂ በሆነው በሄጌ ኃላፊነት ሥር እንድትሆን ተደረገ።
እሱም በወጣቷ ደስ ተሰኘባት፤ እንዲሁም በእሱ ዘንድ ሞገስ አገኘች፤ በመሆኑም የውበት እንክብካቤ እንዲደረግላትና የተለየ ምግብ እንዲሰጣት ወዲያውኑ ዝግጅት አደረገ፤ ከንጉሡም ቤት የተመረጡ ሰባት ወጣት ሴቶች መደበላት። በተጨማሪም እሷንና የተመደቡላትን ሴቶች በሴቶቹ ቤት ውስጥ ወደሚገኘው ምርጥ ወደሆነው ቦታ አዛወራቸው።
መርዶክዮስ ለማንም እንዳትናገር አዟት ስለነበር አስቴር ስለ ሕዝቦቿም ሆነ ስለ ዘመዶቿ ምንም አልተናገረችም።
መርዶክዮስ ስለ አስቴር ደህንነትና ስላለችበት ሁኔታ ለማወቅ በሴቶቹ ቤት ግቢ ፊት ለፊት በየዕለቱ ይመላለስ ነበር።
እያንዳንዷ ወጣት ለሴቶቹ በታዘዘው መሠረት 12 ወር የሚፈጅ እንክብካቤ ከተደረገላት በኋላ ተራዋ ደርሶ ወደ ንጉሥ አሐሽዌሮስ ትገባ ነበር፤ የውበት እንክብካቤው በተሟላ ሁኔታ የሚከናወንላቸው በዚህ መንገድ ነበርና፤ ስድስት ወር በከርቤ ዘይት፣ ስድስት ወር ደግሞ በበለሳን ዘይት እንዲሁም በተለያዩ ቅባቶች የውበት እንክብካቤ ይደረግላቸው ነበር።
ከዚያም ወጣቷ ወደ ንጉሡ ለመግባት ዝግጁ ትሆናለች፤ ከሴቶቹ ቤት ወደ ንጉሡ ቤት በምትሄድበት ጊዜም የምትጠይቀው ነገር ሁሉ ይሰጣት ነበር።
ምሽት ላይ ትገባለች፤ ጠዋት ላይ ደግሞ የቁባቶች ጠባቂ በሆነው በንጉሡ ጃንደረባ በሻአሽጋዝ ኃላፊነት ሥር ወዳለው ወደ ሁለተኛው የሴቶች ቤት ትመለሳለች። ንጉሡ በጣም ካልተደሰተባትና በስም ጠቅሶ ካላስጠራት በስተቀር ዳግመኛ ወደ ንጉሡ አትገባም።
መርዶክዮስ እንደ ልጁ አድርጎ የወሰዳት የአጎቱ የአቢሃይል ልጅ አስቴር ወደ ንጉሡ የምትገባበት ተራ ሲደርስ የሴቶች ጠባቂ የሆነው የንጉሡ ጃንደረባ ሄጌ እንድትጠይቅ ከነገራት ነገር በስተቀር ምንም አልጠየቀችም። (በዚህ ሁሉ ጊዜ አስቴር ባዩአት ሁሉ ዘንድ ሞገስ አግኝታ ነበር።)
አስቴር ንጉሥ አሐሽዌሮስ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ቴቤት ተብሎ በሚጠራው አሥረኛ ወር ወደ ንጉሡ ቤት ተወሰደች።
ንጉሡም ከሌሎቹ ሴቶች ሁሉ ይበልጥ አስቴርን ወደዳት፤ ከሌሎቹም ደናግል ሁሉ ይበልጥ በእሱ ዘንድ ሞገስና ተቀባይነት አገኘች። በመሆኑም በራሷ ላይ የንግሥትነት አክሊል አደረገላት፤ በአስጢንም ፋንታ ንግሥት አደረጋት።
ንጉሡም ለመኳንንቱ ሁሉና ለአገልጋዮቹ በሙሉ እጅግ ታላቅ ግብዣ አዘጋጀ፤ ይህን ታላቅ ግብዣ ያዘጋጀው ለአስቴር ክብር ሲል ነው። ከዚያም በአውራጃዎቹ ውስጥ ለሚኖሩ ምሕረት አደረገ፤ ንጉሡም ካለው ብልጽግና የተነሳ ስጦታዎችን ይሰጥ ነበር።
ደናግሉ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሰበሰቡ መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ነበር።
መርዶክዮስ ባዘዛት መሠረት አስቴር ስለ ዘመዶቿም ሆነ ስለ ሕዝቦቿ ምንም አልተናገረችም፤ አስቴር ከመርዶክዮስ ጋር በነበረችበት ጊዜ ታደርግ እንደነበረው ሁሉ አሁንም እሱ የሚለውን ትታዘዝ ነበር።
በዚያን ጊዜ መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ሳለ በር ጠባቂዎች የሆኑት ቢግታን እና ቴሬሽ የተባሉ የንጉሡ ሁለት የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት ተቆጡ፤ ንጉሥ አሐሽዌሮስንም ለመግደል አሴሩ።
ሆኖም መርዶክዮስ ይህን ጉዳይ አወቀ፤ ወዲያውኑም ለንግሥት አስቴር ነገራት። ከዚያም አስቴር ጉዳዩን በመርዶክዮስ ስም ለንጉሡ ነገረችው።
በመሆኑም ሁኔታው ሲጣራ እውነት ሆኖ ተገኘ፤ ከዚያም ሁለቱ ሰዎች እንጨት ላይ ተሰቀሉ፤ ይህ ሁኔታም በዘመኑ በነበረው የታሪክ መጽሐፍ ላይ በንጉሡ ፊት ተጻፈ።
ንጉሥ አሐሽዌሮስ በምድሪቱና በባሕር ደሴቶች ላይ የሚኖሩ ሰዎች የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ አደረገ።
ንጉሡ ያከናወናቸው ታላላቅና አስደናቂ ሥራዎች በሙሉ እንዲሁም መርዶክዮስን ከፍ ከፍ እንዲያደርገው ስላነሳሳው ስለ መርዶክዮስ ታላቅነት የሚገልጸው ዘገባ በሜዶንና በፋርስ ነገሥታት ዘመን ስለተከናወኑ ነገሮች በሚተርከው መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?
አይሁዳዊው መርዶክዮስ ከንጉሥ አሐሽዌሮስ ቀጥሎ ያለ ሁለተኛ ሰው ነበር። በአይሁዳውያን መካከል ትልቅ ቦታ የነበረው፣ በብዙ ወንድሞቹ ዘንድ የተከበረ፣ ለወገኖቹ ጥቅም የቆመ እንዲሁም ለዘሮቻቸው ሁሉ ደህንነት የሚቆረቆር ሰው ነበር።
በሦስተኛው ቀን አስቴር ልብሰ መንግሥቷን ለብሳ ከንጉሡ ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው በንጉሡ ቤት ውስጠኛ ግቢ ቆመች፤ ንጉሡም በመግቢያው ፊት ለፊት በሚገኘው በንጉሡ ቤት ውስጥ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ነበር።
ንጉሡ፣ ንግሥት አስቴርን ግቢ ውስጥ ቆማ ሲያያት በፊቱ ሞገስ አገኘች፤ ንጉሡም እጁ ላይ የነበረውን የወርቅ በትረ መንግሥት ለአስቴር ዘረጋላት። በዚህ ጊዜ አስቴር ቀርባ የበትሩን ጫፍ ነካች።
ንጉሡም “ንግሥት አስቴር ሆይ፣ ምን ችግር አጋጠመሽ? የምትፈልጊው ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ብትጠይቂ ይሰጥሻል!” አላት።
አስቴርም መልሳ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ ንጉሡ ለእሱ ባዘጋጀሁት ግብዣ ላይ ዛሬ ከሃማ ጋር ይገኝልኝ” አለች።
በመሆኑም ንጉሡ አገልጋዮቹን “አስቴር ባቀረበችው ጥያቄ መሠረት በአስቸኳይ እንዲመጣ ለሃማ ንገሩት” አለ። ስለዚህ ንጉሡና ሃማ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ መጡ።